የተከለከሉ ዕፆች ሕይወትህን የሚነኩት እንዴት ነው?
ዕፆች አንድን ምሰሶ በልቶ ከጥቅም ውጭ እንደሚያደርግ ጥንጣን መላውን የኅብረተሰብ መዋቅር ሸርሽረው ከጥቅም ውጭ ሊያደርጉ ይችላሉ። ሰብዓዊው ኅብረተሰብ ተገቢ እንቅስቃሴውን እንዲያከናውን ከተፈለገ ጽኑ መሠረት ያላቸው ቤተሰቦች፣ ጤነኛ ሠራተኞች፣ እምነት የሚጣልባቸው መንግሥታት፣ ሐቀኛ ፖሊሶችና ሕግ አክባሪ ዜጎች ሊኖሩት ይገባል። ዕፆች እነዚህን መሠረታዊ የሆኑ የኅብረተሰብ ክፍሎች በሙሉ ያነቅዛሉ።
መንግሥታት ዕፆች ከሕክምና ውጭ ለሆነ ጠቀሜታ እንዳይውሉ ካገዱባቸው ምክንያቶች አንዱ በዜጎቻቸው ጤና ላይ ጉዳት ስለሚያደርሱ ነው። በየዓመቱ በሺህ የሚቆጠሩ የዕፅ ሱሰኞች ከመጠን ያለፈ ዕፅ በመውሰዳቸው ምክንያት ይሞታሉ። ሌሎች በጣም ብዙ ሰዎች ደግሞ በኤድስ ምክንያት ይሞታሉ። እንዲያውም ኤች አይ ቪ ከያዛቸው የዓለም ሰዎች መካከል 22 በመቶ የሚሆኑት ራሳቸውን በቫይረሱ በተበከለ መርፌ የወጉ ዕፅ ወሳጆች ናቸው። በቅርቡ በተደረገ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጉባኤ ላይ የኳታሩ ናስር ቢን ሐማድ አል-ከሊፋ “ሕገ ወጥ በሆነው የዕፅ ንግድ ምክንያት ይህች እንደ ትንሽ መንደር የሆነችው ዓለማችን በሚልዮን ለሚቆጠሩ ሰዎች የጋራ መቃብር ልትሆን ተቃርባለች” በማለት ያስጠነቀቁት ያለ በቂ ምክንያት አይደለም።
ይሁን እንጂ ችግሩ በተጠቃሚዎቹ ላይ በሚደርሰው የጤና እክል ብቻ ተወስኖ የሚቀር አይደለም። በዩናይትድ ስቴትስ ከሚወለዱት ጠቅላላ ሕፃናት መካከል 10 በመቶ የሚሆኑት በእናታቸው ማሕጸን እንዳሉ ለተከለከሉ ዕፆች፣ አብዛኛውን ጊዜ ለኮኬይን፣ የተጋለጡ ናቸው። የእነዚህ ሕፃናት ችግር ሱሱ በመቋረጡ ምክንያት በሚደርስባቸው ሥቃይ የሚቆም አይደለም። ምክንያቱም በማሕጸን ውስጥ እያሉ ለዕፅ መጋለጣቸው አእምሮአዊና አካላዊ ጉዳት ሊያስከትልባቸው ይችላል።
በዕፅ ሳቢያ በቀላሉ የሚገኝ የሚያማልል ገንዘብ
ከጨለመ በኋላ በአካባቢህ መዘዋወር አያስፈራህም? የሚያስፈራህ ከሆነ ሥጋት ያሳደሩብህ ምናልባት የዕፅ አዘዋዋሪዎች ይሆናሉ። አፈናና ዝርፊያ እንዲሁም የመንገድ ላይ አምባጓሮ ከዕፆች ጋር የማይነጣጠሉ ሆነዋል። የዕፅ ተጠቃሚዎች አብዛኛውን ጊዜ ሱሳቸው የሚጠይቅባቸውን የገንዘብ ወጪ የሚሸፍኑት በወንጀል ወይም በዝሙት አዳሪነት ነው። በተጨማሪም ተቀናቃኝ የሆኑ የወንጀለኞች ቡድኖች በዕፅ ስርጭት ላይ ያላቸው ቁጥጥር ከእጃቸው እንዳይወጣ እርስ በርሳቸው ይገዳደላሉ። በብዙ ከተሞች ፖሊሶች አብዛኞቹ የግድያ ወንጀሎች የሚፈጸሙት ከዕፆች ጋር በተያያዙ ምክንያቶች እንደሆነ ያምናሉ።
