የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • g98 4/8 ገጽ 18-21
  • ኪሊማ ንጃሮ የአፍሪካ ጣሪያ

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ኪሊማ ንጃሮ የአፍሪካ ጣሪያ
  • ንቁ!—1998
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • የአፍሪካ “ጣሪያ”
  • አስደናቂ የሆኑት የተራራው ጫፎች
  • በጣም የረቀቀ ሥነ ምህዳር
  • “ኪሊን” ድል መንሳት
  • ተራሮች ለአደጋ ተጋልጠዋል
    ንቁ!—2005
  • ተራሮች አለ እነርሱ መኖር የማንችለው ለምንድን ነው?
    ንቁ!—2005
  • በገደል አፋፍ ላይ የሚታይ የአክሮባት ትርዒት
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1997
ንቁ!—1998
g98 4/8 ገጽ 18-21

ኪሊማ ንጃሮ የአፍሪካ ጣሪያ

በኬንያ የሚገኝ የንቁ! ዘጋቢ እንዳጠናቀረው

የዛሬ 150 ዓመት የአፍሪካ ውስጣዊ ክፍል በአብዛኛው አይታወቅም ነበር። ይህች ታላቅ አሕጉር በውጭው ዓለም ገና ያልታወቀችና ብዙ ምሥጢር ያዘለች ነበረች። ከወደ ምሥራቅ አፍሪካ ከሚነገሩ ታሪኮች መካከል በተለይ አንደኛው ለአውሮፓውያን የማይታመን ሆኖባቸው ነበር። ዮሐነስ ረፕማንና ዮሐን ኤል ክራፕፍ የተባሉ ጀርመናዊ ሚስዮናውያን ያስተላለፉት ዜና ነበር። እነዚህ ሰዎች በ1848 በምድር ወገብ አካባቢ በጣም ረዥም ከመሆኑ የተነሣ አናቱ በበረዶ የተሸፈነ አንድ ተራራ እንደተመለከቱ ተናገሩ።

በሐሩር ቀጣና በምትገኘው አፍሪካ ጫፉ በበረዶ የተሸፈነ ተራራ አለ የሚለው ወሬ ሊታመን የማይችል ከመሆኑም በላይ በብዙዎች ዘንድ መሳለቂያ ሆኖ ነበር። ቢሆንም በጣም ግዙፍ ተራራ የመኖሩ ዜና የጂኦግራፊ ተመራማሪዎችንና የምድር አሳሾችን ጉጉት በመቀስቀሱ የሚስዮናውያኑ ትረካ እውነት መሆኑ ሊረጋገጥ ቻለ። በእርግጥም በምሥራቅ አፍሪካ ኪሊማንጃሮ የሚባል አናቱ በበረዶ የተሸፈነና በእሳተ ገሞራ የሚናጥ ግዙፍ ተራራ ነበር። አንዳንድ ሰዎች እንደሚሉት ኪሊማንጃሮ ማለት “የታላቅነት ተራራ” ማለት ነው።

የአፍሪካ “ጣሪያ”

በአሁኑ ጊዜ ታላቁ ኪሊማንጃሮ በአስደናቂ ውበቱና በግርማ ሞገሱ ከፍተኛ ዝና አትርፏል። በርካታ የዝሆን መንጋዎች ግዙፉንና የበረዶ ቆብ የሸፈነውን “ኪሊ” ከበስተጀርባቸው አድርገው በደረቁና በአቧራማው የአፍሪካ የተንጣለለ ሜዳ ላይ ተሰማርተው የማየትን ያህል በጣም አስደናቂ የሆነና ሊረሳ የማይችል ትዕይንት ሊኖር አይችልም።

