የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • g99 9/8 ገጽ 27-29
  • የሌሎችን ፌዝ መቋቋም የምችለው እንዴት ነው?

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • የሌሎችን ፌዝ መቋቋም የምችለው እንዴት ነው?
  • ንቁ!—1999
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • የሚያፌዙበት ምክንያት
  • መልስ መስጠት
  • በግልጥ መናገር
  • የተፈተነ እምነት ጠንካራ ነው
  • ክርስቲያን ወጣቶች በእምነት ጥብቅ ሁኑ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1991
  • ወጣቶች—ይሖዋ ያደረጋችሁትን ሥራ አይረሳም!
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2003
  • አብረውኝ ለሚማሩት ልጆች መስበክ የምችለው እንዴት ነው?
    ንቁ!—2002
  • በትምህርት ቤት ስለ እምነቴ መናገር የሚያስፈራኝ ለምንድን ነው?
    ወጣቶች የሚጠይቋቸው ጥያቄዎችና ተግባራዊ መሆን የሚችሉ መልሶች፣ ጥራዝ 1
ለተጨማሪ መረጃ
ንቁ!—1999
g99 9/8 ገጽ 27-29

ወጣቶች የሚጠይቋቸው ጥያቄዎች ...

የሌሎችን ፌዝ መቋቋም የምችለው እንዴት ነው?

ከእኩዮቻቸው የተለየ ምግባር ወይም አለባበስ ያላቸው ወጣቶች የሰላ ትችት ይደርስባቸዋል። ይህ ሁኔታ በተለይ ከሌሎች ወጣቶች የተለየ ጠባይ በሚያሳዩ ክርስቲያን ወጣቶች ላይ ይደርሳል። ክርስቶስ ለእውነተኛ ተከታዮቹ “እኔን አሳደውኝ እንደ ሆኑ እናንተን ደግሞ ያሳድዱአችኋል” በማለት ተናግሮ አልነበረምን?—ዮሐንስ 15:20

ይህ ሁኔታ የይሖዋ ምሥክር የሆኑ ወጣቶችን የሚነካቸው እንዴት ነው? አንዳንዶቹ በዓላትን ባለማክበራቸው የተነሳ ይሾፍባቸዋል፣ ሌሎች ደግሞ ለባንዲራ ሰላምታ ባለመስጠታቸው ምክንያት ይተቻሉ። ብዛት ያላቸው ሌሎች ደግሞ አደገኛ ዕፆችን ባለመውሰዳቸው፣ ሃቀኞች በመሆናቸውና የመጽሐፍ ቅዱስን የሥነ ምግባር ደረጃዎች ጠብቀው በመኖራቸው የተነሳ ሌሎች ያፌዙባቸዋል።

ይህ ሁኔታ አዲስ ነገር አይደለም። እንዲያውም ሐዋርያው ጴጥሮስ በመጀመሪያው መቶ ዘመን ይኖሩ የነበሩ ክርስቲያኖችን “ከእነርሱ [ከአሕዛብ] ጋር ስለማትሮጡ እየተሳደቡ ይደነቃሉ” ብሏቸው ነበር። (1 ጴጥሮስ 4:4) አንድ ሌላ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ይህን ጥቅስ “ያለ ስማችሁ ስም ይሰጧችኋል” በማለት ተርጉሞታል።—ኖክስ

በያዝከው ሃይማኖታዊ አቋም ምክንያት ሰዎች አፊዘውብህ ያውቃሉ? ከሆነ ተስፋ አትቁረጥ። እንዲህ ዓይነቱ ተጽዕኖ የሚደርሰው በአንተ ላይ ብቻ አይደለም! እንዲሁም በእምነትህ ምክንያት የሚደርስብህን ፌዝ መቋቋም የምትችል መሆኑን ማወቅህ ያስደስትሃል።

የሚያፌዙበት ምክንያት

አንዳንዶች ከእነርሱ የተለየ እምነትና ጠባይ ባላቸው ሰዎች ላይ የሚያላግጡት ለምንድን ነው? አንዳንድ ጊዜ ፌዘኞች እንደ ጉልበተኞች ሁሉ በራስ የመተማመን መንፈስ ይጎድላቸዋል። በእኩዮቻቸው ዘንድ አድናቆት ለማትረፍ ሲሉ ይዘብቱብህ ይሆናል። ብዙዎቹ ብቻቸውን በሚሆኑበት ወቅት አንተን በግልጽ ለመዝለፍ ፍላጎቱም ሆነ ወኔው አይኖራቸውም።

