የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • g01 8/8 ገጽ 8-11
  • የጥላቻን ሰንሰለት መበጠስ

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • የጥላቻን ሰንሰለት መበጠስ
  • ንቁ!—2001
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • የ“ፍቅር” ትርጉም
  • ማፍቀርን መማር
  • የብሔር ልዩነትን ማሸነፍ
  • ያለፈውን መርሳት
  • ጥላቻ የሌለበት ዓለም!
  • ጥላቻን ማስወገድ የሚቻልበት ብቸኛ መንገድ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2000
  • ጥላቻ ይህን ያህል የበዛው ለምንድን ነው?—መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?
    ተጨማሪ ርዕሰ ጉዳዮች
  • በመላው ዓለም ጥላቻ የሚያከትምበት ጊዜ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1995
  • ጥላቻ የተስፋፋው ለምንድን ነው?
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (ለሕዝብ የሚሰራጭ)—2022
ለተጨማሪ መረጃ
ንቁ!—2001
g01 8/8 ገጽ 8-11

የጥላቻን ሰንሰለት መበጠስ

“ጠላቶቻችሁን ውደዱ።”​—⁠ማቴዎስ 5:44

በጠላትነት የሚተያዩ የሁለት ብሔራት መሪዎች ለቀናት የዘለቀ ሰፊ የሰላም ድርድር አድርገዋል። በኢንዱስትሪ የበለጸገች የአንዲት ኃያል አገር ፕሬዚዳንት በውይይቱ ላይ በመገኘት ያላቸውን ተደማጭነትና ዲፕሎማሲያዊ ክህሎት ተጠቅመው ሁለቱን መሪዎች ለማስማማት ሞክረዋል። ይሁን እንጂ ይህ ሁሉ ጥረት መጨረሻው ሐዘን ከመሆን አላለፈም። በሳምንታት ጊዜ ውስጥ ሁለቱ ብሔራት ወደ ግጭት ያመሩ ሲሆን ኒውስዊክ መጽሔት ይህንኑ ግጭት “በሁለት አሥርተ ዓመታት ውስጥ በሁለቱ ብሔራት መካከል ከተከሰቱት ግጭቶች ሁሉ የከፋ ነው” ሲል ገልጾታል።

በዓለም ዙሪያ ባሉ የተለያዩ ጎሳዎችና ብሔራት መካከል የሚታየው ጥላቻና ጠላትነት የብሔራት መሪዎች አቅማቸው የፈቀደውን ያህል ቢጥሩም መፍትሔ ሊያገኙለት ያልቻሉ ችግር ነው። ጥላቻ በጭፍን አስተሳሰብ፣ በግትር አመለካከትና ፕሮፓጋንዳ እየተቀጣጠለ በፍጥነት መስፋፋቱን ቀጥሏል። ዛሬ ያሉት መሪዎች አዲስና ዘመናዊ መፍትሔ ለማግኘት በከንቱ ሲማስኑ አስተማማኝ የሆነው መፍትሔ የተራራውን ስብከት ያህል ረጅም ዘመን ያስቆጠረ ጥንታዊ እንደሆነ ሳያስተውሉ ቀርተዋል። በዚያ ስብከት ወቅት ኢየሱስ ክርስቶስ አድማጮቹ የአምላክን መንገዶች እንዲታዘዙ አበረታትቷል። ከተናገራቸው ነገሮች መካከል “ጠላቶቻችሁን ውደዱ” የሚሉት ከላይ የተጠቀሱት ቃላት ይገኙበታል። ይህ ማሳሰቢያ ለጥላቻና ለወገናዊነት የተሻለ ብቻ ሳይሆን ብቸኛም መፍትሔ ነው!

ተጠራጣሪ የሆኑ ሰዎች ጠላትህን ውደድ የሚለውን ሐሳብ ምንም እንደማይፈይድ ሕልም አድርገው በመቁጠር ያጣጥሉታል። ይሁን እንጂ ጥላቻ ከጊዜ በኋላ የሚዳብር ባሕርይ ከሆነ እንዳይዳብር ማድረግም እንችላለን ብሎ ማሰቡ ምክንያታዊ አይደለምን? እንግዲያውስ ኢየሱስ የተናገራቸው ቃላት ለሰው ዘር እውነተኛ ተስፋ ይሰጣሉ። ለረጅም ዘመን የዘለቀን ጠላትነት ሳይቀር ማስወገድ እንደሚቻል የሚገልጹ ናቸው።

