የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • g98 12/8 ገጽ 10-13
  • ውጥረትን መቋቋም ይቻላል!

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ውጥረትን መቋቋም ይቻላል!
  • ንቁ!—1998
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • ለራስህ ተገቢውን እንክብካቤ አድርግ
  • ከሌሎች ጋር ያለህ ግንኙነት ጤናማ ይሁን
  • ኑሮህ ሚዛኑን የጠበቀ ይሁን
  • ውጥረትን በተመለከተ ምክንያታዊ የሆነ አመለካከት ይኑርህ
  • መንፈሳዊነትን ማዳበር
  • አስተማማኝ ተስፋ
  • ውጥረትን መቆጣጠር የምንችልበት መንገድ
    ንቁ!—2010
  • ጥሩና መጥፎ ውጥረት
    ንቁ!—1998
  • በትምህርት ቤት የሚያጋጥመኝን ውጥረት እንዴት ልቋቋመው?
    ወጣቶች የሚጠይቋቸው ጥያቄዎችና ተግባራዊ መሆን የሚችሉ መልሶች፣ ጥራዝ 1
  • ውጥረት—መንስኤዎቹና የሚያስከትላቸው ችግሮች
    ንቁ!—2005
ለተጨማሪ መረጃ
ንቁ!—1998
g98 12/8 ገጽ 10-13

ውጥረትን መቋቋም ይቻላል!

“ምንም ጊዜ ቢሆን ውጥረት ይኖራል። ስለዚህ ሊያሳስበን የሚገባው የውጥረቱን ምክንያት ማስወገድ መቻላችን ሳይሆን ለውጥረቱ የምንሰጠው ምላሽ መሆን ይኖርበታል።”—ሊዮን ቻይቶፍ፣ እውቅ የጤና ጉዳዮች ጸሐፊ

መጽሐፍ ቅዱስ “በመጨረሻው ቀን የሚያስጨንቅ ዘመን” ይመጣል ሲል ተንብዮአል። ዛሬ የምንኖረው በዚህ ዘመን መሆኑን የሚያረጋግጡ በርካታ ማስረጃዎች አሉ። ሰዎች ልክ ትንቢቱ እንደሚለው “ትምክህተኞች፣ ትዕቢተኞች፣ ተሳዳቢዎች፣ ለወላጆቻቸው የማይታዘዙ፣ የማያመሰግኑ፣ ቅድስና የሌላቸው፣ ፍቅር የሌላቸው፣ ዕርቅን የማይሰሙ፣ ሐሜተኞች፣ ራሳቸውን የማይገዙ፣ ጨካኞች፣ መልካም የሆነውን የማይወዱ፣ ከዳተኞች፣ ችኩሎች፣ በትዕቢት የተነፉ” ሆነዋል።—2 ጢሞቴዎስ 3:1-5

በዚህ ዘመን መጠነኛ የሆነ የመንፈስ እርጋታ እንኳን ማግኘት አስቸጋሪ መሆኑ ሊያስደንቅ አይገባም። ሰላማዊ ኑሮ ለመኖር የሚጥሩ እንኳን በችግሩ መነካታቸው አልቀረም። መዝሙራዊው ዳዊት እንደጻፈው “የጻድቃን መከራቸው ብዙ ነው።” (መዝሙር 34:19፤ ከ2 ጢሞቴዎስ 3:12 ጋር አወዳድር።) ቢሆንም በአስጨናቂ ሁኔታዎች ሙሉ በሙሉ ተሸንፈህ እንዳትወድቅ ልታደርግ የምትችላቸው ብዙ ነገሮች አሉ። የሚከተሉትን ምክሮች ተመልከት።

ለራስህ ተገቢውን እንክብካቤ አድርግ

በአመጋገብ ረገድ ጥንቃቄ አድርግ። ጤናማ አመጋገብ ፕሮቲኖችን፣ ፍራ ፍሬዎችን፣ አትክልቶችን፣ ጥራጥሬዎችንና ሌሎች የእህል ዘሮችን እንዲሁም የወተት ተዋጽኦዎችን ያካትታል። በፋብሪካ ተጣርቶ ከወጣ ነጭ ዱቄትና ከእንስሳት ከሚገኝ ቅባት ተጠንቀቅ። የጨው፣ ከፋብሪካ ተጣርቶ የወጣ ስኳር፣ የአልኮልና የካፌይን ፍጆታህን ተቆጣጠር። አመጋገብህን ብታሻሽል ውጥረት የመቋቋም አቅምህ ሊሻሻል ይችላል።

