የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • g98 8/8 ገጽ 5-12
  • የአዝጋሚ ለውጥ ንድፈ ሐሳብ መሠረት አለውን?

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • የአዝጋሚ ለውጥ ንድፈ ሐሳብ መሠረት አለውን?
  • ንቁ!—1998
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • ኢተከፋፋይ ውስብስብነት የአዝጋሚ ለውጥ ንድፈ ሐሳብ ሊወጣው ያልቻለው ትልቅ ችግር
  • የደም መርጋት ኢተከፋፋይ ውስብስብነት
  • ‘ጆሮ ጭው የሚያደርግ ዝምታ’
  • የሕይወትን አጀማመር በተመለከተ የሚነሱ ችግሮች
  • ብዙ ሰዎች የሚያምኑበት ለምንድን ነው?
  • ሕይወት ካላቸው ነገሮች መካከል ውስብስብ ያልሆነ አለ?
    የሕይወት አመጣጥ​—መልስ የሚያሻቸው አምስት ጥያቄዎች
  • መልስ የሚያሻቸው ሁለት ጥያቄዎች
    ንቁ!—2015
  • ሕይወት እንዴት ጀመረ?
    ተጨማሪ ርዕሰ ጉዳዮች
  • ከአንድ ባዮኬሚስት ጋር የተደረገ ቃለ ምልልስ
    ንቁ!—2006
ለተጨማሪ መረጃ
ንቁ!—1998
g98 8/8 ገጽ 5-12

የአዝጋሚ ለውጥ ንድፈ ሐሳብ መሠረት አለውን?

የዳርዊን የአዝጋሚ ለውጥ ንድፈ ሐሳብ ፍሬ ነገር ምንድን ነው? “በስነ ሕይወታዊ ፍቺው . . . አዝጋሚ ለውጥ ማለት ሕይወት ከግዑዛን ነገሮች ሙሉ በሙሉ ያለ ማንም ጣልቃ ገብነት ቀስ በቀስ በመሻሻል የተገኘበት ሂደት ነው።” የዳርዊናውያን የአዝጋሚ ለውጥ ንድፈ ሐሳብ “ሕይወት ሙሉ በሙሉ ወይም ቢያንስ የሕይወት ጉልሕ ገጽታዎች የተገኙት በነሲባዊ የዓይነት ምርጫ ላይ በተመሠረተው ተፈጥሯዊ ምርጦሽ (ናቹራል ሴሌክሽን) ነው” ይላል።—ዳርዊንስ ብላክ ቦክስ—ባዮኬሚካል ቻሌንጅ ቱ ኢቮሉሽንa፤ በፔንሲልቬኒያ ዩ ኤስ ኤ በሚገኘው ሌሂይ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ተባባሪ ፕሮፌሰር ሆነው በሚሠሩት ማይክል ቤ የተዘጋጀ።

ኢተከፋፋይ ውስብስብነት የአዝጋሚ ለውጥ ንድፈ ሐሳብ ሊወጣው ያልቻለው ትልቅ ችግር

ዳርዊን ንድፈ ሐሳቡን በቀመረበት ዘመን ሳይንቲስቶች አስገራሚ ስለሆነው የሕያው ህዋስ ወይም ሴል ውስብስብ ባሕርይ የነበራቸው እውቀት እጅግ አነስተኛ ነበር፤ ወይም ደግሞ ጭራሽ የሚያውቁት ነገር አልነበረም። የሕይወትን ሞለኪውላዊ ሁኔታ የሚያጠናው የዘመናችን ባዮኬሚስትሪ ይህንን ውስብስብ ሁኔታ በተወሰነ መጠን እንድናስተውል አስችሎናል። እንዲሁም የዳርዊን ንድፈ ሐሳብ ትልቅ ጥያቄ ላይ እንዲወድቅ አድርጓል።

የአንድ ህዋስ የተለያዩ ክፍሎች በሞለኪውሎች የተገነቡ ናቸው። ሁሉም ሕያዋን ነገሮች የተገነቡት ደግሞ በህዋሳት ወይም በሴሎች ነው። ፕሮፈሰር ቤ የሮማ ካቶሊክ እምነት ተከታይ ሲሆኑ ኋለኞቹ እንስሳት የተገኙት በአዝጋሚ ለውጥ እንደሆነ የሚያምኑ ሰው ናቸው። ይሁን እንጂ የአዝጋሚ ለውጥ ንድፈ ሐሳብ ህዋስ ወይም ሴል መገኘት ስለቻለበት ሁኔታ በቂ ማብራሪያ ሊሰጥ መቻሉን ይጠራጠራሉ። በአንድ ህዋስ ውስጥ በሞለኪውል የተገነቡ የተለያዩ መሣሪያዎች እንዳሉ ሲያስረዱ እንዲህ ብለዋል:- “በህዋስ ውስጥ ያለ አንድ ከሞለኪውል የተገነባ መሣሪያ ከሌሎች ሞለኪውሎች በተሠሩ ‘አውራ ጎዳናዎች’ ላይ ከአንድ ቦታ ወደ ሌላው ዕቃ ያጓጉዛል። . . . ህዋሳት ሞለኪውላዊ መሣሪያዎችን ተጠቅመው ይንሳፈፋሉ፣ በሞለኪውላዊ መሣሪያዎች እገዛ ራሳቸውን ያባዛሉ እንዲሁም በመሣሪያዎች ረዳትነት ምግብ ወደ ውስጣቸው ያስገባሉ። በአጭሩ በህዋሳት ውስጥ የሚከናወነውን እያንዳንዱን እንቅስቃሴ የሚቆጣጠሩ እጅግ የረቀቁ ሞለኪውላዊ መሣሪያዎች አሉ። ከሕይወት ጋር ዝምድና ያለው እያንዳንዱ ጥቃቅን ነገር ረቂቅ በሆነ መንገድ የተስተካከለ ሲሆን የሕይወት መሣሪያዎችም እጅግ በሚያስገርም መንገድ የተወሳሰቡ ናቸው።”

ታዲያ ይህ ሁሉ ነገር የሚከናወነው ምን ያህል ስፋት ባለው ቦታ ላይ ነው? አንዲት ዓይነተኛ ህዋስ ያላት የጎን ስፋት 0.03 ሚሊ ሜትር ብቻ ነው! በዚያች ኢምንት ቦታ ላይ ለሕይወት የግድ አስፈላጊ የሆኑ ውስብስብ ነገሮች ይከናወናሉ። (ገጽ 8, 9 ላይ የሚገኘውን ስዕል ተመልከት።) “ዋናው ነገር የሕይወት መሠረት የሆነው ህዋስ ያለው ውስብስብነት ለማመን እንኳን የሚከብድ መሆኑ ነው” መባሉ አያስገርምም።

