ወጣቶች የሚጠይቋቸው ጥያቄዎች . . .
ጓደኞቼ የሚተዉኝ ለምንድን ነው?
“ጓደኛዬና እኔ ተመሳሳይ ፍላጎቶች የነበሩን ከመሆኑም በላይ ብዙ ነገሮችን አብረን እንሠራ ነበር፤ እንዲሁም አብረን ጊዜ እናሳልፍ ነበር። ይሁን እንጂ የነበረን ጓደኝነት በድንገት መቀዝቀዝ ጀመረ። ይህም ከፍተኛ የጭንቀት ስሜት አሳድሮብኛል።”—ማሪያ
ከብዙ ጥረት በኋላ ስሜትህን የሚረዳልህና በትንሹ በትልቁ የማይነቅፍህ ጓደኛ አገኘህ እንበል። ከዚያም የነበራችሁ ጓደኝነት በድንገት ተቋረጠ። ችግሩን ለመፍታት ሞከርክ፤ ሆኖም ሳይሳካልህ ቀረ።
ታማኝ ጓደኛ እጅግ ውድ ነው። (ምሳሌ 18:24) ለተወሰነ ጊዜ በወዳጅነት አብሮ የቆየን ጓደኛ ማጣት ደግሞ በጣም አሳዛኝ ነው። ኢዮብ ጓደኞቹ በተዉት ጊዜ “ዘመዶቼ ተቋረጡ፣ ወዳጆቼም ረሱኝ” በማለት በምሬት እንደተናገረ መጽሐፍ ቅዱስ ይነግረናል። (ኢዮብ 19:14) አንተም ከጓደኛህ ጋር የነበረህ ቅርርብ በቅርቡ ተቋርጦ ከነበረ ተመሳሳይ የሆነ የሐዘን ስሜት ሊሰማህ ይችላል። ወጣቱ ፓትሪክ እንደተናገረው “የምትወደው ሰው የሞተብህ ያክል ሆኖ ይሰማሃል።” ይሁን እንጂ የምትመሠርተው ጓደኝነት ሁሉ የሚፈርስ ቢሆንስ?
በቀላሉ የሚፈርስ ጓደኝነት
ኢስትዉድ አትዎተር ያዘጋጁት አዶለሰንስ የተባለው መጽሐፍ በአሥራዎቹ ዕድሜ ላይ ያሉ ወጣቶች የሚመሠርቱት ጓደኝነት “ተለዋዋጭ ሲሆን ጓደኝነቱም በሚቋረጥበት ጊዜ ድንገተኛና ከፍተኛ የሆነ ለውጥ እንዲሁም መሪር ሐዘን ያስከትልባቸዋል” በማለት ይዘግባል። በአሥራዎቹ ዕድሜ ላይ የሚገኙ ወጣቶች የሚመሠርቱት ጓደኝነት በቀላሉ የሚፈርሰው ለምንድን ነው? አንዱ ምክንያት በዕድሜ እየገፋህ በሄድክ መጠን ስሜትህ፣ አመለካከትህ፣ ግቦችህና ፍላጎቶችህ ለውጥ ማድረግ ይጀምራሉ። (ከ1 ቆሮንቶስ 13:11 ጋር አወዳድር።) በአንዳንድ ሁኔታዎች እኩዮችህን አልፈህ ልትሄድ አሊያም ወደ ኋላ ልትቀር ትችላለህ።