ኪሊማንጃሮ በከፍታው በአፍሪካ አሕጉር አንደኛ ሲሆን በዓለም ካሉት ትላልቅ ዋልጌ እሳተ ገሞራዎች አንዱ ነው። ይህ ተራራ የሚገኘው በታንዛንያ አገር ከምድር ወገብ በስተ ደቡብ በኬንያ ድንበር አቅራቢያ ነው። በዚህ ሥፍራ አራት ቢልዮን ሜትር ኩብ የሚያክል በእሳተ ገሞራ የቀለጠ አለት ከምድር እምብርት ተገፍቶ በመውጣቱ ይህ ሰማይ ጠቀስ ተራራ ሊፈጠር ችሏል።

ተራራው ብቻውን ጉብ ብሎ የሚገኝ መሆኑ ግዝፈቱ ይበልጥ ጎልቶ እንዲታይ አድርጓል። ከባሕር ወለል በላይ በ900 ሜትር ከፍታ ላይ ከሚገኘው የማሳይ ቁጥቋጦአማ ገጠር ተነስቶ 5,895 ሜትር ከፍታ ላይ የሚደርሰው ግዙፉ ተራራ ለብቻው ተንሰራፍቶ ይታያል። ኪሊማንጃሮ አንዳንድ ጊዜ የአፍሪካ ጣሪያ ተብሎ መጠራቱ የሚገባው ነው።

በተጨማሪም ኪሊማንጃሮ በማንኛውም አቅጣጫ የሚጓዙ መንገደኞች የሚያብረቀርቀውን የበረዶ ክምር በመቶ ከሚቆጠር ኪሎ ሜትር ጀምረው ሊመለከቱ ስለሚችሉ “የመንገደኞች ተራራ” ተብሎም ይጠራል። ባለፉት መቶ ዘመናት ገና ጠፍ ከነበረው የአፍሪካ ማዕከላዊ ክፍል የዝሆን ጥርስ፣ ወርቅና ባሮች አጋብሰው የሚወጡ ነጋዴዎች መንገዳቸው እንዳይጠፋቸው ተመርተው የሚወጡት በዚህ በረዷማ የተራራ ጫፍ ነበር።

አስደናቂ የሆኑት የተራራው ጫፎች

ኪሊማንጃሮ እሳተ ገሞራ የፈነዳባቸው ሁለት የተራራ ጫፎች አሉት። ዋነኛው ጫፍ ኪቦ የተባለው ሲሆን አናቱ የተስተካከለ ክብ ቅርጽ ያለውና ክረምት ከበጋ በበረዶ የተሸፈነ ነው። በስተ ምሥራቅ በኩል ማዌንዚ የሚባል ሁለተኛ ጫፍ ሲገኝ ከፍታው 5,354 ሜትር ይደርሳል። ይህ የተራራ ጫፍ ራሱ በከፍታው ከኪቦ ቀጥሎ የሁለተኛነት ደረጃ ያለው ተራራ ነው። የኪቦ ቁልቁለት ወጣ ገባነት የሌለው ሲሆን ማዌንዚ ግን በሁሉም ጎኖች ገደላ ገደል ይበዛበታል። የኪቦና የማዌንዚ ጫፎች በ4,600 ሜትር ከፍታ ላይ አልፎ አልፎ ቋጥኞች በሚታዩበት እንደ ኮርቻ ያለ ሰፊ ሜዳ ይገናኛሉ። ከኪቦ በስተ ምዕራብ በጥንት ዘመን የእሳተ ገሞራ ፍንዳታ የተከሰተበትና ለበርካታ ዓመታት በነፋስና በውኃ ሲሸረሸር ቆይቶ በአሁኑ ጊዜ ከባሕር ወለል በላይ በ4,000 ሜትር ከፍታ ላይ ያለው ሼኢር ይገኛል።

