ድልድዮች ባይኖሩ ኖሮ እንዴት እንሆን ነበር?
“አዝሎ ያሻገረህን ድልድይ አመስግን።”—ጆርጅ ኮልማን፣ የ19ኛው መቶ ዘመን እንግሊዛዊ ጸሐፌ ተውኔት
ድልድይ ከተሻገርክ ምን ያህል ጊዜ ሆኖሃል? ድልድይ መኖሩን እንኳን ልብ ብለህ ነበር? በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች በየዕለቱ ድልድዮችን ይሻገራሉ። ይሁን እንጂ ድልድይ መኖሩን እንኳን ልብ አንልም። በድልድይ ላይ ወይም በድልድይ ሥር በእግር እየሄድን፣ እየጋለብን ወይም እየነዳን እናልፋለን፤ ሆኖም ድልድይ ስለመኖሩ እንኳ አናስብም። ይሁን እንጂ ድልድይ የሚባል ባይኖር ኖሮስ?
የተለያየ አሠራር ላላቸው ድልድዮች ምስጋና ይድረሳቸውና ሰዎችም ሆኑ እንስሳት ድልድዮች ባይኖሩ ኖሮ ለመሻገር ከባድ የሆኑ ገደሎችንና ወንዞችን በድልድዮች አማካኝነት በቀላሉ መሻገር ከጀመሩ በሺህ የሚቆጠሩ ዓመታት አልፈዋል። እንደ ካይሮ፣ ለንደን፣ ሞስኮ፣ ኒው ዮርክና ሲድኒ የመሰሉ ሌሎች ትላልቅ ከተሞች ድልድይ ባይኖራቸው ኖሮ ምን ይመስሉ እንደነበረ ለመገመት እንኳን ያስቸግራል። አዎን፣ ድልድዮች የረዥም ዘመን ታሪክ አላቸው።
የጥንት ዘመን ድልድዮች
ከ2,500 ዓመታት በፊት የባቢሎኗ ንግሥት ኒቶክሪስ በኤፍራጥስ ወንዝ ላይ ድልድይ አሠራች። ለምን? ሄሮዶቱስ የተባለው ግሪካዊ ታሪክ ጸሐፊ መልሱን ይነግረናል። “[ባቢሎን] በወንዙ ምክንያት ለሁለት ተከፍላ ነበር። ቀደም ባሉት ነገሥታት ዘመን አንድ ሰው ከአንዱ ወደ ሌላው ማለፍ ይችል የነበረው በጀልባ ብቻ ነበር። ይህ ደግሞ እንደሚመስለኝ በጣም አስቸጋሪ መሆን አለበት።” ኒቶክሪስ ለግንባታ ሥራ የሚያገለግሉ የእንጨት ምሰሶችን፣ የተቃጠሉ ሸክላዎችንና ጥርብ ድንጋዮችን እንዲሁም ለማጣበቂያነት ብረትና እርሳስ ተጠቅማ ዝነኛ ከሆኑት የጥንት ወንዞች አንዱ በሆነው በኤፍራጥስ ወንዝ ላይ ድልድይ ዘረጋች።
ድልድዮች የታሪክ ሂደት እንዲቀየር ያደረጉበት ጊዜም አለ። የፋርሱ ንጉሥ ታላቁ ዳርዮስ በሲታውያን ላይ ጦሩን ለማዝመት ሲል ከእስያ ወደ አውሮፓ በአጭር ጊዜ ውስጥ ሊያደርሰው የሚያስችለውን መንገድ ለማግኘት ፈለገ። ይህ ደግሞ 600,000 የሚያክለውን ሠራዊት በቦስፖረስ የባሕር ወሽመጥ ማሻገርን የሚጠይቅበት ሆነ። ከባድ ጭጋግና ኃይለኛ ማዕበል የሚበዛበት ስለነበረ የባሕሩን ወሽመጥ በጀልባ መሻገር በጣም አደገኛ ነበር። በዚህም ምክንያት ዳርዮስ ጀልባዎችን በማቀጣጠል 900 ሜትር ርዝመት ያለው ተንሳፋፊ ድልድይ ሠራ። ዛሬ ይህን ወሽመጥ ለማቋረጥ የዳርዮስን ያህል ብዙ ችግር ውስጥ መግባት አያስፈልግህም። በቱርክ፣ በኢስታንቡል ከተማ በሚገኘው የቦስፖረስ ድልድይ ከተጠቀምክ ከሁለት ደቂቃ ባነሰ ጊዜ ውስጥ በመኪና መሻገር ትችላለህ።
የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪ ከሆንክ የድልድይ አለመኖር የታሪክን አቅጣጫ ያስቀየሰበትን አንድ ወቅት ታስታውስ ይሆናል። የባቢሎኑ ንጉሥ ናቡከደነፆር የደሴት ከተማ የነበረችውን ጢሮስን በከበበ ጊዜ የሆነውን ነገር አስታውስ። ከተማይቱን ለመያዝ ለ13 ዓመታት ሙከራ ያደረገ ቢሆንም ሳይሳካለት ቀርቷል። ይህ የሆነበት ከፊሉ ምክንያት ደሴቲቱን ከዋነኛው አሕጉር ጋር የሚያገናኝ ድልድይ ባለመኖሩ ነበር። (ሕዝቅኤል 29:17–20) ታላቁ እስክንድር አፈር ደልድሎ ደሴቲቱን ከዋነኛው አሕጉር ጋር የሚያገናኝ ጎዳና እስኪሠራ ድረስ ለ300 ዓመታት ያህል ሳትደፈር ቆይታለች።
በመጀመሪያው መቶ ዘመን ‘መንገዶች ሁሉ ወደ ሮም ያደርሳሉ’ የተባለ ቢሆንም ሮማውያን ሰፊ ግዛታቸውን ለማገናኘትና ለማስተሳሰር ድልድዮችና ጎዳናዎች አስፈልገዋቸው ነበር። ሮማውያን መሐንዲሶች እያንዳንዳቸው እስከ ሰማንያ ኩንታል የሚመዝኑ ድንጋዮች በመጠቀም ቅስት ድልድዮችን ሠርተዋል። እነዚህ ድልድዮች በከፍተኛ ጥበብ የተሠሩ በመሆናቸው አንዳንዶቹ ከሁለት ሺህ ዓመታት በኋላ እንኳን ምንም ሳይሆኑ እስከ ዛሬ ድረስ ቆመዋል። የውኃ መተላለፊያ ቦዮችና ቱቦዎችም በድልድይነት ያገለግሉ ነበር።
በመካከለኛው ዘመን ድልድዮች አንዳንድ ጊዜ እንደ ምሽግ ሆነው አገልግለዋል። በ944 እዘአ ሳክሰኖች የዴኖችን ጥቃት ለመመከት በለንደን በሚገኘው የቴምስ ወንዝ ላይ የእንጨት ድልድይ ሠርተው ነበር። ከሦስት መቶ ዓመታት በኋላ ማለት ይቻላል በዚህ የእንጨት ድልድይ ምትክ ብዙ የተተረከለትና የተዜመለት አሮጌው የለንደን ድልድይ ተሠራ።
ቀዳማዊት ንግሥት ኤልሳቤጥ በእንግሊዝ ዙፋን ላይ በተቀመጠችበት ዘመን አሮጌው የለንደን ድልድይ ተራ የድንጋይ ምሽግ መሆኑ አብቅቶ ነበር። በድልድዩ ላይ ሕንጻዎች ተሠርተው ነበር። ምድር ቤቱ ለሱቆች ሆነ። ፎቆቹስ? ለከበርቴ ነጋዴዎችና ለንጉሣዊ ቤተሰብ አባሎች በመኖሪያነት ያገለግሉ ነበር። የለንደን ድልድይ የለንደን ማኅበራዊ ሕይወት ማዕከል ሆኖ ነበር። ከሱቆቹና ከመኖሪያ ቤቶቹ ኪራይ የሚገኘው ገንዘብ ለድልድዩ ጥገናና እንክብካቤ ይውል ነበር። አዎን፣ የለንደን ድልድይ ገንዘብ የሚከፈልበት ድልድይ ነበር።
አውሮፓውያን ከእንጨትና ከድንጋይ ድልድይ ይሠሩ በነበረበት ወቅት የደቡብ አሜሪካዎቹ ኢንካዎች ድልድያቸውን የሚሠሩት ከገመድ ነበር። ከእነዚህ ድልድዮች በፔሩ አገር በአፑሪማክ ወንዝ ላይ የተዘረጋው ሳን ሉዊስ ራ የተባለው ድልድይ እንደ ምሳሌ ሆኖ የሚጠቀስ ነው። ኢንካዎች የተክሎችን ቃጫ ሰብስበው የሰው አካል የሚያክል ውፍረት ያለው ገመድ ገመዱ። ገመዶቹን በአንደኛው የወንዙ ዳር ባሉት የድንጋይ አምዶች ላይ አስረው ወደ ሌላኛው የወንዙ ዳር ይዘረጉታል። ገመዶቹን በሁለቱም የወንዙ ዳርቻዎች አጥብቀው ካሠሩ በኋላ ለመተላለፊያነት የሚያገለግሉ የእንጨት ጣውላዎችን በገመዶቹ ላይ ይረበርባሉ። ለእድሳት ሥራ የተመደቡ ሠራተኞች በየሁለት ዓመቱ ገመዶቹን ይቀይራሉ። ይህ ድልድዩ በጥሩ ሁኔታ የተሠራና ተገቢ እንክብካቤ የሚደረግለት በመሆኑ ለአምስት መቶ ዓመታት ሊቆይ ችሏል!
