የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • g99 11/8 ገጽ 16-19
  • “ልጃችሁ የስኳር በሽታ ይዟታል!”

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • “ልጃችሁ የስኳር በሽታ ይዟታል!”
  • ንቁ!—1999
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • በሆስፒታል የገጠመን ፈተና
  • ማስተካከያ የሚጠይቅ ወቅት
  • አሁን ያለንበት ሁኔታ ምን ይመስላል?
  • የሕክምናው አስቸጋሪነት
    ንቁ!—2003
  • የስኳር በሽታ—በበሽታው የመያዝ አጋጣሚህን መቀነስ ትችላለህ?
    ንቁ!—2014
  • የስኳር በሽታ—“ድምፅ የለሹ ቀሳፊ”
    ንቁ!—2003
  • መጽሐፍ ቅዱስ የስኳር ሕመምተኞችን ሊረዳ የሚችለው እንዴት ነው?
    ንቁ!—2003
ለተጨማሪ መረጃ
ንቁ!—1999
g99 11/8 ገጽ 16-19

“ልጃችሁ የስኳር በሽታ ይዟታል!”

ሐኪሙ የተናገራቸው እነዚህ ቃላት ያሳደሩት ተጽዕኖ ወዲያውኑ ከአእምሮ የሚፋቅ አልነበረም። ልጄ ሶንያ በወቅቱ የአሥር ዓመት ልጅ ነበረች። ጥሩ ጤናና የተሟላ ጉልበት ያላት ትመስል ነበር። እንዲያውም አንዳንዴ ሕመም የሚባል የሚያውቃት አትመስልም ነበር። ለመጨረሻ ጊዜ ሐኪም ቤት የወሰድናት የአምስት ዓመት ልጅ በነበረችበት ጊዜ ነበር።

ይሁን እንጂ ወደ ሐኪሙ ከመሄዳችን በፊት የነበሩት ቀናት በጣም ከባድ ነበሩ። ሶንያ ጥሩ ጤና አልነበራትም። በጣም ይጠማታል፣ ስትጠጣ ደግሞ ሽንቷ አሁንም አሁንም ይመጣል፤ እንዲያውም አንዳንዴ በየ15 ደቂቃው ወደ መጸዳጃ ቤት ትመላለሳለች። ሌሊት ሌሊት ደግሞ ለሽንት ቢያንስ ሦስት ጊዜ ትነሳለች። መጀመሪያ ላይ የፊኛ ኢንፌክሽን ሊሆን ይችላል፤ ከትንሽ ጊዜ በኋላ ይሻላታል ብዬ አሰብኩ። ሆኖም ከጥቂት ቀናት በኋላ ኢንፌክሽኑ እንዲተዋት ለማድረግ አንቲባዮቲክ መድኃኒቶች መውሰድ ያስፈልጋት ይሆናል የሚል ሐሳብ አደረብኝ።

ወደ ሐኪም ዘንድ የወሰድኳት ከዚህ በኋላ ነበር። እኔ ገምቼው የነበረውን ነገርኩት። ሐኪሙ የሽንት ምርመራ እንድታደርግ አዘዘ። ሽንቱን ስመለከተው አመዳይ በሚመስሉ ነገሮች የተሞላ ነበር። ነርሷም ተመልክታው ነበር። ጥርጣሬያቸው በአንድ ቀላል የደም ምርመራ ተረጋገጠ። ሶንያ ዓይነት 1 የስኳር በሽታ ይዟታል።

