የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • g98 8/8 ገጽ 18-20
  • ማንን ለመምሰል ብጣጣር ይሻላል?

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ማንን ለመምሰል ብጣጣር ይሻላል?
  • ንቁ!—1998
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • ሰዎችን ለመምሰል መጣር የሚያስገኘው ጥቅምና ጉዳት
  • ጥሩ አርአያ የሚሆን ሰው ለመምሰል መጣጣር ሊረዳህ የሚችለው እንዴት ነው?
  • ወላጆችን ለመምሰል መጣጣር
  • ከሁሉ የሚበልጠው አርአያችን
  • ጥሩ አርዓያ የሚሆነኝን ሰው መምረጥ የምችለው እንዴት ነው?
    የወጣቶች ጥያቄ
  • የማንን አርዓያ ብከተል ይሻላል?
    ንቁ!—2012
  • ሃይማኖቴን መምረጥ ያለብኝ እኔ ነኝ ወይስ ወላጆቼ?
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2009
  • ወጣቶች ሆይ፤ ምን ነገር እየተከታተላችሁ ነው?
    መጠበቂያ ግንብ—1993
ለተጨማሪ መረጃ
ንቁ!—1998
g98 8/8 ገጽ 18-20

ወጣቶች የሚጠይቋቸው ጥያቄዎች . . .

ማንን ለመምሰል ብጣጣር ይሻላል?

“ቅርጫት ኳስ ሲጫወት ማንም አይደርስበትም። ጓደኞቼ ሁሉ ይወዱታል። ልክ እንደርሱ ለመሆን፣ እርሱ ያለው ሁሉ እንዲኖረኝ እፈልግ ነበር።”—ፒንግ የተባለ እስያዊ ወጣት

ብዙ ሰዎች በሌሎች ዘንድ አድናቆት ያተረፉ ሰዎችን ለመምሰል ይጣጣራሉ። ሊንዳ ኔልሰን የተባሉ ደራሲ “ወጣቶች ብጤዎቻቸውንና እነርሱ ራሳቸው ሊያገኙት የሚመኙትን ዝናና አድናቆት ያተረፉ ሰዎችን ለመምሰል ይጥራሉ” በማለት ገልጸዋል። በዚህም የተነሳ ወጣቶች በሰዎች ዘንድ እውቅና ያተረፉትን ወይም ማራኪ የሆነ ቁመና ያላቸውን የዕድሜ እኩዮቻቸውን የማድነቅ ዝንባሌ አላቸው። በተለይ ግን ብዙ ወጣቶች ለመምሰል የሚጣጣሩት የታወቁ የፊልም ተዋንያንን፣ ዘፋኞችንና ስፖርተኞችን ነው።

ዝናን ያተረፉ አብዛኞቹ ሰዎች በሌሎች ዘንድ የሚደነቁትና የሚወደሱት እንከን የለሽ ሆነው እንዲታዩ እንዲሁም ውዳሴና ብዙ ገበያ እንዲስብላቸው የታሰቡ የተጋነኑና ሐሳብ ወለድ የሆኑ ወሬዎች ስለሚነገሩላቸው እንደሆነ የተረጋገጠ ነው። ቀደም ሲል የተጠቀሰው ፒንግ “የዚህን ዝነኛ የሆነ የቅርጫት ኳስ ተጫዋች ፊልሞች በሙሉ ገዛሁ፤ እርሱ የሚለብሳቸውን ዓይነት ልብሶችና ጫማዎች መልበስ ጀመርኩ” በማለት ሳይሸሽግ ተናግሯል። አንዳንድ ወጣቶች እንደ አምላክ አድርገው የሚያመልኳቸው የቴሌቪዥን ወይም የስፖርት ሰዎች የሚለብሱትን ዓይነት ልብስ ይለብሳሉ፤ እንደ እነርሱ ያበጥራሉ፣ እንዲያውም የእነርሱን አረማመድና አነጋገር ይቀዳሉ።

