የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • g98 5/8 ገጽ 30-31
  • ከዓለም አካባቢ

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ከዓለም አካባቢ
  • ንቁ!—1998
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • የእንግሊዝ ቤተ ክርስቲያን አባሎቿን እያጣች ነው
  • በአርሴኒክ መመረዝ
  • ሚስቱ ሲጋራ ማጨስ ባለማቆሟ ባሏ ከሰሳት
  • ልጆች በጦርነት ጊዜ የሚደርስባቸው መከራ
  • ሥራ የሚውሉ እናቶች
  • አውዳሚ የሆነ ዓሣ የማጥመድ ዘዴ
  • በአፍላ ጉርምስና ዕድሜ የሚገኙ ወጣቶች ሥነ ምግባር በብሪታንያ
  • በፍጥነት እየተዛመተ ያለው የውፍረት ችግር
  • ስደተኞች ሕይወታቸውን አደጋ ላይ ይጥላሉ
  • አደንዛዥ ዕፅ መውሰድ እምቢ መባል የሚኖርበት ለምንድን ነው?
    ወጣቶች የሚጠይቋቸው ጥያቄዎችና ተግባራዊ መሆን የሚችሉ መልሶች
  • ለጥሩ ሕይወት ቁልፉ አደንዛዥ መድኃኒቶች ናቸውን?
    ወጣትነትህን በተሻለ መንገድ ተጠቀምበት
  • አደንዛዥ ዕፆች
    ከቅዱሳን ጽሑፎች እየጠቀሱ ማመራመር
  • ስለ ሲጋራ ምን ማወቅ ይኖርብኛል?
    ወጣቶች የሚጠይቋቸው ጥያቄዎችና ተግባራዊ መሆን የሚችሉ መልሶች፣ ጥራዝ 1
ለተጨማሪ መረጃ
ንቁ!—1998
g98 5/8 ገጽ 30-31

ከዓለም አካባቢ

የእንግሊዝ ቤተ ክርስቲያን አባሎቿን እያጣች ነው

በየሳምንቱ እሑድ እሑድ ቤተ ክርስቲያን የሚሄዱ የእንግሊዝ ቤተ ክርስቲያን ምዕመናን ቁጥር አንድ ሚልዮን እንደሚደርስ የቤተ ክርስቲያኒቱ ይፋዊ ግምት ያመለክታል። አንዳንድ ከፍተኛ ሥልጣን ያላቸው ካህናት ግን ይህ ቁጥር 25 በመቶ ሊቀንስ እንደሚችል ይናገራሉ። ይሁን እንጂ አንድ ሳይንሳዊ ጥናት እንዳመለከተው በዋነኛነት የሚታዩ ሥጋ ወደሙ የሚቀበሉ አባላት ቁጥር ለመጀመሪያ ጊዜ ከግማሽ ሚልዮን በታች ሆኗል። ቀሳውስት በአብያተ ክርስቲያናት የሚገኙትን ምዕመናን ቁጥር ይህን ያህል አጋንነው ሪፖርት የሚያደርጉት ለምንድን ነው? መሠረታዊ ምክንያታቸው ቤተ ክርስቲያናቸውን ከመዘጋት ለማዳን ነው። አንድ ቤተ ክርስቲያን በሚዘጋበት ጊዜ ሰበካዎች ስለሚታጠፉ የሚያስፈልጉት ቀሳውስት ብዛት ይቀንሳል። አንድ ቄስ “ቁጥሩን ጨማምሬ ሪፖርት የማድረግ አዝማማያ አለኝ። የተሳላሚዎች ቁጥር ሲያንስ ተስፋ ያስቆርጣል። ስለዚህ ቁጥሩን በዛ ማድረጌ ያጽናናኛል” በማለት በሐቀኝነት እንደተናገሩ የለንደኑ ዘ ሳንደይ ታይምስ ሪፖርት አድርጓል።

