የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • g98 11/8 ገጽ 4-9
  • ችግሩ ይበልጥ አሳሳቢ የሆነባቸው ቦታዎች

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ችግሩ ይበልጥ አሳሳቢ የሆነባቸው ቦታዎች
  • ንቁ!—1998
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • አንዳንዶች ሲኖራቸው ሌሎች ግን የላቸውም
  • የአሥርተ ዓመት ተስፋ
  • የሕዝብ ቁጥር ሲያድግ ፍጆታውም የዚያኑ ያህል ይጨምራል
  • ብክለት
  • የተበከለ ውኃ፣ የጤና መታወክ
  • ወንዞችን መጋራት
  • የዘላለም ሕይወት የሚያስገኝ የውኃ ምንጭ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2008
  • መፍትሔው ምንድን ነው?
    ንቁ!—1998
  • መጽሐፍ ቅዱስ በዓለም ላይ ስለተከሰተው የውኃ እጥረት ምን ይላል?
    ተጨማሪ ርዕሰ ጉዳዮች
  • ውኃ ለፕላኔታችን እጅግ አስፈላጊ የሆነ ነገር
    ንቁ!—1998
ለተጨማሪ መረጃ
ንቁ!—1998
g98 11/8 ገጽ 4-9

ችግሩ ይበልጥ አሳሳቢ የሆነባቸው ቦታዎች

በዩናይትድ ስቴትስ የምትኖረው ሜሪ ጠዋት እንደተነሳች ገላዋን ትታጠባለች፣ ውኃው ያለማቋረጥ እየፈሰሰ ጥርሷን ትፍቃለች፣ በመጸዳጃው ውስጥ ውኃ ትለቃለች፣ ከዚያም እጆቿን ትታጠባለች። ቁርስ ለመብላት ማዕድ ፊት ከመቅረቧ በፊት እንኳ አንድ መለስተኛ የመታጠቢያ ገንዳ ሊሞላ የሚችል ውኃ ልትጠቀም ትችላለች። ምሽት ላይ ሜሪ በዩናይትድ ስቴትስ የሚኖሩ ሌሎች ብዙ ሰዎች እንደሚያደርጉት ሁሉ እሷም ስትጠቀምበት የዋለችው ውኃ ቢለካ 350 ሊትር የሚደርስ ሲሆን ይህ ደግሞ አንድ የመታጠቢያ ገንዳን ሁለት ከግማሽ ጊዜ ሊሞላ የሚችል ነው። ንጹሕና የተትረፈረፈ ውኃ ቤቷ ውስጥ ባለ ቧንቧ በቀላሉ ማግኘት ትችላለች። ሁልጊዜ እንደ ልቧ ስለምታገኝ ከምንም አትቆጥረውም።

በምዕራብ አፍሪካ የምትኖረው ዴዴ ያለችበት ሁኔታ ግን ፈጽሞ የተለየ ነው። ጎህ ከመቅደዱ በፊት ከእንቅልፏ ተነስታ ልብሷን ትለባብስና አንድ ትልቅ ባሊ ጭንቅላቷ ላይ አስተካክላ አስቀምጣ ስምንት ኪሎ ሜትር ያህል በመጓዝ በአቅራቢያ ወዳለው ወንዝ ትሄዳለች። እዚያም እንደ ደረሰች ገላዋን ታጥባ ባሊዋን ከሞላች በኋላ ወደ ቤቷ ትመለሳለች። በየዕለቱ ይህን ተግባር ለማከናወን አራት ሰዓት ያህል ይወስድባታል። ከዚያ በኋላ ባለው ሰዓት ጥገኛ ተውሳኮቹን ለማስወገድ ውኃውን ታጣራና በሦስት የተለያዩ ዕቃዎች ውስጥ ታስቀምጠዋለች፤ አንደኛውን ለመጠጥ፣ ሁለተኛውን ለቤት ውስጥ ሥራ፣ ሦስተኛውን ደግሞ ማታ ለመታጠቢያ ታውለዋለች። ልብስ ለማጠብ ወንዝ መውረድ የግድ ነው።

“የውኃ እጥረት እየፈጀን ነው” ስትል ዴዴ ትናገራለች። “ከጠዋቱ ክፍለ ጊዜ ውስጥ ግማሹን ውኃ በመቅዳት ብቻ የምናጠፋ ከሆነ ለግብርና ሥራ ወይም ለሌሎች ሥራዎች ምን ያህል ጊዜ ይቀረናል?”

