አንበሳ ግርማ ሞገስ የተላበሰው የአፍሪካ ባለ ጎፈር አውሬ
ኬንያ የሚገኘው የንቁ! ዘጋቢ እንዳጠናቀረው
በአፍሪካ የሴረንጌቲ ሜዳ ላይ ፀሐይ ብርሃኗን እየፈነጠቀች ነው። በቀዝቃዛው የማለዳ አየር ላንድሮቨራችን ውስጥ ተቀምጠን ከግልገሎቻቸው ጋር የተቀመጡ ሴት አንበሶች እናያለን። ዞማ የሆነው ወርቃማ ፀጉራቸው በረጃጅሙ ደረቅ ሣር ውስጥ ሲታይ ልዩ ውበት አጎናጽፏቸዋል። ግልገሎቹ ሲፈነጩ ዘለው የማይጠግቡ ይመስላሉ። ለእነርሱ ምንም ትኩረት የሰጡ በማይመስሉት ሴት አንበሶች ግዙፍ ሰውነት ዙሪያ ይዘላሉ፣ ይቦርቃሉ።
ድንገት ሁሉም ነገር እረጭ አለ። ሁሉም አንበሶች ዓይናቸውን ተክለው ወደ አንድ አቅጣጫ መመልከት ጀመሩ። ከዚያው ካለንበት ከፍ ያለ ቦታ ላይ ሆነን የሚመለከቱበትን አቅጣጫ ተከትለን ስንመለከት ትኩረታቸውን የሳበው ነገር ምን እንደሆነ ተረዳን። ፍንትው ብሎ በፈነጠቀው የንጋት ብርሃን መካከል ያማረና ግርማ ሞገስ የተላበሰ አንድ ግዙፍ ወንድ አንበሳ ቆሞ ይታያል። ትኩር ብሎ ሲመለከተን ዓይን ለዓይን ተጋጨን። ሰውነታችን ሲንቀጠቀጥ ተሰማን። ያንቀጠቀጠን የጠዋቱ ብርድ አልነበረም፤ አስፈሪ ዓይኖቹ እኛ ላይ ማረፋቸውን መገንዘባችን እንጂ። በጣም አስፈሪ ቢሆንም እንኳ ቁመናው ማራኪ ነበር። ግዙፍ ጭንቅላቱ ጥቁር ክፈፍ ባለው ጥቅጥቅ ያለ ወርቃማ ጎፈር ተሸፍኗል። ደማቅ ቢጫ ቀለም ያላቸው ትላልቅ ዓይኖቹ ንቁ ናቸው። ይሁን እንጂ ቤተሰቡ ትኩረቱን ስለሳቡት ቀስ ብሎ ዓይኑን ወደ እነሱ በማዞር ወደ እነሱ መሄድ ጀመረ።
አረማመዱ ማራኪ፣ አልፎ ተርፎም ግርማ ሞገስ የተላበሰ ነው። ዳግመኛ መለስ ብሎ ሳያየን በቀጥታ በመኪናችን ፊት ለፊት አልፎ ሴቶቹ አንበሶችና ግልገሎቻቸው ወዳሉበት ቦታ ደረሰ። ሁሉም ተነስተው በድመት ዝርያ ሥር የሚመደቡ እንስሳት ሁሉ እንደሚያደርጉት አንድ በአንድ ፊታቸውን ከጠንካራው አፉ ጋር በማፋተግ አቀባበል አደረጉለት። ወንዱ አንበሳ በሽርሽሩ የተዳከመ ይመስል አንበሶቹ መካከል ገብቶ ዘፍ አለና በጀርባው ተንደባለለ። የእሱ የድካም ስሜት ወደ ሌሎቹም ተጋባና ሁሉም የጠዋቷን ፀሐይ እየሞቁ አሸለቡ። ከፊታችን ገላጣው ሜዳ ላይ ንፋስ ወዲያና ወዲህ በሚያዘናፍለው ወርቃማ ሣር መካከል የሚታየው ሁኔታ ሁሉ ሰላምና እርካታ የሚንጸባረቅበት ነበር።
ቀልብ የሚስብ አስደናቂ ፍጡር
የአንበሳን ያህል የሰውን ልጅ ቀልብ በእጅጉ የሳበ ሌላ እንስሳ መኖሩ ያጠራጥራል። ከብዙ ዓመታት በፊት የአፍሪካ ሠዓሊያን አንበሳ እንስሶችን ሲያድን በሚያሳዩ ምስሎች ዓለቶችን ያስጌጡ ነበር። የጥንት ቤተ መንግሥታትና ቤተ መቅደሶች ከግዙፍ ድንጋይ በተሠሩ የባለ ጎፈር አንበሳ ሐውልቶች ያሸበረቁ ነበሩ። በዛሬውም ጊዜ ሰዎች ይህን አስደናቂ እንስሳ ለመመልከት ወደ አራዊት መጠበቂያ ሥፍራዎች ይጎርፋሉ። አንበሳ በመጻሕፍትና በፊልሞችም ላይ ትልቅ ቦታ ተሰጥቶታል። ወላጆቹ በመሞታቸው ምክንያት ሰዎች ስላሳደጉትና በመጨረሻ ስለ ተለቀቀው አንድ አንበሳ የሚናገረው ቦርን ፍሪ የተባለው ታሪክ ለዚህ በምሳሌነት ሊጠቀስ ይችላል። በተጨማሪም አንበሳ ከፊል እውነታን ባዘሉ ታሪኮች ላይ ሰውን የሚበላ ተንኮለኛ አውሬ ተደርጎ ተገልጿል። አንበሳ ዛሬም ድረስ ቀልብ የሚስብ አስደናቂ ፍጡር መሆኑ ምንም አያስደንቅም!
