የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • g99 6/8 ገጽ 10-13
  • ‘ልጆቹ ደካሞች ናቸው’

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ‘ልጆቹ ደካሞች ናቸው’
  • ንቁ!—1999
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • ከፍ ያሉ መሠረታዊ ሥርዓቶች
  • በዘመናችን ያሉት እውነታዎች
  • እውነተኛው መፍትሔ
  • ልጆቻችሁን ከሕፃንነታቸው ጀምሮ አሠልጥኗቸው
    ለቤተሰብ ደስታ ቁልፉ ምንድን ነው?
  • በመንፈሳዊ ጠንካራ የሆነ ቤተሰብ መገንባት
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2001
  • ልጆቻችሁ ይሖዋን እንዲወዱ አስተምሯቸው
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2007
  • ልጆች የሚያስፈልጋቸውን ትኩረት መስጠት
    ንቁ!—2005
ለተጨማሪ መረጃ
ንቁ!—1999
g99 6/8 ገጽ 10-13

‘ልጆቹ ደካሞች ናቸው’

‘ልጆቹ ደካሞች ናቸው፤ በሕፃናቱ እርምጃ መጠን በዝግታ እከተላለሁ።’—ያዕቆብ፣ የብዙ ልጆች አባት፣ 18 ኛው መቶ ዘመን ከዘአበ

በሕፃናት ላይ የሚፈጸመው በደል ከጊዜ በኋላ የመጣ ነገር አይደለም። እንደ አዝቴኮች፣ ከነዓናውያን፣ ኢንካዎችና ፊንቃውያን ያሉ የጥንት ኅብረተሰቦች ሕፃናትን መሥዋዕት አድርጎ የማቅረብ መጥፎ ልማድ ነበራቸው። የፊንቃውያን ከተማ በነበረችው በካርቴጅ (በአሁኑ ጊዜ በሰሜን አፍሪካ በቱኒስ ዳርቻ ላይ ትገኛለች) የተካሄዱ ቁፈራዎች ከአምስተኛው እስከ ሦስተኛው መቶ ዘመን ከዘአበ በነበሩት ዓመታት ውስጥ 20,000 የሚሆኑ ሕፃናት በኣል ለተባለው አምላክና ታኒት ለተባለችው የሴት አምላክ መሥዋዕት ሆነው መቅረባቸውን አረጋግጠዋል! ከተማዋ በዚያ ገናና በነበረችበት ዘመን የሕዝቧ ቁጥር 250,000 ገደማ ብቻ የነበረ መሆኑ ሲታይ እነዚህ ሁሉ ሕፃናት መሠዋታቸው በጣም አስደንጋጭ ነው።

ይሁን እንጂ የተለየ አቋም የነበረው አንድ ጥንታዊ ኅብረተሰብ ነበር። የእስራኤል ሕዝብ በሕፃናት ላይ አሰቃቂ ድርጊቶች በሚፈጽሙ ጎረቤት ሕዝቦች መካከል ይኖር የነበረ ቢሆንም እንኳ ለልጆች የነበረው አመለካከት ፈጽሞ የተለየ ነበር። የዚህ ሕዝብ ማለትም የዕብራውያን አባት የነበረው ያዕቆብ ጥሩ ምሳሌ ትቷል። የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የሆነው የዘፍጥረት መጽሐፍ እንደሚለው ያዕቆብ ወደ ትውልድ አገሩ እየተመለሰ በነበረበት ወቅት ሕፃናቱ ጉዞው በጣም አስቸጋሪ እንዳይሆንባቸው ሲል ቤተሰቡም ሆነ አገልጋዮቹ በሙሉ በዝግታ እንዲራመዱ አድርጓል። ‘ልጆቹ ደካሞች ናቸው’ ሲል ተናግሯል። በዚያ ወቅት ልጆቹ ከ5 እስከ 14 ዓመት ባለው የዕድሜ ክልል ውስጥ ይገኙ ነበር። (ዘፍጥረት 33:13, 14) ዘሮቹ የሆኑት እስራኤላውያንም የእሱን አርአያ በመከተል ሕፃናት ለሚያስፈልጓቸው ነገሮችና በኅብረተሰቡ ውስጥ ላላቸው ቦታ ተመሳሳይ አክብሮት አሳይተዋል።

በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን ሕፃናት ብዙ የሚሠሯቸው ነገሮች እንደነበሩ የታወቀ ነው። ወንዶች ልጆች እያደጉ ሲሄዱ አባቶቻቸው በግብርና ወይም ደግሞ እንደ አናጢነት በመሳሰሉ ሙያዎች ተግባራዊ ሥልጠና ይሰጧቸው ነበር። (ዘፍጥረት 37:2፤ 1 ሳሙኤል 16:11) ልጃገረዶች ትልልቆች በሚሆኑበት ጊዜ በጣም የሚጠቅሟቸውን የቤት ውስጥ ሙያዎች ከእናቶቻቸው ይማራሉ። የያዕቆብ ሚስት የሆነችው ራሔል በልጅነቷ እረኛ ነበረች። (ዘፍጥረት 29:6-9) ወጣት ሴቶች መከር በሚሰበሰብበት ወቅት በማሳዎች ላይና በወይን ተክል ቦታዎችም ላይ ይሠሩ ነበር። (ሩት 2:5-9፤ መኃልየ መኃልይ 1:6)a እነዚህን ሥራዎች ያከናውኑ የነበረው ከትምህርት ጎን ለጎን በወላጅ ፍቅራዊ ክትትል ሥር ሆነው ነበር።

ይህ ሁኔታ ሴቶች ከቤት ውስጥ ወይም ከእርሻ ሥራ ውጪ ምንም ነገር መሥራት የማይችሉ ዝቅተኛ ደረጃ የሚሰጣቸው የቤተሰብ አባላት እንደሆኑ አድርጎ የሚያስቆጥራቸው አይደለም። በምሳሌ መጽሐፍ ውስጥ ስለ “ባለሞያ ሚስት [NW]” የተሰጠው መግለጫ አንዲት ያገባች ሴት ቤተሰቧን ማስተዳደር ብቻ ሳይሆን ርስት መግዛትና መለወጥ፣ ምርታማ የእርሻ ቦታ ማዘጋጀትና አነስተኛ ንግድ ማካሄድ እንደምትችል ያሳያል።—ምሳሌ 31:10, 16, 18, 24

በተጨማሪም እስራኤላውያን ሕፃናት ይዝናኑና ይጫወቱ ነበር። ነቢዩ ዘካርያስ ‘የከተማይቱ አደባባዮች በሚጫወቱ ወንዶችና ሴቶች እንደሚሞሉ’ ተናግሯል። (ዘካርያስ 8:5) ኢየሱስ ክርስቶስም በገበያ ሥፍራ ተቀምጠው እንቢልታ የሚነፉና የሚጨፍሩ ልጆችን ጠቅሷል። (ማቴዎስ 11:16, 17) ሕፃናትን በእንዲህ ዓይነት አክብሮት በተሞላበት መንገድ እንዲይዟቸው አስተዋጽኦ ያደረገው ነገር ምንድን ነው?