ዴዴ ያለችበት ሁኔታ እንግዳ አይደለም። የዓለም የጤና ድርጅት (WHO) እንዳለው ከሆነ በርቀት ከሚገኙና ብዙውን ጊዜ ከተበከሉ ወንዞች ወይም የውኃ ጉድጓዶች ውኃ ተሸክመው የሚያመጡ በርካታ ሴቶችና ልጆች በአንድ ዓመት ውስጥ የሚያጠፉት ጊዜ አንድ ላይ ሲደመር ከአሥር ሚልዮን ዓመታት ይበልጣል!

አንዳንዶች ሲኖራቸው ሌሎች ግን የላቸውም

ምንም እንኳ ጨዋማ ያልሆነ ውኃ በዓለም ዙሪያ በብዛት የሚገኝ ቢሆንም በእኩል መጠን የተሰራጨ አይደለም። አንዱ ዋነኛ ችግር ይህ ነው። ለምሳሌ ያህል ሳይንቲስቶች ምንም እንኳ በዓለም ላይ ባሉት ሐይቆችና ወንዞች ውስጥ ከሚገኘው ውኃ መካከል 36 በመቶው ያለው በእስያ ውስጥ ቢሆንም ከዓለም ሕዝብ መካከል 60 በመቶው የሚኖረው በዚህ አህጉር ውስጥ እንደሆነ ይናገራሉ። በአንጻሩ በዓለም ላይ የሚገኙት ወንዞች ከያዙት ውኃ 15 በመቶ የሚሆነው በአማዞን ወንዝ ውስጥ የሚገኝ ቢሆንም ከዓለም ሕዝብ መካከል በዚህ ወንዝ ውኃ መጠቀም በሚቻልበት ርቀት ላይ የሚኖረው ሕዝብ 0.4 በመቶ ብቻ ነው። የዝናቡ ስርጭትም ቢሆን እንዲሁ ያልተመጣጠነ ነው። አንዳንድ የምድር ክፍሎች ከዓመት እስከ ዓመት ለማለት ይቻላል፣ ደረቅ ሲሆኑ ሌሎቹ ደግሞ ሁልጊዜ ደረቅ ባይሆኑም እንኳ አልፎ አልፎ በድርቅ ይመታሉ።

በርከት ያሉ ጠበብት የሰው ልጅ በአየር ንብረት ላይ አንዳንድ ለውጦችን ሊያስከትል እንደሚችል ያምናሉ፤ ይህ ደግሞ በዝናብ ላይ ተጽዕኖ ያሳድራል ባይ ናቸው። የደን ምንጠራና መሬቱ ከሚገባው በላይ ለእርሻና ለግጦሽ መዋሉ አፈሩን ራቁቱን ያስቀረዋል። አንዳንዶች እንዲህ ዓይነቱ ሁኔታ በሚከሰትበት ጊዜ የምድር ገጽ ተጨማሪ የፀሐይ ብርሃን ወደ ከባቢ አየር መልሶ ያንጸባርቃል። በውጤቱም ከባቢ አየሩ ይሞቅና ደመናዎች ይበተናሉ፤ የዝናቡም መጠን ይቀንሳል።

በተጨማሪም በደኖች ላይ የሚዘንበው አብዛኛው ዝናብ መጀመሪያ ከዕጽዋት ማለትም ከዛፎች ቅጠሎችና ከቁጥቋጦ የተነነው ውኃ በመሆኑ ጠፍ የሆነ ምድር ለዝናብ መቀነስ ምክንያት ሊሆን ይችላል። በሌላ አነጋገር ዕጽዋት ዝናብን መጥጦ እንደሚይዝ ግዙፍ ስፖንጅ ናቸው ማለት ይቻላል። ዛፎቹና ቁጥቋጦቹ ከተወገዱ የሚተነውና ዝናብ የያዙ ደመናዎችን የሚሠራው ውኃ አነስተኛ ይሆናል።