ሶንያ ይህ ምን ማለት እንደሆነ ታውቅ ነበር። ገና የአሥር ዓመት ልጅ የነበረች ቢሆንም ትምህርት ቤት ስለ ስኳር በሽታ ተምራ ነበር። ፊቷ ላይ ይነበብ የነበረው ፍርሃትና ድንጋጤ ከእኔ የሚተናነስ አልነበረም። ሐኪሙ ተጨማሪ ችግር እንዳይከሰት ለማድረግ በፍጥነት ወደ ሆስፒታል መሄድ እንዳለብን ነገረን። በፖርትላንድ፣ ኦሪገን፣ ዩ ኤስ ኤ ውስጥ በሚገኝ አንድ ሆስፒታል ድንገተኛ ክፍል ውስጥ ገብታ እንድትታከም ሁኔታዎችን አመቻቸልን። ሶንያ ይህ ሁኔታ በእሷ ላይ በመድረሱ በጣም ተበሳጨች። በሕይወት መቀጠል ስላልፈለገች መርፌ ለመወጋት ሁሉ አሻፈረኝ ብላ ነበር። ለምን እያለች በተደጋጋሚ በመጠየቅ ታለቅስ ነበር። የተሰማኝን ጥልቅ ሐዘን ለመቆጣጠር ከራሴ ጋር ከባድ ትግል ገጠምኩ። መጨረሻ ግን ከአቅሜ በላይ ሆነ። ስለዚህ መቆያ ክፍል ውስጥ ተቀምጠን አንዳችን ሌላውን ተደግፈን ይሖዋ መከራችንን አይቶ እንዲረዳን እየተማጸንን ማንባት ጀመርን።

በሆስፒታል የገጠመን ፈተና

ሐኪሙ አንዳንድ ነገሮችን ለመያዝ፣ ለባለቤቴ ለፊል ስልክ ለመደወልና ወንዱን ልጃችንን ኦስቲንን ከትምህርት ቤት የሚያመጣልን ሰው ለመፈለግ እንድችል ሶንያን ቤት ይዣት እንድሄድ ፈቀደልኝ። ባለቤቴና እኔ በአንድ ሰዓት ጊዜ ውስጥ ሶንያን ሆስፒታል አደረስናት። ወዲያውኑ ሐኪሞቹ በደሟ ውስጥ ያለውን ከልክ ያለፈ ስኳርና ኬቶን የሚያስወግድ ፈሳሽ በደም ሥሯ ሰጧት።a ይህን ማድረጉ በጣም አስቸጋሪ ሆኖ ነበር። ሶንያ ከሰውነቷ ብዙ ፈሳሽ ወጥቶ ስለነበር ከሦስት ኪሎ ግራም በላይ ቀንሳ ነበር። የተሰወሩትን የደም ሥሮቿን ማግኘት አስቸጋሪ ሆኖ ነበር። በመጨረሻ ነርሷ ተሳካላትና ለጊዜው ሁኔታው ረገብ አለ። ሶንያን ወደ ቤት ከመውሰዳችን በፊት ልናነባቸውና ልንረዳቸው ስለሚገቡ ነገሮች የሚገልጽ አንድ ትልቅ መጽሐፍና ሌሎች ሰነዶች ተሰጡን።

ከብዙ ሐኪሞች፣ ነርሶችና የአመጋገብ ሥርዓት ባለሙያዎች ጋር ተገናኘን። ከዚያ ጊዜ አንስቶ ሶንያ በቀን ሁለት ጊዜ መወጋት ያለባትን የኢንሱሊን መርፌ እንዴት ልንወጋት እንደምንችል አሳዩን። ሶንያ በደሟ ውስጥ ያለውን ስኳር መጠን መከታተል እንድትችል በቀን አራት ጊዜ ልታደርገው የሚገባውን የደም ምርመራ እንዴት ማከናወን እንደሚቻል ተማርን። ብዙ መረጃዎች መሰብሰብ ነበረብን! እንዴት ልንመግባት እንደሚገባም ተነገረን። ከሰውነቷ እድገት ጋር የሚመጣጠን ምግብ መመገብ ያለባት ከመሆኑ በተጨማሪ ከፍተኛ የስኳር መጠን ያላቸውን ምግቦች ማስወገድና በእያንዳንዱ የምግብ ሰዓት ትክክለኛውን የካርቦሃይድሬት መጠን መውሰድ ያስፈልጋት ነበር።

