ከሥራ አጥነት መላቀቅ የሚቻለው እንዴትና መቼ ነው?
እንደ ፈጣሪው ሁሉ ሰውም ሥራ ሲሠራ ደስ ይለዋል። ሥራ “የእግዚአብሔር ስጦታ ነው” ተብሎ በትክክል ተገልጿል። (መክብብ 3:12, 13፤ ዮሐንስ 5:17) የሚያነቃቃ ሥራ ደስታ ሊያመጣልንና ጠቃሚና ተፈላጊ እንደሆንን እንዲሰማን ሊያደርግ ይችላል። ማንም ሰው ሥራውን የቱንም ያህል ባይደሰትበት ሊያጣው አይፈልግም። ተቀጥሮ መሥራት ገቢ ከማስገኘቱም በተጨማሪ ለሕይወታችን ቅርጽና ዓላማ ይሰጠዋል፤ ራስን የመቻል ስሜትም ያሳድራል። “ሥራ አጥ የሆነ ሰው ከምንም ነገር በላይ የሚፈልገው ሥራ ነው” መባሉ ምንም አያስደንቅም።
ሥራ ፍለጋ
ቀደም ሲል እንደተመለከትነው በሥራው መስክ ያለው ሁኔታ እጅግ የተወሳሰበ ነው። ይህም በመሆኑ ሥራ መፈለግ የሚቻልባቸው ብዙ ጥሩ ዘዴዎች ተፈጥረዋል። ለሥራ አጦች ድጎማ በሚሰጥባቸው ቦታዎች የዚሁ ዝግጅት ተጠቃሚ መሆን ይቻላል። ሥራ የሌላቸው ሰዎች የሚመዘገቡባቸው ቦታዎች ካሉና ብቃቱንም የሚያሟሉ ከሆነ ሄደው ሊመዘገቡና መሥሪያ ቤቱ የሚሰጠውን ግልጋሎት መቀበል ይችላሉ። ሌሎች ደግሞ የራሳቸውን ሥራ በመፍጠር ባለ ሥራ ይሆናሉ። ይሁን እንጂ ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል። ብዙውን ጊዜ የራሳቸውን ሥራ የሚፈጥሩ ሰዎች ሥራውን ሲጀምሩ ብዙ ገንዘብ ያወጣሉ፤ ዕዳውን መክፈል ግን ቀላል ላይሆን ይችላል። በተጨማሪም የግብር እና የቀረጥ ሕጎችን ማወቅና ማክበር ይኖርባቸዋል። በአንዳንድ አገሮች ይህ ከባድ ጫና ነው።— ሮሜ 13:1-7፤ ኤፌሶን 4:28
አንዳንዶች ሥራ ፍለጋን ሥራዬ ብለው ተያይዘውታል። በብልህነትና በትዕግሥት ይህን ግባቸውን ዳር ለማድረስ ከፍተኛ ጥረት ያደርጋሉ። ሌሎች ደግሞ ሠራተኛ መቅጠር ወደሚፈልጉ ኩባንያዎች ማመልከቻ አስገብተዋል ወይም በጋዜጦች ላይ ሥራ እንደሚፈልጉ የሚገልጽ ማስታወቂያ አውጥተዋል። አንዳንድ የውጭ ጋዜጦች የሥራ ፈላጊዎችን ማስታወቂያ በነፃ አትመው ያወጣሉ። ንቁ! በተለያዩ ጊዜያት በዚህ ጉዳይ ላይ ለወጣቶችም ሆነ ለአዋቂዎች ጠቃሚና ተግባራዊ መሆን የሚችሉ ሐሳቦች ሰጥቷል።a— በገጽ 11 ላይ ያሉትን ሣጥኖች ተመልከት።
ከአዳዲስ ሁኔታዎች ጋር የምትስማማ መሆን አለብህ፤ ማንኛውንም ዓይነት ሥራ፣ የማትወደውንም ጭምር፣ ለመሥራት ፈቃደኛ ሁን። ሰዎች በአንድ መሥሪያ ቤት ለመቀጠር ቃለ መጠይቅ ሲደረግላቸው በቅድሚያ የሥራ ልምዳቸውንና ሥራ ከፈቱ ምን ያህል ጊዜ እንደሆናቸው የሚጠየቁ መሆኑን ባለሞያዎች ይናገራሉ። ለረጅም ጊዜ ሥራ ፈተህ መቆየትህ ለቀጣሪው በጎ ነገር አይጠቁምለትም።