የሰው ልጅ የሚያደርጋቸው ነገሮች በዝናብ ላይ ምን ያህል ተጽዕኖ ያሳድራሉ የሚለው ጉዳይ አሁንም አከራካሪ ነው፤ ተጨማሪ ምርምር ማድረግ ይጠይቃል። ሆኖም የውኃ እጥረት በሰፊው መዛመቱ ምንም አያጠያይቅም። በአሁኑ ጊዜ እንኳ የውኃ እጥረት የ80 አገሮችን ኢኮኖሚና ጤና አስጊ ሁኔታ ላይ ጥሎታል ሲል የዓለም ባንክ አስጠንቅቋል። በተጨማሪም በአሁኑ ጊዜ ከምድር ነዋሪዎች መካከል 40 በመቶው ማለትም ከሁለት ቢልዮን በላይ የሚሆነው ሕዝብ ንጹሕ ውኃ አያገኝም ወይም የጤና አጠባበቅ የለውም።

ሀብታም አገሮች የውኃ እጥረት ሲገጥማቸው ብዙውን ጊዜ ከባድ ችግሮችን የመወጣት አቅሙ ይኖራቸዋል። ግድቦች ይገነባሉ፣ የተጠቀሙበትን ውኃ መልሰው መጠቀም የሚችሉበትን ብዙ ወጪ የሚጠይቅ ቴክኖሎጂ ይቀይሳሉ፣ ወይም ደግሞ ጨዉን እያስወገዱ የባሕር ውኃ ይጠቀማሉ። ድሃ አገሮች ግን እንዲህ ዓይነቶቹ አማራጮች የሏቸውም። ብዙውን ጊዜ እድገትን የሚገታውንና የምግብ ምርትን የሚቀንሰውን፣ ንጹሕ ውኃን በራሽን የማከፋፈል ዘዴ ይጠቀማሉ፤ አለዚያም ደግሞ በሽታ የሚያዛምተውን ያልተጣራ ውኃ ለመጠቀም ይገደዳሉ። በየቦታው የውኃ ፍጆታ እየጨመረ ሲሄድ የወደፊቱ ሁኔታ እጅግ አሳሳቢ እየሆነ ይሄዳል።

የአሥርተ ዓመት ተስፋ

ኅዳር 10, 1980 ላይ የተባበሩት መንግሥታት ጠቅላላ ጉባኤ ስለ መጪው “ዓለም አቀፋዊ የመጠጥ ውኃ አቅርቦትና የጤና አጠባበቅ አሥርተ ዓመት” በእርግጠኝነት ተናግሮ ነበር። ጉባኤው እንደገለጸው ግቡ በ1990 በታዳጊ አገሮች የሚኖሩ ሰዎች በሙሉ በተሟላ መንገድ ንጹሕ ውኃና የጤና አጠባበቅ እንዲያገኙ ማድረግ ነበር። ከአንድ ቢልዮን በላይ የሚሆኑ ሰዎች ንጹሕ ውኃ እንዲያገኙና ከ750 ሚልዮን በላይ የሚሆኑት ደግሞ የቆሻሻ ማስወገጃዎች እንዲኖሯቸው ለማድረግ የወጣው ወጪ በአሥርተ ዓመቱ ማብቂያ ላይ 134 ቢልዮን የአሜሪካ ዶላር ደርሶ ነበር፤ ይህ ታላቅ እመርታ ነው።

ይሁን እንጂ በማደግ ላይ ባሉ አገሮች ያለው የሕዝብ ቁጥር በ800 ሚልዮን በማሻቀቡ የተገኘው እመርታ ብዙም ለውጥ አላመጣም። በመሆኑም በ1990 ንጹሕ ውኃና በቂ የጤና አጠባበቅ ያላገኙ ከአንድ ቢልዮን የሚበልጡ ሰዎች ነበሩ። ይህ አስቸጋሪ ሁኔታ ስሩ ዘ ሉኪንግ-ግላስ በተባለው የልጆች የተረት መጽሐፍ ላይ የተጠቀሰችው ንግሥት ለአሊስ የነገረቻትን ቃል የሚያስተጋባ ይመስላል:- “ባለሽበት ቦታ ለመቆየት የቻልሽውን ያህል መሮጥ አለብሽ። ወደፊት መግፋት ከፈለግሽ ቢያንስ ቢያንስ አሁን ከምትሮጪው ሁለት እጥፍ መሮጥ አለብሽ!”