በጣም የረቀቀ ሥነ ምህዳር

በኪሊማንጃሮ ሥነ ምህዳር ወይም ኤኮ ሲስተም ውስጥ በከፍታ፣ በዝናብ መጠንና በተክሎች አይነት የሚለያዩ አካባቢዎች አሉ። የተራራው ግርጌ ጥንታዊ በሆኑ የሐሩር አካባቢ ደኖች የተሸፈነ ሲሆን በርካታ ዝሆኖችና ጎሾች ይሰማሩበታል። በደኖቹ አናት ላይ የተለያዩ የዝንጀሮ ዝርያዎች ሲኖሩ አንድ ጎብኚ አንዳንድ ጊዜ ድንጉጥ የሆኑ ድኩላዎችና ሚዳቋዎች ራሳቸውን ለመሸሸግ ጥቅጥቅ ወዳለው ደን ዘልለው ሲገቡ ሊመለከት ይችላል።

ከደን አካባቢው ከፍ ብሎ የአስታ ቀጣና ይገኛል። በኃይለኛ ነፋስና በእርጅና የተጠማዘዙ አሮጌና ቀጫጫ ዛፎች ረዣዥም ጺም ተላብሰው ይታያሉ። በዚህ አካባቢ የአስታ ቁጥቋጦዎች በብዛት ይገኛሉ። በየመካከሉ ደማቅ ቀለም ያላቸው አበቦች የሚታዩበት ለምለም ሣር ለዚህ ገጠራማ አካባቢ ልዩ ውበት አላብሶታል።

አሁንም ከደን አካባቢው ከፍ ሲል በጣም ደጋማ የሆነ አካባቢ ብቅ ይላል። በዛፎች ፋንታ ግራውንድሴል የሚባሉ ቁመታቸው እስከ 4 ሜትር የሚደርሱ ተክሎችና የጂብራ ዝርያዎች ይገኛሉ። በቋጥኞችና አለቶች ዙሪያ የበቀሉ ድርቆሽ የመሰሉ አበቦች ግራጫ ቀለም ላለው መስክ ተጨማሪ ውበት ይሰጣሉ።

አሁንም ከፍ ሲል የዱር አካባቢው ለአልፒን ቀጣና ቦታውን ይለቃል። አካባቢው ምንም አይነት ደማቅ ቀለም የሌለበት ቡናማና ግራጫ ዓለቶች የበዙበት ቦታ ነው። በዚህ ደረቅና የተራቆተ አካባቢ ሊበቅሉ የሚችሉ ተክሎች በጣም ጥቂት ናቸው። እዚህ ቦታ ላይ ስንደርስ ኪቦና ማዌንዚ በረሐማ፣ ደረቅና ድንጋያማ በሆነ ሰፊ ኮርቻ መሰል መሬት ይገናኛሉ። በዚህ አካባቢ ያለው ከፍተኛ ሙቀት በቀን እስከ 38 ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ ሲደርስ ማታ ደግሞ ከዜሮ ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ በታች ይወርዳል።

በመጨረሻ ከተራራው ጫፍ አካባቢ እንደርሳለን። እዚህ አካባቢ አየሩ ቀዝቃዛና ንጹህ ነው። ጥርት ካለው ሰማይ አንጻር የሚታዩት ትላልቅ የበረዶ ክምር ሜዳዎች በነጭና በአንጸባራቂ ቀለማቸው ጠቆር ብሎ ለሚታየው ተራራ ልዩ ውበት ሰጥተውታል። አየሩ በጣም ስስ ሲሆን በዚህ አካባቢ ያለው የኦክስጅን መጠን በባሕር ወለል ከሚገኘው በግማሽ ያንሳል። ጠፍጣፋ ከሆነው የኪቦ አናት ላይ ክብ ቅርጽ ያለውና 2.5 ኪሎ ሜትር ስፋት ያለው የእሳተ ገሞራ ጉድጓድ ይገኛል። በዚህ ጉድጓድ እምብርት ውስጥ የ300 ሜትር ስፋትና የ120 ሜትር ጥልቀት ያለው ትልቅ የአመድ ቁልል ይገኛል። ከዚህ ጉድጓድ በትናንሽ ጭስ መውጫዎች ቀስ እያለ ወደ ቀዝቃዛው አየር የሚወጣው የድኝ ጭስ በዚህ ግዙፍ ተራራ ከርስ ውስጥ ከፍተኛ ትርምስ በመካሄድ ላይ መሆኑን ይመሰክራል።

