የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w92 12/15 ገጽ 21-23
  • መዋሸት በጣም ቀላል የሆነው ለምንድን ነው?

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • መዋሸት በጣም ቀላል የሆነው ለምንድን ነው?
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1992
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • ሰዎች የሚዋሹባቸው ምክንያቶች
  • ውጤቶቹን እንመልከት
  • መዋሸት ቀላል የሆነበት ምክንያት
  • እውነተኛ መሆን ያለብን ለምንድን ነው?
  • መዋሸት—ስህተት የማይሆንበት ሁኔታ ሊኖር ይችላልን?
    ንቁ!—2000
  • የውሸት እውነተኛ ገጽታ
    ንቁ!—1998
  • እውነትን ተናገሩ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2018
  • እውነት ጊዜ ያለፈበት ነገር ሆኗል?
    ተጨማሪ ርዕሰ ጉዳዮች
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1992
w92 12/15 ገጽ 21-23

መዋሸት በጣም ቀላል የሆነው ለምንድን ነው?

ማንም ሰው ቢሆን ሌላ ሰው እንዲዋሸው አይፈልግም። ሆኖም በዓለም በሙሉ ያሉ ሰዎች በተለያዩ ምክንያቶች አንዱ ሌላውን ይዋሻል። በጄምስ ፓተርሰንና በፒተር ኪም የተጻፈው አሜሪካ እውነትን የተናገረችበት ቀን በተባለው መጽሐፍ ላይ የወጣው ጥናት 91 በመቶ የሚሆኑት አሜሪካውያን አዘውትረው እንደሚዋሹ ያስረዳል። ደራሲዎቹ “ብዙዎቻችን ሳንዋሽ ሳምንቱን ማሳለፍ በጣም ይከብደናል። ከአምስት ሰዎች አንዱ ሳይዋሽ አንድም ቀን እንኳ ማለፍ አይችልም። ሆን ተብሎ የሚደረግና ቀደም ብሎ የተውጠነጠነ ውሸት ማለታችን ነው” ብለዋል።

ውሸት በአብዛኛው ዘመናዊ የኑሮ ዘርፍ የተለመደ ነገር ሆኖአል። የፖለቲካ መሪዎች ለሕዝቦቻቸውና እርስ በርሳቸው ውሸት ይናገራሉ። በተደጋጋሚ በቴሌቪዥን ቀርበው ሲናገሩም በጥልቅ ተካፋይ ከሆኑባቸው አሳፋሪ ዱለታዎች ጋር ምንም ግንኙነት እንደሌላቸው ይክዳሉ። ሲሰላ ቦክ መዋሸት—በግለሰብና በሕዝብ ፊት ያለ የሥነ ምግባር ምርጫ በተባለው መጽሐፋቸው ላይ እንዳመለከቱት “ውሸትን በተመለከተ ሕግ የማውጣት ዝንባሌ ያላቸው ውሸት ተናጋሪዎች ለውሸቱ ማሳበቢያ የሚሆን በቂ ምክንያት እንዳለ ከተሰማቸው በሕግና በጋዜጠኝነት ተቋማት፣ በመንግሥትና በማኅበራዊ ኑሮ ሳይንስ ዘንድ ማታለል እንደ ተራ ነገር ተደርጎ ይወሰዳል።”

ኮመን ኮዝ የተባለ መጽሔት በግንቦት/ሰኔ 1989 እትሙ ላይ በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ያለውን የፖለቲካ ማጭበርበር አስመልክቶ እንደሚከተለው ብሏል፦ “አሜሪካ በምሥጢር ለኢራን የሸጠችው የጦር መሣሪያ እንዲሁም ከመሣሪያውም ሽያጭ የሚገኘው ትርፍ “ኮንትራ” ተብሎ ለሚጠራው ለኒካራጓ የተቃዋሚዎች ቡድን እንዲውል የተደረገው አሳፋሪ ተግባር ከዎተርጌት ቅሌትና ከቪየትናም ጦርነት ባላነሰ መንገድ ሕዝቡ መንግሥትን እንዲጠራጠር አድርጎታል። የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዚደንት የነበሩት ሬገን አሜሪካን ያስተዳደሩባቸው ዓመታት ይህን ያህል አቅጣጫ የሚያስለውጡ የሆኑት ለምንድን ነው? ብዙዎች ይዋሹ ነበር፤ በሠሩት ሥራ የተጸጸቱት ግን ጥቂቶች ናቸው።” ተራው ሕዝብ የፖለቲካ መሪዎቹን አለማመኑ በጥሩ ምክንያት ነው።

