የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • g98 9/8 ገጽ 2-8
  • ጥላቻን የተማረ ዓለም

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ጥላቻን የተማረ ዓለም
  • ንቁ!—1998
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • ከልጆች ይጀምራል
  • ሃይማኖት የሚያስተምረው ምንድን ነው?
  • ፍርሃት፣ ቁጣ ወይም በደል ደርሶብኛል የሚል ስሜት
  • ጥላቻ የሚወገድበት ጊዜ ይኖር ይሆን?
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1995
  • ጥላቻን ማስወገድ የሚቻልበት ብቸኛ መንገድ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2000
  • የአንባቢያን ጥያቄዎች
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2005
  • ጥላቻ የተስፋፋው ለምንድን ነው?
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (ለሕዝብ የሚሰራጭ)—2022
ለተጨማሪ መረጃ
ንቁ!—1998
g98 9/8 ገጽ 2-8

ጥላቻን የተማረ ዓለም

ሰዎች በባሕርያቸው ራስ ወዳድ ናቸው። ራስ ወዳድነት ደግሞ ልጓም ካልተደረገለት ወደ ጥላቻ ሊያመራ ይችላል። በተፈጥሮ የሚወረሰው ራስ ወዳድነት ያነሰ ይመስል ሰብዓዊው ኅብረተሰብ ደግሞ ሰዎች ራስ ወዳድ እንዲሆኑ ያስተምራል!

ሰዎችን በሙሉ በአንድ ዓይን መመልከት ትክክል ላይሆን የሚችልበት ጊዜ ቢኖርም አንዳንድ ዝንባሌዎች ግን በጣም የተስፋፉ በመሆናቸው አልፎ አልፎ ብቻ የሚታዩ ናቸው ተብለው ሊታለፉ የሚችሉ አይደሉም። ብዙውን ጊዜ ፖለቲከኞች የወከሏቸውን ሕዝቦች ከመርዳት ይልቅ አብልጠው የሚያስቡት በምርጫ ስለማሸነፍ አይደለም? ነጋዴዎች ብዙውን ጊዜ የሚጨነቁት ጉዳት የሚያስከትሉ ሸቀጦች ገበያ ላይ እንዳይወጡ ለማድረግ ሳይሆን አስፈላጊ ከሆነ ሕጋዊ ባልሆኑ ዘዴዎች ተጠቅሞም ቢሆን ገንዘብ ስለማጋበስ አይደለም? ቀሳውስት የሚያስቡት መንጎቻቸውን በጥሩ ሥነ ምግባርና በፍቅር ጎዳና ስለመምራት ሳይሆን ተወዳጅነት ስለማትረፍ ወይም ብዙ ገንዘብ ስለማግኘት አይደለም?

ከልጆች ይጀምራል

ልጆች ስድ ተለቀው እንዲያድጉ ሲደረግ ራስ ወዳድ እንዲሆኑ ማሰልጠኛ እየተሰጣቸው ነው ለማለት ይቻላል። ይህ የሚሆንበት ምክንያት የልጅነት ፍላጎቶቻቸውን ለማሟላት ሲሉ ለሌሎች አሳቢ የመሆንንና ራስ ወዳድ ያለመሆንን ባሕርይ አሽቀንጥረው ስለሚጥሉ ነው። በትምህርት ቤቶችና በኮሌጆች ያሉ ተማሪዎች በቀለም ትምህርቶች ብቻ ሳይሆን በስፖርት ጭምር አንደኛ እንዲሆኑ ግፊት ይደረግባቸዋል። ሁልጊዜ “ሁለተኛ መሆን መጨረሻ ከመሆን አይሻልም!” የሚል መፈክር ይነገራቸዋል።