የዓለም የጤና ድርጅት እንዳለው ከሆነ ከ1990 ወዲህ ውኃና የጤና አጠባበቅ የሌላቸውን ሰዎች ሁኔታ በማሻሻል ረገድ የታየው አጠቃላይ እድገት “አመርቂ አይደለም።” ሳንድራ ፖስቴል በወርልድ ዎች ኢንስቲትዩት የምርምር ምክትል ፕሬዚዳንት በነበሩበት ወቅት እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል:- “በአሁኑ ጊዜ 1.2 ቢልዮን የሚሆን ሕዝብ ለበሽታ ወይም ለሞት የማያጋልጥ ንጹሕ ውኃ ማግኘት አለመቻሉ ትልቅ የሞራል ድክመት ነው። ይህ የሆነው ከባድ የውኃ እጥረት ተፈጥሮ ወይም የቴክኖሎጂ ችግር ኖሮ ሳይሆን ድሆቹ የሚያስፈልጓቸውን መሠረታዊ ነገሮች የማሟላት ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ኃላፊነት የሚሰማው አካል ባለመኖሩ ነው። በአሁኑ ጊዜ በበለጸገው ዓለም የሚኖረው አብዛኛው ሰው እንደ ቀላል ነገር የሚመለከተውን ንጹሕ የመጠጥ ውኃና ለጤና አጠባበቅ የሚያገለግል የቆሻሻ ማስወገጃ ለመላው የሰው ዘር ለማሟላት በየዓመቱ ተጨማሪ 36 ቢልዮን የአሜሪካ ዶላር ገደማ ማውጣት የሚያስፈልግ ሲሆን ይህ አኃዝ በግምት በዓለም አቀፍ ደረጃ ለወታደራዊ ጉዳዮች ከሚወጣው ወጪ መካከል 4 በመቶ ገደማ የሚሆነውን የሚያክል ነው።”

የሕዝብ ቁጥር ሲያድግ ፍጆታውም የዚያኑ ያህል ይጨምራል

የውኃ ስርጭት አለመመጣጠኑ ያስከተለው አሳሳቢ ሁኔታ በሌላ ሁለተኛ ችግር ይበልጥ ተወሳስቧል:- የሕዝብ ቁጥር ሲያድግ የውኃ ፍጆታም የዚያኑ ያህል ያድጋል። በዓለም አቀፍ ደረጃ ያለው የዝናብ መጠን ከሞላ ጎደል ሁልጊዜ ተመሳሳይ ሲሆን የሕዝብ ቁጥር ግን ያሻቅባል። የውኃ ፍጆታ በዚህ መቶ ዘመን ቢያንስ ቢያንስ በሁለት እጥፍ ያደገ ሲሆን አንዳንዶች በቀጣዮቹ 20 ዓመታት ውስጥ እንደገና በእጥፍ እንደሚጨምር ይገምታሉ።

እርግጥ ነው፣ የሕዝብ ቁጥር ሲያድግ የመጠጥ ውኃ ብቻ ሳይሆን የምግብ ፍጆታም የዚያኑ ያህል ይጨምራል። የእህል ምርት ደግሞ በበኩሉ ከምንጊዜውም የበለጠ ውኃ ይፈልጋል። ይሁን እንጂ ኢንዱስትሪዎችና ሰዎች የግብርናውን መስክ የውኃ ፍጆታ እየተቀናቀኑ ይገኛሉ። ከተሞችና የኢንዱስትሪ ተቋሞች እየሰፉ ሲሄዱ ብዙውን ጊዜ የግብርናው መስክ እየተጎዳ ይሄዳል። “ምግቡ ከየት ሊመጣ ነው?” ሲሉ አንድ ተመራማሪ ጥያቄ አቅርበዋል። “የ5 ቢልዮን ሕዝብን ፍላጎት ማሟላት በተቸገርንበት በአሁኑ ወቅት ለግብርናው ሥራ የሚውለውን ውኃ እየወሰድን ከሆነ ወደፊት የ10 ቢልዮን ሕዝብን ፍላጎት ልናሟላ የምንችለው እንዴት ነው?”

