የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • g98 4/8 ገጽ 30-31
  • ከዓለም አካባቢ

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ከዓለም አካባቢ
  • ንቁ!—1998
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • መጽሐፍ ቅዱስ ማንበብ ጥቅም አለው
  • ሕፃናት ምን ይሰማሉ?
  • በእግር ላይ የሚደርስ ጉዳት
  • አንድ ከመሆን ሁለት መሆን ይሻላል
  • ለድምፅ እንክብካቤ ማድረግ
  • ጉንዳኖችን በመድኃኒትነት
  • የፑንጃብ ተወላጆችና የኩላሊት ጠጠር
  • የነጭ ሽንኩርት ትንፋሽ
  • ልጆች ማምለጫ ቀዳዳ አላገኙም
  • ከሐሰት መድኃኒቶች ተጠንቀቁ
  • ስለ ዓለም ሰላም እተወራ ነው
  • ከዓለም አካባቢ
    ንቁ!—1998
  • ከዓለም አካባቢ
    ንቁ!—2012
  • ከዓለም አካባቢ
    ንቁ!—1997
  • ከዓለም አካባቢ
    ንቁ!—2003
ለተጨማሪ መረጃ
ንቁ!—1998
g98 4/8 ገጽ 30-31

ከዓለም አካባቢ

መጽሐፍ ቅዱስ ማንበብ ጥቅም አለው

አሶሲዬትድ ፕሬስ በዘገበው አንድ ጥናት መሠረት መጽሐፍ ቅዱስን ቢያንስ በሳምንት አንድ ጊዜ የሚያነቡ አሜሪካውያን አዘውትረው ከማያነቡ ሰዎች ይበልጥ ደስተኞች፣ እርካታ የሚሰማቸውና የመኖር ዓላማ ያላቸው ናቸው። በኢሊኖይስ የሚገኘው ማርኬት ፋክትስ ኢንኮርፖሬትድ የተባለው ድርጅት በነሲብ በተመረጡ ሰዎች ላይ ባደረገው ጥናት አዘውትረው መጽሐፍ ቅዱስ ከሚያነቡ ሰዎች መካከል 90 በመቶ የሚሆኑት ሁልጊዜ ወይም አብዛኛውን ጊዜ ሰላም እንዳላቸው ሲናገሩ በወር ውስጥ ከአንድ ለማይበልጥ ጊዜ መጽሐፍ ቅዱስ ከሚያነቡ ሰዎች መካከል ግን ሰላም እንዳላቸው የተናገሩት 58 በመቶ የሚሆኑት ብቻ ናቸው። በተጨማሪም አዘውትረው መጽሐፍ ቅዱስ ከሚያነቡ ሰዎች መካከል በሌሎች ዘንድ ተቀባይነት ማግኘታቸው የሚያሳስባቸው 15 በመቶ የሚሆኑት ሲሆኑ አዘውትረው መጽሐፍ ቅዱስ ከማያነቡ ሰዎች መካከል ግን ይህን የተናገሩት 28 በመቶ ሆነዋል። እንሞታለን ብለው አንዳንድ ጊዜ ወይም ብዙ ጊዜ የሚጨነቁት ከአዘውታሪ የመጽሐፍ ቅዱስ አንባቢዎች መካከል 12 በመቶ የሚሆኑት ሲሆኑ ከማያዘወትሩት መካከል ግን 22 በመቶ ናቸው።

ሕፃናት ምን ይሰማሉ?

