የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • g99 12/8 ገጽ 30-31
  • ከዓለም አካባቢ

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ከዓለም አካባቢ
  • ንቁ!—1999
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • ብቁ የሆኑ ወላጆች እጥረት
  • ስኬት የሚያስገኝ አለባበስ
  • ከኮምፒዩተሮች ጋር ጠብ መፍጠር
  • የግብፅ የወርቅ ማዕድን ማውጫዎች
  • ስድስት ቢልዮን ደርሷል፣ አሁንም በማሻቀብ ላይ ይገኛል
  • የእናት ውለታ
  • የዓይነ ሥውርነት ማስጠንቀቂያ
  • ከፍተኛ የአየር ሙቀት መጠን
  • በከተሞች ውስጥ የሚሰማ ድምፅና አስደሳች ሕልሞች
  • የማሰብ ችሎታን ማወደስ ይሻላል ወይስ ጥሮሽን?
  • የተቀበሩ ፈንጂዎች የሚያስከትሉትን ኪሣራ መመዘን
    ንቁ!—2000
  • በወርቅ ታሪክ ዙሪያ ያለው ምሥጢር
    ንቁ!—1998
  • ሕዝብ ነክ ጥናት፣ መጽሐፍ ቅዱስ እና መጪው ጊዜ
    ንቁ!—2004
  • አሁን ያለው ፍርሃት ለዘላለም ይወገዳል!
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1995
ለተጨማሪ መረጃ
ንቁ!—1999
g99 12/8 ገጽ 30-31

ከዓለም አካባቢ

ብቁ የሆኑ ወላጆች እጥረት

ወላጆች ልጆችን በማሳደግ ረገድ ያላቸውን ብቃት አስመልክቶ በካናዳ በብሔራዊ ደረጃ ለመጀመሪያ ጊዜ የተካሄደው ጥናት “ብዙ [ወላጆች] ልጆች እድገት የሚያደርጉት እንዴት እንደሆነና ወላጆች በዚህ ሂደት ውስጥ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ማበርከት የሚችሉት እንዴት እንደሆነ ለመገንዘብ የሚያስችል መሠረታዊ እውቀት እንኳ” እንደሌላቸው አመልክቷል ሲል ናሽናል ፖስት ዘግቧል። ጥናቱ ከተካሄደባቸው ከ1,600 በላይ የሚሆኑ “ከስድስት ዓመት በታች የሆኑ ልጆች ያሏቸው አባቶች፣ እናቶችና ነጠላ ወላጅ የሆኑ እናቶች” መካከል 92 በመቶዎቹ ልጅ ማሳደግ ከሁሉ የበለጠ ትልቅ ሥራ እንደሆነ አምነዋል። ሆኖም “ለልጆቻቸው በማንበብ፣ ከልጆቻቸው ጋር በመጫወት፣ በመደባበስ ወይም በማቀፍ የልጆቻቸውን የማሰብ ችሎታ ማሳደግ እንደሚችሉ በሚገባ የተገነዘቡት ከግማሽ ያነሱት ናቸው።” ከዚህም በተጨማሪ 30 በመቶ የሚሆኑት “እያንዳንዱ ሕፃን የተወሰነ የማሰብ ችሎታ ይዞ የሚወለድ በመሆኑ ወላጆቹ ከእሱ ጋር የሚኖራቸው ግንኙነት ይህን ችሎታ ማሳደግም ሆነ መቀነስ አይችልም የሚል እምነት ያላቸው ናቸው።” ጥናቶች እንደሚያሳዩት “በአንድ ሕፃን ሕይወት ውስጥ የመጀመሪያዎቹ አምስት ዓመታት የመማር፣ የመፍጠር፣ የማፍቀርና በሌላው ላይ እምነት የመጣል ችሎታ እንዲያዳብርና ለራሱ ጥሩ ግምት እንዲኖረው በመርዳት ረገድ ወሳኝ ሚና” የሚጫወቱ በመሆኑ እንዲህ ዓይነቶቹ ግኝቶች በጣም ይረብሻሉ ይላል ፖስት።

ስኬት የሚያስገኝ አለባበስ

ሥራ ለመቀጠር ለቃለ መጠይቅ በምትዘጋጁበት ጊዜ “ጥሩ አለባበስ ያላቸው ሰዎች በሌሎች ሰዎች ላይ ጥሩ ስሜት እንደሚያሳድሩ” ማስታወሱ ጠቃሚ ነው ይላል ቶሮንቶ ስታር የተባለው ጋዜጣ። ይህን ማድረጉ ጠቃሚ የሚሆነው በሌሎች ሰዎች ላይ መጀመሪያ የምናሳድረው ተጽእኖ ለረጅም ጊዜ የሚዘልቅ በመሆኑ ነው። ስለዚህ “በሥራ ዓለም የሚሠማሩ ሰዎች የሚከተለውን መሠረታዊ መልእክት ልብ ማለት አለባቸው:- ለቁመናችሁ ግድ የለሽ ከሆናችሁ ሰዎች ለሁሉም ነገር ግድ የለሾች እንደሆናችሁ አድርገው ይደመድማሉ” ይላል ዘገባው። አንድ ሰው አለባበሱ ንጹሕና ሥርዓታማ ከሆነ ሊቀጥሩት ያሰቡት ሰዎችም ሆኑ ደንበኞች ጥራት ያለው ሥራ እንደሚያከናውንላቸው እምነት ያድርባቸዋል ሲሉ ጠበብት ይናገራሉ። አንዳንድ አማካሪዎችም “ቀጥ ያለ ቁመናና ንቃት የተሞላበት አቀራረብ መጀመሪያ ላይ በሰዎች ዘንድ የሚያሳድረው ተጽዕኖ ቀላል አይደለም። የድምፃችሁ ቃናና የንግግራችሁ ፍጥነት ትልቅ ለውጥ ያመጣል” ሲሉ ጠበቅ አድርገው ይገልጻሉ።

ከኮምፒዩተሮች ጋር ጠብ መፍጠር

“ኮምፒዩተርህ የምትፈልገውን ነገር ሳያደርግልህ ሲቀር ምን ታደርጋለህ?” ሲል በኢንተርኔት ለንባብ የሚበቃው ፒሲ ቬልት የተባለው የጀርመን ጋዜጣ ጥያቄ አቅርቧል። “ኮምፒዩተሩን ትመታዋለህ? ወይም ደግሞ በመስኮት ትወረውረዋለህ?” እንዲህ ዓይነቶቹ ድርጊቶች እምብዛም ያልተለመዱ አይደሉም። በዓለም ዙሪያ ጥናት ከተካሄደባቸው 150 የመረጃ ቴክኖሎጂ ሥራ አስኪያጆች መካከል 83 በመቶ የሚሆኑት በኮምፒዩተሮቻቸው ላይ በቁጣ እንደሚገነፍሉ ወይም ቀጥተኛ የኃይል ድርጊት እንደሚፈጽሙ ታውቋል። መረጃዎችን ለመቀበል በሚወስደው ረጅም ጊዜ የሚበሳጩ ወይም ደግሞ መሥራቱን ባቆመ አይጦ (mouse) የሚናደዱ የኮምፒዩተር ተጠቃሚዎች አንዳንድ ጊዜ ሞኒተሩን ይሰባብሩታል፣ ቁልፍ ሰሌዳውን በቡጢ ይደበድባሉ፣ አይጦውን ወርውረው ከግድግዳ ጋር ያጋጩታል፣ አልፎ ተርፎም ኮምፒዩተሩን በካልቾ ይሉታል። ተጠቃሚው ብስጭቱን በኮምፒዩተሩ ላይ ይወጣ እንጂ ብዙውን ጊዜ ለችግሩ መንስኤ የሚሆነው ራሱ ተጠቃሚው ነው። ለምሳሌ ያህል አንዲት ሠራተኛ የኢ-ሜይል ፕሮግራሟ ምንም ዓይነት መልእክት ሊልክላት ስላልቻለ ተበሳጨች። በኋላ ግን ሲታይ ችግሩ የተፈጠረው በኢ-ሜይል አድራሻው ላይ መተየብ ሲገባት የጎዳና አድራሻ በሚሰፍርበት ቦታ ላይ በመተየቧ እንደሆነ ሊረጋገጥ ችሏል።