የሰውነት ማጠንከሪያ። መጽሐፍ ቅዱስ “የአካል እንቅስቃሴ . . . ይጠቅማል” በማለት ይመክራል። (1 ጢሞቴዎስ 4:8 NW) በእርግጥም ልከኛና ቋሚ የሆነ የአካል እንቅስቃሴ (አንዳንዶች በሳምንት ሦስት ቀን እንደሚበቃ ይናገራሉ) ልብ ያጠነክራል፣ የደም ዝውውር ያሻሽላል፣ የኮሌስትሮል መጠን ይቀንሳል፣ በልብ ሕመም የመያዝን አጋጣሚ ይቀንሳል። ከዚህም በላይ የአካል እንቅስቃሴ የጤነኛነት ስሜት እንዲሰማ ያደርጋል። ይህ የሚሆነው በከባድ እንቅስቃሴ ጊዜ ሰውነት ኢንዶርፊን የተባለውን ንጥረ ነገር ስለሚያመነጭ ሊሆን ይችላል።

በቂ እንቅልፍ ማግኘት። እንቅልፍ ማጣት ሰውነት ስለሚያደክም ውጥረት የመቋቋም ችሎታህ ይቀንሳል። እንቅልፍ አልወስድ እያለህ የምትቸገር ከሆነ በአንድ የተወሰነ ሰዓት በመተኛትና በመነሳት ሰውነትህን አስለምድ። አንዳንዶች ቀን መተኛት የማታውን እንቅልፍ ስለሚያዛባ ቀን ከ30 ደቂቃ በላይ መተኛት ጥሩ እንዳልሆነ ይናገራሉ።

የተደራጀህ ሁን። ጊዜያቸውን በጥሩ ሁኔታ የሚጠቀሙ ሰዎች የሚያጋጥማቸውን ውጥረት በተሻለ ሁኔታ የመቋቋም ችሎታ አላቸው። የተደራጀህ መሆን እንድትችል በመጀመሪያ የትኞቹ ኃላፊነቶች ቅድሚያ ሊሰጣቸው እንደሚገባ ወስን። ከዚያም ሁሉንም በአግባቡ ማከናወን እንድትችል ፕሮግራም አውጣ።—ከ1 ቆሮንቶስ 14:33, 40 እና ከፊልጵስዩስ 1:10 ጋር አወዳድር።

ከሌሎች ጋር ያለህ ግንኙነት ጤናማ ይሁን

የሌሎችን እርዳታ ጠይቅ። አስጨናቂ በሆኑ ወቅቶች ጥሩ ወዳጆችና ጓደኞች ያሏቸው ሰዎች ቢያንስ ባጋጠማቸው ውጥረት ተደናግጠው ተስፋ ከመቁረጥ ይድናሉ። የልብን ገልጠው የሚያዋዩት አንድ የታመነ ወዳጅ ማግኘት እንኳን በጣም ሊጠቅም ይችላል። አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌ “እውነተኛ ባልንጀራ ሁልጊዜ ይወድዳል፣ በመከራ ጊዜም እንደ ወንድም ይሆናል” ይላል።—ምሳሌ 17:17 NW

አለመግባባቶችን አስወግድ። ሐዋርያው ጳውሎስ “በቊጣችሁ ላይ ፀሐይ አይግባ” ሲል ጽፏል። (ኤፌሶን 4:27) ቁጣና ቂም አምቆ ከመያዝ ይልቅ ቶሎ ብሎ መተራረቅ ጠቃሚ መሆኑ 929 በሚያክሉ የልብ ድካም ይዟቸው በሕይወት የተረፉ ሰዎች ላይ በተደረገ አንድ ጥናት ተረጋግጧል። በውስጣቸው ከፍተኛ ጥላቻ ያለባቸው ሰዎች ከመጀመሪያው የልብ ድካም ሕመም በኋላ ባሉት አሥር ዓመታት ውስጥ ልባቸው ቀጥ ብሎ የመሞታቸው ዕድል ይበልጥ የዋሃን ከሆኑ ተመሳሳይ ሰዎች ሦስት ጊዜ እጥፍ ይበልጣል። የዚህ ጥናታዊ ጽሑፍ ደራሲዎች እንዳመለከቱት ከሁሉም ይበልጥ ለዚህ አስተዋጽኦ የሚያደርገው ነገር የቁጣ ስሜት ቢሆንም ሰውነት በውጥረት ሆርሞኖች እንዲጥለቀለቅ የሚያደርግ ማንኛውም አሉታዊ ስሜት ተመሳሳይ ውጤት ሊያስከትል ይችላል። ምሳሌ 14:30 “ቅንዓት . . . አጥንትን ያነቅዛል” ይላል።