ስለዚህ ሁለት ጓደኛሞች ዕድሜያቸው እየጨመረ በሚሄድበት ጊዜ አንዳቸው ሌላውን በማስቀየማቸው ምክንያት ሳይሆን የተለያዩ ግቦችን፣ ፍላጎቶችንና የሥነ ምግባር አቋሞችን እያዳበሩ ስለሚሄዱ ወዳጅነታቸው እየቀዘቀዘ ይሄዳል። እንዲያውም ግንኙነቱ ቢያከትም የተሻለ ሊሆን የሚችልበት ሁኔታ አለ። በዕድሜ ስትገፋና ለመንፈሳዊ ነገሮች ከፍተኛ ትኩረት መስጠት ስትጀምር ከቀድሞ ጓደኞችህ መካከል አንዳንዶቹ በጎ ተጽዕኖ እንደማያሳድሩብህ ትገነዘብ ይሆናል። (1 ቆሮንቶስ 15:33) ስለነርሱ ታስብ ይሆናል፤ ሆኖም ከዚህ ቀደም እንደነበረው ዓይነት ጓደኝነት እንዲኖራችሁ አትፈልግም።
ወዳጅነትን የሚበክሉ ነገሮች
ሆኖም ቅርርባችሁን ጠብቀህ ለማቆየት እየፈለግህ ጓደኞችህ ሁልጊዜ የሚተዉህ ከሆነስ? በግልጽ ለመናገር ልታሻሽላቸው የሚገቡ አንዳንድ የግል ድክመቶች አሉብህ ማለት ነው። ለምሳሌ ያህል ቅናት በጓደኝነት መካከል ያለውን ዝምድና ያበላሻል። ከአንተ የበለጠ ሃብት፣ ለየት ያለ ተሰጥኦ፣ ጥሩ ቁመና ያለው ወይም በብዙ ሰዎች ዘንድ ተወዳጅ የሆነ ጓደኛ አለህ እንበል። ልዩ ትኩረት በማግኘቱ ቅር ትሰኛለህ? “ቅንዓት . . . አጥንትን ያነቅዛል።” (ምሳሌ 14:30) ወጣቱ ኪነን “ጓደኛዬ በብዙ ሰዎች ዘንድ ተወዳጅ በመሆኑና እኔ የሌሉኝ ነገሮች ሁሉ ስለነበሩት እቀናበት ነበር” በማለት ሃቁን ሳይሸሽግ ተናግሯል። “ይህም ጓደኝነታችንን ክፉኛ ጎድቶታል።”
ሁሌ የእኔ ይሁን የሚል መንፈስ ሌላው ጓደኝነትን ሊያበላሽ የሚችል ባሕርይ ነው። ጓደኛህ የበለጠውን ጊዜ ከሌሎች ጋር እያሳለፈ ከአንተ ጋር የሚያሳልፈውን ጊዜ ቢያሳንስ ምን ታደርጋለህ? አንዲት ወጣት “ሌሎች አንዳንድ ጓደኞቼን ሲያነጋግሯቸው እንኳን እቀና ነበር” በማለት አምናለች። ጓደኛህ ከሌሎች ጋር ሲቀራረብ ስታይ የክህደት ድርጊት እንደፈጸመ ሆኖ ሊሰማህ ይችላል።
ፍጽምናን መጠበቅም ለጓደኝነት መፍረስ አንዱ ምክንያት ሊሆን ይችላል። ለምሳሌ ያህል ጓደኛህ ስለ አንተ በማውራት ምናልባትም አንዳንድ ምስጢር ነክ የሆኑ ነገሮችን በመግለጥ እንዳማህ ሰምተህ ይሆናል። (ምሳሌ 20:19) “ሁለተኛ አላምነውም!” በማለት በብስጭት ትናገራለህ።
ጓደኝነት—መስጠት ነው መቀበል?
