ጡንቻዎች ምርጥ የንድፍ ሥራ ውጤቶች
ሕይወት ከእንቅስቃሴ ጋር በእጅጉ የተቆራኘ ነው። ለምሳሌ ያህል በተነፈስክ ቁጥር ደረትህ ከፍ ዝቅ ይላል። ልብህ ደግሞ ወጥ በሆነ መንገድ ይመታል። ይህም በሕይወት እንድትቀጥል ይረዳሃል። ይህን እንቅስቃሴ የሚያካሂደው ምንድን ነው? ጡንቻዎች ናቸው!
ጡንቻዎች የሰውነትህ ክፍለ አካሎች ሥራቸውን እንዲያከናውኑና ሐሳብህንና ስሜትህን በድርጊት መግለጽ እንድትችል የሚረዱ የመለጠጥ ባህርይ ያላቸው ጠንካራ ህብረህዋሳት ናቸው። ድርጊቱ ፈገግታ፣ ሳቅ፣ ለቅሶ፣ ወሬ፣ እርምጃ፣ ሩጫ፣ ሥራ፣ ጨዋታ፣ ንባብም ይሁን መብላት ተግባሩን የሚያከናውኑት ጡንቻዎች ናቸው። ያለ ጡንቻ የምታከናውነው ነገር ይኖራል ብሎ ማሰብ ያስቸግራል።
በሰውነትህ ውስጥ ወደ 650 የሚጠጉ ጡንቻዎች አሉ። በጣም አነስተኛ የሚባሉት ጡንቻዎች በጆሮ ውስጥ ካሉት ጥቃቅን አጥንቶች ጋር ተያይዘው የሚገኙት ናቸው። ትልልቆቹ ደግሞ በመቀመጫ ውስጥ የሚገኙትና እግራችን እንዲንቀሳቀስ የሚያደርጉት ቂጣይ ጡንቻዎች (gluteus muscles) ተብለው የሚጠሩት ናቸው። ከወንድ አካል ግማሽ ያህሉን ክብደት ከሴት አካል ደግሞ አንድ ሦስተኛ የሚሆነውን ክብደት የሚሸፍኑት ጡንቻዎች ትልቅ ተግባር እንዲያከናውኑ ሆነው የተነደፉ ናቸው። ጡንቻዎች “ስነ ሕይወታዊ ሞተር” ተደርገው የሚቆጠሩ ሲሆን ‘በየዕለቱ ወደ እንቅስቃሴ የሚለውጡት ጉልበት አውቶሞቢልን ጨምሮ ሰው ሠራሽ የሆኑ ሞተሮች ሁሉ አንድ ላይ ተዳምረው ወደ እንቅስቃሴ ከሚለውጡት ጉልበት የበለጠ እንደሆነ’ ጄረልድ ኤች ፖለክ የተባሉ የባዮኤንጅነሪንግ ፕሮፌሰር ገልጸዋል።
በዕረፍት ላይ እያለህ እንኳ ጡንቻዎችህ ለማንኛውም እንቅስቃሴ ዝግጁ ሆነው ይጠብቃሉ። በማንኛውም ጊዜ ቢሆን በእያንዳንዱ ጡንቻ ውስጥ የተኮማተሩ የጡንቻ ክሮች (fibers) ይገኛሉ። ጭረቶቹ ካልተኮማተሩ አገጭህ ወደ ታች ይንጠለጠላል፤ የሰውነትህ የውስጥ አባላካላቶችም (organs) ምንም ድጋፍ አይኖራቸውም። ቆመህ ወይም ተቀምጠህ እያለህ እንኳ ጡንቻዎችህ አቋቋምህን ወይም ያለህበትን ሁኔታ ጠብቀህ መቆየት እንድትችል ወይም ደግሞ ከተቀመጥክበት ወንበር እንዳትወድቅ ለማገዝ አነስተኛ ማስተካከያዎች ያደርጋሉ።
የጡንቻ ዓይነቶች
በሰውነትህ ውስጥ ሦስት ዓይነት ጡንቻዎች አሉ። እያንዳንዳቸው የሚያከናውኑት ተግባር የተለያየ ነው። አንዱ ልብ ጡንቻ ሲሆን ልብ እንዲመታ የሚያደርግ ነው። ልብ ጡንቻ አንዴ ከተኮማተረ በኋላ እንደገና ከመኮማተሩ በፊት ዘና ስለሚል ከዕድሜው መካከል ግማሽ ያህሉን የሚያሳልፈው በዕረፍት ነው ለማለት ይቻላል።