ከቤተሰብህ ጋር የምታሳልፈው በቂ ጊዜ ይኑርህ። እስራኤላውያን ወላጆች ለልጆቻቸው በቂ ጊዜ እንዲመድቡና በልባቸው ውስጥ ትክክለኛ የሆኑ መሠረታዊ ሥርዓቶችን እንዲቀርጹ ታዝዘዋል። (ዘዳግም 6:6, 7) በዚህ መንገድ የሚፈጠረው መቀራረብ በአሁኑ ጊዜ እየጠፋ የሄደውን የቤተሰብ አንድነት ያጠናክራል። አንድ ጥናት እንዳመለከተው መሥሪያ ቤት የሚውሉ አንዳንድ ባልና ሚስት በቀን ውስጥ ከልጆቻቸው ጋር በመጫወት የሚያሳልፉት ጊዜ በአማካይ ከ3.5 ደቂቃ አይበልጥም። ይሁን እንጂ ቤተሰብ ውጥረት በሚያጋጥምበት ጊዜ በጣም ጠቃሚ ምርኩዝ ሊሆን ይችላል። ስለ ውጥረት የተጻፈ አንድ መጽሐፍ “በቤተሰብ ውስጥ ማንነትህን በትክክል የሚያውቅና አንተነትህን የሚወድ የአንድ ድጋፍ ሰጪ ቡድን አባል የመሆን ቅድመ ሁኔታ የማይጠይቅ መብት አለህ” ይላል። “በቤተሰብ እንደ አንድ ቡድን ሆኖ መሥራት በጣም ጥሩ ከሆኑ የውጥረት መቀነሻ ዘዴዎች አንዱ ነው።”

ኑሮህ ሚዛኑን የጠበቀ ይሁን

ምክንያታዊ ሁን። ሁልጊዜ አካላዊና ስሜታዊ አቅሙን አሟጥጦ የሚሠራና ከመጠን በላይ ራሱን የሚያደክም ሰው በአእምሮም ሆነ በአካል መዛሉ ወይም ከባድ በሆነ የጭንቀት ስሜት መዋጡ አይቀርም። ሚዛን መጠበቅ በጣም ወሳኝ ነው። ደቀ መዝሙሩ ያዕቆብ እንደጻፈው “ላይኛይቱ ጥበብ . . . ምክንያታዊ ናት።” (ያዕቆብ 3:17 NW፤ ከመክብብ 7:16, 17 እና ከፊልጵስዩስ 4:5 ጋር አወዳድር።) ከአቅምህ በላይ የሆነ ነገር እንድታደርግ ስትጠየቅ አልችልም ማለትን ተለማመድ።

ራስህን ከሌላ ሰው ጋር አታወዳድር። ገላትያ 6:4 “ነገር ግን እያንዳንዱ የገዛ ራሱን ሥራ ይፈትን፣ ከዚያም በኋላ ስለ ሌላው ሰው ያልሆነ ስለ ራሱ ብቻ የሚመካበትን ያገኛል” ይላል። አዎን፣ በአምልኮ ጉዳዮች እንኳን አምላክ የየግል ሁኔታችንን ከግምት ውስጥ ሳያስገባ ከሌሎች ሰዎች ጋር አያወዳድረንም። ‘በሌለን መጠን ሳይሆን ባለን መጠን’ የምናቀርባቸውን ስጦታዎችና መሥዋዕቶች ይቀበላል።—2 ቆሮንቶስ 8:12