ከሦስት ቀን በኋላ ከሆስፒታል ወጣች። እኔ መርፌውን ስወጋት እርሷ ደግሞ የደም ምርመራውን ታደርግ ነበር። በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ የኢንሱሊን መርፌውን ራሷ መውጋት ጀመረች። ከዚያን ጊዜ አንስቶ ራሷን የምትወጋው ራሷ ነች። ውሎ አድሮ በሽታውን አምና በመቀበል እንዴት ተቋቁማ መኖር እንደምትችል መማሯን ማየቱ የሚያስደንቅ ነበር። መሞትንና በገነት ውስጥ ዳግመኛ ሕያው መሆንን መርጣ እንዳልነበር ሁሉ አሁን አመለካከቷ ተለውጦ አካላዊ ምልክቶቿን፣ ስሜቶቿንና ገደቦቿን ከመገንዘቧም በላይ የሚያስፈልጋት ነገር ሲኖር ስሜቷን አውጥታ መግለጽ ችላለች።

ማስተካከያ የሚጠይቅ ወቅት

የመጀመሪያዎቹ ጥቂት ወራት በጣም ከባድ ነበሩ። እያንዳንዱ የቤተሰቡ አባል የተለያዩ ስሜቶችን መቋቋም ነበረበት። ውጥረት በዝቶብኝ ስለነበር ሁሉን ትተሽ ጥፊ ጥፊ የሚል ስሜት አድሮብኝ ነበር። ውልፍት የማያደርገው ፕሮግራም በተለይ ከክርስቲያናዊ ስብሰባዎችና ከስብከት ሥራችን ጋር በሚጋጭበት ጊዜ ችግር ይፈጠር ነበር። ይበልጥ አስቸጋሪ ሆኖብን የነበረው ደግሞ ዕለታዊው የትምህርት ሰዓትና የዕረፍት ጊዜያት ነበሩ። ሆኖም ባለቤቴና እኔ አዘውትረን በመጸለይ ለነገ መጨነቃችንን ትተን አዳዲስ ኃላፊነቶቻችንን መቀበል ጀመርን።

በኢ-ሜይል ሳይቀር ከእኛ ጋር በመገናኘት ምንጊዜም የሚያስጨንቀን ነገር ሲኖር የሚረዳን የኢንዶክሪኖሎጂ ስፔሽያሊስት የሆነ አንድ ጥሩ ሐኪም አገኘን። አዘውትረን ወደ ቢሮው በመሄድ እናነጋግረዋለን። ምርመራ ለማድረግ በየሦስት ወሩ ወደ ሐኪሙ መሄዳችን የሶንያን ጤና ለመከታተል ብቻ ሳይሆን ልናደርግላት የምንችለውን ሁሉ እያደረግንላት እንዳለን እንዲሰማንም ረድቶናል።

መገመት እንደሚቻለው ወንዱ ልጃችን ትኩረታችን ሁሉ እህቱ ላይ እንዳረፈ ሲያይ በጣም ተሰማው። በጉባኤ ያሉ ወንድሞችና እህቶች እንዲሁም የትምህርት ቤት አስተማሪው ይህን በመገንዘብ ራሱን በተለያዩ ነገሮች እንዲያስጠምድና ማስተካከያዎች ማድረግ እንደሚያስፈልገው እንዲያስተውል ረዱት። አሁን የሶንያን ሁኔታ በንቃት በመከታተል ትልቅ እርዳታ እያበረከተ ነው። ወላጆቿ እንደመሆናችን መጠን አንዳንድ ጊዜ ለደህንነቷ ከልክ በላይ የምንጨነቅ ከመሆኑም በላይ ከመጠን ያለፈ ስጋት ያድርብናል። እነዚህን ስጋቶች ለማስወገድ ከሁሉ የተሻለ ዘዴ ሆኖ ያገኘነው በሽታው በእርግጥ በሰውነት ላይ ምን ሊያስከትል እንደሚችል ለማወቅ ምርምር ማድረግ ነው።

አሁን ያለንበት ሁኔታ ምን ይመስላል?

