በካምቦዲያ ያደረግሁት ረዥሙ የሞት ሽረት ጉዞ
ዋታና ሚየስ እንደተናገረው
ጊዜው 1974 ሲሆን በካምቦዲያ ውስጥ ከከሜር ሩዥ ጋር እየተዋጋሁ ነበር። የካምቦዲያ ጦር ሠራዊት መኮንን ነበርኩ። በአንድ ውጊያ ላይ አንድ የከሜር ሩዥ ወታደር ማረክን። ይህ ወታደር ስለ ፖል ፖ የወደፊት እቅድ የነገረኝ ነገር ሕይወቴን ከመቀየሩም በላይ ቃል በቃልም ሆነ በመንፈሳዊ ሁኔታ ረዥም ጉዞ እንድጓዝ አድርጎኛል።a
በቅድሚያ ግን ወደ ኋላ ልመልሳችሁና ውጣ ውረድ የሞላበት ሕይወቴ እንዴት እንደ ጀመረ ልንገራችሁ። የተወለድኩት በ1945 በከሜር ቋንቋ ካምፑቺያ (ካምቦዲያ) ተብላ በምትታወቀው በፕኖም ፔን ነበር። ከጊዜ በኋላ እናቴ በደህንነት ፖሊስ ውስጥ ቁልፍ የሥራ ቦታ ያዘች። የአገሪቱ መሪ ለነበሩት ለልዑል ኖረደም ሲሃኑክ ልዩ ወኪል ነበረች። አለረዳት ታሳድገኝ ስለነበረና ፕሮግራሟ የተጣበበ በመሆኑ ትምህርት እንድማር በአንድ የቡዲስት መቅደስ ልታስገባኝ አሰበች።
ቡዲስት ሆኜ ያሳለፍኩት ሕይወት
ከዋናው የቡዲስት መነኩሴ ጋር መኖር ስጀምር የስምንት ዓመት ልጅ ነበርኩ። ከዚያ ዓመት ጀምሮ እስከ 1969 ድረስ ገሚሱን ጊዜዬን በቤተ መቅደሱ ገሚሱን ደግሞ በቤት አሳልፍ ነበር። አገለግለው የነበረው መነኩሴ ቹን ናት የሚባል ሲሆን በዚያን ወቅት በካምቦዲያ ከፍተኛው የቡዲስት ባለ ሥልጣን ነበር። ለጥቂት ጊዜ ጸሐፊው በመሆን የሠራሁ ሲሆን “ሦስቱ ቅርጫቶች” (ታይፒተካ ወይም በሳንስክሪት ቋንቋ ትሪፒተካ) የተባለውን የቡዲስት ቅዱስ መጽሐፍ ከአንድ ጥንታዊ የሕንድ ቋንቋ ወደ ካምቦዲያ ቋንቋ በመተርጎም ሥራ ረድቼዋለሁ።
በ1964 መነኩሴ ሆኜ ተሾምኩና እስከ 1969 ድረስ አገለገልሁ። በዚህ ወቅት ይከነክኑኝ የነበሩ በርካታ ጥያቄዎች ነበሩኝ፤ ከእነዚህም ውስጥ በዓለም ውስጥ መከራ የበዛው ለምንድን ነው? የጀመረውስ እንዴት ነው? የሚሉት ይገኙበታል። ሰዎች በተለያዩ መንገዶች አምላኮቻቸውን ለማስደሰት ሲጣጣሩ አይቻለሁ፤ ሆኖም ችግሮቻቸውን አምላኮቻቸው እንዴት ሊያስወግዱላቸው እንደሚችሉ አያውቁም። በቡዲስት ጽሑፎች ውስጥ አጥጋቢ መልሶች ማግኘት አልቻልኩም፤ ሌሎች መነኮሳትም ሊመልሱልኝ አልቻሉም። በጣም ግራ ስለተጋባሁ ቤተ መቅደሱን ለመተው ወሰንኩ፤ ቆቤንም ጣልኩ።
በመጨረሻም በ1971 የካምቦዲያ ጦር ሠራዊት አባል ሆንኩ። በ1971 አካባቢ ወደ ቪየትናም ተላክሁ፤ በነበረኝ የትምህርት ደረጃ ምክንያት የምክትል መቶ አለቅነት ማዕረግ አገኘሁና በልዩ ጦር ውስጥ ተመደብኩ። ኮሚኒስት ከነበረው ከከሜር ሩዥ እና ከቪየትኮንግ ኃይሎች ጋር እንዋጋ ነበር።
ጦርነትና በካምቦዲያ የታዩ ለውጦች
