እንደ ቸነፈር የተዛመተው ሥራ አጥነት
ኢጣሊያ የሚገኘው የንቁ! መጽሔት ዘጋቢ እንዳጠናቀረው
በርካታ የበለጸጉ አገሮች አፋጣኝ መፍትሔ የሚሻ ዱብ ዕዳ ሆኖባቸዋል፤ ታዳጊ አገሮችንም አስጨንቋል። ከዚህ በፊት ጨርሶ ወዳልታየባቸው ስፍራዎች እየዘለቀ ነው። በመቶ ሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን በር አንኳኩቷል፤ ብዙዎቹም እናቶችና አባቶች ናቸው። ለሁለት ሦስተኛው የኢጣሊያ ሕዝብ “ቁጥር 1 ስጋት” ሆኖባቸዋል። አዳዲስ ማኅበራዊ ችግሮችን ይፈጥራል። የአደንዛዥ ዕፅ ሱሰኞች ወደዚህ አደጋ እንዲወድቁ በከፊል ምክንያት ሆኗል። በሚልዮን የሚቆጠሩትን እንቅልፍ ነስቷል፣ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሌሎችን ደግሞ አድብቶ ይጠብቃቸዋል . . .
“ሥራ አጥነት ምናልባት በዘመናችን ውስጥ በስፋት የተዛመተው ዋናው አስፈሪ ክስተት ሳይሆን አይቀርም” በማለት የኢኮኖሚ ትብብርና ልማት ድርጅት (OECD) አረጋግጧል። የአውሮፓ ማኅበረሰቦች ኮሚሽን “የዚህ ክስተት ስፋትና ያስከተለው ውጤት ይታወቃል፤ ችግሩን ማስወገድ ግን በጣም አዳጋች ነው” ሲል ጽፏል። አንድ ተመራማሪ “የዚህን ጥንታዊ አህጉር [የአውሮፓን] አውራ ጐዳናዎች በፍርሃት ያጥለቀለቀ መቅሰፍት” በማለት ገልጸውታል። በአውሮፓ ኅብረት (EU) ውስጥ ባሁኑ ጊዜ የሥራ አጦች ቁጥር 20 ሚልዮን የደረሰ ሲሆን በኢጣሊያ 2,726,000 መድረሱን ጥቅምት 1994 ይፋ የወጣው አኃዝ ጠቁሟል። በአውሮፓው ኅብረት ኮሚሽነር ፓድራይግ ፍላይን አመለካከት “ከሥራ አጥነት ጋር የሚደረገው ትግል በፊታችን ከተደቀኑት ማኅበረሰባዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ሁሉ የላቀ ተፈታታኝ ነው።” አንተ ራስህ ሥራ አጥ ከሆንክ ወይም ከሥራ የመባረር አደጋ ተደቅኖብህ ከሆነ ይህ ሁኔታ የሚፈጥረውን ፍርሃት ታውቀዋለህ።
ይሁንና ሥራ አጥነት የአውሮፓ ችግር ብቻ አይደለም። የሰሜንና የደቡብ አሜሪካን አገሮች በሙሉ አጥለቅልቋል። አፍሪካን፣ እስያንና በውቅያኖሶች ያሉትን ደሴቶች አዳርሷል። ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የምሥራቅ አውሮፓ አገሮችም መነካት ጀምረዋል። እርግጥ፤ ከአገር ወደ አገር የችግሩ መጠን ይለያያል። ሆኖም አንዳንድ የኢኮኖሚ ጠበብት እንደሚሉት በአውሮፓና በሰሜን አሜሪካ የሥራ አጦች ብዛት ካለፉት አሥርተ ዓመታት ሁሉ ዛሬ የላቀ ደረጃ ደርሷል፤ ለረጅም ጊዜም በዚሁ ይቀጥላል። ሬናቶ ብሩኔታ የተባሉት የኢኮኖሚ ምሁር “በቂ ሥራ ያለማግኘት ችግር እየጨመረ ሲሄድና ያሉትም ሥራዎች ቢሆኑ የጥራት ደረጃቸው እያዘቀጠ ሲሄድ ሁኔታው መባባሱ አይቀርም” ብለዋል።
