የውሸት እውነተኛ ገጽታ
“አንተ ውሸታም!” እነዚህ የሚያሳምሙ ቃላት ተሰንዝረውብህ ያውቃሉ? እንዲህ ያለው ሁኔታ አጋጥሞህ ከሆነ ምን ያህል ስሜትን እንደሚደቁስ እንዳስተዋልክ ምንም ጥርጥር የለውም።
አንድ ደስ የሚል የአበባ ማስቀመጫ ወለል ላይ ከወደቀ እንደሚሰባበር ሁሉ ውሸትም ውድ የሆነን ወዳጅነት ሊያበላሽ ይችላል። እርግጥ ነው፣ ከጊዜ በኋላ ጉዳቱን ለመጠገን ትችል ይሆናል፤ ይሁን እንጂ ወዳጅነቱ በፍጹም እንደ ቀድሞው አይሆንም።
ላይንግ—ሞራል ቾይዝ ኢን ፐብሊክ ኤንድ ፕራይቬት ላይፍ የተባለው መጽሐፍ እንዲህ ብሏል:- “አንድ ሰው ዋሽቷቸው እንደነበር የተገነዘቡ ሰዎች የሚቀርብላቸውን አዲስ ሐሳብ የሚያዩት በጥርጣሬ ዓይን ነው። በተጨማሪም ሰዎች አንዴ ከተታለሉ በኋላ ቀደም ሲል ያመኑባቸውንም ሆነ ያደረጓቸውን ነገሮች እንደገና ማውጠንጠን ይጀምራሉ።” የማታለሉ ተግባር ሲጋለጥ በአንድ ወቅት ግልጽ በሆነ የሐሳብ ግንኙነትና በመተማመን መንፈስ የበለጸገው ወዳጅነት በእምነት ማጣትና በጥርጣሬ ይኮሰምናል።
የውሸትን አፍራሽ ጎኖች ሁሉ ከተመለከትን በኋላ ‘ይህን የመሰለው ብልሹ ልማድ የጀመረው እንዴት ነው?’ ብለን መጠየቃችን የተገባ ነው።
የመጀመሪያው ውሸት
ይሖዋ አምላክ የመጀመሪያዎቹን ሰዎች ማለትም አዳምንና ሔዋንን ከፈጠረ በኋላ ውብ በሆነ የአትክልት ስፍራ ውስጥ አስቀመጣቸው። ቤታቸው ከማንኛውም ዓይነት የማታለልም ሆነ የማጭበርበር ተግባር የጸዳ ነበረ። በእውነትም ገነት ነበረ!
ይሁን እንጂ ሔዋን ከተፈጠረች ከጥቂት ጊዜ በኋላ ሰይጣን ዲያብሎስ አንድ የሚያጓጓ ግብዣ አቀረበላት። ሔዋን አምላክ እንዳይበሉ ካዘዛቸው “ከዛፉ ፍሬ” ብትበላ አምላክ እንዳለው እንደማትሞት ነገራት። ከዚህ ይልቅ እንደ ‘እግዚአብሔር መልካምንና ክፉን የምታውቅ ትሆናለች።’ (ዘፍጥረት 2:17፤ 3:1-5) ሔዋን ሰይጣንን አመነች። ፍሬውን ወስዳ በላች፤ ከዚያም ለባሏ ሰጠችው። ነገር ግን አዳምና ሔዋን ሰይጣን እንዳላቸው እንደ አምላክ ከመሆን ይልቅ ዓመፀኛ፣ ኃጢአተኞችና የጥፋት ባሪያዎች ሆኑ። (2 ጴጥሮስ 2:19) እንዲሁም የመጀመሪያውን ውሸት በመናገር ሰይጣን “የውሸቶች ሁሉ አባት” ሆነ። (ዮሐንስ 8:44 Today ’s English Version) ከጊዜ በኋላ እነዚህ ሦስት ኃጢአተኞች አንድ ሰው በሚዋሽበት ወይም ትምክህቱን በውሸት ላይ በሚጥልበት ጊዜ ሊሳካለት እንደማይችል ተምረዋል።
ለሞት የሚዳርጉ ውጤቶች
ይሖዋ ሥራዬ ብለው ሳይታዘዙ የሚቀሩ ሰዎችን ሳይቀጣ እንደማያልፍ በሰማይም ሆነ በምድር የሚገኙ ፍጡሮቹ እንዲያውቁ ፈለገ። ይሖዋ አፋጣኝ እርምጃ በመውሰድ ዓመፀኛውን መንፈሳዊ ፍጡር የተቀረውን የሕይወት ዘመኑን ከአምላክ ቅዱስ ድርጅት ውጪ እንዲያሳልፍ ፈረደበት። ከዚህም በላይ ይሖዋ አምላክ በመጨረሻ ሰይጣንን ጨርሶ ያጠፋዋል። ይህም የሚሆነው አምላክ ተስፋ የሰጠበት “ዘር” ሰይጣንን ጭንቅላቱን በመጨፍለቅ ከህልውና ውጭ በሚያደርገው ጊዜ ነው።—ዘፍጥረት 3:14, 15፤ ገላትያ 3:16
