አውዳሚ ከሆነ ዓውሎ ነፋስ የሰዎችን ሕይወት መታደግ!
ባለፈው ዓመት ሚች የተባለው ዓውሎ ነፋስ ያስከተለው ውድመት በዓለም ዙሪያ በሚገኙ መገናኛ ብዙሐን ርዕሰ ዜና ሆኖ ነበር። ይሁንና የይሖዋ ምሥክሮች ለዚህ አውዳሚ ዓውሎ ነፋስ ሰለባዎች እርዳታ ለማድረስ ሲሉ የከፈሉት ከፍተኛ መሥዋዕትነት እምብዛም ትኩረት አልተሰጠውም። የሚከተለው ሪፖርት እውነተኛ ክርስትና እና ወንድማማችነት እጅግ አስቸጋሪ በሆኑ ሁኔታዎች ሥር እንኳን እንዴት ድል ሊያደርግ እንደሚችል የሚያሳይ ነው።
ጥቅምት 22, 1998 ከደቡብ ምዕራብ ካሪቢያን ውኃዎች አንድ አውዳሚ ተነሳ። መጀመሪያ ላይ ቀላል ሐሩራዊ ነፋስ ሆኖ ነበር የተነሳው። በ24 ሰዓታት ውስጥ ከባድ ወደ ሆነ ሐሩራዊ ውሽንፍር ተለውጦ ለረጅም ጊዜ በአስፈሪነቱና በአስጨናቂነቱ ሲታወስ የሚኖርበት ሚች የሚባል ስም ተሰጠው። ሚች ኃይሉን በማጠናከር ወደ ሰሜን አቅጣጫ አቀና። ጥቅምት 26 ላይ በ5ኛ እርከን የሚመደብ ዓውሎ ነፋስ ሆነ። ዓውሎ ነፋሱ በሰዓት ከ290 ኪሎ ሜትር በላይ ይጓዝ የነበረ ሲሆን አልፎ አልፎም በሰዓት ከ320 ኪሎ ሜትር በላይ ፍጥነት ያለው የነፋስ ሽውታም ነበረው።
መጀመሪያ ላይ ሚች ጃማይካንና የኬይማን ደሴቶችን ለመምታት የተዘጋጀ መስሎ ነበር። ሆኖም አውዳሚው ዓውሎ ነፋስ ወደ ምዕራብ አቅጣጫ ዞረና በመካከለኛው አሜሪካ ባሕር ጠረፍ ላይ ወደምትገኘው ወደ ቤሊዝ አመራ። ይሁንና ጥቃቱን ከመጀመር ይልቅ በሰሜናዊ የሆንዱራስ ጠረፍ ላይ በአስጊ ሁኔታ ሲያንዣብብ ቆየ። ከዚያም በድንገት ይህ አውዳሚ ለጥፋት ተንቀሳቀሰ። ጥቅምት 30 ላይ ሚች ሆንዱራስን በመምታት እልቂትና ውድመት አስከተለ።
ሚች ሆንዱራስን መታ
ሚች መምጣቱን ያስታወቀው ዶፍ ዝናብ በማውረድ ነበር። “ቅዳሜ ጥቅምት 31 ከሌሊቱ ሰባት ሰዓት ገደማ ላይ እጅግ ኃይለኛ የሆነ ነጎድጓዳማ ድምፅ ሰማን” ይላል በቴጉሲጋልፓ የሚኖር ቢክቶር አቤላር የሚባል አንድ የሙሉ ጊዜ ወንጌላዊ። “ትንሽ የነበረችው ጅረት ትልቅ ወንዝ ሆና ነበር! ደራሽ ውኃ ሁለት ቤቶችን የወሰደ ሲሆን ነዋሪዎቻቸው መውጣት አቅቷቸው ይጮሁ ነበር።” በሌላ የከተማዋ ክፍል ደግሞ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስ ያጠኑ የነበሩ 8 ግለሰቦችን ጨምሮ 32 ሰዎች በጭቃ ተውጠው ሞተዋል። ይሁን እንጂ አንድም የተጠመቀ ምሥክር ሕይወቱን አላጣም።
የሆንዱራስ ባለ ሥልጣናት ለአደጋው አፋጣኝ ምላሽ በመስጠት የስደተኞች መጠለያዎች አቋቋሙ። በተጨማሪም በደርዘን ከሚቆጠሩ አገሮች የተውጣጣ ዓለም አቀፍ የእርዳታ ቡድን ለተግባር ተንቀሳቀሰ። የይሖዋ ምሥክሮችም በተመሳሳይ “እንግዲያስ ጊዜ ካገኘን ዘንድ ለሰው ሁሉ ይልቁንም ለሃይማኖት ቤተ ሰዎች መልካም እናድርግ” የሚሉትን የመጽሐፍ ቅዱስ ቃላት በማስታወስ የእርዳታ ሥራቸውን ተያያዙት። (ገላትያ 6:10) በመሆኑም አስቸኳይ የእርዳታ ኮሚቴዎች ተቋቋሙ። በባሕር ጠረፎች በሚገኙ መንደሮች ያለው ሁኔታ እጅግ አሳሳቢ መሆኑን በመገንዘብ ምሥክሮቹ የነፍስ አድን ተልእኳቸውን ማከናወን ጀመሩ።
ኤድጋርዶ አኮስታ የተባለ ምሥክር ያከናወኑትን ሥራ መለስ ብሎ በማስታወስ እንዲህ ሲል ተናግሯል:- “ቅዳሜ ጥቅምት 31 ዕለት አንዲት ትንሽ ጀልባ አገኘንና በጎርፍ ወደ ተጥለቀለቀው ሥፍራ ሄድን። ሁለት ወንድሞችንa ለማውጣት ብንችልም ሁሉንም ወንድሞች ለማውጣት ግን ትልቅ ጀልባ እንደሚያስፈልገን ተገነዘብን። ስለዚህ ትልቅ ጀልባ አመጣንና እሁድ ዕለት ጧት ሁለተኛ ጉዟችንን ጀመርን። በመጨረሻም ሁሉንም የጉባኤው አባላትና በጎረቤት የሚኖሩ አንዳንድ ሰዎችን ጨምሮ በአጠቃላይ 189 ሰዎችን አወጣን።”
