ዘላቂ ወዳጅነት መመሥረት ትችላለህ
ወዳጅነት ለመመሥረት እንቅፋት የሚሆኑ ነገሮች አሉ። እንዲያውም መጽሐፍ ቅዱስ በእነዚህ ‘የመጨረሻ ቀናት’ ፍቅር፣ ተፈጥሯዊ የመውደድ ስሜትና ታማኝነት እንደሚጠፉ ተንብዮአል። (2 ጢሞቴዎስ 3:1-5፤ ማቴዎስ 24:12) እነዚህ ሁኔታዎች ከዚህ በፊት ታይቶ የማይታወቅ የብቸኝነት ወረርሽኝ አስከትለዋል። አንዲት ሴት “በአካባቢዬ ያለው ሁኔታ በኖኅ መርከብ ሊመሰል ይችላል። ወደ መርከቡ የገቡት ጥንድ ጥንድ እየሆኑ እንደነበረ ሁሉ እናንተም ጥንድ ካልሆናችሁ የአካባቢው ሰው ሁሉ ያገልላችኋል” በማለት ተናግራለች። አንድ ሰው ብቸኛ ቢሆን ብቸኛ የሆነው ሙሉ በሙሉ በገዛ ራሱ ጥፋት ነው ሊባል አይቻልም። የሰዎች በተደጋጋሚ ጊዜያት መኖሪያ መቀየር፣ የቤተሰብ መፍረስ፣ ሞቅ ያለ ስሜት የማያሳዩ ሰዎች የሚኖሩባቸውና አደገኛ የሆኑ ከተማዎች እንዲሁም ትርፍ ጊዜ ማጣት በአንዳንድ የምድራችን ክፍሎች ዘላቂ ጓደኝነት እንዳይኖር ከሚፈታተኑ ነገሮች መካከል ናቸው።
በጊዜያችን አንድ በከተማ ውስጥ የሚኖር ሰው በአንድ ሳምንት የሚያገኛቸው ሰዎች ብዛት በ18ኛው መቶ ዘመን አንድ በመንደር ውስጥ የሚኖር ሰው በአንድ ዓመት ውስጥ ወይም ዕድሜ ልኩን ከሚያገኛቸው ሰዎች ይበልጣሉ! ቢሆንም በዛሬው ጊዜ ያለው ግንኙነት ብዙውን ጊዜ ላይ ላዩን ነው። ብዙ ሰዎች አብዛኛውን ጊዜያቸውን ከሰዎች ጋር ለማሳለፍና ራሳቸውን ለማስደሰት ይጥራሉ። ነገር ግን ከመጥፎ ሰዎች ጋር የሚደረግ ዋጋ የሌለው ፈንጠዝያ እሾህን ለማገዶነት የመጠቀም ያህል እንደሆነ ማወቅ አለብን። መክብብ 7:5, 6 እንዲህ ይላል፦ “ሰው የሰነፎችን ዜማ ከሚሰማ ይልቅ የጠቢባንን ተግሣጽ መስማት ይሻለዋል። ከድስት በታች እንደሚቃጠል እሾህ ድምፅ የሰነፍ ሳቅ እንዲሁ ነው።” እሾህ ለአንድ አፍታ ኃይለኛና የሚንጣጣ እሳት ቢኖረውም ለረጅም ጊዜ ሙቀት ሊሰጠን አይችልም። በጣም የሚያወኩና የሚስቁ ጓደኞችም ለጥቂት ጊዜ ትኩረታችንን ሊስቡት ይችላሉ፤ ሆኖም ያለብንን ብቸኝነት ሙሉ በሙሉ አያስወግዱልንም። በተጨማሪም እውነተኛ ጓደኞች ለማግኘት ያለንን ፍላጎት አያረኩልንም።
ራስን ከሰዎች ማግለል ከብቸኝነት ይለያል። አንዳንድ ጊዜ መንፈሳችንን ለማደስና በዚህ መንገድ ራሳችንን ይበልጥ ለሰዎች ጓደኛ አድርገን ለማቅረብ ብቻችንን መሆን ያስፈልገናል። ብዙ ሰዎች ብቸኝነት ሲሰማቸው ወዲያውኑ ወደ ኤሌክትሮኒክ መዝናኛዎች ዞር ይላሉ። ሰዎች ብቸኝነት ሲሰማቸው ከሚወስዷቸው በጣም ከተለመዱ እርምጃዎች አንዱ ቴሌቪዥን መመልከት እንደሆነ አንድ ጥናት አሳይቷል። ቢሆንም ለረጅም ጊዜ ቴሌቪዥን ማየት ብቸኝነት ሲሰማን ከምናደርጋቸው ነገሮች መካከል የከፋው እንደሆነ ተመራማሪዎች ደርሰውበታል። ችግሩን ከመፍታት ችላ እንድንል፣ እንድንሰለችና የቁም ቅዠት እንዲይዘን ከማድረጉም በተጨማሪ ከሰዎች ጋር በአካል የምናደርገውን ግንኙነት ያዳክምብናል።