አዳምና ሔዋን ደግሞ ከኤደን የአትክልት ስፍራ ተባረሩ። አምላክ በአዳም ላይ እንደሚከተለው ሲል ፈረደበት:- “ወደ ወጣህበት መሬት እስክትመለስ ድረስ በፊትህ ወዝ እንጀራን ትበላለህ፤ አፈር ነህና፣ ወደ አፈርም ትመለሳለህና።” ከጊዜ በኋላ አምላክ በተናገረው መሠረት አዳምና ሔዋን ሞቱ።—ዘፍጥረት 3:19
ጠቅላላው ሰብዓዊ ቤተሰብ የአዳም ዝርያ ስለሆነ ‘ለኃጢአት ተሽጧል።’ ሁሉም የሰው ልጆች ወደ ሞት የሚመራቸውን አለፍጽምና ወርሰዋል። (ሮሜ 5:12፤ 6:23፤ 7:14) የመጀመሪያው ውሸት ያስከተላቸው መዘዞች እንዴት አሳዛኝ ነበሩ!—ሮሜ 8:22
ሥር የሰደደ ልማድ
ሰይጣን እንዲሁም አምላክን በመቃወም በዓመፁ የተባበሩት መላእክት ጨርሶ ስላልተደመሰሱ ሰዎችን ‘ውሸት እንዲናገሩ’ የሚያነሳሱ መሆናቸው ሊያስደንቀን አይገባም። (1 ጢሞቴዎስ 4:1-3) በዚህም ምክንያት ውሸት በሰው ልጅ ኅብረተሰብ ውስጥ ሥር ሰዷል። ሎስ አንጀለስ ታይምስ “ውሸት ባህል ከመሆኑ የተነሣ ከኅብረተሰቡ ጋር ተዋኅዷል” ብሏል። ዛሬ ብዙዎች ፖለቲካንና ፖለቲከኞችን ከውሸት ጋር ያያይዛሉ፤ ይሁን እንጂ ከቀንደኛ ውሸታሞች መካከል ሃይማኖታዊ መሪዎችም እንደሚገኙበት ታውቅ ኗሯል?
ሃይማኖታዊ ተቃዋሚዎች በኢየሱስ ምድራዊ አገልግሎት ወቅት በእሱ ላይ የውሸት ወሬ ይነዙ ነበር። (ዮሐንስ 8:48, 54, 55) ኢየሱስ እንደሚከተለው በማለት በግልጥ አውግዟቸዋል:- “እናንተ ከአባታችሁ ከዲያብሎስ ናችሁ የአባታችሁንም ምኞት ልታደርጉ ትወዳላችሁ። . . . ሐሰት ሲናገር ከራሱ ይናገራል፣ ሐሰተኛ የሐሰትም አባት ነውና።”—ዮሐንስ 8:44
ኢየሱስ ከሙታን ከተነሣ በኋላ መቃብሩ ባዶ ሆኖ በመገኘቱ የተነዛውን የውሸት ወሬ ታስታውሳለህ? መጽሐፍ ቅዱስ የካህናት አለቆች “ለጭፍሮች ብዙ ገንዘብ ሰጥተዋቸው:- እኛ ተኝተን ሳለን ደቀ መዛሙርቱ በሌሊት መጥተው ሰረቁት በሉ” እንዳሏቸው ይናገራል። ይህ ውሸት በሰፊው ስለተነዛ ብዙዎች ተታለውበታል። እነዚያ የሃይማኖት መሪዎች ምን ያህል ክፉዎች ነበሩ!—ማቴዎስ 28:11-15
በጊዜያችን ያሉ ሃይማኖታዊ ውሸቶች
ዛሬ በሃይማኖታዊ መሪዎች የሚነዛው ታዋቂው ውሸት ምንድን ነው? ሰይጣን ለሔዋን “ሞትን አትሞቱም” ሲል ከነገራት ውሸት ጋር የሚመሳሰል ነው። (ዘፍጥረት 3:4 በሰያፍ የጻፍነው እኛ ነን።) ነገር ግን ሔዋን ሞተች፤ እንዲሁም ወደ ወጣችበት ምድር ማለትም ወደ ተሠራችበት አፈር ተመለሰች።
ይሁን እንጂ ሔዋን የሞተች ቢመስልም በሌላ ቦታ የተለየ አካል ይዛ እየኖረች ይሆን? ሞት ወደ ሌላ ሕይወት የሚመራ በር ነውን? መጽሐፍ ቅዱስ ከሔዋን ውስጥ አንድ ክፍል ሕያው ሆኖ መቀጠሉን በተመለከተ ምንም ፍንጭ አይሰጥም። ነፍሷ በሕይወት አልቀጠለችም። አምላክን ባለመታዘዟ ኃጢአት ሠርታለች። መጽሐፍ ቅዱስ ደግሞ “ኃጢአት የምትሠራ ነፍስ እርስዋ ትሞታለች” ይላል። (ሕዝቅኤል 18:4) ሔዋን የተፈጠረችው ልክ እንደ ባሏ ሕያው ነፍስ ሆና ነበር። አሁን ግን ሕያው ነፍስ ሆና መኖሯ አከተመ። (ዘፍጥረት 2:7 የ1879 ትርጉም) መጽሐፍ ቅዱስ ሙታን የሚገኙበትን ሁኔታ አስመልክቶ ሲናገር “ሙታን ግን አንዳች አያውቁም” ይላል። (መክብብ 9:5) ይሁን እንጂ አብያተ ክርስቲያናት በተለምዶ የሚያስተምሩት ምንድን ነው?