ሰዎችን ለመምሰል መጣር የሚያስገኘው ጥቅምና ጉዳት

‘ይሁን እንጂ አንድን ሰው ማድነቅ ምን ጉዳት አለው?’ ብለህ ትጠይቅ ይሆናል። ይህ የሚመካው በምታደንቀው ሰው ማንነት ላይ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ “ከጠቢባን ጋር የሚሄድ ጠቢብ ይሆናል፤ የሰነፎች ባልንጀራ ግን ክፉ መከራን ይቀበላል” ይላል። (ምሳሌ 13:20) መጽሐፍ ቅዱስ የሰዎች ተከታይ እንድንሆን አያበረታታም። (ማቴዎስ 23:10) ሆኖም “በእምነትና በትዕግሥትም የተስፋውን ቃል የሚወርሱትን” እንድንመስል ይነግረናል። (ዕብራውያን 6:11) እነዚህን ቃላት የጻፈው ሐዋርያው ጳውሎስ በመጀመሪያው መቶ ዘመን ይኖሩ ለነበሩ ሰዎች ጥሩ ምሳሌ ትቶላቸዋል። በዚህም የተነሳ “እኔ ክርስቶስን እንደምመስል እኔን ምሰሉ” ለማለት ችሏል።—1 ቆሮንቶስ 11:1

ጢሞቴዎስ የተባለ አንድ ወጣት ያደረገው ይህንኑ ነበር። ከጳውሎስ ጋር በሚስዮናዊ አገልግሎት አብሮ በተጓዘባቸው ጊዜያት ከእርሱ ጋር የቀረበ ወዳጅነት መሥርቷል። (ሥራ 16:1-4) ጳውሎስ ጢሞቴዎስን ‘የምወደውና የታመነው በጌታ ልጄ የሆነ’ ብሎ እስከመጥራት ደርሷል። (1 ቆሮንቶስ 4:17) ጢሞቴዎስ ከጳውሎስ ባገኘው እርዳታ እውቅ ክርስቲያን ለመሆን ችሏል።—ፊልጵስዩስ 2:19-23

ጥሩ ምሳሌ የማይሆን ሰው ለመምሰል ብትጣጣርስ? ሪቻርድ የተባለ አንድ ወጣት እንዲህ በማለት ይገልጻል:- “የ15 ዓመት ልጅ በነበርኩበት ጊዜ የትምህርት ቤት ጓደኛዬ ከነበረው ከማርዮ ጋር የልብ ወዳጅነት መሠረትን። ወላጆቼ ክርስቲያኖች ስለነበሩ መንፈሳዊ እርዳታ ሊሰጡኝ ይጣጣሩ ነበር። ማርዮ ግን በየዳንስ ቤቱ እየሄደ በመጨፈር፣ ሞተር ሳይክል በመንዳትና እንዲህ የመሰሉ ሌሎች ነገሮች በማድረግ ዓለሙን ይቀጭ ነበር። የሚፈልገውን ነገር ባሰኘው ጊዜ ያደርግ ነበር። እኔ ግን እንዲህ ማድረግ አልችልም ነበር። በዚህም የተነሳ ልክ 16 ዓመት ሲሞላኝ ክርስቲያን መሆን እንደማልፈልግ ለቤተሰቦቼ ነገርኳቸውና እውነትን ተውኩ።”

ዝነኛ የሆኑና የታወቁ ስፖርተኞችን ለመምሰል መጣጣር ተመሳሳይ የሆነ አደጋ ላይ ይጥል ይሆን? አዎን፣ አደጋ ላይ ይጥላል። የአንድን ስፖርተኛ፣ የአንድን ተዋናይ ወይም የአንድን ዘፋኝ ችሎታ ማድነቅ ምንም ስህተት የለውም። ይሁን እንጂ ‘እነዚህ ሰዎች በግል አኗኗራቸው የሚያሳዩት ምሳሌነት ምን ዓይነት ነው?’ ብለህ ራስህን ጠይቅ። ብዙዎቹ ኮከብ ስፖርተኞች፣ ሙዚቀኞችና የኪነ ጥበብ ሰዎች የፆታ ብልግና በመፈጸም፣ አደገኛ ዕፆችን በመውሰድና አልኮል ያለ ልክ በመጠጣት የሚታወቁ አይደሉም? በተጨማሪም ብዙ ገንዘብና ዝና ያተረፉ ቢሆኑም ደስታና እርካታ የራቀው ሕይወት የሚመሩ መሆናቸው እውነት አይደለም? ነገሮችን ከዚህ አንጻር ስትመለከት እንደነዚህ ያሉ ሰዎችን ለመምሰል ከመጣጣር ምን ጥቅም የሚገኝ ይመስልሃል?

