የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w93 10/15 ገጽ 3-4
  • ስርቆት እየጨመረ ያለው ለምንድን ነው?

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ስርቆት እየጨመረ ያለው ለምንድን ነው?
  • መጠበቂያ ግንብ—1993
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • ሰዎች ለምን ይሰርቃሉ?
  • አትስረቅ
  • ስርቆት ተገቢ ያልሆነው ለምንድን ነው?
    ንቁ!—1996
  • ድህነት ለስርቆት ማሳበቢያ ሊሆን ይችላልን?
    ንቁ!—1998
  • ሌባ እንዳትሆን ተጠንቀቅ!
    ከታላቁ አስተማሪ ተማር
  • በእርግጥ ስርቆት ነውን?
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1994
ለተጨማሪ መረጃ
መጠበቂያ ግንብ—1993
w93 10/15 ገጽ 3-4

ስርቆት እየጨመረ ያለው ለምንድን ነው?

ጊዜው እሑድ ጥቅምት 18, 1992 ሲሆን ቦታ ው ሪዮ ዲ ጃኔሮ ነበር። የታወቁት የኮፓካባና እና የኦፓኔማ የባሕር ዳርቻዎች በሰው ተጨናንቀዋል። በድንገት የወጣቶች ጭፍራ የባሕሩን ዳርቻ ወረረው፤ እርስ በእርሳቸው እየተሻኮቱ በባሕሩ ዳርቻ ከነበሩት ሰዎች ውድ ዋጋ ያለውን ነገር ሁሉ ዘረፉ። ቁጥራቸው በዘራፊዎቹ ብዛት የተዋጠው ፖሊሶች ግን ቆመው ቀሩ። ይህ ድርጊት ለሪዮ ዲ ጃኔሮ ነዋሪዎችም ሆነ ለአገር ጎብኚዎቹ አስደንጋጭ የቀን ቅዠት ነበር።

ከንብረት ጋር በተያያዘ መንገድ የሚሠሩ ወንጀሎች የተለመዱ ሆነዋል። በትላልቅ ከተሞች ሌቦች ወጣቶችን እንደሚዘርፉና ለስኒከር ጫማዎቻቸው ሲሉ እንኳ እንደሚገድሏቸው የታወቀ ሆኖአል። በቤት ውስጥ ሰው ኖረም አልኖረ ሌቦች ወደ ሰዎች ቤት ዘው ብለው ይገባሉ። እምነት አጉዳይ የሆኑ የቤት ሠራተኞች የቤቱን ሁኔታ ካጠኑ በኋላ ጌጣጌጥና ገንዘብ ዘርፈው ይሰወራሉ። ብዙ ሰዎች ተሰብስበው መጋዘኖችን ይዘርፋሉ። በብራዚል ውስጥ ቁጥሩ እየጨመረ በመጣው አፈና እንደሚታየው ሰዎችን እንኳን ሳይቀር ይሰርቃሉ። አንተም ከራስህ ተሞክሮ ወይም በምትኖርበት አካባቢ ከተፈጸመው ነገር ሌሎች ምሳሌዎችን ልትሰጥ እንደምትችል ግልጽ ነው። ነገር ግን ስርቆት ይህን ያህል የተስፋፋው ለምንድን ነው?

ሰዎች ለምን ይሰርቃሉ?

ምንም እንኳን እየጨመረ የመጣው ድህነትና የዕፅ ሱሰኝነት ሁለት ትልልቅ ምክንያቶች ቢሆኑም የጥያቄው መልስ በዚህ ብቻ ግልጽ የሚሆን አይደለም። ዘ ኒው ኢንሳይክሎፔዲያ ብሪታኒካ በዚህ ላይ ያለውን አስተያየት ሲሰጥ “አንድ ወንጀል የተፈጸመበትን ምክንያት ለማግኘት የሚደረግ ምርምር ፍሬ አልባ ስለሚሆን ግብ ላይ ሳይደርስ ይቋረጣል” ብሏል። በተመሳሳይም ይኸው ኢንሳይክሎፔዲያ እንደ ሥርቆት ላሉ ችግሮች መንስዔ ከሆኑት ነገሮች መካከል “ወጣቶች ያደረባቸው የከንቱነት ስሜትና ሌላው ሰው ካገኛቸው ቁሳዊ ሀብቶች ተካፋይ አለመሆናቸው ይገኙበታል” ብሏል። አዎ ን፣ ከፍተኛ ከሆነው ንብረት የማካበት ግፊት የተነሳ ብዙዎች የተመኙትን ነገር ለማግኘት ከስርቆት በስተቀር ሌላ አማራጭ እንደሌለ ሆኖ ይሰማቸዋል።