በሌላው በኩል ደግሞ ጴጥሮስ እንደተናገረው አንዳንድ ፌዘኞች “ይደነቃሉ።” አዎን፣ በምግባርህ ግራ ይጋቡ ይሆናል። ለምሳሌ ያህል የይሖዋ ምሥክር ከሆንክ ከአንዳንድ በዓላት ጋር በተያያዙ እንቅስቃሴዎች አለመካፈልህ በጣም ሊያስገርማቸው ይችላል። ሥራዬ ብለው የይሖዋ ምሥክሮችን የሚቃወሙ ሰዎች የሚነዙት የተሳሳተ ወሬ ደርሷቸውም ሊሆን ይችላል።

ምክንያቱ ምንም ይሁን ምን መጥፎ የትችት ቃል ሲዘነዘርብህ “ያለ ጥንቃቄ የተነገረ ቃል እንደ ሰይፍ ያቆስላል” ከሚለው የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌ ጋር ሙሉ በሙሉ ሳትስማማ አትቀርም። (ምሳሌ 12:18 የ1980 ትርጉም) ይሁን እንጂ እንዲህ ያለውን ጎጂ ቃል የሚሰነዝሩብህ በቀጥታ አንተን ስለሚጠሉህ ላይሆን እንደሚችል ማወቅ ይኖርብሃል። ይህን የሚያደርጉት የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌ እንደሚለው ‘ያለ ጥንቃቄ ስለሚናገሩ’ ሊሆን ይችላል።

ያም ሆኖ ሲፌዝብን እንደተወጋ ቁስል ያህል ሊያመን ይችላል። እንዲያውም የሚወርድብህን የስድብ ናዳ ለማስቆም ስትል አቋምህን ለማላላት ትፈተን ይሆናል። ታዲያ በእምነትህ ምክንያት የሚደርስብህን ፌዝ መቋቋም የምትችለው እንዴት ነው?

መልስ መስጠት

ሐዋርያው ጴጥሮስ “በእናንተ ስላለ ተስፋ ምክንያትን ለሚጠይቁአችሁ ሁሉ መልስ ለመስጠት ዘወትር የተዘጋጃችሁ ሁኑ፣ ነገር ግን በየዋህነትና በፍርሃት [“በጥልቅ አክብሮት፣” NW] ይሁን” በማለት ክርስቲያኖችን መክሯል። (1 ጴጥሮስ 3:15) ለእምነትህ መልስ መስጠት ትችል ዘንድ ትክክለኛ እውቀት መቅሰምና ለእምነትህ መሠረት የሆኑትን ነገሮች ማወቅ ይኖርብሃል።

ከዚህም በተጨማሪ “በጥልቅ አክብሮት” ወይም ዘ ባይብል ኢን ቤዚክ ኢንግሊሽ እንዳስቀመጠው “ሳትኮራ” ለሌሎች ሐሳብህን እንዴት መግለጽ እንደምትችል መማር አለብህ። መጽሐፍ ቅዱስንና መጽሐፍ ቅዱስ የሚያስተምራቸውን ነገሮች ማወቅህ በሌሎች ላይ እንድትሠለጥን ሰበብ ሊሆንህ አይገባም። ከዚህ ይልቅ አገልግሎቱን በማስመልከት “የሚበልጡትን እንድጠቅም እንደ ባሪያ ራሴን ለሁሉ አስገዛለሁ” ብሎ የጻፈውን የሐዋርያው ጳውሎስን ዝንባሌ ለማዳበር መጣር ይኖርብሃል።—1 ቆሮንቶስ 9:19

ስለ እምነትህ መልስ መስጠት የሚያስፈራህ ከሆነ ተስፋ አትቁረጥ። በርካታ ወጣት ምሥክሮች ተመሳሳይ ችግር ነበረባቸው። “የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪ በነበርኩበት ጊዜ” ይላል ጀማል “በዓላትን ለምን እንደማላከብር ወይም ለባንዲራ ለምን ሰላምታ እንደማልሰጥ ወይም ሌላው ቀርቶ ለምን ከቤት ወደ ቤት እየሄድኩ እንደማገለግል ለሌሎች መግለጽ ያስቸግረኝ ነበር።” ታዲያ ምን ነገር ረዳው? “እነዚህን ነገሮች ጥሩ አድርጌ ማብራራት ወደምችልበት ደረጃ እስክደርስ ድረስ አባቴ ሳያቋርጥ እርዳታ ያደርግልኝ ነበር። ይህም ከፍተኛ ለውጥ አምጥቶልኛል።” አንተም ስለ እምነትህ ለሌሎች ማስረዳት የሚቸግርህ ከሆነ የአምላክን ቃል ሙሉ በሙሉ መረዳት ትችል ዘንድ ወላጆችህ ወይም በጉባኤ ውስጥ የሚገኙ ሌሎች የጎለመሱ ክርስቲያኖች እንዲረዱህ ማድረግ ትችላለህ።—ኤፌሶን 3:17-19

