የዝሆን ጥርስ ምን ያህል ተፈላጊ ነው?
ኬንያ የሚገኘው የንቁ! ዘጋቢ እንዳጠናቀረው
በሰኔ ወር 1997 በሃራሬ፣ ዚምባቡዌ በተደረገ አንድ ዓለም አቀፍ ስብሰባ ላይ በዝሆን ጥርስ ንግድ ላይ ለሰባት ዓመታት ያህል ተጥሎ የቆየውን ዓለም አቀፍ ማዕቀብ ለማላላት ከ138 አገሮች የመጡ ልዑካን ድምፀ ውሳኔ አስተላልፈው ነበር። የጦፈ ክርክር ከተደረገ በኋላ የተላለፈው ውሳኔ አንዳንድ ቅድመ ሁኔታዎችን በማስቀመጥ በደቡባዊ አፍሪካ የሚገኙ ሦስት አገሮች ቦትስዋና፣ ናሚቢያ እና ዚምቧቡዌ ለአንዲት አገር ማለትም ለጃፓን ብቻ የዝሆን ጥርስ እንዲሸጡ ፈቀደ። ከደቡባዊ አፍሪካ የመጡ ተወካዮች ውሳኔውን በፈንጠዝያ ሲቀበሉት ሌሎች ልዑካን ግን በአፍሪካ በሚገኙ ዝሆኖች ላይ ምን ዓይነት ሁኔታ ሊከተል እንደሚችል በማሰብ ስጋት አድሮባቸዋል።
ሃኒባል በሦስተኛው መቶ ዘመን ከዘአበ የሮም ሠራዊትን ጦርነት በገጠመ ጊዜ በርከት ያሉ ለማዳ የአፍሪካ ዝሆኖችን አስከትሎ ነበር። በዚያ ጊዜ በአፍሪካ የነበሩት ዝሆኖች ቁጥር በአሥር ሚልዮን የሚቆጠር እንደነበር የሚገመት ሲሆን ከኬፕ እስከ ካይሮ ባሉት ቦታዎች ሁሉ ይገኙ ነበር።
አሁን ሁኔታው ተለውጧል። አንድ ታዛቢ እንዳሉት “ዝሆኖች እንደ ባሕር፣ ሰዎች እንደ ደሴት የነበሩበት ሁኔታ ተለውጦ አሁን ሰዎች እንደ ባሕር፣ ዝሆኖች ደግሞ እንደ ደሴት ሆነዋል።” የሰው ልጅ በቁጥር እየበዛ ሲሄድ መኖሪያ ለማግኘት በሚያደርገው መስፋፋት ዝሆኖች መኖሪያቸው እየተመናመነ ይሄዳል። የዝሆኖች ቁጥር እያሽቆለቆለ እንዲሄድ የሚያደርገው ሌላው ምክንያት የሰሃራ በረሃ በደቡብ አቅጣጫ እየተስፋፋ መሄዱ ነው።
ከሁሉም የሚብሰው ምክንያት ግን የዝሆን ጥርስ ያለው ተፈላጊነት ነው። የዝሆን ጥርስ የሚፈለገው እንደ ነብር አጥንትና እንደ አውራሪስ ቀንድ ለመድኃኒትነት ያገለግላል በሚል መሠረተ ቢስ ሐሳብ አይደለም። ከዚያ ይልቅ የዝሆን ጥርስ ውብ የሆነ፣ ማራኪነት ያለው፣ ለረዥም ጊዜ በደህና ሁኔታ ተጠብቆ ሊቆይ የሚችልና በቀላሉ ሊቀረጽ የሚችል ነው። ከጥንት ዘመን ጀምሮ የዝሆን ጥርስ ከከበሩና ተፈላጊ ከሆኑ ነገሮች መካከል ሲመደብ ቆይቷል።
