የተበላሸና የጠፋ ሕይወት
ዶክተር ኤሪክ ኔስለር “ዕፆች እንደ ከባድ መዶሻ ናቸው” ይላሉ። በእርግጥም ከእነዚህ በመዶሻ ከተመሰሉ ዕፆች አንዱን ለአንድ ጊዜ ብቻ መውሰድ ለሞት ሊያደርስ ይችላል። “ለምሳሌ ያህል ክራክ ኮኬይን ለመጀመሪያ ጊዜ የወሰደውን ሰው እንደሚገድል የታወቀ ነው” ይላል ድራግስ ኢን አሜሪካ የተባለው መጽሐፍ።
በስፋት የተሠራጩት አዲሶቹ ሰው ሠራሽ ዕፆችም በአደገኛነታቸው ከቀድሞዎቹ ያነሱ አይደሉም። “‘በቅጥ የለሽ’ ፓርቲዎች ላይ ዕፆችን የሚገዙ የዋህ ወጣቶች አንጎላቸው በምን ዓይነት ኬሚካላዊ ውህድ እንደሚደበደብ አያውቁም” በማለት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ወርልድ ድራግ ሪፖርት ያስጠነቅቃል። ይሁን እንጂ የሚከተሉት ምሳሌዎች እንደሚያሳዩት አብዛኞቹ ወጣቶች የዕፅ ሱሰኛ የሚሆኑት ቀስ በቀስ ነው።
“ከሕልውና መሸሽ”
ከዘጠኝ ልጆች አንዱ የሆነው ፔትሮa የተወለደው በስፔይን አገር በኮርዶባ ከተማ ወሮበሎች በሚበዙበት አካባቢ ነው። አባቱ የአልኮል ሱሰኛ ስለነበረ በልጅነቱ ብዙ ችግር አሳልፏል። ፔትሮ 14 ዓመት እንደሆነው የአክስቱ ልጅ ከሐሺሽ ጋር ያስተዋውቀዋል። በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ የሐሺሽ ሱሰኛ ይሆናል።
ፔትሮ “ዕፅ መውሰድ የጊዜ ማሳለፊያ፣ ከሕልውና መሸሺያና የአንድ ቡድን አባል የመሆኛ መንገድ ነው” ይላል። “15 ዓመት እንደሆነኝ በሐሺሽ ላይ ኤል ኤስ ዲ እና አምፊታሚን አክዬ መውሰድ ጀመርኩ። ከሁሉም በጣም የምወደው ዕፅ ኤል ኤስ ዲ ሲሆን ይህን ዕፅ መግዣ ገንዘብ ለማግኘት የትርፍ ጊዜ ዕፅ አሻሻጭ ሆንኩ። በዋነኛነት የማዘዋውረው ሐሺሽ ነበር። አንድ ጊዜ ኤል ኤስ ዲ ከመጠን አሳልፌ በመውሰዴ ሙሉውን ሌሊት ሳልተኛ አደርኩ። ያበድኩ መስሎኝ ነበር። የደረሰብኝ ሁኔታ በጣም አስፈራኝ። ዕፅ መውሰድ ከቀጠልኩ መታሠሬ ወይም መሞቴ እንደማይቀር ተሰማኝ። ይሁን እንጂ ለዕፆች ያለኝ ጥማት ይህን መሰሉን ፍርሃት ወደ ጎን ገሸሽ አደረገብኝ። ከባድ የሆነ የኤል ኤስ ዲ ሱስ ስለያዘኝ የምወስደው ዕፅ መጠን ከቀን ወደ ቀን እየጨመረ ሄደ። ዕፁን ከወሰድኩ በኋላ የሚሰማኝ ስሜት በጣም አስፈሪ ቢሆንም ማቆም አልቻልኩም። እንዴት መላቀቅ እንደምችል ግራ ገባኝ።