የኃይል ድርጊቶችን ጎላ አድርገው የሚያሳዩ የቪዲዮ ጨዋታዎች ወጣቶች ችግሮችን በራስ ወዳድነት መንፈስ ጠላቶቻቸውን በማስወገድ እንዲፈቱ ያስተምራሉ! እንዲህ ያለው አመለካከት ፍቅር እንዲስፋፋ የሚያግዝ እንዳልሆነ ግልጽ ነው! የቪዲዮ ጨዋታዎች ለልጆች በጣም አደገኛ መሆናቸውን የዩናይትድ ስቴትስ ጤና አጠባበቅ ሚኒስትር ከአሥር ዓመት በፊት አስጠንቅቀው ነበር። “ጠላትህን ረሽን ከማለት በስተቀር ገንቢ የሆነ አንዳች ትምህርት የላቸውም” ብለዋል። ለኒው ዮርክ ታይምስ የተጻፈ አንድ ደብዳቤ ብዙ የቪዲዮ ጨዋታዎች “የሰው ልጅ የአውሬነት ባሕርይ እንዲኖረው የሚያደርጉ ናቸው። አእምሮ የጎደላቸው ግልፍተኛ ጎረምሶችን በብዛት እያመረቱልን ነው” ብሏል። አንድ የቪዲዮ ጨዋታ የሚያዘወትር ጀርመናዊ ወጣት የዚህን አባባል ትክክለኛነት በሐቀኝነት አምኗል። “እነዚህን ጨዋታዎች በምጫወትበት ጊዜ ‘ግደል ወይም ሙት’ የሚለው የቆየ መፈክር ተግባራዊ ወደሚሆንበት የቅዠት ዓለም እገባለሁ” ብሏል።

ጥላቻ ከዘረኝነት ባሕርይ ጋር በሚጣመርበት ጊዜ ይበልጥ አደገኛ ይሆናል። ስለዚህ በባዕድ አገር ሰዎች ላይ፣ በተለይም በቱርኮች ላይ የሚፈጸሙ የኃይል ድርጊቶችን የሚያሳዩ ቀኝ-ዘመም ቪዲዮዎች መኖራቸው ጀርመናውያንን የሚያሳስብ ችግር መሆኑ ትክክል ነው። እስከ ጥር 1, 1994 ባለው ጊዜ በጀርመን አገር ከሚኖሩት 6,878,100 የባዕድ አገር ሰዎች መካከል 27.9 በመቶ የሚሆኑት ቱርኮች ናቸው።

ብሔራዊ ስሜት ልጆችን ከሕፃንነታቸው ጀምሮ የአገርህን ጠላቶች መጥላት ምንም ስህተት የለበትም የሚል ትምህርት ስለሚያስተምራቸው የዘረኝነት ስሜት ሥር እየሰደደ ይሄዳል። ለታይም መጽሔት የሚጽፉ ጆርጅ ኤም ቴበር የተባሉ ሰው ያዘጋጁት አንድ ጽሑፍ እንዲህ ይላል:- “ከፖለቲካ አስተሳሰቦች ሁሉ ጠንካራው ብሔራዊ ስሜት ሳይሆን አይቀርም።” በመቀጠልም እንዲህ ሲሉ ገልጸዋል:- “ከሃይማኖት በስተቀር የብሔረተኝነትን ስሜት ያህል ብዙ ደም ያቃባ ነገር የለም። ባለፉት ብዙ መቶ ዘመናት የፖለቲካ መሪዎች ችግሮቻቸውን ሁሉ ጎረቤታቸው በሆነ አንድ ጎሣ ላይ በማላከክ የአክራሪዎችን ዓመፅ ሲያነሳሱ ኖረዋል።”

በዛሬው ጊዜ በዓለም ላይ ላሉት ለብዙዎቹ ችግሮች መንስኤው ለረጅም ጊዜ የዘለቀ የጎሣ፣ የዘር ወይም የብሔር ጥላቻ ነው። በተጨማሪም የባዕድ አገር ሰዎችን በጥርጣሬና በጥላቻ ዓይን የመመልከት ስሜት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ነው። የሚገርመው ነገር ግን እንዲህ ዓይነቱ ስሜት ይበልጥ ጎላ ብሎ የሚታየው ጥቂት የባዕድ አገር ሰዎች በሚኖሩባቸው አካባቢዎች መሆኑን የጀርመን ማኅበራዊ ጉዳይ አጥኚዎች ደርሰውበታል። ይህም እንዲህ ዓይነቱ ስሜት ብዙውን ጊዜ በግል ሕይወት ላይ በደረሰ ገጠመኝ ሳይሆን ወገናዊ በሆነ ጥላቻ ላይ የተመሠረተ መሆኑን የሚያመለክት ነው። “ወጣቶች ብዙውን ጊዜ ይህ ወገናዊ ጥላቻ የሚያድርባቸው በጓደኞቻቸውና በወላጆቻቸው አማካኝነት” እንደሆነ የማኅበራዊ ጉዳይ አጥኚዎቹ ገልጸዋል። ቃለ መጠይቅ ከተደረገላቸው መካከል 77 በመቶ የሚሆኑት እንዲህ ዓይነቱን ወገናዊ ጥላቻ የሚደግፉ ቢሆንም እንኳ ከባዕድ አገር ሰዎች ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት የሌላቸው ወይም መጠነኛ የሆነ ግንኙነት ያደረጉ ናቸው።