የማይገታ ግስጋሴ
ሥራ አጥነት ሁሉንም የኢኮኖሚ ዘርፎች አንድ በአንድ መቷል። በመጀመሪያ በአዳዲስ መሣሪያዎች በይበልጥ እየታገዘ ሰዎችን ከሥራ ውጭ ያደረገው የግብርና ክፍለ ኢኮኖሚ የጥቃቱ ዒላማ ሆኖአል። ቀጥሎም በተለይ ከ1970ዎቹ ዓመታት ወዲህ የነዳጅ ዋጋ በፈጠረው ቀውስ ምክንያት የታመሰው የኢንዱስትሪው ክፍለ ኢኮኖሚ ተጠቂ ሆኗል። አሁን ደግሞ ጨርሶ አይነካም ይባልለት ወደነበረው አገልግሎት ሰጪ ክፍለ ኢኮኖሚ፣ ይኸውም ወደ ንግድና ትምህርት ተቋማት ተዛምቷል። ከሃያ ዓመት በፊት የሥራ አጦች ብዛት ከ2 ወይም ከ3 በመቶ በላይ ከፍ ቢል ብዙዎችን ያሸብር ነበር። ዛሬ ግን አንድ በኢንዱስትሪ የበለጸገ አገር የሥራ አጡን መጠን ከ5 ወይም 6 በመቶ እንዳይበልጥ መከላከል ከቻለ ደኅና ተሳክቶለታል ወደሚባልበት ደረጃ ተደርሷል። በበርካታ የበለጸጉ አገሮች ግን የሥራ አጦች ብዛት ከዚህ በላይ ነው።
በዓለም አቀፍ የሠራተኞች ድርጅት (ILO) አተረጓጐም መሠረት ሥራ አጥ ማለት ለመሥራት ዝግጁ ሆኖ ሳለ፣ ሥራም ቢያፈላልግ ምንም ሥራ ያላገኘ ሰው ማለት ነው። ሥራው ቋሚና የሙሉ ቀን ስላልሆነው ወይም በሳምንት ውስጥ ለጥቂት ሰዓታት ብቻ ለመሥራት ስለሚገደደው ሰውስ ምን ለማለት ይቻላል? የከፊል ጊዜ ተቀጣሪነት በተለያዩ አገሮች የተለያየ ትርጓሜ ይሰጠዋል። በአንዳንድ አገሮች ከእውነታው አንፃር ሲታይ ሥራ ያልያዙ ሰዎች ሥራ እንዳላቸው ተደርገው ይታያሉ። አንድ ወጥ የሆነ አተረጓጐም ስለሌለ ሥራ አጥ የሆነው ማን እንደሆነ ለማወቅ አስቸጋሪ ይሆናል። በመሆኑም ስለዚህ ጉዳይ የወጡት አኃዞች የሚያሳዩት ከፊሉን እውነታ ብቻ ነው። አንድ በአውሮፓ የተካሄደ ጥናት “በኢኮኖሚ ትብብርና ልማት ድርጅት በታቀፉት አገሮች ውስጥ 35 ሚልዮን ሥራ አጦች አሉ ቢባልም ይህ አኃዝ የሥራ አጥነቱን ስፋት ሙሉ በሙሉ አያንጸባርቅም” ብሏል።
ሥራ አጥነት የሚያስከትለው ከፍተኛ ኪሣራ
