ኑሮህን ለማሻሻል የሚረዱ አምስት መንገዶች
በመካከለኛው አፍሪካ ሪፑብሊክ የሚገኘው የንቁ! ዘጋቢ እንዳጠናቀረው
የዕቃዎች ዋጋ መናር፣ በሽታ፣ የተመጣጠነ ምግብ እጥረትና ድህነት በታዳጊ አገሮች ውስጥ በእጅጉ ተስፋፍተው የሚገኙ ችግሮች ናቸው። በዚህ ላይ ደግሞ ቢያንስ ቢያንስ ከሰብዓዊ አመለካከት አንጻር ሲታይ ምንም ዓይነት አፋጣኝ መፍትሔ የለም። በታዳጊ አገር ውስጥ የምትኖር ከሆነ ኑሮህን ለማሻሻል ልታደርገው የምትችለው ነገር ይኖር ይሆን? አዎን፣ አለ! ጠቃሚና ተግባራዊ ሆነው ልታገኛቸው የምትችላቸው አምስት ሐሳቦች ከዚህ ቀጥሎ ቀርበዋል።
አንደኛ:- የጓሮ አትክልት ትከል
መጽሐፍ ቅዱስ በምሳሌ 28:19 ላይ “ምድሩን የሚያርስ እንጀራ ይጠግባል” ይላል። በእርግጥም አነስተኛ በሆነ መሬት ላይ ምን ያህል ምርት ሊገኝ እንደሚችል ስታውቅ ትገረም ይሆናል። ደራሲው ሄንክ ቮየንቤርክ ለ ዣርደ ፖታዤ ሱ ሌ ትሮፒክ (በሐሩር ክልል የሚገኝ የአትክልት ሥፍራ) በተባለው መጽሐፋቸው ላይ ከ50 እስከ 100 ስኩዌር ሜትር በሚሆን መሬት ላይ ስድስት አባላት ያሉትን ቤተሰብ መመገብ የሚያስችል አትክልት ማምረት ይቻላል ብለዋል!
ራስህ ልታበቅላቸው በምትችላቸው ነገሮች ላይ ለምን ገንዘብህን ታጠፋለህ? እንደ አፈሩ ለምነትና እንደ አየር ንብረቱ ጠባይ በራስህ ጓሮ ባቄላ፣ ቃሪያ፣ ጎመን፣ ሰላጣ፣ ካሮት፣ ሽንኩርት፣ ድንች፣ ዱባ፣ ስኳር ድንች፣ ሸንኮራ፣ ቲማቲም፣ ዝኩኒና በቆሎ የመሳሰሉ ተክሎችን ማብቀል ትችል ይሆናል። እንዲህ ዓይነቱ የጓሮ አትክልት ቢያንስ ቢያንስ ቤተሰብህን በሚገባ ሊመግብ ይችላል፤ አልፎ ተርፎም ልትሸጠው የምትችል ተጨማሪ ምርት ታገኝ ይሆናል።
በቂ የሆነ መሬት ካለህ የተለያዩ ዓይነት የፍራፍሬ ዛፎችን መትከል ትችል ይሆናል። በአንዳንድ ሁኔታዎች አንድ የፍራፍሬ ዛፍ ብቻ እንኳ አንተና ቤተሰብህ ልትመገቡት ከምትችሉት የበለጠ ብዙ ፍሬ ሊያፈራ ይችላል። የከብት ፍግና የቅጠላ ቅጠሎች ብስባሽን በማዳበሪያነት መጠቀም ጥሩ ምርት እንድታገኝ ይረዳሃል። ዛፎች ለቤተሰብህ አስፈላጊውን ምርት ከመስጠትና ተጨማሪ ገቢ ከማስገኘትም በተጨማሪ የሚሰጡት ሌላ ጥቅምም አለ። በጥሩ ቦታ የተተከሉ ዛፎች ጥላ ሊሰጡ፣ አየሩን ሊያጠሩና አካባቢውን ይበልጥ ማራኪና ውብ ሊያደርጉት ይችላሉ።
ስለ አትክልተኝነት ብዙም የማታውቅ ብትሆንስ? በዚህ ረገድ ልምድ ያላቸው ጓደኞች፣ ጎረቤቶች ወይም ደግሞ ሌሎች የምታውቃቸው ሰዎች አሉህ? ካሉህ እርዳታና ምክር እንዲለግሱህ ለምን አትጠይቃቸውም? በተጨማሪም ስለ አትክልተኝነት የሚገልጹ መጻሕፍትን መግዛት ወይም መዋስ ትችል ይሆናል።—ግንቦት 22, 1974 ንቁ! መጽሔት (የእንግሊዝኛ) እትም ላይ የወጣውን “የጓሮ አትክልት ለምን አትተክልም?” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።