አንድ ሕፃን የሚሰማቸው ቃላት መጠንና ቃና፣ ችግሮችን በመፍታትና ሐሳባዊ ምክንያቶችን በማፍለቅ ችሎታው ላይ ተጽእኖ እንደሚያሳድር አንድ ጥናት ማረጋገጡን ዘ ኒው ዮርክ ታይምስ ዘግቧል። በአዮዋ ዩኒቨርሲቲ የተደረገ አንድ ጥናት እንዳመለከተው በከፍተኛ ሞያ ከተሰማሩ ወላጆች የተወለዱ ልጆች በሰዓት በአማካይ 2,100 ቃላት ሲሰሙ የተራ ሞያተኞች ልጆች 1,200 ቃላት፣ መንግሥት በሚሰጠው ድጎማ የሚተዳደሩ ወላጆች ልጆች ደግሞ 600 ቃላት ብቻ ይሰማሉ። በተጨማሪም የወላጆቹ የድምፅ ቃና የሚያበረታታ፣ የሚነቅፍ፣ ፍቅርን የሚያንጸባርቅ ወይም የሚያስገድድ መሆኑ የሚያመጣው ለውጥ ተጢኖአል። ሁለት ዓመት ተኩል የፈጀው ጥናት እንዳመለከተው “እያንዳንዱ ሕፃን የሚሰማቸው ቃላት ብዛትና ቃና ልጁ በ4 ዓመት ዕድሜው ላይ በሚኖረው ችግሮችን የመፍታትና ሐሳብ የማፍለቅ ችሎታ ላይ ከፍተኛ ውጤት ያስከትላል።” ምርምሩን ካካሄዱት ሰዎች አንዱ የሆኑት ዶክተር ቤቲ ሐርት እንደተናገሩት በሰው ልጆች ሕይወት ውስጥ የመጀመሪያዎቹ ሦስት ዓመታት ልዩ የሆነ ሚና አላቸው። ምክንያቱም ሕፃናት አስተዳደጋቸውና የቋንቋ ችሎታቸው ሙሉ በሙሉ የተመካው በትላልቅ ሰዎች ላይ ነው።

በእግር ላይ የሚደርስ ጉዳት

በጀርመን አገር የሐኪሞች ፌዴራላዊ ማኅበር የጤና አገልግሎት በሰጠው ግምታዊ አኃዝ ከዚህች አገር ዜጎች ግማሽ የሚሆኑት በእግራቸው ላይ ጉዳት ያደርሳሉ። ናሳዊሸ ኖየ ፕሬሰ የተባለው ጋዜጣ እንደዘገበው “ብዙ ሰዎች ለእግራቸው በቂ እንክብካቤ አያደርጉም ወይም በጣም ጠባብ ጫማ በማድረግ እግራቸውን ያሰቃያሉ አለዚያም በሌላ መልኩ ጤናቸውን ሊጎዳ የሚችል ጫማ ያደርጋሉ።” ረዥም ተረከዝ ያለው ወይም ምቹ ያልሆነ ጫማ አዘውትሮ ማድረግ ጉልበት፣ ሽንጥ ወይም ወገብ ላይ ሕመም ሊያስከትል ይችላል። እንደ ጮቅ ያሉት በፈንገስ ምክንያት የሚመጡ በሽታዎችም በጣም እየተስፋፉ መጥተዋል። ለዚህ መከላከያው “እግር ሲታጠቡ ሳሙናው እስኪጠራ ድረስ ማለቅለቅና በየጣቶች መሀል ያለውን እርጥበት በጥንቃቄ ማድረቅ” እንደሆነ የሐኪሞች ፌዴራላዊ ማኅበር ይመክራል።

አንድ ከመሆን ሁለት መሆን ይሻላል

ለጤንነት የሚያግዝ አኗኗር በመልመድ ረገድ ከብቸኛ ሰዎች ይልቅ ተመሳሳይ ጥረት የሚያደርግ የኑሮ ጓደኛ ያላቸው ሰዎች ይበልጥ እንደሚሳካላቸው ኒው ሳይንቲስት መጽሔት ዘግቧል። እዚህ መደምደሚያ ላይ ሊደረስ የተቻለው በ1,204 ባልና ሚስት ላይ ጥናት ከተደረገ በኋላ እንደሆነ በአርካይቭስ ኦቭ ፋሚሊ ሜዲስን ላይ ተገልጿል። የለንደን የሃይጅንና የሞቃት አገሮች ሕክምና ትምህርት ቤት ባልደረባ የሆኑት እስቲፈን ፓይክ እንዲህ ብለዋል:- “ሁለቱም የኑሮ ተጓዳኞች ተመሳሳይ ምክር የሚከተሉ ከሆነ ማጨስ የማቆም፣ የኮሌስትሮል መጠናቸውንና ክብደታቸውን የመቀነስ ዕድላቸው ከፍተኛ ነው።”