ማይክል ቤ ህዋስ ሙሉ ሳይሆን ወይም ከፊል ሆኖ ሥራውን ማከናወን እንደማይችል ተናግረዋል። ስለዚህ አዝጋሚ በሆነ ለውጥ በመሻሻል ላይ የሚገኝ ህዋስ ሥራውን ለማከናወን የሚያስችል ብቃት ሊኖረው አይችልም። ይህን ሁኔታ ለማስረዳት አንድን የአይጥ ወጥመድ እንደ ምሳሌ ተጠቅመዋል። ይህ በጣም ቀላል የሆነ መሣሪያ እንኳን ሊሠራ የሚችለው ሁሉም ክፍሎቹ ከተገጣጠሙ ብቻ ነው። እያንዳንዱ ክፍል ማለትም ወለሉ፣ ሞላው፣ ማሠሪያ ሽቦው፣ የወጥመዱ መደገፊያ ወይም ተወርዋሪ መያዣው ብቻውን የአይጥ ወጥመድ ሊሆን ወይም እንደ አይጥ ወጥመድ ሆኖ ሊያገለግል አይችልም። አገልግሎት የሚሰጥ ወጥመድ እንዲኖር ከተፈለገ ሁሉም ክፍሎች በአንድ ተመሳሳይ ወቅት ተገጣጥመው መገኘት ይኖርባቸዋል። ልክ እንደዚሁ አንድ ህዋስ እንደ ህዋስ ሆኖ ሊሠራ የሚችለው ሁሉም ክፍሎቹ ካሉ ብቻ ነው። ቤ ይህን ምሳሌ የተጠቀሙት “ኢተከፋፋይ ውስብስብነት” (irreducible complexity) የሚል ስያሜ የሰጡትን ሁኔታ ለማስረዳት ነው።b

ይህ ደግሞ በጣም አስፈላጊ የሆኑ ባሕርያት ደረጃ በደረጃ በአዝጋሚ ለውጥ ተገኙ ለሚለው የአዝጋሚ ለውጥ ንድፈ ሐሳብ ዋነኛ ችግር ሆኗል። ዳርዊን በተፈጥሯዊ ምርጦሽ አማካኝነት አዝጋሚ ለውጥ ይካሄዳል የሚለው ንድፈ ሐሳቡ ትልቅ ፈተና እንደተጋረጠበት አውቆ ነበር። ይህንንም ሲያረጋግጥ “በርከት ያሉ ተከታታይና አዝጋሚ መሻሻሎችን ሳያደርግ በአንድ ጊዜ ሕልውና ያገኘ ውስብስብ አካል እንዳለ ማረጋገጥ ከተቻለ የእኔ ንድፈ ሐሳብ ያከትምለታል ማለት ነው” ብሏል።—ኦሪጂን ኦቭ ስፒሺስ

ህዋስ የኢተከፋፋይ ውስብስብነት ባሕርይ ያለው መሆኑ በዳርዊን ንድፈ ሐሳብ ለሚያምኑ ሁሉ ትልቅ እንቅፋት ሆኗል። በመጀመሪያ ደረጃ አዝጋሚ ለውጥ ግዑዛን ነገሮች ወደ ሕያውነት እንዴት እንደተለወጡ ማስረዳት አይችልም። ከዚያ በኋላ ደግሞ የመጀመሪያዋ ውስብስብ ህዋስ ሊነጣጠሉ የማይችሉትን ክፍሎቿን በሙሉ አሟልታ በአንድ ጊዜ ካልሆነ ልትኖር የማትችል መሆኗ የሚያስከትለው ችግር ይመጣል። በሌላ አባባል አንዲት ህዋስ (ወይም የአይጥ ወጥመድ) ካለመኖር ወደመኖር ብቅ ልትል የምትችለው ሙሉ በሙሉ ተገጣጥማና መሥራት የሚያስችል አቅም ኖሯት ብቻ ነው።

የደም መርጋት ኢተከፋፋይ ውስብስብነት

ኢተከፋፋይ ውስብስብነት የሚታይበት ሌላው ምሳሌ አብዛኞቻችን እምብዛም ትኩረት የማንሰጠው አንድ ነገር ሲቆርጠን ደማችን መርጋት መቻሉ ነው። አንድ ጀሪካን ቢበሳ ወዲያው በውስጡ ያለው ፈሳሽ መፍሰስ ይጀምርና እስኪያልቅ ድረስ መውረዱን አያቋርጥም። ቆዳችን ሲበሳ ወይም አንድ ነገር ሲቆርጠን ግን ደማችን ረግቶ ቀዳዳው ስለሚደፈን ወዲያው መፍሰሱን ያቆማል። ይሁን እንጂ ሐኪሞች እንደሚያውቁት “የደም መርጋት እርስ በርሳቸው የተቆራኙ በርካታ የፕሮቲን ክፍሎችን ያካተተ በጣም ውስብስብ ሥርዓት ነው።” ደም እንዲረጋ የሚያደርጉት እነዚህ ፕሮቲኖች ናቸው። ይህ እጅግ ረቂቅ የሆነ የመጠገን ሂደት “ትክክለኛውን ጊዜና ፍጥነት መጠበቁ በጣም አስፈላጊ ነው።” አለዚያ ግን የግለሰቡ ደም ሙሉ በሙሉ ሊረጋ ወይም በተቃራኒው ፈስሶ ሊያልቅና ሊሞት ይችላል። በትክክለኛው ጊዜና ፍጥነት መፈጸሙ ወሳኝ ነው።