አብዛኛው የሕዝብ ቁጥር ጭማሪ የሚታየው በማደግ ላይ ባሉ አገሮች ውስጥ ነው፤ በእነዚህ አገሮች ደግሞ በአሁኑ ጊዜም እንኳ በአብዛኛው የውኃ እጥረት አለ። የሚያሳዝነው ደግሞ እነዚህ አገሮች ችግሩን ለመቋቋም የሚያስችል የገንዘብ አቅሙም ሆነ የቴክኒክ ብቃቱ እምብዛም የላቸውም።

ብክለት

ከውኃ እጥረትና ከጊዜ ወደ ጊዜ ቁጥሩ እየጨመረ የመጣው ሕዝብ ፍጆታው ከማደጉ በተጨማሪ ሌላ ተዛማጅ ችግርም አለ:- ይኸውም ብክለት ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ‘ሕይወት ውኃ ወንዝ’ የሚናገር ቢሆንም እንኳ በዛሬው ጊዜ ያሉት ብዙዎቹ ወንዞች የሞት ወንዞች ሆነዋል። (ራእይ 22:1) በአንድ ግምታዊ ዘገባ መሠረት ከኢንዱስትሪዎችና ከየቤቱ እየወጣ በዓለም ላይ ወዳሉት ወንዞች በየዓመቱ የሚገባው ቆሻሻ ውኃ 450 ኪዩቢክ ኪሎ ሜትር ይሆናል። ብዙዎቹ ወንዞችና ጅረቶች ከመነሻቸው እስከ መድረሻቸው ድረስ የተበከሉ ናቸው።

በዓለም ዙሪያ በማደግ ላይ በሚገኙ አገሮች ያሉ ትላልቅ ወንዞች በሙሉ ለማለት ይቻላል በቆሸሹ ፍሳሾች ይበከላሉ። በሩስያ በሚገኙ 200 ትላልቅ ወንዞች ላይ የተካሄደው ጥናት እንደሚያሳየው ከአሥሩ ወንዞች መካከል ስምንቱ እጅግ አደገኛ በሆነ መጠን የባክቴሪያና የቫይረስ ተሸካሚ ነፍሳት የሞሉባቸው ናቸው። እጅግ በበለጸጉ አገሮች የሚገኙ ወንዞችና መሬት ውስጥ ያለው ውኃ በፍሳሽ የተበከሉ ባይሆንም እንኳ ብዙውን ጊዜ ከእርሻ ማዳበሪያዎች የሚወጣውን መርዝ ጨምሮ በመርዛማ ኬሚካሎች ይመረዛሉ። በሁሉም የዓለም ክፍሎች ማለት ይቻላል፣ በባሕር አጠገብ የሚገኙ አገሮች ቆሻሻ ፍሳሾቻቸው በባሕር ዳርቻዎች በሚገኙ ጥልቀት የሌላቸው ውኃዎች ውስጥ እንዲፈስሱ ያደርጋሉ፤ ይህ ደግሞ የባሕር ዳርቻዎችን ክፉኛ ይበክላል።

ስለዚህ የውኃ ብክለት ዓለም አቀፋዊ ችግር ሆኗል። የኦደቤን ማኅበር ያሳተመው ወተር:- ዚ ኢሴንሻል ሪሶርስ የተባለው ቡክሌት እንዲህ በማለት ሁኔታውን ጠቅለል አድርጎ ያስቀምጠዋል:- “ከሰው ዘር መካከል አንድ ሦስተኛ የሚሆነው የተበከለ ውኃ በሚያስከትለው ሕመም ያለማቋረጥ እየማቀቀ ይገኛል፤ ሌላው አንድ ሦስተኛ የሚሆነው ኅብረተሰብ ደግሞ የረጅም ጊዜ ጠንቃቸው ምን እንደሆነ የማይታወቅ ኬሚካላዊ ንጥረ ነገሮች ከውኃ ጋር በመቀላቀላቸው ለከፍተኛ አደጋ ተጋልጧል።”