ሃኒባል ከሞተ ከአራት መቶ ዓመት በኋላ የሮማ ንጉሣዊ ግዛት የዝሆን ጥርስ ፍላጎትን ለማሟላት በሰሜን አፍሪካ የሚገኙ በርካታ ቁጥር ያላቸው ዝሆኖች ጨፍጭፏል። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በተለይ በምዕራቡ ዓለም የዝሆን ጥርስ የማግኘት ከፍተኛ ፍላጎት ተቀጣጥሏል። በዚህ መቶ ዓመት መግቢያ ላይ የዝሆን ጥርስ እንደ ቀድሞው ለሥነ ጥበብና ለሃይማኖታዊ ቅርጻ ቅርጾች ሳይሆን ለፒያኖ ኪቦርድ መሥሪያ ተፈላጊነቱ ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ ከፍ ብሏል። ባትል ፎር ዚ ኤለፋንትስ የተባለው መጽሐፍ እንደዘገበው በ1910 ብቻ በዩናይትድ ስቴትስ 350,000 ኪቦርድ ለመሥራት 700 ቶን የሚሆን የዝሆን ጥርስ (13,000 ዝሆኖች ተገድለው ማለት ነው) ጥቅም ላይ ውሏል።
ሕገ ወጥ አዳኞች የሚያካሄዱት ጭፍጨፋ
ከአንደኛው የዓለም ጦርነት በኋላ የዝሆን ጥርስ ያለው ተፈላጊነት ቀነሰ። አዳዲስ የዱር አራዊት ጥበቃ ሕጎች ወጡ። በዚህም የተነሳ የዝሆኖች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መጣ። ይሁን እንጂ በ1970ዎቹ መግቢያ ላይ መጠነ ሰፊ የሆነ ግድያ እንደገና ተጀመረ። በዚህ ጊዜ ዋነኞቹ የዝሆን ጥርስ ሸማች አገሮች በቅርብ ጊዜ የበለጸጉ በእስያ የሚገኙ አገሮች ናቸው።
በዚህ ጊዜ በአፍሪካ በሚገኙት ዝሆኖች ላይ ከባድ አደጋ እንዲያንዣብብ አስተዋጽኦ ያደረጉ ሁለት ነገሮች አሉ። አንደኛው ቀላል ክብደት ያላቸውና የተራቀቁ የጦር መሣሪያዎችን እንደ ልብ ማግኘት መቻሉ ነው። በአንድ ዝሆን ላይ ብቻ ሳይሆን በመላው መንጋ ላይ የጥይት እሩምታ መክፈት ተቻለ። ሁለተኛው ደግሞ በኤሌክትሪክ የሚሠሩ ቅርጽ ማውጫ መሣሪያዎች በጥሬ ዕቃነት የመጡ የዝሆን ጥርሶችን ወዲያው ለውጠው ለገበያ ማቅረብ ማስቻላቸው ነው። ቀደም ባሉት ጊዜያት አንድ ጃፓናዊ ቅርጽ አውጪ አንድን የዝሆን ጥርስ ለመቅረጽ አንድ ዓመት ይወስድበት ነበር። ይሁን እንጂ ስምንት ሠራተኞች ያሉት አንድ ፋብሪካ በአንድ ሳምንት ጊዜ ውስጥ በኤሌክትሪክ በሚሠራ ቅርጽ ማውጫ መሣሪያ አማካኝነት የ300 ዝሆኖችን ጥርስ በመጠቀም ጌጣጌጥና ሃንኮ (በጃፓን በስፋት የሚታወቀው የስም ማኅተም) መሥራት ይችላል። የዝሆን ጥርስ ያለው ተፈላጊነት ከፍ እያለ መምጣቱ ዋጋው እንዲያሻቅብ አስተዋጽኦ አድርጓል። እርግጥ ነው ከፍተኛውን ገንዘብ የሚዝቁት ሕገ ወጥ አዳኞቹ ሳይሆኑ አሻሻጮቹና ነጋዴዎቹ ናቸው፤ በዚህም ሳቢያ ብዙዎቹ የናጠጡ ሀብታሞች ሆነዋል።
