የመጽሐፍ ቅዱስ አመለካከት
አጋንንት በእርግጥ አሉ?
በ17ኛውና በ18ኛው መቶ ዘመን በአብዛኛው የአውሮፓ ክፍል በአስማተኞችና በጠንቋዮች ላይ ይህ ነው የማይባል የስደት ዘመቻ ተካሂዶ ነበር። አስማተኛ ነው የሚባል ሰው ሁሉ ከባድ መከራ ይደርስበት ነበር። በሐሰት ከተከሰሱት ሰዎች መካከል አንዳንዶቹ ከሚደርስባቸው የምርመራ ሥቃይ ለመዳን ሲሉ ብቻ አስማተኞች መሆናቸውን አምነዋል። በጥርጣሬና በሐሜት ብቻ የተገደሉ ሰዎች በጣም በርካታ ናቸው።
እንዲህ ያለው እንደ አስማት ያሉትን አጋንንታዊ ሥራዎች በሚሠሩ ሰዎች ላይ የተፈጸመው የግድያ ዘመቻ የቅዱሳን ጽሑፎች ድጋፍ እንዳለው ቢነገርለትም በአክራሪነት ላይ የተመሠረተ ለመሆኑ ሊካድ አይችልም። ክርስቲያኖች አስማተኞችንም ሆነ ማንኛውንም አጋንንታዊ ሥራዎች የሚፈጽሙ ሰዎችን የማሰቃየትና የመግደል ሥልጣን አልተሰጣቸውም። (ሮሜ 12:19) በዛሬው ጊዜ በስፋት ተንሰራፍቶ የሚገኘው ዝንባሌስ እንዴት ያለ ነው?
ልል የሆነ ዝንባሌ
በአሁኑ ጊዜ በሕዝበ ክርስትና ውስጥ የሚኖሩ ብዙ ሰዎች መናፍስታዊ ድርጊቶችን እንደ ከባድ ነገር አድርገው አይቆጥሩም። አንዳንዶች የማወቅ ጉጉት ስላደረባቸው ብቻ እንደ ኮከብ ቆጠራ፣ አስማት፣ ሟርትና ጥንቆላ ባሉት ድርጊቶች ይካፈላሉ። እነዚህን የአስማት ሥራዎች አጋንንታዊ እንደሆኑ አድርገው አይቆጥሩም። የኪነ ጥበብ ሰዎች፣ ስፖርተኞችና የፖለቲካ ሰዎች በአስማታዊ ድርጊቶች የሚካፈሉ መሆናቸውን በይፋ የሚናገሩበት ጊዜ አለ። አንድ ኢንሳይክሎፔድያ እንደሚለው አንዳንድ መጻሕፍትና ፊልሞች ጠንቋዮችና አስማተኞች “በማንም ላይ ጉዳት የማያደርስ ከተፈጥሮ ውጭ የሆነ ኃይል ያላቸው፣ ማራኪና በጥቂቱ ከሌሎች የተለዩ ዓይነት ሰዎች አድርገው ያቀርቧቸዋል።” ሕፃናትን ለማዝናናትና ለማስተማር ተብለው የተዘጋጁ ጽሑፎችና ፊልሞች አስማታዊ ድርጊቶችን የሚያስፋፉ ሊሆኑ ይችላሉ።
ለአጋንንታዊ ሥራዎች እንዲህ ያለ ልል የሆነ ዝንባሌ መያዝ አጋንንት መኖራቸውን እስከ መካድ ሊያደርስ ይችላል። አጋንንት እንዳሉና እኛን ለመጉዳት ብርቱ ጥረት በማድረግ ላይ መሆናቸውን ታምናለህ? በአሁኑ ጊዜ ከሚኖሩ ሰዎች አብዛኞቹ ከአጋንንት ጋር ተገናኝተው እንደማያውቁና የሚፈጽሟቸውንም ተግባሮች ተመልክተው እንደማያውቁ ይናገራሉ። ታዲያ አጋንንት በእርግጥ አሉ?
አለማመን ግራ በሚያጋባ ሁኔታ ውስጥ ይጥላል
መጽሐፍ ቅዱስን እንቀበላለን እያሉ አጋንንት መኖራቸውን የማያምኑ ሰዎች ግራ በሚያጋባ ሁኔታ ውስጥ ይወድቃሉ። በአጋንንት መኖር የማያምኑ ከሆኑ መጠነኛም ቢሆን በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ እምነት ይጎድላቸዋል ማለት ነው። ለምን? ምክንያቱም መጽሐፍ ቅዱስ ከሰው የበለጠ ኃይል ያላቸው ክፉ መንፈሳዊ ፍጥረታት መኖራቸውን ያስተምራል።
የመጽሐፍ ቅዱስ የመጀመሪያ መጽሐፍ የሆነው ዘፍጥረት የማሰብ ችሎታ ያለው አንድ ፍጡር በእባብ ተጠቅሞ ሔዋንን እንዴት እንዳሳተና በአምላክ ላይ እንድታምፅ እንዳደረገ ይተርካል። (ዘፍጥረት 3:1-5) የመጨረሻ የመጽሐፍ ቅዱስ መጽሐፍ የሆነው ራእይ ይህ ክፉ አታላይ፣ “የቀደመው እባብ፣” “ዓለሙንም ሁሉ የሚያስተው፣ ዲያብሎስና ሰይጣን የሚባለው ታላቁ ዘንዶ” እንደሆነ ይገልጻል። (ራእይ 12:9) ሰይጣን ሌሎች መላእክትንም እንዲያምፁ በማድረግ በኩል ተሳክቶለታል። (ይሁዳ 6) እነዚህ ማዕረጋቸውን የተገፈፉ መላእክት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አጋንንት ተብለው ይጠራሉ። በምድር አካባቢ የሚንቀሳቀሱ በመሆናቸው በአምላክና አምላክን በሚያገለግሉ ሁሉ ላይ በጣም ተቆጥተዋል።—ራእይ 12:12