በብሔራት መካከል ባለው ግንኙነትም እንኳን መሪዎች እርስ በርሳቸው ለመተማመን በጣም ያዳግታቸዋል። ግሪካዊው ፈላስፋ ፕላቶ የተገነዘበውን ሲገልጽ “የአገር መሪዎች . . . ለአገራቸው ሲሉ እንዲዋሹ ሊፈቀድላቸው ይችላል” ብሏል። “በአንድ ገበታም ተቀምጠው ሐሰት ይናገራሉ” በማለት መጽሐፍ ቅዱስ በዳንኤል 11:27 ላይ የተናገረው ትንቢት በዓለም አቀፋዊ ግንኙነቶች ላይ ተፈጽሟል።

በንግዱ ዓለም ስለ ምርት ውጤቶችና ስለ አገልግሎቶች መዋሸት የተለመደ ተግባር ሆኖአል። ዕቃ ገዥዎች ኮንትራት ሲፈርሙ ጥንቃቄ ያደርጋሉ። በደቃቅ ፊደላት የሚጻፉ የንግድ ምልክቶችን በጥንቃቄ ያነባሉ። አንዳንድ አገሮች ሕዝቡን ከሐሰት ማስታወቂያ፣ ጥቅም ያላቸውና ጉዳት የማያደርሱ ከሚመስሉ ጎጂ ሸቀጦችና ሕዝቡን ከመጭበርበር ለማዳን የሚቆጣጠሩ መሥሪያ ቤቶች አሏቸው። እነዚህ ጥረቶች ሁሉ እየተደረጉ ሰዎች አጭበርባሪ ነጋዴዎች ከሚያደርሱት ኪሣራ አልዳኑም።

ለአንዳንድ ሰዎች መዋሸት በጣም ቀላል ከመሆኑ የተነሣ ልማድ ይሆንባቸዋል። ሌሎች ደግሞ በአጠቃላይ ሲታዩ እውነት ይናገራሉ፤ ሆኖም አስቸጋሪ ሁኔታ ሲያጋጥማቸው ይዋሻሉ። በማናቸውም ሁኔታ ቢሆን ላለመዋሸት የጸና አቋም የሚወስዱት ግን ጥቂቶች ናቸው።

ውሸት “1. ሆን ተብሎ ለማጭበርበር የታቀደ አነጋገር ወይም ድርጊት . . . 2. የውሸት ግምት ለማሳደር የታቀደ ማንኛውም ነገር” ነው የሚል ፍቺ ተሰጥቶታል። ዓላማው የሚዋሸው ሰው ከሚናገረው ነገር እውነት እንዳልሆነ እያወቀ ሌሎች ሰዎች ሐሰት የሆነውን ነገር እንዲያምኑት ማድረግ ነው። በሐሰት ወይም ግማሽ እውነት ብቻ በመናገር እውነቱን ማወቅ የሚገባቸውን ሰዎች ለማታለል ጥረት ያደርጋል።

ሰዎች የሚዋሹባቸው ምክንያቶች

ሰዎች በተለያዩ ምክንያቶች የተነሳ ይዋሻሉ። አንዳንዶች በዚህ በውድድር በተሞላው ዓለም ውስጥ ዕድገት ለማግኘት ስለ ችሎታዎቻቸው ለመዋሸት እንደሚገደዱ ያስባሉ። ሌሎች ደግሞ ስህተታቸውን ወይም ጥፋታቸውን በውሸት ለመሸፈን ይሞክራሉ። ሌሎች ደግሞ ሰዎችን ለማስደነቅ ሲሉ ያልሠሩትን ሠርተናል ብለው በውሸት ያወራሉ። የሌሎችን ሰዎች ጥሩ ስም ለማጉደፍ፣ ከውርደት ለመዳን፣ አስቀድመው የተናገሩት ውሸት እውነት እንደሆነ ለማስመሰል ወይም አጭበርብረው የሰዎችን ገንዘብ ለመውሰድ ሲሉ የሚዋሹም አሉ።