በአንዳንድ አገሮች ሰርጎ ገቦች በጣም አትራፊ ከሆነው የዕፅ ንግድ ተካፋይ ለመሆን ኃይል መጠቀም እንደሚያስፈልግ ተገንዝበዋል። በደቡብ አሜሪካ የሚገኝ አንድ የደፈጣ ተዋጊዎች ቡድን በአሁኑ ጊዜ ከጠቅላላ ገቢው ግማሹን የሚያገኘው ለዕፅ አዘዋዋሪዎች ሽፋንና ጥበቃ በመስጠት ነው። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዓለም አቀፍ የዕፅ ቁጥጥር ፕሮግራም “በጣም ከባድ ከሆኑት የሃይማኖትና የጎሳ ጦርነቶች መካከል አንዳንዶቹ የሚካሄዱት በሕግ ከተከለከሉ ዕፆች ንግድ በሚገኘው ገቢ ነው” ሲል ዘግቧል።
ዕፅ ሲወሰድ የሚያስከትለው አሳዛኝ ውጤት
ዕፅ የሚወስዱ ሰዎች በሌሎች መንገዶችም ጎዳናዎችን አደገኛ ያደርጋሉ። “ማሪዋና ወይም ኤል ኤስ ዲ ወስዶ መኪና ማሽከርከር ሰክሮ የማሽከርከርን ያህል አደገኛ” እንደሆነ ማይክል ክሮነንዌተር ድራግስ ኢን አሜሪካ በተባለው መጽሐፋቸው ላይ ገልጸዋል። ዕፅ የሚወስዱ ሰዎች በሥራ ቦታቸው ላይ አደጋ የማድረስ ዕድላቸው ከሌሎቹ ከሦስት እስከ አራት እጥፍ የሚበልጥ መሆኑ ምንም አያስገርምም።
ይሁን እንጂ ዕፆች በቤት ውስጥ የሚያደርሱት ጉዳት ከሁሉም ይበልጣል። ወርልድ ድራግ ሪፖርት “ዕፅ መውሰድና የተመሰቃቀለ የቤተሰብ ሕይወት በአብዛኛው የማይነጣጠሉ ነገሮች ናቸው” ይላል። ቀልባቸውን በሙሉ የዕፅ ሱሳቸውን በማርካት ላይ ያሳረፉ ወላጆች ልጆቻቸውን በተረጋጋ ሁኔታ ማሳደግ አይችሉም። በአንድ ሕፃን የመጀመሪያ ሳምንታት ዕድሜ ውስጥ በጣም አስፈላጊ የሆነው የልጅና የወላጅ ትስስር ሊታገድ ይችላል። በተጨማሪም ሱሰኛ ወላጆች ከዕዳ ስለማይላቀቁ ከጓደኞቻቸውና ከቤተሰቦቻቸው ሊሰርቁ ወይም ከሥራ ሊባረሩ ይችላሉ። እንዲህ ባለው ሁኔታ የሚያድጉ ብዙ ልጆች የጎዳና ተዳዳሪዎች ይሆናሉ ወይም ከዚያም አልፈው ራሳቸው የዕፅ ሱሰኛ ወይም አስተላላፊ ይሆናሉ።
ከዚህም በላይ ዕፅ አላግባብ መውሰድ የትዳር ጓደኛን ወይም ልጆችን ወደ መደብደብ ሊመራ ይችላል። ኮኬይን በተለይ ከአልኮል ጋር ሲወሰድ በጣም ጨዋ የነበረውን ሰው እንኳን ጠበኛ ሊያደርግ ይችላል። በካናዳ አገር በኮኬይን ወሳጆች ላይ በተደረገ አንድ ጥናት ጥያቄ ከቀረበላቸው መካከል 17 በመቶ የሚሆኑት ዕፁን ከወሰዱ በኋላ ጠበኛ እንደሚሆኑ ተናግረዋል። በተመሳሳይ በኒው ዮርክ ከተማ በሕፃናት ላይ ስለሚፈጸም በደል የተጠናቀረ ሪፖርት እንደሚያመለክተው ተደብድበው ከተገደሉ ልጆች መካከል 73 በመቶ የሚሆኑት ዕፅ የሚወስዱ ወላጆች ያሏቸው ናቸው።
ሙስና እና ብክለት