ላ ሁንታ አቅራቢያ በተካሄደው የነፍስ አድን ሥራ ላይ ክዋን አልባራዶ ተካፍሎ ነበር። እንዲህ ሲል ያስታውሳል:- “ሰዎች ‘እርዱን! ድረሱልን!’ እያሉ ሲጮኹ እንሰማ ነበር። በሕይወቴ እንዲህ ያለ አሰቃቂ ተሞክሮ ገጥሞኝ አያውቅም። ወንድሞች ምንም ማምለጫ ቀዳዳ አልነበራቸውም። ብዙዎቹ ጣሪያ ላይ ወጥተው ነበር።” በሕይወት ከተረፉት መካከል ማሪአ ቦኒያ የምትባል ሴት እንዲህ ብላለች:- “በዙሪያችን የነበረው ውኃ ውቅያኖስ ይመስል ነበር። ሁላችንም እናለቅስ ነበር።” ይሁን እንጂ የነፍስ አድን ሥራው ስኬታማ ነበር። ኡምቤርቶ አልባራዶ የተባለው ተራፊ “ወንድሞች ሕይወታችንን ከማትረፋቸውም በላይ መጠለያ፣ ምግብና ልብስ ሰጥተውናል” ብሏል። ኡምቤርቶ አክሎ እንዲህ ብሏል:- “የነፍስ አድን ሥራውን የተመለከተ አንድ ሰው ከእሱ ቤተ ክርስቲያን አባላት መካከል ሊያድነው የሞከረ ሰው እንደሌለና እንዲህ ያደረጉት የይሖዋ ምሥክሮች ብቻ መሆናቸውን ነግሮናል። አሁን እውነተኛ ሃይማኖት ያላቸው የይሖዋ ምሥክሮች መሆናቸውን አምኗል!”
ላ ሊማ በሚባል ከተማ ውስጥ የተወሰኑ ምሥክሮች መግቢያ መውጪያ አጥተው በአንድ ቤት ውስጥ ይገኙ ነበር። በዙሪያቸው ያለው ውኃ እየጨመረ ሲመጣ ወደ ኮርኒሱ የሚያስገባ ቀዳዳ አበጅተው በጣሪያው ተሸካሚ እንጨቶች ላይ ወጡ። ጋቢ የምትባል አንዲት እህት እንዲህ ትላለች:- “ለጥቂት ቀናት የሚሆን ምግብ ነበረን። ይህ ምግብ ሲያልቅ አንድ ወንድም በሕይወቱ ቆርጦ በውኃ ውስጥ በመጓዝ ኮኮናቶች ይዞ መጣ። ጭንቀታችን ቀለል እንዲልልን ስንል የመንግሥቱን መዝሙሮች እንዘምር ነበር።” የጉባኤ አገልጋይ የሆነው ጁአን እንዲህ ሲል ያስታውሳል:- “በሕይወት እንተርፋለን ብለን አላሰብንም። ስለዚህ መጽሐፍ ቅዱሳዊ መጽሔት የሆነውን መጠበቂያ ግንብን ለማጥናት ወሰንን። አንድ ላይ የምናጠናበት የመጨረሻው ጊዜ ይህ ይሆናል ብለን በማሰብ ሁላችንም ማልቀስ ጀመርን። ጥናቱ ለመጽናት የሚያስችለንን ጥንካሬ ሰጥቶናል።” በዚህ መልኩ ለስምንት ቀናት ያህል ከቆዩ በኋላ በባለ ሥልጣናቱ የነፍስ አድን ቡድን ሕይወታቸው ሊተርፍ ችሏል።
ከዚህ የጎርፍ መጥለቅለቅ የተረፉ ሰዎች ምንም እንኳ ደህንነታቸው ቢጠበቅም መራራ የሆኑ እውነታዎችን ለመቀበል ተገድደዋል። ሊሊያን የምትባል ምሥክር እንዲህ ስትል በግልጽ ተናግራለች:- “ልብሶችን፣ የቤት እቃዎችንና የቤተሰብ ፎቶዎችን የመሳሰሉ የግል ነገሮችን ማጣት በጣም የሚያሳዝን ነው። ቤቴ በጭቃ፣ በቆሻሻና ሌላው ቀርቶ በእባቦች ተሞልቶ ማየቱ እጅግ የሚሰቀጥጥ ነበር!” አሁንም እንደገና ክርስቲያናዊ ወንድማማችነት ከፍተኛ ዋጋ ያለው መሆኑን አስመስክሯል። “ወንድሞች ሊረዱን መጡ” ትላለች ሊሊያን። “የይሖዋ ምሥክር ያልሆነው ባለቤቴ ‘ውለታቸውን የምንመልሰው እንዴት ነው?’ በማለት ጠየቀ። አንደኛዋ እህት ‘እኔን ማመስገን አያስፈልግሽም። እኔ እህትሽ ነኝ!’ በማለት መለሰችልኝ።”
ኤል ሳልቫዶር የሚችን ምት ቀመሰች
ሚች የተባለው ዓውሎ ነፋስ በምዕራብ አቅጣጫ በመጓዝ ወደ ኤል ሳልቫዶር ሲያመራ ኃይሉ እየቀነሰ ቢመጣም የማውደም አቅም ግን ነበረው። በዚያን ወቅት በኤል ሳልቫዶር የሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮች “የአምላክ የሕይወት መንገድ” የተባለውን የአውራጃ ስብሰባ ለማካሄድ በዝግጅት ላይ ነበሩ። ከ40,000 በላይ የሚሆኑ ሰዎች ይገኛሉ ተብሎ ይጠበቅ ነበር። ሚች እየቀረበ ሲመጣ ሁሉም ወንድሞች በዚህ የአውራጃ ስብሰባ ላይ ለመገኘት መቻላቸው አጠራጣሪ እየሆነ መጣ። ወንዞች ሞልተው በመፍሰስ ሰብሎችን፣ አውራ መንገዶችንና ቤቶችን አጥለቀለቁ። በደን ምንጠራ የተራቆቱት ኮረብቶች ከፍተኛ የሆነ የጭቃ ጎርፍ ፈጠሩ።
ኔልሶን ፍሎርስ በቺላንጌራ ከተማ የሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤ ሰብሳቢ የበላይ ተመልካች ነበር። ቅዳሜ ጥቅምት 31 ጠዋት ላይ ከእንቅልፉ ተነስቶ ከወንዙ ባሻገር ሲመለከት በአንድ ወቅት ቺላንጌራ ትገኝበት የነበረው ቦታ እንዳልነበረ ሆኗል! አምስት መቶ የሚሆኑ ቤቶች ተጠርገው ተወስደዋል! ለራሱ ደህንነት ብዙም ሳይጨነቅ ለመንፈሳዊ ወንድሞቹ ሕይወት በማሰብ በሞላው ወንዝ ውስጥ ገባ። “ወደ ወንዙ ማዶ ስደርስ” ይላል ኔልሰን፣ “ቆምኩና ያለሁበትን ቦታ ለማጣራት ሞከርሁ። በዚህ አካባቢ በየቀኑ እየተመላለስኩ ከቤት ወደ ቤት ሰብኬያለሁ፤ ሆኖም ቦታውን ለመለየት የሚያስችል አንድም የማውቀው ምልክት ላገኝ አልቻልኩም!”