ለውሸት የሚሰጠው በጣም የተለመደው ሰበብ ሌላውን ከጉዳት ለመጠበቅ አደረግሁት የሚል ነው። አንዳንዶች ይህን የመሰለው ውሸት ሰዎችን እንደማይጎዳ ስለሚያስቡ ነጭ ውሸት ብለው ይጠሩታል። ይሁን እንጂ ነጭ ውሸት ተብለው የሚጠሩት ውሸቶች ምንም ዓይነት ጉዳት የላቸውምን?

ውጤቶቹን እንመልከት

ነጭ ውሸት ከባድ የሆኑ ስህተቶችን ለመፈጸም ለሚጋብዙ ልማደኛ ውሸታምነት መንገድ ሊጠርግ ይችላል። ሲሰላ ቦክ ሐሳባቸውን ሲገልጹ “‘ነጭ’ ተብለው የሚገለጹት ውሸቶች ሁሉ በቀላሉ ሊታለፉ የሚችሉ አይደሉም። በመጀመሪያ ደረጃ ውሸት ጉዳት የለውም የሚለው አባባል የሚያከራክር መሆኑ የታወቀ ነው። ውሸታሙ ሰው የማይጎዱ እንዲያውም የሚጠቅሙ ናቸው ብሎ የሚያስባቸው ውሸቶች በተታለለው ሰው ፊት እንደዚያ ተደርገው አይታዩም” ብለዋል።

ውሸቶች ምንም ያህል በቅን ልቦና የተነገሩ መስለው ቢታዩም የሰዎችን መልካም ግንኙነት ያበላሻሉ። የዋሸው ሰው ከዚያ በኋላ አይታመንም፤ ምናልባትም ለሁልጊዜው የሰዎችን አመኔታ ሊያጣ ይችላል። የታወቁት ደራሲ ራልፍ ዋልዶ ኢመርሰን “እውነትን ባለማክበር ውሸት የሚናገር ሰው ራሱን መግደሉ ብቻ ሳይሆን የኅብረተሰቡንም ጤንነት በጩቤ እንደወጋ ያህል ነው” ብለዋል።

ስለ ሌላ ሰው ውሸት የሆነ ነገር መናገር ለውሸታሙ ሰው ቀላል ነው። ምንም እንኳን ለሚናገረው ነገር ማስረጃ ባያቀርብም የተነገረው ውሸት ስለ ሌላው ሰው ጥርጣሬን ይፈጥራል፤ ብዙ ሰዎችም የሚናገረውን ነገር ሳይመረምሩ ያምኑታል። በዚህም ምክንያት የንጹሑ ሰው መልካም ስም ይጎድፍና ከነገሩ ንጹሕ መሆኑን የማሳመኑን ሸክም የሚሸከመው ራሱ ይሆናል። ስለዚህ ሰዎች ንጹሑን ሰው ሳይሆን ውሸት ተናጋሪውን ሲያምኑት ይበሳጫል፤ ከውሸተኛው ጋር የነበረውንም ግንኙነት ያሻክርበታል።

ውሸታም ሰው በቀላሉ ውሸት የመናገር ልማድ ሊፈጠርበት ይችላል። ብዙ ጊዜ አንድ ውሸት ወደ ሌላ ውሸት ይመራል። ከመጀመሪያዎቹ የአሜሪካ መሪዎች አንዱ የሆኑት ቶማስ ጀፈርሰን “እንደ ውሸት በጣም መጥፎ፣ ወራዳና ሊናቅ የሚገባው አመል የለም። አንድ ጊዜ መዋሸት የጀመረ ሰው ለሁለተኛና ለሦስተኛ ጊዜ መዋሸቱን ቀላል ሆኖ ያገኘዋል። ቆይቶም ልማድ ይሆንበታል” ብለዋል። ውሸት ወደ ሥነ ምግባር ውድቀት የሚመራ መንገድ ነው።