ብዙውን ጊዜ አብያተ ክርስቲያናት ሰው የማትሞት ነፍስ እንዳለችውና በሞት ጊዜ በተድላ ወይም በሥቃይ ለመኖር ከሰውየው የምትወጣ መሆኑን ያስተምራሉ። ለምሳሌ ያህል ዘ ካቶሊክ ኢንሳይክሎፔድያ “የሲኦል ሥቃይ ዘላለማዊነት አንድ ሰው የለየለት መናፍቅ ካልሆነ በቀር ሊክደውም ሆነ ሊጠራጠረው የማይችል የሃይማኖት እውነት ነው ብላ ቤተ ክርስቲያን አፏን ሞልታ ታስተምራለች” ብሏል።—ጥራዝ 7 ገጽ 209 የ1913 እትም።
ይህ ትምህርት መጽሐፍ ቅዱስ በግልጽ ከሚናገረው ነገር ጋር እንዴት የተለየ ነው! መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚያስተምረው አንድ ሰው በሚሞትበት ጊዜ “ወደ መሬቱም ይመለሳል፤ ያን ጊዜ ምክሩ ሁሉ ይጠፋል።” (መዝሙር 146:4) ስለዚህ እንደ መጽሐፍ ቅዱስ አባባል ሙታን ምንም ዓይነት ስሜት ስለሌላቸው ሥቃይ የሚባል ነገር ሊሰማቸው አይችልም። በዚህ ምክንያት መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ሲል አጥብቆ ይመክራል:- “አንተ በምትሄድበት በሲኦል [በሰው ልጆች ተራ መቃብር] ሥራና አሳብ እውቀትና ጥበብ አይገኙምና እጅህ ለማድረግ የምታገኘውን ሁሉ እንደ ኃይልህ አድርግ።”—መክብብ 9:10
መጠንቀቅ ይገባል
በኢየሱስ ዘመን በካህናቱ ውሸት ብዙዎች እንደተታለሉ ሁሉ ዛሬ ባሉትም ሃይማኖታዊ መሪዎች የመታለል አደጋ አለ። እነዚህ ሰዎች “የእግዚአብሔርን እውነት በውሸት” በመለወጥ የሰው ነፍስ አትሞትም እንዲሁም የሰዎች ነፍሳት በሲኦል እሳት ይሠቃያሉ እንደሚሉት ያሉትን የሐሰት ትምህርቶች ያስፋፋሉ።—ሮሜ 1:25
ከዚህ በተጨማሪ በጊዜያችን የሚገኙ ሃይማኖቶች የሰዎችን ወጎችና ፍልስፍናዎች ከመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ጋር በእኩል ደረጃ ያስቀምጧቸዋል። (ቆላስይስ 2:8) በመሆኑም አምላክ ሐቀኝነትንና ፆታን ጨምሮ ስለ ሥነ ምግባር ያወጣቸውን ሕግጋት የሚመለከቷቸው ፍጹም እንደሆኑ ሳይሆን አንጻራዊ እውነት እንደሆኑ አድርገው ነው። ታይም የተባለው መጽሔት የዚህን ውጤት ሲገልጽ እንዲህ ብሏል:- “ሰዎች አንዳቸው ለሌላው ማሳየት የሚገባቸው ባሕርይ ምን እንደሆነ ሳይገባቸው ወይም ሳይስማሙ ሲቀሩ በዚህ መተማመን በጠፋበት ኅብረተሰብ ውስጥ ውሸት ይስፋፋል።”—ከኢሳይያስ 59:14, 15ና ከኤርምያስ 9:5 ጋር አወዳድር።
ለእውነት ደንታ በሌለው ዓለም ውስጥ መኖራችን ውሸት አትናገሩ የሚለውን የአምላክን ምክር መከተል አስቸጋሪ ያደርገዋል። ታዲያ ሁልጊዜ እውነተኞች ሆነን እንድንኖር ምን ሊረዳን ይችላል?