በጦርነት ብዙ ጊዜ ማሳለፌ ስሜቴን አደንዝዞት ነበር። በየቀኑ ለማለት ይቻላል ሰዎች ሲሞቱ እመለከት ነበር። እኔ ራሴ እንኳ በ157 ውጊያዎች ተካፍያለሁ። በአንድ ወቅት የከሜር ሩዥ ኃይሎች በአንድ ጥሻ ውስጥ ለአንድ ወር ያህል ከበቡን። ከ700 የሚበልጡ ሰዎች ሞቱ። በሕይወት የተረፉ 15 ሰዎች ብቻ ነበሩ፤ ከተረፉት መካከል ብሆንም ቆስዬ ነበር። ሆኖም በሕይወት ለማምለጥ ቻልኩ።
በሌላ ጊዜ ደግሞ በ1974 አንድ የከሜር ሩዥ ወታደር ማረክን። እየመረመርኩት ሳለ ፖል ፖ በሠራዊቱ ውስጥ የሚያገለግሉትን ጨምሮ ሁሉንም የቀድሞ መንግሥት ባለ ሥልጣናት ፈጽሞ የማጥፋት እቅድ እንዳለው ነገረኝ። ሁሉንም ነገር እርግፍ አድርጌ ትቼ እንድሸሽ ነገረኝ። እንዲህ አለ:- “ስምህን ለዋውጥ። ስለ ማንነትህ ማንም ሰው ማወቅ የለበትም። ምንም እንደማታውቅና እንዳልተማርክ ለመምሰል ሞክር። ስለ ቀድሞ ሕይወትህ ለማንም አትናገር።” ወደ ቤቱ እንዲሄድ ከለቀቅሁት በኋላ የሰጠኝ ማስጠንቀቂያ በአእምሮዬ ውስጥ ተቀርጾ ቀረ።
እኛ ወታደሮች የምንዋጋው ለአገራችን እንደሆነ ይነገረን የነበረ ቢሆንም እንገድል የነበረው ግን የካምቦዲያ ተወላጆችን ነበር። ሥልጣን ለመጨበጥ ይዋጋ የነበረው የከሜር ሩዥ ኮሚኒስታዊ አንጃ አባላት የእኛው ሕዝቦች ነበሩ። እንዲያውም ዘጠኝ ሚልዮን ከሚሆኑት የካምቦዲያ ነዋሪዎች መካከል አብዛኞቹ የከሜር ዝርያ ያላቸው ናቸው፤ ሆኖም ብዙዎቹ የከሜር ሩዥ አባላት አይደሉም። ይህ ለእኔ ትርጉም የለሽ ሆኖብኝ ነበር። እንገድል የነበረው ጠመንጃ ያልያዙትንና የጦርነት ፍላጎት የሌላቸውን ንጹሐን ገበሬዎች ነበር።
ከውጊያ ስንመለስ የሚያጋጥመን ነገር ሁሉ እጅግ የሚያሳዝን ነበር። ሚስቶች ባለቤታቸው ልጆች ደግሞ አባታቸው መመለሱን ለማየት በጭንቀት ይጠባበቃሉ። ለብዙዎቹ የቤተሰብ አባላቸው መሞቱን ማርዳት ነበረብኝ። በዚህ ሁሉ ሁኔታ ሥር እያለሁ ስለ ቡዲዝም የነበረኝ እውቀት ምንም ሊያጽናናኝ አልቻለም።
በካምቦዲያ የነበሩ ሁኔታዎች እንዴት መልካቸውን እንደቀየሩ መለስ ብዬ አስባለሁ። ከ1970 በፊት አንጻራዊ የሆነ ሰላምና ደኅንነት ነበር። አብዛኞቹ ሰዎች ጠመንጃ አልነበራቸውም፤ ፈቃድ እስከሌለ ድረስ ጠመንጃ መያዝ ሕገ ወጥ ነበር። ዝርፊያም ሆነ ስርቆት እምብዛም አይፈጸምም ነበር። ይሁን እንጂ የፖል ፖ እና የእሱ ኃይሎች ዓመፅ የቀሰቀሰው የእርስ በርስ ጦርነት ከጀመረ በኋላ ሁሉም ነገር ተቀያየረ። በየቦታው ጠመንጃዎች መታየት ጀመሩ። ሌላው ቀርቶ የ12ና የ13 ዓመት ልጆች ሳይቀር እየተመለመሉ እንዴት መተኮስና መግደል እንደሚችሉ በመማር ለወታደራዊ አገልግሎት ይሠለጥኑ ጀመር። የፖል ፖ ተከታዮች አንዳንድ ልጆችን የራሳቸውን ወላጆች እንዲገድሉ አሳምነዋቸው ነበር። ወታደሮቹ ልጆቹን እንዲህ ይሏቸው ነበር:- “አገራችሁን የምትወድዱ ከሆነ ጠላቶቻችሁን መጥላት አለባችሁ። ወላጆቻችሁ ለመንግሥት የሚሠሩ ከሆነ ጠላቶቻችን ናቸው፤ ስለዚህ ልትገድሏቸው ይገባል አሊያም እናንተው ራሳችሁ መገደል አለባችሁ።”