የተበከለ ውኃ፣ የጤና መታወክ

ቀደም ሲል የተጠቀሰችው ዴዴ “የውኃ ችግር እየፈጀን ነው” ብላ ስትናገር ምሳሌያዊ አነጋገር መጠቀሟ ነበር። ሆኖም ጨው አልባ የሆነ ንጹሕ ውኃ አለማግኘት ቃል በቃል ሊገድል ይችላል። እሷም ሆነች እሷን የመሰሉ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች የጅረቶችንና የወንዞችን ውኃ ከመጠቀም ሌላ አማራጭ የላቸውም፤ እነዚህ ወንዞች ደግሞ ብዙውን ጊዜ ክፍት ከሆኑ የቆሻሻ ፍሳሽ መውረጃዎች ተለይተው የሚታዩ አይደሉም። የዓለም የጤና ድርጅት እንደገለጸው በየስምንት ሴኮንዱ አንድ ሕፃን ከውኃ ጋር በተያያዘ በሽታ ሳቢያ መሞቱ እምብዛም የሚያስደንቅ አይደለም!

ወርልድ ዎች የተባለው መጽሔት እንዳለው ከሆነ በታዳጊ አገሮች ውስጥ ካሉት በሽታዎች ሁሉ 80 በመቶ የሚሆኑት የሚዛመቱት ንጹሕ ያልሆነ ውኃ በመጠቀም ነው። ውኃ ወለድ በሆኑ በሽታ አምጪ ቫይረሶች ወይም ባክቴሪያዎች እንዲሁም በብክለት ሳቢያ በየዓመቱ 25 ሚልዮን ሰዎች ይሞታሉ።

የተቅማጥ በሽታን፣ ኮሌራንና የአንጀት ተስቦን የመሳሰሉ ከውኃ ጋር የተያያዙ ቀሳፊ በሽታዎች በአብዛኛው ሰለባ የሚያደርጉት በሐሩር ክልል የሚኖሩ ሰዎችን ነው። ሆኖም ውኃ ወለድ በሽታዎች የሚገኙት በታዳጊ አገሮች ውስጥ ብቻ አይደለም። በ1993 በዩናይትድ ስቴትስ ሚልዎኪ ዊስካንሰን ውስጥ 400,000 የሚሆኑ ሰዎች ክሎሪንን የመቋቋም አቅም ያለው ሚክሮብ ያለበትን የቧንቧ ውኃ ከጠጡ በኋላ ታመው ነበር። በዚያው ዓመት እንደ ዋሽንግተን ዲ ሲ፣ ኒው ዮርክ ሲቲና ካቡል፣ ሚዙሪ ባሉት ሌሎች የዩናይትድ ስቴትስ ከተሞች የውኃ መስመሮች ውስጥ አደገኛ ሚክሮቦች መግባት በመጀመራቸው ነዋሪዎች በቧንቧ የሚመጣውን ውኃ አፍልተው ለመጠቀም ተገደው ነበር።

ወንዞችን መጋራት

የውኃ እጥረት ያስከተላቸው እርስ በርሳቸው የተጣመሩ ችግሮች፣ የሕዝቡ ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ሲሄድ ፍጆታውም የዚያኑ ያህል መጨመሩና የጤና መታወክን የሚያስከትለው ብክለት ውጥረትና ግጭት እንዲፈጠር ሊያደርጉ የሚችሉ ነገሮች ናቸው። ውኃ ደግሞ የቅንጦት ዕቃ አይደለም። ከውኃ ችግር ጋር ትንቅንቅ የገጠሙ አንድ ስፔናዊ ፖለቲከኛ “ይህ ኢኮኖሚያዊ ትግል ሳይሆን በሕይወት ለመኖር የሚደረግ ግብግብ ነው” ብለዋል።

