እግር ወይም እጅ ማጣት ለአደጋው የሚያጋልጡ ሁኔታዎችን መቀነስ የምትችልበት መንገድ
አንድ ሰው እግሩን ወይም እጁን እንዲያጣ የሚያደርጉት አብዛኞቹ ሁኔታዎች ሊወገዱ የሚችሉ ናቸው! ፐሪፌራል ቫስኩላር ዲዚዝ (ፒ ቪ ዲ) ያለባቸው ሰዎችም እንኳ ይህን አደጋ መከላከል ይችላሉ። በፊተኛው ርዕስ ላይ እንደተጠቀሰው ብዙውን ጊዜ ለፒ ቪ ዲ መንስኤ የሚሆነው የስኳር በሽታ ነው።a የሚያስደስተው ግን ብዙውን ጊዜ የስኳር በሽታን መቆጣጠር የሚቻል መሆኑ ነው።
ዚ ኢንሳይክለፒዲያ ብሪታኒካ “ኢንሱሊን ታዘዘም አልታዘዘ ጥሩ የአመጋገብ ልማድ ለስኳር በሽታ ሕክምና በጣም ወሳኝ ነው” ይላል። በኒው ዮርክ ሲቲ የሚገኘው የኪንግስ ካውንቲ ሆስፒታል ባልደረባ የሆኑት ዶክተር ማርሴል ባዮል ለንቁ! መጽሔት ዘጋቢ የሚከተለውን ሐሳብ ሰጥተዋል:- “የስኳር በሽተኞች ሁኔታቸውን በሚገባ የሚከታተሉ ከሆነ፣ ለአመጋገባቸው ጥንቃቄ የሚያደርጉ ከሆነና የሚሰጣቸውን የሕክምና መመሪያ ተግባራዊ የሚያደርጉ ከሆነ እግራቸውን ወይም እጃቸውን ሊያጡ የሚችሉበትን አጋጣሚ መቀነስ ይችላሉ።” እንዲያውም ይህን ምክር የሚከተሉ የዓይነት 2 የስኳር በሽተኞች ውሎ አድሮ በሚሰማቸው ህመም ላይ ለውጥ ሊያዩ ይችላሉ።b
የአካል ብቃት እንቅስቃሴ በጣም አስፈላጊ ነው
የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግም ጠቃሚ ነው። የሰውነታችን የግሉኮስ ወይም የስኳር መጠን የተስተካከለ እንዲሆን አስተዋጽኦ ያደርጋል። አንድ ሰው ፒ ቪ ዲ እንደያዘው ከተረጋገጠ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረጉ ጥሩ ጉልበትና ቅልጥፍና እንዲኖረው እንዲሁም ደም ወደተጎዳው የአካል ክፍሉ መፍሰሱን እንዲቀጥል ይረዳዋል። በተጨማሪም የፒ ቪ ዲ ህሙማን በሚራመዱበት ወይም የአካል ብቃት እንቅስቃሴ በሚያደርጉበት ጊዜ አልፎ አልፎ እንዲያነክሱ የሚያደርጋቸውን በባት ጡንቻዎቻቸው ላይ የሚሰማቸውን ህመም ለመቀነስ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረጋቸው ሊረዳቸው ይችላል። ይሁን እንጂ እንዲህ ዓይነቶቹ ሕሙማን በቅልጥሞቻቸው ላይ ውጥረት የሚፈጥሩና እግሮቻቸው ድንገት ከቁጥጥር ውጪ በሆነ መንገድ እንዲወላከፉ የሚያደርጉ የአካል ብቃት እንቅስቃሴዎችን ማስወገድ ይኖርባቸዋል። ይበልጥ ተስማሚ ከሆኑት የአካል ብቃት እንቅስቃሴዎች መካከል በእግር መጓዝ፣ ብስክሌት መንዳት፣ ጀልባ ቀዘፋ፣ ዋና እና የውኃ ላይ አይሮቢክስ ይገኙበታል። አንድ ሰው ለየት ያለ የአመጋገብ ዘዴ ወይም የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ከመጀመሩ በፊት ምንጊዜም ሐኪም ማማከር ይኖርበታል።
ጥሩ ጤንነት እንዲኖረው የሚፈልግ ማንኛውም ሰው ሲጋራ ከማጨስ መታቀብ አለበት። ሲጋራ ማጨስ ከሚያስከትላቸው ወይም ከሚያባብሳቸው በርካታ የጤና ችግሮች አንዱ ፒ ቪ ዲ ነው። “ሲጋራ ማጨስ በተለይ አጫሹ የስኳር በሽታና ፒ ቪ ዲ ካለበት እግሩ ወይም እጁ እንዲቆረጥ ትልቅ ተጽዕኖ ያሳድራል” ሲሉ ዶክተር ባዮል ተናግረዋል። ትልቅ ተጽዕኖ ያሳድራል ሲባል እስከ ምን ድረስ ነው? እግራቸው ወይም እጃቸው የተቆረጠባቸው ሰዎች የተሃድሶ ፕሮግራም መመሪያ “የሚያጨሱ ሰዎች እግራቸው ወይም እጃቸው የመቆረጡ አጋጣሚ ከማያጨሱ ሰዎች በ10 እጥፍ ይበልጣል” ሲል ይገልጻል።