የደም መርጋት ብዙ ነገሮችን ያካተተ ሲሆን ሂደቱ በተሳካ መንገድ እንዲከናወን ከእነዚህ ነገሮች መካከል አንዳቸውም ቢሆኑ መጉደል እንደሌለባቸው ባዮኬሚካል ምርምሮች አረጋግጠዋል። ቤ እንዲህ ሲሉ ጠይቀዋል:- “አንድ ጊዜ ደም መርጋት ከጀመረ . . . በሰውነት ውስጥ ያለው ደም በሙሉ እስኪረጋ ድረስ ሂደቱ እንዳይቀጥል የሚያግደው ምንድን ነው?” “ደም መርጋት የሚጀምርበት፣ መርጋቱን የሚያቆምበት፣ የረጋው ደም የሚጠነክርበትና የሚወገድበት” ሂደት አንዱ ከሌላው የማይነጣጠል ባዮሎጂካዊ ሥርዓት መሆኑን አስረድተዋል። ከዚህ መካከል አንዱ ከተበላሸ ጠቅላላ ሥርዓቱ ይቃወሳል።

በካሊፎርኒያ ዩኒቨርሲቲ የባዮኬምስትሪ ፕሮፌሰርና የአዝጋሚ ለውጥ አማኝ የሆኑት ራስል ዶሊትል እንዲህ ሲሉ ጠይቀዋል:- “እንዲህ ያለው ውስብስብ የሆነና በረቀቀ መንገድ ሚዛኑን ጠብቆ የሚሠራ ሂደት እንዴት በአዝጋሚ ለውጥ መጣ ሊባል ይችላል? . . . አንዱ ፕሮቲን በሌላው ፕሮቲን ካልተቀሰቀሰ ተግባሩን በተናጠል ሊያከናውን የማይችል ከሆነ ጠቅላላ ሥርዓቱ እንዴት ሊጀምር ቻለ? ሁሉም ነገር አንድ ላይ ካልተሰባሰበ የተወሰነው ክፍል ብቻ መገኘቱ ምን ዋጋ ይኖረዋል?” ዶሊትል የአዝጋሚ ለውጥን የመከራከሪያ ነጥቦች በመጠቀም ሂደቱ እንዴት እንደጀመረ ለማስረዳት ሞክረዋል። ይሁን እንጂ ፕሮፌሰር ቤ እንደገለጹት “ትክክለኛዎቹ በራሂዎች (gene) በትክክለኛዎቹ ቦታዎች ላይ እንዲገኙ ማድረግ እጅግ ከፍተኛ እድል” ይጠይቃል። ዶሊትል የሰጡት ማብራሪያና የተጠቀሙባቸው ቃላት ቀላልነት የችግሩን ከባድነት እንዳድበሰበሰ አስረድተዋል።

በመሆኑም የዝግመተ ለውጥን ሐሳብ ውድቅ ከሚያደርጉት ማስረጃዎች መካከል ዋነኛውና የማይዘለል ትልቅ መሰናክል የሆነው የኢተከፋፋይ ውስብስብነት ባሕርይ ነው። ቤ እንዲህ ሲሉ ተናግረዋል:- “ለዳርዊናዊው አዝጋሚ ለውጥ እንደ ሞተር የሆነው ተፈጥሮአዊ ምርጦሽ ሊሠራ የሚችለው የሚመረጥ ነገር ማለትም ወደፊት ሳይሆን አሁን የሚጠቅም ነገር ከኖረ ብቻ ነው የሚለውን ሐሳብ ጠበቅ አድርጌ መግለጽ እወዳለሁ።”

‘ጆሮ ጭው የሚያደርግ ዝምታ’

ፕሮፌሰር ቤ እንደገለጹት አንዳንድ ሳይንቲስቶች “የአዝጋሚ ለውጥን ሂደት በሂሣብ ስሌት ለማሳየት ወይም ስለ አዝጋሚ ለውጥ የተሰባሰቡ መረጃዎችን ለማነጻጸርና ለመተርጎም የሚያስችል አዲስ ዓይነት የሂሣብ ቀመር ለማውጣት ሞክረዋል።” ይሁን እንጂ “ሒሳቡ የሚያስረዳው በተጨባጭ የሚፈጸመው አዝጋሚ ለውጥ ቀስ በቀስ የሚካሄድ ነሲባዊ ሂደት እንደሆነ ነው። ይህ ሒሳብ ሂደቱን አያብራራውም (ሊያብራራውም አይችልም)” ከሚል መደምደሚያ ላይ ደርሰዋል። (የመጨረሻውን ሐረግ በሰያፍ የጻፍነው እኛ ነን።) ቀደም ሲል እንደሚከተለው ብለው ነበር:- “ስለ አዝጋሚ ለውጥ የተጻፉትን ሳይንሳዊ ጽሑፎች በሙሉ ብትመረምሩና የሕይወት መሠረት የሆኑት ሞለኪውላዊ መሣሪያዎች እንዴት ወደዚያ ደረጃ ደረሱ በሚለው ጥያቄ ላይ ብቻ ብታተኩሩ ጆሮ ጭው ከሚያደርግ ዝምታ በስተቀር አንዳች ነገር ማግኘት አትችሉም። የሕይወት መሠረት የሆነው ሞለኪውል እጅግ ውስብስብ መሆኑ እንዴት ወደ ሕልውና እንደመጣ ለማስረዳት ሳይንስ ያደረገውን ሙከራ በሙሉ አምክኖበታል። እስካሁን ድረስ እጅግ ውስብስብ የሆኑት ሞለኪውላዊ መሣሪያዎች ለዳርዊናውያን ንድፈ ሐሳብ ሊደፈር የማይችል ትልቅ ችግር ሆኗል።”

ይህም ጠንቃቃ የሆኑ ሳይንቲስቶች በርካታ ከሆኑ ጥያቄዎች ጋር እንዲፋጠጡ አስገድዷቸዋል። “የብርሃን አስተጻምሮ (photosynthesis) ሂደት የተገኘው እንዴት ነው? ከሞለኪውል ወደ ሞለኪውል የሚደረገው መጓጓዝ የተጀመረው እንዴት ነው? የኮሌስትሮል ሕይወታይ አስተፃምሮ (biosynthesis) እንዴት ጀመረ? እይታ ድራብ (retina) የእይታ ክፍል ሊሆን የቻለው እንዴት ነው? የፎስፎ ፕሮቲን የመልእክት መተላለፊያ እንዴት ሊገኝ ቻለ?”c ቤ ጨምረው እንዲህ ብለዋል:- “እነዚህ ችግሮች መቋጫ ሊያገኙ ይቅርና ስለ ችግሩ የሚናገር እንኳ መጥፋቱ ራሱ፣ የዳርዊናውያን ፍልስፍና ውስብስብ የሆነው የባዮኬሚካል ሥርዓት እንዴት እንደተገኘ ለማስረዳት የሚያስችል ብቃት እንደሌለው የሚያረጋግጥ ጠንካራ ማስረጃ ነው።”

