የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • g98 1/8 ገጽ 4-8
  • በ20ኛው መቶ ዘመን የተከሰተ ወረርሽኝ

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • በ20ኛው መቶ ዘመን የተከሰተ ወረርሽኝ
  • ንቁ!—1998
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • የድሮዎቹ በሽታዎች ይበልጥ ቀሳፊ ሆኑ
  • በሽታና ድህነት
  • አዲስ የታወቁ በሽታዎች
  • ለሚክሮቦች አመቺ የሆኑ ሁኔታዎች
  • ከበሽታ የጸዳ ዓለም
    ንቁ!—2004
  • ከበሽታ ጋር በተደረገው ትግል የተገኙ ድሎችና ያጋጠሙ ሽንፈቶች
    ንቁ!—2004
  • የተሻለ ጤና ለማግኘት የተደረገ የዘመናት ትግል
    ንቁ!—2004
  • ተላላፊ በሽታዎች አደገኛ ቢሆኑም መከላከል ይቻላል
    ንቁ!—2001
ለተጨማሪ መረጃ
ንቁ!—1998
g98 1/8 ገጽ 4-8

በ20ኛው መቶ ዘመን የተከሰተ ወረርሽኝ

ብዙዎች እንደተነበዩት ጥቁር ሞት የተባለው የአውሮፓ የ14ኛው መቶ ዘመን ወረርሽኝ የዓለምን ፍጻሜ አላመጣም። በዘመናችንስ? በዚህ ዘመን የሚታዩት በሽታዎችና ወረርሽኞች መጽሐፍ ቅዱስ “የመጨረሻ ቀን” በሚለው ዘመን የምንኖር መሆናችንን ያረጋግጣሉ?—2 ጢሞቴዎስ 3:1

‘በፍጹም አያረጋግጡም’ ብለህ ታስብ ይሆናል። በሕክምናም ሆነ በሳይንስ መስክ የተደረገው እድገት ከማንኛውም የታሪክ ዘመን በተሻለ ሁኔታ በሽታዎችን እንድናውቅና እንድንከላከል አስችሎናል። የሕክምና ሳይንቲስቶች በሽታዎችንና በሽታ አምጪ የሆኑትን ሚክሮቦች በመዋጋት ረገድ ኃይለኛ መሣሪያዎች ሆነው የሚያገለግሉ የተለያዩ ክትባቶችንና አንቲባዮቲክ መድኃኒቶችን አዘጋጅተዋል። በሆስፒታሎች፣ የመጠጥ ውኃ በማጣራት፣ በአካባቢ ንጽሕና እንዲሁም በምግብ አዘገጃጀት ረገድ ብዙ መሻሻል ስለተደረገ ተዛማች በሽታዎችን ለመዋጋት ተችሏል።

ከጥቂት አሥርተ ዓመታት በፊት ብዙዎች ተዛማች በሽታዎች ፈጽመው ተሸንፈዋል ብለው አስበው ነበር። ፈንጣጣ ከዓለም ፈጽሞ ሲወገድ ሌሎች በሽታዎችንም ከዓለም ለማጥፋት ታቅዶ ነበር። መድኃኒቶች በርካታ በሽታዎችን ለማሸነፍ ችለዋል። የጤና ባለሞያዎች የወደፊቱን ጊዜ ብሩሕ በሆነ ተስፋ መመልከት ጀመሩ። ተዛማች በሽታዎች መሸነፋቸው አይቀርም፣ ከድል ወደ ድል እንሸጋገራለን ብለው አሰቡ። የሕክምና ሳይንስ ያሸንፋል አሉ።

ይሁን እንጂ የሕክምና ሳይንስ ድል አልተቀዳጀም። በዛሬው ጊዜ የዓለማችን ዋነኛ የሞት ምክንያት ተዛማች በሽታ ሲሆን በ1996 ብቻ 50 ሚልዮን የሚያክሉ ሰዎች በተዛማች በሽታዎች ሳቢያ ሞተዋል። የበፊቱ ብሩሕ ተስፋ በጭንቀትና በስጋት ተተክቷል። የዓለም ጤና ድርጅት (ደብልዩ ኤች ኦ) ያዘጋጀው የ1996 የዓለም ጤና ሪፖርት “በአሁኑ ጊዜ በቅርብ አሥርተ ዓመታት የሰው ልጆችን ጤና በማሻሻል ረገድ የተገኘው ውጤት በአብዛኛው አደጋ ላይ ወድቋል። ምድር አቀፍ የሆነ የተዛማች በሽታዎች ታላቅ ችግር ከፊታችን ተጋርጧል። ይህ ችግር አይደርስብኝም ሊል የሚችል አገር የለም” ሲል አስጠንቅቋል።