ፖል ፖ እና የምንጠራ ዘመቻው
በ1975 ፖል ፖ በጦርነቱ ድል ተቀዳጀና ካምቦዲያ ኮሚኒስታዊ አገር ሆነች። ፖል ፖ ተማሪዎችን፣ አስተማሪዎችን፣ መንግሥታዊ ባለ ሥልጣኖችንና ማንኛውንም የተማረ ሰው መመንጠር ጀመረ። መነጽር አድርገህ ከተገኘህ የተማርክ ነህ ተብሎ ስለሚገመት ልትገደል ትችላለህ! የፖል ፖ መንግሥት ብዙ ሰዎች ከከተሞች ወደ ገጠር እንዲሄዱና ገበሬ እንዲሆኑ አስገድዷል። ሁሉም ሰው አንድ ዓይነት ልብስ መልበስ ነበረበት። ያለ በቂ ምግብ፣ ያለ መድኃኒትና ያለ ልብስ 2 ወይም 3 ሰዓታት ብቻ እየተኛን በቀን ውስጥ ለ15 ሰዓታት ያክል መሥራት ነበረብን። ነገሮች ከመባባሳቸው በፊት አገሬን ጥዬ ለመሄድ ወሰንኩ።
የከሜር ሩዥ ወታደር የሰጠኝን ምክር አስታወስኩ። ፎቶ ግራፎች፣ ሰነዶችና ሊያስጠረጥሩኝ የሚችሉ ነገሮችን በሙሉ አስወገድኩ። አንዳንድ ሰነዶቼን ጉድጓድ ቆፍሬ ቀበርኩ። ከዚያም በምዕራብ በኩል ወደ ታይላንድ ተጓዝኩ። ሁኔታው አደገኛ ነበር። ከኬላዎች መራቅና ከሰዓት እላፊ በኋላ ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ ነበረብኝ። ከሰዓት እላፊ በኋላ መንቀሳቀስ የሚችሉት ሕጋዊ ፈቃድ ያላቸው የከሜር ሩዥ ወታደሮች ብቻ ነበሩ።
ወደ አንድ አካባቢ ሄድኩና ለጊዜው በአንድ ጓደኛዬ ቤት አረፍኩ። ከዚያም ከሜር ሩዥ በዚያ ቦታ የነበሩትን ሰዎች በሙሉ ወደ ሌላ ስፍራ አዛወሯቸው። አስተማሪዎችንና ሐኪሞችን መግደል ጀመሩ። ከሦስት ጓደኞቼ ጋር ሆኜ አመለጥኩ። በጫካ ውስጥ በመደበቅ በዛፎች ላይ የምናገኘውን ማንኛውንም ዓይነት ፍሬ እንበላ ነበር። በመጨረሻ በባተምባን ክፍለ ሃገር በምትገኝ አንዲት ትንሽ መንደር ውስጥ ወደሚኖር አንድ ጓደኛዬ ዘንድ ደረስኩ። እዚያም እንዴት ማምለጥ እንዳለብኝ የመከረኝን ያንን የቀድሞ ወታደር ሳገኝ በጣም ተገረምሁ! በነፃ ለቅቄው ስለነበር ለሦስት ወራት ያህል በጉድጓድ ውስጥ ደበቀኝ። አንድ ልጅ ወደ ጉድጓዱ ምግብ እንዲወረውር ይልክ ነበር፤ ሆኖም ልጁ ወደ ጉድጓዱ ውስጥ እንዳይመለከት ይነግረው ነበር።