የትምህርት ዘመኑን አንድ ዓይነት ሞያ ለመቅሰም የተጠቀመበት ሰው ትምህርት ከጨረሰ በኋላ የመጀመሪያውን ሥራ ለመያዝ የተሻለ ዕድል ይኖረዋል። የሥነ ገንዘብ ሳይንስ አስተማሪ የሆኑት አልቤርቶ ማዮኪ “ሥራ አጥነት በተለይ የሚያጠቃው ምንም ሞያ የሌላቸውን ሰዎች ነው” ብለዋል።
የሞራል ድጋፍ አስፈላጊነት
መደረግ ካለባቸው ዋና ነገሮች አንዱ ብሩህ አመለካከት መያዝ ነው። ይህ አቋም ሥራ ለመያዝ ወይም ላለመያዝ ምክንያት ሊሆን ይችላል። ሥራ አጥ የሆኑ ሰዎች አይዞህ መባልን በጣም ይፈልጋሉ። ይህ ዓይነቱ የሞራል ድጋፍ ራሳቸውን እንዳያገሉ ወይም ለሁሉም ነገር ግድ የሌላቸው እንዳይሆኑ ይረዳቸዋል። በተጨማሪም ራሳቸውን ከሥራ ካልወጡት ጋር በማወዳደር የሞራል ውድቀት እንዳይሰማቸው ለመከላከል ይረዳል።
አነስተኛ በሆነ ገንዘብ ኑሮ መግፋቱም እንኳ ቀላል ላይሆን ይችላል። “ጭንቀት ይሰማኝ ስለነበረ ጊዜዬን በደንብ ልጠቀምበት አልቻልኩም” ሲል ስቴፋኖ ተናግሯል። ፍራንቼስኮም ያለፈውን በማውሳት “ሁኔታው ከባድ ጭንቀት ውስጥ ስለከተተኝ ሆደ ባሻ ሆንኩና ውድ ወዳጆቼን እንኳ በትንሽ በትልቁ እቀየማቸው ጀመር” ብሏል። ቤተሰቡ ድጋፍ መስጠት ያለበት እዚህ ላይ ነው። ገቢ ከተቋረጠ መላው ቤተሰብ የአኗኗር ደረጃውን ዝቅ ማድረግና ይህን ለውጥ ለመቀበል ፈቃደኛ መሆን ያስፈልገዋል። ለአንድ ኩባንያ 23 ዓመት ከሠራ በኋላ ከሥራ የተባረረው የ43 ዓመቱ ፍራንኮ “ከሥራ ከተባረርኩበት ዕለት ጀምሮ ሚስቴ ብሩህ አመለካከት ያዘች፣ በጣም ታጽናናኝ ነበር” ብሏል። አርማንዶ ደግሞ ሚስቱ በተለይ “ገበያ ስትገበይ በጣም ጠንቃቃ” በመሆኗ እርሷን የሚያመሰግንበት ልዩ ምክንያት ነበረው።— ምሳሌ 31:10-31፤ ማቴዎስ 6:19-22፤ ዮሐንስ 6:12፤ 1 ጢሞቴዎስ 6:8-10
የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች አዎንታዊ መንፈስ እንድንይዝና ይበልጥ ዋጋ ያላቸውን ነገሮች እንዳንዘነጋ ሊረዱን ይችላሉ። ንቁ! ጥያቄ ያቀረበላቸው ከዚህ በላይ የተጠቀሱት ግለሰቦች ከመጽሐፍ ቅዱስ መንፈስን የሚያረጋጋ አጽናኝ ሐሳብ አግኝተዋል። ይህም ወደ አምላክ ይበልጥ እንደቀረቡ እንዲሰማቸው አድርጓል። (መዝሙር 34:10፤ 37:25፤ 55:22፤ ፊልጵስዩስ 4:6, 7) ይሖዋ አምላክ “አልለቅህም፣ ከቶም አልተውህም” ብሎ ቃል ስለገባልን ከእርሱ ጋር በጣም መቀራረብ ከምንም ነገር በላይ አስፈላጊ ነው።— ዕብራውያን 13:5