እውነት ነው፣ የዝነኛ ሰዎችን የፀጉር አበጣጠር፣ አለባበስ ወይም አነጋገር መቅዳት እንደ ትልቅ ነገር የሚቆጠር አይደለም ሊባል ይችላል። ይሁን እንጂ ይህ ‘ዓለም በራሱ መልክ ሊቀርጽህ’ የሚያደርገው የመጀመሪያ እርምጃ ሊሆን ይችላል። (ሮሜ 12:2 ፊሊፕስ) መጀመሪያ ላይ ይህ የዓለም መልክ የሚያስደስት ሊመስል ይችላል። ይሁን እንጂ ለዚህ ዓለም ተጽእኖ ሙሉ በሙሉ እጅህን ከሰጠህ ከአምላክ ጋር ሊያጋጭህ የሚችል መልክ እንድትይዝ እንደሚያደርግ የተረጋገጠ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ “የዓለም ወዳጅ ሊሆን የሚፈቅድ ሁሉ የእግዚአብሔር ጠላት ሆኖአል” በማለት በያዕቆብ 4:4 ላይ ይናገራል።

ጥሩ አርአያ የሚሆን ሰው ለመምሰል መጣጣር ሊረዳህ የሚችለው እንዴት ነው?

ይሁን እንጂ ጥሩ አርዓያ የሚሆን ሰው ለመምሰል መጣጣር በኑሮህ ላይ በጎ ተጽዕኖ ሊያሳድር ይችላል! ከክርስቲያን ባልደረቦቻችን መካከል “በቃልና በኑሮ በፍቅርም በእምነትም በንጽሕናም . . . ምሳሌ” ሊሆኑ የሚችሉ በርካታ ሰዎች ማግኘት ትችላለህ። (1 ጢሞቴዎስ 4:12) እርግጥ፣ በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥም ቢሆን ልትቀርባቸው የምትፈልጋቸውን ሰዎች በምትመርጥበት ጊዜ ጥንቃቄ ማድረግ ይኖርብሃል። (2 ጢሞቴዎስ 2:20, 21) በጉባኤ ውስጥ ከልባቸው ‘በእውነት እየሄዱ ያሉት’ እነማን እንደሆኑ ለይቶ ማወቅ ይህን ያህል አስቸጋሪ አይደለም። (2 ዮሐንስ 4) ዕብራውያን 13:7 ላይ የሚገኘው መሠረታዊ ሥርዓት “የኑሮአቸውን ፍሬ እየተመለከታችሁ በእምነታቸው ምሰሉአቸው” ይላል። የብዙዎቹ የዕድሜ እኩዮቻችሁ የኑሮ ፍሬ ገና ያልታየ ነው። ከነዚህ ይልቅ ታማኝነታቸውን ያስመሰከሩ በርካታ በዕድሜ የበሰሉ ሰዎች በጉባኤህ ውስጥ ይኖራሉ። ወደነዚህ ሰዎች ቀረብ ብለህ ብትተዋወቃቸው በጣም ጥሩ ይሆናል።

‘በዕድሜ ትላልቅ ከሆኑ ሰዎች ጋር አንዴት መቀራረብ እችላለሁ?’ ብለህ ትጠይቅ ይሆናል። መጀመሪያ ላይ አስቸጋሪ እንደሚሆንብህ የታወቀ ነው። ይሁን እንጂ ጢሞቴዎስ በዕድሜ ከሚበልጠው ከሐዋርያው ጳውሎስ ጋር መሥርቶ የነበረውን የቅርብ ወዳጅነት አስታውስ። ጳውሎስ፣ ጢሞቴዎስ የነበረውን ችሎታ ተገንዝቦ ስለነበር በእርሱ ውስጥ ያለውን “የእግዚአብሔርን ስጦታ” እንደ እሳት እንዲያቀጣጥል መክሮታል። (2 ጢሞቴዎስ 1:6) የሚረዳህና የሚያበረታታህ እንዲሁም ከአምላክ ያገኘኸውን ስጦታ እንድታዳብር የሚያነሳሳህ ሰው ማግኘት ጠቃሚ አይሆንም?