ለታመመ እግር ወይም እጅ እንክብካቤ ማድረግ
ፒ ቪ ዲ ወደ ታችኛዎቹ የእግር ወይም የእጅ ክፍሎች የሚፈስሰውን የደም ዑደት ሊቀንስ ስለሚችል ኒውሮፓቲ ማለትም የነርቮች መሞት ወይም መደንዘዝ ሊያስከትል ይችላል። ከዚያ በኋላ ሰውየው ተኝቶ ባለበት ጊዜም እንኳ ሳይቀር እግሩ ወይም እጁ በቀላሉ ለጉዳት ሊጋለጥ ይችላል። ለምሳሌ ያህል የኤሌክትሪክ ማሞቂያ ያለው ብርድ ልብስ ወይም ማሞቂያ ያለው ፍራሽ ከልክ በላይ ሊሞቅና ግለሰቡ ምንም ዓይነት የሕመም ስሜት ስለማይሰማው በጣም ሊያቃጥለው ይችላል። በመሆኑም የፋብሪካ ባለቤቶች የስኳር በሽተኞች በእነዚህ ምርቶች በሚገለገሉበት ጊዜ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ይመክራሉ።
በተጨማሪም የታመመ እግር ወይም እጅ ለኢንፌክሽን ይበልጥ የተጋለጠ ነው። ሌላው ቀርቶ ትንሽ ጭረት እንኳ አልሰር አልፎ ተርፎም ምውት አባል (gangrene) ሊያስከትል ይችላል። ስለዚህ እግርን መንከባከብ በጣም አስፈላጊ ነው። ይህም ምቹና ልክ የሆኑ ጫማዎች ማድረግን እንዲሁም ቅልጥምና እግር ንጹሕና ደረቅ እንዲሆኑ ማድረግን ይጨምራል። ብዙዎቹ ሆስፒታሎች ሕሙማን እግራቸውን እንዴት መንከባከብ እንደሚችሉ የሚያስተምሩ የእግር ክሊኒኮች አሏቸው።
ፒ ቪ ዲ ተባብሶ ቀዶ ሕክምና አስፈላጊ ወደሚሆንበት ደረጃ በሚደርስበት ጊዜ ቀዶ ሐኪሞች ብዙውን ጊዜ የአካል መቆረጥን ለማስወገድ ይጥራሉ። አንዱ አማራጭ የባሉን አንጂዮፕላስቲ የቀዶ ሕክምና ዘዴን መጠቀም ነው። የደም ቧንቧዎች ቀዶ ሐኪም ጫፉ ላይ ፊኛ ያለው ካቴተር ያስገባል። ፊኛው ይነፋና የጠበበውን ደም ወሳጅ ቧንቧ ያሰፋዋል። ሌላው አማራጭ በበሽታው ክፉኛ የተጠቁ ደም ሥሮችን ከሌላ የአካል ክፍል በተወሰዱ ደም ሥሮች በመተካት የሚከናወነው ባይፓስ ቀዶ ሕክምና ነው።
የ54 ዓመቷ ባርብራ ከአራት ዓመቷ ጀምሮ ከዓይነት 1 የስኳር በሽታ ጋር ስትታገል ኖራለች። የመጀመሪያ ልጅዋን ከወለደች በኋላ እግሮቿ የፒ ቪ ዲ ተጠቂዎች ሆኑ። አንዳንድ ዶክተሮች እግሮቿን እንድታስቆርጣቸው ሐሳብ አቀረቡላት። ይሁን እንጂ ባርብራ ስመ ጥር ከሆነ አንድ የደም ቧንቧ ቀዶ ሐኪም ጋር ተገናኘችና ወደ እግሯ የሚፈስሰውን የደም ዑደት ለማሻሻል የአንጂዮፕላስቲ ቀዶ ሕክምና አደረገላት። ባርብራ ይህ ቀዶ ሕክምና ለተወሰነ ጊዜ የረዳት ቢሆንም ውሎ አድሮ ባይፓስ ቀዶ ሕክምና ማድረግ አስፈልጓት ነበር። ቀዶ ሕክምናውም በተሳካ ሁኔታ ተከናወነ። በአሁኑ ጊዜ ባርብራ ለእግሮቿ ከፍተኛ እንክብካቤ ታደርጋለች።
ከመቁሰል አደጋ ተጠበቅ
ብዙዎች እግራቸውን ወይም እጃቸውን እንዲያጡ መንስኤ ከሚሆኑት ዋና ዋና ነገሮች መካከል በሁለተኛ ደረጃ የሚጠቀሰው የመቁሰል አደጋ ነው። በየትኛውም የአካል ክፍል ላይ ሊደርስ የሚችለው የመቁሰል አደጋ ማንኛውንም የአካል ክፍል ከጥቅም ውጪ ሊያደርግ ይችላል። ይሁን እንጂ አንድ ሰው ለሕይወት አምላካዊ አመለካከት መያዙ ለመቁሰል አደጋ የሚጋለጥበትን አጋጣሚ በመቀነስ ረገድ ትልቅ አስተዋጽኦ ሊያበረክትለት ይችላል። ክርስቲያኖች በሚሠሩበት፣ በሚያሽከረክሩበትም ሆነ በሚዝናኑበት ጊዜ ሰውነታቸውን ከአምላክ እንደተሰጠ ስጦታ አድርገው መያዝ አለባቸው። በመሆኑም ማንኛውንም የጥንቃቄ መሥፈርት ያሟላሉ፤ እንዲሁም ራስን ለአደጋ የሚያጋልጡ የቂልነት ድርጊቶች ከመፈጸም ይታቀባሉ።—ሮሜ 12:1, 2፤ 2 ቆሮንቶስ 7:1