ይሖዋ ስለሰጣቸው ተስፋዎችና በሽታ የተረሳ ስለሚሆንበት መጪ ጊዜ በተደጋጋሚ እያነሳን እናወራለን። (ኢሳይያስ 33:24) እስከዚያው ጊዜ ድረስ የአምላክ መንግሥት ስለሚያመጣቸው በረከቶች ለሌሎች በመናገሩ ሥራ የቻልነውን ያህል በመካፈል በቤተሰብ ደረጃ በይሖዋ አገልግሎት ንቁዎች ሆነን ለመቀጠል ቁርጥ ውሳኔ አድርገናል። በተጨማሪም በጉባኤ ስብሰባዎች አዘውትረን ለመገኘት የተቻለንን ሁሉ ጥረት እናደርጋለን።

ከጥቂት ዓመታት በፊት ባለቤቴ ጊዜያዊ የሥራ ምድብ ተሰጥቶት እስራኤል ውስጥ እንዲሠራ ጥያቄ ቀረበለት። የሶንያን የሕክምና ሁኔታ ግምት ውስጥ በማስገባት ጉዳዩን በጥሞናና በጸሎት አሰብንበት። ለሶንያ የሚሆን ተስማሚ ምግብ ማግኘትን ጨምሮ ጥሩ ዝግጅት ካደረግን ይህ ጉዞ መንፈሳዊ በረከቶችም ሊያስገኝልን እንደሚችል ተሰማን። ለአንድ ዓመት ተኩል ያህል የቴል አቪቭ እንግሊዝኛ ጉባኤ አባል የመሆን መብት አግኝተናል። ፈጽሞ የተለየ በሆነው የስብከት ዘዴ መካፈል የቻልን ሲሆን ይህ ቤተሰባችን ጥሩ ትምህርት መቅሰም የቻለበት አጋጣሚ ነበር።

“ልጃችሁ የስኳር በሽታ ይዟታል!” የሚሉት ጥቂት ቃላት ሕይወታችንን በእጅጉ ለውጠውታል። ሆኖም በተስፋ መቁረጥ ስሜት ከመዋጥ ይልቅ የልጃችንን አካላዊ ደህንነት የመጠበቁን ኃላፊነት የቤተሰባችን ፕሮጄክት አድርገነዋል። ይህ ደግሞ ይበልጥ አቀራርቦናል። “የመጽናናትም ሁሉ አምላክ” የሆነው ይሖዋ ይህን አስቸጋሪ ሁኔታ መቋቋም እንድንችል ረድቶናል። (2 ቆሮንቶስ 1:3)—ሲንዲ ኸርድ እንደተናገረችው።

[የግርጌ ማስታወሻ]

a “ሕክምና ያልተደረገለት የስኳር በሽታ ስብ በደም ውስጥ በሚፈረካከስበት ጊዜ የሚከሰቱት ኬቶኖች እንዲከማቹ በማድረግ ደምኬቶናዊነት (ketosis) ያስከትላል፤ ይህ ደግሞ አሲዶሲስ (በደም ውስጥ የሚፈጠር የአሲድ ክምችት) እንዲሁም የማቅለሽለሽና የማስመለስ ችግር ያስከትላል። የካርቦሃይድሬትና የስብ የተዛባ ገንባፍራሽ ቅንባሮ (metabolism) መርዘኛ ውጤቶች መከማቸታቸውን ሲቀጥሉ ሕመምተኛው በስኳር በሽታ ሳቢያ በሚከሰት ኮማ ውስጥ ይገባል።”—ኢንሳይክለፒድያ ብሪታኒካ

[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

የስኳር በሽታ ምንድን ነው?