ሰይጣንና አጋንንት በሰዎች ላይ ተጽእኖና ጉዳት የማድረስም ሆነ ከሰዎች ጋር የመነጋገር ችሎታ አላቸው። (ሉቃስ 8:27-33) የሰው ልጆችን ባሕርይ በሺህ ለሚቆጠሩ ዓመታት አጥንተዋል። በሰዎች ድክመቶች እንዴት ሊጠቀሙ እንደሚችሉ ያውቃሉ። መጽሐፍ ቅዱስ በወንዶች፣ በሴቶችና በሕፃናት ላይ አድረው ወይም እነዚህን ሙሉ በሙሉ ተቆጣጥረው ያደረጓቸውን ነገሮች ይገልጻል። (ማቴዎስ 15:22፤ ማርቆስ 5:2) ሕመም ወይም እንደ ዓይነ ስውርነት ያለውን የአካል ጉዳት ሊያስከትሉ ይችላሉ። (ኢዮብ 2:6, 7፤ ማቴዎስ 9:32, 33፤ 12:22፤ 17:14-18) በተጨማሪም የሰዎችን አእምሮ ሊያሳውሩ ይችላሉ። (2 ቆሮንቶስ 4:4) አጋንንት “የሚውጠውን ፈልጎ እንደሚያገሳ አንበሳ” እንደሚዞረው እንደ መሪያቸው እንደ ሰይጣን ለአንድ አፍታ፤ እንኳን ሥራ አይፈቱም። (1 ጴጥሮስ 5:8) መጽሐፍ ቅዱስ ስለ አጋንንት መኖር ብዙ ይናገራል። በመጽሐፍ ቅዱስ የምታምን ከሆነ በዐይን የማይታዩ ክፉ ፍጥረታት መኖራቸውን ማመን ይኖርብሃል።
ክፉ አታላዮች
ታዲያ እነዚህ ኃይለኛ አጋንንት እያሉ ዓለማችን በማያባራ ብጥብጥ ያልተዋጠችው ለምንድን ነው? ሕልውናቸውና እንቅስቃሴያቸው ይበልጥ ግልጽ ሆኖ የማይታየው ለምንድን ነው? መጽሐፍ ቅዱስ “ሰይጣን ራሱ የብርሃንን መልአክ እንዲመስል ራሱን ይለውጣል” በማለት መልሱን ይሰጠናል። (2 ቆሮንቶስ 11:14) ዲያብሎስ አታላይ ነው። አጋንንታዊ እንቅስቃሴ አብዛኛውን ጊዜ ጉዳት የሌለው፣ እንዲያውም ጠቃሚ እንደሆነ ነገር ሆኖ ይቀርባል። ስለዚህ ለይቶ ለማወቅ ያስቸግራል።
ሰይጣንና አጋንንት በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመናት ያደርጉ እንደነበረው ዛሬም በተለያዩ መንገዶች ሰዎችን ማሰቃየታቸውን ቀጥለዋል። በአሁኑ ጊዜ እውነተኛ ክርስቲያኖች የሆኑ አንዳንዶች በመናፍስታዊ ሥራዎች ይካፈሉ ስለነበረ የአጋንንት ጥቃት እንዴት ያለ ሥቃይ እንደሚያስከትል ሊመሠክሩ ይችላሉ። አጋንንት ዛሬ፣ ምናልባትም ከማንኛውም ጊዜ በበለጠ መጠንና ስፋት፣ ከሰው በላይ የሆነ ኃይላቸውን በመጠቀም ሰዎችን አስተው ወደ መናፍስታዊ ድርጊቶች በመምራት ላይ ናቸው። ያላቸውን ኃይል አቅልለን መመልከት አይኖርብንም። ይሁን እንጂ የበለጠ ውጤት የሚያገኙት በማሰቃየትና በማስጨነቅ ሳይሆን በማባበልና በማሳት ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ሰይጣንና አጋንንት ‘ዓለሙን በሙሉ እንደሚያስቱ’ ይናገራል። (ራእይ 12:9) መሠሪና ስውር በሆኑ ዘዴዎች የሰዎችን መንፈሳዊነት ይሸረሽራሉ።
አጋንንት በእርግጥ አሉ። ባይኖሩ ኖሮ በአሁኑ ጊዜ ሰዎች ይህን ያህል ደም የጠማቸውና የመጨፋጨፍ አምሮት የተጠናወታቸው እንዴት ሊሆኑ ይችላሉ? የሰው ልጆች በተፈጥሮአቸው የሚፈልጉት በሰላምና በደስታ መኖር ነው። አጋንንት የሰው ልጆችን አእምሮ የመለወጥና የማበላሸት ችሎታ ስላላቸው ክፋትን ያስፋፋሉ።
ቢሆንም ይሖዋ ሁሉን የሚችል አምላክ በመሆኑ ከአጋንንት የበለጠ ኃይል አለው። “የዲያብሎስን የተንኮል” ዘዴዎች የምንቋቋምበትን ኃይልና መከላከያ ይሰጠናል። (ኤፌሶን 6:11-18 የ1980 ትርጉም) “ለእግዚአብሔር ተገዙ፤ ዲያብሎስን ግን ተቃወሙ ከእናንተም ይሸሻል” የሚል ዋስትና አምላክ ስለሚሰጠን አጋንንትን በመፍራት ስሜት ልንዋጥ አይገባንም።—ያዕቆብ 4:7
[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
Sipa Icono