“ኤል ኤስ ዲ በቀላሉ የሚገኝ ዕፅ አልነበረም። ስለዚህም የጌጣ ጌጥ ሱቆችን መዝረፍ፣ የቱሪስቶችን ቦርሳ መንጠቅ፣ የመንገደኞችን ሰዓትና ቦርሳ መስረቅ ተማርኩ። አሥራ ሰባት ዓመት ሲሞላኝ በምኖርበት አካባቢ የታወቅኩ የዕፅ አስተላላፊ ከመሆኔም በላይ አንዳንድ ጊዜም በጦር መሣሪያ በሚፈጸም ዘረፋ መካፈል ጀመርኩ። በምኖርበት አካባቢ በጠበኛነትና በወንጀለኛነት በጣም የታወቅኩ መሆኔ ኤል ቶርሲዶ የሚል የቅጽል ስም ሊያተርፍልኝ ችሏል። ‘ጠማማው’ ማለት ነው።
“ዕፅ ከአልኮል ጋር ሲቀናጅ ጠባይህ ፈጽሞ ይለወጥና አብዛኛውን ጊዜ ጠበኛ ትሆናለህ። ተጨማሪ ዕፅ ለመውሰድ ያለህ ፍላጎት በጣም ጠንካራ ስለሚሆን ሕሊናህ ሙሉ በሙሉ ይሸነፋል። ሕይወት ማምለጫ የሌለው እሽክርክሪት ይሆንብሃል። የምትኖረው ከዕፅ ለምታገኘው የሚያስፈነድቅ ስሜት ብቻ ይሆናል።”
“በዕፅ ዓለም ሙሉ በሙሉ ተዋጥኩ”
የፔትሮ ባለቤት አና ያደገችው በስፔይን አገር ጥሩ የቤተሰብ እንክብካቤ እየተደረገላት ነበር። አና 14 ዓመት እንደሆናት በአቅራቢያዋ በነበረ ሌላ ትምህርት ቤት ከሚማሩ ሐሺሽ የሚያጨሱ ወንዶች ልጆች ጋር ተገናኘች። በመጀመሪያ እንግዳ የሆነ ጠባያቸው በጣም አስጠልቷት ነበር። ይሁን እንጂ የአና ጓደኛ የሆነችው ሮሳ አንደኛውን ልጅ ትወድ ነበር። ልጁ ሮሳን ሐሺሽ ማጨስ ምንም ዓይነት ጉዳት እንደማያስከትልባትና እንዲያውም በጣም እንደሚያስደስታት በመግለጽ አሳመናት። ሮሳም ዕፁን ከሞከረች በኋላ አና እንድታጨሰው ሰጠቻት።
አና “ሳጨሰው ደስ የሚል ስሜት ተሰማኝ። በጥቂት ሳምንት ውስጥ በየቀኑ ሐሺሽ ማጨስ ጀመርኩ” ትላለች። “ከአንድ ወር በኋላ ሐሺሽ ብቻውን ስሜቴን ሊያነሳሳ ባለመቻሉ ከሐሺሽ ጋር አምፊታሚን መውሰድ ጀመርኩ።
“ብዙም ሳይቆይ እኔና ጓደኞቼ በዕፁ ዓለም ሙሉ በሙሉ ተዋጥን። ምንም የሕመም ስሜት ሳይሰማው ብዙ ዕፅ ሊወስድ የሚችለው ማን እንደሆነና ከፍተኛ ደስታ ሊያገኝ የቻለው ማን እንደሆነ እንነጋገራለን። ቀስ በቀስ ራሴን ከጤነኛው ዓለም አገለልኩ። ትምህርት ቤት የምገባውም አልፎ አልፎ ነበር። ሐሺሽና አምፊታሚን ሊጠቅመኝ ስላልቻለ ከተለያዩ ፋርማሲዎች የማገኛቸውን የሞርፊን ቅመሞች በመርፌ መውጋት ጀመርኩ። በበጋ ወራት እንደ ኤል ኤስ ዲ የመሰሉትን ዕፆች በቀላሉ ማግኘት ወደሚቻልባቸው የሙዚቃ ድግሶች እንሄዳለን።