ከፍ ያሉ መሠረታዊ ሥርዓቶች

እስራኤላውያን የአምላክን ሕግጋት በጠበቁበት ጊዜ ሁሉ በልጆቻቸው ላይ በደል አልፈጸሙም ወይም ጉልበታቸውን አላግባብ አልበዘበዙም። (ዘዳግም 18:10⁠ን ከኤርምያስ 7:31 ጋር አወዳድር።) ወንዶችና ሴቶች ልጆቻቸውን ‘ከእግዚአብሔር እንዳገኟቸው ስጦታዎች’ እና እንደ “በረከት” አድርገው ይመለከቷቸው ነበር። (መዝሙር 127:3-5) አንድ ወላጅ ልጆቹን ‘በማዕዱ ዙሪያ እንዳሉ የወይራ ቡቃያዎች’ አድርጎ ይቆጥራቸው ነበር። የወይራ ዛፎች ደግሞ በግብርና ይተዳደር በነበረው በዚያ ኅብረተሰብ ውስጥ በጣም ውድ ነገሮች ነበሩ! (መዝሙር 128:3-6) የታሪክ ምሁሩ አልፍረድ ኤደርሻይም የጥንቱ ዕብራይስጥ ልጆችን በተመለከተ ወንድ ልጅና ሴት ልጅ ከሚሉት ቃላት በተጨማሪ የተለያዩ የሕይወት ደረጃዎችን የሚያመለክቱ ዘጠኝ ቃላት እንደነበሩት ገልጸዋል። ሐሳባቸውን ሲያጠቃልሉም እንዲህ ብለዋል:- “እያንዳንዱን የእድገት ደረጃ የሚወክል ስያሜ እስከማውጣት ድረስ የልጆቻቸውን ሕይወት በቅርብ የሚከታተሉ መሆናቸው ከልጆቻቸው ጋር ጠንካራ ፍቅራዊ ትስስር እንደነበራቸው የሚያሳይ ነው።”

በክርስትና ዘመን ወላጆች ልጆቻቸውን ከፍ አድርገው እንዲመለከቷቸውና በአክብሮት እንዲይዟቸው ጥብቅ ምክር ተሰጥቷቸዋል። ኢየሱስ ከሌሎች ሰዎች ልጆች ጋር በነበረው ግንኙነት ግሩም ምሳሌ ትቷል። ምድራዊ አገልግሎቱ እየተገባደደ በነበረበት በአንድ ወቅት ሰዎች ልጆቻቸውን ወደ እርሱ ማምጣት ጀመሩ። ደቀ መዛሙርቱ ኢየሱስ ሥራ እንደበዛበት በማሰብ ይመስላል፣ ሰዎቹን ለመከልከል ሞከሩ። ሆኖም ኢየሱስ “ሕፃናትን ወደ እኔ ይመጡ ዘንድ ተዉ አትከልክሉአቸው” ሲል ገሠጻቸው። እንዲያውም ኢየሱስ “አቀፋቸው።” ልጆቹን እንደ ውድ ነገርና በደግነት ሊያዙ እንደሚገባቸው አድርጎ እንደተመለከታቸው ምንም ጥርጥር የለውም።—ማርቆስ 10:14, 16፤ ሉቃስ 18:15-17

ከጊዜ በኋላ ሐዋርያው ጳውሎስ አባቶችን “ልባቸው እንዳይዝል ልጆቻችሁን አታበሳጩአቸው” ብሏቸዋል። (ቆላስይስ 3:21) ከዚህ ትእዛዝ ጋር በሚስማማ መንገድ በዚያን ጊዜ የነበሩትም ሆኑ ዛሬ ያሉት ክርስቲያን ወላጆች ልጆቻቸው አስከፊ በሆኑ ሁኔታዎች ሥር እንዲሠሩ አይፈቅዱም። ሕፃናት በአካል፣ በስሜትና በመንፈሳዊ እንዲያድጉ ፍቅር፣ እንክብካቤና ጥበቃ የሚያገኙበት ሁኔታ መኖር እንዳለበት ይገነዘባሉ። ወላጆች ግልጽ በሆነ መንገድ ለልጆቻቸው እውነተኛ ፍቅር ማሳየት አለባቸው። ይህ ደግሞ ልጆቻቸውን ከሚያመነምኑ አስከፊ የሥራ ሁኔታዎች መጠበቅን ይጨምራል።