በዚያ ሌሊት በቺላንጌራ 150 የሚሆኑ ሰዎች ሞተዋል። ከእነዚህ ሰዎች መካከል ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን የሚያጠኑ የተወሰኑ ግለሰቦች ይገኙ ነበር። ይሁን እንጂ ሕይወቱን ያጣ አንድም የተጠመቀ ምሥክር አልነበረም።
የነፍስ አድን ሥራው ወዲያውኑ ጀመረ። እነዚህን እንቅስቃሴዎች በማደራጀት እገዛ ያበረከተው አሪስቴዴስ ኤስትራዳ እንዲህ በማለት ያብራራል:- “ወደ ቺላንጌራ ለመሄድ ፈቃድ አላገኘንም ነበር። የውኃው መጠን በመጨመር ላይ ነበር! የራሳቸውን ሕይወት ለማዳን ሲሉ ቦታውን ጥለው ለመሸሽ ለተገደዱ የነፍስ አድን ሠራተኞች የእርዳታ ጥሪ ያሰሙ የነበሩትን ሰዎች በፍጹም አልረሳቸውም።” ይሁንና ከጊዜ በኋላ ሁሉም ወንድሞች በደህና ከቦታው እንዲወጡ ማድረግ ተችሏል። የመንግሥት አዳራሾች የስደተኞች መጠለያ ሆነው አገልግለዋል። በተጨማሪም በሆስፒታሎች፣ በትምህርት ቤቶችና በሌሎች ቦታዎች የተጎዱና ቤታቸውን ያጡ ምሥክሮች ስም ዝርዝር መኖሩን እንዲያጣሩ የተለያዩ ወንድሞች ተመድበው ነበር። በአካባቢው የሚገኙ ጉባኤዎች አስፈላጊ የሆኑ ቁሳቁሶችን በአስቸኳይ አቅርበዋል።
ይሁንና ቁሳቁሶችን ወደ ማሰባሰቢያ ጣቢያዎች ማድረሱ አስቸጋሪ የሚሆንባቸው ጊዜያት ነበሩ። ኮሪንቶ በሚባል ከተማ የሚኖሩ ወንድሞች ከራሳቸው ማሳ የሰበሰቡትን እህል ተሸክመው ጉዞ ከጀመሩ ከጥቂት ጊዜ በኋላ መንገዱ በመሬት መንሸራተት ተዘግቶ አገኙት። ምን ያደርጉ ይሆን? መፍትሔው ቆፍሮ ማለፍ ነበር! መጀመሪያ ላይ በአካባቢው የነበሩት ሰዎች የሚሆን ነገር አልመሰላቸውም ነበር። በኋላ ላይ ግን መንገዱን ለመክፈት በሚያደርጉት ጥረት አገዟቸው። ከኮሪንቶ የመጡት ወንድሞች ያሰቡት ቦታ የደረሱት በጭቃ ተጨማልቀው ቢሆንም የአቅማቸውን ለማድረግ በመቻላቸው ተደስተው ነበር።
የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ቅርንጫፍ ቢሮ አንደኛው የማሰባሰቢያ ጣቢያ ነበር። በዚያ የሚያገለግለውና መዋጮዎችን በማሰባሰቡ ሥራ የረዳው ሂልቤርቶ እንዲህ ሲል ያስታውሳል:- “እጅግ የሚያስገርም ነበር! በጣም ብዙ ተሽከርካሪዎች በመምጣታቸው በመኪና ማቆሚያውና በቅርንጫፍ ቢሮው ፊት ለፊት ባለው መንገድ ላይ የነበሩትን ተሽከርካሪዎች ለማስተናገድ ፈቃደኛ ሠራተኞች መመደብ አስፈልጎ ነበር።” ወደ 25 ቶን የሚጠጋ ልብስና 10 ቶን የሚሆን ምግብ ተዋጥቶ ነበር። ልብሶቹን ለመለየትና ለመላክ 15 የሚሆኑ ፈቃደኛ ሠራተኞች አንድ ሙሉ ሳምንት ፈጅቶባቸዋል።
ሚች በኒካራጉዋ በኩል አለፈ
ሚች በኒካራጉዋ ድንበር በኩል ተጠግቶ በማለፍ በዚያች አገር ላይ ከፍተኛ መጠን ያለው ዝናብ እንዲጥል አድርጓል። በሺህ የሚቆጠሩ ቤቶች የወደሙ ሲሆን አውራ መንገዶችም ተጠርገው ተወስደዋል። የጭቃ ጎርፍ በፖሶልቴጋ ከተማ አቅራቢያ የሚገኙ መንደሮችን ከ2,000 በላይ ከሚሆኑ ሰዎች ጋር ሙሉ በሙሉ ቀብሯቸዋል።
በኒካራጉዋ የሚገኙ ምሥክሮች ስለዚህ አሳዛኝ ሁኔታ ሲሰሙ እርዳታ ለመስጠት ከፍተኛ የሆነ ዝግጅት ማድረግ ጀመሩ። ፈቃደኛ ሠራተኞች አድካሚና አደገኛ የሆነ ጉዞ በማድረግ ወንድሞቻቸውን ፍለጋ ሄዱ! ሁለት የምሥክሮች ቡድን አንዱ ከሌኦን (ከፖሶልቴጋ በስተ ደቡብ የሚገኝ ከተማ)፣ ሌላኛው ደግሞ ከቺቺጋልፓ (በስተ ሰሜን በኩል የሚገኝ ከተማ) በመነሳት ወደ ፖሶልቴጋ ተንቀሳቀሰ። እያንዳንዱ ወንድም ከባድ የእርዳታ ቁሳቁስ ተሸክሞ ነበር። የነፍስ አድን ሠራተኞች በዚያ በኩል ያለው መንገድ በፍጹም የማያሳልፍ መሆኑን ቢናገሩም ወንድሞች ግን ለመሄድ ቆርጠው ነበር።