ብርያን የተባለ አንድ ወጣት የዚህን ጠቃሚነት ተገንዝቧል። ከሚሰማው የበታችነት ስሜት ጋር ይታገል በነበረበት ጊዜ በጉባኤ ውስጥ ካለ አንድ በእድሜ የገፋ ነጠላ የጉባኤ አገልጋይ ጋር ተዋወቀ። ብርያን እንዲህ ይላል:- “ለእኔም ሆነ ለሌሎች ሰዎች ያሳይ የነበረውን ፍቅራዊ አሳቢነት፣ ለአገልግሎት የነበረውን ቅንዓትና ያቀርብ የነበረውን ግሩም ንግግር ስመለከት ለእርሱ ያለኝ አድናቆት ከፍ አለ።” ብርያን ከዚህ በእድሜ ታላቁ ከሆነ ክርስቲያን ያገኘው ትኩረትና ክትትል ጠቅሞታል። እንዲህ በማለት በግልጽ ይናገራል:- “በፊት ከነበረብኝ የዓይን አፋርነትና የዝምተኝነት ባሕርይ እንድለወጥ ረድቶኛል።”

ወላጆችን ለመምሰል መጣጣር

አዶለሰንስ—ጀነሬሽን አንደር ፕሬሸር የተባለው መጽሐፍ “አካለ መጠን የደረሱ ወንዶችና ሴቶች ጥሩ ባሕርይ እንዲያዳብሩ በመርዳት ወይም በማሰናከል ረገድ የወላጆችን ያህል ከፍተኛ የሆነ ውጪያዊ ተጽእኖ የለም” ይላል። መጽሐፉ በማከል ወጣቶች ማንነታቸውን እንዲያውቁ ካልተደረገና ግልጽ የሆነ መመሪያ ካላገኙ “በባሕር ማዕበል ወዲያና ወዲህ እንደሚንቀሳቀስ መቅዘፊያ የሌለው መርከብ ይሆናሉ” በማለት ይገልጻል።

ይህ ምክር ያዕቆብ 1:6 ላይ የተመዘገበውንና ከ1,900 ዓመት በፊት ደቀ መዝሙሩ ያዕቆብ የጻፈውን ሐሳብ የሚያጠናክር ነው። “በምንም ሳይጠራጠር በእምነት ይለምን፤ የሚጠራጠር ሰው በነፋስ የተገፋና የተነቃነቀ የባሕርን ማዕበል ይመስላልና።” እንዲህ የመሰሉ አንዳንድ ወጣቶችን ሳታውቅ አትቀርም። ነገን ረስተው ዛሬን ብቻ ተደስተው መኖር ይፈልጋሉ።

በጉባኤ ውስጥ ጥሩ ምሳሌ የሚሆኑ ፈሪሃ አምላክ ያላቸው ወላጆች አሉህ? ካሉህ የእነርሱን ምሳሌ በታዛዥነት ትከተላለህ ወይስ በእያንዳንዱ ጉዳይ ላይ ትጨቃጨቃለህ? እውነት ነው፣ ወላጆችህ ፍጹማን አይደሉም። ሆኖም ብትመስላቸው ሊጠቅሙህ የሚችሉትን መልካም ባሕርዮቻቸውን ለማየት መቻል ይኖርብሃል። “ለወላጆቼ ያለኝ አድናቆት በጣም ከፍተኛ ነው” በማለት ጃሮድ የተባለ አንድ ወጣት ክርስቲያን ጽፏል። “ለአገልግሎት ያላቸው ቅንዓት የማይቀዘቅዝ መሆኑ፣ የኢኮኖሚ ችግሮችን የተቋቋሙባቸው መንገዶችና በሙሉ ጊዜ አገልግሎት እንድካፈል የሰጡኝ ማበረታቻ በእኔ ላይ ትልቅ ተጽዕኖ አሳድረውብኛል። ሁልጊዜ ለመምሰል የምጣጣረው ወላጆቼን ነው።”