ሁላችንም ፍጹም ካልሆኑት ወላጆቻችን በተወሰነ ደረጃ የራስ ወዳድነት ባሕርይ የወረስን በመሆኑ ራስ ወዳድነትን ማስተማሩ ቀላል ነው። ይሁን እንጂ በፍቅርና በጥላቻ መካከል ባለው ቅራኔ ረገድ ሃይማኖት ምን ሚና ተጫውቷል?

ሃይማኖት የሚያስተምረው ምንድን ነው?

በጥቅሉ ሲታይ ሰዎች ሃይማኖት ፍቅርን ያስፋፋል ብለው ያስባሉ። እንደዚያ ከሆነ በሰሜን አየርላንድ፣ በመካከለኛው ምሥራቅ፣ በሕንድና በሌሎችም ቦታዎች ላለው ውጥረት መንስኤው የሃይማኖት ልዩነቶች የሆኑት ለምንድን ነው? እርግጥ አንዳንድ ሰዎች ለእንዲህ ዓይነቱ ብጥብጥ ምክንያቱ ሃይማኖታዊ ሳይሆን ፖለቲካዊ ልዩነቶች ናቸው ብለው ይከራከራሉ። ይህ አከራካሪ ጉዳይ ነው። በዚያም ሆነ በዚህ ሃይማኖቶች ፖለቲካዊና ጎሣዊ ጥላቻዎችን መቋቋም የሚችል ፍቅር በሰዎች ልብ ውስጥ መትከል ተስኗቸዋል። በመሆኑም በርካታ የካቶሊክ፣ የኦርቶዶክስና የሌላ እምነት ተከታዮች ወደ ጠበኝነት የሚመራውን ወገናዊ ጥላቻ ያሳድራሉ።

አንድ ሰው ትክክል አይደሉም የሚላቸውን የአንድ ሃይማኖት ትምህርቶችና ልማዶች ማስተባበሉ ምንም ስህተት የለውም። ይሁን እንጂ ይህ ሁኔታ በሃይማኖት ቡድኑ ወይም በአባላቱ ላይ የኃይል ድርጊት እንዲፈጽም መብት ይሰጠዋልን? ዚ ኢንሳይከለፒዲያ ኦቭ ሪሊጂን የሚከተለውን ሐቅ በግልጽ አስቀምጧል:- “በመካከለኛው ምሥራቅና በአውሮፓ የሚገኙ ሃይማኖታዊ መሪዎች በሌሎች ሃይማኖቶች ላይ የጥቃት እርምጃ እንዲወሰድ በተደጋጋሚ ትእዛዝ አስተላልፈዋል።”

ይህ ኢንሳይክለፒዲያ የኃይል እርምጃ የሃይማኖት ዋነኛ አካል መሆኑን ሲገልጽ እንዲህ ይላል:- “ግጭት ለማኅበራዊና ለሥነ ልቦናዊ እድገት አስፈላጊ ነው ብለው የሚያምኑት የዳርዊን ተከታዮች ብቻ አይደሉም። ሃይማኖት የማያቋርጥ የግጭትና የጠብ ምንጭ ሆኖ አገልግሏል፤ ይህም ለእድገት አስተዋጽኦ አድርጓል።”

ጠብ ለእድገት አስፈላጊ ነው በሚል ትክክል እንደሆነ አድርጎ ማቅረብ አይቻልም፤ ይህ ሐዋርያው ጴጥሮስ ኢየሱስን ለመታደግ ሲል እርምጃ በወሰደ ጊዜ ኢየሱስ ክርስቶስ ከገለጸው የታወቀ መሠረታዊ ሥርዓት ጋር ይጋጫል። ጴጥሮስ “እጁን ዘርግቶ ሰይፉን መዘዘና የሊቀ ካህናቱን ባሪያ መትቶ ጆሮውን ቈረጠው። በዚያን ጊዜ ኢየሱስ እንዲህ አለው:- ሰይፍ የሚያነሡ ሁሉ በሰይፍ ይጠፋሉና ሰይፍህን ወደ ስፍራው መልስ።”—ማቴዎስ 26:51, 52፤ ዮሐንስ 18:10, 11