የግብፅ የወርቅ ማዕድን ማውጫዎች

የግብፅ የወርቅ ማዕድን ማውጫዎች በጥንት ዘመናት ከ1,500 ቶን በላይ የሚሆን ወርቅ እንደተመረተባቸው ይነገራል። ከእነዚህ ማዕድን ማውጫዎች ከፍተኛ መጠን ያለው ወርቅ ከተመረተ 2,000 ዓመት ገደማ ያለፈ ቢሆንም እንኳ አሁንም ከፍተኛ መጠን ያለው ወርቅ በእነዚህ ቦታዎች ውስጥ ሊገኝ እንደሚችል የስነ ምድር ተመራማሪዎች ይናገራሉ። “የፈርዖኖቹን ክብር መመለስና ከ6,000 ዓመታት በላይ ያስቆጠሩትን የማዕድን ማውጫዎቻችንን እንደገና መክፈት እንፈልጋለን” ሲሉ የአንድ የአውስትራሊያ የወርቅ ማዕድን አውጪ ኩባንያ ዋና ዲሬክተር የሆኑት ሳሚ ኤል-ራጊ ተናግረዋል። የግብፅ መንግሥት 16 የፈርዖኖች የማዕድን ማውጫዎች እንደሚገኙበት የሚታወቀውን በቀይ ባሕር አቅራቢያ የሚገኘውን የምሥራቅ በረሃ እንዲያስስ ለዚህ ኩባንያ ሥልጣን ሰጥቶታል። ይሁን እንጂ በ1820 በሉክሶር (በጥንቷ ቲብዝ) የተገኘው የ2,900 ዓመት ዕድሜ ያለው አንድ ካርታ በዚያው አካባቢ በበረሃ አሸዋ ተቀብረው የሚገኙ 104 የጠፉ ማዕድን ማውጫዎች እንዳሉ ያመለክታል። ዘ ዎል ስትሪት ጆርናል እንዳለው ከሆነ ዘመናዊ ዘዴዎችን በመጠቀም አንዳንዶቹን ዳግመኛ ጥሩ የወርቅ ማዕድን ማውጫዎች ማድረግ እንደሚቻል ይታመናል።

ስድስት ቢልዮን ደርሷል፣ አሁንም በማሻቀብ ላይ ይገኛል

የተባበሩት መንግሥታት የሥነ ሕዝብ ተቋም የዓለም ሕዝብ ቁጥር ጥቅምት 12, 1999 ላይ ስድስት ቢልዮን እንደደረሰ ይገምታል። የዓለም ሕዝብ ቁጥር ከአምስት ወደ ስድስት ቢልዮን ለመሸጋገር የፈጀበት ጊዜ 12 ዓመት ብቻ እንደሆነ የሥነ ሕዝብ መረጃ ቢሮ ባልደረባ የሆኑት ካርል ሃውብ ተናግረዋል። ቢሮው ያወጣው ዘገባ እንደሚገልጸው ከሆነ “በ20ኛው መቶ ዘመን የዓለም ሕዝብ ቁጥር በ4.4 ቢልዮን ያደገ” ሲሆን በ19ኛው መቶ ዘመን ግን “የሕዝቡ ቁጥር ያደገው በ600 ሚልዮን ያህል ብቻ ነበር።” በ20ኛው መቶ ዘመን የዓለም ሕዝብ ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ እንዲጨምር ያደረገው ዋነኛው ምክንያት የሰው ልጅ አማካይ ዕድሜ ማደጉ ነው። “በዛሬው ጊዜ ከዓለም ሕዝብ ቁጥር ዕድገት መካከል 98 በመቶው የሚከሰተው የዕድገት ደረጃቸው ዝቅተኛ በሆነ አገሮች ውስጥ ነው” ሲሉ ሃውብ ተናግረዋል።

