“ሁሉም የብልጽግናው ተቋዳሽ አልሆነም”
የተባበሩት መንግሥታት የልማት ፕሮግራም ወይም ዩ ኤን ዲ ፒ ያጠናቀረው ዓመታዊው የ1998 የተባበሩት መንግሥታት ሰብዓዊ እድገት ሪፖርት ይህ ነው በማይባል መጠን በዓለም ላይ በታየው የፍጆታ ጭማሪ ላይ ትኩረት አድርጎ ነበር። በዓለም አቀፍ ደረጃ በዛሬው ጊዜ ለፍጆታ ዕቃዎች የሚውለው ወጪ በ1950 ከነበረው ጋር ሲነጻጸር በስድስት እጥፍ የሚበልጥ ሲሆን በ1975 ከነበረው ደግሞ በሁለት እጥፍ እንደሚበልጥ ሪፖርቱ ገልጿል። ይህን የመሰለ ከፍተኛ የፍጆታ ጭማሪ ቢኖርም የዩ ኤን ዲ ፒ ዋና ዲሬክተር የሆኑት ጄምስ ጉስታቭ ስፔት “ሁሉም የብልጽግናው ተቋዳሽ አልሆነም” ሲሉ ገልጸዋል።
ነገሩን በምሳሌ ለማስረዳት:- ከዓለም ሕዝብ መካከል 20 በመቶ የሚሆኑት እጅግ ባለጸጋ የሆኑ ሰዎች በዓለም ላይ ካሉት 20 በመቶ የሚሆኑ የመጨረሻ ድሆች ጋር ሲነጻጸሩ የዓሣ ፍጆታቸው በ7 እጥፍ ይበልጣል። በተጨማሪም 20 በመቶ የሚሆኑት የዓለማችን ባለጸጎች 20 በመቶ ከሚሆኑት የመጨረሻ ድሆች ጋር ሲነጻጸሩ የሥጋ ፍጆታቸው በ11 እጥፍ፣ የኤሌትሪክ ፍጆታቸው በ17 እጥፍ፣ የስልክ መስመራቸው በ49 እጥፍ፣ የወረቀት ፍጆታቸው በ77 እጥፍ እንዲሁም ያላቸው መኪና ቁጥር በ149 እጥፍ ይበልጣል።
የተመድ ራዲዮ እነዚህን ግኝቶች አስመልክቶ ሐሳብ ሲሰጥ የምድራችንን የተፈጥሮ ሀብት መመናመን ለመቀነስ በኢንዱስትሪ የበለጸገው ዓለም የፍጆታ አጠቃቀም ዘይቤውን መቀየር እንዳለበት ገልጿል። ከዚህ በተጓዳኝ የዓለማችን ድሀ አገሮች ምድራችን ካላት የተፈጥሮ ሀብት ይበልጥ ተጠቃሚ መሆን እንዲችሉ ባለጸጋ አገሮች ካላቸው ሀብት ውስጥ ተጨማሪ ድርሻ መስጠት አለባቸው። መሰጠት ያለበት ገንዘብ ምን ያህል ነው?
ሚስተር ስፔት በኢንዱስትሪ የበለጸጉ አገሮች አሁን ለልማት የሚሰጡትን እርዳታ መጠን በእጥፍ ማለትም በዓመት ከ50 ቢልዮን የአሜሪካ ዶላር ወደ 100 ቢልዮን ዶላር ቢያሳድጉ በዓለም ዙሪያ የሚኖሩ ድሆች ባጠቃላይ ምግብ፣ ሕክምና፣ ትምህርትና መጠለያ ማግኘት እንደሚችሉ አስልተው ደርሰውበታል። ተጨማሪ 50 ቢልዮን የአሜሪካ ዶላር ሲባል በጣም ብዙ ገንዘብ ይመስል ይሆናል። ይሁን እንጂ “ይህ ገንዘብ አውሮፓ በየዓመቱ ለሲጋራ ከምታውለው ገንዘብ ጋር ተመጣጣኝ ሲሆን ዩናይትድ ስቴትስ ደግሞ በዛሬው ጊዜ ለአልኮል መጠጦች ከምታውለው ውስጥ ግማሽ መሆኑ ነው” ሲሉ ስፔት አስገንዝበዋል።
ይህች ፕላኔት የያዘችው የተፈጥሮ ሀብት በተሻለ ሁኔታ እኩል እንዲዳረስ የተቀናጀ ጥረት ከተደረገ አስከፊ የሆነውን ድህነት ወደ ድምዳሜ ለማምጣት ከፍተኛ እገዛ እንደሚያደርግ ግልጽ ነው። ይህ ግቡን እንዲመታ ምን መደረግ አለበት? አንድ የተባበሩት መንግሥታት ባለሥልጣን እንዲህ ብለዋል:- “በዚያም ሆነ በዚህ አስፈላጊው ነገር የልብ፣ የአስተሳሰብና የፍላጎት ለውጥ ማድረግ ነው።” ብዙዎች በዚህ ቢስማሙም እንኳ ዛሬ ያሉት ፖሊሲ አርቃቂ ድርጅቶች የቱንም ያህል በጎ ዓላማ ያላቸው ቢሆኑ እንደ ስግብግብነት ያሉ ባሕርያትን ሊያስወግዱ ይቅርና እንዲህ ዓይነቶቹን ለውጦች ማምጣት እንደማይችሉ ይገነዘባሉ።
ሆኖም የሰው ልጅ ቤተሰብና የፕላኔታችን የወደፊት ዕጣ ለሚያሳስባቸው ሰዎች የሚሆን ተስፋ አለ። የምድር ፈጣሪ ሰዎች የገጠሟቸውን ችግሮች ከሥረ መሠረቱ ለማስወገድ ቃል መግባቱን ማወቁ ያበረታታል። መዝሙራዊው እንዲህ ሲል ተንብዮአል:- “ምድር ፍሬዋን ሰጠች፤ እግዚአብሔር አምላካችንም ይባርከናል። በምድር ውስጥ በተራሮች ላይ መጠጊያ ይሆናል።” (መዝሙር 67:6፤ 72:16) አዎን፣ በዚያን ጊዜ እያንዳንዱ የምድር ነዋሪ “የብልጽግናው ተቋዳሽ” ይሆናል!