አንድ ሰው ሥራ ይኑረውም አይኑረው የአምላክ ቃል ለዕለት ተዕለት ኑሮ ጠቃሚ የሆኑ ባሕርያትን ኮትኩቶ እንዲያፈራ ያበረታታዋል። የይሖዋ ምሥክሮች በአሠሪዎች ዘንድ ተፈላጊ መሆናቸውና እንደ ሐቀኛ ሠራተኞች ተቆጥረው መመስገናቸው ባጋጣሚ የመጣ ነገር አይደለም። መጽሐፍ ቅዱስ ሰነፍ እንዳይሆኑ፣ ከዚህ ይልቅ ትጉና እምነት የሚጣልባቸው እንዲሆኑ የሚሰጣቸውን ምክር ይከተላሉ።— ምሳሌ 13:4፤ 22:29፤ 1 ተሰሎንቄ 4:10-12፤ 2 ተሰሎንቄ 3:10-12
ሥራ አጥነት ካመጣው ፍርሃት መላቀቅ
ለሥራ አጥነት ሥረ መሠረት የሆነ ነገር አለ፤ እርሱም ሰብዓዊ ራስ ወዳድነትና ስግብግብነት ነው። መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚለው “ሰው ሰውን የገዛው ለጉዳቱ ነው።”— መክብብ 8:9 አዓት
ሥራ አጥነትም ይሁን ሌሎች ችግሮች ባሁኑ ሰዓት ‘በመጨረሻ ቀኖቹ’ ላይ የሚገኘው ሰብዓዊ አገዛዝ ሲወገድ መፍትሔ ያገኛሉ። (2 ጢሞቴዎስ 3:1-3) አዲስ የሆነ ዓለም በእርግጥ ያስፈልገናል። አዎን፣ በፍትሐዊ አገዛዝ ሥር እየኖረ መሥራት የሚችል ጻድቅ ሰብዓዊ ኅብረተሰብ የሚኖርበት፣ ስግብግብነት የሚቀርበት ዓለም ያስፈልገናል። (1 ቆሮንቶስ 6:9, 10፤ 2 ጴጥሮስ 3:13) ኢየሱስ የአምላክ መንግሥት እንዲመጣና ፈቃዱ በምድር ላይ እንዲሆን እንዲጸልዩ ሰዎችን ያስተማረው በዚህ ምክንያት ነው።— ማቴዎስ 6:10
የአምላክ ቃል የሰው ልጆች አንዳንድ ዐበይት ችግሮች መወገዳቸውን በማመልከት ያ መንግሥት የሚያመጣቸውን ለውጦች በትንቢት መልክ እንዲህ ሲል ይገልጻል:- “ቤቶችንም ይሠራሉ ይቀመጡባቸውማል፤ ወይኑንም ይተክላሉ ፍሬውንም ይበላሉ። ሌላ እንዲቀመጥበት አይሠሩም፣ ሌላም እንዲበላው አይተክሉም፤ . . . በእጃቸው ሥራ ረጅም ዘመን ደስ ይላቸዋልና። . . . በከንቱ አይደክሙም ለጥፋትም አይወልዱም።” (ኢሳይያስ 65:21-23) በዓለም ላይ አስፈሪ ጥላውን የዘረጋው ሥራ አጥነት ለዘወትር ይገፈፋል። አምላክ ስላዘጋጀው መፍትሔ ይበልጥ ለማወቅ የምትሻ ከሆነ ባካባቢህ የሚገኙትን የይሖዋ ምሥክሮች አግኝተህ አነጋግር።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a ንቁ! ሚያዝያ—ሰኔ 1995 ገጽ 10-12፤ በእንግሊዝኛ እትሞች ደግሞ ነሐሴ 8, 1991 ገጽ 6-10፤ ጥር 22, 1983 ገጽ 17-19፤ ሰኔ 8, 1982 ገጽ 3-8 ተመልከት።