ዕፆች የሚያደርሱት ጉዳት በቤተሰብ ብቻ ተወስኖ የሚቀር አይደለም። በመንግሥታት ላይም ደርሷል። የመንግሥታትን መዋቅር በመመረዝ ላይ የሚገኘው ግን ዕፁ ራሱ ሳይሆን ከዕፅ የሚገኘው ገንዘብ ነው። የአንድ ደቡባዊ አሜሪካ አገር አምባሳደር “ዕፆች የመንግሥት ባለ ሥልጣኖች፣ ፖሊሶችና የጦር ሠራዊት አባላት በሙስና እንዲዘፈቁ አድርገዋል” በማለት አማርረዋል። በመቀጠልም ከእጅ ወደ አፍ በሆነ ኑሮ የሚማቅቁት ባለ ሥልጣኖች እንዲሁም የፖሊስና የጦር ሠራዊት አባላት የዕፅ አዘዋዋሪዎች የሚሰጧቸውን መደለያ አልቀበልም ማለት “በጣም አዳጋች” ይሆንባቸዋል ብለዋል።
በየአገሩ ዳኞች፣ ከንቲባዎች፣ ፖሊሶችና የዕፅ ቁጥጥር ሠራተኞች በሙስና መረብ ተተብትበዋል። ለምርጫ በሚወዳደሩበት ጊዜ ከዕፅ ቱጃሮች የመወዳደሪያ ገንዘብ አግኝተው የነበሩ ፖለቲከኞች በዕፅ ስርጭት ላይ ጠንከር ያለ እርምጃ እንዲወሰድ ጥያቄ በሚቀርብበት ጊዜ ጆሮ ዳባ ልበስ ይላሉ። በድፍረት የዕፅ አዘዋዋሪዎችን በመዋጋታቸው ምክንያት የተገደሉ ሐቀኛ ባለሥልጣኖች ጥቂቶች አይደሉም።
አፈራችን፣ ደናችንና በእነዚህ የሚኖሩት ሕያዋን ፍጥረታት ሳይቀሩ በዓለም አቀፉ የዕፅ አለንጋ ተገርፈዋል። አብዛኛው ኦፕየምና ኮኬይን የሚመረተው በቀላሉ በአካባቢ ላይ በሚደርስ ጉዳት ሊጠቁ በሚችሉት ሁለት የዓለማችን ክፍሎች ማለትም በምዕራብ አማዞንና በደቡብ ምሥራቅ እስያ ጥቅጥቅ ያሉ ደኖች አካባቢ ነው። በእነዚህ አካባቢዎች የደረሰው ውድመት በቀላሉ የሚገመት አይደለም። ሕገ ወጥ የሆኑ የዕፅ ሰብሎችን ለማጥፋት የሚደረገው አስመስጋኝ ጥረት እንኳን መርዛማ ፀረ አረም መድኃኒቶችን ስለሚጠቀም ከባድ ጉዳት ያደርስባቸዋል።
የሚጎዳው ማን ነው?
በዕፆች ምክንያት ለሚደርሰው ጉዳት የተጋለጠው ማን ነው? ሁላችንም ነን። አዎን፣ በዕፆች ምክንያት የሚደርሰው የምርታማነት መቀነስ፣ የሕክምና ወጪ፣ በንብረት ላይ የሚደርስ ሥርቆት ወይም ጉዳት፣ ለሕግ ማስከበሪያ የሚወጣው ወጪ ሁላችንንም የሚነካ ነው። “በዕፆች ምክንያት ከሥራ በሚቀሩ ሠራተኞች፣ በሚደርሱ አደጋዎችና የሕክምና ወጪዎች፣ እንዲሁም ለሠራተኞች በሚከፈል ካሣ ምክንያት በአሜሪካ የንግድ ድርጅቶችና ኢንዱስትሪዎች ላይ በየዓመቱ የሚደርሰው ኪሣራ ከ75 እስከ 100 ቢልዮን ዶላር” እንደሚደርስ የዩናይትድ ስቴትስ የሥራ ጉዳይ አስተዳደር ያወጣው ሪፖርት አመልክቷል።
ይህ ሁሉ ገንዘብ የሚወጣው ከግብር ከፋዮችና ከሸማቾች ኪስ ነው። በ1995 በጀርመን አገር የተደረገ አንድ ጥናት በዚያች አገር ሕገ ወጥ ዕፅ የሚያስከትለው ጠቅላላ ዓመታዊ ወጪ ለእያንዳንዱ ዜጋ ሲካፈል በነፍስ ወከፍ 120 ዶላር እንደሚደርስ አመልክቷል። በዩናይትድ ስቴትስ ቁጥሩ ከዚህ ከፍ ያለ ሲሆን 300 ዶላር ይደርሳል።