“አንድ ቀን እናቴ ሐሺሽ ሳጨስ አገኘችኝ። ወላጆቼ እኔን ከጉዳት ለመጠበቅ የተቻላቸውን ሁሉ አደረጉ። ዕፅ መውሰድ ስለሚያስከትለው ጉዳት ነገሩኝ። እንደሚወዱኝና እንደሚያስቡልኝም አረጋገጡልኝ። ሆኖም እኔን ለመርዳት ያደረጉትን ጥረት አስፈላጊ እንዳልሆነ ጣልቃ ገብነት አድርጌ ቆጠርኩት። አሥራ ስድስት ዓመት ሲሆነኝ ከቤት ለመውጣት ወሰንኩ። በመላይቱ ስፔይን እየተዘዋወሩ በእጅ የተሠሩ ሐብሎችን ከሚሸጡና ዕፅ ከሚወስዱ ወጣቶች ጋር ተቀላቀልኩ። ከሁለት ወር በኋላ ፖሊሶች በማላጋ ያዙኝ።
“ፖሊሶቹ ለወላጆቼ መልሰው ሲሰጡኝ ወላጆቼ እጃቸውን ዘርግተው ተቀበሉኝ። ያደረግኩት ሁሉ አሳፈረኝ። አባቴ እያለቀሰ ነበር። አባቴ ሲያለቅስ ሳይ የመጀመሪያዬ ነበር። ይህን ያህል ስላሳዘንኳቸው ተፀፀትኩ። የተሰማኝ ፀፀት ግን ከዕፅ እንድርቅ ሊያደርገኝ አልቻለም። በየቀኑ ዕፅ መውሰዴን ቀጠልኩ። ወደ ሕሊናዬ ስመለስ ዕፅ መውሰድ ሊያስከትልብኝ የሚችለውን አደጋ አስባለሁ። ግን ወዲያው እረሳዋለሁ።”
ከግንበኝነት ወደ ዕፅ አዘዋዋሪነት
ወዳጃዊ ስሜት ያለውና የቤተሰብ ኃላፊ የሆነው ሆሴ ለአምስት ዓመታት ያህል ካናቢስ ከሞሮኮ ወደ ስፔይን ሲያዘዋውር ቆይቷል። እንዴት እዚህ ውስጥ ሊገባ ቻለ? “በግንበኝነት እሠራ በነበረበት ጊዜ አብሮኝ ይሠራ የነበረ አንድ ሰው ዕፅ ማዘዋወር ጀመረ” ሲል ሆሴ ይገልጻል። “ገንዘብ ያስፈልገኝ ስለነበረ ‘እኔስ ለምን እንደርሱ አልሠራም’ ብዬ አሰብኩ።
“በሞሮኮ ካናቢስ መግዛት ቀላል ስለሆነ የምችለውን ያህል እገዛ ነበር። ፖሊሶችን በቀላሉ ሊያመልጥ የሚችል ፈጣን ጀልባ ነበረኝ። ዕፁን ወደ ስፔይን ካስገባሁ በኋላ በጅምላ እሸጠዋለሁ። በአንድ ጊዜ እስከ 600 ኪሎ ግራም እሸጣለሁ። የነበሩኝ ደንበኞች ሦስት ወይም አራት ሲሆኑ ላመጣ የምችለውን በሙሉ ይገዙኝ ነበር። የፖሊሶች ቁጥጥር ቢኖርም ዕጾቹ ድንበር አቋርጠው መግባታቸው አልቀረም። ዕፅ የምናዘዋውረው ሰዎች ፖሊሶቹ ካሏቸው መገልገያዎች በጣም የተሻሉ መገልገያዎች ነበሩን።
“በቀላሉ ብዙ ገንዘብ አገኘሁ። ከሰሜን አፍሪካ ወደ ስፔይን አንድ ጉዞ ሳደርግ ከ25,000 እስከ 30,000 ዶላር አገኛለሁ። በአጭር ጊዜ ውስጥ 30 የሚያክሉ ሰዎችን ቀጥሬ ማሠራት ጀመርኩ። በእንቅስቃሴዬ ላይ ክትትል በሚደረግበት ጊዜ አስቀድሞ የሚነግረኝ ሰው ቀጥሬ ስለነበረ አንድ ጊዜም ተይዤ አላውቅም።
“አንዳንድ ጊዜ እነዚህ ዕፆች በሌሎች ላይ ስለሚያስከትሉት ጉዳት አስባለሁ። ቢሆንም ካናቢስ ማንንም ለሞት የማይዳርግ ለስላሳ ዕፅ ነው ብዬ ራሴን አሳምኜ ነበር። በጣም ብዙ ገንዘብ አገኝበት ስለነበረ በዚህ ጉዳይ ላይ ብዙም አላስብም ነበር። እኔ አንድም ጊዜ ዕፅ ወስጄ አላውቅም።”
ገንዘብህና ሕይወትህ!