ቅናት፣ ሁሌ የእኔ ይሁን የሚል መንፈስ ወይም ፍጽምናን መጠበቅ ጓደኝነትህን አደጋ ላይ ጥሎት ከሆነ ‘ከጓደኝነት የምፈልገው ነገር ምንድን ነው?’ ብለህ ራስህን ጠይቅ። ጓደኝነት አንድን ሰው እንደፈለግከው የምታዘውና የጠየከውን ሁሉ የሚፈጽም አገልጋይ እንደሆነ አድርገህ ታስባለህ? ጓደኝነት መመሥረት የምትፈልገው ዝና፣ ተወዳጅነት ወይም ደግሞ የሆነ ጥቅም ለማግኘት ነውን? ጓደኛህ ሙሉ በሙሉ ለአንተ ያደረና ግንኙነታችሁ ለሌሎች ምንም ቦታ የማይሰጥ እንዲሆን ትፈልጋለህን? እንግዲያው ጓደኝነትን በሚመለከት ያለህን አመለካከት ማስተካከል ይኖርብሃል።
ከሌሎች ጋር ጥሩ ዝምድና ሊመሠረት የሚቻለው በመቀበል ሳይሆን በመስጠት እንደሆነ መጽሐፍ ቅዱስ ከያዛቸው ትምህርቶች እንማራለን! ኢየሱስ ክርስቶስ ማቴዎስ 7:12 ላይ “እንግዲህ ሰዎች ሊያደርጉላችሁ የምትወዱትን ሁሉ እናንተ ደግሞ እንዲሁ አድርጉላቸው” በማለት ተናግሯል። ከጓደኞች አንዳንድ ነገሮችን መጠበቅህ ያለ ነገር ነው። አንደርስታዲንግ ሪሌሽንሺፕስ የተባለው መጽሐፍ “ጓደኛችን ሁልጊዜ ሃቀኛና ግልጽ፣ አፍቃሪ፣ ሚስጥሩንና ችግሩን የሚያካፍለን በሚያስፈልገን ጊዜ ሁሉ እርዳታ የሚለግሰን፣ የሚያምነንና በተጨማሪም . . . አለመግባባቶችን ለማስተካከል ዝግጁ የሆነ ሰው እንዲሆን እንጠብቃለን” በማለት ይናገራል። ሆኖም ጉዳዩ በዚህ ብቻ አያበቃም። መጽሐፉ ጨምሮ ሲናገር “እነዚህ ነገሮች ሰዎች ጓደኛቸው እንዲያደርግላቸው የሚጠብቋቸውና በምላሹም ለጓደኛቸው ማድረግ የሚጠበቅባቸው ነገሮች ናቸው” ብሏል።—ጋደል አድርገን የጻፍነው እኛ ነን።
ኢየሱስ ራሱ ይቀርቡት የነበሩትን ሰዎች እንዴት ይይዛቸው እንደነበር ልብ በል። ደቀ መዛሙርቱን “ባሮች አልላችሁም፤ ባርያ ጌታው የሚያደርገውን አያውቅምና፤ ወዳጆች ግን ብያችኋለሁ” ብሏቸዋል። ይሁን እንጂ ኢየሱስ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር የነበረው ጓደኝነት እነርሱ ለእርሱ ሊያደርጉት በሚችሉት ነገር ላይ የተመሠረተ ነበር? በጭራሽ። “ነፍሱን ስለ ወዳጆቹ ከመስጠት ይልቅ ከዚህ የሚበልጥ ፍቅር ለማንም የለውም” ብሏል። (ዮሐንስ 15:13, 15) አዎን፣ የጓደኝነት እውነተኛ መሠረት የራስን ጥቅም መሥዋዕት የሚያደርግ ፍቅር ነው! ጓደኝነት በፍቅር ላይ የተመሠረተ ከሆነ በመካከል የሚፈጠሩ የሚያስቆጡ ነገሮችንና አንዳንድ ችግሮችን ሊያሸንፍ ይችላል።
ችግሮች በሚነሱበት ጊዜ