ሰኞ ኅዳር 2 ማለዳ ላይ በሌኦን የሚገኙ ወንድሞች የእርዳታ ቁሳቁሶችን በአንድ የጭነት መኪና ላይ ጭነው በጎርፍ ተጠርጎ እስከ ተወሰደ አንድ ድልድይ ድረስ እየነዱ ሄዱ። ወንድሞች የእርዳታ ቁሳቁሱን ከጭነት መኪናው ላይ ካወረዱ በኋላ ሁለት የብስክሌት ቡድኖች በማደራጀት አንደኛው ወደ ፖሶልቴጋ ሌላኛው ደግሞ ቴሊካ ወደምትባል በጎርፍ የተጥለቀለቀች ከተማ እንዲሄዱ ዝግጅት ተደረገ። ወንድሞች ጉዟቸውን ከመጀመራቸው በፊት ጸለዩ። በነፍስ አድን ተልዕኮው ከተሠማሩት ወንድሞች አንዱ “ከጸሎቱ በኋላ ከፍተኛ የሆነ ብርታት ተሰማን” ሲል ገልጿል። እንዲህ ያለው ጥንካሬ ያስፈልጋቸው ነበር። ሰፋፊ ቦዮችን ማቋረጥ የነበረባቸው ሲሆን አንዳንድ ጊዜ በጭቃ ላይ መንሸራተት በሌሎች ጊዜያት ደግሞ ብስክሌቶቻቸውን በትከሻቸው መሸከም ነበረባቸው። ብዙውን ጊዜ የወዳደቁ ዛፎች መንገዳቸውን ይዘጉባቸው ነበር። እንዲሁም በኩሬዎች ላይ ይንሳፈፍ የነበረውን ሬሳ እየተመለከቱ ማለፍን የመሰለ ዘግናኝ ነገር በጽናት መቋቋም ነበረባቸው።
የሚያስገርመው ነገር ከሌኦንና ከቺቺጋልፓ የተነሱት ብስክሌተኞች ፖሶልቴጋ የደረሱት በተመሳሳይ ጊዜ ውስጥ ነበር! የዚህ የነፍስ አድን ቡድን አባል የነበረው ኔሪዮ ሎፔስ እንዲህ ሲል ያስታውሳል:- “የብስክሌቴ ጎማዎች አልቀው ነበር። አንድ ወይም ሁለት ኪሎ ሜትር ቢያስኬደኝ ነው ብዬ ገምቼ ነበር።” ሆኖም ብስክሌቱ ከታሰበው በላይ ሊጓዝ ችሏል። ሁለቱም ጎማዎች የፈነዱት በመልስ ጉዞው ላይ ነበር። በዚያም ሆነ በዚህ በቦታው የደረሱት የመጀመሪያዎቹ የነፍስ አድን ሠራተኞች ወንድሞች ነበሩ። በአካባቢው ከሚገኙ ክርስቲያን ወንድሞችና እህቶች ጋር ሲገናኙ ምንኛ ተደስተው ነበር! አንዲት እህት እንዲህ ብላለች:- “ድጋፋቸውንና እርዳታቸውን ስለ ለገሱን ይሖዋንና ወንድሞቻችንን በጣም አመሰግናቸዋለሁ። ወንድሞቻችን በዚህን ያክል ፍጥነት መጥተው ይረዱናል ብለን አልጠበቅንም ነበር።”
በጎርፍ ወደ ተጥለቀለቁ መንደሮች ከተደረጉት በርካታ የብስክሌት ጉዞዎች መካከል ይህ አንዱ ብቻ ሲሆን አብዛኛውን ጊዜም ወንድሞች በእነዚህ አካባቢ ለመገኘት የመጀመሪያዎቹ የነፍስ አድን ሠራተኞች ነበሩ። የላሬናጋ ከተማ በብስክሌት የመጡ 16 ወንድሞችን አስተናግዳለች! በአካባቢው የሚገኙ ወንድሞች በእነዚህ ወንድሞች ጥረት ተነክተው አለቀሱ። አንዳንድ ጊዜ እነዚህ ብስክሌተኞች 20 ኪሎ ግራም የሚመዝን ቁሳቁስ በጀርባቸው ላይ መሸከም ነበረባቸው። ሁለት ወንድሞች ከ100 ኪሎ ግራም በላይ የሚመዝን የእርዳታ ቁሳቁስ ተሸክመው ወደ ኤል ግዋያቦ ተጉዘዋል! አንድ ብስክሌተኛ የሚችለውን ያህል እቃ በብስክሌቱ ላይ ጭኖ በሚጓዝበት ጊዜ በኢሳይያስ 40:29 ላይ በሚገኘው የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ ላይ ማሰላሰሉ አጽናንቶታል:- “[ይሖዋ] ለደካማ ኃይልን ይሰጣል፣ ጉልበት ለሌለውም ብርታትን ይጨምራል።”
በቶናላ የሚገኙ ወንድሞች ምግባቸው መሟጠጡን ኃላፊነት ላላቸው ወንድሞች ለማሳወቅ አንድ መልእክተኛ ላኩ። መልእክተኛው ሲደርስ የእርዳታ ቁሳቁሶቹ አስቀድመው መላካቸውን በመስማቱ በጣም ተገረመ! ወደ መንደሩ ሲመለስ ደግሞ ለእሱ የሚሆን ምግብ በቤቱ ተቀምጦለት ነበር። በቺናንዴጋ ዙሪያ በሚገኙ በጎርፍ የተጥለቀለቁ አካባቢዎች የእርዳታ ቁሳቁሶችን በማድረሱ ሥራ የተካፈለው ማርለን ቻቫሪአ እንዲህ ሲል ያስታውሳል:- “በአንድ ከተማ 44 የሚሆኑ የምሥክሮች ቤተሰቦች ነበሩ። ይሁን እንጂ ወንድሞች ምግባቸውን በማካፈላቸው 80 ቤተሰቦች ተጠቃሚዎች ሊሆኑ ችለዋል።”
እነዚህ የእርዳታ እንቅስቃሴዎች የባለ ሥልጣናትን ትኩረት ስበው ነበር። የዋምብላን ከተማ ከንቲባ ለምሥክሮቹ እንዲህ ሲሉ ጽፈው ነበር:- “የምንጽፍላችሁ አንዳንድ እርዳታ ልታደርጉልን ትችሉ እንደሆነ ለማወቅ ነው። . . . በዚህ በዋምብላን የሚገኙ ወንድሞቻችሁንና እህቶቻችሁን እንዴት እየረዳችሁ እንዳላችሁ ተመልክተናል፤ ለእኛም ልታደርጉልን የምትችሉት ነገር እንዳለ ለማወቅ እንፈልጋለን።” የይሖዋ ምሥክሮች ምግብ፣ መድኃኒትና ልብስ በመላክ ምላሹን ሰጥተዋል።