አንበሶች በጣም ቁጡ ሊሆኑ ይችላሉ፤ አንዳንድ ጊዜ ደግሞ የሙጭሊትን ያህል ገራምና ተጫዋች ይሆናሉ። ሲጠግቡ በዝግታ የሚያንኮራፉ ቢሆንም እንኳ እስከ ስምንት ኪሎ ሜትር ድረስ ሊሰማ በሚችል ኃይለኛ ድምፅ ሊያገሡ ይችላሉ። አንዳንድ ጊዜ ሰነፎችና ልፍስፍሶች ይመስሉ ይሆናል፤ ሆኖም በሚያስገርም ፍጥነት የመንቀሳቀስ ችሎታ አላቸው። የሰው ልጅ፣ አንበሳ ባለው ድፍረት ለዘላለም ሲወሳ እንዲኖር አድርጓል፤ በመሆኑም ደፋር ሰው አንበሳ ተብሎ ይጠራል።
ሲምባa—በማኅበር የሚኖር እንስሳ
አንበሶች በማኅበር ከሚኖሩት የድመት ወገን የሆኑ እንስሶች መካከል የሚጠቀሱ ናቸው። በትልልቅ መንጋ ተከፋፍለው የሚኖሩ ሲሆን እያንዳንዱ መንጋ ከጥቂት አባሎች አንስቶ ከ30 በላይ ሊደርስ ይችላል። አንድ መንጋ የጠበቀ ዝምድና ያላቸው በርከት ያሉ ሴት አንበሶች ይኖሩታል። አንድ ላይ ይኖራሉ፣ ያድናሉ እንዲሁም ይወልዳሉ። ዕድሜ ልካቸውን ሊዘልቅ የሚችለው ይህ የጠበቀ ትስስር ለመንጋው ጠንካራ መሠረት የሚጥል ከመሆኑም በላይ ለመንጋው ሕልውና ጥሩ ዋስትና ይሆናል።
እያንዳንዱ መንጋ እየተዘዋወሩ የሚጠብቁና የመንጋውን የክልል ወሰን የሚያወጡ አንድ ወይም ከአንድ በላይ የሆኑ ለአካለ መጠን የደረሱ ወንድ አንበሶች ይኖሩታል። እነዚህ ዕጹብ ድንቅ የሆኑ አውሬዎች ከጥቁሩ የአፍንጫቸው ጫፍ አንስቶ እስከ ጭራቸው ጫፍ ድረስ ከሦስት ሜትር በላይ ርዝመት ያላቸው ሲሆን ከ225 ኪሎ ግራም በላይ ሊመዝኑ ይችላሉ። ቤተሰቡን በበላይነት የሚቆጣጠሩት ወንዶቹ ቢሆኑም አመራር የሚሰጡት ግን ሴቶቹ ናቸው። ወደ ጥላ ሥፍራ መሄድን ወይም አደን መጀመርን በመሳሰሉት ሁኔታዎች ብዙውን ጊዜ መንጋውን ለአንድ ዓይነት እንቅስቃሴ የሚያነሳሱት ሴቶቹ አንበሶች ናቸው።
ሴት አንበሶች በአብዛኛው በየሁለት ዓመቱ ይወልዳሉ። ግልገሎቹ በሚወለዱበት ጊዜ ምንም ዓይነት አቅም አይኖራቸውም። ግልገሎችን ማሳደግ የሁሉም የጋራ ሥራ ነው፤ በመሆኑም ሴቶቹ አንበሶች በሙሉ በመንጋው ውስጥ ያሉትን ግልገሎች ይጠብቃሉ እንዲሁም ያጠባሉ። የግልገሎቹ ዕድገት ፈጣን ሲሆን በሁለት ወር ጊዜ ውስጥ መሮጥና መቦረቅ ይጀምራሉ። ልክ እንደ ሙጭሊቶች እየተንደባለሉ ይጫወታሉ፤ ከሚያጫውቷቸው ጋር ይታገላሉ፤ እንዲሁም በረጃጅሙ ሣር ውስጥ ወዲያና ወዲህ ይዘላሉ። እያንዳንዱ የሚንቀሳቀስ ነገር ሁሉ ስሜታቸውን ይማርከዋል፤ ቢራቢሮዎችን ለመያዝ ይዘላሉ፣ ትናንሽ ነፍሳትን ያሳድዳሉ፣ ከየጭራሮና ከየሐረጉ ጋር ይታገላሉ። ይበልጥ ስሜታቸውን የሚማርከው ግን እነርሱን ለማጫወት እናታቸው ወዲያና ወዲህ የምታወናጭፈው ጭራዋ ነው።