በአርሴኒክ መመረዝ

ዘ ታይምስ ኦቭ ኢንዲያ ሪፖርት እንዳደረገው “15 ሚልዮን የሚያክሉ የባንግላዴሽ ዜጎችና ካልካታን ጨምሮ 20 ሚልዮን የሚያክሉ የምዕራብ ቤንጋል ነዋሪዎች ለአርሴኒክ መርዝ ተጋልጠዋል።” ችግሩ አረንጓዴው አብዮት ያስከተለው ያልተጠበቀ ውጤት ነው። ለመስኖ የሚያገለግሉ ጥልቅ የውኃ ጉድጓዶች ሲቆፈሩ በምድር ከርስ ውስጥ ተቀብሮ የቆየው አርሴኒክ ወደ ጥልቅ ጉድጓድ ውኃዎች፣ ቀስ እያለም ለመጠጥ ወደሚያገለግሉ የውኃ ጉድጓዶች መስረግ ጀመረ። የኮሎራዶ ዩ ኤስ ኤ ዩኒቨርሲቲ ባልደረባና የአካባቢ ሁኔታዎች ሊቅ የሆኑት ዊላርድ ቻፐል በችግሩ የተጠቃውን አካባቢ በቅርቡ ከጎበኙ በኋላ “እስከ ዛሬ ድረስ በዓለም ላይ በመርዝ ሳቢያ ከተከሰቱት ችግሮች ሁሉ በትልቅነቱ ተወዳዳሪ የሌለው ነው” ብለዋል። እስካሁን ድረስ ከ200,000 የሚበልጡ ሰዎች በአርሴኒክ የመመረዝ ምልክት የሆነው የቆዳ መቁሰል ችግር ደርሶባቸዋል። ኢሻክ አሊ የተባሉት የባንግላዴሽ መንግሥት ባለ ሥልጣን “(በአረንጓዴው አብዮት አማካኝነት) ረሃብ ለማስወገድ ጥረት ስናደርግ ከረሃብ የከፋ ሥቃይ ፈጥረናል” ብለዋል።

ሚስቱ ሲጋራ ማጨስ ባለማቆሟ ባሏ ከሰሳት

ሪቻርድ ቶማስ ሚስቱ ሲጋራ ማጨሷን እንድትተው ቢማጸናትና ቢለማመጣትም ከ20 ዓመት በላይ ያደረገው ጥረት ሁሉ ከንቱ ይሆንበታል። ስለዚህ ይከሳትና ፍርድ ቤት ያቆማታል። ሚስተር ቶማስ የሚወዳት ሚስቱ የምትሰጠውን ፍቅር፣ ድጋፍና ባልንጀርነት ከማጣት መንግሥት እንዲያድነው አመለከተ። ከዚህ ቀደም ብሎ እናቱን በልብ በሽታ ምክንያት ሲያጣ አባቱ በአንጎል ውስጥ በሚከሰት የደም መፍሰስ ችግር ሳቢያ አልጋ ላይ ከዋሉ ሰባት ዓመት ሆኗቸዋል። ሁለቱም ወላጆቹ ከባድ አጫሾች የነበሩ ሲሆን አሁን ደግሞ ሚስቱን በኒኮቲን ሱስ ምክንያት ማጣት አልፈለገም። ፍርድ ቤቱ የራሱን ብይን ከመስጠቱ በፊት ግን ሚስተር ቶማስ አንድ የምሥራች ይዞ ወደ ችሎቱ ተመለሰ። “ባለቤቴ ማጨስ ለመተው ተስማምታለች” አለ። ሚስስ ቶማስ ሱስ ወደሚያስተው የሕክምና ማዕከል ገብታ ማጨሷን እርግፍ አድርጋ ለመተው ምላለች። ዘ ኒው ዮርክ ታይምስ እንዳለው ባልና ሚስቱ ከችሎት ሲወጡ እጅ ለእጅ ተያይዘው ነበር።