በዘመናችን ያሉት እውነታዎች

የምንኖረው በ“ሚያስጨንቅ ዘመን” ውስጥ እንደሆነ የታወቀ ነው። (2 ጢሞቴዎስ 3:1-5) በብዙ አገሮች ባለው አስቸጋሪ የኢኮኖሚ ሁኔታ ሳቢያ ክርስቲያን ቤተሰቦች ሳይቀሩ ልጆቻቸው በሥራው ዓለም እንዲሠማሩ ለማድረግ ይገደዱ ይሆናል። ቀደም ሲል እንደተገለጸው ሕፃናት ጤናማና ትምህርት ሰጪ ሥራ መሥራታቸው ምንም ችግር የለውም። እንዲህ ዓይነቱ ሥራ አንድ ልጅ ሊያገኘው የሚገባው ትምህርት፣ ሚዛናዊ መዝናኛና አስፈላጊ የሆነ ዕረፍት ሳይስተጓጎል አካላዊ፣ አእምሯዊ፣ መንፈሳዊ፣ ሥነ ምግባራዊ ወይም ማኅበራዊ እድገቱ እንዲፋጠን ምቹ ሁኔታ ሊፈጥር ይችላል።

ክርስቲያን ወላጆች ልጆቻቸው አሳቢነት በጎደላቸውና ያሻቸውን ከማድረግ በማይመለሱ ጨካኝ አሠሪዎች ሥር በባርነት እንዲሠሩ ከማድረግ ይልቅ በራሳቸው እንክብካቤና ክትትል ሥር ሆነው እንዲሠሩ ማድረግ እንደሚፈልጉ ምንም ጥርጥር የለውም። እንዲህ ዓይነቶቹ ወላጆች ልጆቻቸው የሚያከናውኑት ማንኛውም ዓይነት ሥራ ለአካላዊ፣ ለጾታዊ ወይም ለስሜታዊ ጥቃት የሚያጋልጣቸው እንዳይሆን ጥንቃቄ ያደርጋሉ። በተጨማሪም ልጆቻቸው ከእነርሱ እንዲርቁ አይፈልጉም። በዚህ መንገድ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተገለጸውን የመንፈሳዊ አስተማሪነት ድርሻቸውን መወጣት ይችላሉ:- “[የአምላክን ቃል] ለልጆችህም አስተምረው፣ በቤትህም ስትቀመጥ፣ በመንገድም ስትሄድ፣ ስትተኛም፣ ስትነሣም ተጫወተው።”—ዘዳግም 6:6, 7

ከዚህም በተጨማሪ አንድ ክርስቲያን ለሌላው ወዳጃዊ ስሜትና ፍቅር ማሳየት እንዲሁም ከአንጀቱ መራራት እንዳለበት ተገልጿል። (1 ጴጥሮስ 3:8) ‘ለሰው ሁሉ መልካም እንዲያደርግ’ ተመክሯል። (ገላትያ 6:10) አንድ ክርስቲያን እንዲህ ዓይነቶቹን አምላካዊ ባህርያት ለሰው ሁሉ ማሳየት የሚገባው ከሆነ ለራሱ ልጆች ደግሞ ይበልጥ ማሳየት እንዳለበት የታወቀ ነው! ክርስቲያኖች “ሰዎች ሊያደርጉላችሁ የምትወዱትን ሁሉ እናንተ ደግሞ እንዲሁ አድርጉላቸው” ከሚለው ወርቃማ ሕግ ጋር በሚስማማ መንገድ የክርስቲያኖችንም ሆነ ክርስቲያን ያልሆኑ ሰዎችን ልጆች ጉልበት አላግባብ አይበዘብዙም። (ማቴዎስ 7:12) በተጨማሪም ክርስቲያኖች ሕግ አክባሪ ዜጎች እንደመሆናቸው መጠን የሚያሠሯቸውን ሰዎች የዕድሜ ገደብ በተመለከተ መንግሥት ያወጣቸውን ሕጎች እንዳይጥሱ ይጠነቀቃሉ።—ሮሜ 13:1