አኃዞች ትክክለኛውን ሁኔታ ቁልጭ አድርገው አያስቀምጡም። የአውሮፓ ማኅበረሰቦች ኮሚሽን “ሥራ አጥነት የሚያስከትለው ኢኮኖሚያዊና ማኅበረሰባዊ ኪሣራ ከፍተኛ ነው። ኪሣራው ለሥራ አጦቹ የሚሰጠው የገንዘብ እርዳታ ብቻ ሳይሆን እነዚህ ሰዎች ቢሠሩ ኖሮ ለመንግሥት ሊገባ ይችል የነበረው ግብር መቅረቱ ጭምር ነው” ብሏል። ለሥራ አጦች የሚሰጠው የገንዘብ ድጎማ ለመንግሥት ብቻ ሳይሆን ተጨማሪ ግብር ለሚቆለልባቸው ተቀጣሪ ሠራተኞች ጭምር ከባድ ሸክም ሆኖባቸዋል።
ሥራ አጥነት የአኃዞችና የማብራሪያዎች ጉዳይ ብቻ አይደለም። ተከትለውት የሚመጡ ልዩ ልዩ መዘዞችም አሉ፤ ምክንያቱም ይህ ቸነፈር ማንኛውንም ሰው፣ ይኸውም በሁሉም ማኅበራዊ መደቦች የሚገኙትን ወንዶች፣ ሴቶችና ወጣቶች አይምርም። ሥራ አጥነት በእነዚህ “መጨረሻ ቀኖች” ከተከሰቱት ሌሎች ችግሮች ጋር ተዳምሮ ይህ ነው የማይባል ጫና ሊፈጥር ይችላል። (2 ጢሞቴዎስ 3:1-5፤ ራእይ 6:5, 6) በተለይ ደግሞ አንድ ሰው ሌሎች ችግሮች እንዳሉ ሆነው ለረጅም ጊዜ ሥራ ፈቶ ከቆየ ከናካቴው ሥራ መያዝ ሊያስቸግረው ይችላል። ነገሩ ቢያሳዝንም አንዳንዶቹ እስከ መጨረሻው ድረስ ሥራ ላይዙ ይችላሉ።
በዛሬው ጊዜ ሥራ አጦች የአእምሮና የስነ ልቦና ችግሮች ይበልጥ እየታየባቸው መምጣቱን የስነ ልቦና ሐኪሞች ይናገራሉ። ከዚህም በላይ የስሜት አለመረጋጋት፣ ብስጭት፣ እያደገ የሚሄድ ግድየለሽነትና የሞራል ውድቀት ይታይባቸዋል። የሚያስተዳድራቸው ልጆች ያሉት ሰው ከሥራ ቢወጣ ዘመድ የሞተበት ያህል ያዝናል። በዙሪያው ያለው ዓለም እንደ ከዳው ይሰማዋል። ዋስትና ያለው ሕይወት እንደ እንፋሎት ይተንበታል። እንዲያውም አንዳንድ ጠበብት በዛሬው ጊዜ ከሥራ እወጣ ይሆን የሚል ስጋት በዓለም ላይ በአዲስ መልክ እየተከሰተ መምጣቱን ይናገራሉ። ይህ ዓይነቱ ስጋት በቤተሰብ ውስጥ ሁከት ፈጥሯል። እንዲያውም በቅርብ ጊዜ ራሳቸውን የሚገድሉ ሥራ አጥ ሰዎች ሁኔታ እንደሚጠቁመው የከፋ ውጤትም ሊያመጣ ይችላል። ከዚህም በተጨማሪ ወደ ሥራው መስክ ለመግባት አለመቻል ወጣቱን ለዓመፅና ከማኅበረሰቡ ለመገለል ከዳረጉት ነገሮች አንዱ ነው።
‘የተዛባ ሥርዓት እስረኞች’
ንቁ! ከሥራ ለወጡ በርካታ ሰዎች ጥያቄ አቅርቦ ነበር። የሃምሳ ዓመቱ አርማንዶ ለእርሱ ከሥራ መውጣት ማለት ‘30 ዓመት የለፋበት ሁሉ ዶግ አመድ እንደሆነበትና ኑሮን እንደ አዲስ መጀመር’ ማለት እንደሆነ ተናግሯል። በመጨመርም ‘የተዛባ ሥርዓት እስረኛ’ እንደሆነ ሆኖ እንደሚሰማው ገልጿል። ፍራንቼስኮ ‘ዓለም ዘጭ ብሎ እንደወደቀብኝ ሆኖ ተሰማኝ’ ብሏል። ስቴፋኖ ‘በአሁኑ የኑሮ ሥርዓት ምንም ያልጠበቀው ነገር ስለደረሰበት ከፍተኛ ብስጭት እንደተሰማው’ ተናግሯል።
