ፍቅርን የተማረ ሕዝብ
ፍቅር በአድናቆት፣ በደግነት ወይም ደግሞ በጋራ ፍላጎቶች ላይ የተመሠረተ የመውደድ ስሜት ነው። ፍቅር የጠበቀ ዝምድና ነው። ከራስ ወዳድነት ነፃ የሆነ፣ ታማኝና ለሌሎች ሰዎች ጥቅም የሚያስብ ነው። ፍቅር የጥላቻ ተቃራኒ ነው። ጥላቻ ያለበት ሰው ለራሱ ፍላጎት ያደረ ሲሆን አፍቃሪ የሆነ ሰው ግን ለሌሎች ሰዎች ያስባል።
ሕይወትህን የሚገዛው የትኛው ነው? ፍቅር ወይስ ጥላቻ? ዘላለማዊ ተስፋህ በዚህ ጥያቄ መልስ ላይ የተመካ በመሆኑ ይህ ጥያቄ ትልቅ ትርጉም አለው። በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ጥላቻን እየተማረ ባለ ዓለም ውስጥ የሚኖሩ ቢሆኑም እንኳን ፍቅርን እየተማሩ ነው። ይህን እያደረጉ ያሉት አዲሱን ሰውነት በመልበስ ነው። እነዚህ ሰዎች እንዲሁ ስለ ፍቅር የሚያወሩ ሳይሆኑ በተግባር ለማሳየት ከፍተኛ ጥረት የሚያደርጉ ናቸው።
በይሖዋ ምሥክሮች ስብሰባዎች ላይ ተገኝተህ የምታውቅ ከሆነ ባየኸው ነገር ሳትደነቅ አትቀርም። የይሖዋ ምሥክሮች ከተለያዩ ዘሮች የተውጣጡ ቢሆኑም እንኳ በአምልኮ አንድ ሆነዋል። እውነተኛ ዓለም አቀፋዊ የወንድማማች ማኅበር መሥርተዋል። ይህን ሁኔታ በየአካባቢያቸው በሚያካሄዷቸው ስብሰባዎችና በትልልቅ ስብሰባዎቻቸው ላይ መመልከት የሚቻል ቢሆንም በይበልጥ ጎልቶ የሚታየው ግን በቤቴል ቤተሰቦች ውስጥ ነው። የቤቴል ቤተሰቦች መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን በማዘጋጀትና በማሰራጨት እንደ አንድ ቤተሰብ ሆነው አብረው የሚኖሩና የሚሠሩ ፈቃደኛ ሠራተኞችን ያቀፉ ናቸው። ከእነዚህም መካከል አንዳንዶቹ በእያንዳንዱ አገር በይሖዋ ምሥክሮች የሚካሄደውን ሥራ በበላይነት የመምራት ኃላፊነት አለባቸው። በ1997 ሪፖርት መሠረት በ233 አገሮች ውስጥ ከ82,000 በላይ የሚሆኑ ጉባኤዎች ስላሉ ይህ ቀላል ሥራ አይደለም። ይህን ሥራ በብቃት ለማከናወን ዋናውን መሥሪያ ቤትና በ103 አገሮች ውስጥ የሚገኙ የተለያዩ ቅርንጫፍ ቢሮዎችን ጨምሮ በዓለም ዙሪያ ከ16,000 የሚበልጡ ሰዎች በቤቴል ቤተሰቦች ውስጥ ያገለግላሉ።