በኢየሱስ ዘመን በአይሁዳውያን አድማጮቹ መካከል የነበረውን ሁኔታ አስብ። ጠላቶቻቸውን ለማግኘት ረጅም ርቀት መጓዝ አያስፈልጋቸውም ነበር። የሮማ ሠራዊት በአይሁዳውያኑ ላይ ከባድ ቀረጥ በመጣል፣ ፖለቲካዊ ሴራ በመፈጸም፣ በማንገላታት እና በብዝበዛ ምድሪቱን መግዛቱን ቀጥሎ ነበር። (ማቴዎስ 5:​39-42) ይሁን እንጂ አንዳንዶች መፍትሔ ባላበጁላቸውና ሲያብላሏቸው በቆዩ ጥቃቅን አለመግባባቶች ምክንያት የገዛ አይሁዳውያን ወንድሞቻቸውን ሳይቀር እንደ ጠላት ተመልክተዋቸው ሊሆን ይችላል። (ማቴዎስ 5:​21-24) በእርግጥ ኢየሱስ የጎን ቁስል የሆኑባቸውን እነዚህን ሰዎች እንዲወድዱ ሊጠብቅባቸው ይችላልን?

የ“ፍቅር” ትርጉም

በመጀመሪያ ደረጃ ኢየሱስ ስለ “ፍቅር” ሲናገር በቅርብ ጓደኛሞች መካከል ስላለው የጠበቀ ወዳጅነት መናገሩ እንዳልነበር ልብ በል። ማቴዎስ 5:​44 ላይ ፍቅርን ለማመልከት የገባው የግሪክኛ መግለጫ አጋፔ ከሚለው ቃል የተገኘ ነው። ቃሉ በመሠረታዊ ሥርዓት የሚመራን ፍቅር የሚያመለክት ነው። የግድ የጠበቀ ወዳጅነት ያካትታል ማለት አይደለም። እንዲህ ያለው ፍቅር በጽድቅ መሠረታዊ ሥርዓቶች የሚመራ በመሆኑ አንድ ሰው ሌሎች ያላቸው ጠባይ ምንም ይሁን ምን የእነርሱን ጥቅም እንዲያስቀድም ያነሳሳዋል። እንግዲያው አጋፔ የተባለው የፍቅር ዓይነት የግል ጠላትነት አያሸንፈውም። ኢየሱስ ራሱ የሰቀሉትን ሮማውያን ወታደሮች ከመርገም ይልቅ “አባት ሆይ፣ የሚያደርጉትን አያውቁምና ይቅር በላቸው” ብሎ በመጸለይ እንዲህ ያለውን ፍቅር አሳይቷል።​—⁠ሉቃስ 23:34

ዓለም የኢየሱስን ትምህርቶች በሰፊው ተቀብሎ ሰዎች እርስ በርሳቸው መዋደድ ይጀምራሉ ብሎ መጠበቅ ምክንያታዊ ይሆናልን? የለም፤ መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚጠቁመው ይህ ዓለም ወደ ጥፋት ከመገስገስ አይመለስም። 2 ጢሞቴዎስ 3:​13 “ክፉዎች ሰዎችና አታላዮች፣ እያሳቱና እየሳቱ፣ በክፋት እየባሱ ይሄዳሉ” በማለት ይተነብያል። ያም ሆነ ይህ ግለሰቦች በመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት አማካኝነት የጽድቅ መሠረታዊ ሥርዓቶችን በጥልቀት በመማር የጥላቻን ሰንሰለት መበጠስ ይችላሉ። ከተሞክሮ እንደታየው ብዙዎች በዙሪያቸው ያለውን የጥላቻ ሞገድ መቋቋምን ተምረዋል። ጥቂት የሕይወት ተሞክሮዎችን ተመልከት።

ማፍቀርን መማር

ሆሴ በ13 ዓመቱ ከአንድ የሽብርተኞች ቡድን ጋር በመቀላቀል ሽምቅ ውጊያ ውስጥ ይገባል።a በዙሪያው ለሚያየው የፍትሕ መጓደል ተጠያቂ ናቸው ለሚባሉት ሰዎች ጥላቻ አዳብሯል። ከተቻለ ግቡ እነርሱን ማጥፋት ነበር። ሆሴ ብዙዎቹ ጓደኞቹ ከጎኑ ሲወድቁ ሲያይ ይበልጥ በምሬትና በበቀል ስሜት ተሞላ። ፈንጂዎችን እየሠራ ‘ይህን ያህል ሥቃይ የኖረው ለምንድን ነው? አምላክ ካለ ይህን ነገር እንዴት አያይም?’ እያለ ራሱን ይጠይቅ ነበር። ብዙ ጊዜ በግራ መጋባትና በጭንቀት ተውጦ አልቅሷል።