ውጥረት በይበልጥ የሚነግሠው የወንዞችን ውኃ በሚጋሩ አካባቢዎች ነው። በዩናይትድ ስቴትስ የሚኖሩ ፒተር ግላይክ የተባሉ አንድ ተመራማሪ ከዓለም ሕዝብ መካከል 40 በመቶ የሚሆነው የሚኖረው በ250 ወንዞች ዳርቻዎች ሲሆን የእነዚህን ወንዞች ውኃ ከአንድ በላይ የሆኑ አገሮች ይጋራሉ። ብራማፑትራ፣ ኢንደስ፣ ሜኮንግ፣ ኒጀር፣ ናይልና ጤግሮስ የተባሉት ወንዞች እያንዳንዳቸው ብዙ አገሮችን አቋርጠው የሚፈስሱ ሲሆን እነዚህ አገሮች የቻሉትን ያህል ከእነዚህ ወንዞች እየቀነሱ መጠቀም ይፈልጋሉ። በመሆኑም የተለያዩ ውዝግቦች ሲካሄዱ ቆይተዋል።

የውኃ ፍጆታ እየጨመረ ሲሄድ እንዲህ ዓይነቱ ውጥረትም እያየለ ይሄዳል። በዓለም ባንክ ሥር ሆኖ በአካባቢ ላይ ጉዳት የማያስከትል ልማት የሚያካሂደው ድርጅት ምክትል ፕሬዚዳንት “በዚህ መቶ ዘመን ብዙዎቹ ጦርነቶች የተካሄዱት የነዳጅ ዘይት ባስነሳው ውዝግብ ሳቢያ ነው፤ በሚቀጥለው መቶ ዘመን ግን አብዛኞቹ ጦርነቶች የሚካሄዱት ውኃ በሚያስነሳው ውዝግብ ይሆናል” ሲሉ ተንብየዋል።

[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

በጉዞ ላይ ያለ ሞሊኪውል

አንድ ነጠላ ሞሊኪውል መጨረሻ የሌለውን ጉዞ ሲያደርግ እስቲ እንመልከት። በጽሑፍ ከሰፈረው ሐሳብ ጋር በቁጥር የተዛመዱት ሥዕሎች አንድ የውኃ ሞሊኪውል ወደ ቀድሞ ቦታው ለመመለስ ከሚከተላቸው ስፍር ቁጥር የሌላቸው ፈለጎች አንዱን ብቻ የሚያሳዩ ናቸው።—ኢዮብ 36:27፤ መክብብ 1:7

በውቅያኖስ ወለል ላይ በሚገኝ አንድ ሞሊኪውል እንጀምራለን።(1) ውኃው በፀሐይ ኃይል ሲተን ሞሊኪውሉ ተነስቶ ከመሬት ብዙ ሺህ ጫማ ርቆ ይሄዳል።(2) ከዚያም ከሌሎች የውኃ ሞሊኪውሎች ጋር ይደባለቅና አንድ ትንሽ ጠብታ ውኃ ይሠራል። ጠብታው በንፋስ እየተገፋ በመቶ የሚቆጠሩ ኪሎ ሜትሮች ይጓዛል። ከጊዜ በኋላ ጠብታው ይተንና ሞሊኪውሉ እንደገና ወደ ላይ ተነስቶ ወደ መሬት ለመውደቅ የሚያስችል መጠን ካለው ከአንድ የዝናብ ጠብታ ጋር ይገናኛል።(3) የዝናብ ጠብታው በቢልዮን ከሚቆጠሩ ሌሎች የዝናብ ጠብታዎች ጋር በአንድ ኮረብታ አጠገብ ይወድቃል፤ ውኃው ወደ አንድ ጅረት ይወርዳል።(4)

ከዚያም አንድ አጋዘን ከጅረቱ ውኃ ሲጠጣ ሞሊኪውሉን ወደ ሰውነቱ ያስገባል።(5) ከሰዓታት በኋላ አጋዘኑ ሲሸና ሞሊኪውሉ ከመሬት ጋር ይደባለቅና የአንድ ዛፍ ሥሮች ይወስዱታል።(6) ከዚያም ሞሊኪውሉ ወደ ዛፉ አናት ይጓዝና በመጨረሻ ከቅጠሉ ላይ ወደ አየር ይተናል።(7) ልክ እንደ በፊቱ አሁንም አንዲት ሌላ ትንሽ ጠብታ ለመሥራት ወደ ላይ ይወጣል። ጠብታው በጣም ከጠቆረ ከባድ የዝናብ ደመና ጋር እስኪገናኝ ድረስ በንፋስ ኃይል ይጓዛል።(8) ሞሊኪውሉ እንደገና ከዝናብ ጋር አብሮ ይወርዳል፤ ሆኖም በዚህ ጊዜ ወደ አንድ ወንዝ ይገባና ከውቅያኖስ ጋር ይደባለቃል።(9) እዚያ ከገባ በኋላ ወደ ውቅያኖሱ ወለል እስኪወጣ፣ እስኪተንና እንደገና አየር ወለድ እስኪሆን ድረስ ብዙ ሺህ ዓመታት ሊወስድበት ይችላል።(10)