አንዲት የ16 ዓመት ወጣት ምሥክር መጽሐፍ ቅዱስን በፕሮግራም ማጥናት መጀመሯ ትምህርት ቤት ውስጥ በግልጽ ለመናገር የሚያስችል ድፍረት እንድታገኝ እንደረዳት ተናግራለች። “በፊት የይሖዋ ምሥክር በመሆኔ ምክንያት የክፍል ጓደኞቼ ሲያሾፉብኝ ምን ብዬ እንደምመልስ አላውቅም ነበር” በማለት ሳትሸሽግ ተናግራለች። “አሁን ግን የሙሉ ጊዜ ወንጌላዊ እንደመሆኔ መጠን መጽሐፍ ቅዱስን አዘውትሬ በደንብ ማጥናቴ ጥሩ መልስ እንድሰጥ አስችሎኛል። በመጠበቂያ ግንብ እና በንቁ! መጽሔቶች ላይ የሚወጡትን ርዕሰ ትምህርቶች ተከታትዬ ማንበቤ ለትምህርት ቤት ጓደኞቼ ስለ እምነቴ ለመናገር እንድችል ረድቶኛል።”

እርግጥ ነው፣ ችግሮች ሁሉ በአንድ ዓይነት መንገድ አይፈቱም። አንዱ ችግር መፍትሔ የሚያገኝበት መንገድ ከሌላው ይለያል። ሆኖም ክፉ ቃል ሲናገሩህ ተናድደህ ‘ክፉን በክፉ’ መመለስ አይገባህም። (ሮሜ 12:17-21) ለቀልድ ብሎ እንኳን መልሶ መሳደብ በእሳት ላይ ነዳጅ ከመጨመርና ተጨማሪ ስድብ ከማስከተል ሌላ የሚፈይደው ነገር የለም። በዚህ የተነሳ አንዳንዶች ስድቡን እንዳልሰሙ ሆነው ማለፉ የተሻለ ሆኖ አግኝተውታል።

አንዳንድ ጊዜ ሌሎችን ለማሳቅ ተብሎ ብቻ የሚነገር ቃል ሲሰነዘርብን ቅር ከመሰኘት ይልቅ አብሮ መሳቁ የተሻለ ሊሆን ይችላል። (መክብብ 7:9) የሚያፌዝብን ግለሰብ የተናገራቸው ቃላት ምንም ለውጥ እንዳላመጡ ሲያውቅ ማፌዙን እንዲያቆም ሊያደርገው ይችላል።—ከምሳሌ 24:29ና ከ1 ጴጥሮስ 2:23 ጋር አወዳድር።

በግልጥ መናገር

በአንዳንድ ወቅቶች እምነትህን በዘዴና አጠር ባለ መንገድ ማብራራት የምትችልበት አጋጣሚ ታገኝ ይሆናል። አንዲት የ13 ዓመት ልጅ እንዲህ ያለ ሙከራ አድርጋ አስደናቂ ውጤት አግኝታለች። እንዲህ ስትል ገልጻለች:- “ወደ ክፍል እየሄድኩ ሳለ የተወሰኑ ተማሪዎች ስለ ይሖዋ ምሥክሮች አንስተው ማሾፍ ጀመሩ። ላነጋግራቸው ፈልጌ የነበረ ቢሆንም ከአንደኛዋ ተማሪ በስተቀር ሁሉም እየሳቁብኝ አልፈውኝ ሄዱ።” የይሖዋ ምሥክር የሆነች ይህች ተማሪ በመቀጠል እንዲህ ብላለች:- “ጄሚ የምትባል አንዲት ልጅ ወደ እኔ ዞር አለችና በምድር ላይ በገነት ለዘላለም መኖር ትችላለህ የተባለ መጽሐፍ እንዳላት ነገረችኝ።a አብዛኛውን የመጽሐፉን ክፍል እንዳነበበችና እምነታችንን በሚመለከት ተጨማሪ ማብራሪያ ማግኘት እንደምትፈልግ ነገረችኝ። ከዚያም ጄሚ ከእኔ ጋር መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት ጀመረች።” ወጣቷ ምሥክር ይህ ያጋጠማት ነገር በጣም ስላበረታታት ሌሎች ወጣቶችንም ማነጋገር ጀመረች። “አብረውኝ የሚማሩ ፍላጎት ያሳዩ አራት ተማሪዎችን አዘውትሬ እያነጋገርኳቸው ሲሆን በቅርቡም ጥናት ይጀምራሉ ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ” በማለት ተናግራለች።