እያንዳንዱ መንጋ የሚኖርበት በደንብ የተከለለ ቦታ ያለው ሲሆን ይህ መኖሪያ ብዙ ስኩዌር ኪሎ ሜትር ስፋት ሊኖረው ይችላል። አንበሶች ውኃ እንደ ልብ ባለበትና ከቀትር ሐሩር የሚከላከል ጥላ በሚያገኙበት ከፍ ያለ ቦታ ላይ መኖር ይመርጣሉ። በእንዲህ ዓይነቱ ሥፍራ ከዝሆኖች፣ ከቀጭኔዎች፣ ከጎሽና ከሌሎች ሜዳማ በሆኑ ሥፍራዎች ከሚኖሩ እንስሶች ጋር በአንድነት ይኖራሉ። አንበሳ አብዛኛውን ጊዜውን በእንቅልፍ ጥቂቱን ጊዜ ደግሞ በአደንና በተዋስቦ ያሳልፋል። እንዲያውም አንበሶች በቀን ውስጥ ወደ 20 የሚጠጋውን ሰዓት የሚያሳልፉት በዕረፍት፣ በመተኛት ወይም በመቀመጥ ነው። ከባድ እንቅልፍ ተኝተው ሲታዩ ሰላማዊና ለማዳ ይመስላሉ። ይሁን እንጂ በዚህ መታለል የለብህም፤ አንበሳ እጅግ ቁጡ ከሆኑት አራዊት መካከል አንዱ ነው!
አዳኝ
አመሻሹ ላይ በሐሩር ፀሐይ ሲቃጠል የዋለው በሣር የተሸፈነ ምድር ቀዝቀዝ ማለት ይጀምራል። ስንመለከተው በቆየነው የአንበሳ መንጋ ውስጥ ያሉት ሦስቱ ሴት አንበሶች ከቀትሩ እንቅልፋቸው መነሳት ጀመሩ። የረሃብ ስሜት ስለተሰማቸው በቢጫ ሣር ከተጨፈነው ሜዳ ባሻገር እየተመለከቱና እያነፈነፉ መንቀሳቀስ ጀመሩ። ቆርኬዎች በብዛት የተሰማሩበት ጊዜ ነው፤ እነዚህ የማይማርክ ቁመና ያላቸው በአሥር ሺዎች የሚቆጠሩ ቆርኬዎች ከእኛ በስተ ደቡብ ተረጋግተው እየጋጡ ነው። ሦስቱ አንበሶች በዚያ አቅጣጫ ተጓዙ። በተንተን ብለው በወጣ ገባው መሬት ላይ በዝግታ መጓዛቸውን ቀጠሉ። ወርቃማዎቹ አንበሶች በረጃጅሙ ሣር ውስጥ ተሸፍነው ምንም ወዳልጠበቀው መንጋ በ30 ሜትር ርቀት ተጠጉ። አንበሶቹ እርምጃ ለመውሰድ የወሰኑት በዚህ ጊዜ ነበር። በብርሃን ፍጥነት በመሮጥ የደነበረውን የቆርኬ መንጋ ማሳደዱን ተያያዙት። በፍርሃት የተሸበረው መንጋ ሕይወቱን ለማዳን በሁሉም አቅጣጫ ፈረጠጠ። በመቶዎች የሚቆጠሩ ኮቴዎች አካባቢውን በቀይ አቧራ በመሸፈን ምድሪቷን ቀውጢ አደረጓት። አቧራው ገፈፍ ሲል ሦስቱ ሴት አንበሶች ብቻቸውን ቆመው ቁና ቁና ሲተነፍሱ አየናቸው። ቆርኬዎቹ አምልጠዋቸው ነበር። የዚያን ዕለት ማታ ማደን የሚችሉበት ሌላ አጋጣሚ ያገኙ ወይም አያገኙ ይሆናል። አንበሶች በጣም ቀልጣፋና ፈጣን ቢሆኑም እንኳ በአደን ጊዜ የሚሳካላቸው 30 በመቶ ብቻ ነው። በመሆኑም አንበሶች ከተደቀኑባቸው ትልልቅ አደጋዎች አንዱ ረኃብ ነው።