የድሮዎቹ በሽታዎች ይበልጥ ቀሳፊ ሆኑ

ሁኔታውን በጣም አሳሳቢ ካደረጉት ምክንያቶች አንዱ በአንድ ወቅት ተሸንፈዋል ተብለው የታሰቡና በደንብ የሚታወቁ በሽታዎች ይበልጥ ቀሳፊና ለመዳን ይበልጥ አስቸጋሪ ሆነው ብቅ ማለታቸው ነው። ለዚህ ምሳሌ የሚሆነን በለሙት አገሮች ሙሉ በሙሉ በቁጥጥር ሥር ውሏል ተብሎ ይታሰብ የነበረው የሳንባ ነቀርሳ ነው። ይሁን እንጂ የሳንባ ነቀርሳ ፈጽሞ አልጠፋም፣ እንዲያውም በአሁኑ ጊዜ በየዓመቱ ሦስት ሚልዮን ሰዎች በዚሁ በሽታ ምክንያት ይሞታሉ። የተሻለ ቁጥጥር ለማድረግ ካልተቻለ በ1990ዎቹ ዓመታት 90 ሚልዮን የሚያክሉ ሰዎች በበሽታው እንደሚለከፉ ይጠበቃል። በብዙ አገሮች ምንም ዓይነት መድኃኒት የማይበግረው የሳንባ ነቀርሳ ዓይነት በመዛመት ላይ ነው።

ሌላው በማገርሸት ላይ የሚገኝ በሽታ ወባ ነው። ከአርባ ዓመታት በፊት ሐኪሞች ከጥቂት ጊዜ በኋላ ወባን ጨርሶ ማጥፋት ይቻላል የሚል ተስፋ ነበራቸው። ዛሬ ግን ይህ በሽታ በየዓመቱ ሁለት ሚልዮን የሚያክሉ ሰዎችን ይገድላል። ወባ 90 በሚያክሉ አገሮች የሚገኝ ሲሆን 40 በመቶ የሚያክሉትን የዓለም ሕዝቦች ሕይወት አደጋ ላይ የሚጥል ነው። የወባ ተውሳኮችን የሚሸከሙ ትንኞች የወባ ማጥፊያ መድኃኒቶች የማይበግሯቸው ሲሆኑ ተውሳኮቹ ራሳቸው ደግሞ ምንም ዓይነት መድኃኒት የማይገድላቸው እየሆኑ በመምጣታቸው ዶክተሮች አንዳንድ የወባ ዓይነቶች ፈውስ ሊገኝላቸው የማይችሉ ይሆናሉ የሚል ስጋት አላቸው።

በሽታና ድህነት

ሌሎች በሽታዎች ደግሞ ጥሩ መድኃኒትና መከላከያ የተገኘላቸው ቢሆኑም ሰዎችን መግደላቸው አልቀረም። ለምሳሌ ማጅራት ገትርን እንውሰድ። ማጅራት ገትርን የሚከላከል ክትባት ከመኖሩም በላይ ከበሽታው የሚፈውሱ መድኃኒቶችም አሉ። በ1996 መጀመሪያ ላይ ይህ በሽታ ከሰሐራ በታች ባሉ የአፍሪካ አገሮች ተዛምቶ ነበር። ስለዚህ ወረርሽኝ ብዙም አልሰማህ ይሆናል፤ ሆኖም 15,000 የሚያክሉ በአብዛኛው ድሆችና ሕፃናት የሆኑ ሰዎችን ገድሏል።