ከጊዜ በኋላ ያደረግሁት ሽሽት ተሳክቶልኝ ወደ ታይላንድ ድንበር ስደርስ እንደ እኔው በመሸሽ ላይ የነበሩትን እናቴን፣ አክስቴንና እህቴን አገኘኋቸው። ይህ ለእኔ በጣም አሳዛኝ ጊዜ ነበር። እናቴ ታምማ ስለነበረ ከጊዜ በኋላ በአንድ የስደተኞች መጠለያ ውስጥ እንዳለች በምግብ እጦትና በበሽታ ሞተች። ይሁን እንጂ በሕይወቴ ውስጥ አንድ የብርሃን ጮራ ፈነጠቀና በተስፋ መኖር ጀመርኩ። ከሶፊ ኡም ጋር ተገናኘሁና ተጋባን። እኔና ባለቤቴ ከአክስቴና ከእህቴ ጋር ሆነን የታይላንድን ድንበር አቋረጥን ወደ ተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች መጠለያ ገባን። በካምቦዲያ የእርስ በርስ ጦርነት ቤተሰባችን ብዙ መከራ ደርሶበታል። ወንድሜንና ባለቤቱን ጨምሮ 18 የቤተሰብ አባሎቻችንን በሞት አጥተናል።
አዲስ ሕይወት በዩናይትድ ስቴትስ
በስደተኞች መጠለያ ጣቢያ ማንነታችን ከተጣራ በኋላ ወደ ዩናይትድ ስቴትስ ለመሄድ እንድንችል የሚያስጠጋን ሰው ለማግኘት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጥረት አደረገ። በመጨረሻም ተሳካልን! በ1980 ሚነሶታ ሴይንት ፖል ደረስን። በአዲሱ አገሬ ለመሻሻል ከፈለግሁ በተቻለ ፍጥነት እንግሊዝኛ መማር እንዳለብኝ ተገነዘብሁ። ረዘም ላለ ጊዜ መማር ያስፈልገኝ የነበረ ቢሆንም ያስጠጋኝ ሰው ትምህርት ቤት ገብቼ እንድማር የፈቀደልኝ ለጥቂት ወራት ብቻ ነበር። ከዚህ ይልቅ በአንድ ሆቴል ውስጥ በጽዳት ሥራ አስቀጠረኝ። ሆኖም የእንግሊዝኛ ቋንቋ ችሎታዬ ውስን ስለነበረ አስቂኝ የሆኑ ስህተቶችን እሠራ ነበር። ባለቤቱ መሰላል እንዳመጣ ሲጠይቀኝ ቆሻሻ እወስድለት ነበር!
የሚያስፈራ ጉብኝት
በ1984 የሌሊት ተረኛ ሆኜ እሠራ ስለነበር ቀን ቀን እተኛ ነበር። የምንኖርበት ቦታ በእስያውያንና በጥቁሮች መካከል ብዙ ግጭት በሚፈጠርበት አካባቢ ነበር። ወንጀል መፈጸምና አደገኛ ዕፆችን መውሰድ የተለመዱ ነገሮች ነበሩ። አንድ ቀን ጠዋት ባለቤቴ በአራት ሰዓት ከእንቅልፌ ቀሰቀሰችኝና አንድ ጥቁር ሰው በሩ ላይ መቆሙን ነገረችኝ። ሊዘርፈን የመጣ ስለመሰላት በጣም ፈርታ ነበር። በሩ ላይ ባለው ቀዳዳ አሾልቄ ሳይ አንድ በደንብ የለበሰና ቦርሳ የያዘ ጥቁር ሰው ከአንድ ነጭ ሰው ጋር ቆሟል። ምንም ዓይነት ችግር የሚፈጠር አልመሰለኝም።
ምን እየሸጠ እንዳለ ጠየቅሁት። የመጠበቂያ ግንብ እና የንቁ! መጽሔት ቅጂዎችን አሳየኝ። ምንም ነገር አልገባኝም። ከሁለት ወራት በፊት አንድ ፕሮቴስታንት ነጋዴ አታልሎ ለአምስት መጽሐፎች 165 ዶላር አስከፍሎኝ ስለነበር መጽሔቶቹን ለመቀበል ፈቃደኛ አለመሆኔን ነገርኳቸው። ይሁን እንጂ ጥቁሩ ሰው በመጽሔቶቹ ላይ የነበሩትን ሥዕሎች አሳየኝ። ሥዕሎቹ የሚያስደስቱና ውብ ነበሩ! እንዲሁም ሰውየው የሚያነጋግረኝ በፈገግታ ነበር። ስለዚህ 1 ዶላር ከፍዬ መጽሔቶቹን ወሰድኩ።