ለድምፅ እንክብካቤ ማድረግ

ሥራቸው ብዙ ድምፅ ማሰማት የሚጠይቅባቸው አስተማሪዎችን የመሰሉ ሰዎች ድምፃቸውን የማድከምና ጨርሶም የማጣት አደጋ ሊገጥማቸው እንደሚችል ዘ ቶሮንቶ ስታር ጋዜጣ ዘግቧል። በጣም ጫጫታ በሚበዛበት አካባቢ ለመሰማት ሲባል ብዙ ጊዜ ድምፅን ከፍ አድርጎ መናገርም በድምፅ ሰረሰሮች ላይ ጉዳት ሊያደርስ ይችላል። በሹክሹክታ መናገርና ጉሮሮ ማጥራትን ልማድ ማድረግም ቢሆን በድምፅ ላይ ጉዳት እንደሚያስከትል የንግግርና የቋንቋ ችግሮች ሊቅ የሆኑት ቦኒ ማን ይናገራሉ። እኚሁ ሴት ችግሩ ተባብሶ ሥር እስኪሰድ ድረስ መቆየት ተገቢ እንዳልሆነና በአንገትና በትከሻ አካባቢ ያሉትን ጡንቻዎች ማዝናናት ጥሩ እንደሆነ ይመክራሉ። በመቀጠልም “ከሁሉ በላይ ጉሮሮ እንዳይደርቅ ማድረግ በጣም አስፈላጊ ነው” ይላሉ። ማን፣ መተዳደሪያችሁ ድምፃችሁ ከሆነ በቀኑ ውስጥ ደጋግማችሁ ውኃ እንድትጎነጩ ይመክራሉ።

ጉንዳኖችን በመድኃኒትነት

የቻይና ወታደሮች ሐኪም የነበሩት ው ጀቺንግ በ1947 በተደረገው ጦርነት ቁስለኞቻቸውን ለማዳን ሲጥሩ መድኃኒት ያልቅባቸዋል። የሚያደርጉት ጠፍቷቸው ግራ ሲጋቡ በአካባቢው ወደሚገኝ አንድ የቻይናውያን የባሕል መድኃኒተኛ ዘንድ ይሄዳሉ። እሱም ውኃ ውስጥ ጉንዳን ጨምረው እንዲያፈሉና በውኃው ቁስሉን እንዲያጥቡ፣ በተጨማሪም ልዩ ከሆኑ ጉንዳኖች የተዘጋጀ መድኃኒት እንዲጠቀሙ ይነግራቸዋል። ቻይና ቱዴይ እንደሚለው ዶክተር ው ያገኙት ውጤት በጣም አበረታች በመሆኑ ጉንዳኖች በመድኃኒትነት በሚሰጡት ጥቅም ላይ የረዥም ዓመታት ምርምር አካሄዱ። ከጉንዳኖች የሚሠሩ መድኃኒቶች የሰውነትን በሽታ የመከላከል ኃይል ያስተካክላሉ ብለው እንደሚያምኑ ከተናገሩ በኋላ “ጉንዳን የአልሚ ምግቦች ጎተራ ነው። ለሰው ልጆች አካል አስፈላጊ የሆኑ 50 አልሚ ምግቦች፣ 28 አሚኖ አሲዶች እና የተለያዩ ማዕድናትና ኬሚካላዊ ውህዶች ይገኙበታል” ብለዋል።