በአብዛኞቹ የቤቴል ቤተሰቦች ውስጥ የሚያገለግሉት ብዙዎቹ ሰዎች የዚያው ቅርንጫፍ ቢሮው የሚገኝበት አገር ዜጎች ናቸው። ሆኖም እነሱ ብቻ አይደሉም። አንዳንድ የቤቴል ቤተሰቦች የተለያየ ብሔር፣ ጎሣና ዘር ያላቸውን ምሥክሮች ያቀፉ ከመሆናቸውም በላይ እነዚህ ምሥክሮች ቀደም ሲል በተለያዩ ሃይማኖቶች ውስጥ የነበሩ ናቸው። ለምሳሌ ያህል በጀርመን ዜልተርስ ውስጥ በሚገኘው የቤቴል ቤተሰብ የታቀፉት 1,200 ገደማ የሚሆኑ ሰዎች ወደ 30 ከሚጠጉ የተለያዩ ብሔራት የተውጣጡ ናቸው። ከጥላቻ በጠራ መንፈስ በሰላምና በአንድነት እንዲኖሩ እንዲሠሩና እንዲያመልኩ ያስቻላቸው ነገር ምንድን ነው? በቆላስይስ 3:14 ላይ የሚገኘውን የሚከተለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር ስለሚከተሉ ነው:-
“ፍቅርን ልበሱት”
ልብስ ለብሶ የተወለደ ሰው የለም፤ ወይም ደግሞ አንድ ሰው ልብስ መልበስ የሚችለው እንዲሁ ስለ ልብስ በማውራት ብቻ አይደለም። መልበስ እንዳለበት ሊሰማውና ተግባራዊ ጥረት ሊያደርግ ይገባዋል። በተመሳሳይም ፍቅርን ለብሶ የተወለደ ሰው የለም። እንዲሁ ዝም ብሎ ስለ ፍቅር ማውራቱም በቂ አይደለም። ጥረት ማድረግ ያስፈልጋል።
ልብስ መልበስ ለብዙ ዓላማዎች ያገለግላል። ሰውነትን ይጠብቃል፣ ለዓይን የማይማርኩ የአካል ክፍሎችን ወይም እንከኖችን ለመሸፈን ያገለግላል፣ እንዲሁም የአንድን ሰው ስብዕና በተወሰነ ደረጃ ይገልጻል። ፍቅርም እንደዚሁ ነው። አንድ ሰው የጽድቅ መሠረታዊ ሥርዓቶችንና ጥሩ ባልንጀርነትን መውደዱ አደገኛ ሁኔታ ሊያስከትል ከሚችል ባልንጀርነትም ሆነ ቦታ እንዲርቅ ስለሚያደርገው ፍቅር ጥበቃ ሆኖ ያገለግላል። በጣም ውድ አድርገን የምንመለከታቸውን የግል ዝምድናዎች ለመጠበቅ ይረዳል። አፍቃሪ የሆነ ሰው በሌሎች ዘንድም ፍቅርን ያተርፋል፤ ሌሎችን ላለመጉዳት የሚጠነቀቅ ሰው እሱም ከጉዳት ይጠበቃል።
በተጨማሪም ፍቅር ሌሎች ሰዎችን ሊረብሹ የሚችሉ ማራኪ ያልሆኑ ባሕርዮቻችንን ለመሸፈን ያገለግላል። ብዙውን ጊዜ ኩሩዎች፣ እብሪተኞች፣ ራስ ወዳዶችና ፍቅር አልባ ከሆኑ ሰዎች ይልቅ አፍቃሪ የሆኑ ሰዎችን ጉድለቶች ማለፉ አይቀለንምን?
ፍቅርን የለበሱ ሰዎች የክርስቶስ ዓይነት ስብዕና ያለውን ውበት በግልጽ ያሳያሉ። አካላዊ ውበት ውጫዊ ብቻ ሲሆን መንፈሳዊ ውበት ግን የአንድን ሰው መላ ስብዕና የሚወክል ነው። በቁመናቸው ሳይሆን ልባዊ በሆነ ወዳጃዊ ባሕርያቸው ምክንያት ውብ ሆነው የሚታዩህ ሰዎች ይኖሩ ይሆናል። በሌላ በኩል ደግሞ ማርከውን የነበሩ ውብ የሆኑ ሴቶች ወይም ወንዶች እውነተኛ ባሕርያቸው ገሃድ ሲወጣ ለእነርሱ የነበረን ግምት ሁሉ በአንድ ጊዜ ይጠፋል። ፍቅርን ከለበሱ ሰዎች ጋር መሆን ምንኛ የሚያስደስት ነው!