መዋሸት ቀላል የሆነበት ምክንያት

አንድ ዓመፀኛ መልአክ ለመጀመሪያዋ ሴት ፈጣሪዋን ባትታዘዝ እንደማትሞት በነገራት ጊዜ ውሸት ተጀመረ። በዚህም ምክንያት አለፍጽምና፣ በሽታና ሞትን በማምጣት በሁሉም የሰው ዘሮች ላይ ቁጥር ስፍር የሌለው ጉዳት አስከተለ።—ዘፍጥረት 3:1-4፤ ሮሜ 5:12

አዳምና ሔዋን ታዛዥነታቸውን ከተዉበት ጊዜ ጀምሮ ያ የውሸት አባት በስውር የሚያደርገው ተንኮል በሰው ልጆች ዓለም ውስጥ ውሸት ለመናገር የሚገፋፋ ሁኔታ ፈጥሯል። (ዮሐንስ 8:44) ዓለም እውነት በአንፃራዊ ሁኔታ ብቻ የሚነገርባት የተበላሸች ቦታ ሆናለች። በ1986 የወጣው ዘ ሳተርዴይ ኢቭኒንግ ፖስት እንደጠቀሰው የውሸት ጉዳይ “የንግድ ሥራን፣ መንግሥታትን፣ የትምህርት መስጫ ተቋማትን፣ የመዝናኛ መድረክንና በዜጎች መካከልና በጎረቤታሞች መካከል የሚደረገውን የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ ነክቷል። . . . ፍጹም እውነት የሆኑ ነገሮች የሉም የሚለውን አንድ ትልቅ ውሸት ይኸውም አንፃራዊነት የሚባል ቲዮሪ ተቀብለናል” ብሏል።

ለሚዋሹት ሰው ምንም ዓይነት የርኅራኄ ስሜት የማያሳድሩት ልማደኛ ውሸታሞች ያላቸው አመለካከት ይኸው ነው። መዋሸት ለእነርሱ በጣም ቀላል ነው። ውሸት የሕይወታቸው መንገድ ሆኗል። ሆኖም ልማደኛ ውሸታም ያልሆኑት ሌሎች ሰዎችም መጋለጥን፣ ቅጣትንና የመሳሰሉትን በመፍራት ውሸት ለመናገር ወደኋላ አይሉም። ይህም ፍጽምና የጎደለው ሥጋ ካሉት ድክመቶች አንዱ ነው። ይህ ዝንባሌ እውነትን ለመናገር በሚደረግ ቁርጥ ውሳኔ እንዴት ሊተካ ይችላል?

እውነተኛ መሆን ያለብን ለምንድን ነው?

እውነት ታላቁ ፈጣሪያችን ለሁላችንም ያስቀመጠው የአቋም ደረጃ ነው። በጽሑፍ የሰፈረው ቃሉ ማለትም መጽሐፍ ቅዱስ በዕብራውያን 6:18 ላይ ‘እግዚአብሔር ሊዋሽ አይችልም’ ይላል። ይኸው የአቋም ደረጃ የአምላክ የግል ተወካይ ሆኖ በምድር ላይ ያገለግል በነበረው በኢየሱስ ክርስቶስ ተደግፏል። ሊገድሉት ያስቡ ለነበሩት አይሁዳውያን መሪዎች ኢየሱስ እንዲህ አለ፦ “ነገር ግን አሁን ከእግዚአብሔር የሰማሁትን እውነት የነገርኳችሁን ሰው ልትገድሉኝ ትፈልጋላችሁ፤ . . . አላውቀውም ብል እንደ እናንተ ሐሰተኛ በሆንሁ።” (ዮሐንስ 8:40, 55) ኢየሱስ ‘ኃጢአት ያላደረገ፣ ተንኮልም በአፉ ያልተገኘበት’ በመሆን ምሳሌ ትቶልናል።—1 ጴጥሮስ 2:21, 22