ልጆች በጦርነት ጊዜ የሚደርስባቸው መከራ

ቴር ደ ሆምስ የተባለው ድርጅት ችግር የደረሰባቸውን ልጆች ይረዳል። በጀርመን የሚገኘው የዚህ ድርጅት ሊቀመንበር የሆኑት ፔትራ ቦክስለር እንደሚሉት “ባለፉት አሥር ዓመታት ሁለት ሚልዮን የሚያክሉ ልጆች በጦርነት፣ በረብሻና በጎዳና ላይ በተፈጠረ አምባጓሮ ምክንያት ሕይወታቸውን አጥተዋል።” ከዚህም በላይ ሱድዶች ዛይቱንግ ሪፖርት እንዳደረገው ስድስት ሚልዮን የሚያክሉ ልጆች ከባድ የአካል ጉዳት ሲደርስባቸው አሥር ሚልዮን የሚያክሉት በቀላሉ ሊሽር የማይችል የስሜት ቁስል ደርሶባቸዋል። ቦክስለር ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ጦርነቶች በልጆች ላይ ሌላ አስከፊ ሁኔታ አስተክለዋል ሲሉ የተሰማቸውን ሃዘን ገልጸዋል። በአንዳንድ አገሮች ልጆች ተገድደው የውትድርና ሥልጠና ይሰጣቸዋል። በሌሎች አገሮች ደግሞ “በፈንጂ አሳሽነት በማገልገል ላይ ናቸው።”

ሥራ የሚውሉ እናቶች

የሠራተኛ ሴቶች ብሔራዊ ማኅበር በ1991 “በ1990ዎቹ ዓመታት አጋማሽ ላይ ለትምህርት ያልደረሱ ልጆች ካሏቸው [የአሜሪካ] ሴቶች መካከል 65 በመቶ የሚሆኑት፣ ለትምህርት የደረሱ ልጆች ካሏቸው መካከል ደግሞ 77 በመቶ የሚሆኑት ወደ ሥራ ዓለም እንደሚገቡ” ገምቶ ነበር። ይህ ትንበያ ምን ያህል ትክክል ሆኗል? የዩ ኤስ ኤ የሕዝብ ቆጠራ ቢሮ እንደገለጸው በ1996 ከአምስት ዓመት ባነሰ ዕድሜ የሚገኙ ልጆች ካሏቸው እናቶች መካከል 63 በመቶ የሚሆኑት ሥራ ገብተዋል በማለት ዘ ዋሽንግተን ፖስት ዘግቧል። ለትምህርት የደረሱ ልጆች ካሏቸው ሴቶች መካከል 78 በመቶ የሚሆኑት ሥራ ይውላሉ። በአውሮፓስ? የአውሮፓ ኅብረት የስታትስቲክስ ጽሕፈት ቤት በሰጠው መረጃ መሠረት በአውሮፓ አገሮች “ከ5 እስከ 16 ዓመት ባለው የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ልጆች እያሏቸው ሥራ የሚውሉ ሴቶች ብዛት” በ1995 በፖርቱጋል 69 በመቶ፣ በኦስትሪያ 67 በመቶ፣ በፈረንሳይ 63 በመቶ፣ በፊንላንድ 63 በመቶ፣ በቤልጅየም 62 በመቶ፣ በብሪታንያ 59 በመቶ፣ በጀርመን 57 በመቶ፣ በኔዘርላንድስ 51 በመቶ፣ በግሪክ 47 በመቶ፣ በሉክሰምበርግ 45 በመቶ፣ በኢጣሊያ 43 በመቶ፣ በአየርላንድ 39 በመቶ እና በስፔይን 36 በመቶ ነበር።