በዝሆኖች ላይ የሚደርሰው ጉዳትም የዚያኑ ያህል አስከፊ ነው። ታንዛኒያ በሃያ ዓመት ጊዜ ውስጥ በአብዛኛው ሕገ ወጥ በሆኑ አዳኞች ምክንያት ከዝሆን ሀብቷ ውስጥ 80 በመቶ የሚሆነውን አጥታለች። ኬንያ 85 በመቶ፣ ኡጋንዳ ደግሞ 95 በመቶ የሚሆነውን የዝሆን ሃብታቸውን አጥተዋል። መጀመሪያ ላይ ሕገ ወጥ አዳኞቹ ረዥም ጥርስ ለማግኘት ሲሉ ትልልቆቹን ዝሆኖች ይገድሉ ነበር። ሆኖም የትላልቆቹ ዝሆኖች ቁጥር እየተመናመነ በመሄዱ ሕገ ወጥ አዳኞቹ አነስተኛ ጥርስ ባላቸው ትንንሽ ዝሆኖች ላይ ማነጣጠር ጀመሩ። በእነዚያ ዓመታት ከአንድ ሚልዮን የሚበልጡ ዝሆኖች ለጥርሶቻቸው ሲባል ሳይገደሉ አልቀረም። ይህም በአፍሪካ የሚገኙትን ዝሆኖች ቁጥር ወደ 625,000 ዝቅ አድርጎታል።
በዓለም አቀፍ ደረጃ የተጣለ ማዕቀብ
የዝሆን ጥርስ ንግድን ለመቆጣጠርና በዝሆኖች ላይ የሚደርሰውን እልቂት ለማስቆም የተደረጉት ጥረቶች ሁሉ ሳይሳኩ ቀርተዋል። በመጨረሻም ጥቅምት 1989 ስዊዘርላንድ በተደረገ አንድ ስብሰባ ላይ ሊጠፉ በተቃረቡ የእፅዋትና የእንስሳት ዝርያዎች ላይ የሚካሄደውን ዓለም አቀፍ ንግድ በተመለከተ የተደረሰው ስምምነት በአባላት አገሮቹ መካከል የዝሆን ጥርስ ንግድ ልውውጥ እንዳይደረግ አገደ። በየጫካው ያሉትን ዝሆኖች ለመጠበቅ የተጣለውን እገዳ ለማጠናከር ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ ተመድቧል።
አንዳንዶች በዝሆን ጥርስ ላይ የተጣለው እገዳ የጥቁር ገበያ ዋጋን ከፍ እንደሚያደርገውና ሕገ ወጡን አደን እንደሚያባብሰው ተንብየው ነበር። ሁኔታው ግን የተገላቢጦሽ ሆኖ ነው የተገኘው። ዋጋው አሽቆለቆለ፤ እንዲሁም በአንድ ወቅት አትራፊ የነበረው ገበያ ነጠፈ። ለምሳሌ ያህል በሕንድ የዝሆን ጥርስ ሽያጭ 85 በመቶ ሲቀንስ በአገሪቱ የነበሩ አብዛኞቹ የእጅ ጥበብ ሠራተኞች ሌላ የሥራ መስክ መፈለግ ግድ ሆኖባቸዋል። ሕገ ወጥ አደንም በሚያስገርም ፍጥነት ቀንሷል። እገዳው ከመጣሉ በፊት በኬንያ ያሉ ሕገ ወጥ አዳኞች በዓመት እስከ 2,000 የሚጠጉ ዝሆኖች ይገድሉ ነበር። በ1995 ይህ አኃዝ ወደ 35 አሽቆልቁሏል። ከዚህም በላይ በ1989 በኬንያ 19,000 የነበረው የዝሆኖች ቁጥር ዛሬ 26,000 አካባቢ ደርሷል።
በእነዚህ ምክንያቶች ተቀማጭነቱ ለንደን የሆነው የአካባቢ ጥናት ድርጅት “ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ባለው የአካባቢ ጥበቃ ታሪክ ውስጥ ከተገኙት ታላላቅ ድሎች አንዱ” እንደሆነ በመግለጽ በዝሆን ጥርስ ንግድ ላይ የተደረገውን እገዳ አወድሶታል። ሆኖም የዚህ ዓይነት ስሜት የተሰማቸው ሁሉም አይደሉም፤ በተለይ ደግሞ በደቡባዊ አፍሪካ የሚገኙ አገሮች ደስተኞች አልነበሩም።