ሁለተኛ:- በብዛት ሸምት
እንደ ዱቄት፣ ሩዝና ዘይት ያሉትን መሠረታዊ ነገሮች የምትሸምተው በትንሽ በትንሹ ነው? እንደዚያ ከሆነ የወር ወጪህን እያባከንክ ሊሆን ይችላል። ከዚህ ይልቅ የሚቻል ከሆነ ከሌሎች ሁለት፣ ሦስት ወይም ከዚያ በላይ የሆኑ ቤተሰቦች ጋር ጥምረት በመፍጠር እንዲህ ያሉትን ነገሮች አንዴ በብዛት ለመሸመት ሞክር። በተወሰኑ ወቅቶች ብቻ በብዛት የሚኖሩ ፍራፍሬዎችን ወይም ቅጠላ ቅጠሎችን በብዛት መግዛቱም ገንዘብህን ለመቆጠብ ሊረዳህ ይችላል። አንዳንዴም በጅምላ መሸመት የምትችልበት ሁኔታ ሊኖር ይችላል።
ሦስተኛ:- የምግብ አጠባበቅ ዘዴን ተማር
በብዛት በሚሸመትበት ጊዜ ቶሎ ሊበላሹ የሚችሉ ነገሮችን ረዘም ላለ ጊዜ ሳይበላሹ ማቆየት የሚቻለው እንዴት ነው የሚል ጥያቄ ይነሳል። ምግብን ማድረቅ አንዱ በብዛት የሚሠራበትና ውጤታማ የሆነ ዘዴ ነው። በአፍሪካ የሚኖሩ ብዙ ሴቶች የሚተዳደሩት ፍራፍሬ፣ ባቄላ፣ አተር፣ ነጭ ሽንኩርት፣ የዱባ ፍሬና ለቅመምነት የሚያገለግሉ የተለያዩ ቅጠላ ቅጠሎች አድርቀው በመሸጥ ነው። እንዲህ ዓይነቶቹን ነገሮች ለማድረቅ ምንም ዓይነት ልዩ መሣሪያ አያስፈልግም። ንጹሕ መሬት ላይ ማስጣት ወይም ጣሪያ ላይ ሰቅሎ ማድረቅ ይቻላል። ዝንቦችን ለመከላከል በስስ ጨርቅ መሸፈን ሊያስፈልግ ይችላል። ከዚህ በተረፈ ንፋሱና ፀሐዩ ያደርቀዋል።—ነሐሴ 8, 1975 ንቁ! መጽሔት (የእንግሊዝኛ) እትም ላይ የወጣውን “በትንሽ ገቢ መተዳደር ትችላለህን?” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።
አራተኛ:- መጠነኛ የሆነ እርባታ ለማካሄድ ሞክር
ዶሮ፣ ፍየል፣ በግ ወይም ሌሎች እንስሳት ማርባት ትችል ይሆን? በብዙ አካባቢዎች ሥጋ የቅንጦት ምግብ ነው። ሆኖም ሌሎች ትንሽ እገዛ እንዲያደርጉልህ በመጠየቅ አነስተኛ ቁጥር ያላቸውን እንስሳት እንዴት ማርባት እንደምትችል ልትማር ትችላለህ። ዓሣ መብላት ትወዳለህ? እንግዲያው ዓሣ ማርባት የምትችልበት አንድ አነስተኛ ኩሬ እንዴት መሥራት እንደምትችል ልትማር ትችል ይሆናል። ሥጋ፣ ዕንቁላልና ዓሣ ለቤተሰብህ ጤንነት አስፈላጊ የሆኑትን እንደ ብረት፣ ካልስየም፣ ቫይታሚኖች፣ ሚኒራሎችና ፕሮቲን ያሉ ንጥረ ነገሮች የያዙ ናቸው።
አምስተኛ:- ጥሩ የንጽሕና አጠባበቅ ልማድ ይኑርህ
ንጽሕናን መጠበቅም ለቤተሰብህ ጤንነት በጣም አስፈላጊ ነው። ንጽሕና የጎደለው አካባቢ የተለያዩ በሽታዎች የሚያዛምቱትን አይጦች፣ ዝንቦችና በረሮዎች ይጋብዛል። ንጽሕናን በሚገባ መጠበቅ ጊዜና ጉልበት ይጠይቃል። ሆኖም ንጽሕናን ለመጠበቅ የሚወጣው ወጪ ለሕክምናና ለመድኃኒት ከሚወጣው ወጪ ያነሰ ነው። ሆኖም የንጽሕና አጠባበቅ ደረጃ በተወሰነ መጠን ከሰው ወደ ሰው እንዲሁም ከአገር ወደ አገር ሊለያይ ይችላል። ይሁን እንጂ በየትኛውም ቦታ ሊሠሩ የሚችሉ አጠቃላይ የሆኑ ጥቂት መሠረታዊ ሥርዓቶች አሉ።