ለእውነት መቆም
ፈጣሪያችንን ከፍ ከፍ ለማድረግ ያለን ፍላጎት እውነተኛ አነጋገር እንድናዳብር የሚያነሣሣ እጅግ በጣም ጥሩ ነገር ነው። መጽሐፍ ቅዱስ “የእውነት አምላክ” በማለት ጎላ አድርጎ ይገልጸዋል። (መዝሙር 31:5) ስለዚህ “ሐሰተኛ ምላስ” የሚጠላውን ፈጣሪያችንን ለማስደሰት ከፈለግን እርሱን ለመምሰል እንገፋፋለን። (ምሳሌ 6:17) ይህን ልናደርግ የምንችለው እንዴት ነው?
የአምላክን ቃል በጥልቅ ማጥናታችን ‘ከባልንጀሮቻችን ጋር እውነትን ለመነጋገር ያስችለናል።’ (ኤፌሶን 4:25) ይሁን እንጂ አምላክ ከእኛ የሚፈልገውን ማወቅ ብቻ በቂ አይሆንም። ዛሬ በዓለም ውስጥ እንደሚገኙ ብዙ ሰዎች ሁልጊዜ እውነትን መናገር የማይቀናን ከሆነ ልዩ ጥረት ልናደርግ ይገባል። የሐዋርያው ጳውሎስን ምሳሌ በመከተል ራሳችንን መገሰጽ ይኖርብናል። ጳውሎስ “ሥጋዬን እየጎሰምሁ አስገዛዋለሁ” ሲል ጽፏል።—1 ቆሮንቶስ 9:27
እውነትን ሁልጊዜ ለመናገር በምናደርገው ትግል ተጨማሪ እርዳታ ሊሰጠን የሚችለው ጸሎት ነው። ይሖዋ እንዲረዳን በመለመን ‘ከተለመደው በላይ የሆነ ኃይል’ ሊኖረን ይችላል። (2 ቆሮንቶስ 4:7) እርግጥ ነው ‘የውሸትን ምላስ’ በማስወገድ ‘የእውነትን ከንፈር’ ይዞ ለመኖር ከፍተኛ ትግል ይጠይቃል። (ምሳሌ 12:19) ይሁን እንጂ ከይሖዋ እርዳታ ጋር ይህን ለማድረግ እንችላለን።—ፊልጵስዩስ 4:13
መዋሸትን ትክክለኛ ነገር አድርጎ የሚያቀርበው ሰይጣን ዲያብሎስ መሆኑን ምንጊዜም አትርሳ። የመጀመሪያዋን ሴት ሔዋንን በተንኮል ዋሽቶ አታሏታል። ይሁን እንጂ የሰይጣን የውሸት መንገዶች የሚያስከትሏቸውን መዘዞች በደንብ እናውቃቸዋለን። በአንድ በራስ ወዳድነት በተነገረ ውሸትና ራስ ወዳድ በሆኑ ሦስት ውሸታም ግለሰቦች ማለትም በአዳም፣ በሔዋንና በሰይጣን ምክንያት በሰው ልጅ ቤተሰብ ላይ ይህ ነው የማይባል የመከራ መዓት ወርዷል።
አዎን፣ የውሸት እውነተኛ ገጽታ ገዳይ ከሆነ መርዝ ጋር ይወዳደራል። ደስ የሚለው ግን አንድ ነገር ማድረግ እንችላለን። የመዋሸትን ልማድ ልናቆምና ‘በፍቅራዊ ደግነትና በእውነት የተሞላውን’ አምላክ የይሖዋን ሞገስ በማግኘት ለዘላለም ልንደሰት እንችላለን።—ዘጸአት 34:6
[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ውሸት የሚያስከትለው መዘዝ ከተሰባበረ የአበባ ማስቀመጫ ጋር ይመሳሰላል
[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ውሸት ገዳይ ከሆነ መርዝ ጋር ሊወዳደር ይችላል