ጥላቻን በፍቅር መተካት
በ1994 በጀርመን በሚገኙ 145,958 የይሖዋ ምሥክሮች ላይ የተካሄደው ጥናት ጥላቻ በፍቅር ሊተካ እንደሚችል በግልጽ የሚያሳይ ነው።
ከልክ በላይ መጠጣት፣ አደገኛ ዕፆችን መውሰድ፣ ወንጀል፣ ቁማርና ፀረ ማኅበራዊ አቋም ወይም የጠበኝነት ባሕርይ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ በቀላሉ ጥላቻን ሊቀሰቅስ የሚችለውን የራስ ወዳድነት ጠባይ የሚያንጸባርቁ ናቸው። ሆኖም ቃለ መጠይቅ ከተደረገላቸው መካከል 38.7 በመቶ የሚሆኑት የይሖዋ ምሥክሮች ከሚደግፏቸው ከፍተኛ የመጽሐፍ ቅዱስ የአቋም ደረጃዎች ጋር ለመስማማት ከላይ ከተጠቀሱት ችግሮች መካከል የተወሰኑትን ማሸነፍ አስፈልጓቸዋል። ለአምላክና እሱ ላወጣቸው የጽድቅ የሥነ ምግባር መሥፈርቶች ያላቸው ፍቅር ይህን እንዲያደርጉ አነሳስቷቸዋል። በግለሰብ ደረጃ የይሖዋ ምሥክሮችን ፍቅራዊ እገዛ ማግኘት ችለዋል። ባለፉት አምስት ዓመታት (1992–1996) በ233 አገሮች የሚገኙ 1,616,894 ሰዎች ሁሉን ድል በሚያደርገው ፍቅር ጥላቻን በማሸነፍ ለውጥ ማድረግ የሚችሉበትን እርዳታ አግኝተዋል።
የይሖዋ ምሥክሮች በትዳራቸው ውስጥ ከራስ ወዳድነት ነፃ የሆነ ፍቅር በማሳየት የማይዋዥቅ ዝምድና ይመሠርታሉ። በአንዳንድ አገሮች ከሁለት ወይም ከሦስት ጋብቻዎች መካከል አንዱ ይፈርሳል። ሆኖም ከላይ የተጠቀሰው ጥናት እንዳመለከተው ከምሥክሮቹ መካከል የተፋቱ ወይም ከትዳር ጓደኞቻቸው የተለያዩ 4.9 በመቶ ብቻ ናቸው። ይሁን እንጂ ከእነዚህ መካከል በርካታዎቹ የተፋቱት የይሖዋ ምሥክሮች ከመሆናቸው በፊት መሆኑ መዘንጋት የለበትም።
የፍቅር አምላክ ለሚወዱት ሁሉ መንገዶቹን የሚያስተምር ታላቅ አስተማሪ በመሆኑ የይሖዋ ምሥክሮች ከሁሉም በፊት ፍቅራቸውን የሚገልጹት ለእሱ ነው። የይሖዋ ምሥክሮች ‘ከእግዚአብሔር ይልቅ ተድላን ከሚወዱ’ ሰዎች በተለየ መልኩ አምላክን ያስቀድማሉ። (2 ጢሞቴዎስ 3:4) ሥርዓት አልበኛ የሆነው ይህ ዓለም ከሚከተለው መንገድ በተለየ ሁኔታ እያንዳንዱ ምሥክር በየሳምንቱ በአማካይ 17.5 ሰዓት ለሃይማኖታዊ እንቅስቃሴዎች ያውላል። ምሥክሮቹ መንፈሳዊ ዝንባሌ እንዳላቸው ግልጽ ነው። ደስተኞች የሚያደርጋቸውም ይኸው ነው። ኢየሱስ “በመንፈሳዊ የጐደላቸው ነገር እንዳለ የሚታወቃቸው ደስተኞች ናቸው። መንግሥተ ሰማያት የእነርሱ ናትና” ብሏል።—ማቴዎስ 5:3 NW