ድልድዮችና እየተለዋወጠ የመጣው ፍላጎታችን
ድልድዮች የምድር ነውጦችን፣ ኃይለኛ ነፋሶችንና የሙቀት መለዋወጥን መቋቋም መቻል አለባቸው። ከላይ እንደተመለከትነው እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ መሐንዲሶች ድልድይ ለመገንባት ይገለገሉባቸው የነበሩት የሕንፃ መሣሪያዎች እንጨት፣ ጡብ ወይም ድንጋይ ነበር። አውቶሞቢል አገልግሎት ላይ ከዋለበት ከ19ኛው መቶ ዘመን መጨረሻ ወዲህ ግን በወቅቱ የነበሩት ድልድዮች ከባድ ተሽከርካሪዎችን ጭምር መሸከም እንዲችሉ መሻሻልና መስፋት አስፈለጋቸው።
የእንፋሎት ባቡር መፈልሰፍም በድልድይ አሠራርና ንድፍ ላይ ከፍተኛ ግፊት አሳድሯል። በጣም አመቺ የሆኑት የባቡር ሐዲዶች ሰፊ የወንዝ መውረጃዎችን ወይም ጥልቅ ገደሎችን አቋርጠው የሚያልፉት ናቸው። በእነዚህ ገደሎች መካከል ያለውን ክፍተት የሚዘጋና በየጊዜው ቁጥራቸው እየጨመረ የሄዱትን ፉርጎዎች ለመሸከም የሚችል ድልድይ ለመሥራት ይቻል ይሆን? ከጊዛ ብረት የተሠሩ ድልድዮች ለጊዜው ብቁ አገልግሎት ሊሰጡ ችለዋል። በ19ኛው መቶ ዘመን ከተሠሩት በጣም ዝነኛ ድልድዮች አንዱ በሰሜናዊ ዌልስ በሜናይ የባሕር ወሽመጥ ላይ በስኮትላንዳዊው መሐንዲስ ተነድፎ በ1826 የተጠናቀቀው ተንጠልጣይ ድልድይ ነው። የ176 ሜትር ርዝመት ሲኖረው እስከ አሁን ድረስ አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛል! ይሁን እንጂ ጊዛ ብረት በቀላሉ የመሰበር ጠባይ ስላለው የድልድዮች መፍረስ የተለመደ እየሆነ መጣ። በመጨረሻ በ1800ዎቹ ዓመታት መገባደጃ ላይ የአረብ ብረት መሠራት ተጀመረ። ይህ የብረት ዓይነት ይበልጥ ረዥምና አስተማማኝ ድልድይ ለመሥራት የሚያስችል ባሕርይ አለው።
የድልድይ አወቃቀር ዓይነቶች
ሰባት ዋና ዋና የድልድይ አሠራር ዓይነቶች አሉ። (ከላይ ያለውን ሣጥን ተመልከት።) እዚህ ላይ ሁለቱን ዓይነቶች በአጭሩ እንመለከታለን።
ወጋግራ ድልድዮች ከወንዙ ዳርና ዳር በጣም ትላልቅ ግንቦች አሏቸው። በእያንዳንዱ ግንብ ላይ በመዋኛ ገንዳ ላይ እንደሚሠራው የመጥለቂያ ጣውላ ያሉ ወጋግራዎች ይሠራሉ። የድልድዩ ሥራ ሲጠናቀቅ ሁለቱ ወጋግራዎች በወንዙ መካከል ላይ በተተከለ ጠንካራ ምሰሶ ይያያዛሉ።