[በገጽ 11 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
የቤት ውስጥ ሥራ መፍጠር
• የጓሮ አትክልትና አበባ መሸጥ
• ልብስ መስፋት፣ ማስተካከልና መጠገን
• ለፋብሪካዎች ጥሬ ዕቃ ማቅረብ
• እንጀራ ወይም ዳቦ ጋግሮ መሸጥ
• ሽሮ፣ በርበሬ፣ በሶ፣ ቅመማ ቅመም እያዘጋጁ ማቅረብ
• ያልጋ ልብስ ወይም ሹራብ መሥራት፣ ጥልፍ፣ የሸክላ ሥራ፣ ጥጥ መፍተል፣ ሌሎች የእጅ ሥራዎች
• ሶፋና ወንበር ማደስ
• የሒሳብ መዝገብ ያዥነት፣ ታይፕ መጻፍ፣ የቤት ውስጥ የኮምፒዩተር አገልግሎት
• ፀጉር ማስተካከል፣ ሽሩባ መሥራት
• ለደንበኞች ምግብ ማብሰል፤ ቤት አከራይቶ መቀለብ
• መኪና ማጠብና መወልወል (ደንበኛው ወደ ቤት እንዲያመጣ በማድረግ)
• ውሻ ማጠብ፣ ማንሸራሸር
• የበር ቁልፍ መሥራትና መጠገን (ቤት ውስጥ ወርክሾፕ ካለ)
• አርቲፊሻል አበባ ሠርቶ መሸጥ
• ልብስ ማጠብና መተኮስ
• ዶሮ ማርባት፣ ላም እያረቡ ወተት መሸጥ
[በገጽ 11 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
ከቤት ውጭ ሥራ መፍጠር
• ሞግዚትነት፣ ልጆችን ትምህርት ቤት ማመላለስ
• ቤት መጠበቅ (ባለቤቶቹ በማይኖሩበት ጊዜ)
• ጽዳት:- ሱቅ፣ መሥሪያ ቤት፣ መኖሪያ ቤት እንዲሁም መስኮት መወልወል (የመሥሪያ ቤት፣ የቤት)
• ልዩ ልዩ የጥገና ሥራ
• ረዳት ሆኖ መሥራት:- የአናጺ፣ የግንበኛ፣ የቀለም ቀቢ፣ ወዘተ . . .
• እርሻ:- አጨዳ፣ ቡና መልቀም፣ እህል ማበጠር
• ጥበቃ:- ቤት፣ ንብረት መጠበቅ
• ደላላነት:- ቤት፣ ንብረት ማሻሻጥ
• ተላላኪነት
• ጋዜጣ ማዞር (ትልልቆችም ሆኑ ትንንሾች)፣ ለደንበኞች ጋዜጣ ማድረስ
• አትክልተኝነት:- ቁፋሮ፣ ሣር ማጨድ፣ ጥድ መከርከም
• ሾፌርነት
• እየተዘዋወሩ ፎቶግራፍ ማንሳት (ግለሰቦችን ወይም በድግስ ቦታ)
• ቧንቧ ሥራ፣ የኤሌክትሪክ ሥራ
• ግንበኝነት፣ አናጺነት፣ ቀለም ቀቢነት
• ልጆችን በየቤታቸው ማስተማር
• ቅቤ፣ ማርና ሌላ ምርት ከምንጩ አምጥቶ መሸጥ
• ሰው ቤት ተቀጥሮ መሥራት
[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
“እኔም የመረጥኋቸው በእጃቸው ሥራ ረጅም ዘመን ደስ ይላቸዋል።”— ኢሳይያስ 65:22