ሌላው የጡንቻ ዓይነት ደግሞ ልሙጥ ጡንቻ ነው። ልሙጥ ጡንቻዎች ደም ሥሮችን ጨምሮ በአብዛኞቹ ውስጣዊ አባላካላትህ ዙሪያ የተጠቀለሉ ናቸው። ኢፍላጎታዊ ተግባር እንደሚያከናውነው እንደ ልብ ጡንቻ ሁሉ ልሙጥ ጡንቻዎችም የሚያከናውኑት ተግባር ታስቦበት የሚደረግ አይደለም። እነዚህ ጡንቻዎች ፈሳሾች በኩላሊትህና በፊኛህ ውስጥ እንዲያልፉ ማድረግን፣ ምግብ የቅንባሮተ ልመትን ጠቅላላ ሂደት እንዲጨርስ ማድረግን፣ ደም በደም ሥሮች ውስጥ የሚያደርገውን ዝውውር መቆጣጠርን፣ የዓይን ሌንስን ቅርጽ እንደ አስፈላጊነቱ መለዋወጥንና የዓይን ብሌንህን እንደ ብርሃን መጠን ማስፋትና ማጥበብን የመሳሰሉ በጣም አስፈላጊ የሆኑ ተግባሮች ያከናውናሉ።
ወደ 650 ከሚጠጉት ጡንቻዎችህ መካከል አብዛኞቹ የአፅም ጡንቻዎች ናቸው። እነዚህ ጡንቻዎች ፍላጎታዊ እንቅስቃሴዎችህን ያከናውናሉ። ከተወለድክበት ጊዜ ጀምሮ እነዚህን ጡንቻዎች እንዴት መቆጣጠር እንደምትችል ትማራለህ። ለምሳሌ ያህል አንድ ሕፃን መራመድና ሚዛኑን መጠበቅ እንዲችል ክንዶቹንና እግሮቹን ማንቀሳቀስ ይማራል። ጡንቻዎች አንድ ተግባር የሚያከናውኑት በመኮማተር ብቻ ስለሆነ የአፅም ጡንቻዎች ሥራቸውን የሚያከናውኑት በጥንድ በጥንድ ሆነው ነው። አንደኛው ጡንቻ ሲኮማተር ሌላኛው ዘና ይላል። እንዲህ ዓይነቱ የኅብረት ሥራ ባይኖር ኖሮ ራስህን ባከክ ቁጥር ክንድህን መልሶ የሚያወርድልህ የስበት ኃይል ብቻ ይሆን ነበር። ከዚህ ይልቅ ግን የባላጡንቻህ (biceps) አጋር የሆነው መንሽ ጡንቻህ (triceps) በመኮማተር ክንድህ ወዲያውኑ ወደ ቦታው እንዲመለስ ያደርገዋል።
ጡንቻዎች በቅርጽና በመጠን ይለያያሉ። ሃምስትሪንግ ተብለው እንደሚጠሩት የቅልጥም ጡንቻዎች ያሉ አንዳንድ ጡንቻዎች ረጅምና ቀጭን ናቸው። በመቀመጫ ውስጥ እንዳሉት ቂጣይ ጡንቻዎች ያሉት ሌሎች ጡንቻዎች ደግሞ ወፍራምና ሰፋፊ ናቸው። ሁሉም እንቅስቃሴ ማድረግ በሚያስችሉህ መንገድ የተነደፉ ናቸው። በጎድን አጥንቶች መካከል ያሉትን ክፍተቶች የሚሸፍኑ ጡንቻዎች ባይኖሩ ኖሮ የጎድን መዋቅር በጣም ድርቅ ያለ ይሆን ነበር። እነዚህ ጡንቻዎች የደረትህ ግድግዳ ልክ እንደ አኮርዲዮን እንዲንቀሳቀስ በማድረግ መተንፈስ እንድትችል ይረዱሃል። የሆድ ጡንቻዎች ከኮምፖንሳቶ ንብብሮች ጋር በሚመሳሰል ሁኔታ ከተለያየ አቅጣጫ በስስ በስሱ በመዘርጋታቸው የሆድ ዕቃ አባላካላትህን አጥብቀው ይይዟቸዋል።
የጡንቻና የጅማት ኅብረት
አጥንቶችህን የሚያንቀሳቅሱት ጡንቻዎች ጅማት ተብለው በሚጠሩ ጠንካራ በሆኑና ገመድ በመሰሉ ነጭ ህብረህዋሳት ከአጥንቶችህ ጋር ተያይዘዋል። ጅማቶች ጡንቻዎች ውስጥ ጠልቀው በመግባት በጡንቻ ክር ዙሪያ ከሚገኘው አጣማሪ ህብረህዋስ ጋር የተያያዙ ናቸው። አጣማሪ ህብረህዋስ ከጡንቻዎችህ ውስጥ የሚወጣው ኃይል ጅማቱን በመጎተት አጥንቶችህን እንዲያንቀሳቅሳቸው ያደርጋል። ከሁሉ ይበልጥ ኃይለኛ የሆነው አኪለስ የተባለው ጅማት ባትህ ውስጥ ከሚገኙት እጅግ ጠንካራ የሆኑ ጡንቻዎች ጋር የተያያዘ ነው። የባት ጡንቻዎች የሰውነት ክውታ ሞሳሽ (shock absorber) ሆነው ያገለግላሉ። ስትራመድ፣ ስትሮጥ ወይም ስትዘል ከአንድ ቶን የሚበልጥ ግፊት መቋቋም ይችላሉ።