ለመዝናኛ ጊዜ መድብ። ትጉህ ሠራተኛ የነበረው ኢየሱስ እንኳን ራሱም ሆነ ተከታዮቹ የሚያርፉበት ጊዜ መድቧል። (ማርቆስ 6:30–32) የመክብብን መጽሐፍ በመንፈስ አነሳሽነት የጻፈው ሰሎሞን ጤናማ የሆነ መዝናኛ ጠቃሚ መሆኑን ገልጿል። እንዲህ ሲል ጽፏል:- “ከሚበላውና ከሚጠጣው ደስም ከሚለው በቀር ለሰው ከፀሐይ በታች ሌላ መልካም ነገር የለውምና እኔ ደስታን አመሰገንሁ፤ ከፀሐይም በታች ከድካሙ እግዚአብሔር በሰጠው በሕይወቱ ዘመን ይህ ደስታው ከእርሱ ጋር ይኖራል።” (መክብብ 8:15) ሚዛኑን የጠበቀ ደስታ አካልን ከማደሱም በላይ ውጥረትን ያረግባል።

ውጥረትን በተመለከተ ምክንያታዊ የሆነ አመለካከት ይኑርህ

ውጥረት የሚያስከትሉ ሁኔታዎች በሚያጋጥሙህ ጊዜ:-

አምላክ ተቀይሞኛል ወይም ጥሎኛል ብለህ አታስብ። ሐና የተባለችው ታማኝ ሴት ለብዙ ዓመታት “በልብዋ ትመረር” (“ከባድ ሐዘን ይሰማት፣” የ1980 ትርጉም) እንደነበረ መጽሐፍ ቅዱስ ይነግረናል። (1 ሳሙኤል 1:4–11) ጳውሎስ በመቄዶንያ ሳለ ‘በሁሉ ነገር መከራ ተቀብሎ ነበር።’ (2 ቆሮንቶስ 7:5) ኢየሱስም ከመሞቱ በፊት “ወዙም በምድር ላይ እንደሚወርድ እንደ ደም ነጠብጣብ” እስኪፈስስ ድረስ እጅግ ተጨንቆ ነበር።a (ሉቃስ 22:44) እነዚህ ሁሉ ታማኝ የአምላክ አገልጋዮች ነበሩ። ስለዚህ ውጥረት ሲያጋጥምህ አምላክ ጨርሶ ትቶኛል ብለህ የምታስብበት ምንም ምክንያት የለም።

ጭንቀት ካስከተሉብህ ሁኔታዎች ትምህርት ቅሰም። ጳውሎስ የነበረበትን “የሥጋ መውጊያ” ችሎ ለመኖር እንደተገደደ ጽፏል። ይህ የሥጋ መውጊያ ብዙ ያስጨነቀው የጤና ችግር ሳይሆን አይቀርም። (2 ቆሮንቶስ 12:7) ይሁን እንጂ ከአምስት ዓመት ያህል ጊዜ በኋላ “በእያንዳንዱ ነገር በነገርም ሁሉ መጥገብንና መራብንም መብዛትንና መጒደልን ተምሬአለሁ። ኃይልን በሚሰጠኝ በክርስቶስ ሁሉን እችላለሁ” ለማለት ችሏል። (ፊልጵስዩስ 4:12, 13) ይህ የሥጋ መውጊያ ጳውሎስን የሚያስደስተው ነገር አልነበረም። ይህን ተቋቁሞ በመኖሩ ግን አምላክ በሚሰጠው ኃይል እንዴት መታመን እንደሚችል ተምሯል።—መዝሙር 55:22

መንፈሳዊነትን ማዳበር

የአምላክን ቃል ማንበብና ማሰላሰል። ኢየሱስ “በመንፈሳዊ የጎደላቸው ነገር እንዳለ የሚታወቃቸው ደስተኞች ናቸው” ብሏል። (ማቴዎስ 5:3 NW) የአምላክን ቃል ማንበብና ማሰላሰል በጣም አስፈላጊ ነው። ብዙ ጊዜ ቅዱሳን ጽሑፎችን በትጋት በምንመረምርበት ጊዜ ቀኑን በሙሉ አበርትቶ የሚያውለንን የማጽናኛ ቃል እናገኛለን። (ምሳሌ 2:1–6) መዝሙራዊው “አሳብና ጭንቀት በያዘኝ ጊዜ አንተ ታጽናናኛለህ፣ ደስም ታሰኘኛለህ” ሲል ጽፏል።—መዝሙር 94:19 የ1980 ትርጉም