ሰውነታችን የምንበላውን ምግብ ልንጠቀምበት እንችል ዘንድ ወደ ጉልበት ይለውጠዋል። ይህ ተግባር የመተንፈስን ያህል እጅግ አስፈላጊ ነው። ምግብ በጨጓራና በአንጀት ውስጥ ይፈጭና የስኳር ዓይነት ወደሆነው ወደ ግሉኮስና ወደ ሌሎች ይበልጥ መሠረታዊ ወደሆኑ ንጥረ ነገሮች ይለወጣል። ጣፊያ ስኳሩ ወደ ሰውነት ሕዋሳት መግባት እንዲችሉ የሚረዳ ኢንሱሊን ያመነጫል። በዚህ ጊዜ ስኳሩ ተቃጥሎ ጉልበት ሊሰጥ ይችላል።

አንድ ሰው የስኳር በሽታ ከያዘው አንድም ጣፊያው በቂ ኢንሱሊን አያመነጭም አለዚያም ደግሞ ሰውነቱ ኢንሱሊኑን በአግባቡ መጠቀም ተስኖታል ማለት ነው። በዚህም የተነሳ በደም ውስጥ ያለው ስኳር ወደ ሰውነት ሕዋሳት ውስጥ ገብቶ ጥቅም ላይ መዋል አይችልም። አንደርስታንዲንግ ኢንሱሊን ዲፔንደንት ዳያቢትስ የተባለው መጽሐፍ “በዚህ ጊዜ በደም ውስጥ ያለው የስኳር መጠን በከፍተኛ ሁኔታ ይጨምርና በኩላሊት በኩል አልፎ ከሽንት ጋር ይቀላቀላል” ሲል ይገልጻል። ሕክምና ያልወሰዱ የስኳር በሽተኞች ሽንታቸው ቶሎ ቶሎ ሊመጣና ሌሎችም ምልክቶች ሊታዩባቸው ይችላሉ።

[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

ዓይነት 1 የስኳር በሽታ

ይሄኛው ዓይነት የስኳር በሽታ አብዛኛውን ጊዜ የሚይዘው ልጆችንና ወጣቶችን በመሆኑ ቀደም ባሉት ጊዜያት የልጆች የስኳር በሽታ በመባል ይታወቅ ነበር። ሆኖም በየትኛውም የዕድሜ ክልል ውስጥ ያሉ ሰዎችን ሊያጠቃ ይችላል። የስኳር በሽታ መንስኤ ባይታወቅም እንኳ ከዓይነት 1 የስኳር በሽታ ጋር ዝምድና አላቸው ብለው አንዳንዶች የሚጠቅሷቸው የተለያዩ ነገሮች አሉ:-

1. የዘር ውርስ (ጀነቲክ)

2. አውቶኢሚውኒቲ (ሰውነት ከራሱ ህብረሕዋሳት ወይም የሕዋሳት ዓይነቶች መካከል ለአንዱ አለርጂክ ይሆናል፤ በዚህ ወቅት አለርጂክ የሚሆነው ለጣፊያ ነው)

3. አካባቢያዊ (ቫይረስ ወይም ኬሚካል)

በቫይረስ የሚመጡ ኢንፌክሽኖችና ሌሎች ምክንያቶች ላንገርሀንስ ደሴት በሚባሉት ሕዋሳት (ኢንሱሊን የሚዘጋጅባቸው በጣፊያ ውስጥ የሚገኙ የሕዋሳት ስብስቦች) ላይ ጉዳት ሊያደርሱ ይችላሉ። እነዚህ ሕዋሳት እያለቁ ሲሄዱ ግለሰቡ በስኳር በሽታ የመያዙ አጋጣሚ ይጨምራል።

የስኳር በሽተኞች በርከት ያሉ ምልክቶች ይታዩባቸዋል:-

1. ቶሎ ቶሎ መሽናት

2. ከወትሮው በተለየ ሁኔታ መጠማት

3. ቶሎ ቶሎ መራብ፤ ሰውነት በቂ ጉልበት ስለማያገኝ ይራባል

4. የሰውነት ክብደት መቀነስ። ሰውነት ወደ ሕዋሳቱ ስኳር በማይገባበት ጊዜ ጉልበት ለማግኘት ሲል የራሱን ስብና ፕሮቲን ያቃጥላል፤ ይህ ደግሞ የሰውነት ክብደት እንዲቀንስ ያደርጋል