የዳርዊን ንድፈ ሐሳብ የህዋሳት ሁሉ መሠረት የሆነው ሞለኪውል እንዴት እንደተገኘ ማስረዳት ካልቻለ ዛሬ በምድር ላይ የሚገኙት በሚልዮን የሚቆጠሩ ሕያዋን ነገሮች እንዴት እንደተገኙ አጥጋቢ ማብራሪያ ይሰጣል ተብሎ እንዴት እምነት ሊጣልበት ይችላል? አዝጋሚ ለውጥ በእያንዳንዱ ወገን መካከል ያለውን ትልቅ ልዩነት ሊያጠቡ የሚችሉ አዳዲስ ወገኖች ሊያስገኝ እንደማይችል የታወቀ ነው።—ዘፍጥረት 1:11, 21, 24

የሕይወትን አጀማመር በተመለከተ የሚነሱ ችግሮች

የዳርዊን የአዝጋሚ ለውጥ ንድፈ ሐሳብ ለአንዳንዶቹ ሳይንቲስቶች ምንም ያህል የሚታመን መስሎ ቢታይ የኋላ ኋላ ሕያዋን ነገሮች በተፈጥሯዊ ምርጦሽ አማካኝነት ተገኙ እንኳ ብንል ሕይወት በመጀመሪያ እንዴት ተገኘ? ለሚለው ጥያቄ መልስ ማግኘት ይኖርባቸዋል። በሌላ አባባል ችግሩ ያለው ትግሉን ያሸነፈው ተረፈ ከሚለው ንድፈ ሐሳብ ላይ ሳይሆን ትግሉን የማሸነፍ ብቃት የነበረውና የመጀመሪያ የሆነው ሕይወት እንዴት ሊገኝ ቻለ? በሚለው ላይ ነው። ዳርዊን ስለ ዓይን አዝጋሚ ለውጥ የሰነዘረው አስተያየት እንደሚያመለክተው ሕይወት እንዴት ጀመረ በሚለው ጉዳይ አልተጨነቀም። እንዲህ ሲል ጽፏል:- “አንድ ነርቭ ብርሃን የመለየት ችሎታ ሊያገኝ የሚችለው እንዴት ነው የሚለው ጉዳይ ሕይወት ራሱ እንዴት ጀመረ እንደሚለው ጥያቄ እምብዛም አያስጨንቀንም።”

ፈረንሳዊው የሳይንስ ጸሐፊ ፌሌፕ ሻምቦ እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል:- “ዳርዊን ራሱ አዳዲስ ዝርያዎች ሙሉ በሙሉ መንቀሳቀስ ከመጀመራቸው በፊት፣ ገና ብቅ እንዳሉ ተፈጥሮ መርጣ ልታጠፋ የምትችለው እንዴት ነው ለሚለው ጥያቄ መልስ ለማግኘት አልቻለም። አዝጋሚ ለውጥ ሊፈታ ያልቻላቸው ምሥጢሮች ብዛት በጣም ብዙ ነው። ዛሬ ያሉት የስነ ሕይወት ተመራማሪዎች በኦርሳ የሚገኘው የሳውዝ ፓሪስ ዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰር እንደሆኑት ዣን ዣንረሞን ‘ልብ ወለድ የሆነው የአዝጋሚ ለውጥ ንድፈ ሐሳብ ውስብስብ የሆኑት የአካል ክፍሎች እንዴት እንደተገኙ በግልጽ ማስረዳት እንደማይችል’ በትሕትና አምነው መቀበል ይኖርባቸዋል።”

አዝጋሚ ለውጥ ሥፍር ቁጥር የሌላቸውንና ውስብስብ የሆኑ የተለያዩ ሕያዋን ነገሮችን ሊያስገኝ የማይችል መሆኑን ስታይ ሁሉም ነገር እንደ አጋጣሚ ሆኖ በትክክለኛው መንገድ ለውጥ እያደረገ መጥቷል ብለህ ለማመን አስቸጋሪ ይሆንብሃል? ዓይኑ ገና በአዝጋሚ ለውጥ ሂደት ላይ እያለ ወይም ወደ ሙሉ ሰውነት ባልተለወጠው አካሉ ላይ ያሉት ጣቶቹ ለውጣቸውን ያልጨረሱ ሆነው ሳለ ለመትረፍ የሚደረገውን ትግል በድል አድራጊነት ለመወጣት የሚችለው ምን ያህሉ ፍጥረት ይሆናል ብለህ አስበህ ታውቃለህ? ሕዋሳት ገና ባልተሟላና ብቁ ባልሆነ ሁኔታ ላይ የሚገኙ ከሆነ እንዴት ሊተርፉ ቻሉ ብለህ ጠይቀህ ታውቃለህ?

አስትሮኖሚ የተባለው መጽሔት ጸሐፊ የሆኑት የአዝጋሚ ለውጥ አማኝ ሮበርት ኔይ በምድር ላይ ያለው ሕይወት እንዴት እንደተገኘ ሲገልጹ እንዲህ ብለው ጽፈዋል:- “በሚልዮን የሚቆጠር ዶላር የሚያስገኝ የሎተሪ ዕጣ በመደዳ አንድ ሚልዮን ጊዜ አሸናፊ ከመሆን ተለይቶ በማይታይ መንገድ ሊሆኑ የማይችሉት ተከታታይ ሁኔታዎች ልክ በሚፈለገው መንገድ ሆነው እኛን ማስገኘት ችለዋል።” ምናልባት ይህ አባባል ለእያንዳንዱ ፍጥረት ይሠራል ይባል ይሆናል። ፈጽሞ ሊሆን የማይችል ነገር ነው። ይሁንና አዲሱ ዝርያ ዘሩን ማቆየት እንዲችል በአዝጋሚ ለውጥ ሂደት በአጋጣሚ በአንድ ጊዜ ወንድና ሴት ተገኙ ብለን ማመን ይኖርብናል። ጎዶሎ ጎኑን ለማሟላትም በአንድ ወቅት ለውጥ አድርገው ተገኙ ብቻ ሳይሆን በአንድ ቦታም ተገኙ ብለን ማመን አለብን! በዚህ መንገድ ተገናኙ ካልተባለ ደግሞ መሰላቸውን መተካት የሚችሉበት መንገድ አይኖርም ነበር!