ብዙ ተግባሮችን የሚያከናውነው እጅህም ለጡንቻና ጅማት ኅብረት ሌላ ምሳሌ ነው። በታንታይ ክንድህ (forearm) ውስጥ የሚገኙት ሀያ ጥንድ ጡንቻዎች በጭረታማ አምባርሠቅ (wristband) ሥር በሚያልፉ ረጃጅም ጅማቶች አማካኝነት ብዙ አንጓዎች ያሉትን እጅህንና የጣቶችህን አጥንቶች አያይዘዋል። እነዚህ ጡንቻዎች መዳፍህና ጣቶችህ ላይ ከተነጠፉት ሌሎች 20 ጡንቻዎች ጋር አንድ ላይ ሆነው እጅህ ጥንቃቄ የሚጠይቁትን የአንድን ግሩም ሰዓት ውስጣዊ ክፍሎች ለመገጣጠም ወይም ደግሞ መጥረቢያ ይዘህ እንጨት ለመፍለጥ የሚያስችል አስደናቂ ቅልጥፍና እንዲኖረው አድርገውታል።
ከ30 የሚበልጡ የፊት ጡንቻዎች
ፊትህ ከየትኛውም የሰውነትህ ገጽታ በበለጠ ሁኔታ ስብዕናህን ይገልጻል። ፊትህ ብዙ ዓይነት የፊት መግለጫዎችን ማስተናገድ እንዲችል ፈጣሪ ብዛት ያላቸው በጥቅሉ ከ30 የሚበልጡ ጡንቻዎች በፊትህ ላይ እንዲኖሩ አድርጓል። ፈገግ ለማለት ብቻ እንኳ 14 ጡንቻዎች ትጠቀማለህ!
የጎረስከውን ምግብ ለማኘክ እስከ 75 ኪሎ ግራም የሚደርስ ኃይል ማመንጨት የሚችሉትን ከአገጭህ ጋር ተያይዘው የሚገኙትን ጡንቻዎች የመሰሉ አንዳንድ የፊት ጡንቻዎች ከፍተኛ ኃይል አላቸው። ዓይንህን ስታርገበግብ በቀን ውስጥ ከ20,000 ጊዜ በላይ ቆሻሻና ጀርም በሚያስወግድ ፈሳሽ ዓይንህን የሚያጥቡትን የአይን ቆቦች የሚቆጣጠሩትን ጡንቻዎች የመሰሉ በቀላሉ ሊጎዱ የሚችሉ ግን ረጅም ዕድሜ ያላቸው ጡንቻዎችም አሉ።
አስደናቂ ንድፍ
እያንዳንዱ ጡንቻ የተሠራው በቀላሉ መኮማተር እንዲችል ተደርጎ ነው። ላባ ስናነሳና 10 ኪሎ ግራም የሚመዝን ዕቃ ስናነሳ አንድ ዓይነት ጉልበት እንዳናጠፋ የአፅም ጡንቻዎች ራሳቸውን ከሁኔታው ጋር ማጣጣም ይኖርባቸዋል። ይህ ሊሆን የሚችለው እንዴት ነው? እስቲ እንመልከት።
ሁሉም ጡንቻዎች ከተለያዩ ህዋሳት የተሠሩ ናቸው። የጡንቻ ህዋሳት ቀጠን ብለው ረዘም ያሉ በመሆናቸው ክር ተብለው ይጠራሉ። አንዳንዶቹ ክሮች ነጣ ያለ ቀለም ያላቸው ሲሆን ሌሎቹ ደግሞ ጠቆር ያሉ ናቸው። ነጣ ያሉት ክሮች በፍጥነት የሚኮማተሩ ናቸው። እነዚህ ክሮች ጥቅም ላይ የሚውሉት ከባድ ዕቃ ማንሣትን ወይም የ100 ሜትር ፈጣን ሩጫ መሮጥን የመሰሉ ለአጭር ጊዜ የሚቆዩና ከፍተኛ ኃይል የሚጠይቁ እንቅስቃሴዎች ማድረግ በምትፈልግበት ጊዜ ነው። በፍጥነት የሚኮማተሩት እነዚህ የጡንቻ ክሮች ከፍተኛ ኃይል ያላቸው ሲሆን የኃይል ምንጫቸው ግላይኮጅን የተባለው ስኳር ነው። ይሁን እንጂ ቶሎ የሚዝሉ ከመሆናቸውም በላይ በውስጣቸው በሚከማቸው ላክቲክ አሲድ ምክንያት ሊሸማቀቁ ወይም የሕመም ስሜት ሊያመጡ ይችላሉ።