በመጨረሻ ሆሴ በአካባቢው ካለ የይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤ ጋር ይገናኛል። ለመጀመሪያ ጊዜ በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ ሲገኝ በዚያ ያለውን ፍቅር ለማስተዋል ብዙ ጊዜ አልወሰደበትም። ሁሉም ሰው ሞቅ ባለ ስሜት ሰላምታ ሰጠው። ከዚያም “አምላክ ሥቃይና መከራ እንዲኖር ለምን ፈቀደ?” በሚለው ጥያቄ ላይ ከተደረገው ውይይት በውስጡ ሲሟገቱት ለቆዩት ጥያቄዎች መልስ አገኘ።b

ውሎ አድሮ ሆሴ ከመጽሐፍ ቅዱስ ያገኘው ተጨማሪ እውቀት በሕይወቱና በአስተሳሰቡ ላይ ለውጥ እንዲያደርግ ረድቶታል። “ወንድሙን የማይወድ በሞት ይኖራል። . . . የሚጠላ ሁሉ ነፍሰ ገዳይ ነው፣ ነፍሰ ገዳይ የሆነ ሁሉ የዘላለም ሕይወት በእርሱ [የለም]” የሚለውን እውነት ተማረ።​—⁠1 ዮሐንስ 3:14, 15

ይሁንና ከሽብርተኛ ጓደኞቹ ጋር ያለውን ትስስር ማቋረጡ ፈተና ሆኖበት ነበር። ወደ ይሖዋ ምሥክሮች የመንግሥት አዳራሽ በሄደ ቁጥር ይከተሉት ነበር። እንዲያውም አንዳንዶቹ የቀድሞ ጓደኞቹ ሆሴን እንዲህ የለወጠው ነገር ምን እንደሆነ ለማወቅ አብረውት በአንዳንድ ስብሰባዎች ላይ ተገኝተዋል። እነርሱን መክዳቱ እንዳልሆነ ወይም በእነርሱ ላይ ስጋት የሚፈጥር ሰው አለመሆኑን ካረጋገጡ በኋላ ተዉት። ሆሴ በ17 ዓመቱ ተጠምቆ የይሖዋ ምሥክር ሆነ። ከዚያ ብዙም ሳይቆይ በሙሉ ጊዜ የስብከት ሥራ ተሰማራ። ዛሬ ሰዎችን ለመግደል ማሴሩን ትቶ የፍቅርና የተስፋ መልእክት ይዞላቸው ይሄዳል!

የብሔር ልዩነትን ማሸነፍ

የተለያየ ብሔር ያላቸው ሰዎች በመካከላቸው ያለውን የጥላቻ አጥር ማፍረስ ይችላሉን? በለንደን እንግሊዝ የሚገኘውን የአማርኛ ተናጋሪዎች የይሖዋ ምሥክሮች ቡድን ሁኔታ ተመልከት። የቡድኑ አባላት 35 ሲሆኑ ከእነርሱ መካከል 20ዎቹ ኢትዮጵያውያን የቀሩት 15ቱ ደግሞ ኤርትራውያን ናቸው። አፍሪካ ውስጥ ኤርትራውያንና ኢትዮጵያውያን በቅርቡ አስከፊ ጦርነት አድርገው የነበረ ቢሆንም እነዚህ ሰዎች በሰላምና በአንድነት አምልኮአቸውን ያካሂዳሉ።

አንድ ኢትዮጵያዊ የይሖዋ ምሥክር ቤተሰቡ ‘ኤርትራውያንን አትመን!’ ይሉት እንደነበር ተናግሯል። ዛሬ ግን ኤርትራውያን ክርስቲያን ወንድሞቹን ማመን ብቻ ሳይሆን ወንድምና እህት ብሎ ይጠራቸዋል! ኤርትራውያኑ የሚናገሩት ትግርኛ ቢሆንም መጽሐፍ ቅዱስን በአንድ ላይ ማጥናት ይችሉ ዘንድ የኢትዮጵያውያን ወንድሞቻቸውን የአማርኛ ቋንቋ ተምረዋል። አምላካዊ ፍቅር “ፍጹም የአንድነት ማሠሪያ” መሆኑን የሚያረጋግጥ እንዴት ያለድንቅ ማስረጃ ነው!​—⁠ቆላስይስ 3:​14 NW