ግባቸውን በመቱ በሚልዮን የሚቆጠሩ ዕድሎች ምክንያት በሚልዮን የሚቆጠሩ ልዩ ልዩ ሕያዋን ነገሮች ተገኝተዋል ብሎ ማመን እንዴት ያለ ፌዝ ይሆናል።

ብዙ ሰዎች የሚያምኑበት ለምንድን ነው?

የአዝጋሚ ለውጥ ንድፈ ሐሳብ በብዙዎቹ ሰዎች ዘንድ ይህን ያህል ተቀባይነት ያገኘውና በምድር ላይ ያለው ሕይወት እንዴት ተገኘ ለሚለው ጥያቄ እንደ ብቸኛ መልስ ተደርጎ የሚታየው ለምንድን ነው? አንደኛው ምክንያት በትምህርት ቤቶችና በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ውስጥ እንደ ትክክለኛ አመለካከት ተደርጎ ትምህርት የሚሰጥበት በመሆኑ ሲሆን አንድ ዓይነት ጥርጣሬ እንዳለህ ብትጠቅስ መጥፎ መዘዝ ያስከትልብሃል። ቤ እንዲህ ሲሉ ተናግረዋል:- “ብዙ ተማሪዎች ዓለምን በአዝጋሚ ለውጥ መነፅር እንዴት መመልከት እንደሚችሉ ከመማሪያ መጽሐፎቻቸው ይማራሉ። ይሁን እንጂ እነዚህ ትምህርቶች የሚጠቅሷቸውን ረቂቅ የሆኑ የባዮኬሚካላዊ ሥርዓቶች የዳርዊናውያን አዝጋሚ ለውጥ እንዴት አድርጎ እንደሚገልጻቸው አይማሩም።” አክለውም እንዲህ ብለዋል:- “ዳርዊኒዝም እንዴት ትክክል ተደርጎ ለመታመን እንደበቃም ሆነ በሞለኪውላዊ ሁኔታዎች ረገድ ሳይንሳዊነቱ ጥያቄ ላይ የወደቀበትን መንገድ ለመረዳት ሳይንቲስት የመሆን ምኞት የነበራቸው ሰዎች የተማሩባቸውን መጻሕፍት መመርመር ይኖርብናል።”

“በዓለም ዙሪያ ካሉት ሳይንቲስቶች በሙሉ አስተያየት ቢሰበሰብ አብዛኛዎቹ የዳርዊን ፍልስፍና እውነት ነው ብለው እንደሚያምኑ ይናገራሉ። ይሁን እንጂ ሳይንቲስቶችም ቢሆኑ እንደ ሌላው ሰው ሁሉ አብዛኞቹ ሐሳቦቻቸው የተመሠረቱት ሌሎች ሰዎች በተናገሯቸው ነገሮች ላይ ነው። . . . ከዚህም ሌላ የሚያሳዝነው አብዛኛውን ጊዜ የሳይንሱ ኅብረተሰብ በፍጥረት ለሚያምኑት ወገኖች ጥይት እንደማቀበል እንዳይሆንበት ሲል ለሚሰነዘሩት ትችቶች ቦታ አይሰጥም። ሳይንስን ከጥቃት ለመጠበቅ በሚል ስም ተፈጥሯዊ ምርጦሽን በተመለከተ እውነታውን ፍርጥ አድርገው የሚያሳዩ ሳይንሳዊ ትችቶችን ወደ ጎን ገሸሽ ማድረጋቸው እንዴት ያለ ፌዝ ነው።”d

ታዲያ ከዳርዊን የአዝጋሚ ለውጥ ንድፈ ሐሳብ ሌላ ምን ተግባራዊና አስተማማኝ አማራጭ ይኖራል? የእነዚህ ተከታታይ ርዕሶች የመጨረሻ ክፍል ይህንን ጥያቄ የሚዳስስ ይሆናል።

[የግርጌ ማስታወሻ]

a ከዚህ በኋላ ዳርዊንስ ብላክ ቦክስ ተብሎ ብቻ ይጠቀሳል።

b “ኢተከፋፋይ ውስብስብነት” “ለመሠረታዊው እንቅስቃሴ የየበኩላቸውን አስተዋጽኦ የሚያደርጉ እርስ በርሳቸው ተደጋግፈውና ተጣጥመው የሚሠሩ በርካታ ክፍሎችን ያቀፈ ሥርዓት ሲሆን ከእነዚህ ክፍሎች አንዱ እንኳን ቢጎድል ሥርዓቱ እንቅስቃሴውን ያቆማል።” (ዳርዊንስ ብላክ ቦክስ) በመሆኑም ይህ ሥርዓት ከዚያ ባነሰ ደረጃ ላይ ቢገኝ ተግባሩን ሊያከናውን አይችልም ማለት ነው።

c ብርሃን አስተጻምሮ የዕጽዋት ህዋሳት ብርሃንንና አረንጓዴ ሃመልሚል በመጠቀም ከካርቦንዳይኦክሳይድና ከውኃ ካርቦሃይድሬት የሚሠሩበት ሂደት ነው። አንዳንዶች በተፈጥሮ ከሚካሄዱት ኬሚካላዊ አጸግብሮቶች ሁሉ እጅግ ከፍተኛ ቦታ የሚሰጠው እንደሆነ ይናገሩለታል። ሕይወታይ አስተጻምሮ ደግሞ ሕያዋን ህዋሳት ውስብስብ ባሕርይ ያላቸውን ኬሚካላዊ ውሁዶች የሚያዘጋጁበት ሂደት ነው። እይታ ድራብ ውስብስብ በሆነው የእይታ ሥርዓት ውስጥ ከፍተኛ ድርሻ አለው። የፎስፎፕሮቲኖች የመልእክት መተላለፊያ መስመር የአንድ ህዋስ ሊነጠል የማይችል ክፍል ነው።

d የፍጥረት ንድፈ ሐሳብ ምድር የተፈጠረችው ቃል በቃል በስድስት ቀናት ውስጥ ነው ወይም አንዳንድ ጊዜ ከተፈጠረች አሥር ሺህ ዓመታት ገደማ ቢሆናት ነው ብሎ ማመንን ይጨምራል። የይሖዋ ምሥክሮች በፍጥረት የሚያምኑ ቢሆኑም የእንዲህ ዓይነቱ የፍጥረት ንድፈ ሐሳብ አማኞች አይደሉም። በዘፍጥረት ውስጥ በሚገኘው የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ መሠረት ምድር በሚልዮን የሚቆጠሩ ዓመታት ዕድሜ ያላት ልትሆን እንደምትችል ያምናሉ።