ጠቆር ያሉት የጡንቻ ክሮች በዝግታ የሚኮማተሩ ሲሆኑ የሚንቀሳቀሱት በኦክሲጅን ገንባፍራሽ ቅንባሮ (metabolism) አማካኝነት ነው። እነዚህ ክሮች ከፍተኛ የደም አቅርቦት ስላላቸውና በፍጥነት ከሚኮማተሩት ክሮች የበለጠ አየራዊ ኃይል ስላላቸው “የጽናት እትብት ናቸው።”
ሌላው የክር ዓይነት በፍጥነት ከሚኮማተሩት ነጣ ያሉ ክሮች በትንሹ ጠቆር ያለ ነው። ይህ ክር በፍጥነት ከሚኮማተሩት ክሮች ጋር የሚመሳሰል ቢሆንም እንኳ ድካም የመቋቋም ብቃት አለው። ይህ ዓይነቱ ክር ስኳርንና ኦክሲጅንን በቀላሉ የኃይል ምንጭ አድርጎ መጠቀም ስለሚችል ጥቅም ላይ የሚውለው ረዘም ላለ ጊዜ የሚቆይ ከባድ ሥራ በምትሠራበት ጊዜ ሳይሆን አይቀርም።
የእያንዳንዱ ግለሰብ ሰውነት በተለያዩ ጡንቻዎች ውስጥ የእነዚህን በርከት ያሉ ክሮች ድብልቅ የያዘ ነው። ለምሳሌ ያህል የረጅም ርቀት ሯጮች በቅልጥማቸው ጡንቻዎች ውስጥ ካሉት ክሮች መካከል 80 በመቶዎቹ በዝግታ የሚኮማተሩ ሊሆኑ ይችላሉ። በአንጻሩ ግን በአጭር ርቀት ሯጮች የቅልጥም ጡንቻዎች ውስጥ ከሚገኙት ክሮች መካከል ከ75 በመቶ በላይ የሚሆኑት በፍጥነት የሚኮማተሩ ሊሆኑ ይችላሉ።
በነርቮች የሚንቀሳቀሱ
ሁሉም የጡንቻ ክሮች የሚንቀሳቀሱት በነርቮች አማካኝነት ነው። እነዚህ ነርቮች በጡንቻዎችህ ላይ ግፊት ሲያሳድሩ ጡንቻዎችህ ይኮማተራሉ። ሆኖም በአንድ ጡንቻ ውስጥ ያሉ ክሮች በሙሉ በአንድ ጊዜ ይኮማተራሉ ማለት አይደለም። ከዚህ ይልቅ የጡንቻ ክሮች በሞተር ዩኒቶች የተከፋፈሉ ናቸው። በአንድ ሞተር ዩኒት ውስጥ አንድ ነርቭ ከብዙ የጡንቻ ክሮች ጋር በመያያዝ ብዙ ክሮችን ይቆጣጠራል።
በቅልጥምህ ጡንቻዎች ውስጥ ያሉትን የመሰሉ አንዳንድ ሞተር ዩኒቶች በአንድ ነርቭ በሚመሩ ከ2,000 በላይ በሚሆኑ ክሮች የተዋቀሩ ናቸው። ሆኖም በዓይንህ ውስጥ ያሉት ሞተር ዩኒቶች እያንዳንዳቸው ሦስት ሦስት ክሮች ብቻ ያላቸው ናቸው። በአንድ ሞተር ዩኒት ውስጥ አነስተኛ ክሮች መኖራቸውና በአንድ ጡንቻ ውስጥ በርከት ያሉ ሞተር ዩኒቶች መኖራቸው በመርፌ ቀዳዳ ውስጥ ክር ማስገባትን ወይም ፒያኖ መጫወትን ለመሰሉ የተሻለ ቅንጅትና ጥንቃቄ ለሚጠይቁ እንቅስቃሴዎች ጥሩ አስተዋጽኦ ያበረክታሉ።
አንድ ላባ በምታነሳበት ጊዜ የሚኮማተሩት ሞተር ዩኒቶች ጥቂት ናቸው። ከባድ ዕቃ በምታነሳበት ጊዜ በጡንቻህ ክር ውስጥ የሚገኙ ለየት ያሉ የስሜት አባላካላት በብርሃን ፍጥነት ወደ አንጎል መልእክት በማስተላለፍ ተጨማሪ ሞተር ዩኒቶች እንዲኮማተሩ ያደርጋሉ። በዚህ መንገድ ዕቃውን ለማንሳት የምትጠቀምበት ኃይል መጠን ይጨምራል። በዝግታ በምትራመድበት ጊዜ የሚንቀሳቀሱት ሞተር ዩኒቶች ጥቂት ናቸው። በምትሮጥበት ጊዜ ግን በርካታ ሞተር ዩኒቶች የሚሠሩ ከመሆናቸውም በላይ የእንቅስቃሴያቸው ፍጥነት ይጨምራል።