ከሁለት ሳምንት ገደማ በኋላ ተመልሶ መጣና በካምቦዲያ ቋንቋ የተዘጋጀ መጽሐፍ ቅዱስ እንዳለኝ ጠየቀኝ። የሚለው ባይገባኝም ከአንድ የናዝራውያን ቤተ ክርስቲያን ያገኘሁት አንድ መጽሐፍ ቅዱስ ነበረኝ። ሆኖም የተለያየ ዘር ያላቸው ሁለት ሰዎች ወደ ቤቴ መምጣታቸው አስገርሞኝ ነበር። ከዚያም “እንግሊዝኛ መማር ትፈልጋለህ?” ሲል ጠየቀኝ። በእርግጥ እፈልግ ነበር፤ ሆኖም ለትምህርቱ የምከፍለው ገንዘብ እንደሌለኝ ነገርሁት። መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፍ በመጠቀም ያለ ምንም ክፍያ ሊያስተምረኝ እንደሚችል ነገረኝ። የየትኛው ሃይማኖት አባል መሆኑን ባላውቅም በልቤ እንዲህ አልኩ:- ‘ሌላው ቢቀር ምንም አልከፍልም፤ ደግሞም እንግሊዝኛ ማንበብና መጻፍ እማራለሁ።’
እንግሊዝኛና መጽሐፍ ቅዱስ መማር
የትምህርቱ ሂደት አዝጋሚ ነበር። የመጽሐፍ ቅዱስ የመጀመሪያ ክፍል የሆነውን የዘፍጥረት መጽሐፍ ያሳየኛል፤ ከዚያም እኔ በካምቦዲያ ቋንቋ “ሎ ኬ ባት” ብዬ እናገራለሁ። “መጽሐፍ ቅዱስ” ሲል “ኮምፒ” እላለሁ። እድገት እያደረግሁ ስለነበር በመንፈሳዊ የበለጠ ለመሥራት ተነሳሳሁ። ከእንግሊዝኛ ወደ ካምቦዲያ ቋንቋ የሚተረጉም መዝገበ ቃላት፣ አንድ የመጠበቂያ ግንብ መጽሔት፣ የአዲሲቱ ዓለም የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉምና የካምቦዲያ መጽሐፍ ቅዱሴን ወደ ሥራ ቦታዬ ይዞ የመሄድ ልማድ ነበረኝ። በእረፍት ጊዜዬ ጽሑፎቹን በማወዳደርና ተራ በተራ ቃላቱን በማጥናት የእንግሊዝኛ ቋንቋ ለመማር ቻልኩ። ይህ አዝጋሚ ሂደት ከሳምንታዊ ትምህርቶች ጋር ከሦስት ዓመት የሚበልጥ ጊዜ ወሰደ። ሆኖም በመጨረሻ እንግሊዝኛ ለማንበብ ቻልኩ!
በዚህ ጊዜ ባለቤቴ ወደ ቡዲስት መቅደስ መሄዷን ገና ያላቆመች ሲሆን ለቀድሞ አባቶችም ምግብ ታስቀምጥ ነበር። እርግጥ ከዚህ ይጠቀሙ የነበረው ዝንቦች ብቻ ነበሩ! በጦር ሠራዊቱ ውስጥም ሆነ ቡዲስት በነበርኩባቸው ጊዜያት የሸመትኳቸው ብዙ ሥር የሰደዱ መጥፎ ልማዶች ነበሩብኝ። መነኩሴ በነበርኩበት ጊዜ ሰዎች ሲጋራዎችን ጨምሮ የተለያዩ መሥዋዕቶችን ያመጡ ነበር። መነኩሴው ሲጋራዎቹን ካጨሰ የቀድሞ አባቶቻቸው አጨሱ ማለት ነው የሚል እምነት ነበራቸው። በመሆኑም የትንባሆ ሱሰኛ ሆኜ ነበር። በሠራዊቱ ውስጥ በነበርኩበት ጊዜም ቢሆን ብዙ እጠጣ የነበረ ሲሆን በውጊያዎች ላይ ድፍረት ለማግኘት ኦፒየም አጨስ ነበር። ስለዚህም መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ስጀምር ብዙ ለውጦች ማድረግ ነበረብኝ። ጸሎት ከፍተኛ እገዛ እንደሚያበረክት የተገነዘብኩት በዚህ ጊዜ ነበር። በጥቂት ወራት ጊዜ ውስጥ መጥፎ ልማዶቼን አሸነፍኩ። በዚህም ምክንያት የተቀረው ቤተሰብ ከፍተኛ ደስታ ተሰምቷቸው ነበር!