ሰዎቹ ጥሩዎችም ሆኑ መጥፎዎች በግለሰቦች ላይ የሚወሰደው የኃይል እርምጃ የፍቅር መንገድ አይደለም። በመሆኑም የኃይል እርምጃ የሚወስዱ ሰዎች ድርጊታቸው አፍቃሪውን አምላክ እንከተላለን የሚለው አባባላቸው ትክክል እንዳልሆነ ያሳያል። ኤሞስ ኦዝ የተባሉ ደራሲ በቅርቡ እንዲህ ብለዋል:- “ሃይማኖታዊ አክራሪዎች . . . በጥቅሉ ሲታይ ከአምላክ ተሰጥቶናል የሚሉት ‘ትእዛዝ’ ሁልጊዜ አንድ ነው። እርሱም ግደል የሚል ነው። የአክራሪዎች አምላክ በይበልጥ ከዲያብሎስ ጋር ይመሳሰላል።”

መጽሐፍ ቅዱስም ተመሳሳይ ሐሳብ ይሰጣል:- “የእግዚአብሔር ልጆችና የዲያብሎስ ልጆች በዚህ የተገለጡ ናቸው፤ ጽድቅን የማያደርግና ወንድሙን የማይወድ ሁሉ ከእግዚአብሔር አይደለም። ወንድሙን የሚጠላ ሁሉ ነፍሰ ገዳይ ነው፣ ነፍሰ ገዳይም የሆነ ሁሉ የዘላለም ሕይወት በእርሱ እንዳይኖር ታውቃላችሁ። ማንም:- እግዚአብሔርን እወዳለሁ እያለ ወንድሙን ቢጠላ ሐሰተኛ ነው፤ ያየውን ወንድሙን የማይወድ ያላየውን እግዚአብሔርን ሊወደው እንዴት ይችላል? እግዚአብሔርንም የሚወድ ወንድሙን ደግሞ እንዲወድ ይህች ትእዛዝ ከእርሱ አለችን።”—1 ዮሐንስ 3:10, 15፤ 4:20, 21

እውነተኛ ሃይማኖት ጠላቶችን እንኳ ሳይቀር ማፍቀርን የሚጨምረውን የፍቅር መንገድ መከተል አለበት። ይሖዋን በተመለከተ እንዲህ እናነባለን:- “እርሱ በክፉዎችና በበጎዎች ላይ ፀሐይን ያወጣልና፣ በጻድቃንና በኃጢአተኞችም ላይ ዝናቡን ያዘንባልና።” (ማቴዎስ 5:44, 45፤ በተጨማሪም 1 ዮሐንስ 4:7–10⁠ን ተመልከት።) የጥላቻ አምላክ ከሆነው ከሰይጣን ምንኛ የተለየ ነው! ሰይጣን ሰዎችን በመማረክና በማታለል በብልግና፣ በወንጀልና በራስ ወዳድነት የተሞላ ሕይወት እንዲመሩ ያደርጋቸዋል፤ ይህ ደግሞ ሕይወታቸው በሥቃይና በመከራ የተሞላ እንዲሆን ያደርገዋል። ይህን የሚያደርገው እንዲህ ዓይነቱ የተበላሸ አኗኗር የኋላ ኋላ ለጥፋት እንደሚዳርጋቸው እያወቀ ነው። የራሱን ተከታዮች መጠበቅ የማይችልና የማይፈልግ እንዲህ ዓይነቱ አምላክ ሊመለክ ይገባዋልን?