ይሁን እንጂ ከዚህ በጣም የሚበልጠው ኪሣራ ዕፆች በማህበረሰቡ ላይ የሚያደርሱት ጉዳት ነው። በዕፅ ምክንያት የሚደርሰው የብዙ ቤተሰቦች መፈራረስ፣ በልጆች ላይ የሚደርሰው ግፍ፣ በብዙ ባለ ሥልጣኖች ዘንድ የሚታየው ሙስና፣ የበርካታ ሰዎች በለጋ ዕድሜ መቀጨት በምን ያህል ገንዘብ ሊተመን ይችላል? ይህ ሁሉ በሰዎች ሕይወት ላይ ምን ያህል ጉዳት አድርሷል? የሚቀጥለው ርዕስ ዕፆች በሚወስዷቸው ሰዎች ሕይወት ላይ የሚያደርሱትን ጉዳት ይመረምራል።
[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]
ዕፅና ወንጀል
ዕፆች ቢያንስ በአራት መንገዶች ከወንጀል ጋር ዝምድና አላቸው፦
1. ፆችን አለፈቃድ ይዞ መገኘትና ማዘዋወር በሁሉም የዓለም አገሮች ማለት ይቻላል፣ ወንጀል ነው። በዩናይትድ ስቴትስ ብቻ ፖሊስ በየዓመቱ አንድ ሚልዮን የሚያክሉ ሰዎችን በዕፅ ወንጀል ይዞ ያስራል። በአንዳንድ አገሮች የዕፅ ወንጀሎች በጣም በመብዛታቸው ምክንያት ፖሊሶችና ፍርድ ቤቶች ሁሉንም መዳኘት ከአቅም በላይ ሆኖባቸዋል።
2. ዕፆች በጣም ውድ ስለሆኑ ሱሰኞቹ ጥማቸውን የሚያረኩበት ገንዘብ ለማግኘት ሲሉ አብዛኛውን ጊዜ ወንጀል ይፈጽማሉ። አንድ የኮኬይን ሱሰኛ ሱሱን ለማርካት በሳምንት እስከ 1,000 ዶላር የሚደርስ ገንዘብ ሊያስፈልገው ይችላል! ዕፆች ሥር በሰደዱባቸው አካባቢዎች ሁሉ ዝርፊያ፣ ቅሚያና ዝሙት አዳሪነት ተስፋፍቶ መገኘቱ አያስገርምም።
3. በምድር ላይ ከሚካሄዱት እጅግ አስከፊ የሆኑ ንግዶች አንዱ የሆነውን የዕፅ ዝውውር ለማቀላጠፍ ሲባል የሚፈጸሙ ሌሎች ወንጀሎችም አሉ። ወርልድ ድራግ ሪፖርት እንደሚገልጸው “የተከለከሉ ዕፆች ኢኮኖሚና የተደራጀ ወንጀል እርስ በርሱ የሚደጋገፍ ነው።“ የዕፅ አዘዋዋሪዎች ዕፆችን አላንዳች እንቅፋት ከቦታ ወደ ቦታ ለማዘዋወር ሲሉ ባለ ሥልጣኖችን ይደልላሉ ወይም ያስፈራራሉ። እንዲያውም አንዳንዶቹ የራሳቸው ጦር ሠራዊት እስከ ማደራጀት ደርሰዋል። በተጨማሪም የዕፅ ቱጃሮች የሚያገኙት የደለበ ትርፍ ራሱ ችግር ፈጣሪ ሆኗል። እጃቸው የሚገባው ከፍተኛ ገንዘብ ሕጋዊ ሽፋን ካላገኘ በቀላሉ ሊያስይዛቸው ስለሚችል ባንኮችና ጠበቆች የገንዘቡን ዱካ እንዲያጠፉ ይደረጋል።
4. ዕፆቹ የሚያስከትሉት ውጤት ራሱ ወንጀል ወደ መፈጸም ሊመራ ይችላል። የቤተሰብ አባሎች በለየላቸው የዕፅ ሱሰኞች ሊጠቁ ይችላሉ። በእርስ በርስ ጦርነት በተጎሳቆሉ አንዳንድ የአፍሪካ አገሮች በዕፅ የሰከሩ ወጣት ወታደሮች በጣም አሰቃቂ የሆኑ ወንጀሎች ፈጽመዋል።
[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የአንድ ሕፃን ሕይወት እናቱ በምትወስደው ዕፅ ሊነካ ይችላል
[ምንጭ]
SuperStock