ትክክለኛ ሚዛን መጠበቅ ለሕይወት ጣዕም ይጨምራል
መቻቻል ቡና ውስጥ እንደሚጨመር ስኳር ነው። መጠኑ ትክክል ከሆነ ለሕይወት ተጨማሪ ጣዕም ይሰጣል። ይሁን እንጂ በስኳር ረገድ ለጋሶች ስንሆን በመቻቻል ረገድ ብዙውን ጊዜ ንፉጎች ነን ማለት ነው። ለምን?
የሚቺጋን ስቴት ዩኒቨርሲቲ ተባባሪ ፕሮፌሰር የሆኑት አርተር ኤም መልዝር “የሰው ልጆች ቻይ መሆንን አይፈልጉም። በተፈጥሯቸው የሚቀናቸው . . . መሠረተ ቢስ ጥላቻን ማሳየት ነው” ሲሉ ጽፈዋል። ስለዚህ ቻይ አለመሆን በጥቂት ሰዎች ላይ ብቻ የሚታይ የባሕርይ ጉድለት አይደለም። ሰው ሁሉ ፍጽምና የጎደለው ስለሆነ ሁላችንም በአመለካከታችን ጠባብ መሆን ይቀናናል።—ከሮሜ 5:12 ጋር አወዳድር።
በሰው ጉዳይ ገቢዎች
ታይም መጽሔት በ1991 በዩናይትድ ስቴትስ ጠባብ አመለካከት እየተስፋፋ ስለመሄዱ ዘግቦ ነበር። ጽሑፉ የራሳቸውን የሥነ ምግባር ደንብ በሰው ሁሉ ላይ ለመጫን የሚሞክሩ ሰዎችን “በሰው ጉዳይ ገቢዎች” በማለት ገልጿቸዋል። የሌሎችን ባሕርይ ለመቀበል አሻፈረኝ ባሉ ሰዎች ላይ ብዙ ጥቃት ተሰንዝሯል። ለምሳሌ ያህል በቦስተን የምትኖር አንዲት ሴት ውበት ጨማሪ መኳኳያዎችን ለመቀባት አሻፈረኝ በማለቷ ከሥራ ተባርራለች። በሎስ አንጀለስ የሚኖር አንድ ሰው ወፍራም በመሆኑ ከሥራ ተባሯል። ሰዎች ከሌሎች ጋር ተመሳስለው እንዲኖሩ ይህን ያህል ግፊት የሚደረግባቸው ለምንድን ነው?
ጠባብ አመለካከት ያላቸው ሰዎች ምክንያተ ቢሶች፣ ራስ ወዳዶች፣ ግትሮችና እልከኞች ናቸው። ይሁን እንጂ ብዙ ሰዎች በተወሰነ ደረጃም ቢሆን ምክንያተ ቢሶች፣ ራስ ወዳዶች፣ ግትሮች ወይም እልከኞች አይደሉምን? እነዚህ ባሕርያት በውስጣችን ሥር ሰድደው የጠባያችን ዋነኛ ክፍል ከሆኑ ጠባብ አመለካከት ያለን እንሆናለን።
አንተስ? የሌላውን ሰው የምግብ ምርጫ ትጸየፋለህን? ከሰዎች ጋር በምትጨዋወትበት ጊዜ የአንተ ሐሳብ ብቻ ተቀባይነት እንዲያገኝ ትፈልጋለህ? ከሌሎች ሰዎች ጋር አብረህ በምትሠራበት ጊዜ ሁሉም ያንተን አስተሳሰብ እንዲከተሉ ትጠብቃለህ? እንዲህ ዓይነት ሰው ከሆንክ ቡናህ ውስጥ ጥቂት ስኳር ብትጨምር ጥሩ ይሆናል!