የልብህ ጡንቻ ሙሉ በሙሉ የሚኮማተር ወይም ዘና የሚል በመሆኑ ከአፅም ጡንቻ የተለየ ነው። በልብ ጡንቻ ውስጥ የሚገኝ አንድ ህዋስ በሚቀሰቀስበት ጊዜ መልእክቱ ወደ ሁሉም ህዋሳት ይዳረስና ሁሉም በአንድ ጊዜ ይቀሰቀሳሉ። ይህም መላው ጡንቻ በደቂቃ 72 ጊዜ ገደማ እንዲኮማተርና ዘና እንዲል ያደርገዋል።
ልሙጥ ጡንቻዎች የሚንቀሳቀሱት ከልብ ጡንቻ ጋር በሚመሳሰል ሁኔታ ነው። አንዴ የመኮማተር ሂደቱ ከጀመረ መላው አባላካል ይኮማተራል። ሆኖም ልሙጥ ጡንቻዎች ከልብ ጡንቻዎች በበለጠ ሳይዝሉ ለረጅም ጊዜ እንደተኮማተሩ መቆየት ይችላሉ። ልሙጥ ጡንቻዎች አልፎ አልፎ በረሐብ ስሜት ወይም ደግሞ በወሊድ ወቅት በኃይል በሚኮማተሩበት ወቅት ካልሆነ በስተቀር መኖራቸውንም ልብ የሚለው አይኖርም።
የጡንቻዎችህን ጤንነት ጠብቅ
መስልስ:- ዘ ማጂክ ኦቭ ሞሽን የተባለው መጽሐፍ “የአካል ብቃት እንቅስቃሴ መላው የሰውነት አካላችን ጤናማ እንዲሆን ይረዳል። . . . ቋሚ በሆነ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ የዳበሩ ጡንቻዎች በማንኛውም ሁኔታ ረገድ የተሻለ ሥራ ማከናወን ይችላሉ” ሲል ይገልጻል። የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ጡንቻዎች ጥሩ ብርታት ኖሯቸው ውስጣዊ አባላካላትህን በተሻለ ሁኔታ ደግፈው እንዲይዙ የሚያስችላቸው ከመሆኑም በላይ ድካምን መቋቋም እንዲችሉ ይረዳቸዋል።
ለጡንቻዎችህ በጣም ጠቃሚ የሆኑ ሁለት ዓይነት የአካል ብቃት እንቅስቃሴዎች አሉ። በየቀኑ ለአጭር ጊዜ ክብደት በማንሳት የምትሠራው አየር አልባ (anaerobic) ተብሎ የሚጠራው የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ጡንቻዎችህን ያጠነክራቸዋል። ጠንካራ ጡንቻዎች ተጨማሪ ስኳርና ፋቲ አሲዶች ማከማቸት ብቻ ሳይሆን እነዚህን የኃይል ምንጮች በተሻለ ቅልጥፍና መጠቀም ይችላሉ። ይህ ደግሞ ጡንቻዎችህ ድካምን መቋቋም እንዲችሉ ይረዳቸዋል።
በዝግታ መሮጥን፣ መዋኘትን፣ ብስክሌት መንዳትን ወይም ፈጠን ባለ ሁኔታ መራመድን የመሳሰሉ አየራዊ (aerobic) ተብለው የሚጠሩት የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ዓይነቶች ደግሞ የተሟላ የአካል ብቃት እንዲኖርህ ይረዱሃል። በጽናት እንዲህ ዓይነቱን የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ ወደ ጡንቻዎች የሚፈስሰውን ደም መጠን የሚጨምር ከመሆኑም በላይ ኤ ቲ ፒን ማለትም ጡንቻዎችህ እንዲኮማተሩ የሚያደርገውን ውሁድ ኃይል የሚፈጥሩት ሃይለህዋሳት እንዲበዙ ያደርጋል። እንዲህ ዓይነቱ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ በተለይ ለልብህ በጣም ጠቃሚ ነው። እንዲያውም ለልብ ድካም በሽታ እንዳትጋለጥ ሊረዳህ ይችላል።