ያለፈውን መርሳት

ይሁን እንጂ አንድ ሰው የጭካኔ ድርጊት ተፈጽሞበት ከነበረስ? ሥቃይ ላደረሰበት ወገን ጥላቻ ማዳበሩ ምን ጥፋት አለበት? ጀርመናዊው የይሖዋ ምሥክር ማንፍሬት የገጠመውን ሁኔታ ልብ በል። የይሖዋ ምሥክር በመሆኑ ምክንያት ብቻ ስድስት ዓመት በኮሚኒስቶች እስር ቤት ውስጥ ቆይቷል። ለጨቆኑት ሰዎች ጥላቻ የማሳደር ወይም እነርሱን የመበቀል ዝንባሌ አሳድሮ ይሆን? የእርሱ መልስ “የለም” የሚል ነው። ሳአርበሩክከር ዜይቱንግ የተባለው የጀርመን ጋዜጣ እንደዘገበው ከሆነ ማንፍሬት እንደሚከተለው ሲል አስረድቷል:- “ፍትሕ የጎደለው ድርጊት መፈጸምና ያን ድርጊት ለመበቀል መሞከር . . . በተደጋጋሚ ወደ ፍትሕ መጓደል የሚመራ ዑደት ውስጥ ያስገባል።” ማንፍሬት የሚከተሉትን የመጽሐፍ ቅዱስ ቃላት ተግባራዊ እንዳደረገ ግልጽ ነው:- “ለማንም ስለ ክፉ ፈንታ ክፉን አትመልሱ፤ . . . ቢቻላችሁስ በእናንተ በኩል ከሰው ሁሉ ጋር በሰላም ኑሩ።”​—⁠ሮሜ 12:17, 18

ጥላቻ የሌለበት ዓለም!

የይሖዋ ምሥክሮች እኛ በዚህ ረገድ ፍጹማን ነን አይሉም። ብዙውን ጊዜ ቀደም ሲል የተፈጠረን የጠላትነት ስሜትና ጥላቻ ማስወገድ ቀላል እንዳልሆነ ይገነዘባሉ። የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች በሕይወት ውስጥ ተግባራዊ ለማድረግ ያልተቋረጠ ትጋት ያስፈልጋል። በጥቅሉ ሲታይ የይሖዋ ምሥክሮች መጽሐፍ ቅዱስ የጥላቻን ሰንሰለት ለመበጠስ የሚያስችል ኃይል እንዳለው የሚያረጋግጡ ሕያው ምሥክሮች ናቸው። የይሖዋ ምሥክሮች በቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት አማካኝነት በየዓመቱ በሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች ከዘረኝነትና ከግትር አስተሳሰብ ማነቆ እንዲላቀቁ በመርዳት ላይ ናቸው።c (“የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር ጥላቻን ለማስወገድ ይረዳል” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።) በዚህ ረገድ ያገኙት ስኬት በቅርቡ ጥላቻንና የጥላቻን መንስኤዎች ጨርሶ ከምድር ገጽ የሚያስወግደው ዓለም ዓቀፍ የትምህርት መርሐ ግብር የሚያስገኘውን ውጤት ከወዲሁ የሚያመላክት ነው። ወደፊት የሚጀመረው ይህ የትምህርት መርሐ ግብር በአምላክ መንግሥት ወይም በምድር አቀፉ መንግሥት የበላይ ቁጥጥር የሚካሄድ ይሆናል። ኢየሱስ በጌታ ጸሎት ውስጥ “መንግሥትህ ትምጣ” ብለን ስለዚህ መንግሥት እንድንጸልይ አስተምሮናል።​—⁠ማቴዎስ 6:​9, 10

መጽሐፍ ቅዱስ በዚህ ሰማያዊ መስተዳድር የበላይ ጥበቃ ‘ምድር እግዚአብሔርን በማወቅ እንደምትሞላ’ ተስፋ ይሰጣል። (ኢሳይያስ 11:​9፤ 54:​13) ብዙውን ጊዜ የሚጠቀሱት የነቢዩ ኢሳይያስ ቃላት በዚያ ወቅት በምድር ዙሪያ ፍጻሜያቸውን ያገኛሉ:- “[አምላክ] በአሕዛብም መካከል ይፈርዳል፣ በብዙ አሕዛብም ላይ ይበይናል፤ ሰይፋቸውንም ማረሻ፣ ጦራቸውንም ማጭድ ለማድረግ ይቀጠቅጣሉ፤ ሕዝብም በሕዝብ ላይ ሰይፍ አያነሣም፣ ሰልፍም ከእንግዲህ ወዲህ አይማሩም።” (ኢሳይያስ 2:​4) በዚህ መንገድ አምላክ ራሱ የጥላቻን ሰንሰለት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ይበጣጥሳል።