ለአካለ መጠን የደረሰ አንድ አንበሳ ያለው ጥንካሬ እጅግ የሚያስገርም ነው። በቤተሰብ ደረጃ የሚያድኑ እንደ መሆናቸው መጠን ከ1,300 ኪሎ ግራም በላይ ክብደት ያላቸውን እንስሳት የመጣልና የመግደል አቅም እንዳላቸው ይነገራል። አንበሶች በመጀመሪያ ላይ በሰዓት እስከ 59 ኪሎ ሜትር ድረስ ሊሮጡ ይችላሉ፤ ሆኖም ይህ ፍጥነታቸው እስከ መጨረሻ አይዘልቅም። በዚህ ምክንያት ቀለባቸውን ለማግኘት አድብቶ የመያዝ ዘዴ ይጠቀማሉ። የማደኑን ተግባር 90 በመቶ የሚያከናውኑት ሴቶቹ አንበሶች ቢሆኑም በሚበሉበት ጊዜ ትልቁን ድርሻ የሚያገኙት ትልልቆቹ ወንድ አንበሶች ናቸው። አደን በሚጠፋበት ጊዜ አንዳንዴ አንበሶች በጣም ስለሚርባቸው ያገኙትን መብል ለራሳቸው ግልገሎች እንኳ ለማካፈል ፈቃደኛ አይሆኑም።
ታዳኝ
ከብዙ ዓመታት በፊት ባለ ግርማ ሞገሱ አንበሳ በመላው የአፍሪካ አህጉር እንዲሁም በእስያ፣ በአውሮፓ፣ በህንድና በፍልስጤም አንዳንድ ቦታዎች ይገኝ ነበር። አዳኝ እንደመሆኑ መጠን ሰውን እየተቀናቀነ የሚኖር እንስሳ ነው። በከብቶች ላይ አደጋ የሚጥልና በሰዎች ላይ ጉዳት የሚያደርስ በመሆኑ አንበሳ ገና እንደታየ በጥይት የሚገደል ፍጡር ሆነ። የሕዝብ ቁጥር ፍንዳታ የአንበሳን መኖሪያ በእጅጉ አመናምኖታል። ዛሬ ከአፍሪካ ውጪ ባለው የዓለም ክፍል በዱር የሚኖሩት አንበሶች በጥቂት መቶዎች ብቻ የሚቆጠሩ ሆነዋል። በአሁኑ ጊዜ አንበሶች ሰው ከሚያደርስባቸው ጥቃት ሙሉ በሙሉ ተጠብቀው መኖር የሚችሉት ጥበቃ በሚደረግባቸው ክልሎች ውስጥና በዱር አራዊት መጠበቂያ ቦታዎች ብቻ ሆኗል።
ይሁን እንጂ ይህ ዕጹብ ድንቅ አውሬ ከዚህ በጣም የተሻሉ ሁኔታዎች ከፊቱ የሚጠብቁት መሆኑ በእጅጉ የሚያስደስት ነው። አንበሳ ከሰዎች ጋር በሰላም የሚኖርበት ጊዜ እንደሚመጣ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። (ኢሳይያስ 11:6-9) አፍቃሪው ፈጣሪያችን በቅርቡ ይህን እውን ያደርገዋል። በዚያ ጊዜ ግርማ ሞገስ የተላበሰው የአፍሪካ ባለ ጎፈር አውሬ ከተቀሩት ፍጥረታት ጋር በሰላምና በስምምነት ይኖራል።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a ሲምባ በስዋሂሊ “አንበሳ” ማለት ነው።
[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
አንበሳ ሲያገሣ
አንበሶች በሚያገሡበት ጊዜ በብዙ ኪሎ ሜትር ርቀት ሊሰማ የሚችል ከፍተኛ ድምፅ የማውጣት ልዩ ችሎታ አላቸው። አንበሳ ሲያገሣ የሚያሰማው ድምፅ “እጅግ ማራኪ ከሆኑት የተፈጥሮ ድምፆች” አንዱ እንደሆነ ይነገራል። ብዙውን ጊዜ አንበሶች በጨለማ ሰዓትና ንጋት ላይ ያገሣሉ። ወንዶቹም ሆኑ ሴቶቹ አንበሶች የሚያገሡ ሲሆን አንዳንዴም የመንጋው አባላት በአንድነት ድምፃቸውን ከፍ አድርገው ያገሣሉ።