ይሁን እንጂ ባለፈው ርዕስ ውስጥ እንደተጠቀሰው አለመቻቻል በከረረ ጥላቻና በጠላትነት ስሜት ሊገለጽ ይችላል። ያለመቻቻል ባሕርይ እንዲባባስ ከሚያደርጉት ምክንያቶች አንዱ ከባድ የሆነ ሥጋት ነው።
“ከፍተኛ የሥጋት ስሜት”
የሰው ልጆችን ጎሣና ነገድ የሚያጠኑ ምሁራን የዘር ጥላቻ የጀመረው መቼና እንዴት እንደሆነ ለማወቅ ሲሉ ወደኋላ ተመልሰው የሰው ልጆችን ታሪክ መርምረዋል። ይህ ዓይነቱ ያለመቻቻል ባሕርይ ሁልጊዜ ይታይ እንዳልነበረና በሁሉም አገሮች በእኩል መጠን እንዳልታየ ተገንዝበዋል። ጋኦ የተባለው የጀርመን የተፈጥሮ ሳይንስ መጽሔት የጎሣ ግጭት የሚፈጠረው “አንድ ሕዝብ ጥልቅ የሆነ የሥጋት ስሜት ሲያድርበትና ማንነቱና ሕልውናው አደጋ ላይ ሊወድቅ እንደተቃረበ ሲሰማው ነው” ሲል ዘግቧል።
ታዲያ እንዲህ ያለው “ጥልቅ የሆነ የሥጋት ስሜት” በአሁኑ ጊዜ ተስፋፍቷል? አዎን፣ ተስፋፍቷል። የሰው ልጅ ከዚህ በፊት ታይቶ በማይታወቅ መጠን የተለያዩ ችግሮች ይፈራረቁበታል። ሥራ አጥነት፣ የኑሮ ውድነት፣ የሕዝብ ቁጥር መጨመር፣ የኦዞን ሽፋን መሳሳት፣ በከተሞች የሚፈጸም ወንጀል፣ የመጠጥ ውኃ ብክለት፣ የዓለም ሙቀት መጨመር ሰዎች በሥጋትና በጭንቀት እንዲዋጡ አድርጓቸዋል። ችግር ጭንቀት ይወልዳል። ተገቢ ያልሆነ ጭንቀት ደግሞ ላለመቻቻል በር ይከፍታል።
የተለያዩ ጎሣዎችና ነገዶች ተደባልቀው በሚኖሩባቸው በአንዳንድ የአውሮፓ አገሮች እንደታየው እንዲህ ያለው ያለመቻቻል ባሕርይ ገንፍሎ መውጣቱ አይቀርም። ናሽናል ጂኦግራፊክ በ1993 እንደዘገበው የምዕራብ አውሮፓ አገሮች ከ22 ሚልዮን የሚበልጡ የውጭ አገር ሰዎችን ተቀብለው ነበር። ብዙ አውሮፓውያን የተለየ ቋንቋ፣ ባሕል ወይም ሃይማኖት ባላቸው ሰዎች “መጥለቅለቃቸው በጣም አስደንግጧቸዋል።” በኦስትሪያ፣ በቤልጅየም፣ በብሪታንያ፣ በፈረንሳይ፣ በጀርመን፣ በኢጣልያ፣ በስፔይንና በስዊድን በባዕዳን ሰዎች ላይ የሚሰነዘረው ጥላቻ በጣም ጨምሯል።
የዓለም መሪዎችስ? ሂትለር በ1930ዎቹና በ1940ዎቹ ዓመታት አለመቻቻልን የመንግሥት መርሕ አድርጎ ነበር። ዛሬም አንዳንድ የፖለቲካና የሃይማኖት መሪዎች የራሳቸውን ዓላማ ለማሳካት አለመቻቻልን እንደ መሣሪያ አድርገው መጠቀማቸው በእጅጉ ያሳዝናል። እንደ ኦስትሪያ፣ ፈረንሳይ፣ አየርላንድ፣ ሩሲያ፣ ሩዋንዳና ዩናይትድ ስቴትስ ባሉ አገሮች የታየው ሁኔታ ይህ ነው።
በደንታ ቢስነት ወጥመድ እንዳትያዝ ተጠንቀቅ
በቡናችን ውስጥ የጨመርነው ስኳር ትንሽ ከሆነ ቡናችን አንድ ነገር እንደጎደለው ይሰማናል። ብዙ ስኳር ከጨመርን ደግሞ ከመጠን በላይ ይጣፍጥና የሚያቅለሸልሽ ጣዕም ይኖረዋል። መቻቻልም እንዲሁ ነው። በዩናይትድ ስቴትስ በሚገኝ አንድ ኮሌጅ የሚያስተምር አንድ ሰው ያጋጠመውን ተሞክሮ እንመልከት።