ከተወሰኑ ዓመታት በፊት በአፍሪካዊቷ አገር በላይቤርያ የሚኖር አንድ ተማሪ ተመሳሳይ ተሞክሮ ገጥሞታል። የሳይንስ ትምህርት እየተማሩ ሳለ የይሖዋ ምሥክር እንደመሆኑ መጠን የሚያምነው በአዝጋሚ ለውጥ ሳይሆን በፍጥረት እንደሆነ በአክብሮት ገለጸ። መጀመሪያ ላይ አብዛኞቹ የክፍሉ ተማሪዎች አምርረው ተቃወሙት። ሆኖም እምነቱን ለክፍሉ እንዲገልጽ መምህሩ ፈቀደለት። ከዚያም መምህሩ ሕይወት እንዴት ተገኘ? በአዝጋሚ ለውጥ ወይስ በፍጥረት?b የተባለውን መጽሐፍ ወሰደ።

መምህሩ መጽሐፉን ካነበበ በኋላ ለተማሪዎቹ “ይህ ተወዳዳሪ የሌለው መጽሐፍ ነው። እስካሁን ካነበብኳቸው ስለ ፍጥረት የሚናገሩ ምርጥ የሳይንስ መጽሐፎች አንዱ ነው” በማለት ተናገረ። ከዚያም ይህን ፍጥረት የተባለውን መጽሐፍ በሚቀጥሉት ሁለት ሴሚስተሮች ከዋነኛ የመማሪያ መጽሐፋቸው ጋር ለማስተማሪያነት የሚጠቀምበት በመሆኑ ምሥክር ከሆነው ተማሪ ለራሳቸው የሚሆን ቅጂ እንዲወስዱ ነገራቸው። በዚህ መንገድ በደርዘን የሚቆጠሩ መጻሕፍት ተበረከቱ፤ እንዲሁም ብዙዎቹ ተማሪዎች ለይሖዋ ምሥክሮች የነበራቸው አመለካከት ተለወጠ!

የተፈተነ እምነት ጠንካራ ነው

እርግጥ ነው፣ አንዳንድ ጊዜ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተውን አቋምህን በማይጋሩ ወይም በማይረዱልህ ሰዎች ብቻ እንደተከበብክ ሆኖ ሊሰማህ ይችላል። (ከመዝሙር 3:1, 2 ጋር አወዳድር።) ስለዚህ የአንተ ዓይነት እምነት ካላቸው ጋር ወዳጅነት ለመመሥረት ጥረት ማድረጉ ጥበብ ይሆናል። (ምሳሌ 27:17) ይሁን እንጂ በትምህርት ቤትህም ሆነ በምትኖርበት አካባቢ የአንተ ዓይነት እምነት ያለው ወጣት ባይኖርስ?

እንደዚያ ከሆነ ከሁሉም የላቀው ወዳጅህ ይሖዋ አምላክ እንደሆነና እርሱም ሊደግፍህ እንደሚችል አስታውስ። ሰይጣን ዲያብሎስ ለብዙ ሺህ ዓመታት በይሖዋ ላይ ሲዘብት ኖሯል። ስለሆነም በእምነትህ ጸንተህ ስትቆም የይሖዋ ልብ ደስ እንደሚሰኝ እርግጠኛ ልንሆን እንችላለን። እንዲህ ያለው አካሄድ ‘ለሚሰድበው ለሰይጣን መልስ መስጠት እንዲችል’ አጋጣሚ ይከፍትለታል።’—ምሳሌ 27:11

አልፎ አልፎ እምነትህ ፈተና ላይ ሊወድቅ እንደሚችል ማወቅ ይኖርብሃል። (2 ጢሞቴዎስ 3:12) ሆኖም የተፈተነ እምነት “በእሳት ምንም ቢፈተን ከሚጠፋው ወርቅ ይልቅ አብልጦ የሚከብር” እንደሆነ ሐዋርያው ጴጥሮስ ማረጋገጫ ሰጥቶናል። (1 ጴጥሮስ 1:6-8) ስለዚህ በእምነትህ የተነሳ ነቀፋ ሲሰነዘርብህ እምነትህን ለማጠንከርና ጽናትህን ለማሳየት እንደሚያስችል አጋጣሚ አድርገህ ተመልከተው። መጽናት “ተቀባይነት ያለው አቋም” እንደሚያስገኝ ሐዋርያው ጳውሎስ ጽፏል። (ሮሜ 5:3-5 NW) አዎን፣ የይሖዋን ሞገስ ለማግኘት ያለህ ምኞት በእምነትህ የተነሳ የሚደርስብህን ፌዝ ለመቋቋም በቆራጥነት ወደፊት እንድትገፋ ይረዳሃል!

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

a ኒው ዮርክ በሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስ እና ትራክት ማኅበር የታተመ።

b ኒው ዮርክ በሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስ እና ትራክት ማኅበር የታተመ።

[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ስለ እምነትህ መልስ መስጠት ትችላለህን?

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