እግርን ወይም እጅን አጥቶም ደስተኛ ሕይወት መምራት
“ተራራ ወጪው በድጋሚ ተራራው ጫፍ ላይ ለመውጣት በቃ።” አንድ ጋዜጣ ይህን የገለጸው ቶም ዊቲከር የኤቨረስት ተራራ ጫፍ ላይ በደረሰበት ጊዜ ነበር። ቀደም ሲል ብዙዎች ይህን ሰማይ ጠቀስ ተራራ መውጣት የቻሉ ቢሆንም እንኳ እግሩ የተቆረጠ ሰው ወደዚህ ተራራ ጫፍ ላይ ሲወጣ ቶም ዊቲከር የመጀመሪያው ሰው ነበር! ዊቲከር እግሩን ያጣው በትራፊክ አደጋ ነው። ሆኖም የተገጠመለት ሰው ሠራሽ እግር ስፖርቱን እንደገና እንዲጀምር አስችሎታል። እግራቸውን ወይም እጃቸውን ያጡ በሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች ተመሳሳይ መሣሪያዎች ተገጥመውላቸው ደስተኛ ሕይወት መምራት ችለዋል። እንዲያውም አሁን አሁን እግራቸውን ወይም እጃቸውን ያጡ ሰዎች በከፍተኛ ፍጥነት ሲሮጡ፣ ቅርጫት ኳስ ሲጫወቱ ወይም ደግሞ ብስክሌት ሲነዱ ማየት ያልተለመደ ነገር አይደለም።
ቀደም ሲል የነበሩት ሰው ሠራሽ እግሮችና እጆች ተራ ከሆኑ የእንጨት ችካሎችና የብረት ሜንጦዎች የተሠሩ ነበሩ። ሆኖም በጦርነቶች ሳቢያ በሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች የአካል ጉዳተኞች እየሆኑ በመምጣታቸው ማሻሻያዎች ተደረጉ። ትክክለኛ ሰው ሠራሽ እግሮችንና እጆችን ለመጀመሪያ ጊዜ ያስተዋወቀው በ16ኛው መቶ ዘመን ይኖር የነበረው አምብሮዊዝ ፓሬ የተባለ ፈረንሳዊ የጦር ሠራዊት ቀዶ ሐኪም መሆኑ ምንም አያስደንቅም። የዛሬዎቹ ሰው ሠራሽ እግሮችና እጆች ሃይድሮሊክስ፣ የረቀቁ የጉልበት አንጓዎች፣ እንደ ልብ የሚተጣጠፉ ከካርቦን ድር የተሠሩ እግሮች፣ ሲሊከን፣ ፕላስቲኮችና ብዙ ሰዎች ከዚህ ቀደም ሊሆን ይችላል ተብሎ ከተገመተው በላይ ተፈጥሯዊና ምቹ በሆነ መንገድ መራመድና መንቀሳቀስ እንዲችሉ የሚረዱ ሌሎች የረቀቁ የዘመናዊ ቴክኖሎጂ ውጤቶች ያሏቸው ናቸው። በማይክሮኤሌክትሮኒክስ መስክ የተደረገው መሻሻል ሰው ሠራሽ ክንዶችና እጆች ይበልጥ ተፈጥሯዊ በሆነ መንገድ እንዲንቀሳቀሱ አስተዋጽኦ አድርጓል። ሰው ሠራሽ እግሮችና እጆች ቅርጻቸውና መልካቸውም ተሻሽሏል። ዘመናዊ የሆኑ ሰው ሠራሽ እግሮችና እጆች ጣቶች ያሏቸው ከመሆኑም በላይ አንዳንዶቹ የደም ሥሮች ያሏቸው ይመስላሉ። እንዲያውም በካንሰር በሽታ ሳቢያ እግሯን ያጣች አንዲት ሞዴል የተገጠመላት ሰው ሠራሽ እግር እጅግ ተፈጥሯዊ የሚመስል በመሆኑ የሞዴልነት ሥራዋን መቀጠል ችላለች።
አመለካከት ወሳኝ ነው
ሆኖም የአእምሮ ሕክምና ባለሙያ የሆኑት ኤለን ዊንቸል የሚከተለውን ማስጠንቀቂያ ሰጥተዋል:- “የእግር ወይም የእጅ መቆረጥን የመሰለ ከባድ ችግር ሲገጥምህ አካላዊ፣ ስሜታዊ፣ አእምሯዊና መንፈሳዊ ሕልውናህ በሙሉ በእጅጉ ይፈተናል።” ጉዳት ከደረሰበት በኋላ በምውት አካል ሳቢያ እግሩን ያጣውን ዊልያምን ተመልከት። “በሕይወት ውስጥ የሚገጥመንን ማንኛውንም ፈተና መቋቋም እንድንችል ከሚረዱን ቁልፍ ነገሮች አንዱ አመለካከታችን ነው። ያለብኝን አካላዊ ጉድለት እንደ እንቅፋት የተመለከትኩበት ጊዜ የለም። ከዚህ ይልቅ አደጋው ከደረሰብኝ ጊዜ ጀምሮ ለገጠሙኝ መሰናክሎች በሙሉ አዎንታዊ አመለካከት ነበረኝ” ሲል ገልጿል። ኤለን ዊንቸል ራሳቸው የአካል ክፍላቸው የተቆረጠ ሲሆን ከዚህ አባባል ጋር በመስማማት እግራቸውን ወይም እጃቸውን ያጡ አዎንታዊ አመለካከት ያላቸው ሰዎች አፍራሽ አመለካከት ካላቸው ሰዎች በተሻለ መንገድ ራሳቸውን ከሁኔታው ጋር ማጣጣም ይችላሉ ሲሉ ተናግረዋል። መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚለው “ደስ ያላት ልብ መልካም መድኃኒት ናት።”—ምሳሌ 17:22
የንቁ! መጽሔት ዘጋቢ እግራቸውን ወይም እጃቸውን አጥተው ከሁኔታው ጋር ራሳቸውን በሚገባ ያላመዱ በርከት ያሉ ክርስቲያኖችን አነጋግሮ ነበር። አብዛኞቹ የሰጡት ሐሳብ እግራቸው ወይም እጃቸው የተቆረጠ ሰዎች ስለ አካላዊ ጉድለታቸው ማውራት የሚያሳፍራቸው ወይም ከልክ በላይ የሚጨነቁ መሆን እንደሌለባቸው ይጠቁማሉ። “ይህ ሁኔታ ፈጽሞ መነሳት እንደሌለበት አድርገው የሚያስቡ ሰዎች ይበልጥ ያስጨንቁኛል” ሲል ከጉልበቱ በታች ያለውን እግሩን ያጣው ዴል ተናግሯል። “እንደ እኔ እንደ እኔ እንዲህ ዓይነቱ ሁኔታ ሁሉንም ሰው የሚረብሽ ይመስለኛል።” ቀኝ እጅህን ያጣህ ከሆንክ ከሰው ጋር በምትተዋወቅበት ጊዜ ግራ እጅህን ዘርግተህ ለመጨበጥ ቀዳሚ መሆን እንዳለብህ አንዳንድ ጠበብት ይመክራሉ። በተጨማሪም አንድ ሰው ስለ ሰው ሠራሽ እግርህ ወይም እጅህ ቢጠይቅህ ንገረው። ለማውራት አለማፈርህ ጠያቂው ዘና እንዲል ይረዳዋል። አብዛኛውን ጊዜ ውይይቱ ብዙም ሳይቆይ ወደ ሌላ ርዕስ ይቀየራል።
“ለመሳቅም ጊዜ አለው።” (መክብብ 3:4) እጅዋን ያጣች አንዲት ሴት እንዲህ ብላለች:- ‘ከሁሉም በላይ ተጫዋች ለመሆን መጣር አለብህ! ሌሎች ሰዎች ለእኛ የሚኖራቸው አመለካከት እኛ ስለ ራሳችን ባለን አመለካከት ላይ በእጅጉ የተመካ እንደሆነ ማስታወስ ይኖርብናል።’
“ለማልቀስ ጊዜ አለው”
ዴል እግሩን ካጣ በኋላ መጀመሪያ ላይ “ከዚህ በኋላ ምንም ዋጋ የለኝም። ሕይወቴ አክትሞለታል” የሚል ስሜት አድሮበት ነበር። ፍሎሪንዱ እና ፍሎርያኑ አንጎላ ውስጥ በተቀበሩ ፈንጂዎች እግራቸውን አጥተዋል። ፍሎሪንዱ ሦስት ቀን ሙሉ እንዳለቀሰ ተናግሯል። ፍሎርያኑም እንደዚሁ ከራሱ ስሜት ጋር ሙግት ገጥሞ ነበር። “ዕድሜዬ ገና 25 ዓመት ነበር” ሲል ጽፏል። “በአንድ ወቅት ማንኛውንም ነገር ማድረግ እችል የነበርኩ ሰው በአንድ ጀንበር መቆም እንኳ ተሳነኝ። በጣም ከመጨነቄም በላይ ተስፋ ቆርጬ ነበር።”