ከእነዚህ ምሳሌዎች መረዳት እንደሚቻለው ዕፆች የሰዎችን ሕይወት ሙሉ በሙሉ ይቆጣጠራሉ። አንዴ የተጠመደ ሰው ከሱሱ መላቀቅ በጣም አስቸጋሪና የሚያሰቃይ ይሆንበታል። ድራግስ ኢን አሜሪካ የተባለው መጽሐፍ እንደሚለው “በድሮው የምዕራብ ዓለም ቀማኞች ጠመንጃቸውን ደግነው የሚዘርፏቸውን ሰዎች ‘ከገንዘብህ ወይም ከሕይወትህ ምረጥ’ ይሉ ነበር። የተከለከሉ ዕፆች ከድሮዎቹ ሽፍቶች ይብሳሉ። ሁለቱንም ይቀማሉ እንጂ ከገንዘብህና ከሕይወትህ አንዱን ምረጥ አይሉም።”
ታዲያ ይህን የአደገኛ ዕፆች የማጥፋት ኃይል ሊገታ የሚችል ነገር ይኖር ይሆን? የሚቀጥለው ርዕስ አንዳንድ መፍትሔዎችን ይመረምራል።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a በዚህ ጽሑፍ ውስጥ የተጠቀሱት አንዳንድ ስሞች ተለውጠዋል።
[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]
“በድሮው የምዕራብ ዓለም ቀማኞች ጠመንጃቸውን ደግነው የሚዘርፏቸውን ሰዎች ‘ከገንዘብህ ወይም ከሕይወትህ ምረጥ’ ይሉ ነበር። የተከለከሉ ዕፆች ከድሮዎቹ ሽፍቶች ይብሳሉ። ሁለቱንም ይቀማሉ”
[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]
ልጅህ ዕፅ እንዲወስድ ግብዣ ሲቀርብለት እምቢ ይል ይሆን?
በአደገኛ ሁኔታ ላይ የሚገኙት እንዴት ያሉ ወጣቶች ናቸው?
ሀ. ነፃነት ያላቸው መሆናቸውን ለማሳየት የሚፈልጉና የጀብደኝነት ድርጊት ለመፈጸም ፈቃደኛ የሆኑ
ለ. ለትምህርት ወይም ለመንፈሳዊ ግቦች ደንታ ቢስ የሆኑ
ሐ. ከኅብረተሰቡ ጋር የማይጣጣሙ
መ. ትክክልና ስህተት ስለሆነው ነገር ግልጽ የሆነ ግንዛቤ የሌላቸው
ሠ. የወላጅ ድጋፍ እንደሚጎድላቸው የሚሰማቸውና ጓደኞቻቸው ዕፅ እንዲወስዱ የሚያደፋፍሯቸው። “አንድን ወጣት ከወላጆቹ ጋር ያለውን ጥሩ ዝምድና ያህል ዕፅ ከመውሰድ የሚጠብቀው ነገር የለም።“—በሰያፍ የጻፍነው እኛ ነን።
ልጆችህን መጠበቅ የምትችለው እንዴት ነው?
ሀ. ከእነርሱ ጋር የተቀራረበ ዝምድናና ጥሩ የሐሳብ ግንኙነት እንዲኖር በማድረግ
ለ. ትክክልና ስህተት ስለሆኑ ነገሮች ግልጽ የሆነ ግንዛቤ እንዲኖራቸው በማድረግ
ሐ. የታወቀና የተቆረጠ ግብ እንዲኖራቸው በመርዳት
መ. አፍቃሪ የሆነ ቤተሰብና ወዳጃዊ መንፈስ ያለው ማህበረሰብ አባሎች እንደሆኑ እንዲሰማቸው በማድረግ
ሠ. ዕፅ መውሰድ እንዴት ያሉ አደጋዎችን እንደሚያስከትል በማስተማር። ልጆች ዕፅ እንዲወስዱ ግብዣ ሲቀርብላቸው እምቢ ማለት የሚገባቸው ለምን እንደሆነ በግልጽ ማወቅ ያስፈልጋቸዋል።
[ምንጭ]
ምንጭ: የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ወርልድ ድራግ ሪፖርት
[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በጂብራልታር የተያዙ ዕፆች
[ምንጭ]
Courtesy of Gibraltar Police
[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ይህን የመሰለ በቀላሉ ከፖሊሶች ሊያመልጥ የሚችል ፈጣን ጀልባ ነበረኝ
[ምንጭ]
Courtesy of Gibraltar Police
[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]
Godo-Foto