የእናት ውለታ

አንዲት እናት ዓመቱን ሙሉ ለምታከናውናቸው ሥራዎች ሊከፈል የሚችለውን ደሞዝ አንድ ላይ ብትደምር ምን ያህል ይሆናል? ዘ ዋሽንግተን ፖስት ላይ የወጣው ዘገባ እንደሚለው ከሆነ አንዲት እናት በዓመት ውስጥ ለምትሰጣቸው ግልጋሎቶች 508,700 ዶላር ሊደርሳት ይችላል! ይህ አኃዝ የተሰጠው እናቶች ለሚያከናውኗቸው የተለመዱ ዓይነት ሥራዎች በሚከፈል አማካይ ደሞዝ ላይ የተካሄደውን ጥናት ምርኩዝ በማድረግ ነው። ከዓመታዊው አማካይ የደሞዝ ክፍያቸው ጋር በዘገባው ላይ ከሠፈሩት 17 የሥራ ዓይነቶች መካከል የሚከተሉት ይገኙበታል:- ሞግዚት፣ 13,000 ዶላር፤ የአውቶብስ ሹፌር፣ 32,000 ዶላር፤ የሥነ ልቦና ሐኪም፣ 29,000 ዶላር፤ የእንስሳት ተንከባካቢ፣ 17,000 ዶላር፤ በሙያው የሰለጠነች ነርስ፣ 35,000 ዶላር፤ የወጥ ቤት ኃላፊ፣ 40,000 ዶላር፤ እና የቢሮ ጸሐፊ፣ 19,000 ዶላር። ይህን ጥናት ያካሄደው የፋይናንስ ግልጋሎቶች ኩባንያ ሊቀ መንበር የሆኑት ሪክ ኤድልማን እነዚህ አኃዞች እንደ ጡረታ አበልና ሌሎች የጡረታ ጥቅማ ጥቅሞችን የመሰሉ ወጪዎችን አይጨምሩም።

የዓይነ ሥውርነት ማስጠንቀቂያ

“ከ200,000 በላይ የሚሆኑ ካናዳውያን ግላኮማ ያለባቸው ቢሆንም እንኳ ይህ እክል እንዳለባቸው የሚያውቁት ግማሽ ያህሉ ብቻ ናቸው” ይላል ዘ ፕሪንስ ጆርጅ ሲትዝን የተባለው ጋዜጣ። ግላኮማ ለዓይነ ሥውርነት ምክንያት ከሚሆኑት ነገሮች ግንባር ቀደሙን ሥፍራ የያዘ ሲሆን ከዓይን በስተጀርባ ያሉት የነርቭ ሕዋሳት ቀስ በቀስ እንዲሞቱ ያደርጋል። በዚህም ሳቢያ የዓይን እይታ ቀስ በቀስ እየደበዘዘ ይሄድና በሽታው የመጨረሻ ደረጃው ላይ እስከሚደርስ ድረስ የዓይን ማዕከላዊ እይታ ብቻ ይቀራል። በግላኮማ የተጠቁ ብዙዎቹ ሰዎች ምንም ሕመም ስለማይሰማቸውና በዚህም ወቅት ቢሆን መኪና ማሽከርከር፣ ማንበብና አብዛኞቹን ሥራዎቻቸውን ማከናወን ስለሚችሉ ሕክምና አያደርጉም። የካናዳ የግላኮማ ምርምር ማኅበር እንደሚለው ከሆነ ለዚህ በሽታ በከፍተኛ ሁኔታ ከተጋለጡት ሰዎች መካከል በዕድሜ የገፉ ሰዎች፣ ግላኮማ የያዘው የቤተሰብ አባል ያላቸው ሰዎች፣ ከ40 ዓመት በላይ የሆኑ ጥቁሮችና ዓይናቸው ውስጥ ከፍተኛ ግፊት የሚሰማቸው ሰዎች ይገኙበታል። “ለአደጋው የተጋለጡ ሰዎች ሐኪም ዘንድ እንዲሄዱ መገፋፋታችን አደጋውን ለመከላከል ትልቅ ሚና ይጫወታል” ሲሉ በቶሮንቶ የሚገኘው የቅዱስ ሚካኤል ሆስፒታል የግላኮማ ክፍል ዲሬክተር የሆኑት ዶክተር ኒሩ ጉፕታ ተናግረዋል። “ዋናው ነገር ቀደም ብሎ ከታወቀና ሕክምና ከተደረገለት ከዓይነ ሥውርነት መትረፍ የሚቻል መሆኑ ነው።”