በደቡባዊ አፍሪካ የሚገኙ ዝሆኖች
ከ200,000 የሚበልጡ ዝሆኖች ወይም በመላው አፍሪካ ከሚገኙት ዝሆኖች ውስጥ ሲሶዎቹ የሚገኙት በደቡባዊ አፍሪካ አገሮች ውስጥ ነው። ይህ የሆነበት አንዱ ምክንያት በእነዚህ አገሮች ያለው የአራዊት ጥበቃ መምሪያ ጥብቅ በመሆኑና በምሥራቅ እና በማዕከላዊ አፍሪካ ካሉት አገሮች በተለየ መንገድ የዝሆን መንጋዎችን የሚፈጁ መሣሪያ የታጠቁ ሚሊሽያዎች በብዛት ባለመኖራቸው ሳይሆን አይቀርም።
ይሁን እንጂ የዝሆኖች ቁጥር እየጨመረ በሄደ መጠን ብዙውን ጊዜ በዝሆኖችና በገጠር አካባቢ በሚኖሩ ሰዎች መካከል ግጭት ይፈጠራል። አንድ ትልቅ ዝሆን ብዙ ስለሚመገብ በአንድ ቀን ውስጥ እስከ 300 ኪሎ ግራም የሚመዝኑ ቅጠላ ቅጠሎችን ሙልጭ አድርጎ ሊጨርስ ይችላል። በአካባቢህ ዝሆኖች የሚኖሩ ከሆነ ሁኔታውን በሚገባ ታውቀዋለህ።
ተቀማጭነቱ ዚምባቡዌ የሆነው አፍሪካ ሪሶርስስ ትረስት የተባለው ድርጅት እንዲህ ሲል ገልጿል:- “በአፍሪካ ገጠራማ አካባቢዎች የሚኖሩ አብዛኞቹ ሰዎች ዝሆኖችን የሚመለከቷቸው በፍርሃት፣ በጥርጣሬና በጥላቻ ነው። ዝሆኖች ሰብላቸውን በመብላት ወይም ከብቶቻቸውን ረጋግጠው በመግደል በጥቂት ሰዓት ውስጥ የሰዎችን መተዳደሪያ ሊያወድሙ ይችላሉ። በተጨማሪም ቤቶችንና ትምህርት ቤቶችን፣ የከብት መጠለያዎችን፣ የፍራፍሬ ዛፎችን፣ ግድቦችንና እርከኖችን ያጠፋሉ። በየዕለቱ የአካባቢው ጋዜጦች ዝሆኖች ስላደረሱት ጥፋት የሚዘግብ ዜና ይዘው ይወጣሉ።”
በደቡባዊ አፍሪካ ያሉ አገሮች የዝሆን ሀብታቸውን በጥሩ ሁኔታ ጠብቀው ማቆየት በመቻላቸው ተደስተዋል። ይሁን እንጂ ለጥበቃ የሚወጣው ወጪ በጣም ከፍተኛ ነው፤ እንዲሁም በሌሎች የአፍሪካ አገሮች በተፈጠሩት ችግሮች ምክንያት እነርሱ ሊቀጡ እንደማይገባቸው ይሰማቸዋል። ቁጥጥር የተደረገበት የዝሆን ጥርስ ንግድ ለጥበቃ የሚሆን ገንዘብ ያስገኛል እንዲሁም በገጠር የሚኖሩ ገበሬዎች ለሚደርስባቸው ውድመት ማካካሻ ይሆናል ብለው ያስባሉ።
የዝሆን ጥርስ ክምር
ዝሆኖች በብዛት በሚገኙባቸው አገሮች የዝሆን ጥርስ ክምችት ይኖራል። የጥርስ ክምችቱ የሚፈጠረው የዝሆኖችን ቁጥር ለመቀነስ ተብሎ በሚወሰደው የግድያ እርምጃና በተፈጥሮ ምክንያት ከሚሞቱ ዝሆኖች እንዲሁም በሕገ ወጥ አደን የተገኙ በርካታ ቁጥር ያላቸው ጥርሶች በመወረሳቸው ምክንያት ነው። እነዚህ የዝሆን ጥርሶች ምን ይደረጋሉ?