የሳምባ ምችን ጨምሮ፣ የታችኛው የመተንፈሻ አካላት በሽታዎች፣ በየዓመቱ አራት ሚልዮን የሚያክሉ ሰዎችን፣ በተለይም ሕፃናትን ይገድላሉ። ኩፍኝ በየዓመቱ አንድ ሚልዮን ሕፃናትን ሲገድል ትክትክ ደግሞ 335,000 ሕፃናትን ይገድላል። ብዙ ወጪ የማይጠይቁ ክትባቶች ቢሰጡ ኖሮ እነዚህ ሁሉ ሕፃናት አይሞቱም ነበር።

በየቀኑ ስምንት ሺህ የሚያክሉ ሕፃናት በተቅማጥ ምክንያት በሰውነታቸው ውስጥ ያለው ፈሳሽ ተሟጥጦ ይሞታሉ። የአካባቢ ንጽሕና ቢጠበቅ ወይም ንጹህ ውኃ ቢኖር ወይም በሰውነት ውስጥ ያለውን ውኃ የሚተካ ፈሳሽ ቢሰጥ ኖሮ እነዚህን ሕፃናት በሙሉ ከሞት ማዳን ይቻል ነበር።

አብዛኛው ሞት የሚደርሰው ድህነት በተንሰራፋባቸው በታዳጊ አገሮች ነው። በቀላሉ የማይገመት ቁጥር ያላቸው የዓለም ሕዝቦች፣ ማለትም 800 ሚልዮን የሚያክሉ ሰዎች ምንም ዓይነት የጤና እንክብካቤ ማግኘት አይችሉም። የ1995 የዓለም ጤና ሪፖርት እንዲህ ሲል አትቷል:- “በመላው ዓለም በገዳይነቱ አንደኛ የሆነውና ትልቁ የጤና መታወክና የሥቃይ መንስኤ በዓለም አቀፉ የበሽታዎች ዝርዝር ውስጥ የመጨረሻውን ረድፍ ይዟል። እርሱም Z59.5 የተባለ የምሥጢር ስም የተሰጠው ከባድ ድህነት ነው።”

አዲስ የታወቁ በሽታዎች

መጤ የሆኑና ገና በቅርቡ የታወቁ በሽታዎችም አሉ። የዓለም ጤና ድርጅት በቅርቡ እንዲህ ሲል አስታውቋል:- “ባለፉት 20 ዓመታት በመቶ ሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን ጤና የሚጻረሩ ቢያንስ 30 የሚያክሉ አዳዲስ በሽታዎች ብቅ ብለዋል። ከእነዚህ በሽታዎች መካከል ለብዙዎቹ ክትባትም ሆነ ሕክምና ገና ያልተገኘ በመሆኑ በሽታዎቹን የመከላከልም ሆነ የመቆጣጠር አቅም የለንም።”

ለምሳሌ ያህል ኤች አይ ቪንና ኤድስን እንውሰድ። ከታወቁ ገና አሥራ አምስት ዓመት እንኳን ያልሞላቸው ቢሆኑም በአሁኑ ጊዜ በሁሉም አህጉሮች የሚገኙ ሕዝቦችን እያጠቁ ነው። በአሁኑ ጊዜ 20 ሚልዮን የሚያክሉ ለአቅመ አዳም የደረሱ ሰዎች በኤች አይ ቪ (ቫይረስ) የተለከፉ ሲሆን ከ4.5 ሚልዮን በላይ የሚሆኑት ኤድስ ጀምሯቸዋል። የ1996 ሂውማን ዴቨሎፕመንት ሪፖርት እንደሚለው በአሁኑ ጊዜ በአውሮፓና በሰሜን አሜሪካ ለሚኖሩ ከ45 ዓመት በታች ዕድሜ ያላቸው ሰዎች ዋነኛው የሞት መንስኤ ኤድስ ነው። በመላው ዓለም በየቀኑ 6,000 የሚያክሉ ሰዎች ወይም በየ15 ሴኮንድ አንድ ሰው በበሽታው ይለከፋል። ወደፊትም ቢሆን የኤድስ ሕሙማን ቁጥር እያሻቀበ መሄዱ እንደማይቀር ስሌቶች ያመለክታሉ። አንድ የዩናይትድ ስቴትስ መሥሪያ ቤት እንዳስታወቀው በ2010 በኤድስ በጣም በተጎዱት የአፍሪካና የእስያ አገሮች የአንድ ሰው አማካይ በሕይወት የመቆያ ዘመን ወደ 25 ዓመት ይወርዳል።

