ኢየሱስ ክርስቶስ ማን ነበር?
በመላው ዓለም በሚገኙ በርካታ አገሮች በታኅሣሥ ወር አካባቢ የገና በዓል ይከበራል። በመቶ ሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ 2,000 ከሚጠጉ ዓመታት በፊት ታኅሣሥ 25 ቀን ወይም እንደ ኢትዮጵያ አቆጣጠር ታኅሣሥ 29 ቀን እንደተወለደ ያምናሉ። ሕፃን ሳለ በረት ውስጥ እንደተኛ የሚያሳዩ በርካታ ሥዕሎች ተስለዋል፣ ብዙ ቅርጾችም ተቀርጸዋል። እርግጥ ሕፃን እንደሆነ አልቀረም፣ አድጎ 33 ዓመት ተኩል እስኪሆነው ድረስ በምድር ላይ ኖሯል።
ኢየሱስ ሙሉ ሰው በሆነበት ጊዜ ምን ዓይነት ቁመና እንደነበረው አስበህ ታውቃለህ? መልኩ ምን ይመስል ነበር? ፈርጠም ያለ ሰውነት የነበረውና መልከ ቀና ነበር ወይስ ባለፉት መቶ ዘመናት የተነሱ የተለያዩ ሠዓሊዎች እንደሳሉት አቅመ ደካማና ከሲታ ነበር? ጺሙን ሙልጭ አድርጎ ይላጭ ነበር ወይስ ረዥም ጺም ነበረው? ፀጉሩስ ረዥም ነበር?
በተጨማሪም ኢየሱስ አንዳንድ ሠዓሊዎች እንደሚስሉት በአናቱ ላይ አክሊለ ብርሃን ነበረው? ወይስ ምንም ዓይነት ልዩ ምልክት ያልነበረውና በዙሪያው ከነበሩ ሰዎች እምብዛም የማይለይ ሰው ነበር?
ባለፉት መቶ ዘመናት የኢየሱስን ቁመና በሚመለከት ዓለማውያን የታሪክ ሊቃውንትና ሠዓሊዎች የተለያዩና እርስ በርሳቸው የሚጋጩ አስተያየቶች ሰንዝረዋል። በተጨማሪም በመጀመሪያው መቶ ዘመን ከኢየሱስ ጋር አብረው የነበሩ የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች በዓይናቸው አይተው ከጻፏቸው ትረካዎች የምናገኛቸው አስተማማኝ ፍንጮች አሉ።
ይሁን እንጂ የሚከተሉት ጥያቄዎች ከአካላዊ ቁመናውና መልኩ ይበልጥ ትልቅ ግምት ሊሰጣቸው የሚገቡ ናቸው:- ኢየሱስ ክርስቶስ በእርግጥ ማን ነበር? በአምላክ ዓላማ ውስጥ ምን ዓይነት ድርሻ አለው? ይህንንስ ድርሻውን ፈጽሟል? ዛሬስ ምን ቦታ አለው? የትስ ይገኛል? መላውን የሰው ልጅ፣ በሞት ያንቀላፉትን እንኳ ሳይቀር የሚነካ አስፈላጊ የሆነ ቦታ አለው?
በመጀመሪያ ግን ስለ ኢየሱስ ቁመናና መልክ ምን ማስረጃዎች እንደምናገኝ እንመርምር። በእርግጥ ምን ይመስል ነበር?