ከበድ ያለ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ከመሥራትህ በፊት ጡንቻዎችህን እጥፍ ዘርጋ ማድረግ ከወለምታ ወይም በጡንቻዎችህ ላይ ሊደርስ ከሚችል ሌላ ጉዳት ሊጠብቅህ ይችላል። በዚህ መንገድ ሰውነትህን ማሟሟቅህ የጡንቻዎችህን የሙቀት መጠን ከፍ እንዲል ያደርገዋል። ይህም ተጨማሪ ደም በጡንቻዎችህ ውስጥ እንዲዘዋወርና ኤንዛይሞች ተጨማሪ ኃይል እንዲያመነጩ የሚረዳ በመሆኑ ጡንቻዎችህ በተሻለ ሁኔታ መኮማተር ይችላሉ። ሰውነትህን ለማሟሟቅ የተጠቀምክባቸውን እንቅስቃሴዎች መልሰህ በመጠቀም ሰውነትህን ማቀዝቀዝህ የተከማቸውን ላክቲክ አሲድ ስለሚያስወግደው የሕመም ስሜትንና የጡንቻ መጓጎልን ለመከላከል ይረዳል።
ይሁን እንጂ በተለይ የሠለጠንክ ካልሆንክ ከባድ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ በመሥራት የአፅም ጡንቻህን ልትጎዳ እንደምትችል መዘንጋት የለብህም። በተጨማሪም ከባድ ሸክምን ቀስ ብሎ ማውረድን ወይም በቁልቁለት ላይ መሮጥን በመሰሉ ሁኔታዎች ጡንቻዎችህ በተደጋጋሚ ረዘም ላለ ጊዜ እንዲኮማተሩ በማድረግ ከባድ ውጥረት የምታሳርፍባቸው ከሆነ የጡንቻ መሰንጠቅ ሊደርስብህ ይችላል። ጉዳቱ አነስተኛ በሚሆንበት ጊዜም እንኳ ከባድ የጡንቻ መሸማቀቅ ወይም ብግነት ሊያስከትል ይችላል።
ስለዚህ ጡንቻዎችህን ተንከባከብ። ጡንቻዎችህ በደንብ እንደተሠራ ሞተር ሰውነትህን ‘በሚገባ ማንቀሳቀሳቸውን’ እንዲቀጥሉ ጥሩ የአካል ብቃት እንቅስቃሴና ዕረፍት አድርግ።
[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]
በሰውነትህ ውስጥ 650 የሚሆኑ ጡንቻዎች አሉ። ከሁሉም ይበልጥ ትልልቅ የሆኑት ጡንቻዎች በመቀመጫ ውስጥ የሚገኙትና እግርን የሚያንቀሳቅሱት ቂጣይ ጡንቻዎች የሚባሉት ናቸው
[በገጽ 20 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
ጡንቻዎችና ያመጋገብ ዘዴ
የጡንቻዎችን ጤንነት ለመጠበቅ ጥሩ ያመጋገብ ልማድ ወሳኝነት አለው። እንደ ወተት ውጤቶች ያሉ በካልሲየም የዳበሩ ምግቦችና እንደ ሙዝ፣ የብርቱካን ዘር የሆኑ ፍራፍሬዎች፣ የደረቁ ፍራፍሬዎች፣ ቢጫ አትክልቶች፣ ለውዝና ጥራጥሬዎች ያሉ በፖታሲየም የዳበሩ ምግቦች የጡንቻን የመኮማተር ሂደት ለመቆጣጠር ይረዳሉ። ካልተፈተጉ የእህል ዝርያዎች የሚዘጋጅ ዳቦና እንደ ስንዴ ያሉ እህሎች ብረትና ቪታሚን ቢ-ኮምፕሌክስ፣ በተለይ ደግሞ ካርቦሃይድሬትን፣ ፕሮቲንና ስብን ጡንቻዎችህ ወደሚያስፈልጋቸው ጉልበት ለመለወጥ በጣም አስፈላጊ የሆነው ቫይታሚን B1 አላቸው። ብዙ ውኃ መጠጣት የኤሌክትሮላይት ሚዛንህን ለመጠበቅ ብቻ ሳይሆን ላክቲክ አሲድንና የጡንቻን ሥራ ሊያስተጓጉሉ የሚችሉ ሌሎች ቆሻሻዎችን ለማስወገድ ይረዳል።