ለምሳሌ ጓደኛህ ከአንተ የበለጠ ገንዘብ፣ እውቀት ወይም ተሰጥኦ አለው እንበል። ከራስ ወዳድነት ነፃ የሆነ ፍቅር ጓደኛህ ባለው ነገር እንድትደሰት ይረዳሃል። እንዲያውም መጽሐፍ ቅዱስ “ፍቅር አይቀናም” ይላል።—1 ቆሮንቶስ 13:4
ወይም ጓደኛህ ስሜትህን የሚጎዳ አንድ ነገር ተናገረ ወይም አደረገ እንበል። ይህ ማለት ጓደኝነታችሁ ያከትምለታል ማለት ነው? ላይሆን ይችላል። ሐዋርያው ጳውሎስ በሚስዮናዊ ጉዞው ወቅት ማርቆስ የተባለ ጓደኛው ትቶት በተመለሰ ጊዜ በጣም ቅር ተሰኝቶ ነበር። በጣም ከማዘኑ የተነሳ በቀጣዩ ጉዞው ወቅት ማርቆስ አብሮት እንዲሄድ አልፈቀደም! እንዲያውም ጳውሎስ በዚሁ ጉዳይ የማርቆስ የአጎት ልጅ ከነበረው ከበርናባስ ጋር አንዳንድ ኃይለኛ ቃላት ተለዋውጦ ነበር። ሆኖም ከዓመታት በኋላ ጳውሎስ ማርቆስን አስመልክቶ ፍቅር በተሞላበት መንገድ ተናግሯል፤ እንዲያውም ሮም መጥቶ እንዲያገለግለው ጠርቶታል። የነበራቸውን አለመግባባት እንዳስተካከሉ ከዚህ ለመረዳት ይቻላል።—ሥራ 15:37-39፤ 2 ጢሞቴዎስ 4:11
ከጓደኛህ ጋር አለመግባባት በሚፈጠርበት ጊዜ እንዲህ ያለ እርምጃ ለመውሰድ ለምን አትሞክርም? ነገሮች እንዲባባሱ አትፍቀድ። (ኤፌሶን 4:26) ቸኩለህ አንድ መደምደሚያ ላይ ከመድረስህ ወይም በቁጣ ከመገንፈልህ በፊት ጓደኛህ እንዲናገር ፍቀድለት። (ምሳሌ 18:13፤ 25:8, 9) ምናልባት በትክክል ያልተረዳኸው ነገር ይኖር ይሆናል። ይሁን እንጂ ጓደኛህ ከእርሱ የማይጠበቅ ነገር አድርጎ ከሆንስ? ጓደኛህ ሰው መሆኑን አትዘንጋ። (መዝሙር 51:5፤ 1 ዮሐንስ 1:10) ሁላችንም ነገሮች ካለፉ በኋላ የሚጸጽተንን ነገር እንናገራለን እንዲሁም እናደርጋለን።—ከመክብብ 7:21, 22 ጋር አወዳድር።
ሆኖም ጓደኛህ የፈጸመው ድርጊት ምን ያህል እንደጎዳህ በግልጽ ልትናገር ትችላለህ። ይህም ጓደኛህ ከልቡ ይቅርታ እንዲጠይቅ ሊያነሳሳው ይችላል። ፍቅር ‘በደልን የማይቆጥር’ ስለሆነ አንተም ጉዳዩን ልትረሳው ትችላለህ። (1 ቆሮንቶስ 13:5) ወጣቱ ኪነን ከዚህ ቀደም ያጣውን ጓደኛ ወደ ኋላ መለስ ብሎ እያስታወሰ “ያጣሁትን ጓደኛዬን እንደገና ማግኘት ብችል ኖሮ ከጓደኝነታችን ፍጽምናን አልጠብቅም ነበር። ስህተቶቹን ከመለቃቀም ይልቅ የበለጠ አዳማጭና ደጋፊው እሆን ነበር። የተሳካ ጓደኝነት ማግኘት የሚቻለው ፈተናዎችንና አስቸጋሪ ሁኔታዎችን በመፍታት እንደሆነ አሁን ተረድቻለሁ” ብሏል።