ብቻችንን የምንሆንበትን ጊዜ ጠቃሚ በሆነ መንገድ ከተጠቀምንበት ከሰዎች ገለል ማለት በጣም ጠቃሚ ሊሆን ይችላል። በማንበብ፣ ደብዳቤ በመጻፍ፣ አንዳንድ ነገሮችን በመሥራትና እረፍት በመውሰድ እንዲህ ማድረግ እንችላለን። ከሌሎች ገለል ብለን ጊዜያችንን ጠቃሚ በሆነ ነገር ላይ ማሳለፍ ወደ አምላክ መጸለይን፣ መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናትንና ባጠናነው ላይ ማሰላሰልን ያካትታል። (መዝሙር 63:6 የ1980 ትርጉም) እነዚህ ከታላቁ ጓደኛችን ከይሖዋ አምላክ ጋር ይበልጥ የምንቀራረብባቸው መንገዶች ናቸው።
በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙ የወዳጅነት ምሳሌዎች
ምንም እንኳ ከብዙ ሰዎች ጋር መወዳጀት ጥሩ ቢሆንም መጽሐፍ ቅዱስ “ከወንድም አብልጦ የሚጠጋጋ ወዳጅ አለ” በማለት ያስታውሰናል። (ምሳሌ 18:24) ሁላችንም ስለ እኛ ከልብ የሚያስቡ፣ ጓደኝነታቸው ደስታ፣ ጥንካሬና ሰላም የሚሰጠን ጥቂት የቅርብ ጓደኞች ያስፈልጉናል። በዛሬው ጊዜ እንዲህ ያሉ እውነተኛ ጓደኞች ማግኘት ቢያስቸግርም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አንዳንድ የጥንት ምሳሌዎች ሰፍረዋል። ለምሳሌ ዳዊትና ዮናታን ጥሩ ጓደኛሞች ነበሩ። ከእነርሱ ምን ልንማር እንችላለን? ወዳጅነታቸው ዘላቂ የሆነው ለምንድን ነው?
ለምሳሌ ያህል ዳዊትና ዮናታን በጣም ጥሩ የሆኑ ተመሳሳይ ፍላጎቶች ነበሯቸው። ከሁሉ በላይ ደግሞ ሁለቱም ለይሖዋ አምላክ ጥልቅ የሆነ ፍቅር ነበራቸው። ዳዊት በአምላክ ላይ ያለውን እምነትና ለይሖዋ ሕዝቦች ሲል ያደረጋቸውን ነገሮች በመመልከት “የዮናታን ነፍስ በዳዊት ነፍስ ታሰረች፣ ዮናታንም እንደ ነፍሱ ወደደው።” (1 ሳሙኤል 18:1) ስለዚህ ለአምላክ ተመሳሳይ የሆነ ጥልቅ ፍቅር ማሳየት እርስ በርስ እንዲተሳሰሩ ይረዳል።
ዮናታንና ዳዊት አምላክ ያወጣቸውን መሠረታዊ ሥርዓቶች አክብረው የሚኖሩ ጠንካራ ሰዎች ነበሩ። በዚህ የተነሳ እርስ በርስ መከባበር ይችሉ ነበር። (1 ሳሙኤል 19:1-7፤ 20:9-14፤ 24:6) በቅዱስ ጽሑፋዊ መሠረታዊ ሥርዓቶች የሚመሩ አምላካዊ ጓደኞች ካሉን በእርግጥ ተባርከናል።
ለዳዊትና ለዮናታን ወዳጅነት አስተዋጽኦ ያደረጉ ሌሎች ነገሮችም ነበሩ። ወዳጅነታቸው በሐቀኝነትና በግልጽነት ላይ የተመሠረተ ሲሆን አንዱ በሌላው ላይ ይተማመን ነበር። ዮናታን በታማኝነት ከራሱ ጥቅም በፊት የዳዊትን ጥቅም ያስቀድም ነበር። ዮናታን ዳዊት እንደሚነግሥ ቃል ስለተገባለት ከመቅናት ይልቅ ስሜታዊና መንፈሳዊ ድጋፍ ሰጥቶታል። ዳዊትም ያደረገለትን ድጋፍ ተቀብሏል። (1 ሳሙኤል 23:16-18) ዳዊትና ዮናታን ቅዱስ ጽሑፋዊ ድጋፍ ባላቸው ተገቢ በሆኑ መንገዶች እርስ በርስ ያላቸውን ስሜት ይገላለጹ ነበር። አምላካዊ ወዳጅነታቸው በእውነተኛ አድናቆትና ፍቅር ላይ የተመሠረተ ነበር። (1 ሳሙኤል 20:41፤ 2 ሳሙኤል 1:26) ሁለቱም ለአምላክ ታማኝ ሆነው ስለቀጠሉ ወዳጅነታቸው ዘላቂ ነበር። እንደነዚህ ያሉ መሠረታዊ ሥርዓቶችን በተግባር ማዋል እውነተኛ ጓደኝነት ለመገንባትና ጠብቆ ለማቆየት ያስችለናል።