የፑንጃብ ተወላጆችና የኩላሊት ጠጠር

በፑንጃብ ክፍለ ሐገርና በአካባቢው የሚኖሩ ሕንዳውያን በዓለም ውስጥ ከሚገኝ ማንኛውም ሕዝብ ይበልጥ በኩላሊት ጠጠር የመያዝ ዕድላቸው ከፍተኛ እንደሆነ ኢንዲያ ቱዴይ ኢንተርናሽናል ዘግቧል። ፑንጃባውያን በሥራ ወዳድነታቸውና በጥሩ በላተኛነታቸው የታወቁ ቢሆኑም ከፍተኛ ሙቀት ባላቸው የበጋ ወራት በቂ ውኃ እንደማይጠጡ ዘገባው ያመለክታል። በዚህ ምክንያት በቅርቡ አካባቢያቸው በተደረገ አንድ ዓለም አቀፋዊ የሽንት አካላት ሕክምና ስብሰባ ላይ የዓለም “የጠጠር ቀጣና” ተብሎ ተጠርቷል። በዚህ አካባቢ የኩላሊት ጠጠሮች አማካይ መጠን ሁለትና ሦስት ሴንቲ ሜትር ሲሆን በአውሮፓና በዩናይትድ ስቴትስ ግን አንድ ሴንት ሜትር ያህል ነው። ይህ የሆነበት ምክንያት ብዙ ሕንዳውያን ጥቃቅን የሕመም ስሜቶችን ከቁም ነገር ስለማይቆጥሩና ፈጥነው የሕክምና እርዳታ ስለማይፈልጉ እንደሆነ ዘገባው አመልክቷል። ጤነኛ የሆኑ ሰዎች በየቀኑ ቢያንስ ሁለት ሊትር ንጹሕ ውኃ መጠጣት እንደሚኖርባቸው የሽንት አካላት ሐኪሞች ይመክራሉ።

የነጭ ሽንኩርት ትንፋሽ

የታይዋን መንግሥት በአገሪቱ የተከሰተውን የነጭ ሽንኩርት ተረፈ ምርት ለማቃለል አንዳንድ እርምጃዎችን ወስዷል። አስተዳዳሪዎች ሕዝቡ “ነጭ ሽንኩርት በብዛት እንዲበላ” ሲያበረታቱ ቆይተዋል በማለት ሳውዝ ቻይና ሞርኒንግ ፖስት ይናገራል። የእርሻ ምክር ቤት አባል የሆኑት ሚስተር ኩ ቴ-ዬህ “በዚህ ዓመት ያመረትነው ነጭ ሽንኩርት ከመጠን ያለፈ ነበር” ሲሉ አብራርተዋል። መንግሥት ፍጆታው ከፍ እንዲል ለማድረግ ነጭ ሽንኩርት እንዴት ባሉ ምግቦች ተጨምሮ ሊበላ እንደሚችል የሚገልጽ አነስተኛ መጽሐፍ በማሳተም ላይ ነው። ይሁን እንጂ ሚስተር ኩ “ሕዝቡ ተረፈ ምርቱን በአጠቃላይ እንዲጨርስ ማድረግ አይቻልም” ማለታቸውን ጋዜጣው ዘግቧል።

ልጆች ማምለጫ ቀዳዳ አላገኙም

“ልጆች በታላላቆቻቸው መካከል በተፈጠረ ጠብ መጠቃት የጀመሩት ጦርነት መላውን ማኅበረሰብ መንካት ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ ነው። ቦምቦችና ሚሳይሎች የሚገድሉት ዕድሜ እየለዩ አይደለም” ይላል ዚ ኢኮኖሚስት። “በአሁኑ ጊዜ በጣም የተለመደ የጦርነት ዓይነት የሆነው የእርስ በርስ ውጊያ አብዛኛውን ጊዜ አንድን አገር እንዳለ ለእልቂት ይዳርጋል። በአሁኑ ጊዜ በአንዳንድ አካባቢዎች የእርዳታ ድርጅቶች መሠረታዊ የሆኑ የምግብ እርዳታዎችን ከማቅረብ በተጨማሪ ልጆችን ትጥቅ ለማስፈታት ለሚደረገው ጥረት ትኩረት ለመስጠት ተገደዋል። በደረሱበት ሁሉ በስደተኞች፣ በቁስለኞችና በአስከሬኖች መካከል ልጆችን እንደሚያገኙ እርግጠኞች ናቸው።” ሁሉ ሰው ልጆችን እንደሚወድ ቢናገርም ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ የመከራ ገፈት ቀማሽ የሆኑት ልጆች ናቸው። ባለፈው ዓመት 24 ሚልዮን የሚያክሉ ዕድሜያቸው ከ18 ዓመት በታች የሆኑ ልጆች በጦርነት ምክንያት ከመኖሪያቸው እንደተፈናቀሉና ባለፉት አሥር ዓመታት 2 ሚልዮን የሚያክሉ እንደተገደሉ የእርዳታ ድርጅቶች ይገምታሉ። ከእነዚህ በተጨማሪ ከአራት እስከ አምስት ሚልዮን የሚሆኑ የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል። ዚ ኢኮኖሚስት “የደረሰውን የሥነ ልቦና ጉዳት ግን ይህ ነው ብሎ ለመናገር እንኳ የሚያስቸግር ነው” ብሏል።