የመዝሙር 118 ጸሐፊ የአምላክ እውነተኛ አገልጋይ ሰዎችን የሚፈራበት ምንም ምክንያት እንደሌለ ገልጿል። “እግዚአብሔር ረዳቴ ነው፣ አልፈራም፤ ሰው ምን ያደርገኛል?” (ቁጥር 6) በአምላክ ሙሉ በሙሉ መታመን ለጥላቻና ሌሎች ሰዎችን ለመፍራት መንስኤ ከሆኑት ነገሮች አንዱን ለማስወገድ ይረዳል።
አንድ ክርስቲያን አምላክ ‘ለቁጣ የዘገየና ፍቅራዊ ደግነቱና እውነቱ የበዛ’ መሆኑን ስለሚያውቅ ለጥላቻ ምክንያት ሊሆን የሚችለውን ቁጣን ለማስወገድ ይጥራል። የዋህነትንና ራስን መግዛትን ጨምሮ የአምላክን መንፈስ ፍሬዎች ማዳበሩ ይህን ማድረግ እንዲችል ይረዳዋል።—መዝሙር 86:15፤ ገላትያ 5:22, 23
አንድ እውነተኛ ክርስቲያን ትሁት ከመሆኑም በላይ ያልሆነውን እንደሆነ አድርጎ በማሰብ ራሱን ከፍ አድርጎ አይመለከትም። (ሮሜ 12:3) ከሌሎች ጋር ባለው ግንኙነት ፍቅርን ያዳብራል። ፍቅር ከጥላቻ በተለየ መልኩ “አይበሳጭም፣ በደልን አይቆጥርም።”—1 ቆሮንቶስ 13:5
አዎን፣ ፍርሃት፣ ቁጣ ወይም ደግሞ በደል ደርሶብኛል የሚለው ስሜት ሰዎች ጥላቻ እንዲያድርባቸው ሊያደርግ ይችላል። ፍቅር ግን ጥላቻን ከሥር መሠረቱ መንግሎ በማስወገድ ድል ያደርጋል። በእርግጥም “እግዚአብሔር ፍቅር” ስለሆነ ፍቅር በአጽናፈ ዓለም ውስጥ ካሉት ኃይሎች ሁሉ ይበልጥ ጠንካራ የሆነ ኃይል ነው።—1 ዮሐንስ 4:8
በቅርቡ ጥላቻ ለዘላለም ይወገዳል
ራስ ወዳድነትና ጥላቻ የይሖዋ አምላክ ባሕርያት ስላልሆኑ ለዘላለም ሊቀጥሉ አይችሉም። መወገድና ለዘላለም ጸንቶ በሚኖረው ፍቅር መተካት አለባቸው። ጥላቻ በሌለበትና ፍቅር በነገሠበት ዓለም ውስጥ ለመኖር የምትጓጓ ከሆነ በዚያ ዓለም ውስጥ ለመኖር የሚያስችሉትን ብቃቶች የይሖዋ ምሥክሮች ከመጽሐፍ ቅዱስ እንዲያብራሩልህ አድርግ።
አዎን፣ እያንዳንዳችን ‘ሕይወቴን የሚገዛው የትኛው ባሕርይ ነው? ፍቅር ነው ወይስ ጥላቻ?’ ብለን መጠየቃችን የተገባ ነው። ይህ በቀላሉ ሊታይ የሚገባው ጥያቄ አይደለም። የጥላቻ አምላክ የሆነውን የአምላክን ባላጋራ የሚከተል ሰው ለረጅም ጊዜ ሊዘልቅ አይችልም። የፍቅር አምላክ የሆነውን ይሖዋን የሚከተል ሰው ግን ለዘላለም ይኖራል!—1 ዮሐንስ 2:15–17
[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በዛሬው ጊዜም እንኳ ሰዎች ፍቅርን ሊለብሱ ይችላሉ