የባርነትን አስከፊ ታሪክ መለስ ብሎ መመልከት
ከአፍሪካዊቷ አገር ከሴኔጋል የባሕር ዳርቻ ብዙም ሳትርቅ በዳካር ከተማ አቅራቢያ የኢል ደ ጎሬ ደሴት ትገኛለች። ይህች ደሴት እስከ 1848 ድረስ ለ312 ዓመታት ያህል የተጧጧፈ የባሪያ ንግድ የሚካሄድባት ማዕከል ነበረች። በፈረንሳይዋ የወደብ ከተማ በናንትስ የተገኙ የታሪክ መዛግብት እንደሚያሳዩት ከ1763 እስከ 1775 ባሉት ዓመታት ብቻ ከ103,000 የሚልቁ ከጎሬ የመጡ ባሪያዎች በናንትስ ወደብ በኩል ተሸጠዋል።
በዛሬው ጊዜ በቀን በአማካይ 200 የሚሆኑ ጎብኚዎች ሜዞን ዴዜስክላቭ የተባለውን የባሮች ቤት ሙዚየም ይጎበኛሉ። ዦዜፍ ንዳይ የተባለው አስጎብኚ ምስኪኖቹ የባርነት ሰለባዎች የደረሰባቸውን አሰቃቂ ሁኔታ እንዲህ ሲል በጥቂቱ ገልጾታል:- “የቀድሞ አባቶቻችን ከአገራቸው ተግዘው ወጥተዋል፣ ቤተሰቦቻቸው ተነጣጥለዋል፣ ቆዳቸው ልክ እንደ ከብት እየተተኮሰ ምልክት ተደርጎባቸዋል።” የየቤተሰቡ አባላት በሙሉ በሰንሰለት ታስረው ይመጣሉ። “እናትየው ወደ አሜሪካ ልትላክ ትችላለች፤ አባትየው ወደ ብራዚል ልጆቹ ደግሞ ወደ አንቲሊስ ሊወሰዱ ይችላሉ” ሲል አስጎብኚው ገልጿል።
“ክብደታቸው ከተመዘነ በኋላ” አለ ንዳይ፣ “ወንዶቹ በዕድሜያቸውና በዘር ሃረጋቸው ላይ የተመሠረተ ተመን ይወጣላቸዋል። አንዳንዶቹ ጎሳዎች በአካላዊ ጥንካሬያቸው ወይም ደግሞ ብዙ ልጆች ይወልዳሉ በሚል ከፍ ያለ የዋጋ ተመን ይወጣላቸው ነበር። ለምሳሌ ያህል የዮሩባ ጎሳ አባላት እንደ ‘አለሌ’ ይታዩ ስለነበር በከፍተኛ ዋጋ ይሸጡ ነበር።”
ከሲታ የሆኑ ምርኮኞችን እንደ እንስሳ ያደልቧቸውና ለጨረታ ያቀርቧቸዋል። የባሪያ ነጋዴዎች ወጣት ሴቶችን እየመለመሉ በየምሽቱ የፆታ ስሜታቸውን ለማርካት ይጠቀሙባቸው ነበር። ዓመፀኛ ባሪያዎችን ሥቃያቸውን ለማራዘም ሲባል ጉሮሯቸውን ሳይሆን ደረታቸውን አስረው ይሰቅሏቸው ነበር።
ሊቀ ጳጳሳት ዳግማዊ ጆን ፖል በ1992 ጎሬን ጎብኝተው ነበር። “የአፍሪካውያንን ባርነት የተለመደ የሕይወት ክፍል አድርገው ተቀብለውት የነበሩትን የካቶሊክ ሚስዮናውያን ጨምሮ በባሪያ ንግድ ተሰማርተው ለነበሩት ሰዎች ሁሉ ይቅርታ መጠየቃቸውን” ዘ ኒው ዮርክ ታይምስ ዘግቧል።
ይሁን እንጂ የተፈጸመውን ነገር አምነው ለመቀበል ፈቃደኛ የሆኑት ሁሉም አይደሉም። የናንትስ መዛግብት በቁፋሮ ከመገኘታቸው ከሁለት ዓመት ተኩል በፊት የኢየሱሳውያን ቤተ ክርስቲያን ወንጌላዊ የሆኑ አንድ ፈረንሳዊ ጎሬ ላይ በዓመት ይሸጡ የነበሩት ባሮች ከ200 እስከ 500 ብቻ የሚደርሱ እንደሆኑ ተናግረዋል። እስካሁን ድረስ “ዓለም የዚህን እኩይ ተግባር መጠነ ሰፊነት አምኖ አልተቀበለም” ሲል ሚስተር ንዳይ ተናግሯል።
[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]
Gianni Dagli Orti/Corbis
Yann Arthus-Bertrand/Corbis
ከዴስፖቲዝም የተወሰደ—የጭቆና አገዛዝ ሥዕላዊ ታሪክ