[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

“በርከት ያሉ ተከታታይና አዝጋሚ መሻሻሎችን ሳያደርግ በአንድ ጊዜ ሕልውና ያገኘ ውስብስብ አካል እንዳለ ማረጋገጥ ከተቻለ የእኔ ንድፈ ሐሳብ ያከትምለታል ማለት ነው።”

[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

በአንድ ህዋስ ውስጥ “የረቀቀ ቴክኖሎጂና አስገራሚ ውስብስብነት” ይታያል።—ኢቮሉሽን:- ኤ ቲዮሪ ኢን ክራይስስ

በአንድ ህዋስ ዲ ኤን ኤ ውስጥ የሚገኘው ዝርዝር መረጃ “በጽሑፍ ቢሰፍር እያንዳንዳቸው 600 ገጾች ያሏቸው አንድ ሺህ መጻሕፍት ይወጣው ነበር።”—ናሽናል ጂኦግራፊክ

[በገጽ 11 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

“ሒሳቡ የሚያስረዳው በተጨባጭ የሚፈጸመው አዝጋሚ ለውጥ ቀስ በቀስ የሚካሄድ ነሲባዊ ሂደት እንደሆነ ነው። ይህ ሒሳብ ሂደቱን አያብራራውም (ሊያብራራውም አይችልም)።”

[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

“ሳይንስን ከጥቃት ለመጠበቅ በሚል ስም ተፈጥሯዊ ምርጦሽን በተመለከተ እውነታውን ፍርጥ አድርገው የሚያሳዩ ሳይንሳዊ ትችቶችን ወደ ጎን ገሸሽ ማድረጋቸው እንዴት ያለ ፌዝ ነው።”

[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

ሞለኪውልና ህዋስ

ባዮኬሚስትሪ—“የሕይወት መሠረት ስለሆነው ነገር ማለትም ህዋሳትና ሕብረ ህዋሳት ስለተሠሩበት እንዲሁም የምግብ መፈጨትን፣ የብርሃን አስተጻምሮን፣ የበሽታ መከላከያ አቅምንና ሌሎች ኬሚካላዊ አጸግብሮቶች ስለሚያፋጥነው ሞለኪውል የሚደረግ ጥናት ነው።”—ዳርዊንስ ብላክ ቦክስ

ሞለኪውል—“አንድ ንጥረ ነገር ወይም ውሁድ ፊዚካላዊና ኬሚካላዊ ይዘቱን ሳይቀይር ሊከፋፈል የሚችልበት የመጨረሻው ትንሹ ደረጃ ሲሆን በኬሚካላዊ ኃይል አንድ ላይ የተሳሰሩ ተመሳሳይ ወይም የተለያዩ አቶሞች ክምችት ነው።”—ዚ አሜሪካን ሄሪቴጅ ዲክሽነሪ ኦቭ ዚ ኢንግሊሽ ላንጉጅ

ህዋስ—የሁሉም ሕያዋን ዘአካሎች (organisims) መሠረታዊ አካል። “እያንዳንዱ ህዋስ እጅግ የተደራጀ አካል ሲሆን የአንድን ዘአካል ዓይነትና ተግባር በመወሰን ረገድ ቁልፍ ሚና ይጫወታል።” አንድ ጎልማሳ ሰው ምን ያህል ሕዋሳት ይኖሩታል? አንድ መቶ ትሪሊዮን (100,000,000,000,000)! በእያንዳንዱ ስኩዌር ሴንቲ ሜትር ቆዳ ላይ 155,000 ህዋሳት የሚገኙ ሲሆን በሰው አእምሮ ውስጥ ከ10 ቢልዮን እስከ 100 ቢልዮን የሚደርሱ ህዋሰ ነርቮች ይገኛሉ። “ህዋስ ውኃ፣ ጨው፣ ልሂቅ ሞለኪውል (macromolecule) እንዲሁም የህዋሱ ገለፈት (membrane) ሕያው የሚሆኑበት ደረጃ በመሆኑ ለሕይወት ሂደት ወሳኝ ነው።”—ባዮሎጂ

[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

‘አቻ የሌለው የህዋስ ውስብስብነት’

“ከሞለኪውላዊ ስነ ህይወት አንጻር የሕይወትን እውነታ መረዳት ከፈለግን አንዷን ህዋስ ዲያሜትሯ ሃያ ኪሎ ሜትር እስኪደርስ ድረስ አንድ ሺህ ሚልዮን ጊዜ ማጉላት ይኖርብናል፤ ያኔ እንደ ለንደን ወይም ኒው ዮርክ ያሉትን ከተሞች ለመሸፈን የሚችል ግዙፍ ኤይር ሺፕ ይወጣታል። ከዚህ በኋላ በውስብስብነቱ አቻ የማይገኝለትና ከአዳዲስ ሁኔታዎች ጋር ራሱን የማስማማት ብቃት ያለው አስገራሚ ንድፍ እንመለከታለን። በህዋሱ ወለል ላይ በሚልዮን የሚቆጠሩ ቀዳዳዎችን የምናይ ሲሆን እነዚህም ብዙ ነገር ያለማቋረጥ ወደ ውስጥና ወደ ውጭ መፍሰስ ይችል ዘንድ ክፍት ዘጋ ሲሉ ይታያሉ። ከነዚህ ቀዳዳዎች ወደ አንዱ ውስጥ ብንዘልቅ ደግሞ እጅግ የረቀቀ ቴክኖሎጂና ግራ የሚያጋባ ውስብስብነት ያለው ዓለም እናገኛለን። ማብቂያ የሌላቸው በሚገባ የተደራጁ መተላለፊያዎች ከህዋሱ ጥግ ወደተለያየ አቅጣጫ ተሠረጫጭተው ይታያሉ። አንዳንዶቹ በኑክለስ ውስጥ ወደሚገኘው ማዕከላዊ የመረጃ ባንክ ሲሄዱ ሌሎቹ ደግሞ ወደ መገጣጠሚያና ማምረቻ ክፍሎች ይሄዳሉ። ኑክለሱ ብቻ ዲያሜትሩ ከአንድ ኪሎ ሜትር የሚበልጥ ድቡልቡል ክፍል የሚወጣው ሲሆን ሥነ ቅርጸ መሬታዊ (geodesic) ጉልላት መስሎ በውስጡ በኪሎ ሜትሮች የሚለካ ርዝማኔ ያላቸውና አንድ ላይ የተጣመሩ የዲ ኤን ኤ ሞለኪውሎች በሥርዓት ተደርድረው እናያለን። በህዋሱ የላይኛው ክፍል ከሚገኙት የተለያዩ የመገጣጠሚያ ክፍሎች የሚወጡና ወደ እነዚህ ክፍሎች የሚገቡ ብዙ ዓይነት ያላቸው ምርቶችና ጥሬ ዕቃዎች በተለያዩት የመተላለፊያ ቅርንጫፎች ላይ ከፍተኛ ሥርዓት በጠበቀ ሁኔታ ይዘዋወራሉ።