5. በትንሽ በትልቁ መበሳጨት። የስኳር በሽተኛው ሌሊት ሽንቱ በተደጋጋሚ የሚቀሰቅሰው ከሆነ ጥሩ እንቅልፍ ሳያገኝ ይቀራል። ይህ ደግሞ የባሕርይ ለውጥ ሊያስከትል ይችላል

በዓይነት 1 የስኳር በሽታ የተያዘ ሰው ጣፊያው የሚያመነጨው ኢንሱሊን በጣም አነስተኛ ይሆናል፤ ወይም ደግሞ ምንም ኢንሱሊን ላያመነጭ ይችላል። እንዲህ ዓይነት ሁኔታ በሚኖርበት ጊዜ በአብዛኛው በመርፌ አማካኝነት በየቀኑ ኢንሱሊን መወሰድ ይኖርበታል። (በአፍ የሚወሰድ ኢንሱሊን ጨጓራ ውስጥ ሲገባ ጥቅም ላይ ሳይውል ይጠፋል።)

[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

ዓይነት 2 የስኳር በሽታ

ይህ ዓይነቱ በሽታ ሰውነታችን ኢንሱሊን በበቂ ሁኔታ ባለማመንጨቱ ወይም ኢንሱሊኑን በሚገባ መጠቀም ባለመቻሉ የሚከሰት ችግር በመሆኑ ከዓይነት 1 የስኳር በሽታ ጋር ሊምታታብን አይገባም። ከ40 ዓመት በላይ በሆኑ ዐዋቂዎች በአብዛኛው የሚከሰተው ይህ ዓይነቱ የስኳር በሽታ ሲሆን ቀስ በቀስ እየጠነከረና እያየለ የመሄድ ባሕርይ አለው። የዘር ውርስ ለዚህ ሕመም አስተዋጽኦ የሚያደርግ ከመሆኑም በላይ ብዙውን ጊዜ የተዛባ የአመጋገብ ሥርዓት ወይም ከልክ ያለፈ የሰውነት ክብደት ሕመሙን ያባብሰዋል። ብዙውን ጊዜ ጣፊያ ተጨማሪ ኢንሱሊን እንዲያመነጭ ለማነቃቃት ቢያንስ ቢያንስ መጀመሪያ ላይ ኪኒኖች መውሰድ ሊያስፈልግ ይችላል። ኪኒኖቹ ኢንሱሊን አይደሉም።

[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

በስኳር በሽታ ሳቢያ ሊከሰቱ የሚችሉ ጠንቆች

ሰውነት ሥራውን ማከናወኑን መቀጠል እንዲችል ነዳጅ ያስፈልገዋል። ግሉኮስን መጠቀም ሳይችል ሲቀር የሰውነትን ስብና ፕሮቲን መጠቀም ይጀምራል። ሆኖም ሰውነታችን ስቡን ማቃጠል ሲጀምር ኬቶን የሚባሉ ቆሻሻዎች ይፈጠራሉ። ኬቶኖች ደም ውስጥ ይከማቹና ሽንት ውስጥ ይገባሉ። እነዚህ ኬቶኖች ከጤናማ የሰውነት ህብረሕዋሳት ይበልጥ የአሲድነት ባሕርይ ስላላቸው በደም ውስጥ ከፍተኛ የኬቶን መጠን ሲኖር ኬቶአሲዶሲስ የተባለ ከባድ ጠንቅ ሊከተል ይችላል።

