የጥቁሩ ሞት መከሰት የዓለም ፍጻሜ አልሆነም
በ1347 የጥቅምት ወር ከምሥራቁ የዓለም ክፍል የመጡ የንግድ መርከቦች በሲሲሊ በምትገኘው የመሲና ወደብ መልሕቃቸውን ጣሉ። መርከበኞቹ የታመሙና ሊሞቱ የተቃረቡ ነበሩ። በመላ ሰውነታቸው ላይ ከሚገኙት እንቁላል የሚያካክሉ ጥቋቁር እባጮች ደምና መግል ይፈስ ነበር። መርከበኞቹ በከባድ ሕመም ከተሰቃዩ በኋላ የመጀመሪያው የሕመም ምልክት በታየባቸው ጥቂት ቀናት ውስጥ ሞቱ።
መርከቦቹ ላይ የነበሩ አይጦች ተሽለኩልከው ወደ ምድር ከወጡ በኋላ ከአገሩ አይጦች ጋር ተደባልቀው መኖር ይጀምራሉ። አይጦቹ ሰዎችን በሚቀስፉ ባክቴሪያዎች የተበከሉ ቁንጫዎችን ተሸክመው ነበር። በዚህ መንገድ ጥቁሩ ወረርሽኝ ወይም ጥቁሩ ሞት እየተባለ የሚጠራውና እስከዚያ ጊዜ ድረስ በአውሮፓ ታሪክ ታይቶ የማይታወቀው አስከፊ ቸነፈር ተዛመተ።
ወረርሽኙ ሁለት መልክ ነበረው። አንደኛው ዓይነት በባክቴሪያው በተለከፉ ቁንጫዎች ንክሻ የሚተላለፍ ሲሆን በደም ሥር በኩል ተሰራጭቶ እባጭና በሰውነት ውስጥ የደም መፍሰስ ያስከትላል። ሌላው ደግሞ በሳል ወይም በማስነጠስ የሚጋባ ሲሆን የሚያጠቃውም ሳንባን ነው። ሁለቱም ዓይነት ወረርሽኞች ስለነበሩ በሽታው በከፍተኛ ፍጥነትና በአስፈሪ ሁኔታ ተሰራጨ። በሦስት ዓመት ጊዜ ውስጥ ብቻ የአውሮፓን አንድ አራተኛ የሚሆን ሕዝብ ቀጠፈ። 25 ሚልዮን የሚያክሉ ሰዎች ሳይሞቱ እንዳልቀረ ይገመታል።
በዚያ ጊዜ በሽታው ከሰው ወደ ሰው እንዴት እንደሚተላለፍ ያወቀ አልነበረም። አንዳንዶች በምድር መናወጥ ወይም ባልተለመደ ሁኔታ የፕላኔቶች አቀማመጥ በመዛባቱ ምክንያት አየሩ ተመርዟል ብለው ያምኑ ነበር። ሌሎች ደግሞ በበሽታው የተለከፈን ሰው በማየት ብቻ የሚጋባ ይመስላቸው ነበር። የተለያዩ አስተያየቶች ይኑሩ እንጂ በሽታው በከፍተኛ ፍጥነት የሚዛመት መሆኑ በግልጽ ይታይ ነበር። አንድ ፈረንሳዊ ሐኪም አንድ የታመመ ሰው “መላውን ዓለም ሊበክል የሚችል” ይመስል እንደነበር ተናግሯል።
በጊዜው መከላከያም ሆነ መድኃኒት አልተገኘም። በመጨረሻው ቀን ቸነፈር እንደሚኖር የሚናገሩትን እንደ ሉቃስ 21:11 ያሉትን የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች ያስታወሱ ሰዎች ብዙዎች ነበሩ። በጣም በርካታ የሆነ የስዕለት ገንዘብ ወደ አብያተ ክርስቲያናት ቢጎርፍም ቸነፈሩ እንደ ሰደድ እሳት መዛመቱን ቀጠለ። በዘመኑ የነበረ አንድ ኢጣልያዊ “አብያተ ክርስቲያናት የሞተ ሰው መኖሩን ለማሳወቅ ደወል መደወላቸውን አቆሙ፣ ሁሉም ሰው ዛሬ ነገ እሞታለሁ ብሎ ይጠብቅ ስለነበረ ማንም ቢሞትበት አያለቅስም ነበር። . . . ሰዎች ‘ይህ የዓለም ፍጻሜ ነው’ ይሉ ነበር” ሲል ጽፏል።
ይሁን እንጂ እንዳሰቡት የዓለም ፍጻሜ አልሆነም። በ14ኛው መቶ ዘመን መጨረሻ ላይ ቸነፈሩ ቆመ። ዓለምም እንደ ቀድሞዋ ቀጠለች።
[በገጽ 3 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
Archive Photos