ከፍተኛ የአየር ሙቀት መጠን

“በ1998 የተመዘገበው የምድር አማካይ የሙቀት መጠን እስከ ዛሬ ከተመዘገበው የሙቀት መጠን ሁሉ የላቀ ሆኖ ተገኝቷል” ሲል ዎርልድዎች ኢንስቲትዩት ያወጣው አንድ መግለጫ ገልጿል። የከባቢ አየር ሙቀት መጠን ሲጨምር ትነትና የዝናብ መጠን እንዲጨምር ያደርጋል። ይህ ደግሞ ይበልጥ አውዳሚ የሆኑ አውሎ ነፋሳት ያስከትላል። ለምሳሌ ያህል “በ1998 በዓለም ዙሪያ ከአየር ጠባይ ጋር በተያያዘ የደረሰው ውድመት 92 ቢልዮን ዶላር የሚገመት ሲሆን ቀደም ሲል ከተመዘገበው በ1996 ከደረሰው 60 ቢልዮን ዶላር የሚገመት ኪሳራ ጋር ሲወዳደር 53 በመቶ ብልጫ አለው” ይላል ዎርልድዎች። ከዚህም በተጨማሪ በ1998 የተከሰቱት ከባድ ውሽንፍሮችና ጎርፍ ወደ 300 ሚልዮን የሚጠጉ ሰዎችን ከመኖሪያቸው እንዳፈናቀሏቸው ይገመታል። ሳይንቲስቶች ይህ አውዳሚ ሂደት በ1998 ብቻ ተወስኖ የሚቀር ያልተለመደ ዓይነት ክስተት ነው ወይስ ወደፊትም ይቀጥላል በሚለው ጉዳይ ላይ በእርግጠኝነት መናገር የቻሉት ነገር የለም። ይሁን እንጂ “ለሙከራ ተብለው የተሠሩ የአየር ንብረት ሞዴሎች በ1998 የተከሰቱት ነገሮች ወደፊት ለሚፈጸሙ ነገሮች መቅድም ሊሆኑ እንደሚችሉ ጠቁመዋል” ሲል ዘገባው አትቷል።