“ፈጽሞ ማብቂያ የሌላቸው መስለው በሚታዩት መተላለፊያዎች ላይ ይህን ያህል ብዛት ያላቸው ነገሮች እንቅስቃሴ እያደረጉም የሚታየው ድንቅ ሥርዓት ያስገርማል። በየአቅጣጫው ሮቦት የመሰሉ ብዙ ዓይነት መሣሪያዎችን እንመለከታለን። ከህዋሱ ክፍሎች ውስጥ በአንጻራዊ ሁኔታ ሲታይ እምብዛም ውስብስብ አይደለም የሚባለው የፕሮቲን ሞለኪውል እንኳ አስገራሚ በሆነ መንገድ ውስብስብ የሆኑ ሞለኪውላዊ መሣሪያዎችን ያካተተ ሆኖ እናገኘዋለን። እያንዳንዳቸው የጠፈርን ገጠሶስት [3-D] መልክ በተላበሰ ሁኔታ እጅግ የተደራጁና ወደ ሦስት ሺህ የሚጠጉ አተሞችን የያዙ ናቸው። እነዚህ ለመረዳት የሚያስቸግሩ ሞለኪውላዊ መሣሪያዎች የሚያደርጉትን ትርጉም አዘል እንቅስቃሴ ስንመለከት ደግሞ ይበልጥ እንገረማለን። በተለይ ደግሞ ምንም ያህል የፊዚክስና የኬሚስትሪ እውቀት ክምችት ቢኖረን እንደዚህ ካሉት ሞለኪውላዊ መሣሪያዎች መካከል አንዷን ማለትም አንዷን ገቢራዊ የፕሮቲን ሞለኪውል እንኳን መንደፍ ከአቅማችን በላይ እንደሆነ ምናልባትም እስከሚቀጥለው መቶ ዘመን መባቻ ድረስ የማንደርስበት ነገር መሆኑን ስናውቅ እጅግ እንደነቃለን። ይሁንና የህዋሱ ሕይወት የተመካው የተለያዩ የፕሮቲን ሞለኪውሎች በሚያደርጓቸው እርስ በርስ የተሳሰሩ በአሥር ሺዎች ምናልባትም በመቶ ሺዎች በሚቆጠሩ እንቅስቃሴዎች ላይ ነው።”—ኤ ቲዮሪ ኢን ክራይስስ

[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

ሐቁና አፈታሪኩ

“ምርምሩ ከሕያዋን ነገሮች በስተጀርባ የማሰብ ችሎታ ያለው ምንጭ የለም በሚለው ሐሳብ ብቻ ተወስኖ እንዲቀር የማይፈልግ ሰው ብዙ ባዮኬሚካላዊ ሥርዓቶች በዓላማ የተነደፉ ናቸው የሚል ቀጥተኛ መደምደሚያ ላይ ይደርሳል። እነዚህ የተነደፉት በተፈጥሮ ሕግ፣ በአጋጣሚ ወይም በሁኔታዎች አስገዳጅነት ሳይሆን በዓላማ ነው። . . . በምድር ላይ የሚገኘው ሕይወት መሠረታዊ ነገር እንዲሁም በጣም ወሳኝ የሆኑት ክፍሎቹ ሁሉ የማሰብ ችሎታ ያለው አካል የሥራ ውጤት ናቸው።”—ዳርዊንስ ብላክ ቦክስ

“የስነ ሕይወት ተመራማሪዎች ለአንድ መቶ ዘመን ከፍተኛ ጥረት ሲያደርጉ ቢኖሩም [የዳርዊንን የአዝጋሚ ለውጥ ጽንሰ ሐሳብ] ተቀባይነት ያለው ማስረጃ በማቅረብ ማረጋገጥ አለመቻላቸው ምንም የሚያጠያይቅ አይደለም። ዛሬም ቢሆን ተፈጥሮ የዳርዊን ጽንሰ ሐሳብ እንደሚለው አንዱ ከሌላው እንደተገኘ የሚያረጋግጥ እርስ በርሱ የተሳሰረ ሂደት አይታይባትም ወይም ሕይወት የተገኘው በአጋጣሚ ነው የሚለው ሐሳብ ተጨባጭ ማረጋገጫ አልተገኘለትም።”—ኢቮሉሽን:- ኤ ቲዮሪ ኢን ክራይስስ

“የአዝጋሚ ለውጥ ጽንሰ ሐሳብ ከስነ ሕይወት ጋር ምንም ግንኙነት በሌላቸው መስኮች ላይ ሳይቀር ተጽዕኖ ማሳደር መቻሉ ምንም ጠንካራ ሳይንሳዊ ማስረጃ ያልተገኘለት አንድ ግምታዊ ሐሳብ የመላውን ኅብረተሰብ አስተሳሰብ ሊቀርጽና የዘመኑን አመለካከት ሊቆጣጠር እንደሚችል የሚያሳይ ግሩም ምሳሌ ነው።”—ኢቮሉሽን:- ኤ ቲዮሪ ኢን ክራይስስ

“ሕይወት የተገኘው በዓላማ ተፈጥሮ ሊሆን ይችላል የሚለውን እምነት ወደ ጎን ገሸሽ የሚያደርግ . . . ጥንታዊ ሳይንስ ካለ እውነትን የመፈለጉን ጉዳይ እርግፍ አድርጎ ትቶታል ማለት ነው። በመሆኑም ናቹራሊዝም የተባለው ውስብስብ ፍልስፍና አገልጋይ (ወይም ባሪያ) ይሆናል።”—ኦሪጂንስ ሪሰርች