በጓቲማላ የደረሰው ምስቅልቅል
ሚች ሆንዱራስንና ኤል ሳልቫዶርን ለቅቆ ከወጣ በኋላ ወዲያውኑ ጓቲማላን ወረረ። ከጓቲማላ ሲቲ በስተ ደቡብ የምትኖረው ሣራ አጉስቲን የምትባል ምሥክር ኃይለኛ በሆነ የጎርፍ ድምፅ ከእንቅልፏ ትነሳለች። በምትኖርበት አካባቢ ያለው ገደል የሚያስገመግም ወንዝ ሆኖ ነበር። ለጎረቤቶቿ የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ለማካፈል ብዙ ጊዜ በሮቻቸውን አንኳኩታለች። አሁን ደግሞ በየቤታቸው እየሄደች ከእንቅልፋቸው ለመቀስቀስ መሯሯጥ ጀመረች! ከጊዜ በኋላ የጭቃ ጎርፍ ከኮረብታው ላይ መጥቶ ብዙዎቹን የጎረቤቶቿን ቤቶች ከበባቸው። በሕይወት የተረፉትን ለማዳን አካፋ በመጠቀም ሰባት ትናንሽ ልጆችን ከጭቃ ውስጥ አወጣች። ሣራ በአዋላጅነት የምትተዳደር ሲሆን ከእነዚህ ልጆች ውስጥ አንዱ በተወለደበት ጊዜ ያዋለደችው እሷ ነበረች። የሚያሳዝነው ቪልማ የምትባል በአሥራዎቹ የዕድሜ ክልል ውስጥ የምትገኝ ልጅ ከሞቱት መካከል ነበረች። ከጥቂት ጊዜ በፊት ሣራ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፍ አበርክታላት ነበር።
ሚች ኃይሉ የተዳከመ ቢሆንም ያለ ማቋረጥ የሚጥለው ዝናብ በሰብል፣ በድልድዮችና በቤቶች ላይ ከፍተኛ ጉዳት አስከትሏል። ከፍተኛ መጠን ያለው የእርዳታ ቁሳቁስ በጓቲማላ ለሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮ ተልኮ ስለነበር ከዚህ እርዳታ ውስጥ የተወሰነው በሆንዱራስ የሚገኙ ወንድሞችን ለመርዳት እንዲውል ተወሰነ። አብዛኞቹ ድልድዮች በመውደማቸውና የአውሮፕላን ማረፊያውም በጎርፍ በመጥለቅለቁ የእርዳታ ቁሳቁሶቹ በጀልባ መላክ ነበረባቸው። በቅርንጫፍ ቢሮው የሚሠራው ፍሬዝ ብሩን እንዲህ ይላል:- “ስምንት ሜትር ርዝመት ያላት ጀልባ ተከራየንና አንድ ቶን የሚሆን መድኃኒትና ምግብ ጭነን ተነሳን። ማዕበል በበዛበት ባሕር ላይ አስቸጋሪ የሆነ ጉዞ ካደረግን በኋላ በመጨረሻ ኦሞአ ወደብ ስንደርስ ከላይ እስከ ታች በውኃ ብስብስ ብለን ነበር።”
ሚች ያስከተለው ውድመት
ሚች በሜክሲኮ ደቡባዊ ምሥራቅ ላይ ጉዞውን የሚገታ መስሎ ነበር። ይሁንና ሚች አንድ የመጨረሻ ሙከራ ለማድረግ የፈለገ ይመስል ወደ ሰሜን ምሥራቅ አቅጣጫ ተጉዞ ዩ ኤስ ኤ ውስጥ የምትገኘውን የፍሎሪዳን ደቡባዊ ክፍል መታ። ሆኖም ሚች ብዙም ሳይቆይ ኃይሉ ተዳከመ። ወደ አትላንቲክ ተመልሶ መበታተን ጀመረ። ኅዳር 5 ላይ ስለ ሐሩራዊ ውሽንፍር የተሰጡ ማስጠንቀቂያዎች በሙሉ ተሰረዙ።
አንዳንድ ባለሙያዎች ሚችን “ባለፉት ሁለት ምዕተ ዓመታት ውስጥ የምዕራቡን ንፍቀ ክበብ ከመቱት ዓውሎ ነፋሳት ሁሉ የሚበልጥ እጅግ አውዳሚ ዓውሎ ነፋስ” በማለት ጠርተውታል! የሞቱት ሰዎች ቁጥር 11,000 ሳይደርስ አይቀርም፤ በሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች እስከ አሁን ድረስ የገቡበት አልታወቀም። ከሦስት ሚልዮን የሚበልጡ ሰዎች ቤት አልባ ሆነዋል አሊያም ከፍተኛ ጉዳት ደርሶባቸዋል። የሆንዱራሱ ፕሬዚዳንት ካርሎስ ፍሎርስ ፋኩሴ “በ50 ዓመታት ውስጥ ቀስ በቀስ የገነባነውን ነገር በአንድ ጊዜ አጣን” ሲሉ በምሬት ተናግረዋል።
ብዙ የይሖዋ ምሥክሮች በሚች ምክንያት ቤታቸውን አጥተዋል። የሚያሳዝነው ነገር ቤቶቻቸው ተጠራርገው በመወሰዳቸው የት የት ጋር እንደነበሩ እንኳን ለማወቅ ተስኗቸው ነበር! ያም ሆኖ ግን የይሖዋ ምሥክሮች የብዙዎቹን ቤቶች በማደሱ ወይም እንደገና በመገንባቱ ሥራ ለማገዝ ዝግጅት አድርገዋል።