አውዳሚ የሆነ ዓሣ የማጥመድ ዘዴ

ዓሣ በማጥመድ ሥራ ላይ የተሰማሩ ጀልባዎች ቁጥራቸው እየተመናመነ የሄዱትን ዓሣዎች ከባሕር ወለል አስሶ ለማውጣት ለሚያስችሉ መሣሪያዎች ብዙ ገንዘብ እያወጡ ነው። ከዚህ በፊት ተፈላጊነት የሌላቸውን የዓሣ ዝርያዎች ከባሕር ወለል ጠራርጎ ለማውጣት ሲባል በ1,200 ሜትር ጥልቀት ላይ ሞባይል ጊዘር የሚባል መሣሪያ ይጎተታል። ሳይንስ ኒውስ እንደሚለው ችግሩ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው “ቲዩብ ዎርም፣ ስፖንጅ፣ አነሞን፣ ሃይድሮዞአን፣ ኡርቺንና ሌሎች በጥልቅ ባሕሮች የሚኖሩ ዴኒዘን” የሚባሉ እንስሳት ተዝቀው ከወጡ በኋላ “እንደ ቆሻሻ ተቆጥረው መጣላቸው ነው።” እነዚህን ማጥፋት ደግሞ የዓሣዎችን ብዛት በጣም ይቀንሳል። እነዚህ እንስሳት ለትናንሽ ዓሦች ለምግብነትና ለመጠለያነት የሚያገለግሉ በመሆናቸው በሬድሞንድ፣ ዋሽንግተን፣ ዩ ኤስ ኤ የባሕር ነፍሳት ጥበቃ ሥነ ሕይወት ኢንስቲትዩት ዳይሬክተር የሆኑት ኤሊዮት ኖርስ በዚህ ዓይነቱ ዓሣ የማጥመድ ዘዴ የሚደርሰው ውድመት “በመሬት ላይ ደን ጥርግርግ ብሎ ሲመነጠር” ከሚደርሰው ውድመት ጋር ሊመሳሰል ይችላል” ብለዋል።

በአፍላ ጉርምስና ዕድሜ የሚገኙ ወጣቶች ሥነ ምግባር በብሪታንያ

አንድ በቅርቡ የወጣ ሪፖርት እንዳመለከተው በብሪታንያ የሚገኙ የሃይማኖት ተቋሞች በአፍላ የጉርምስና ዕድሜ ላይ የሚገኙ ወጣቶች ጥሩ ሥነ ምግባር እንዲኖራቸው ለማስቻል በሚያደርጉት ተጋድሎ ሽንፈት እየገጠማቸው ነው። ለንደን ዩኒቨርሲቲ 3,000 ለሚያክሉ በአፍላ የጉርምስና ዕድሜ ላይ የሚገኙ ወጣቶች “በጋብቻ ያልተሳሰሩ ወንዶችና ሴቶች ሩካቤ ሥጋ ቢፈጽሙ ስህተት ነው ወይስ አይደለም” የሚል ጥያቄ አቅርቦ ነበር። በአምላክ አናምንም ወይም ስለ አምላክ ማወቅ አይቻልም ከሚሉ ወጣቶች መካከል፣ ሁሉ ማለት ይቻላል፣ ስህተት አይደለም ብለዋል። ይህ የሚያስገርም አልነበረም። ይሁን እንጂ ከካቶሊካውያን መካከል 85.4 በመቶ የሚሆኑት ከአንግሊካኖች መካከል ደግሞ 80 በመቶ የሚሆኑት ስህተት አይደለም ብለዋል። ሙስሊሞችን፣ አይሁዶችን፣ ሂንዱዎችንና ሌሎችን ጨምሮ በሌሎች ሃይማኖታዊ ቡድኖች ላይ በተደረገው ጥናትም ተመሳሳይ ውጤት ተገኝቷል። የለንደኑ ዘ ታይምስ በሰጠው አስተያየት የጥናቱ ውጤት “ነባሩን የወሲብ ሥነ ምግባር ጠብቀው ለመቆየት ለሚፈልጉ የአብያተ ክርስቲያናት ሰዎች በጣም አሳዛኝ ሆኖባቸዋል” ብሏል።