“ቻርልስ ዳርዊን ውስብስብ የሆነው ስነ ሕይወት ከየት ተገኘ የሚለውን እንቆቅልሽ ፈትቶታል የሚባለው . . . አፈታሪክ ነው። ስለ ሕይወት ምንጭ በቂ እውቀት ይቅርና መጠነኛ ግንዛቤ እንኳን አለን ወይም ትክክለኛዎቹ ማብራሪያዎች ያተኮሩት ሕይወት የተገኘው ባጋጣሚ ነው በሚለው ሐሳብ ላይ ነው የሚባለው አፈታሪክ ነው። በእርግጥም እነዚህና ሌሎቹም የናቹራሊዝም ፍልስፍና አፈታሪኮች አንድ ዓይነት ክብር ተሰጥቷቸዋል። እነዚህን ፍልስፍናዎች በተከበሩ ሰዎች ፊት የሚያክፋፋ ሰው የለም። ይሁን እንጂ እንዲሁ በደፈናው የሚቀበልም ሊኖር አይገባም።”—ኦሪጂንስ ሪሰርች

“ብዙ ሳይንቲስቶች በግላቸው ሕይወት እንዴት ጀመረ ለሚለው ጥያቄ ሳይንስ ምንም መልስ እንደሌለው ያምናሉ። . . . በጣም መሠረታዊ በሆነው የሕይወት ደረጃ እንኳን የሚታየው እጅግ የረቀቀ ውስብስብ ባሕርይ ዳርዊን ፈጽሞ ያላለመው ነገር ነበር።”—ዳርዊንስ ብላክ ቦክስ

“ሞለኪውላዊ አዝጋሚ ለውጥ በሳይንሳዊ መረጃዎች ላይ የተመሠረተ ነገር አይደለም። . . . እንዲህ ዓይነቱ አዝጋሚ ለውጥ እንደተከናወነ ይነገር እንጂ አንድም በምርምር ወይም በስሌት የተረጋገጠ ነገር የለም። ሞለኪውላዊ አዝጋሚ ለውጥ ሲከናወን በተግባር ያየ አንድም ሰው ባለመኖሩና እንዲህ ያለ ነገር ተከናውኗል ለማለት የሚያስችል ማስረጃ ስለ ሌለ ሞለኪውላዊ አዝጋሚ ለውጥ ተካሂዷል የሚለው የዳርዊናውያን አባባል እንዲሁ ከንቱ ልፈፋ ብቻ ነው . . . ሊባል ይችላል።”—ዳርዊንስ ብላክ ቦክስ

[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

አዝጋሚ ለውጥ “የዕድል ጨዋታ”

በእርግጥም የአዝጋሚ ለውጥ ንድፈ ሐሳብ ከቁማርተኞች ሕልም ተለይቶ አይታይም። ለምን? ምክንያቱም የአዝጋሚ ለውጥ አማኞች እንደሚሉት ከሆነ ይህ ንድፈ ሐሳብ እጅግ ብዙ እንከኖች ቢኖሩበትም ድል ያደርጋል።

ሮበርት ኔይ እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል:- “አዝጋሚ ለውጥ በአንደኛ ደረጃ የዕድል ጨዋታ በመሆኑ ቀላል መስላ የምትታይ አንዲት ድርጊት ተፈጽማ ቢሆን ኖሮ ለውጡ ወደ ሰው ልጅ ደረጃ ከመድረሱ በፊት ልታጨናግፈው ትችል ነበር።” ይሁን እንጂ በተቃራኒው እያንዳንዱ አጋጣሚ በሚልዮን ለሚቆጠር ጊዜ ያህል ግቡን መትቷል። ኔይ እንደሚከተለው ሲሉ ሳይሸሽጉ ተናግረዋል:- “የአዝጋሚ ለውጥ ሂደት በተከታታይ የሚገጥሙት ከባድ ችግሮች የማሰብ ችሎታ ያለው ሕያው ነገር መገኘቱ በአንድ ወቅት ሳይንቲስቶች ያስቡት የነበረውን ያህል ቀላል እንዳልሆነ የሚያረጋግጡ ናቸው። ምናልባትም ሳይንቲስቶቹ ገና ያላጋጠሟቸው ሌሎች እንቅፋቶች ሊኖሩ ይችላሉ።”

[በገጽ 8, 9 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

ቀለል ብሎ የቀረበ የአንድ ህዋስ ሥዕላዊ መግለጫ

መካነ ፕሮቲን (Ribosomes)

ፕሮቲኖች የሚሠሩበት ክፍል

ቤተህዋስ (Cytoplasm)

በኑክለሱና በህዋስ ክርታሱ መካከል ያለ ቦታ

ህዋስ ሰናስልት (Endoplasmic reticulum)

በላያቸው የተጣበቁት መካነ ፕሮቲኖች የሚሠሩትን ፕሮቲን የሚያጓጉዙ ወይም የሚያከማቹ ገለፈቶች

ኑክለስ

የህዋሱን እንቅስቃሴ የሚቆጣጠር ማዕከል ነው

ኑክሎለስ

መካነ ፕሮቲኖች የሚሠሩበት ቦታ

ሃብለበራሂ (Chromosomes)

የህዋሱ በራሂያዊ ዋና ንድፍ የሆነው ዲ ኤን ኤ የሚገኝበት ክፍል

ፊኝት (Vacuole)

ውኃ፣ ጨው፣ ፕሮቲን እንዲሁም ካርቦሃይድሬት ያከማቻል

አፈራራሽ ክፍለ ህዋስ (Lysosome)

ለማብላላት የሚረዱ ኢንዛይሞችን ያከማቻል

የጎልጂ ዕቃ (Golgi body)

በህዋሱ ውስጥ የተሠሩትን ፕሮቲኖች አሽገው የሚያከፋፍሉ የገለፈት ከረጢቶች

ህዋስ ክርታስ

ማእከሊት (Centriole)

ህዋሱ እንዲባዛ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደርጋል

ኃይለ ህዋስ (Mitochondrion)

ህዋሱ የሚያስፈልገውን ኃይል የሚያቀርቡት ኤ ቲ ፒ የተባሉ ሞለኪውሎች የሚመረቱበት ማዕከል

[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የተነጣጠሉት ክፍሎች የአይጥ ወጥመድ አይወጣቸውም—የአይጥ ወጥመድ እንዲሆኑ ከተፈለገ ሙሉ በሙሉ መገጣጠም አለባቸው

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