ሚች የተባለውን ዓውሎ ነፋስ የመሳሰሉ አስከፊ አደጋዎች ‘አስጨናቂ በሆኑት የመጨረሻ ቀናት’ ውስጥ እንደምንኖር የሚያስገነዝቡን አሳዛኝ ክስተቶች ናቸው። (2 ጢሞቴዎስ 3:1-5) እነዚህን ከመሳሰሉ አደጋዎች አስተማማኝ ጥበቃ ማግኘት የምንችለው የአምላክ መንግሥት ይህችን ፕላኔት ማስተዳደር ሲጀምር ብቻ ነው። (ማቴዎስ 6:9, 10፤ ራእይ 21:3, 4) ያም ሆኖ ግን በቀጥታ በሚች ምክንያት ሕይወቱን ያጣ አንድም ወንድም ወይም እህት ባለመኖሩ የይሖዋ ምሥክሮች አመስጋኞች ናቸው።b አካባቢውን ለቅቆ ስለ መውጣት የተሰጡ መመሪያዎችን መታዘዛቸውና በአካባቢው የነበሩ ጉባኤዎች የነበራቸው ጥሩ ቅንጅት ብዙዎች ከአደጋ እንዲጠበቁ ረድቷቸዋል።
ባለፉት ጥቂት ወራት ጉዳቱ በደረሰባቸው አገሮች ውስጥ የሚገኙት የይሖዋ ምሥክሮች ዘወትር የሚያደርጓቸውን መንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች መልሰው ለመጀመር ሲጥሩ ቆይተዋል። ለምሳሌ ያህል በኤል ሳልቫዶር ሚች በቦታው ካለፈ ከጥቂት ቀናት በኋላ በተደረገው የአውራጃ ስብሰባ ላይ የዓውሎ ነፋሱ ተጠቂ የሆኑት እንዲካፈሉ ለመርዳት ዝግጅቶች ተደርገው ነበር። ወንድሞችን ለማመላለስ አውቶቡሶች ተከራይተው የነበረ ሲሆን የሚያርፉበትም ቦታ ተዘጋጅቶ ነበር። የታመሙት እንኳን ሳይቀር ስብሰባውን እንዲካፈሉ ሲባል የሕክምና አገልግሎት ለመስጠት ዝግጅት ተደርጎ ነበር! የአውራጃ ስብሰባው በተሳካ ሁኔታ የተከናወነ ሲሆን 46,855 የደረሰ ከፍተኛ የተሰብሳቢዎች ቁጥር ተገኝቷል፤ ይህ ደግሞ መጀመሪያ ላይ ከታሰበው ቁጥር የሚበልጥ ነበር። በሚች ምክንያት ቤቱንና ሥራውን ያጣው ሳልቫዶሪያዊ ወንድም ሆሴ ሪቬራ “የደረሰብን ነገር ስሜታችንን አቃውሶት ነበር” ብሏል። “ይሁንና ወንድሞቻችን ያላቸውን የእንግዳ ተቀባይነት መንፈስ በመመልከታችን መንፈሳችን ታድሶ ከስብሰባው ልንመለስ ችለናል።” የተለያዩ ዘገባዎች እንደሚያሳዩት በእነዚህ አገሮች የሚደረጉ የይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤዎች የተሰብሳቢ ቁጥራቸው በሚያስደንቅ ሁኔታ የጨመረ ሲሆን ይህም የእርዳታ እንቅስቃሴያችን በሌሎች ሰዎች ላይ ያሳደረው ቀጥተኛ ተጽእኖ ውጤት ነው።
ይሁን እንጂ ከማንም ይበልጥ ከፍተኛ የሆነ ተጽእኖ ያሳደረው በራሳቸው በምሥክሮቹ ላይ ነበር ለማለት ይቻላል። ሆንዱራስን ካጥለቀለቀው ጎርፍ በሕይወት የተረፈው ካርሎስ “ይህን የመሰለ ነገር በፍጹም አይቼ አላውቅም። ወንድሞች ለእኔ ያላቸውን ፍቅር በግሌ ለመመልከት ችያለሁ” ብሏል። አዎን፣ ሚች የተባለው ዓውሎ ነፋስ ያደረሰው ጉዳት አንድ ቀን የተረሳ ነገር ይሆናል። ሆኖም የይሖዋ ምሥክሮች ወንድሞቻቸውን ለመርዳት ሲሉ ሕይወታቸውንና አካላቸውን አደጋ ላይ በመጣል ያሳዩት ፍቅር በፍጹም አይረሳም።
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
a የይሖዋ ምሥክሮች አንዳቸው ሌላውን የሚጠሩት “ወንድም” እና “እህት” በማለት ነው።
b ዓውሎ ነፋሱ ካለፈ በኋላ ተላላፊ በሽታዎች ተበራክተው ነበር። በዚህ ምክንያት አንድ በኒካራጉዋ የሚኖር ወንድም ሕይወቱን አጥቷል።
[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]
በጎረቤት አገሮች የሚገኙ ምሥክሮች እገዛ አድርገዋል
የአየር ትንበያ ባለሙያዎች ቤሊዝ ሚች በተባለው ዓውሎ ነፋስ ትመታለች ብለው በተነበዩ ጊዜ አገሪቱ ለዚህ አደጋ ራሷን ማዘጋጀት ጀመረች። መንግሥት በባሕር ዳርቻዎችና በዝቅተኛ ቦታዎች የሚገኙ ሰዎች ያሉበትን አካባቢ ለቅቀው እንዲወጡ ባወጣው ትእዛዝ መሠረት የይሖዋ ምሥክሮች 80 ኪሎ ሜትር ወደ ውስጥ ገባ ብላ ወደምትገኘው ወደ ዋና ከተማዋ ወደ ቤልሞፓን ወይም በከፍተኛ ቦታዎች ላይ ወደሚገኙ ሌሎች ከተሞች ተዛወሩ።