ከሐሰት መድኃኒቶች ተጠንቀቁ

ዓመታዊ ሽያጩ 16 ቢልዮን ዶላር የደረሰው የሐሰት መድኃኒቶች ንግድ ተጧጡፏል። ለ ሞንድ የተባለው የፓሪስ ጋዜጣ እንዳለው “በየዓመቱ በመላው ዓለም ከሚሸጡት መድኃኒቶች መካከል 7 በመቶ የሚሆኑት የሐሰት መድኃኒቶች እንደሆኑ የዓለም የጤና ድርጅት (WHO) ይገምታል።” በብራዚል እስከ 30 በመቶ ሊደርስ የሚችል ሲሆን በአፍሪካ 60 በመቶ ይደርሳል። የሐሰት መድኃኒቶች እውነተኛውን መድኃኒት የሚመስሉ ርካሽ ምርቶች ወይም ምንም ጥቅም የሌላቸው፣ እንዲያውም መርዛማ በሆኑ ቅመሞች የተሞሉ ሊሆኑ ይችላሉ። ለ ሞንድ በምሳሌነት የጠቀሰው በኒጀር የደረሰውን የማጅራት ገትር ወረርሽኝ ነው። በዚህች አገር በሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች የተሰጣቸው ክትባት ንጹሕ ውሃ እንደነበረ ተደርሶበታል። በናይጀርያ ደግሞ 109 የሚያክሉ ልጆች ፀረ-ቀረት (antifreeze) የተጨመረበት ሽሮፕ በመውሰዳቸው ሞተዋል። ይኸው ጋዜጣ “ሆስፒታሎች እንኳን የዋጋ ቅናሽ ስለሚያገኙ ሕጋዊ ካልሆኑ የመድኃኒት ገበያዎች አዘውትረው ይገዛሉ” ብሏል። በብዙ አገሮች ያለው ሕግና አፈጻጸሙ በጣም ደካማ በመሆኑ የጤና ባለሥልጣኖች ለዚህ ችግር መፍትሔ ማግኘት በጣም አስቸጋሪ ሆኖባቸዋል።

ስለ ዓለም ሰላም እተወራ ነው

በስቶክሆልም የሚገኘው የዓለም አቀፍ ሰላም ምርምር ተቋም የ1997 የዓመት መጽሐፍ እንደገለጸው ከሆነ በአንድ ወቅት በቀዝቃዛው ጦርነት ውስጥ ከፍተኛ ሚና ይጫወቱ የነበሩት የአካባቢ ግጭቶች አሁን ያበቁ ይመስላል። በ1989 በቀዝቃዛው ጦርነት የመጨረሻ ዓመት ላይ 36 “ከፍተኛ ግጭቶች ነበሩ።” ይህ ቁጥር በ1996 ወደ 27 የወረደ ሲሆን ከአንዱ ማለትም በሕንድና በፓኪስታን መካከል ይደረግ ከነበረው በስተቀር የቀሩት በሙሉ የውስጥ ግጭቶች ነበሩ። ከዚህም በተጨማሪ ከሚሞቱት ሰዎች ቁጥር አንጻር ሲታይ ከእነዚህ ግጭቶች አብዛኞቹ በአውዳሚነት ስፋታቸው አነስተኛ ሆነው ተገኝተዋል ወይም በዝቅተኛ መጠን ቀጥለዋል። በደቡብ አፍሪካ የሚታተመው ዘ ስታር መጽሔት “የዚህን ያህል ወደ ዓለም ሰላም የቀረበ ትውልድ ኖሮ አያውቅም” ሲል ደምድሟል። ታይም መጽሔት ደግሞ “የአሜሪካ የበላይነት . . . በዚህ መቶ ዘመን ታይቶ የማይታወቅና በሰው ልጅ ታሪክም ቢሆን እምብዛም ያልታየ ዓለም አቀፍ ሰላምና ፀጥታ ለመላው ዓለም አጎናጽፏል” ብሏል።

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