በሌላው በኩል ደግሞ በኢጣሊያ ውስጥ በአንድ ትልቅ የመኪና ፋብሪካ ውስጥ የቴክኒካል ዘርፍ ኃላፊ ሆኖ ለ30 ዓመት ያህል የሠራው ሉቻኖ ከሥራው ሲባረር ‘ለብዙ ዓመታት የደከምኩት ድካም፣ ለሥራዬ ያሳየሁት ጥንቃቄና ታማኝነት ሁሉ ከንቱ ሆኖ ሲቀር ቁጣና ቁጭት ተሰምቶኛል’ ብሏል።
ትንበያዎችና በከንቱ የተጠበቁ ተስፋዎች
አንዳንድ የኢኮኖሚ ጠበብት አሻግረው የተመለከቱት ትዕይንት ከዚህ የተለየ ነበር። በ1930 የኢኮኖሚ ምሁር ጆን ሜይናርድ ኪንስ ብሩህ ተስፋ በመስጠት በቀጣዮቹ 50 ዓመታት ውስጥ “ሁሉም ሰው ሥራ ይኖረዋል” የሚል ትንበያ አሰምተው ነበር። ለአያሌ አሥርተ ዓመታት ሁሉም ሰው የሙሉ ቀን ሥራ የማግኘቱ ጉዳይ ሊጨበጥ የሚችል ግብ እንደሆነ ተደርጎ ይታይ ነበር። በ1945 የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ቻርተር ሲቀረጽ ለሁሉም ሰው ሙሉ የሥራ ዕድል በአፋጣኝ ማስገኘትን ግቡ አድርጎ አስቀምጦ ነበር። የኢኮኖሚው ሁኔታ እየተሻሻለ ሲሄድ እያንዳንዱ ሰው ሥራ እንደሚያገኝና የሥራ ሰዓትም እንደሚቀነስለት እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ሲታመንበት ነበር። በመጨረሻ ላይ ግን ሁሉ ነገር እንደታሰበው ሳይሆን ቀርቷል። ‘በ1930ዎቹ ዓመታት ከደረሰው ታላቅ የኢኮኖሚ ድቀት ወዲህ ያለፈው አሥርተ ዓመት በገበያ መቀዝቀዝ ሳቢያ ተወዳዳሪ ያልተገኘለት የሥራ አጥነት ቀውስ’ እንዳስከተለ ዓለም አቀፍ የሠራተኞች ድርጅት አስታውቋል። በደቡብ አፍሪካ ውስጥ ቢያንስ 3.6 ሚልዮን ሰዎች ሥራ የሌላቸው ሲሆኑ ከእነዚህ መካከል 3 ሚልዮን የሚያክሉት ጥቁሮች ናቸው። ጃፓንም ባለፈው ዓመት ከሁለት ሚልዮን በላይ ሠራተኞች ከሥራ የተባረሩባት በመሆኑ ከፍተኛ ቀውስ ውስጥ ገብታለች።
ሥራ አጥነት ይህን ያህል እንደ ቸነፈር የተዛመተው ለምንድን ነው? ችግሩን ለመቅረፍስ ምን የመፍትሔ ሐሳቦች ቀርበዋል?
[በገጽ 2, 3 ላይ የሚገኝ ካርታ]
(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)
ካናዳ—9.6 ከመቶ
ዩ ኤስ ኤ—5.7 ከመቶ
ኮሎምቢያ—9 ከመቶ
አየርላንድ—15.9 ከመቶ
ስፔይን—23.9 ከመቶ
ፊንላንድ—18.9 ከመቶ
አልባኒያ—32.5 ከመቶ
ደቡብ አፍሪካ—43 ከመቶ
ጃፓን—3.2 ከመቶ
ፊሊፒንስ—9.8 ከመቶ
አውስትራሊያ—8.9 ከመቶ
[ምንጭ]
Mountain High Maps™ copyright © 1993 Digital Wisdom, Inc.