ደግነቱ ቤሊዝ የሚችን ቁጣ ከመቅመስ ልትተርፍ ችላለች። ሆኖም በቤሊዝ የሚገኙ ወንድሞች በሆንዱራስ፣ ኒካራጉዋና ጓቲማላ የሚገኙ ወንድሞቻቸው የደረሰባቸውን ጉዳት ሲሰሙ ምግብ፣ ልብስ፣ የተጣራ ውኃና ገንዘብ አዋጥተው ለገሱ።
በሌሎቹ ጎረቤት አገሮች የሚገኙ ወንድሞችም እንዲህ ዓይነት ምላሽ ሰጥተዋል። በኮስታ ሪካ የሚገኙ ምሥክሮች በአራት ትላልቅ ኮንቴይነሮች ምግብ፣ ልብስና መድኃኒት ልከዋል። በፓናማ የሚገኙ ወንድሞች የተሰባሰቡ ቁሳቁሶችን ለመረከብ፣ ለመለየትና ለማሸግ አራት ጣቢያዎችን አቋቋሙ። በጥቂት ቀናት ውስጥ ከ20,000 ኪሎ ግራም በላይ የሚሆን የእርዳታ ቁሳቁስ ተሰበሰበ። አንድ ምሥክር ያልሆነ ሰው “የእርዳታ ሥራዎችን በማደራጀት ረገድ በአንደኛ ደረጃ የሚጠቀሰው የጦር ሠራዊቱ ነው ብዬ አስብ ነበር። አሁን ግን ግንባር ቀደሙን ስፍራ የያዙት የይሖዋ ምሥክሮች መሆናቸውን ተገንዝቤአለሁ” ብሏል። በአሁኑ ጊዜ ምሥክሮቹ አዘውትረው ወደዚህ ሰው በመሄድ የመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶችን እያስተማሩት ነው።
በትራንስፖርት አገልግሎት ሥራ የተሠማራ አንድ ወንድም የእርዳታ ቁሳቁሶችን ወደ ኒካራጉዋ ለማጓጓዝ የሚረዳ ተሳቢና አንድ ሹፌር (ምሥክር ያልሆነ) አቅርቦ ነበር። በፓናማም ሆነ በኮስታ ሪካ የሚገኙ ባለ ሥልጣናት የጭነት መኪናው የጉምሩክ ፍተሻ ሳይደረግበት ድንበሮቻቸውን አቋርጦ እንዲያልፍ ፈቅደዋል። አንድ የነዳጅ ማደያ የጭነት መኪናው ባሉት ሁለት በርሜሎች ሊይዘው የሚችለውን ያህል ነዳጅ የለገሰ ሲሆን ይህ ደግሞ የደርሶ መልስ ጉዞ ለማድረግ የሚበቃ ነበር! በኒካራጉዋ የሚገኙ ባለ ሥልጣናትም በተመሳሳይ ጥቅሎቹ ሳይፈተሹ እንዲያልፉ አድርገዋል። “ይህ የመጣው ከይሖዋ ምሥክሮች ከሆነ መፈተሽ አያስፈልገንም” አሉ። “በእነሱ በኩል ምንም ችግር አጋጥሞን አያውቅም።”
ይሁን እንጂ በሆንዱራስ የየብስ ማጓጓዣ አገልግሎት አስቸጋሪ ነበር። ሆኖም በሆንዱራስ ኤምባሲ የምትሠራ አንዲት እህት የእርዳታ እቃዎቹን ያለ ምንም ክፍያ በአውሮፕላን ለመላክ ከኤምባሲው ጋር ተነጋግራ ዝግጅት አደረገች! ከ10,000 ኪሎ ግራም በላይ የሚመዝን እቃ በዚህ መንገድ ተጓጉዟል።
ደስ የሚለው ነገር ምሥክር ያልሆኑ አንዳንድ ሰዎችም በምሥክሮቹ የእርዳታ ሥራ ተነክተው ነበር። አንዳንድ ኩባንያዎች ካርቶኖችን፣ ፕላስተሮችንና የፕላስቲክ መያዣዎችን በመስጠት ረድተዋል። ሌሎች ደግሞ የገንዘብ መዋጮዎችንና ቅናሾችን አድርገዋል። በተለይ በፓናማ የሚገኙት የአየር መንገድ ሠራተኞች ወደ ሆንዱራስ የሚላከውን የእርዳታ ቁሳቁስ በማራገፉ ሥራ ከ20 የሚበልጡ ምሥክሮች በፈቃደኛ ሠራተኛነት ሲያገለግሉ በመመልከታቸው ስሜታቸው በጥልቅ ተነክቶ ነበር። በሚቀጥለው ቀን ከእነዚህ የአየር መንገድ ሠራተኞች አንዳንዶቹ ያሰባሰቡትን እርዳታ አምጥተው ነበር።
[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
በሜክሲኮ የተከናወነ ተመሳሳይ የእርዳታ ሥራ
ሜክሲኮ በሚች ዓውሎ ነፋስ የደረሰባት ጉዳት አነስተኛ ነበር። ሆኖም ይህ አውዳሚ የሆነ ዓውሎ ነፋስ መካከለኛውን አሜሪካ ከመምታቱ ከጥቂት ሳምንታት በፊት በቺያፓስ ግዛት ከፍተኛ ጎርፍ ተከስቶ ነበር። ወደ 350 የሚጠጉ መንደሮች ጉዳት የደረሰባቸው ሲሆን አንዳንዶቹም ሙሉ በሙሉ ተጠርገው ተወስደዋል።