እውነተኛው መፍትሔ

ስለ ወደፊቱ ጊዜ ምን ለማለት ይቻላል? ሕፃናትም ሆኑ ዐዋቂዎች የተሻለ ጊዜ ይጠብቃቸዋል። እውነተኛ ክርስቲያኖች በሕፃናት ላይ ለሚፈጸመው የጉልበት ብዝበዛ ዘላቂው መፍትሔ መጽሐፍ ቅዱስ “መንግሥተ ሰማያት” ብሎ የሚጠራው መጪው የዓለም መንግሥት እንደሆነ አጥብቀው ያምናሉ። (ማቴዎስ 3:2) ፈሪሃ አምላክ ያላቸው ሰዎች “በሰማያት የምትኖር አባታችን ሆይ፣ ስምህ ይቀደስ፤ መንግሥትህ ትምጣ፤ ፈቃድህ በሰማይ እንደ ሆነች እንዲሁ በምድር ትሁን” በማለት ይህ መንግሥት እንዲመጣ ለብዙ መቶ ዘመናት ሲጸልዩ ኖረዋል።—ማቴዎስ 6:9, 10

ይህ መንግሥት ከሚያከናውናቸው ነገሮች አንዱ ሕፃናትን ለጉልበት ብዝበዛ የሚዳርጉ ሁኔታዎችን ማስወገድ ነው። ድህነትን ያስወግዳል። “ምድር ፍሬዋን ሰጠች፤ እግዚአብሔር አምላካችንም ይባርከናል።” (መዝሙር 67:6) የአምላክ መንግሥት ሁሉም ሰው በአምላካዊ ባህርያት ላይ የተመሠረተ ትክክለኛ ትምህርት እንዲያገኝ ያደርጋል። “ፍርድህን በምድር ባደረግህ ጊዜ በዓለም የሚኖሩ ጽድቅን ይማራሉ።”—ኢሳይያስ 26:9

የአምላክ መንግሥት አድልዎ የሚያስፋፉ የኢኮኖሚ ሥርዓቶችን ያስወግዳል። የዚህ መንግሥት ዋነኛ ሕግ “ባልንጀራህን እንደ ነፍስህ ውደድ” የሚለውን ትእዛዝ አቅፎ የያዘው የፍቅር ሕግ በመሆኑ በዚያ ወቅት የዘር፣ የዕድሜ፣ የጾታ ወይም ማኅበራዊ መድልዎ ቦታ አይኖረውም። (ማቴዎስ 22:39) በዚህ ጻድቅ የዓለም መስተዳድር የሕፃናት ጉልበት ብዝበዛ ሙሉ በሙሉ ይወገዳል!

[የግርጌ ማስታወሻ]

a ይህ ሁኔታ ሴቶች ከቤት ውስጥ ወይም ከእርሻ ሥራ ውጪ ምንም ነገር መሥራት የማይችሉ ዝቅተኛ ደረጃ የሚሰጣቸው የቤተሰብ አባላት እንደሆኑ አድርጎ የሚያስቆጥራቸው አይደለም። በምሳሌ መጽሐፍ ውስጥ ስለ “ባለሞያ ሚስት [NW]“ የተሰጠው መግለጫ አንዲት ያገባች ሴት ቤተሰቧን ማስተዳደር ብቻ ሳይሆን ርስት መግዛትና መለወጥ፣ ምርታማ የእርሻ ቦታ ማዘጋጀትና አነስተኛ ንግድ ማካሄድ እንደምትችል ያሳያል።—ምሳሌ 31:10, 16, 18, 24