“ለማልቀስ ጊዜ አለው።” (መክብብ 3:4) አንድ ትልቅ ነገር ስታጣ ሐዘን ላይ መውደቅህ አይቀርም። (ከመሳፍንት 11:37 እና ከመክብብ 7:1-3 ጋር አወዳድር።) ኤለን ዊንቸል “አንድ ሰው ከሐዘን ስሜቱ እንዲላቀቅ በሐዘን ስሜት ውስጥ ማለፍ መቻል አለበት” ሲሉ ጽፈዋል። ብዙውን ጊዜ ችግሩ ለሚሰማው ጥሩ አዳማጭ ስሜትን ማካፈል ጠቃሚ ነው። (ምሳሌ 12:25) ሆኖም ሐዘኑ ለዘላለም የሚቀጥል አይደለም። አንዳንድ ግለሰቦች እግራቸውን ወይም እጃቸውን ካጡ በኋላ ለተወሰነ ጊዜ ስሜታቸው ሊለዋወጥ፣ በሆነ ባልሆነው ሊያማርሩ፣ ሊጨነቁ ወይም ደግሞ ራሳቸውን ሊያገልሉ ይችላሉ። ይሁን እንጂ ብዙውን ጊዜ እንዲህ ዓይነቶቹ ስሜቶች እየከሰሙ ይሄዳሉ። ለረጅም ጊዜ ከዘለቁ ግን ግለሰቡ የሕክምና እርዳታ የሚያስፈልገው የመንፈስ ጭንቀት ይዞት ሊሆን ይችላል። የቤተሰብ አባላትና ጓደኞች እንዲህ ዓይነት እርዳታ ያስፈልገው እንደሆነና እንዳልሆነ የሚጠቁሙ ምልክቶችን በንቃት መከታተል አለባቸው።a
ሁለቱም እግሮቹ ሽባ የሆኑበት ደብሊው ሚቸል እንዲህ ሲል ጽፏል:- “ሁላችንም የሚያስቡልን ሰዎች ያስፈልጉናል። አንድ ሰው በብዙ ወዳጅ ዘመዶች እንደተከበበ ሆኖ ከተሰማው ማንኛውንም ነገር ይቋቋማል ብሎ መናገር ይቻላል። በሕይወት ለመቀጠል ብቻውን የሚፍጨረጨር ሰው ግን ትንሿ መሰናክል እንኳ ትልቅ ጋሬጣ ልትሆንበት ትችላለች። ወዳጅነት ደግሞ እንዲሁ በአጋጣሚ የሚመጣ ነገር አይደለም። በሚገባ መኮትኮትና መዳበር ያለበት ነገር ነው። አለዚያ ይከስማል።”—ከምሳሌ 18:24 ጋር አወዳድር።
እግርን ወይም እጅን አጥቶም ደስተኛ ሕይወት መምራት
እግራቸውን ወይም እጃቸውን ያጡ በርካታ ሰዎች አካላዊ ጉድለት ቢኖርባቸውም እንኳ ደስተኛ ሕይወት መምራት ችለዋል። ለምሳሌ ያህል ራስል የግራ እግሩን የላይ አካል ብቻ ይዞ ነበር የተወለደው። ምንም እንኳ በአሁኑ ጊዜ በምርኩዝ የሚሄድ የ78 ዓመት ሰው ቢሆንም አሁንም ድረስ አዘውትሮ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ የሚያደርግ ከመሆኑም በላይ ሕይወቱን በተሟላ ሁኔታ በመምራት ላይ ይገኛል። ራስል በተፈጥሮው ፍልቅልቅ በመሆኑ ከረጅም ጊዜ አንስቶ ደስተኛው በሚል ቅጽል ስም ሲጠራ እንደኖረ ገልጿል።
በሁለተኛው የዓለም ጦርነት እግሩን ያጣው ዳግላስ የሚራመደው በዘመናዊ ሰው ሠራሽ እግር አማካኝነት ነው። የይሖዋ ምሥክር በመሆኑ የዘወትር አቅኚ ማለትም የሙሉ ጊዜ ወንጌላዊ ሆኖ ለስድስት ዓመታት ሲያገለግል ቆይቷል። እግሩን ባጣ ጊዜ ሕይወቱ እንዳከተመለት ተሰምቶት የነበረውን ዴልን ታስታውሳለህ? እሱም አቅኚ ሆኖ በማገልገል አስደሳች ሕይወት በመምራት ላይ ከመሆኑም በላይ ራሱን ማስተዳደር ችሏል።
ይሁን እንጂ ድሃ በሆኑ ወይም በጦርነት በሚታመሱ አገሮች ውስጥ የሚኖሩ እግራቸውን ወይም እጃቸውን ያጡ ሰዎች እርዳታ የሚያገኙት ምን ያህል ነው? የዓለም የጤና ድርጅት “በዛሬው ጊዜ የአካል ጉዳት ከደረሰባቸው ሰዎች መካከል እርዳታ የሚያገኙት ጥቂቶቹ ብቻ ናቸው” ሲል ገልጿል። ብዙዎቹ ወዲያና ወዲህ የሚንቀሳቀሱት በከዘራ ወይም በምርኩዝ ነው። ሆኖም አንዳንድ ጊዜ እርዳታ የሚያገኙበት ሁኔታ ይፈጠራል። በአንጎላ ውስጥ በተቀበሩ ፈንጂዎች እግራቸውን ያጡት ፍሎሪያኑ እና ፍሎሪንዱ በዓለም አቀፍ የቀይ መስቀል ማኅበርና በስዊስ መንግሥት አማካኝነት ሰው ሠራሽ እግር ማግኘት ችለዋል። ፍሎሪያኑ በአካባቢው በሚገኝ የይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤ ውስጥ የጉባኤ አገልጋይ ሆኖ በደስታ በማገልገል ላይ ሲሆን ፍሎሪንዱ ደግሞ ሽማግሌና የሙሉ ጊዜ ወንጌላዊ ሆኖ በማገልገል ላይ ይገኛል።