ኬንያ የነበራትን የዝሆን ጥርስ ክምችት አቃጥላለች። ከሐምሌ 1989 ወዲህ ኬንያ በሚልዮን ዶላር የሚቆጠር ዋጋ ያላቸውን የዝሆን ጥርሶች በይፋ ያቃጠለች ሲሆን ይህንን ስታደርግም ከውጪ አገሮች ምንም ዓይነት የማካካሻ ገንዘብ አልተሰጣትም። እንዲሁም ዛምቢያ በ1992 በአገሯ የነበረውን የዝሆን ጥርስ ክምችት አቃጥላለች። እንዲህ ያደረጉበት ምክንያት ኬንያና ዛምቢያ በዝሆን ጥርስ ንግድ ውስጥ እጃቸውን ማስገባት እንደማይፈልጉ ግልጽ ለማድረግ ነው።
ሌሎች አገሮች ደግሞ ወደፊት ገበያ ላይ ለማዋል አከማችተው አስቀምጠውታል። ትራፊክ (TRAFFIC) የተባለው የዓለማችን ትልቁ የዱር እንስሳት ተቆጣጣሪ ድርጅት እንደገመተው በአሁኑ ጊዜ በአፍሪካ አገሮች 46 ሚልዮን ዶላር የሚያወጣ 462 ቶን የሚሆን የዝሆን ጥርስ ቁልል እንደሚገኝ ተናግሯል። ለጃፓን እንዲሸጡ አሁን ፈቃድ የተሰጣቸው ሦስቱ አገሮች ማለትም ቦትስዋና፣ ናሚቢያ እና ዚምባቡዌ 120 ቶን የዝሆን ጥርስ ክምችት አላቸው። በዚህም የተነሳ ብዙዎች ‘የኢኮኖሚ ችግር ያለባቸው ሰዎች በሚኖሩባቸው አገሮች የዝሆን ጥርሶቹ በመጋዘን ተቀምጠው አቧራ እንዲጠጡ የሚደረገው ለምንድን ነው? ጥርሶቹ ተሸጠው ገንዘቡ ለጥበቃ ሥራ እንዲውል ለምን አይደረግም?’ ብለው ይጠይቃሉ።
የጉዳዩ አሳሳቢነት አሁንም እንዳለ ነው
በዝሆን ጥርስ ላይ የተጣለውን እገዳ ላላ ማድረጉ ለዝሆኖች ጥበቃ ጠቃሚ እንደሆነ አንዳንድ የአፍሪካ አገሮች ቢናገሩም ሌሎች ደግሞ በሕገ ወጥነት የሚደረገው አደን እንዳያንሰራራ የሚያደርገው ብቸኛው መፍትሄ በዝሆን ጥርስ ንግድ ላይ አጠቃላይ እገዳ መጣል እንደሆነ ያምናሉ። ትልቁ አሳሳቢ የሆነው ነገር ንግዱን ሙሉ በሙሉ መቆጣጠር የሚቻልበት መንገድ ነው። የንግዱ ሥርዓት በሕገ ወጥ መንገድ የተገኙ የዝሆን ጥርሶች ወደ ሕጋዊው ንግድ ሰርገው መግባት የሚችሉበትን መንገድ ይከፍት ይሆን? ያለ ፈቃድ የሚደረገውን አደን በተመለከተስ? እገዳውን ላላ ማድረግ ማለት ወደፊትም ይበልጥ ሊላላ ይችላል በማለት ሰዎች ተጨማሪ ዝሆኖችን እንዲገድሉና ጥርሶቹን ደብቀው እንዲያከማቹ መንገድ መክፈት ማለት ይሆን?