ለምሳሌ ያህል መጸዳጃ ቤቶችን እንውሰድ። በገጠር አካባቢዎች የሚኖሩ ሰዎች የመጸዳጃ ቤቶች ሲቆሽሹና ሲፈራርሱ ዝም ብለው ስለሚመለከቷቸው ለሕመምና ለበሽታ ዋነኛ መንስኤ ይሆናሉ። የአካባቢው የጤና ሠራተኞች አነስተኛ በሆነ ወጪ ንጹሕ መጸዳጃ ቤት እንዴት መሥራት እንደምትችል አንዳንድ መመሪያዎች ሊሰጡህ ይችሉ ይሆናል።
ቤትህስ እንዴት ነው? ንጹሕና በደንብ የተያዘ ነው? ጥሩ መዓዛ አለው? ማዕድ ቤትህስ እንዴት ነው? ንጹሕና በሚገባ የተደራጀ ነው? የምታዘጋጀው ምግብ ጤናማ እንዲሆን ንጹሕና በደንብ የበሰለ መሆን አለበት። የተበከለ ውኃ በጀርሞችና በጥገኛ ተውሳኮች የተሞላ ነው። ስለዚህ ውኃውን ከመጠቀምህ በፊት ማጣራት ወይም ማፍላት ያስፈልግሃል። ምግብ ለማዘጋጀትም ሆነ ለማቅረብ የምትጠቀምባቸውን ዕቃዎች በፈላ ውኃ እጠባቸው። በተጨማሪም ምግብ ከመሥራትህም ሆነ ከመመገብህ በፊት እጅህን በደንብ ታጠብ። ውኃ የምታስቀምጥባቸው ዕቃዎች ንጹሕና መክደኛ ያላቸው መሆን አለባቸው።
ጤናህ የተጠበቀ እንዲሆን ለማድረግ ከፈለግህ ውሾች፣ ድመቶች፣ ዶሮዎችና ፍየሎች ወደ ማዕድ ቤት እንዲገቡ መፍቀድ የለብህም። በተጨማሪም አይጦች በየድስቱና በየመጥበሻው ላይ እየተሯሯጡ ምግብህን እንዲበክሉት መፍቀድ የለብህም። ችግሩን ለማስወገድ አንድ የአይጥ ወጥመድ መጠቀሙ ብቻ በቂ ሊሆን ይችላል።—ጥቅምት—ታኅሣሥ 1994 የንቁ! መጽሔት እትም ላይ የወጣውን “ንጹሕ ለመሆን ያለውን ትግል ማሸነፍ” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።
በመሠረቱ፣ የሰው ልጆችን ችግሮች ሙሉ በሙሉ የሚያስወግደው የአምላክ መንግሥት ብቻ ነው። (ማቴዎስ 6:9, 10) እስከዚያው ጊዜ ድረስ ግን እነዚህ ቀለል ያሉ ሐሳቦች ኑሮህን ለማሻሻል ሊረዱህ ይችላሉ።
[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የጓሮ አትክልት ትከል
[በገጽ 27 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በብዛት ሸምት
[በገጽ 27 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የምግብ አጠባበቅ ዘዴ ተማር
[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
መጠነኛ የሆነ እርባታ ለማካሄድ ሞክር
[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ጥሩ የንጽሕና አጠባበቅ ልማድ ይኑርህ