የኪሊማንጃሮ ግዙፍነትና ትልቅነት በአይነቱ ልዩ የሆነ የአየር ንብረት እንዲኖር አስችሏል። ደረቅ የሆኑትን ቆላማ አካባቢዎች አልፎ የሚሄደው ከሕንድ ውቅያኖስ የሚነፍሰው እርጥበት አዘል አየር ከተራራው ጋር በመላተም ታጥፎ ወደ ላይ ይወጣና ቀዝቅዞ ዝናብ ሆኖ ይወርዳል። በዚህ ምክንያት የተራራው ታችኛ ክፍል በጣም ለም ስለሆነ በተራራው ግርጌ ለሚኖሩ ሰዎች የምግብ እህሎችንና ቡና ያበቅላል።

“ኪሊን” ድል መንሳት

በኪሊማንጃሮ አቅራቢያ የሚኖሩ ሕዝቦች የተራራው ቁልቁለት የክፉ መናፍስት መኖሪያ ስለሆነ ወደ በረዷማው ጫፍ በሚጠጋ ማንኛውም ሰው ላይ ጉዳት ያደርሳሉ የሚል አጉል እምነት ነበራቸው። በዚህ ምክንያት የአካባቢው ሰዎች ወደ ተራራው አናት እንዳይወጡ አግዷቸው ነበር። ሁለት ጀርመናውያን አሳሾች ለመጀመሪያ ጊዜ ተራራውን ወጥተው በአፍሪካ የመጨረሻ ከፍታ ላይ የቆሙት በ1889 ነበር። ለመውጣት ይበልጥ አስቸጋሪ የሆነው የማዌንዚ ጫፍ እስከ 1912 ድረስ የደፈረው ማንም አልነበረም።

ዛሬ ግን ማንም ጥሩ ጤንነት ያለው ሰው ኪሊማንጃሮን ለመውጣት ሲችል በምሥራቅ አፍሪካ ጎብኚዎች ዘንድ በጣም ተወዳጅ ሆኗል። የታንዛንያ ፓርክ ባለሥልጣኖች ተራራውን ለመውጣት ለሚፈልጉ ሁሉ በደንብ የተደራጀ ዝግጅት አላቸው። ልብሶችንና ሌሎች ዕቃዎችን በኪራይ ማግኘት ይቻላል። የሰለጠኑ ተሸካሚዎችና መንገድ መሪዎች ሲኖሩ ከተራራው ግርጌ አንስቶ እስከ አናቱ ድረስ ጥሩ መስተንግዶ የሚሰጡ በርካታ ሆቴሎች ይገኛሉ። ተራራ ወጪዎች በተራራው የተለያዩ ከፍታዎች ላይ በተሠሩ ጥሩ ጎጆዎች ውስጥ ማደርና መጠለል ይችላሉ።

ኪሊማንጃሮን በአካል ማየት የሚያስደንቅና የፈጣሪን ታላቅነት የሚያስገነዝብ ነው። ይህን ተራራ የተመለከተ ሰው “ተራራዎችን በየስፍራቸው አጽንተህ በማኖርህ ብርቱ ኀይልህን አሳይተሃል” ከሚለው ስለ ፈጣሪ የተነገረ ቃል ጋር መስማማቱ አይቀርም። (መዝሙር 65:6 የ1980 ትርጉም) አዎን፣ በአፍሪካ ጣሪያ ላይ ብቻውን ከፍ ብሎ የቆመው ኪሊማንጃሮ የፈጣሪን ታላቅ ኃይል የሚመሠክር ነው።

[በገጽ 20 ላይ የሚገኝ ካርታ]

(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)

አፍሪካ

ኬንያ

ኪሊማንጃሮ

ታንዛንያ

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