ዑደቱ ማብቂያ የለውም:- ውኃ ከባሕር ይተናል፣ ከምድር በላይ ይጓዝና ዝናብ ሆኖ ይወርዳል፤ ከዚያም ተመልሶ ከባሕሩ ጋር ይደባለቃል። በዚህ መንገድ ውኃ በምድር ላይ ያለውን ሕይወት ሁሉ ጠብቆ ያቆያል።

[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

ሲሰነዘሩ የቆዩ ሐሳቦች

ጨውን የሚያስወግዱ ተቋሞችን መገንባት። እነዚህ ተቋሞች በባሕር ውኃ ውስጥ የሚገኘውን ጨው ያስወግዳሉ። ብዙውን ጊዜ ይህ የሚደረገው ውኃውን በፓምፕ ስቦ ዝቅተኛ ግፊት ወዳላቸው ፉካዎች በመጨመር ነው፤ በዚያም ውኃው እስኪፈላ ድረስ እንዲሞቅ ይደረጋል። የጨዉን ቡረሌ በማስቀረት ውኃው እየተነነ ወደተፈለገው አቅጣጫ እንዲሄድ ይደረጋል። ይህ ከፍተኛ ወጪ የሚጠይቅ ሂደት በመሆኑ ከብዙዎቹ ታዳጊ አገሮች አቅም በላይ ነው።

የበረዶ አለቶችን ማቅለጥ። አንዳንድ ሳይንቲስቶች ከጨው የጠራ ንጹሕ ውኃ የያዙ ግዙፍ የበረዶ አለቶችን በትልልቅ ጎታች ጀልባዎች አማካኝነት ከአንታርክቲክ ጎትቶ ወስዶ በማቅለጥ በደቡባዊ ንፍቀ ክበብ ለሚገኙ ደረቅ አገሮች ውኃ ማቅረብ ይቻላል ብለው ያምናሉ። አንዱ ችግር እያንዳንዱ የበረዶ አለት የታሰበበት ቦታ ከመድረሱ በፊት ግማሽ በግማሽ በባሕር ላይ የሚቀልጥ መሆኑ ነው።

ከውኃ ያዠንብር ውኃ ማውጣት። ውኃ ያዠንብሮች (aquifers) መሬት ውስጥ የሚገኙ ውኃ የያዙ አለቶች ናቸው። እጅግ ደረቅ በሆኑ በረሃማ ሥፍራዎች እንኳ ሳይቀር ከእነዚህ አለቶች ውኃ ማውጣት ይቻላል። ሆኖም ከእነዚህ አለቶች ውኃ ማውጣት ከፍተኛ ወጪ የሚጠይቅ ከመሆኑም በላይ ውኃ የሚገኝበትን ወለል ያርቀዋል። ሌላው ጉዳት ደግሞ አብዛኞቹ ውኃ ያዠንብሮች ወደ ቀድሞ ሁኔታቸው ለመመለስ ብዙ ጊዜ የሚወስድባቸው ሲሆን እንዲያውም አንዳንዶቹ ውኃ አልባ እንደሆኑ ይቀራሉ።

[ምንጭ]

ፎቶ:- Mora, Godo-Foto

[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ውኃ መቅዳት በየዕለቱ አራት ሰዓት ያህል ሊወስድ ይችላል

[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በየዓመቱ 450 ኪዩቢክ ኪሎ ሜትር የሚሆን ፍሳሽ ወደ ወንዞች ይገባል

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