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

a ስሙ ተቀይሯል።

b የይሖዋ ምሥክሮች ባሳተሙት ወደ ዘላለም ሕይወት የሚመራ እውቀት በተባለው መጽሐፍ ላይ ያለውን “አምላክ ሥቃይና መከራ እንዲኖር ለምን ፈቀደ?” የሚለውን 8ኛ ምዕራፍ ተመልከት።

c በአካባቢህ ያሉትን የይሖዋ ምሥክሮች በማነጋገር ወይም ለዚህ መጽሔት አሳታሚዎች ደብዳቤ በመጻፍ ያለ ክፍያ የቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት እንዲደረግልህ መጠየቅ ይቻላል።

[በገጽ 11 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር ጥላቻን ለማስወገድ ይረዳል

● “በእናንተ ዘንድ ጦርና ጠብ ከወዴት ይመጣሉ? በብልቶቻችሁ ውስጥ ከሚዋጉ ከእነዚህ ከምቾቶቻችሁ [‘ከሥጋዊ ምኞቶቻሁ፣’ የ1980 ትርጉም] አይደሉምን?” (ያዕቆብ 4:​1) ብዙውን ጊዜ የራስ ወዳድነት ፍላጎቶችን መቆጣጠር ከተማርን ከሌሎች ጋር የሚፈጠረውን ግጭት ማስወገድ ይቻላል።

● “እያንዳንዱ ለራሱ የሚጠቅመውን አይመልከት፣ ለባልንጀራው ደግሞ እንጂ።” (ፊልጵስዩስ 2:4) ከራሳችን ይልቅ የሌሎችን ፍላጎት ማስቀደም አላስፈላጊ ግጭቶችን ማስወገድ የሚቻልበት ሌላው መንገድ ነው።

● “ከቍጣ ራቅ መዓትንም ተው፤ እንዳትበድል አትቅና።” (መዝሙር 37:8) ጎጂ የሆኑ ውስጣዊ ግፊቶችን መቆጣጠር እንችላለን ደግሞም ይኖርብናል።

● “እግዚአብሔር . . . በምድር ሁሉ ላይ እንዲኖሩ የሰውን ወገኖች ሁሉ ከአንድ ፈጠረ።” (ሥራ 17:24, 26) ሁላችንም ከአንድ ሰብዓዊ ቤተሰብ የመጣን በመሆኑ ሌላ ዘር ካላቸው ሰዎች እንደምንበልጥ አድርጎ ማሰቡ ምክንያታዊ አይደለም።

● “ለወገኔ ይጠቅማል በማለት ወይም በከንቱ ውዳሴ ምክንያት አንድ እንኳ አታድርጉ፣ ነገር ግን እያንዳንዱ ባልንጀራው ከራሱ ይልቅ እንዲሻል በትሕትና ይቊጠር።” (ፊልጵስዩስ 2:3) ሌሎችን ዝቅ አድርጎ መመልከት ትልቅ ሞኝነት ነው። ብዙውን ጊዜ እኛ የሌለን ባሕርይና ችሎታ ይኖራቸዋል። ሁሉንም ጥሩ ነገሮች ጠቅልሎ ለብቻው የያዘ ዘር ወይም ባሕል የለም።

● “እንግዲያስ ጊዜ ካገኘን ዘንድ ለሰው ሁሉ . . . መልካም እናድርግ።” (ገላትያ 6:10) ዘራቸውን ወይም ባሕላቸውን ሳናስብ ወዳጃዊ ሆነን ለመቅረብ እና ሌሎችን ለመርዳት ቀዳሚዎች መሆናችን በመካከላችን ያለውን የሐሳብ ግንኙነት ለማጠናከርና አለመግባባትን ለማስወገድ ያስችላል።

[በገጽ 9 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

ኢትዮጵያውያንና ኤርትራውያን የይሖዋ ምሥክሮች በሰላም አንድ ላይ አምልኳቸውን ያካሂዳሉ

[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በኮሚኒስቶች እስር ቤት የነበረው ማንፍሬት ለጥላቻ እጁን አልሰጠም

[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

መጽሐፍ ቅዱስ ሰዎችን የሚለያየውን አጥር የማፍረስ ኃይል አለው

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