መፍትሔው ምንድን ነው?
ኤክስፐርቶች የሰው ልጅ በገጠሙት ውስብስብ የውኃ ችግሮች ላይ የጦፈ ክርክር ያደርጋሉ። የዓለም ባንክ በሚቀጥሉት አሥር ዓመታት ለጤና አጠባበቅና ለውኃ ፕሮጄክቶች 600 ቢልዮን የአሜሪካ ዶላር ማዋል ይፈልጋል። ይህን መዋዕለ ንዋይ ለዚህ ፕሮጄክት አለማዋሉ የከፋ ወጪ ሊያስከትል ይችላል። ለምሳሌ ያህል በቅርቡ በፔሩ በተበከለ ውኃ ሳቢያ ለአሥር ሳምንታት ሲዛመት የቆየው የኮሌራ ወረርሽኝ 1 ቢልዮን ዶላር ገደማ የሚደርስ ወጪ አስከትሏል፤ ይህ በ1980ዎቹ ዓመታት በሙሉ አገሪቱ ለውኃ አቅርቦት ካዋለችው መዋዕለ ንዋይ ጋር ሲነፃፀር ሦስት እጥፍ ይበልጣል።
ሆኖም ብዙውን ጊዜ የውኃ ፕሮጀክቶችን የሚያስፋፉ ሰዎች ምንም ያህል ጥሩ ዓላማ ይዘው ቢነሱ እነዚህ ፕሮጀክቶች በድህነት ማጥ ውስጥ ለሚገኙት ሰዎች እምብዛም የሚፈይዱት ነገር የለም። በማደግ ላይ ባለው ዓለም ውስጥ በሚገኙት ትልልቅ ከተሞች የሚታየው የሕዝብ ቁጥር ጭማሪና የከተሞቹ እድገት እጅግ ፈጣን ከመሆኑም በላይ ምስቅልቅሉ የወጣ ነው። ድሆቹ የቧንቧ ውኃና የጤና አጠባበቅ በሌላቸው በጣም የተጨናነቁ ደሳሳ ጎጆች ውስጥ ይኖራሉ። መንግሥት በዝቅተኛ ዋጋ የሚሰጠውን የውኃ አገልግሎት ስለማያገኙ ከግል ቸርቻሪዎች በውድ ዋጋ ለመግዛት ይገደዳሉ፤ ለዚያውም ቆሻሻ ውኃ።
በግልጽ መረዳት እንደሚቻለው ዓለም አቀፋዊው የውኃ ችግር የተወሳሰበ ከመሆኑም በላይ ለዚህ አስተዋጽኦ ያደረጉት ነገሮች እርስ በርስ የተዛመዱ ናቸው:- የውኃ እጥረት፣ ብክለት፣ ድህነት፣ በሽታና ከጊዜ ወደ ጊዜ ቁጥሩ እያደገ የሄደው ሕዝብ የውኃ ፍጆታ መጨመር። በተጨማሪም ሰዎች እነዚህን ችግሮች ለመፍታት እንደማይችሉ ግልጽ ነው።
ተስፋ ለመጣል የሚያስችል መሠረት
ይሁን እንጂ የወደፊቱ ጊዜ ብዙዎች እንደሚተነብዩት ተስፋ አስቆራጭ አይደለም። ለምን? ምክንያቱም የዓለምን የውኃ ችግር ለመፍታት የሚያስችለው መፍትሔ ያለው በሰው ሳይሆን በአምላክ እጅ ውስጥ በመሆኑ ነው። ሁሉንም ዓይነት የውኃ ችግሮች ለመፍታት ችሎታውም ሆነ ፍላጎቱ ያለው እርሱ ብቻ ነው።
ይሖዋ አምላክ እነዚህን ችግሮች ሊፈታቸው እንደሚችል ምንም አያጠያይቅም። እርሱ የምድር ብቻ ሳይሆን በላይዋ ላይ ያለው ውኃ ንድፍ አውጪና ፈጣሪ ነው። አስደናቂውን የውኃ ዑደትና ሕይወት በምድር ላይ እንዲኖር ያስቻሉትን ሌሎች የተፈጥሮ ዑደቶች በሙሉ ሥራ ላይ ያዋለው እሱ ነው። ራእይ 14:7 ይሖዋን ‘ሰማይንና ምድርንም ባሕርንም የውኃንም ምንጮች የሠራ’ ሲል ይገልጸዋል።