በከተሞች ውስጥ የሚሰማ ድምፅና አስደሳች ሕልሞች

ቀን ላይ ከ40 ሚልዮን የሚበልጡ ኢጣሊያውያን፣ ከጠቅላላው ሕዝብ 72 በመቶ የሚሆኑት ማለት ነው፣ በጣም ለሚረብሽ ድምፅ የተጋለጡ እንደሆኑ የኢጣሊያ የአካባቢ ጥበቃ ሚኒስቴር ገልጿል። ለእንዲህ ዓይነቱ ድምፅ ለረጅም ጊዜ የሚጋለጡ ሰዎች የልብ ምታቸው ሊጨምር፣ የደም ግፊታቸውና አተነፋፈሳቸው ሊለዋወጥ እንዲሁም የጨጓራ ብግነት ሊከሰትባቸውና ሊያቅለሸልሻቸው እንደሚችል ኮሪዬሬ ዴልላ ሴራ ዘግቧል። በትልልቅ ከተሞች ውስጥ ከሚተራመሱት ተሽከርካሪዎች የሚወጣው ድምፅ በእንቅልፍ ላይ ችግር ይፈጥራል። በከተሞች ውስጥ ሌሊት ሌሊት የሚሰማው ድምፅ ከ70 ዴሲቤል ሊበልጥ የሚችል በመሆኑ አንድ ሰው ጭልጥ ያለ እንቅልፍ ሊተኛና ሊያልም የሚችልበትን የጊዜ መጠን ሊቀንሰው ይችላል። ሌጋምቢዬንቴ ተብሎ የሚጠራው የኢጣሊያን የአካባቢ ጥበቃ ማኅበር የሳይንስ ዲሬክተር የሆኑት ሉቺያ ቬንቱሪ እንዲህ ሲሉ ገልጸዋል:- ‘በትልልቅ ከተሞች የሚኖሩት 18 ሚልዮን ሰዎች እያንዳንዳቸው በእያንዳንዱ ሌሊት የ30 ደቂቃ እንቅልፍ እንደሚያጡ ይገመታል። ይህ በዓመት ሲሰላ እያንዳንዱ ሰው 22 የእንቅልፍ ሌሊቶች እንዳጣ ሊቆጠር ይችላል።’

የማሰብ ችሎታን ማወደስ ይሻላል ወይስ ጥሮሽን?

ብዙ ወላጆች ልጆችን ባላቸው የማሰብ ችሎታ ማወደስ ጥሩ ነው የሚል እምነት አላቸው። ይሁን እንጂ እንዲህ ዓይነቱ ውዳሴ አንድ ነገር ለማድረግ እንዲነሳሱ በሚያደርጋቸው ውስጣዊ ግፊትና በወደፊት ክንውኖቻቸው ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ሊያሳድር እንደሚችል በቅርቡ የተካሄደ አንድ ጥናት አመልክቷል ሲል በኒው ዮርክ ኮሎምቢያ ዩኒቨርሲቲ እየታተመ የሚወጣው ኮሎምቢያ ማገዚን ዘግቧል። ፕሮፌሰር ካሮል ድዌክ እንዳሉት ከሆነ ልጆችን ለሚያደርጉት ጥሮሽ ማመስገኑ የተሻለ ነው። ይህ በሕይወት ውስጥ የሚገጥሟቸውን ፈታኝ ሁኔታዎች መቋቋም የሚያስችል ጥንካሬ ይሰጣቸዋል። “ባላቸው የማሰብ ችሎታ የሚወደሱ ልጆች ይበልጥ የሚያሳስባቸው ነገር ከሌሎች ልቆ መታየት ከመሆኑም በላይ ብዙውን ጊዜ ልቀው ለመታየት ሲሉ በጣም ጠቃሚ የሆነ ነገር መማር የሚችሉበትን አጋጣሚ እንኳ መሥዋዕት ያደርጋሉ” ሲሉ ድዌክ ተናግረዋል። በሌላ በኩል ደግሞ በጥሮሻቸውና በመንፈሰ ጠንካራነታቸው የሚወደሱ ልጆች በሚያገኙት ትምህርትና ውድቀትን በማሸነፍ ላይ ይበልጥ እንደሚያተኩሩ ዘገባው ይገልጻል። “ስለዚህ እነዚህ ልጆች በሌሎች ዘንድ ልቀው ለመታየት ከመሞከር ይልቅ ለሚቀስሙት ትምህርት ቅድሚያ ይሰጣሉ” ይላሉ ድዌክ። “አንድ ነገር ሳይሳካላቸው ቢቀር እንኳ ተስፋ ስለማይቆርጡ ወዲያውኑ ያገግማሉ።”

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