ስሙ ይሖዋ የሆነው ፈጣሪያችን ሐሰትን እንደሚጠላ በግልጽ ሲናገር ምሳሌ 6:16-19 እንዲህ ይላል፦ “እግዚአብሔር የሚጠላቸው ስድስት ነገሮች ናቸው፣ ሰባትንም ነፍሱ አጥብቃ ትጸየፈዋለች፤ ትዕቢተኛ ዓይን፣ ሐሰተኛ ምላስ፣ ንጹሕን ደም የምታፈስስ እጅ፣ ክፉ አሳብን የሚያበቅል ልብ፣ ወደ ክፉ የምትሮጥ እግር፣ በሐሰት የሚናገር ሐሰተኛ ምስክር፣ በወንድማማች መካከልም ጠብን የሚዘራ።”

ይህ እውነተኛ አምላክ በእርሱ ፊት ተቀባይነት እንድናገኝ እርሱ ያወጣቸውን የአቋም ደረጃዎች አክብረን እንድንኖር ይፈልግብናል። በእርሱ አነሳሽነት የተጻፈው ቃሉ “እርስ በርሳችሁ ውሸት አትነጋገሩ፤ ምክንያቱም አሮጌውን ሰው ከነሥራው አውልቃችሁ ጥላችሁታል” በማለት ያዘናል። (ቆላስይስ 3:9 የ1980 ትርጉም) የመዋሸት ልማዳቸውን ለማቆም የማይፈልጉ ሰዎች በእርሱ ዘንድ ተቀባይነት የላቸውም፤ የሕይወት ስጦታውንም አይቀበሉም። እንዲያውም መዝሙር 5:6 በግልጽ እንደሚናገረው አምላክ ‘ሐሰትን የሚናገሩትን ያጠፋቸዋል።’ በተጨማሪም ራእይ 21:8 “የሐሰተኛዎችም ሁሉ” ዕድላቸው “ሁለተኛው ሞት ነው።” ይህም ለዘላለም መጥፋት ማለት ነው። ስለዚህ አምላክ ስለ ሐሰት ያለውን አመለካከት መቀበላችን እውነትን እንድንናገር ጠንካራ ምክንያት ይሆነናል።

ይሁን እንጂ እውነትን መናገር የሚያሳፍር ወይም መጥፎ ስሜት የሚፈጥር ከሆነ ምን መደረግ ይኖርበታል? መዋሸት በፍጹም መፍትሔው አይሆንም። አንዳንድ ጊዜ ግን ዝም ማለቱ ጥሩ ይሆናል። በሰዎች ዘንድ ያለህን አመኔታ አጥፍቶ መለኮታዊ ተቀባይነት የሚያሳጣህ ከሆነ ለምን ትዋሻለህ?

በፍርሃት እና በሰብዓዊ ድክመቶች የተነሳ አንድ ሰው ሊፈተንና ውሸትን ከለላው ለማድረግ ይሞክር ይሆናል። ይህ ችግሩን ለመወጣት ቀላሉ መንገድ ወይም የተሳሳተ ደግነት ነው። ሐዋርያው ጴጥሮስ ኢየሱስ ክርስቶስን ማወቁን ሦስት ጊዜ በመካድ ይህን በመሰለው ፈተና ተሸንፎ ነበር። ከዚያ በኋላ ግን በመዋሸቱ ከልቡ አዘነ። (ሉቃስ 22:54-62) እውነተኛ ንስሐ መግባቱ አምላክ ይቅር እንዲለው አድርጎታል። ይህም በአገልግሎቱ በርካታ መብቶች በማግኘት በመባረኩ ታይቷል። አምላክ የሚጠላውን ካደረግን መለኮታዊ ይቅርታ የሚያስገኘው መንገድ ስንል መግባትና መዋሸትን ለማቆም ቁርጥ ውሳኔ ማድረጉ ነው።

ይሁን እንጂ ከዋሸህ በኋላ አምላክን ይቅርታ ከመለመን ይልቅ እውነትን በመናገር ከፈጣሪህ ጋር ያለህን ግንኙነትና በሌሎች ዘንድ ያለህን ተአማኒነት ጠብቅ። “አቤቱ፣ በድንኳንህ ውስጥ ማን ያድራል? በተቀደሰውም ተራራህ ማን ይኖራል? በቅንነት የሚሄድ፣ ጽድቅንም የሚያደርግ፣ በልቡም እውነትን የሚናገር” የሚለውን መዝሙር 15:1, 2⁠ን አስታውስ።

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