የጦር መሣሪያዎች በአፍሪካ ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ እንደ ልብ መገኘት መቻላቸው ሁኔታውን ይበልጥ አስጊ ያደርገዋል። በእነዚህ አካባቢዎች የሚደረጉ የእርስ በርስ ጦርነቶች በብዙ ሰዎች እጅ አውቶማቲክ መሣሪያዎች እንዲገቡ አጋጣሚ ስለከፈቱ ከባድ የኢኮኖሚ ችግር ያለባቸው ሰዎች ገንዘብ ለማግኘት ሲሉ እነዚህን መሣሪያዎች ከመጠቀም ወደኋላ አይሉም። የምሥራቅ አፍሪካ የዱር አራዊት ማኅበር ዲሬክተር የሆኑት ነህማያ ሮቲክ እንዲህ ብለው ጽፈዋል:- “[እንደገና ባንሰራራው ንግድ ምክንያት] የዝሆን ጥርስ እንደገና ገበያ ላይ በመዋሉ አዳኞቹ እነዚህን መሣሪያዎች ዝሆኖች ላይ ማነጣጠራቸው የማይቀር ነው። እንዲያውም በአንድ ከተማ ያለን ባንክ ከመዝረፍ ይልቅ በጣም ሰፊ በሆነው ጫካ ዝሆን መግደሉ ይበልጥ ቀላል ነው።”
ሌላው ችግር ደግሞ ሕጋዊ ያልሆኑ አደኖችን ለማስቀረት የሚደረገው ጥረት ከፍተኛ ወጪ የሚያስወጣ ከመሆኑም በላይ በጣም አዳጋች ነው። ዝሆኖች የሚርመሰመሱበትን አካባቢ እየተዘዋወሩ መጠበቅ ከፍተኛ የገንዘብ ወጪ ይጠይቃል። በምሥራቅ አፍሪካ እንዲህ ማድረጉ በጣም ከባድ ነው።
ዝሆኖች የወደፊት ዕጣ ፈንታ ምንድን ነው?
በዝሆን ጥርስ ንግድ ላይ የተጣለው እገዳ መላላቱ የሚያስከትለው ውጤት ወደፊት የምናየው ነገር ይሆናል። ሆኖም ነገሮች ቢሰምሩ እንኳ በዝሆኖች ላይ የተጋረጠው አስጊ ሁኔታ እንዳለ ይቀጥላል። ለእርሻና ለሌላ ዓላማ የሚውል መሬት የሚፈልጉ ሰዎች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱም በዝሆኖች ሕይወት ላይ አስጊ ሁኔታ ፈጥሯል። በደቡባዊ አፍሪካ አካባቢ ብቻ በአብዛኛው ለግብርና የሚሆን መሬት ለማግኘት ሲሉ ሰዎች በየዓመቱ 850,000 ሄክታር የሚሸፍን ደን ይመነጥራሉ። ይህም ከእስራኤል የቆዳ ስፋት ግማሽ ያህሉን የሚሸፍን ደን ይወድማል ማለት ነው። የሰዎች ቁጥር እየበዛ ሲሄድ እንደ ደሴት ያሉት ዝሆኖች ቁጥር ይበልጡኑ እየተመናመነ ይሄዳል።
ዎርልድ ዎች የተባለው መጽሔት እንዲህ ሲል ይገልጻል:- “የአፍሪካ ዝሆኖች የወደፊት ዕጣ በጣም የጨለመ መሆኑን ችግሩን የተገነዘቡ ሰዎች ሁሉ የሚስማሙበት ጉዳይ ነው። ዝሆኖች የሚኖሩበት ክልል [በሰዎች ቁጥር መጨመር ምክንያት] እየተመናመነ መሄዱ በዚህም ሆነ በዚያ በርካታ ቁጥር ያላቸው ዝሆኖች ያለ እድሜያቸው እንዲቀጩ እንደሚያደርግ የታወቀ ነው። ዝሆኖች በሕጋዊ ፈቃድ በሚካሄድ አደን፣ ቁጥራቸውን ለመመጠን ተብሎ በሚወሰድባቸው የግድያ እርምጃም ሆነ ሕገ ወጥ በሆኑ አዳኞች ባይገደሉ እንኳ በረሃብ ምክንያት ቁጥራቸው በፍጥነት ማሽቆልቆሉ አይቀሬ ነው።”