ዴቪድ አር ካርልን ጁንየር ከጥቂት ዓመታት በፊት ተማሪዎችን ለጥሩ ውይይት የሚያነሳሳ አንድ ቀላል ግን ውጤታማ ዘዴ ያገኛሉ። ተማሪዎቻቸው እንደሚቃወሙት የሚያውቁትን ሆኖም የተማሪዎቻቸውን አመለካከት ለማወቅ የሚያስችል አንድ ዓረፍተ ነገር ያዘጋጃሉ። በዚህ ምክንያት ሞቅ ያለ ውይይት ይደረጋል። ይሁን እንጂ ይኸው ዘዴያቸው በ1989 እንዳልሠራ ጽፈዋል። ለምን? ተማሪዎቹ ሰውየው ከተናገሩት ሐሳብ ጋር የማይስማሙ ቢሆኑም ለመከራከር ግን ግድ አልነበራቸውም። ካርልን እንዳብራሩት “ከተጠራጣሪነት የሚመጣ የምንቸገረኝነት ባሕርይ”፣ የራሱ ጉዳይ የማለት ዝንባሌ አዳብረዋል።
‘የራሱ ጉዳይ’ የማለት ዝንባሌ ቻይ ከመሆን ጋር አንድ ነውን? ማንም ሰው ሌላው ስለሚያስበው ወይም ስለሚያደርገው ነገር ግድ ካልኖረው ምንም ዓይነት የሥነ ምግባር ደንብ አይኖርም ማለት ነው። የሥነ ምግባር ደንብ አለመኖር ደግሞ ደንታ ቢስ ወይም ፈጽሞ ግድየለሽ መሆን ነው። እንዲህ ያለው ዝንባሌ ሊመጣ የሚችለው እንዴት ነው?
ፕሮፌሰር መልዘር እንደሚሉት ከሆነ ብዙና የተለያዩ መስፈርቶችን በሚቀበል ኅብረተሰብ ውስጥ የደንታ ቢስነት ዝንባሌ ይስፋፋል። ሰዎች ማንኛውም ዓይነት ጠባይና ምግባር ተቀባይነት እንዳለውና ማንኛውም ነገር በግል ምርጫ የሚወሰን ነገር ነው ብለው ማመን ይጀምራሉ። ሰዎች ተስማሚ የሆነው የቱ ነው፣ ተስማሚ ያልሆነውስ ብሎ ከማሰብና ከመጠየቅ ይልቅ “ጨርሶ አለማሰብን ይመርጣሉ።” የሌሎችን ቻይ አለመሆን ባሕርይ በቆራጥነት እንዲቃወሙ የሚያስችላቸው የሥነ ምግባር ጥንካሬ ይጎድላቸዋል።
አንተስ? የራሱ ጉዳይ የሚለው ዝንባሌ አንተንም ቀስ በቀስ እየነካህ እንዳለ ይሰማሃል? ጸያፍ ወይም የሌላውን ዘር የሚያንኳስሱ ቀልዶች ሲነገሩ ትስቃለህ? በአፍላ የጉርምስና ዕድሜ ላይ የሚገኝ ልጅህ ስግብግብነትን ወይም የብልግና ድርጊቶችን የሚደግፉ ቪዲዮዎች እንዲመለከት ትፈቅዳለህ? ልጆችህ አሰቃቂ የኃይል ድርጊቶች ካሉባቸው የኮምፒዩተር ጨዋታዎች ጋር ሲጋጠሙ ምንም አይደለም ብለህ ታልፋለህ?
ትክክል ወይም ስህተት ስለሆነ ነገር የሚያውቅ ወይም ለማወቅ የሚፈልግ ሰው ስለማይኖር ከመጠን በላይ ቻይ የሆነ ቤተሰብ ወይም ኅብረተሰብ መከራና ሐዘን ያጭዳል። የዩናይትድ ስቴትስ ምክር ቤት አባል የሆኑት ዳን ኮትስ “በቻይነት ስም ደንታ ቢስ በመሆን ስለሚመጣ ወጥመድ” አስጠንቅቀዋል። ቻይ መሆን ሰፋ ያለ አመለካከት ለመያዝ ሲረዳ ከመጠን በላይ ቻይ መሆን በሌላ አባባል ደንታቢስ መሆን ደግሞ ድንቁርናን ያስከትላል።
ታዲያ ችለን ማለፍ የሚኖርብንና መቃወም ያለብን የትኞቹን ነገሮች ነው? ትክክለኛውን ሚዛን ለመጠበቅ የሚያስችለው ቁልፍ ምንድን ነው? የሚቀጥለው ጽሑፍ በዚህ ርዕሰ ጉዳይ ላይ የሚያተኩር ይሆናል።
[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ለሁኔታዎች ያለህ አመለካከት ሚዛናዊ እንዲሆን ተጣጣር