አዘውትረህ ጸልይ። ጳውሎስ “በእግዚአብሔር ዘንድ ልመናችሁን አስታውቁ . . . አእምሮንም ሁሉ የሚያልፍ የእግዚአብሔር ሰላም ልባችሁንና አሳባችሁን በክርስቶስ ኢየሱስ ይጠብቃል” ሲል ጽፏል። (ፊልጵስዩስ 4:6, 7) አዎን፣ “ከወትሮው የበለጠ ኃይል” በሚያስፈልግበት ጊዜ እንኳን “የአምላክ ሰላም” የተረበሸውን ስሜታችንን ሊያሸንፍና ሊያረጋጋን ይችላል።—2 ቆሮንቶስ 4:7

በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ተገኝ። የክርስቲያን ጉባኤ ከፍተኛ የሆነ ድጋፍ ይሰጣል። ምክንያቱም አባሎቹ በሙሉ “ለፍቅርና ለመልካምም ሥራ እንድንነቃቃ እርስ በርሳችን እንተያይ . . . እርስ በርሳችን እንመካከር [“እንበረታታ፣” የ1980 ትርጉም]” የሚል ምክር ተሰጥቷቸዋል። ጳውሎስ የመጀመሪያው መቶ ዘመን ዕብራውያን ክርስቲያኖች ‘መሰብሰባቸውን እንዳይተዉ’ አጥብቆ የመከረው ያለበቂ ምክንያት አልነበረም።—ዕብራውያን 10:24, 25

አስተማማኝ ተስፋ

ውጥረትን መቀነስ ቀላል ነገር እንዳልሆነ የታወቀ ነው። ብዙውን ጊዜ በአስተሳሰብ ላይ መሠረታዊ ለውጥ ማድረግ ይጠይቃል። ለምሳሌ ያህል አንድ ሰው በሚያጋጥሙት ሁኔታዎች ተደናግጦ እንዳይሸነፍ የሚያስችሉትን አዳዲስ መንገዶች መማር ሊያስፈልገው ይችላል። በውጥረቱ ተደጋጋሚነትና ክብደት ምክንያት የባለሞያ ወይም የሕክምና እርዳታ ማግኘት ግዴታ የሚሆንበት ጊዜ ሊኖር ይችላል።

በዛሬው ጊዜ ከመጥፎ ውጥረት ሙሉ በሙሉ ነጻ የሆነ ኑሮ የሚመራ አንድም ሰው የለም። ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ አምላክ በቅርቡ ፊቱን ወደ ሰው ልጆች አዙሮ ይህን ያህል ከባድ ጭንቀት ያመጡባቸውን ሁኔታዎች እንደሚያስወግድ ያረጋግጥልናል። ራእይ 21:4 ላይ እንደምናነበው እግዚአብሔር “እንባዎችንም ሁሉ ከዓይኖቻቸው ያብሳል፣ ሞትም ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም፣ ኀዘንም ቢሆን ወይም ጩኸት ወይም ሥቃይ ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም።” ከዚያ በኋላ ታማኝ የሆኑ የሰው ልጆች ፍጹም በሆነ ፀጥታና የተረጋጋ ሁኔታ ይኖራሉ። ነቢዩ ሚክያስ እንደሚከተለው በማለት ተንብዮአል:- “የሠራዊት ጌታ የእግዚአብሔር አፍም ተናግሮአልና ሰው እያንዳንዱ ከወይኑና ከበለሱ በታች ይቀመጣል፣ የሚያስፈራውም የለም።”—ሚክያስ 4:4

[የግርጌ ማስታወሻ]

a በአንዳንድ ሁኔታዎች ከፍተኛ የሆነ የአእምሮ ጭንቀት በሚያጋጥምበት ጊዜ የደም ላብ እንደሚወጣ ሪፖርት ተደርጓል። ለምሳሌ ሂመተድሮሲስ የሚባለው ሁኔታ በሚከሰትበት ጊዜ ከደም ጋር የተቀላቀለ ወይም የደም ቀለም ያለው ላብ ወይም ደግሞ ከደም ጋር የተቀላቀለ የሰውነት ፈሳሽ ይወጣል። በኢየሱስ ሁኔታ የተከሰተው የትኛው እንደሆነ ግን በትክክል ማወቅ አይቻልም።

[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

መንፈሳዊነትን ማዳበር ተረጋግተህ እንድትኖር ሊረዳህ ይችላል

[በገጽ 11 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ጤንነትህን መንከባከብ ውጥረት ይቀንሳል

እረፍት

ጥሩ አመጋገብ

የሰውነት ማጠንከሪያ

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