ኤድስ በዓይነቱ ልዩ የሆነና ብቸኛ በሽታ ነው ወይስ ሌሎች ወረርሽኞችም ተነስተው ይህን የመሰለ ወይም ከዚህ የሚብስ እልቂት ሊያስከትሉ ይችላሉ? የዓለም ጤና ድርጅት “እስካሁን ያልታወቁ፣ ነገር ግን የነገው ኤድስ የመሆን ሙሉ አቅም ያላቸው ወረርሽኞች ከበስተኋላችን በማንዣበብ ላይ መሆናቸው ጥርጥር የለውም” በማለት ይመልስልናል።

ለሚክሮቦች አመቺ የሆኑ ሁኔታዎች

የጤና ባለሞያዎች ወደፊት ሊነሱ ስለሚችሉ ወረርሽኞች የሚሰጉት ለምንድን ነው? አንደኛው ምክንያት የከተሞች ማደግ ነው። ከመቶ ዓመት በፊት በከተሞች ይኖሩ የነበሩት ከጠቅላላዎቹ የዓለም ሕዝቦች 15 በመቶ ብቻ የሚሆኑት ነበሩ። በ2010 ግን ከዓለም ሕዝቦች መካከል ከግማሽ የሚበልጡት በከተሞች፣ በይበልጥም በልማት ወደ ኋላ በቀሩ አገሮች በሚገኙ ትላልቅ ከተሞች እንደሚኖሩ ስለወደፊቱ ጊዜ የተደረጉ ስሌቶች ያመለክታሉ።

በሽታ ተሸካሚ ተውሳኮች የሚመቻቸውና እንደ ልባቸው የሚራቡት ብዙ ሰዎች በሚኖሩባቸው አካባቢዎች ነው። በአንድ ከተማ ውስጥ ጥሩ የመኖሪያ አካባቢ፣ በቂ የቆሻሻ ማስወገጃና ጥሩ የጤና እንክብካቤ ካለ ከተማው ለወረርሽኝ የተጋለጠ አይሆንም። ይሁን እንጂ በከፍተኛ ፍጥነት በማደግ ላይ የሚገኙት ከተሞች በድሃ አገሮች ውስጥ የሚገኙት ከተሞች ናቸው። በአንዳንድ ከተሞች አንድ መጸዳጃ ቤት ለ750 ሰዎች ይደርሳል። በተጨማሪም ብዙ ከተሞች በቂና ጥሩ የመኖሪያ ቤት፣ ንጹሕ የመጠጥ ውኃና በቂ የመታከሚያ ድርጅቶች የሏቸውም። በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች በደሳሳ ቤቶች ተጨናንቀው በሚኖሩበት አካባቢ ተዛማች በሽታ በቀላሉ መነሳቱ የማይቀር ነው።

ታዲያ እንዲህ ሲባል ወደፊት የሚነሱት ወረርሽኞች ሰዎች ተጣበውና ተጨናንቀው በሚኖሩባቸውና በድህነት በተጠቁ ትላልቅ ከተሞች ብቻ የተወሰኑ ይሆናሉ ማለት ነውን? አርካይቭስ ኦቭ ኢንተርናል ሜዲስን የተባለው ጋዜጣ እንዲህ ሲል ይመልሳል:- “እዚያና እዚህ የሚታዩት የኑሮ ጉስቁልናዎች፣ ተስፋ ቢስ ኢኮኖሚዎችና እነዚህ ሁኔታዎች የሚያስከትሏቸው ውጤቶች የወረርሽኝ በሽታዎች መስፋፋትና መሰራጨት የሚችሉባቸውን በጣም አመቺ የሆኑ ሁኔታዎች እንደሚፈጥሩና ይህም የቀረውን የሰው ዘር ዓለም ቴክኖሎጂ እንደሚያጠፋ መረዳት ይኖርብናል።”