ወዳጅነት መመሥረት የሚቻልባቸው የተለያዩ አቅጣጫዎች
እውነተኛ ጓደኞች እየፈለግህ ነውን? ጓደኛ ለመፈለግ ራቅ ብለህ መሄድ ላያስፈልግህ ይችላል። ዘወትር ከምታገኛቸው ሰዎች መካከል አንዳንዶቹ ጓደኞችህ ሊሆኑ ይችላሉ። እነርሱም ጓደኝነትህን ይፈልጉ ይሆናል። በተለይ ከመሰል ክርስቲያኖች ጋር ባለን ግንኙነት “ተስፋፉ” የሚለውን የሐዋርያው ጳውሎስ ምክር በሥራ ላይ ማዋሉ ጥሩ ነው። (2 ቆሮንቶስ 6:11-13) ሆኖም ጓደኛ ለማግኘት ሙከራ አድርገህ አንድም የልብ ወዳጅ ባታገኝ ሐዘን አይግባህ። ወዳጅነት መመሥረት ጊዜ የሚጠይቅ ሲሆን የመሠረትነው ጓደኝነት ሁሉ አንድ ዓይነት ጥልቀት አይኖረውም። (መክብብ 11:1, 2, 6) ልባዊ የሆነ ጓደኛ ለማግኘት ከራስ ወዳድነት መራቅና “እንግዲህ ሰዎች ሊያደርጉላችሁ የምትወዱትን ሁሉ እናንተ ደግሞ እንዲሁ አድርጉላቸው” የሚለውን የኢየሱስ ምክር መከተል ያስፈልጋል።—ማቴዎስ 7:12
ከአንተ ጋር ወዳጅነት መመሥረት የሚፈልግ ማን ሊኖር ይችላል? እኩዮችህን ብቻ ሳይሆኑ ታናናሾችህን ወይም ታላላቆችህን ጓደኛ ብታደርግስ? ጓደኛሞች የነበሩት ዳዊትና ዮናታን፣ ሩትና ኑኃሚን እንዲሁም ጳውሎስና ጢሞቴዎስ በመካከላቸው የዕድሜ ልዩነት ነበር። (ሩት 1:16, 17፤ 1 ቆሮንቶስ 4:17) ወዳጅነትህን በማስፋት ከመበለቶችና ነጠላ ከሆኑ ሰዎች ጋር ጓደኝነት መፍጠር ትችላለህን? በቅርቡ ወደምትኖርበት አካባቢ ስለተዛወሩ ሰዎችም አስብ። እነዚህ ሰዎች መኖሪያቸውን በመለወጥ ወይም አኗኗራቸውን በመቀየር አብዛኞቹን ወይም ሁሉንም ጓደኞቻቸውን አጥተው ሊሆን ይችላል። ሌሎች እስኪፈልጉህ ድረስ አትጠብቅ። ክርስቲያን ከሆንክ “በወንድማማች መዋደድ እርስ በርሳችሁ ተዋደዱ፤ እርስ በርሳችሁ ተከባበሩ” የሚለውን የጳውሎስ ምክር በተግባር ላይ በማዋል ዘላቂ ጓደኝነት መሥርት።—ሮሜ 12:10
ወዳጅነት ማለት መስጠት እንደሆነ አድርገን ልናስብ እንችላለን። ኢየሱስ የምንሰጥ ከሆነ ሰዎች እንደሚሰጡን ተናግሯል። በተጨማሪም ይበልጥ ደስታ የሚያስገኘው መቀበል ሳይሆን መስጠት እንደሆነ ተናግሯል። (ሉቃስ 6:38፤ ሥራ 20:35) የተለያየ አስተዳደግ ካላቸው ሰዎች ጋር ትገናኛለህን? የተለያየ ባህል ያላቸው ሰዎች በአንድነት አምላክን በሚያመልኩበት ጊዜ እውነተኛና ዘላቂ ወዳጅነት ሊመሠርቱ እንደሚችሉ በይሖዋ ምሥክሮች ብሔራት አቀፍ ስብሰባዎች ላይ ታይቷል።
ወዳጅነታችንን ከአደጋ መጠበቅ
ጓደኛሞች ተደርገው ይታዩ የነበሩ ሰዎች እርስ በርስ ሲቆሳሰሉ መመልከት ያሳዝናል። እውነተኛ ጓደኛህ አድርገህ የምታስበው ሰው ጎጂ ሐሜት ከጀመረ፣ ምሥጢር የሚያወጣ ከሆነና አድናቆቱ እየጠፋ ከመጣ በጣም ያሳዝናል። እንደዚህ ያለ ሁኔታ ሲፈጠር ምን ማድረግ ይቻላል?