ጎርፉ በዚያ አካባቢ በሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮች ላይ በርካታ ችግሮችን እንደሚፈጥር የታወቀ ነው። ይሁን እንጂ በአካባቢው ጉባኤዎች ውስጥ የሚገኙ ሽማግሌዎች ዓውሎ ነፋሱ የሚያስከትለውን አደጋ ለመቀነስ ከፍተኛ እገዛ አድርገዋል። ለምሳሌ ያህል በአንድ አነስተኛ መንደር ውስጥ ሽማግሌዎች እያንዳንዱን የጉባኤ አባል እየዞሩ ከጎበኙ በኋላ ዝናቡ የሚቀጥል ከሆነ በመንግሥት አዳራሹ ውስጥ እንዲጠለሉ አሳሰቧቸው። በአካባቢው ከሚገኙት ሕንፃዎች ውስጥ ጥንካሬ አለው የሚባለው የመንግሥት አዳራሹ ነበር። ጎህ ሲቀድ ከተማዋ ከሁለት ወንዞች በመጣ ጎርፍ ተጥለቀለቀች! ምሥክሮቹና በርካታ ጎረቤቶቻቸው ወደ መንግሥት አዳራሹ ሄደው ጣሪያው ላይ በመውጣት ከዚህ አደጋ ሊያመልጡ ችለዋል። አንድም ምሥክር ሕይወቱን አላጣም።
ሆኖም በሜክሲኮ የሚገኙ 1,000 የሚያክሉ ምሥክሮች መንግሥት ወዳዘጋጃቸው መጠለያዎች ለመግባት ተገደው ነበር። ወደ 156 የሚጠጉ የወንድሞች ቤቶች ሙሉ በሙሉ የወደሙ ሲሆን 24ቱ ደግሞ ጉዳት ደርሶባቸዋል። በተጨማሪም ሰባት የመንግሥት አዳራሾች ሙሉ በሙሉ ወድመዋል።
በመሆኑም የይሖዋ ምሥክሮችና ጎረቤቶቻቸው የሚያስፈልጋቸውን በማሟላቱ ሥራ እንዲረዱ ስድስት የእርዳታ ኮሚቴዎች ተቋቋሙ። ምግብ፣ ልብስ፣ ብርድ ልብሶችና ሌሎች የእርዳታ ቁሳቁሶች በአስቸኳይ ተሰራጩ። እንዲያውም በአካባቢው የሚገኙ ባለ ሥልጣናት ስለ እርዳታ ሥራው በተገለጸላቸው ጊዜ “የጦር ሠራዊቱ እንኳ በዚህን ያክል ፍጥነት ሊያከናውነው አልቻለም” በማለት ተናግረዋል።
የይሖዋ ምሥክሮች ከረዥም ጊዜ ጀምሮ በሐቀኝነታቸው የታወቁ ናቸው፤ ይህ ደግሞ ጠቅሟቸዋል። ለምሳሌ ያህል የተወሰኑ ሰዎች በአካባቢያቸው ከሚገኙ ባለ ሥልጣናት እርዳታ በጠየቁ ጊዜ ባለ ሥልጣናቱ በሚኖሩበት መንደር የይሖዋ ምሥክሮች እንዳሉ ጠየቋቸው። የአዎንታ ምላሽ በሰጡ ጊዜ ባለ ሥልጣናቱ “አንደኛውን አምጡትና የእርዳታ ቁሳቁሶቹን ለእሱ እንሰጠዋለን!” አሏቸው።
በአካባቢው የሚገኝ አንድ የጉባኤ ሽማግሌ እንደሚከተለው ብሎ በመጻፍ ሁኔታውን ጠቅለል አድርጎ ገልጾታል:- “ምንም እንኳ ወንድሞች ይህን የመሰለ ከባድ ውድመት ያስከተለ አደጋ ቢያጋጥማቸውም አዎንታዊ አመለካከት ነበራቸው። በቅርብ በሚገኙ መንደሮች ውስጥ የሚኖሩ ብዙ ወንድሞች ሕይወታቸውን አደጋ ላይ ጥለው የምንመገበው ምግብና በመንፈሳዊ የሚያጠነክሩንን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎች አምጥተውልናል። ይሖዋን የምናመሰግንበት በርካታ ምክንያቶች አሉን።”
[በገጽ 20 ላይ የሚገኝ ካርታ/ሥዕል]
(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)
ሜክሲኮ
ጓቲማላ
ቤሊዝ
ኤል ሳልቫዶር
ሆንዱራስ
ኒካራጉዋ
ኮስታ ሪካ
[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ሆንዱራስ
◼ ግዋሴሪኬ ወንዝ
[በገጽ 22 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]
ኤል ሳልቫዶር
◼ በቺላንጌራ የሚገኝ አውራ መንገድ
◼ ከመንግሥት አዳራሹ ጋር የተረፉት ሆሴ ሌመስና ሴት ልጆቹ
◼ ሆሴ ሳንቶስ ኤርናንዴስ ከፈራረሰው ቤቱ ፊት ለፊት
[በገጽ 23 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]
ኒካራጉዋ
◼ ቴሊካ የደረሰው የመጀመሪያው የብስክሌተኞች ቡድን
◼ በኤል ጋያቦ የሚገኙ ምሥክሮች ታሽገው የተላኩላቸውን ምግቦች በማግኘታቸው ተደስተዋል
[በገጽ 24 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]
ኒካራጉዋ
◼ ፈቃደኛ ሠራተኞች ከሠሯቸው ብዙ ቤቶች መካከል የመጀመሪያውን ሲገነቡ
◼ በአካባቢው ባሉ ጉባኤዎች ውስጥ የሚገኙ ምሥክሮች ምግብ በማሸጉ ሥራ ተካፍለዋል
[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ጓቲማላ
◼ ሣራ ሰባት ልጆችን ከጭቃ ውስጥ በማውጣት ሕይወታቸውን አድናለች