ይሁን እንጂ ጓደኛህ እንደ በፊቱ ረዘም ያለ ወይም አንተ የምትፈልገውን ያህል ጊዜ አብሮህ ባያሳልፍስ? ይህ ስሜት ያደረብህ የጓደኛህን ጊዜና ትኩረት ከሚገባው በላይ ለመውሰድ በመፈለግህ ይሆን? ይህ ቅርርባችሁን በአጭሩ ሊቀጨው ይችላል። የተሳካ ጓደኝነት ያላቸው ሰዎች አንዱ ለሌላው የተወሰነ ነፃነት ይሰጣሉ። (ከምሳሌ 25:17 ጋር አወዳድር።) ሌሎች ሰዎችም አብረዋቸው የሚደሰቱበትን አጋጣሚ ይከፍታሉ! እንዲያውም መጽሐፍ ቅዱስ ክርስቲያኖች ጓደኝነታቸውን ‘እንዲያሰፉ’ ያበረታታቸዋል። (2 ቆሮንቶስ 6:13) ስለዚህ አንድ ጓደኛ እንዲህ ያለ ነገር ቢያደርግ እንደ ከሃዲ አድርጎ መመልከት ተገቢ አይሆንም።
እንዲያውም በአንድ ሰው ላይ ከመጠን በላይ ጥብቅ ማለት ተገቢ አይደለም። (መዝሙር 146:3) በዕድሜ እኩዮችህ ከሆኑት ውጪ ለምሳሌ ከወላጆችህ፣ ከሽማግሌዎችና ኃላፊነት ከሚሰማቸው አሳቢ ከሆኑ ሰዎች ጋር ጓደኝነት መመሥረት ጥበብ ነው። አና “እናቴ የልብ ጓደኛዬ ናት። ስለ ፈለግሁትና ስለ ማንኛውም ነገር ላነጋግራት እችላለሁ” በማለት በፍቅር ስሜት ተናግራለች።
ዘላቂ ጓደኛ ማግኘት ይቻላል!
መጽሐፍ ቅዱስ በ1 ጴጥሮስ 3:8 ላይ “በመጨረሻው ሁላችሁ በአንድ ልብ ሁኑ፣ የሌላው መከራ ለእናንተ እንደሚሆን አድርጉ፣ እንደ ወንድሞች ተዋደዱ፣ ርኅሩኆችና ትሑታን ሁኑ” በማለት ይናገራል። አዎን፣ ደግነትን፣ ርህራሄን፣ ጽኑ የሥነ ምግባር አቋምንና ልባዊ አሳቢነትን ለሌሎች አሳይ፤ በዚህ መንገድ ጓደኞችን ማፍራት ትችላለህ! ለረዥም ጊዜ የሚዘልቅ ጓደኝነት ለመመሥረት ጥረትና ቆራጥነትን እንደሚጠይቅ ጥርጥር የለውም። ሆኖም ከሚያስገኘው ወሮታ አንፃር ሲታይ ቢደከምለት የሚያስቆጭ አይደለም።
መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ዳዊትና ስለ ዮናታን የሚሰጠው ሐሳብ ትኩረት የሚስብ ነው። ልዩ የሆነ ጓደኝነት መሥርተው ነበር። (1 ሳሙኤል 18:1) የቅንዓት ስሜትንና የግል ድክመቶችን ማሸነፍ ችለው ነበር። እንዲህ ሊያደርጉ የቻሉት ዳዊትም ሆነ ዮናታን ከይሖዋ አምላክ ጋር የመሠረቱትን ወዳጅነትና ለእሱ የነበራቸውን ታማኝነት ከምንም በላይ አስበልጠው ይመለከቱት ነበር። አንተም እንዲሁ ካደረግህ ፈሪሃ አምላክ ያላቸውን ጓደኞች ይዘህ ለመቆየት ብዙም አትቸገርም!
[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ብዙውን ጊዜ ጓደኝነት የሚፈርሰው አንድ ሰው ከአንድ በላይ ጓደኛ መያዝ ክህደት እንደሆነ የሚሰማው ከሆነ ነው