በኃይል የሚፈስ ወንዝ ባለበት ወይም ከወንዙ በታች ያለው መሬት በጣም ልል በሚሆንበት ጊዜ የወጋግራ ድልድይ አሠራር በጣም ተመራጭነት አለው። ምክንያቱም በወንዙ ውስጥ ምሰሶዎች መትከል አስፈላጊ አይሆንም። ወጋግራ ድልድዮች በጣም ጠንካራ በመሆናቸው እንደ ባቡር ላሉ ከፍተኛ ክብደት ላላቸው ተሽከርካሪዎች በጣም አመቺ ናቸው።
አንድ የአክሮባት ተጫዋች በተወጠረ ገመድ ላይ ሲሄድ አይተህ ታውቅ ይሆናል። በእርግጥ በተንጠልጣይ ድልድይ ላይ እየተራመደ እንዳለ ተገንዝበሃል? በዛሬው ጊዜ አገልግሎት በመስጠት ላይ ከሚገኙት ተንጠልጣይ ድልድዮች መካከል አንዳንዶቹ ከተወጠረ ገመድ እምብዛም የተራቀቁ አይደሉም። አንድ ገመድ ከዳርና ዳር ይወጠርና አንድ ቅርጫት ይንጠለጠልበታል። የሚሻገረው ሰው ቅርጫቱ ውስጥ ይቀመጥና ራሱን ቀስ በቀስ እየገፋ ወደሌላው ዳርቻ ይደርሳል። በሁሉም የዓለም ክፍል የሚኖሩ ሰዎች ቀላል በሆኑ የገመድ ድልድዮች ይጠቀማሉ።
እርግጥ ነው ከገመድ በተሠራ ድልድይ ላይ በመኪና ለመሻገር እንደማታስብ የታወቀ ነው። የብረት ሰንሰለቶችና የአረብ ብረት ካቦዎች ጥቅም ላይ መዋል ከጀመሩ በኋላ ከባድ ጭነት ሊሸከሙ የሚችሉ ተንጠልጣይ ድልድዮች መሥራት ተችሏል። ዘመናዊ ተንጠልጣይ ድልድዮች እስከ 1,200 ሜትር የሚደርስ ርዝመት አላቸው። አንድ ተንጠልጣይ ድልድይ ብዙውን ጊዜ ሁለት ከአረብ ብረት የተሠሩ ምሰሶዎች ይኖሩታል። በእያንዳንዱ ምሰሶ ላይ አምድ ይሠራል። በሺህ ከሚቆጠሩ የብረት ክሮች የተገመዱ የአረብ ብረት ካቦዎቹ በአምዶቹና ከአምዶቹ ግርጌ ባለው ጎዳና ላይ ይቸነከራሉ። የተሽከርካሪዎቹን ክብደትና የጎዳናውን ሸክም በዋነኛነት የሚሸከሙት ካቦዎቹ ናቸው። ተንጠልጣይ ድልድይ በትክክል ከተሠራ በዓለም ከሚገኙት ድልድዮች ሁሉ በጣም አስተማማኝ ነው።
ከዚህ ቀደም ስለ ድልድዮች እምብዛም አስበህ አታውቅ ይሆናል። ከአሁን በኋላ ግን አንድ ድልድይ ስትሻገር ‘ስለዚህ ድልድይ ምን አውቃለሁ? የተሠራው መቼ ነው?’ ብለህ ራስህን ጠይቅ። ቀረብ ብለህ ተመልከተው። ወጋግራ ድልድይ ነው ወይስ ተንጠልጣይ ወይም ሌላ ዓይነት ድልድይ? ይህ ዓይነቱ የድልድይ አሠራር የተመረጠው ለምንድን ነው?