አንድን በሽታ በአንድ አካባቢ ብቻ ገድቦ ማቆየት ቀላል አይደለም። በጣም ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሰዎች ከቦታ ወደ ቦታ ይጓዛሉ። በየቀኑ አንድ ሚልዮን የሚያክሉ ሰዎች የአገራቸውን ድንበር ይሻገራሉ። በየአንዳንዱ ሳምንት አንድ ሚልዮን የሚያክሉ ሰዎች ከሀብታም አገሮች ወደ ድሃ፣ ወይም ከድሃ አገሮች ወደ ሀብታም አገሮች ይጓዛሉ። ሰዎች ከአንዱ ቦታ ወደ ሌላው ቦታ በሚንቀሳቀሱበት ጊዜ ቀሳፊ ሚክሮቦችን አስከትለው ይጓዛሉ። ዘ ጆርናል ኦቭ ዚ አሜሪካን ሜዲካል አሶሲዬሽን እንዲህ ብሏል:- “በአሁኑ ጊዜ በየትኛውም የዓለም ክፍል የሚነሳ በሽታ ለአብዛኞቹ አገሮች፣ በተለይም የዓለም አቀፍ ዝውውር መናኸሪያዎች ለሆኑ አገሮች አስጊ እንደሆነ መታወቅ አለበት።”

ስለዚህ በዚህ በ20ኛው መቶ ዘመን የሕክምና ጥበብ በጣም የተስፋፋ ቢሆንም ተዛማች በሽታዎች የብዙ ሰዎችን ሕይወት መቅጠፋቸው አልቀረም። እንዲያውም ብዙዎቹ ሰዎች የወደፊቱ ሁኔታ የባሰ እንዳይሆን ስጋት አድሮባቸዋል። ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ወደፊቱ ጊዜ ምን ይላል?

[በገጽ 4 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

በመላው ዓለም ዋነኛው የሞት ምክንያት ተዛማች በሽታ ሲሆን በ1996 ብቻ ከ50 ሚልዮን የሚበልጡ ሰዎች ሞተዋል

[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

አንቲባዮቲክ መድኃኒቶችን የመቋቋም ችሎታ

ብዙ ተዛማች በሽታዎች አንቲባዮቲክ መድኃኒቶችን የመቋቋም ችሎታ ስላዳበሩ ከእነዚህ በሽታዎች መዳን እያደር አስቸጋሪ እየሆነ መጥቷል። እንዲህ የሚሆነው ለምንድን ነው? አንድ ሰው በባክቴሪያዎች በሚለከፍበት ጊዜ ባክቴሪያዎቹ አለማቋረጥ ይራባሉ። ጀነቲካዊ ባሕርያቸውንም ወደ ልጆቻቸው ያስተላልፋሉ። አንድ አዲስ ባክቴሪያ በሚወለድበት ጊዜ አዲሱ ባክቴሪያ አዲስ ዓይነት ባሕርይ እንዲኖረው የሚያስችል አነስተኛ የሆነ የባሕርይ አወራረስ ስህተት ይፈጠራል። አንድ ባክቴሪያ በባሕርይ አወራረስ ስህተት ምክንያት አንቲባዮቲክ መድኃኒቶችን የመቋቋም ችሎታ ለማግኘት ያለው ዕድል በጣም አነስተኛ ነው። ቢሆንም ባክቴሪያዎች በጣም በፍጥነት ስለሚራቡ በአንድ ሰዓት ጊዜ ውስጥ እስከ ሦስት ትውልድ ድረስ ተዋልደው በቢልዮን የሚቆጠሩ ይሆናሉ። በዚህ ምክንያት አዘውትሮ የማይፈጸም ሁኔታ የሚፈጠርበት ጊዜ አለ። በአንቲባዮቲክ ሊገደል የማይችል ባክቴሪያ ይወለዳል።