በፍጥነት እየተዛመተ ያለው የውፍረት ችግር

“በፍጥነት እየተዛመተ ያለው የውፍረት ችግር በዓለም ዙሪያ ያሉ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን ጤንነት አደጋ ላይ እየጣለ ነው” በማለት ዘ ጆርናል ኦቭ ዚ አሜሪካን ሜዲካል አሶሲዬሽን የዓለም የጤና ድርጅት ያወጣውን ማስጠንቀቂያ በመጥቀስ ዘግቧል። “ከ25 አገሮች የተውጣጡ የአመጋገብ ልማድና የጤና ባለሙያዎች እንደገለጹት ይህ የውፍረት ችግር ምዕራብ አውሮፓ በሚገኙ አንዳንድ አገሮችና በአሜሪካ ከሚኖሩ ጎልማሶች መካከል 25 በመቶ የሚደርሱትን ያጠቃል። በምሥራቅ አውሮፓ፣ በሜዲትራኒያን አገሮችና በዩናይትድ ስቴትስ በሚኖሩ ጥቁር ሴቶች ዘንድ ደግሞ አኃዙ ወደ 40 በመቶ ከፍ ይላል። ማሌኔዥያ፣ ማይክሮኔዥያና ፖሊኔዥያ ከፍተኛ የውፍረት ችግር የሚታይባቸው ሲሆን በአንዳንድ ቦታዎች እስከ 70 በመቶ የሚደርሱት በችግሩ ይጠቃሉ።” ባለሙያዎቹ እንዳስጠነቀቁት አነስተኛ ስብ ያለባቸውን ምግቦች መመገብና አንዳንድ እንቅስቃሴ ማድረግ እስካልጀመሩ ድረስ ብዙ አገሮች በልብ ሕመም፣ በአተነፋፈስ ችግር፣ በጭንቅላት ውስጥ ደም መፍሰስ፣ በሃሞት ከረጢት በሽታ፣ በካንሰር፣ በስኳር በሽታና የጡንቻና የአጥንት ሕመም በሚጠቁ ከፍተኛ ቁጥር ባላቸው ሰዎች ይሞላሉ። “የውፍረት ችግር ‘በጊዜያችን ጨርሶ ቸል የተባለ የሕዝብ የጤና ችግር መካከል አንዱ ተደርጎ መታየት እንዳለበትና በጤና ላይ የሚያስከትለውም ጉዳት ከማጨስ የማይተናነስ እንደሆነ’ ባለሙያዎቹ ተናግረዋል።”

ስደተኞች ሕይወታቸውን አደጋ ላይ ይጥላሉ

በደቡብ አፍሪካ በየዓመቱ በሺህ የሚቆጠሩ ሕገ ወጥ ስደተኞች የተሻለ ሥራና ኑሮ ለማግኘት ሲሉ ሕይወታቸውን ለአደጋ ያጋልጣሉ። በመቶ የሚቆጠሩ ሰዎች የሊምፖፖን ወንዝ በዋና ለማቋረጥ ሲሞክሩ በአዞዎች ተውጠው እንደሚቀሩ ይነገራል። ሌሎች ደግሞ የክሩገርን ብሔራዊ ፓርክ በእግር ሲያቋርጡ በዝሆኖች ተረግጠው ወይም በአንበሶች ተበልተው ይሞታሉ። በቅርቡ የፓርኩ ሠራተኞች ሰው በላተኞች የሆኑ አምስት አንበሶች ገድለዋል። ዘ ስታር የተባለው የጆሃንስበርግ ጋዜጣ እንዳለው “አምስቱ አንበሶች ታርደው ሲታዩ ሆድቃቸው ውስጥ የሰው አካል ቅሪቶች ተገኝተዋል።” በዱር አራዊት የሚገደሉ ሕገ ወጥ ስደተኞች ቁጥር በትክክል አይታወቅም። ጋዜጣው እንዳለው “ቋሚ አሰሳ በሚደረግበት ጊዜ በድንገት የት እንደደረሱ የማይታወቁ በርካታ የሰው ኮቴዎች ተገኝተዋል። አንድ ሙሉ ዕድሜ ላይ የደረሰ ወንድ [አንበሳ] በአንድ ጊዜ 70 ኪሎ ግራም የሚመዝን ሥጋ ሊበላ ይችላል። በተለይ ጅቦችና ቀበሮዎች ከአንበሳ የተረፈውን ስለሚቀራመቱ የሰው አካል ቅሪት የማግኘቱ ዕድል በጣም አነስተኛ ነው።”

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