[በገጽ 18, 19 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕላዊ መግለጫ]
የጡንቻ መኮማተር አስደናቂ አሠራር
የጡንቻ እንቅስቃሴ ቀላል ሊመስል ይችላል። ሆኖም የጡንቻ መኮማተር አሠራር እጅግ አስደናቂ ነው። ፕሮፌሰር ጄረልድ ኤች ፖለክ እንዲህ ሲሉ ገልጸዋል:- “በተፈጥሮ ንድፍ ላይ የተንጸባረቀው ከፍተኛ የፈጠራ ችሎታ በግርምት ያስደምመኛል። ኬሚካላዊ ጉልበት ወደ ሜካኒካዊ ጉልበት የሚለወጥበት ቅጽበታዊ የሆነ መንገድ እጅግ አስገራሚ ከመሆኑም በላይ ከዚህ ንድፍ በስተጀርባ ያለውን ከፍተኛ የማሰብ ችሎታ አምኖ ለመቀበል የሚያስገድድ ነው።”
የጡንቻ መኮማተርን የረቀቀ አሠራር ለመመልከትና ፈጣሪያችን ስለነደፈው ስለዚህ ድንቅ የሥራ ውጤት ይበልጥ ለማወቅ እንድንችል እስቲ አንድ የኤሌክትሮን ማጉያ መነፅር እንጠቀም።
እያንዳንዱ የጡንቻ ህዋስ ወይም ክር ትይዩ በሆነ መንገድ የተቀመጡ ማዮፋይብረልስ ተብለው የሚጠሩ ትናንሽ ክሮች ጥምረት ነው። እያንዳንዱ ማዮፋይብረል ደግሞ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ በጣም ቀጫጭን የሆኑ ማዮፊላመንት የያዘ ነው። አንዳንድ ማዮፊላመንት ወፈር ያሉ ሲሆኑ አንዳንዶቹ ደግሞ በጣም ቀጫጭን ናቸው። ወፈር ወፈር ያሉት ማዮሰን የተባለ ፕሮቲን የያዙ ሲሆን ቀጫጭኖቹ ደግሞ አክተን የተባለ ፕሮቲን የያዙ ናቸው። እነዚህ ፕሮቲኖች የጡንቻ ህዋስ እንዲኮማተር ይረዳሉ።
በእያንዳንዱ የጡንቻ ክር ገጽ ላይ ክፍተት አለ። ከአከርካሪ አጥንት የተዘረጋው የነርቭ ክር እስከ እዚህ ክፍተት ድረስ ይመጣና ከክፍተቱ ጋር ይጋጠማል። ጡንቻዎቻችን የሚንቀሳቀሱት አንጎል የሚያስተላልፈው ትእዛዝና መልእክት በማእከላዊ ስርአተ ነርቭ የሚገኙትን በሚልዮን የሚቆጠሩ የነርቭ ህዋሳት አልፎ የነርቩ ጭራ ጋር ሲደርስ ነው። እያንዳንዱ የነርቭ ጭራ በሚቀሰቀስበት ጊዜ ከ100 የሚበልጡ ትናንሽ ከረጢቶች ተከፍተው ነርቩ ከጡንቻው ህዋስ ገለፈት ጋር በሚገናኝበት ጊዜ የሚያሳድረውን ግፊት የሚያገንን ኬሚካል ያፈስሳሉ። ይህ ሁኔታ መላውን የጡንቻ ህዋስ የሚያጦፍ የኤሌክትሪክ እንቅስቃሴ ሞገድ ይፈጥራል። ይህ ደግሞ የህዋሱ ገለፈት የመኮማተርን ሜካኒካዊ ሂደት የሚቀሰቅሱ የኤሌክትሪክ ኃይል ያላቸው ካልሲየም አዮኖች እንዲያመነጭ ያደርገዋል።
ካልሲየም አዮኖቹ በጣም ትናንሽ በሆኑ ቱቦዎች መረብ በኩል አድርገው በመላው የጡንቻ ክር ውስጥ ይሰራጩና ከተለያዩ ፕሮቲኖች ጋር ይገናኛሉ። ካልሲየሙ በእነዚህ ፕሮቲኖች ላይ የሚያመጣው ለውጥ በቀጭኑ የአክተን ፊላመንት ዘንግ ዳር ያሉት ጥብቅ የፕሮቲን ቀጣናዎች በሆነ መንገድ እንዲከፈቱ ወይም እንዲጋለጡ ያደርጋቸዋል።