ስለዚህ በባክቴሪያዎች የተለከፈ አንድ ሰው አንቲባዮቲክ በሚወስድበት ጊዜ መድኃኒቱን የመቋቋም ችሎታ የሌላቸው ባክቴሪያዎች በሙሉ ተጠራርገው ስለሚጠፉ ሕመምተኛው የመሻል ስሜት ይሰማው ይሆናል። ይሁን እንጂ የመቋቋም ችሎታ ያላቸው ባክቴሪያዎች ኑሯቸውን ይቀጥላሉ። በዚህ ጊዜ ግን ምግብና የመኖሪያ ስፍራ የሚሻሟቸው ባክቴሪያዎች አይኖሩም። አለምንም ገደብ ለመራባት ይችላሉ። አንድ ባክቴሪያ በአንድ ቀን ውስጥ ተራብቶ 16 ሚልዮን ሊደርስ ስለሚችል ሰውዬው ብዙም ሳይቆይ ተመልሶ ይታመማል። በዚህ ጊዜ ግን የተለከፈው የሚገድላቸውን መድኃኒት የመቋቋም አቅም ባላቸው ባክቴሪያዎች ነው። በተጨማሪም እነዚህ ባክቴሪያዎች ሌሎች ሰዎችን ሊለክፉና ባሕርያቸውን ለውጠው ሌሎች አንቲባዮቲኮችን የመቋቋም አቅም ሊያገኙ ይችላሉ።

አርካይቭስ ኦቭ ኢንተርናል ሜዲስን የተባለው ጋዜጣ ርዕሰ አንቀጽ እንዲህ ብሏል:- “በአሁኑ ጊዜ ያሉንን የሕክምና መሣሪያዎችና ዘዴዎች የሚቋቋሙ ባክቴሪያዎች፣ ቫይረሶች፣ ፈንገሶችና ጥገኛ ተውሳኮች በከፍተኛ ፍጥነት እየጨመሩ መሄዳቸው የሰው ልጅ ከሚክሮቦች ጋር በሚያደርገው ውጊያ ይሸነፍ ይሆን? ከማለት ይልቅ የሚሸነፈው መቼ ነው ብለን እንድንጠይቅ ያስገድደናል።”—በሠያፍ የጻፍነው እኛ ነን።

[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

ከ1976 ወዲህ የተከሰቱ አንዳንድ አዳዲስ ተዛማች በሽታዎች

በሽታው መጀመሪያ

የታወቀበት የታየበት ወይም

ዓመት የበሽታው ስም የታወቀበት አገር

1976 ሊጅነርስ ዲዚዝ ዩናይትድ ስቴትስ

1976 ክሪፕቶስፖሪዲኦሲስ ዩናይትድ ስቴትስ

1976 ኢቦላ ደም አፍሳሽ ትኩሳት ዛይር

1977 ሃንታን ቫይረስ ኮሪያ

1980 ሄፓታይተስ ዲ (ዴልታ) ኢጣሊያ

1980 ሂውማን ቲ-ሴል ሊምፎትሮፒክ ቫይረስ 1 ጃፓን

1981 ኤድስ ዩናይትድ ስቴትስ

1982 ኢ. ኮሊ 0157:H7 ዩናይትድ ስቴትስ

1986 የእብድ ላም በሽታ እንግሊዝ

1988 ሳልሞኔላ ኢንተራይትዲስ ፒቲ4 እንግሊዝ

1989 ሄፓታይተስ ሲ ዩናይትድ ስቴትስ

1991 ቬንዝዌላን ሄሞሬጅክ ፊቨር ቬንዝዌላ

1992 ቪብሪዮ ኮሌራ 0139 ሕንድ

1994 ብራዚልያን ሄሞሬጅክ ፊቨር ብራዚል

1994 ሂውማን ኤንድ ኤክዊን ሞርቢሊቫይረስ አውስትራሊያ

በእንስሳት ላይ ብቻ የታየ ነው።

[ምንጭ]

ምንጭ:- የዓለም ጤና ድርጅት

[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የቀድሞዎቹ በሽታዎች እንደገና ማገርሸት ጀምረዋል

ሳንባ ነቀርሳ:- በዚህ አሥር ዓመት ውስጥ ከ30 ሚልዮን የሚበልጡ ሰዎች በሳንባ ነቀርሳ እንደሚሞቱ ይገመታል። ባለፉት ዓመታት የተሰጡት ሕክምናዎች አጥጋቢ ስላልነበሩ መድኃኒት የማይበግረው ሳንባ ነቀርሳ በመላው ዓለም በመስፋፋት ላይ ነው። አንዳንዶቹ የበሽታው ዓይነቶች በአሁኑ ጊዜ ከዚህ በፊት ባክቴሪያዎቹን ፈጽመው ይገድሉ የነበሩትን መድኃኒቶች ሙሉ በሙሉ ለመቋቋም ችለዋል።