ፈንጂዎች በብዛት በተቀበሩባቸው አካባቢዎች የሚኖሩ ሰዎች ለአደጋ የሚጋለጡበትን አጋጣሚ ለመቀነስ ምን እየተከናወነ ነው? በብዙ አገሮች ውስጥ በመንግሥት የሚደገፉ ስለ ፈንጂዎች ትምህርት የሚሰጥባቸው ፕሮግራሞች አሉ። የተባበሩት መንግሥታት ዋና ጸሐፊ ባቀረቡት አንድ ሪፖርት ላይ እንደተገለጸው እነዚህ ፕሮግራሞች “ለአደጋው የተጋለጡ ሕዝቦችን . . . ፈንጂዎች በተቀበሩባቸው ቦታዎች እየኖሩና እየሠሩ የአደጋው ሰለባዎች ሊሆኑ የሚችሉበትን አጋጣሚ እንዴት መቀነስ እንደሚችሉ” ያስተምሯቸዋል።
የሚያሳዝነው ግን ይላል አንድ የተባበሩት መንግሥታት ሪፖርት፣ “ሰዎች ከፈንጂዎች ጋር ይላመዱና ግዴየለሾች ይሆናሉ።” “አንዳንድ ጊዜ ሃይማኖታዊ አስተሳሰቦች [ሰዎች] ለእንዲህ ዓይነቶቹ አደጋዎች የሚያጋልጡ አደገኛ አመለካከቶች እንዲያዳብሩ ይገፋፏቸዋል።” ይሁን እንጂ ለአደጋዎች የሚያጋልጥ አመለካከት ማዳበር የአምላክ ቃል ድጋፍ የለውም። ከዚህ ይልቅ መጽሐፍ ቅዱስ ጠንቃቃ መሆንንና ራስን ከአደጋ መጠበቅን ያበረታታል።—ዘዳግም 22:8፤ መክብብ 10:9
ስለዚህ ጥንቃቄ በማድረግና ጤንነትህን ለመጠበቅ የሚያስችሉ ምክንያታዊ እርምጃዎች በመውሰድ እግርህን ወይም እጅህን እንድታጣ ሊያደርጉ የሚችሉ ሁኔታዎችን በእጅጉ መቀነስ ትችላለህ። ይሁን እንጂ እግራቸውን ወይም እጃቸውን ስላጡ ሰዎችስ ምን ለማለት ይቻላል? ደስታ የሞላበት ሕይወት ሊመሩ ይችላሉ?
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
a እግርን ጥብቅ አድርጎ የሚይዝ ልብስ መልበስ ወይም ጠባብ ጫማዎች ማድረግ ወይም ደግሞ ለረጅም ሰዓት (በተለይ እግሮችን አጣምሮ) መቀመጥ ወይም መቆም በእግር ላይ የሚያጋጥሙ ከደም ቧንቧዎች ጋር የተያያዙ ችግሮችን ሊቀሰቅሱ ወይም ሊያባብሱ ይችላሉ።
b የዓይነት 1 የስኳር በሽተኞች በየዕለቱ የሚወጉት የኢንሱሊን መርፌ ይታዘዝላቸዋል። የዓይነት 2 የስኳር በሽተኞች (የኢንሱሊን ጥገኛ የማያደርግ የስኳር በሽታ ዓይነት ነው) ብዙውን ጊዜ በአመጋገብና በአካል ብቃት እንቅስቃሴ ህመማቸውን ሊቆጣጠሩ ይችላሉ። በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ከሚገኙት የስኳር በሽተኞች መካከል 95 በመቶ የሚሆኑት የዓይነት 2 የስኳር በሽተኞች ናቸው።
[በገጽ 4 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ሲጋራ ማጨስ በተለይ የደም ቧንቧ በሽታ ያለባቸው ሰዎች እግራቸውን ወይም እጃቸውን ሊያጡ የሚችሉበትን አጋጣሚ በእጅጉ ይጨምራል
[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ተስማሚ የሆነ የአካል ብቃት እንቅስቃሴና ጥሩ የአመጋገብ ልማድ ጤናማ የሆነ የደም ቧንቧ ሥርዓት እንዲኖር ይረዳል