በዚሁ ጊዜ ኤ ቲ ፒ ተብሎ የሚጠራ ከፍተኛ ጉልበት ያለው ውሁድ ያላቸው ጥንድ ጥንድ ቅርጸ ክብ እምቡጦች ወፈር ወፈር ካሉት የማዮሰን ፊላመንቶች ተነስተው እንቅስቃሴ ማድረግ ይጀምራሉ። በማዮሰን ፊላመንት ጭንቅላት ላይ ከሚገኙት እምቡጦች አንዱ በአክተን ፊላመንት ላይ ከሚገኙት በእንቅስቃሴ ላይ ያሉ የተጋለጡ ቀጣናዎች መካከል ከአንዱ ጋር ይያያዝና መሸጋገሪያ ድልድይ ይሠራል። ሌላው እምቡጥ መሸጋገሪያ ድልድዩ አክተን ፊላመንቱን በማዮሰን ፊላመንቱ ጎን ወይም ላይ መሳብ ይችል ዘንድ ኤ ቲ ፒውን ሰባብሮ በቂ ጉልበት ያመነጫል። እጃቸውን ቀስ በቀስ ወደፊት እያስጠጉ ገመድ እንደሚጎትቱ ሰዎች የማዮሰን ጭንቅላቶችም የጨበጡትን ለቅቀው ወደፊት እየተጠጉ በመያዝ የአክተን ዘንጉን ስበው ወደ ማዮሰን ፊላመንቱ ዕምብርት ያመጡታል። የመኮማተር ሂደቱ የተሟላ እስኪሆን ድረስ ይህ እንቅስቃሴ ይቀጥላል። እንደ ሰንሰለት የተሳሰረው መላው ሂደት የሚከናወነው በአንድ ሰኮንድ ጥቂት ሺህኛ ጊዜ ውስጥ ነው!
የመኮማተር ሂደቱ ሲጠናቀቅ ካልሲየሙ ወደመጣበት ወደ ጡንቻ ህዋሱ ገለፈት ይመለሳል። በአክተን ፊላመንቱ ዳር ያሉት የተጋለጡ ቀጣናዎች እንደገና ይሸፈናሉ። የጡንቻ ጭረቱም እንደገና እስኪቀሰቀስ ድረስ ዘና ይላል። በእርግጥም ‘የተፈጠርነው ግሩምና ድንቅ ሆነን ነው’!—መዝሙር 139:14
[ሥዕላዊ መግለጫ]
(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)
ጡንቻዎቻችን እርስ በርሳቸው የተጣመሩ ክሮች ንብር ናቸው
ወፍራምና ቀጫጭን ማዮፊላመንቶች (በጣም ጎልቶ የቀረበ)
ማዮፋይብረል
እርስ በርሳቸው የተጣመሩ ማዮፋይብረሎች
የጡንቻ ክር
ጡንቻ
[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
(ሁለት እጥፍ ጎልቶ ሲታይ)
በጣም አነስተኛ የሚባሉት ጡንቻዎች በጆሮ ውስጥ ካሉት ጥቃቅን አጥንቶች ጋር ተያይዘው የሚገኙት ናቸው
[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ፈገግ ለማለት ብቻ እንኳ 14 ጡንቻዎች ትጠቀማለህ!
[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ጡንቻዎች ዓይንህን በቀን ውስጥ ከ20,000 ጊዜ በላይ እንድታርገበግብ ያስችሉሃል
[በገጽ 20 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የልብህ ጡንቻ በደቂቃ 72 ጊዜ ያህል ወይም ደግሞ በሕይወት ዘመንህ በሙሉ በአማካይ 2.6 ቢልዮን ጊዜ እየተኮማተረ ይፈታል
[በገጽ 20 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
አየር አልባ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ
[በገጽ 16 ላይ የሚገኙ የሥዕል ምንጮች]
ሰው፣ ገጽ 16፤ ዓይን፣ ገጽ 17፤ ልብ፣ ገጽ 20:- The Complete Encyclopedia of Illustration/J. G. Heck