ከሁሉ የሚበልጠው አርአያችን

ጋሉፕ የተባለ አንድ ጥናት የሚያካሂድ ድርጅት በዩናይትድ ስቴትስ ለሚገኙ የተወሰኑ ወጣቶች በታሪክ ውስጥ ከሁሉ የሚበልጥ ታላቅ ሰው ማን እንደሆነ ላቀረበው ጥያቄ ብዙዎቹ የሰጡት መልስ የአሜሪካ የፖለቲካ ሰዎችን ስም ነው። ኢየሱስ ክርስቶስ በማለት የመለሱት 6 በመቶ ብቻ ናቸው። ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ ኢየሱስ ክርስቶስ ‘ፍለጋውን እንድንከተል ፍጹም ምሳሌ ትቶላችኋል’ በማለት ይነግረናል። (1 ጴጥሮስ 2:21፤ ዕብራውያን 12:3) ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱ ከእርሱ እንዲማሩ ያበረታታል። (ማቴዎስ 11:28, 29) ይሁን እንጂ ከኢየሱስ መማር የምትችለው እንዴት ነው?

የኢየሱስን የሕይወት ታሪክ በጥንቃቄ አጥና። እስከ ዛሬ ከኖሩት ሁሉ የሚበልጠው ታላቅ ሰው በተባለው መጽሐፍ እየታገዝክ መላውን የወንጌል ዘገባ ለማንበብ ጥረት አድርግ።a ኢየሱስ ያስተማረበትን መንገድ፣ ለሰዎች ያሳየውን አዛኝነትና በመከራ ውስጥ ሆኖ ያሳየውን ጥንካሬ አንድ በአንድ መርምር። እንዲህ ካደረግክ ልትመስለው የሚገባህ ከኢየሱስ የተሻለ ሰው ሊኖር እንደማይችል ትገነዘባለህ።

ፍጹም የሆነውን አርአያ በይበልጥ እያወቅህ በሄድክ መጠን በዕድሜ እኩዮችህ ወይም ዝነኛ በሆኑ ሌሎች ሰዎች ተስበህ የመወሰድህ አደጋ በእጅጉ ይቀንሳል። ለአንድ የስፖርት ኮከብ ከፍተኛ አድናቆት የነበረውን ፒንግ የተባለ ወጣት ታስታውሳለህ? ፒንግ አሁንም ቢሆን አልፎ አልፎ ቅርጫት ኳስ የሚጫወት ቢሆንም ዝነኛ የሆነን ሰው ለመምሰል መጣጣር ሞኝነት እንደሆነ ተገንዝቧል።

ሪቻርድስ? ምሳሌነቱን ለመከተል የመረጠው ግለሰብ ክርስቲያናዊ እምነቱን እንዲተው አድርጎት ነበር። ይሁን እንጂ ሪቻርድ በ20ዎቹ እድሜ ላይ የሚገኝ ሳይመን ከሚባል ከአንድ የይሖዋ ምሥክር ጋር ተዋወቀ። “ከሳይመን ጋር ጓደኛሞች ሆንን” በማለት ሪቻርድ ይናገራል። “የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች ወደ ጎን ገሸሽ ሳያደርጉ መደሰት እንደሚቻል እንድገነዘብ ረዳኝ። ወዲያው ለሳይመን ያለኝ አክብሮት እያደገ መጣ። የእርሱ ምሳሌነት ወደ ጉባኤ እንድመለስና ራሴን ለይሖዋ እንድወስን ትልቅ አስተዋጽኦ አድርጎልኛል። አሁን ይበልጥ ደስተኛ ነኝ። ሕይወቴም እውነተኛ ትርጉም አግኝቷል።”

አዎን፣ ልትመስለው የመረጥከው ግለሰብ በሕይወትህ ላይ ከፍተኛ ለውጥ ያመጣል!

[የግርጌ ማስታወሻ]

a ኒው ዮርክ በሚገኘው መጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር የታተመ።

[በገጽ 19 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በሌሎች ዘንድ ጥሩ ስም ካተረፉ በእድሜ የሚበልጡህ ሰዎች ጋር መወዳጀት በጣም ሊረዳህ ይችላል

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