ይሖዋ በዓለም ዙሪያ ያለውን ውኃ የመቆጣጠር ኃይል አለው። “በምድር ላይ ዝናብን ይሰጣል፣ በእርሻም ላይ ውኃ ይልካል።” (ኢዮብ 5:10) መጽሐፍ ቅዱስ ስለ እርሱ ሲናገር “ምድረ በዳን ለውኃ መቆሚያ፣ ደረቁንም ምድር የውኃ ምንጮች አደረገ” ይላል።—መዝሙር 107:35
ውኃ የመስጠት ችሎታውን በተደጋጋሚ ጊዜያት አሳይቷል። ለምሳሌ ያህል እስራኤላውያን በምድረ በዳ ባሳለፏቸው 40 ዓመታት የሚያስፈልጋቸውን ውኃ ሰጥቷቸዋል፤ አንዳንድ ጊዜ ይህን ያደርግ የነበረው ተአምራዊ በሆነ መንገድ ነበር። መጽሐፍ ቅዱስ “ውኃን ከጭንጫ አወጣ፣ ውኃንም እንደ ወንዞች አፈሰሰ” ይላል። “ዓለቱን መታ፣ ውኆችም ወጡ፣ ወንዞችም ጎረፉ።”—መዝሙር 78:16, 20
አምላክ የሚያደርገው ነገር
አምላክ ይህ የውኃ ችግር ለዘላለም እንዲቀጥል አይፈቅድም። መጽሐፍ ቅዱስ አምላክ በቅርቡ ምድርን በሚቆጣጠረው ሰማያዊ መንግሥቱ ፍቅራዊ አገዛዝ ሥር መኖር ለሚፈልጉ በዓለም ዙሪያ የሚገኙ ሰዎች ሲል እርምጃ የሚወስድበት ጊዜ መቅረቡን ይናገራል።—ማቴዎስ 6:10
ይህ መንግሥት ወይም መስተዳድር ውኃ ወለድ በሽታዎችን ጨምሮ ሁሉንም በሽታዎች ያስወግዳል። መጽሐፍ ቅዱስ ለአምላክ ታማኝ ለሆኑ ሰዎች የሚከተለውን ዋስትና ይሰጣል:- “[አምላክ] እህልህንና ውኃህን ይባርካል፤ በሽታንም ከመካከልህ [ያርቃል]።” (ዘጸአት 23:25) በተጨማሪም ‘ምድርን የሚያጠፉትን በሚያጠፋበት’ ጊዜ የምድርን ውኃ የሚበክሉትንም አብሮ ያጠፋል።—ራእይ 11:18
መላዋ ምድር በአምላክ ፍቅራዊ እንክብካቤ ሥር ሆና ትለመልማለች። ሰዎች ከጨው የጠራ ንጹሕ ውኃ ለማግኘት ሲሉ ዳግመኛ ፍዳቸውን ማየት አያስፈልጋቸውም። ሁልጊዜ እውነት የሚናገረው ሁሉን ቻይ አምላክ የወደፊቱን ጊዜ በተመለከተ ነቢዩ የሚከተለውን ቃል እንዲጽፍ በመንፈሱ አነሳስቶታል:- “በምድረ በዳ ውኃ፣ በበረሀም ፈሳሽ ይፈልቃልና። ደረቂቱ ምድር ኩሬ፣ የጥማት መሬት የውኃ ምንጭ ትሆናለች።”—ኢሳይያስ 35:6, 7፤ ዕብራውያን 6:18
[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
አምላክ “በምድረ በዳ ውኃ . . . ይፈልቃልና። . . . የጥማት መሬት የውኃ ምንጭ ትሆናለች” ሲል ቃል ገብቷል።—ኢሳይያስ 35:6, 7