ጥሩ ምሳሌ ሁን። መቆሳሰልን ሊያስከትሉ የሚችሉ ነገሮችን ለማስወገድ የቻልከውን ሁሉ አድርግ። በአንዳንድ ቦታዎች ጓደኛሞች አንዱ በሌላኛው ስሕተት ማሾፋቸው የተለመደ ነው። ‘ለጨዋታ’ ቢሆንም እንኳ አንዱ በሌላው ላይ ሸር መሥራት ወይም ማታለል ጓደኛሞችን ያራርቃል።—ምሳሌ 26:18, 19
በወዳጅነታችሁ ለመቀጠል ጥረት አድርጉ። አንዱ ከሌላው ብዙ ሲጠብቅ አንዳንድ ጊዜ በመካከላቸው አለመግባባቶች ይፈጠራሉ። አንድ የታመመ ወይም በውስጡ የታመቀ ችግር ያለበት ጓደኛ እንደወትሮው ሞቅ ያለ ስሜት ላያሳይ ይችላል። እንደነዚህ ባሉ ጊዜያት የጓደኛህን ችግር ለመረዳትና እርዳታ ለመስጠት ሞክር።
ችግሮችን ደግነት በተሞላበት መንገድ በቶሎ እልባት አብጅላቸው። እንዲህ ስታደርግ የሚቻል ከሆነ ሌላ ሰው ጣልቃ አታስገባ። (ማቴዎስ 5:23, 24፤ 18:15) ጥሩ ግንኙነት እንዲኖራችሁ እንደምትፈልግ ለጓደኛህ አሳውቀው። ከልብ የሚዋደዱ ጓደኛሞች እርስ በርስ ይቅር ይባባላሉ። (ቆላስይስ 3:13) ከወንድም ይበልጥ የሚቀርብ ጓደኛ ትሆን ይሆን?
ስለ ወዳጅነት ማንበብና ማሰላሰል ወዳጅነት ለመመሥረት የመጀመሪያው ደረጃ ነው። ብቸኝነት ሲሰማን ተገቢ እርምጃ ከወሰድን ለረጅም ጊዜ ብቸኛ ሆነን አንቀርም። ጥረት ካደረግን እውነተኛ ጓደኞች ልናፈራ እንችላለን። ከእነዚህም መካከል ከአንዳንዶቹ ጋር ልዩ ትስስር እንፈጥራለን። ሆኖም ማንም ሰው ቢሆን ታላቁን ጓደኛችንን አምላክን ሊተካ አይችልም። ሙሉ በሙሉ ሊያውቀን፣ ያሉብንን ችግሮች ሊረዳና፣ ሊደግፈን የሚችለው ይሖዋ ብቻ ነው። (መዝሙር 139:1-4, 23, 24) በተጨማሪም ቃሉ ዘላቂ የሆኑ እውነተኛ ጓደኞች የምናገኝበት አዲስ ዓለም ይመጣል በማለት ስለወደፊቱ ጊዜ አስደናቂ ተስፋ ይሰጣል።—2 ጴጥሮስ 3:13
[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በዳዊትና በዮናታን መካከል የነበረውን ዓይነት እውነተኛ ወዳጅነት ልንመሠርት እንችላለን