በተጨማሪም የስኳር በሽታ ያለበት ሰው በደሙ ውስጥ ያለው ስኳር ከትክክለኛው መጠን በጣም በሚያንስበት ጊዜ (ሃይፖግላይሲሚያ የሚባል) ችግር ሊፈጠር ይችላል። በሽተኛው የሚታዩበት ጥሩ ያልሆኑ ምልክቶች ይህ ችግር እንዳለበት ሊጠቁሙት ይችላሉ። ሊንቀጠቀጥ፣ ሊያልበው፣ ሊደክመው፣ ሊርበው፣ በቀላሉ ሊበሳጭ፣ ወይም ግራ የመጋባት ስሜት ሊሰማው ወይም ልቡ በኃይል ሊመታ፣ አጥርቶ ለማየት ሊቸገር፣ ራስ ምታት ሊይዘው፣ ሊደነዝዘው ወይም አፉና ከንፈሩ አካባቢ ውርር የሚያደርግ ስሜት ሊሰማው ይችላል። አልፎ ተርፎም ሊጥለው ወይም ራሱን ሊስት ይችላል። ብዙውን ጊዜ ጥሩ የአመጋገብ ልማድ ማዳበርና ዘወትር በተገቢው ሰዓት መመገብ እንዲህ ዓይነቶቹን ችግሮች ለመከላከል ሊረዳ ይችላል።

ከላይ የተዘረዘሩት ምልክቶች ከተከሰቱ የፍራፍሬ ጭማቂ በመጠጣት ወይም የግሉኮስ እንክብሎች በመዋጥ ስኳር መውሰድ በሽተኛው ሌላ ምግብ እስኪመገብ ድረስ በደሙ ውስጥ ያለው የስኳር መጠን አስተማማኝ ደረጃ ላይ እንዲደርስ ሊረዳው ይችላል። ሁኔታው ከባድ በሚሆንበት ጊዜ ግሉካጎን የተባለ መድኃኒት በመርፌ መውሰድ ይገባል። ግሉካጎን በደም ውስጥ ያለው የስኳር መጠን ከፍ እንዲል በጉበት ውስጥ የተከማቸው ስኳር እንዲሠራጭ የሚያደርግ ሆርሞን ነው። የስኳር በሽተኛ የሆነ ልጅ ያለው ወላጅ የልጁን ሁኔታ ለሚማርበት ትምህርት ቤትና የትምህርት ቤቱን አውቶብስ ለሚያሽከረክረው ሹፌር ወይም ልጁ ለሚውልበት መዋዕለ ሕፃናት መንገር ይኖርበታል።

[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

ለረጅም ጊዜ የሚዘልቁ ሌሎች የጤና እክሎች

የስኳር በሽታ ያለበት ሰው ልብ ድካምን፣ በአንጎል ውስጥ የሚከሰት የደም መፍሰስ ችግርን፣ የዓይን ችግርን፣ የኩላሊት በሽታን፣ የእግር ሕመምንና በተደጋጋሚ ጊዜያት በኢንፌክሽን በሽታዎች መያዝን ጨምሮ ለረጅም ጊዜ የሚዘልቁ የጤና እክሎች ሊገጥሙት ይችላሉ። እነዚህ የጤና እክሎች በደም ሥሮች ላይ በሚደርስ ጉዳት፣ በነርቮች ላይ በሚደርስ ጉዳትና ኢንፌክሽኖችን የመከላከል አቅም በማጣት የሚከሰቱ ናቸው። ይሁን እንጂ ሁሉም የስኳር በሽተኞች እነዚህ ለረጅም ጊዜ የሚዘልቁ የጤና እክሎች ይገጥሟቸዋል ማለት አይደለም።

በደም ውስጥ ያለው የስኳር መጠን ምንጊዜም ከትክክለኛው መጠን ጋር የተቀራረበ እንዲሆን ማድረግ እነዚህ የጤና እክሎች የሚያስከትሏቸውን ጠንቆች ለማዘግየት ወይም ለመቀነስ ሊረዳ ይችላል። ከዚህም በተጨማሪ የሰውነት ክብደትንና የደም ግፊትን መቆጣጠርና ሲጋራ ከማጨስ መታቀብ ለአደጋ የሚያጋልጡ ሁኔታዎችን ለመቀነስ የሚያስችሉ ውጤታማ ዘዴዎች ሊሆኑ ይችላሉ። የስኳር በሽተኛው ብዙ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ፣ ጥሩ የአመጋገብ ሥርዓት መከተልና የታዘዘለትን መድኃኒት መውሰድ አለበት።

[በገጽ 19 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የኸርድ ቤተሰብ

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