[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

አንዲት ሴት ታሠራቸው የነበሩትን ሴቶች ልጆች አሰናበተች

ሴሲልያb ለ15 ዓመታት ያህል በአንድ የካሪቢያን ደሴት ላይ የሴተኛ አዳሪዎች ቤት ከፍታ ታሠራ ነበር። ከ12 እስከ 15 የሚሆኑ ልጃገረዶችን በአንድ ጊዜ ገዛች። ከእነዚህ መካከል አብዛኞቹ ዕድሜያቸው ከ18 ዓመት በታች ነበር። ልጆቹ ቤተሰቦቻቸው ለገቡት ዕዳ ያለፈቃዳቸው በመያዣነት የተሰጡ ነበሩ። ሴሲልያ ዕዳውን ከፍላ ልጆቹ ሴተኛ አዳሪ ሆነው እንዲሠሩላት ወሰደቻቸው። የሚያገኙትን ገንዘብ ምግባቸውን ለመግዛትና የጥገና ወጪዎችን ለመሸፈን ትጠቀምበት የነበረ ከመሆኑም በላይ ከላዩ ላይ የተወሰነውን እነሱን ለመግዛት ላወጣችው ወጪ መተኪያ እንዲሆን ታስቀምጠው ነበር። ነፃነታቸውን መልሰው ለማግኘት ዓመታት ወስዶባቸዋል። ልጆቹ ከጠባቂ ጋር ካልሆነ በስተቀር ከቤት መውጣት አይፈቀድላቸውም ነበር።

ሴሲልያ ምንጊዜም ከአእምሮዋ የማይፋቅ አንድ ታሪክ አለ። የአንዲት ሴተኛ አዳሪ ልጅ እናት ልጅዋ “ሠርታ“ በምታገኘው ገንዘብ የሚሸፈን ምግብ በየሳምንቱ እየመጣች ትወስድ ነበር። ልጅቷ አንድ ወንድ ልጅ ታሳድግ ስለነበር ዕዳዋን ምንም ያህል ማቃለል አልቻለችም። በመሆኑም ነፃ የመውጣት ተስፋዋ በጣም የመነመነ ነበር። አንድ ቀን ልጅዋን ለእመቤቷ በአደራ መስጠቷን የሚገልጽ ማስታወሻ ጽፋ የራሷን ሕይወት አጠፋች። ሴሲልያ ልጁን ከራሷ አራት ልጆች ጋር አሳደገችው።

ከሴሲልያ ልጆች አንዷ ከይሖዋ ምሥክሮች ሚስዮናውያን ጋር መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት ጀመረች። ሴሲልያ በጥናቱ ላይ እንድትሳተፍ ሐሳብ ቢቀርብላትም ማንበብና መጻፍ የማትችል ስለነበረች መጀመሪያ ላይ ፈቃደኛ አልሆነችም ነበር። ይሁን እንጂ ቀስ በቀስ ከመጽሐፍ ቅዱስ የሚያደርጉት ውይይት አልፎ አልፎ ወደ ጆሮዋ ጥልቅ ሲል የአምላክን ፍቅርና ትዕግሥት ከመረዳቷም በላይ የአምላክን ይቅር ባይነት በጣም አደነቀች። (ኢሳይያስ 43:25) መጽሐፍ ቅዱስን ራሷ የማጥናት ፍላጎት ስላደረባት ብዙም ሳትቆይ ማንበብና መጻፍ መማር ጀመረች። የመጽሐፍ ቅዱስ እውቀቷ እያደገ ሲሄድ ከአምላክ ከፍ ያሉ የሥነ ምግባር መሥፈርቶች ጋር ተስማምቶ የመኖርን አስፈላጊነት ተረዳች።

አንድ ቀን ልጆቹን መሄድ እንደሚችሉ ስትነግራቸው ጆሯቸውን ማመን አቃታቸው! ሲያደርጉት የቆዩት ነገር ይሖዋን በጣም የሚያሳዝን ድርጊት እንደነበረ ገለጸችላቸው። አንዳቸውም ቢሆኑ እሷ ላይ ያለባቸውን ዕዳ አልከፈሉም። ይሁን እንጂ ሁለቱ ከእሷ ጋር ለመኖር ወሰኑ። ሌላዋ ደግሞ ከጊዜ በኋላ የተጠመቀች ምሥክር ሆነች። ሴሲልያ ሌሎች ሰዎች አምላክን ከማያስከብሩ ልማዶች እንዲላቀቁ በመርዳት የሙሉ ጊዜ የመጽሐፍ ቅዱስ አስተማሪ ሆና ለ11 ዓመታት ስታገለግል ቆይታለች።

[የግርጌ ማስታወሻ]

b ስሟን ቀይረነዋል።

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