ጥላቻ የተስፋፋው ለምንድን ነው?
ዓለማችን ይህን ያህል በጥላቻ የተሞላው ለምንድን ነው? ምክንያቱን ለማወቅ የጥላቻን ምንነት፣ ጥላቻ የሚጀመረው እንዴት እንደሆነ እንዲሁም እንዴት እንደሚስፋፋ ማወቅ ይኖርብናል።
ጥላቻ ምንድን ነው?
ጥላቻ አንድን ሰው ወይም አንድን ቡድን የመጸየፍ ወይም ፀር የመሆን ስሜት ነው። ጥላቻ ለአጭር ጊዜ ከሚቆይ የብስጭት ስሜት የዘለለ ነው።
ጥላቻ የሚጀመረው እንዴት ነው?
ሰዎች ሌሎችን መጥላት እንዲጀምሩ የሚያደርጓቸው ብዙ ምክንያቶች አሉ። ብዙዎች የጥላቻ ሰለባ የሚሆኑት ባደረጉት ነገር የተነሳ ሳይሆን በማንነታቸው የተነሳ ነው። እነዚህ ሰዎች ክፉ እንደሆኑ፣ ሌሎችን እንደሚጎዱ ወይም መሻሻል እንደማይችሉ ተደርገው ሊቆጠሩ ይችላሉ። ዝቅተኛ እንደሆኑ፣ አደጋ እንደሚያደርሱ ወይም ችግር ፈጣሪ እንደሆኑ ተደርገው ሊታዩም ይችላሉ። ብዙዎች ለሌሎች ጥላቻ የሚያድርባቸው ቀደም ሲል በደረሰባቸው ዓመፅ፣ የፍትሕ መጓደል ወይም ሌላ መጥፎ ነገር የተነሳ ሊሆን ይችላል።
የሚስፋፋው እንዴት ነው?
አንድ ሰው ጨርሶ አግኝቶ የማያውቀውን ሰው እንኳ ሊጠላ ይችላል። ለምሳሌ ያህል፣ አንድ ሰው የሚወዳቸውና የሚቀርባቸው ሰዎች ያላቸውን የተዛባ አመለካከት ሳያስበው ሊወርስ ይችላል። በዚህ መንገድ ጥላቻ በቀላሉ ይዛመታል፤ ብዙም ሳይቆይ መላው ማኅበረሰብ ተመሳሳይ አመለካከት ሊያዳብር ይችላል።
ጥላቻ ያለውን የመዛመት ኃይል ስንረዳ ይህን ያህል የተስፋፋው ለምን እንደሆነ ግልጽ ይሆንልናል። ይሁንና ዓለምን ተብትቦ የያዘውን የጥላቻ ሰንሰለት ለመበጠስ የጥላቻን አነሳስ ማወቅ ይኖርብናል። መጽሐፍ ቅዱስ ስለዚህ ጉዳይ ይነግረናል።
መጽሐፍ ቅዱስ የጥላቻን ምንጭ ይነግረናል
ጥላቻ የጀመረው ከሰዎች አይደለም። ጥላቻ የጀመረው አንድ የሰማይ መልአክ በአምላክ ላይ ባመፀበት ጊዜ ነው፤ ይህ መልአክ ከጊዜ በኋላ ሰይጣን ዲያብሎስ ተብሎ ተጠርቷል። ዲያብሎስ ዓመፁን “ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ ነፍሰ ገዳይ ነበር።” “ውሸታምና የውሸት አባት” ስለሆነ ጥላቻንና ዓመፅን ማነሳሳቱን ቀጥሏል። (ዮሐንስ 8:44፤ 1 ዮሐንስ 3:11, 12) መጽሐፍ ቅዱስ፣ ዲያብሎስ ክፉ፣ ብስጩና ቁጡ እንደሆነ ይገልጻል።—ኢዮብ 2:7፤ ራእይ 12:9, 12, 17
ፍጹም ያልሆኑ ሰዎች የጥላቻ ዝንባሌ አላቸው። የመጀመሪያው ሰው አዳም የሰይጣንን የኃጢአት ጎዳና ተከትሏል። በመሆኑም የሰው ልጆች በሙሉ ኃጢአትንና አለፍጽምናን ወርሰዋል። (ሮም 5:12) የአዳም የበኩር ልጅ የሆነው ቃየን በጥላቻ ተነሳስቶ የገዛ ወንድሙን አቤልን ገድሎታል። (1 ዮሐንስ 3:12) እርግጥ ነው፣ ፍቅርና ርኅራኄ የሚያሳዩ ብዙ ሰዎች አሉ። ሆኖም ኃጢአትን ስለወረስን ብዙዎች ለጥላቻ መንስኤ የሆኑትን እንደ ራስ ወዳድነት፣ ምቀኝነትና ኩራት ያሉትን ባሕርያት ያንጸባርቃሉ።—2 ጢሞቴዎስ 3:1-5
አለመቻቻል ጥላቻን ያቀጣጥላል። የምንኖርበት ዓለም ጭካኔንና ጎጂ ባሕርያትን በማስፋፋት ጥላቻን ያባብሳል። ‘መላው ዓለም በክፉው ማለትም በሰይጣን ዲያብሎስ ቁጥጥር ሥር ስለሆነ’ አለመቻቻል፣ መድልዎ፣ ስድብ፣ ጉልበተኝነትና ሥርዓት አልበኝነት ተስፋፍቷል።—1 ዮሐንስ 5:19
ይሁንና መጽሐፍ ቅዱስ የጥላቻን መንስኤ በመናገር ብቻ አያበቃም። መፍትሔውንም ይጠቁመናል።