ከዚያም በመሻገር ላይ እንዳለህ ‘ይህ ድልድይ ባይኖር ኖሮ እንዴት እሆን ነበር?’ ብለህ ራስህን ጠይቅ።
[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]
የድልድይ አሠራር
1. የወለል ድልድይ ብዙውን ጊዜ የሚያገለግለው ለአውራ ጎዳናዎች ነው። ወለሉ በአምዶችና በግፊት አዘል ግንቦች ላይ ያርፋል። እንደዚህ ዓይነቱ ድልድይ እስከ 300 ሜትር የሚደርስ ርዝመት ሊኖረው ይችላል።
2. ውቅር ድልድይ በባለ ሦስት ማዕዘን ውቅሮች ላይ ተደግፎ የሚቆም የድልድይ ዓይነት ነው። እንደነዚህ ዓይነቶቹ ድልድዮች ብዙውን ጊዜ የሚያገለግሉት ለባቡር ሐዲዶች ሲሆን ገደሎችን፣ ወንዞችንና ሌሎች እንቅፋቶችን ለመሻገር ያገለግላል።
3. በቅስት ድልድዮች እያንዳንዱ የድልድይ ክፍልፋይ በቅስት ላይ ይቆማል። ይህ እጅግ ጥንታዊ ከሆኑት የድልድይ ዓይነቶች አንዱ ነው። ሮማውያን የውኃ መተላለፊያ ቦዮችንና ዋሻዎችን ይሠሩ የነበረው በዚህ ዓይነቱ ቅስት ሲሆን ቅስቱን ለማጠናከር በድንጋይ ግንብ ይደመድሙ ነበር። እስከዛሬ ድረስ ያልፈረሱ የቅስት ድልድዮች አሉ።
4. በካቦ የተወጠረ ድልድይ ከተንጠልጣይ ድልድይ ጋር ተመሳሳይ ሲሆን የሚለየው ካቦዎቹ በቀጥታ ከአምዶቹ ጋር የተገናኙ በመሆናቸው ብቻ ነው።
5. ተንቀሳቃሽ ድልድይ ወደ ላይ ተነስቶ ወይም ተከፍቶ መርከቦችን ሊያሳልፍ የሚችል የድልድይ ዓይነት ነው። ለዚህ ጥሩ ምሳሌ የሚሆነን የለንደኑ ታወር ድልድይ ነው።
6. ወጋግራ ድልድይ በዋናው ጽሑፍ ውስጥ ተብራርቷል።
7. ተንጠልጣይ ድልድይ በዋናው ጽሑፍ ውስጥ ተብራርቷል።—ወርልድ ቡክ ኢንሳይክለፒድያ፣ 1994
[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሰንጠረዥ]
አንዳንድ ዝነኛ ድልድዮች
ተንጠልጣይ
ስቶርቤልት ዴንማርክ 1,624 ሜትር
ብሩክሊን ዩ ኤስ ኤ 486 ሜትር
ጎልደን ጌት ዩ ኤስ ኤ 1,280 ሜትር
ጂያይን ያንግይን ቻይና 1,385 ሜትር
ወጋግራ
ፎርት (ሁለት ድልድዮች) ስኮትላንድ እያንዳንዳቸው 521 ሜትር
ኩቤክ ካናዳ 549 ሜትር
ሚሲሲፒ ወንዝ ዩ ኤስ ኤ 480 ሜትር
የአረብ ብረት ቅስት
ሲድኒ ሃርበር አውስትራሊያ 500 ሜትር
ብሪችንፍ ዚምባብዌ 329 ሜትር
በካቦ የተወጠረ
ፖን ደ ኖርማንዲ ፈረንሳይ 856 ሜትር
ስካርንስን ኖርዌይ 530 ሜትር
[በገጽ 14 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በስፔይን፣ አልሜራ በጥንታዊ ቅስት ድልድይ ላይ የተሠራ ዘመናዊ የወለል ድልድይ
[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ብሩክሊን ብሪጅ፣ ኒው ዮርክ፣ ዩ ኤስ ኤ (ተንጠልጣይ)
[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ታወር ብሪጅ፣ ለንደን፣ እንግሊዝ (ተንቀሳቃሽ)
[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ሲድኒ ሃርበር ብሪጅ፣ አውስትራሊያ (ቅስት)
[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ሴቶ ኦሃሺ፣ ጃፓን (በካቦ የተወጠረ)