እንዲህ ዓይነቱ የጨለመ ተስፋ የዝሆኖች ፈጣሪ ከሆነው ከይሖዋ አምላክ አመለካከትም ሆነ ዓላማ ጋር የሚስማማ አይደለም። ኢየሱስ ክርስቶስ የተናገራቸው የሚከተሉት ቃላት አምላክ ለፍጥረታቱ ያለውን አሳቢነት የሚያሳዩ ናቸው:- “አምስት ድንቢጦች በአሥር ሳንቲም ይሸጡ የለምን? ከእነርሱም አንዲቱ ስንኳ በእግዚአብሔር ፊት አትረሳም።” (ሉቃስ 12:6) አምላክ በጣም ትንሽ የሆነችን አንዲት ድንቢጥ የማይረሳ መሆኑ ግዙፍ የሆነው ዝሆን እየደረሰበት ያለውን ችግር ችላ ብሎ እንደማያልፍ እርግጠኞች እንድንሆን ሊያደርገን ይችላል።
[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
የዝሆን ጥርስ
“የዝሆን ጥርስ ውብ ለመሆኑ ምንም የሚያጠራጥር ነገር የለም። ለጌጣጌጥ ወይም ለቅርጻ ቅርጽ መሥሪያ ከሚውሉ ከሌሎች ነገሮች በተለየ መንገድ የዝሆን ጥርስ አንጸባራቂና አብረቅራቂ ነው። ይሁን እንጂ ሰዎች የዝሆን ጥርስ ከዝሆን የሚገኝ መሆኑን የሚዘነጉ ይመስለኛል። አንድ ሰው የዝሆን ጥርስን ከከበረ ድንጋይ፣ እንደ ጥቁር እንጨት ከመሳሰሉ ውድ እንጨቶች ሌላው ቀርቶ ከወርቅና ከብር ጋር ሊፈርጀው ይችላል። ይሁን እንጂ ከእነዚህ ሁሉ ፈጽሞ የተለየ ነው። ሌሎቹ ከእንስሳት የሚገኙ አይደሉም። አንድ ሰው ከዝሆን ጥርስ የተሠራ የሚያምር አምባር ወይም ውብ ጌጥ በሌላ ሰው እጅ ላይ ሲመለከት በአንድ ወቅት ጥርሱን ለመመገቢያ፣ ለመቆፈሪያ፣ ለመውጊያ፣ ለመጫወቻና ለማጥቂያ ይጠቀምበት ከነበረ ከአንድ ዝሆን የተገኘ መሆኑን ማወቅ ይኖርበታል። ከዚህም በላይ ያቺ ቁራጭ የዝሆን ጥርስ ጌጥ በአንድ ሰው እጅ ላይ ለመታየት የበቃችው አንድ ዝሆን ተሰውቶ እንደሆነ ማወቅ ይኖርበታል።”—ኤለፋንት ሜሞሪስ፣ በሲንቲያ ሞስ የተዘጋጀ
[በገጽ 27 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
ዝሆን
ዝሆኖች እጅግ ከፍተኛ የሆነ ኃይል አላቸው። በሚቆጡበት ጊዜ ምድር ትንቀጠቀጣለች። አንድ ዝሆን እንደ አንድ ትንሽ ድንጋይ በኩንቢው ይዞ ወደ ሰማይ ሊያጎንህ ይችላል። ሆኖም ዝሆን በኩንቢው ሊደባብስህ ወይም ከእጅህ ላይ ምግብ ሊወስድ ይችላል። ዝሆኖች ብልሆች፣ ለመረዳት የሚያስቸግር ባሕርይ ያላቸውና የሚያስደንቁ ፍጥረታት ናቸው። ጠንካራ የቤተሰብ ትስስር ያላቸውና አንዳቸው የሌላውን ቁስል የሚያክሙ፣ የታመሙትን የሚያስታምሙና ለሞተ የቤተሰባቸው አባል ሃዘን የሚሰማቸው ናቸው። የሌሎች ዝሆኖችን አጥንት ከሌሎች እንስሳት ቅሪቶች ለይተው ያውቃሉ። ይህንንም አጥንቶቹን በመበተን ወይም በማቅበር ያሳያሉ።
[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ሁለት አገሮች የነበሯቸውን የዝሆን ጥርሶች አቃጥለዋል፤ ሌሎች ደግሞ ወደፊት ገበያ ላይ ለማዋል አከማችተው አስቀምጠዋቸዋል