ፍርሃት፣ ቁጣ ወይም በደል ደርሶብኛል የሚል ስሜት

እነዚህ ነገሮች ጥላቻ እንደሚቀሰቅሱ የታወቀ ነው። አንድ የታይም ዘገባ እንዲህ ይላል:- “ከ1930ዎቹ አስቸጋሪ ዓመታት ወዲህ በአውሮፓ ውስጥ የሚገኙ የተለያዩ ቀኝ-ዘመም እንቅስቃሴዎች በአሁኑ ጊዜ ያሉትን ጥሩ የሚመስሉ በርካታ አጋጣሚዎች የአሁኑን ያህል መጠቀም የቻሉበት ጊዜ የለም። . . . ሰዎች ሥራቸውን የማጣት ስጋት ስላደረባቸው ተጽዕኖ የማሳደር ኃይል በሌላቸው ለዘብተኛ መንግሥታት ላይ መራራ ቁጣ እያሰሙ ከመሆኑም በላይ በመካከላቸው ያሉትን የባዕድ አገር ሰዎች ለችግሮቻቸው ተጠያቂ እያደረጓቸው ነው።” ዮርግ ሺንድለር ራይኒሸር ሜርኩር/ክሪስት ዩንት ቬልት በተባለው ጋዜጣ ላይ ባለፉት ሁለት አሥርተ ዓመታት ወደ ጀርመን የጎረፉትን በአሥር ሺዎች የሚቆጠሩ የፖለቲካ ስደተኞች አስመልክተው ጽፈዋል። ዘ ጀርመን ትሪቡን “ዘረኝነት በመላው አውሮፓ በመስፋፋት ላይ ነው” ሲል አስጠንቅቋል። የስደተኞች መጉረፍ የጥላቻ ስሜት ይፈጥራል። ሰዎች ‘የገንዘብ ኪሳራ ያስከትሉብናል፣ ሥራ አልባ እያደረጉን ነው፣ በሴቶች ልጆቻችንም ላይ አስጊ ሁኔታ እየፈጠሩ ነው’ እያሉ ሲያማርሩ ይሰማል። ኦክስፎርድ ውስጥ የሚገኘው የሴይንት አንቶኒ ኮሌጅ አባል የሆኑት ቴዎዶር ዜልደን ሰዎች “ጠበኛ የሚሆኑት ስጋት ሲያድርባቸው ወይም ሲዋረዱ ነው። ትኩረት ሊሰጠው የሚገባው ለቁጣቸው መንስኤ የሆነው ነገር ነው” ብለዋል።

ብሪታንያዊቷ የቴሌቪዥን ጋዜጠኛ ጆአን ቤክዌል ዜጎቹን ጥላቻ የሚያስተምረውን ይህን ዓለም ጥሩ አድርገው ገልጸውታል። እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል:- “አጥባቂ ክርስቲያን ባልሆንም እንኳ በኢየሱስ ትምህርት ውስጥ ጥልቅ ትርጉም ያለውና ፍጹም የሆነ እውነት እንዳለ አውቃለሁ:- ክፋት የፍቅር መጥፋት ውጤት ነው። . . . የምንኖረው በፍቅር መሠረተ ትምህርት ላይ እምነት በሌለው ኅብረተሰብ ውስጥ እንደሆነ አውቃለሁ። በጣም አስመሳይ የሆነ ኅብረተሰብ ነው፤ የዋህና ሆደ ቡቡ መሆንን እንዲሁም ቀና አስተሳሰብ መያዝን አይደግፍም። ለራስ ጥቅም ብቻ ከማሰብ ይልቅ ለሌሎች አሳቢ መሆን የሚለውን ሐሳብ አይቀበልም። የንግዱ ዓለም ‘በሐቅ እንሥራ እንጂ’ እያለ ለማስመሰል ይጥራል፤ ያጭበረብራል፤ እንዲሁም ከሥነ ምግባር ውጪ የሆነ ድርጊቱን የሚያጋልጥበትን ማስረጃ ለመሸፋፈን ይሞክራል። እንዲህ ዓይነቱ ዓለም ኅብረተሰቡ ከፍ አድርጎ የሚመለከታቸውን ነገሮች ማለትም ስኬትን፣ በራስ የመተማመንን መንፈስና ደስተኛ ቤተሰብን ማግኘት ያልቻሉ ምንም ያልሰመረላቸውንና ራሳቸውን ከሌሎች የሚያገሉ ሰዎችን ያፈራል።”

የዚህ ዓለም አምላክ የሆነው ሰይጣን የሰውን ዘር ጥላቻ እያስተማረው እንዳለ በግልጽ ማየት ይቻላል። ሆኖም በግለሰብ ደረጃ ፍቅርን መማር እንችላለን። የሚቀጥለው ርዕስ ይህ የሚቻል መሆኑን ያሳያል።

[ምንጭ]

Tina Gerson/Los Angeles Daily News

[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የቪዲዮ ጨዋታዎች ልጆቻችሁን ጥላቻ እያስተማሯቸው ይሆን?

[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በጦርነት ጊዜ የሚወሰደው የኃይል እርምጃ ድንቁርናንና ጥላቻን የሚያሳይ ነው

[ምንጭ]

Pascal Beaudenon/Sipa Press

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