ወባ:- በየዓመቱ በዚህ በሽታ የሚጠቁ ሰዎች ቁጥር 500 ሚልዮን የደረሰ ሲሆን 2 ሚልዮን የሚያክሉት ይሞታሉ። በመድኃኒቶች እጥረት ወይም መድኃኒቶችን አለአግባብ በመጠቀም ምክንያት በሽታውን መቋቋም ሳይቻል ቀርቷል። በዚህ ምክንያት የወባ ተውሳኮች ከዚህ በፊት ይገድሏቸው የነበሩትን መድኃኒቶች መቋቋም ችለዋል። ትንኞች ፀረ ተባይ መድኃኒቶችን ለመቋቋም መቻላቸው ችግሩን ይበልጥ አወሳስቦታል።

ኮሌራ:- ኮሌራ በአብዛኛው ወረርሽኙ በሚታይበትና በተስፋፋበት የአፍሪካ አህጉር በየዓመቱ 120,000 ሰዎች ይገድላል። ለበርካታ አሥርተ ዓመታት በደቡብ አሜሪካ ተከስቶ የማያውቀው ኮሌራ በ1991 ፔሩን የመታት ሲሆን ከዚያ ወዲህ በአህጉሪቱ በሙሉ ተሰራጭቷል።

ዴንግ:- ይህ ትንኝ ወለድ ቫይረስ በየዓመቱ 20 ሚልዮን የሚገመቱ ሰዎችን ያጠቃል። በ1995 በ15 ዓመት ጊዜ ውስጥ በላቲን አሜሪካና በካሪቢያን ደሴቶች ታይቶ በማያውቅ መጠን የተከሰተው የዴንግ ወረርሽኝ 14 አገሮችን መትቷል። በትላልቅ ከተሞች መስፋፋት፣ ዴንግ ተሸካሚ ትንኞች በብዙ አካባቢዎች በመሰራጨታቸውና በበሽታው የተለከፉ ሰዎች ከአገር ወደ አገር በመዘዋወራቸው ምክንያት የዴንግ ወረርሽኝ እየጨመረ መጥቷል።

ዘጊ አናዳ:- ከ50 ዓመት በፊት ጀምሮ የክትባት ዘመቻ ፕሮግራም ሲካሄድ በመቆየቱ ምክንያት ይህ በሽታ በኢንዱስትሪ በበለጸጉ አገሮች እየጠፋ መጥቷል። ይሁን እንጂ ከ1990 ወዲህ የዘጊ አናዳ ወረርሽኝ በምሥራቅ አውሮፓና በቀድሞይቱ ሶቪዬት ኅብረት በሚገኙ 15 አገሮች ተሰራጭቷል። በበሽታው ከተለከፉት መካከል ከአራት አንዱ ሞተዋል። በ1995 የመጀመሪያ አጋማሽ ላይ 25,000 የሚያክሉ ሕሙማን ሪፖርት ተደርገዋል።

ቡቦኒክ ፕሌግ:- በ1995 ቢያንስ 1,400 ሰዎች በዚህ ቸነፈር እንደተመቱ ለዓለም ጤና ድርጅት ሪፖርት ተደርጓል። በዩናይትድ ስቴትስና በሌሎች አገሮች በሽታው ለበርካታ አሥርተ ዓመታት ደርሶ በማያውቅባቸው አካባቢዎች ተዳርሷል።

[ምንጭ]

ምንጭ:- የዓለም ጤና ድርጅት

[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በጤና አጠባበቅ ረገድ ብዙ መሻሻል የተደረገ ቢሆንም የሕክምና ሳይንስ የተዛማች በሽታዎችን መስፋፋት ማቆም ተስኖታል

[ምንጭ]

WHO photo by J. Abcede

[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ሰዎች በቆሻሻ አካባቢዎች ተፋፍገው ሲኖሩ በሽታዎች በቀላሉ ይዛመታሉ

[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በታዳጊው የዓለም ክፍል የሚኖሩ 800 ሚልዮን የሚያክሉ ሰዎች የጤና እንክብካቤ አያገኙም

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