በ1989 በሚነሶታ የይሖዋ ምሥክር ለመሆን ተጠመቅሁ። በዚህ ጊዜ ገደማ የካምቦዲያ ቋንቋ ተናጋሪ የሆነ የምሥክሮች ቡድንና ብዙ የካምቦዲያ ማኅበረሰብ በካሊፎርኒያ ሎንግ ቢች እንደሚገኝ ሰማሁ። ከባለቤቴ ጋር ከተወያየሁ በኋላ ወደ ሎንግ ቢች ለመሄድ ወሰንን። የወሰድነው እርምጃ ብዙ ውጤቶች ያስገኘ ነበረ! በመጀመሪያ እህቴ ከዚያም አክስቴና (በአሁኑ ጊዜ 85 ዓመቷ ነው) ሚስቴ ተጠመቁ። ቀጥሎ ሦስቱ ልጆቼ ተጠመቁ። ከጊዜ በኋላ እህቴ በአሁኑ ጊዜ በጉባኤ ውስጥ ሽማግሌ ሆኖ በማገልገል ላይ የሚገኝ አንድ ምሥክር አገባች።
በዚህ በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ብዙ ችግሮችን አሳልፈናል። ከባድ የሆኑ የኢኮኖሚ ችግሮችና አንዳንድ የጤና እክሎች ያጋጠሙን ቢሆንም የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶችን የሙጥኝ በማለት በይሖዋ ላይ ያለንን ትምክህት ለመጠበቅ ችለናል። በመንፈሳዊ መስክ ያደረግሁትን ጥረት ይሖዋ ባርኮልኛል። በ1992 የጉባኤ አገልጋይ ሆኜ የተሾምኩ ሲሆን በ1995 ደግሞ በዚሁ በሎንግ ቢች ሽማግሌ ሆኛለሁ።
በቡዲዝም እምነት ውስጥ በምንኩስና ከዚያም በጦርነት በፈራረሰችው በካምቦዲያ የጦር አውድማዎች ላይ በመኮንንነት የጀመርኩት ረዥሙ ጉዞዬ በአዲሱ ቤታችንና አገራችን ውስጥ ሰላምና ደስታ በማግኘት ተደምድሟል። እንዲሁም በይሖዋ አምላክና በክርስቶስ ኢየሱስ ማመንን የሚያስተምር አዲስ እምነት አግኝተናል። አሁንም በካምቦዲያ ሰዎች እርስ በርሳቸው እየተገዳደሉ መሆናቸውን መስማቱ በጣም ያሳዝነኛል። ይህ ደግሞ እኔም ሆንኩ ቤተሰቤ ተስፋ የተሰጠበትን አዲስ ዓለም እንድንጠባበቅና እንድናውጅ የሚያደርግ ተጨማሪ ምክንያት ይሆነናል፤ ያ ጊዜ ጦርነት የሚባል ነገር የማይኖርበትና ሰዎች ሁሉ ሌሎችን እንደ ራሳቸው አድርገው የሚወዱበት ጊዜ ይሆናል!—ኢሳይያስ 2:2-4፤ ማቴዎስ 22:37-39፤ ራእይ 21:1-4
[የግርጌ ማስታወሻ]
a ፖል ፖ በወቅቱ የከሜር ሩዥ የጦር ሠራዊት ኮሚኒስታዊ መሪ የነበረ ሲሆን በጦርነቱ አሸንፎ በካምቦዲያ ስልጣን ለመያዝ በቅቷል።
[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ ሥዕል/ካርታ]
(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)
ቪየትናም
ላኦስ
ታይላንድ
ካምቦዲያ
ባተምባን
ፕኖም ፔን
የቡዲስት መነኩሴ በነበርኩባቸው ዓመታት
[ምንጭ]
Mountain High Maps® Copyright © 1997 Digital Wisdom, Inc.
[በገጽ 14 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ከቤተሰቤ ጋር በመንግሥት አዳራሹ