የአካል ጉዳተኞችን የሚረዳ አንድ ማኅበር “በእርግጥ አካለ ስንኩላን ሊባሉ የሚችሉት ቅስማቸው የተሰበረ ብቻ ናቸው!” ሲል ሁኔታውን ጥሩ አድርጎ ገልጾታል። መጽሐፍ ቅዱስ ለአካል ጉዳተኞች የመንፈስ ጥንካሬ በመስጠት ረገድ ትልቅ ሚና የሚጫወት መሆኑ ትኩረት የሚስብ ነው። “እያገገምኩ በነበረበት ወቅት ላይ የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት መማሬ በእጅጉ ረድቶኛል” ሲል ዴል ተናግሯል። በተመሳሳይም ራስል “በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተው ተስፋዬ ምንጊዜም ችግሮችን ለመወጣት እንድችል ረድቶኛል” ብሏል። ለመሆኑ መጽሐፍ ቅዱስ ለአካል ጉዳተኞች የሚሰጠው ተስፋ ምንድን ነው?
[የግርጌ ማስታወሻ]
a በ6-111 መጠበቂያ ግንብ እትም ላይ የወጣውን “የመንፈስ ጭንቀት ያለባቸውን ሰዎች እንዴት መርዳት ይቻላል?” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።
[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
የፋንተም ሕመም
ፋንተም የሚባለው ስሜት የሚሰማቸው ሰዎች የተቆረጠው የአካል ክፍላቸው እንዳለ አድርገው ያስባሉ። ይህ ስሜት የአካል ክፍላቸው የተቆረጠ ሰዎች ከቀዶ ሕክምናው በኋላ የሚያጋጥማቸው የተለመደ ስሜት በመሆኑ አንድ ቡክሌት የሚከተለውን ሐሳብ ሰጥቷል:- “ሰው ሠራሽ እግራችሁን ሳታደርጉ ከአልጋ በምትወርዱበት ወይም ከመቀመጫ ላይ በምትነሱበት ጊዜ የፋንተም ስሜት እንዳይገጥማችሁ መጠንቀቅ ይኖርባችኋል። ምንጊዜም እግራችሁ አለመኖሩን እንድታስታውሱ ወደ ታች ተመልከቱ።” ሁለቱንም እግሮቿን ያጣች አንዲት ታካሚ ተነስታ ዶክተሩን ለመጨበጥ በመሞከሯ ወለል ላይ ወድቃለች!
ሌላው ችግር ደግሞ የፋንተም ሕመም ነው። ይህ ከተቆረጠው እግር ወይም እጅ የሚመጣ የሚመስል እውነተኛ ሕመም ነው። የፋንተም ሕመም መጠን፣ ዓይነትና ሕመሙ የሚቆይበት ጊዜ ከሰው ወደ ሰው ይለያያል። ጥሩነቱ ግን ብዙውን ጊዜ የፋንተም ስሜትም ሆነ የፋንተም ሕመም እያደር ይቀንሳሉ።
[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ዘመናዊ ሰው ሠራሽ እግሮችና እጆች የብዙ አካል ጉዳተኞች ሕይወት ይበልጥ አስደሳች እንዲሆን አድርገዋል
[ምንጭ]
Photo courtesy of RGP Prosthetics
[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
አንድ ትልቅ ነገር ስናጣ ማዘናችን ያለ ነገር ነው
[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በርካታ የአካል ጉዳተኞች የተሟላ ሕይወት መምራት ችለዋል