ሆኖም ዘ ወርልድ ቡክ ኢንሳይክሎፔዲያ እንዲህ በማለት ይጠቁማል:- “የአሁኑ አኗኗራቸው ይቀጥላል ብለው በሚያስቡ ባሕላዊ ኅብረተሰቦች መሐከል ያለው የወንጀል ብዛት ከሌላው ጋር ሲነጻጸር ባለበት የረጋ ይመስላል። ሰዎች ከሚኖሩበት ቦታ፣ ለኑሮአቸው ከሚያደርጉት ነገርና ለወደፊቱ ደኅንነታቸው ካላቸው ተስፋ ጋር በተያያዘ ፈጣን ለውጥ በሚካሄድባቸው ኅብረተሰቦች ውስጥ የሚፈጸመው የወንጀል ብዛት እያደገ የሚሄድበት አጋጣሚ ብዙ ነው።” ኢንሳይክሎፔዲያው በመጨመር እንዲህ ይላል:- “ወጣቶች ሥራ ለማግኘት ያላቸው እድል ያነሰ ነው። ሊያገኙት የሚችሉትን ሙያ የማይጠይቅ ሥራ በስርቆት ከሚገኘው ፈጣንና የሚያጓጓ ውጤት ጋር ሲያወዳድሩት አሰልቺ መስሎ ይታያቸዋል። ወጣቶች እሥራትን ባለመፍራት የመጣው ይምጣ በማለት ይሰርቃሉ፤ ምክንያቱም ይህ ቢያጋጥማቸውም እንኳ በሕይወታቸው የሚጎድልባቸው ጥቂት ነገር ብቻ ነው።”

ይሁንና ሥራ የሌላቸው ወይም ደሞዛቸው ዝቅተኛ የሆነ ብዙዎች ከስርቆት ሲቆጠቡ ብዙ የቢሮ ሠራተኞችና የፋብሪካ ወዛደሮች በሥራ ላይ እያሉ ይመዘብራሉ። ይህንንም የደሞዛቸው ክፍል አድርገው ይቆጥሩታል። እንዲያውም አንዳንድ ጊዜ የዓመፅ ድርጊቶችን ለመፈጸም አንድ ዓይነት ማኅበራዊ ሥልጣን ያስፈልጋል። ፖለቲከኞች፣ የመንግሥት ባለ ሥልጣኖችና ታላላቅ የንግድ ሰዎች ስለተካፈሉባቸው ከፍተኛ መጠን ባለው ገንዘብ ስለተሠሩ አሳፋሪ ቅሌቶች አልሰማህምን? ስርቆት በድሆች ብቻ አለመወሰኑ ምንም ጥያቄ የለውም።

ስለ ስርቆት በቀልድ መልክ የሚቀርቡ የሲኒማና የቴሌቭዥን ፕሮግራሞችንም አስታወስ። (ምናልባትም ጐበዙ ተዋናይ ሌባ ሊሆን ይችላል) እነዚህ ፊልሞች ስርቆት የበለጠ ተቀባይነት እንዲኖረው በር የሚከፍቱ ናቸው። እርግጥ ነው እንደዚህ ዓይነት ፊልሞችን መመልከቱ መዝናኛ ነው ሊባል ይችላል፤ ነገር ግን እግረ መንገዱን ተመልካቾቹን እንዴት መስረቅ እንደሚቻል ያስተምራል። ወንጀል ምናልባት ሊጠቅም ይችላል የሚለው ሐሳብ በረቀቀ መንገድ አልተላለፈምን? ያለጥርጥር ስስት፣ ስንፍናና ሁሉም ያደርገዋል ደግሞም ማንም አይቀጣም የሚለው አስተሳሰብ ለስርቆት መስፋፋት አስተዋጽኦ አድርገዋል። የምንኖረው የራስን ፍላጎት የማሳደድና የገንዘብ ፍቅር ባየለበት አስቀድሞ በተነገረው “አስጨናቂ ዘመን” ላይ መሆኑ አይካድም። — 2 ጢሞቴዎስ 3:​1–5

አትስረቅ

ምንም እንኳ ዓለም የተዛባ አቋም ቢኖረውም “የሰረቀ ከእንግዲህ ወዲህ አይስረቅ” የሚለውን ሕግ መታዘዝ በጣም አስፈላጊ ነው። (ኤፌሶን 4:​28) ንብረት ማካበትን ወይም ማሳደድን ከሚገባው በላይ ከፍ አድርጎ የሚመለከት ሰው ስርቆት ማንኛውም ዓይነት ዋጋ ሊከፈልለት ይገባል ብሎ በማመን ራሱን ሊያታልል ይችላል። ነገር ግን ስርቆት በአምላክ ዓይን ለመሰል ሰብዓዊ ፍጡሮች ፍቅር ማጣትን የሚያሳይ ከባድ ነገር ነው። በተጨማሪም የተሠረቁት ጥቃቅን ነገሮች ቢሆኑ እንኳ የሰውየውን ልብ ሊያደነድኑት ይችላሉ። እንደ እምነት አጉዳይ መታየቱስ ግምት ውስጥ ሊገባ አይገባውምን? ሌባን ማን ያምነዋል? የአምላክ ቃል በጥበብ እንዲህ ይላል:-“ከእናንተ ማንም ነፍሰ ገዳይ ወይም ሌባ ወይም ክፉ አድራጊ እንደሚሆን . . . መከራን አይቀበል።” — 1 ጴጥሮስ 4:⁠15

የስርቆትን መስፋፋት እንደምትኮንነው የተረጋገጠ ነው። ነገር ግን ወንጀል በተስፋፋባቸው አካባቢዎች ያሉ ሰዎች እንዴት ሊወጡት ይችላሉ? ቀደም ሲል ሌቦች የነበሩ አኗኗራቸውን የለወጡት እንዴት ነው? አንድ ቀን ስርቆት በዓለም ዙሪያ ያቆም ይሆንን? “ሌቦች የማይኖሩበት ዓለም” በሚል ርዕስ የቀረበውን የሚቀጥለውን ትምህርታዊ ጽሑፍ እንድታነብ እንጋብዝሃለን።

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