በአንበሶች ላይ ጥናት የሚያካሂዱ ሳይንቲስቶች አንበሶች የሚያገሡባቸው የተወሰኑ ምክንያቶች እንዳሉ ይናገራሉ። ወንዶቹ አንበሶች የሚኖሩበትን ክልል ድንበር ለማሳወቅ እንዲሁም ሌሎች ወንድ አንበሶች ወደ ክልላቸው እንዳይገቡ ለማስጠንቀቅ ሲሉ ያገሣሉ። መጽሐፍ ቅዱስ የአምላክን ሕዝብ ክፉኛ የተቃወሙትንና የዋጡትን ጠበኛ፣ ኩሩና ስግብግብ የአሦርና የባቢሎን ገዥዎች እንደሚያገሡ የ“አንበሳ ደቦሎች” አድርጎ መግለጹ ተገቢ ነው።—ኢሳይያስ 5:29፤ ኤርምያስ 50:17
በርቀት ወይም በጨለማ ተነጣጥለው ያሉ የአንድ መንጋ አባላት ያሉበትን ቦታ ለመጠቆም ያገሣሉ። በተጨማሪም አንድ እንስሳ ከገደሉ በኋላ ለሌሎቹ የቤተሰቡ አባላት ምግቡ ያለበትን ቦታ ለማሳወቅ ያገሣሉ። መጽሐፍ ቅዱስ ይህን ሁኔታ ሲጠቁም እንዲህ ይላል:- “የአንበሳ ደቦል አንዳች ሳይዝ በመደቡ ሆኖ ይጮኻልን?”—አሞጽ 3:4
የሚያስገርመው ግን፣ አንበሶች በሚያድኑበት ጊዜ የሚያድኗቸውን እንስሳት ለማስደንበር ብለው አያገሡም። ሪቻርድ ኤስቲዝ ዘ ቢሄቭየር ጋይድ ቱ አፍሪካን ማማልስ በተባለው መጽሐፋቸው ላይ “አንበሶች የሚያድኑትን እንስሳ ለማጥመድ ሲሉ ሆን ብለው እንደሚያገሡ የሚጠቁም ምንም ነገር የለም (በተሞክሮዬ እንዳየሁት በአንበሳ የሚታደኑ እንስሳት አንበሳ ለሚያሰማው የግሣት ድምፅ ብዙም ትኩረት አይሰጡም)።”
ታዲያ መጽሐፍ ቅዱስ ሰይጣን ‘የሚውጠውን እንደሚፈልግ የሚያገሣ አንበሳ’ እንደሆነ አድርጎ የሚገልጸው ለምንድን ነው? (1 ጴጥሮስ 5:8) ምንም እንኳ የዱር አራዊት በአንበሳ ግሣት የማይሸበሩ ቢመስሉም የሰውና የቤት እንስሳት ሁኔታ ግን ከዚህ የተለየ ነው። በሌሊት ጨለማ የሚያስተጋባው አስፈሪው የአንበሳ ግሣት አውላላ ሜዳ ላይ ያለን ሁሉ ፍርሃትና ሽብር ይለቅበታል። ሁኔታው ከብዙ ዓመታት በፊት በትክክል ተገልጿል:- “አንበሳው አገሣ፤ የማይፈራ ማን ነው?”—አሞጽ 3:8
ሰይጣን ሰዎች ተሸብረው እንዲገዙለት ለማድረግ ፍርሃትን መሣሪያ አድርጎ በመጠቀም ረገድ የተዋጣለት ነው። ደስ የሚለው ግን፣ የአምላክ ሕዝቦች ኃያል አጋር ያላቸው መሆኑ ነው። ይሖዋ በሚሰጠው ድጋፍ ላይ ጠንካራ እምነት በማሳደር ይህን ኃይለኛ ‘የሚያገሣ አንበሳ’ በተሳካ ሁኔታ መቋቋም ይችላሉ። ክርስቲያኖች ‘በእምነት ጸንተው እንዲቃወሙት’ ማበረታቻ ተሰጥቷቸዋል።—1 ጴጥሮስ 5:9