የወጣቶች ጥያቄ . . .
የተናደደ ሰው ሲያጋጥመኝ ምን ማድረግ ይኖርብኛል?
“በጣም ተናድዶ ነበር። ትንሽ መሆኔን ስላየ ነው መሰለኝ ሊደበድበኝ ፈለገ። ወደ ኋላዬ እየሸሸሁ ‘ቆይ እንጂ! ረጋ በል! ለምንድን ነው የምትመታኝ? ምን አደረግሁህ? ለምን እንደ ተናደድህ እንኳን አላውቅም። ብንነጋገር አይሻልም?’ አልኩት።”—የ16 ዓመቱ ዳዊት
በንዴት የጦፈ ጉልበተኛ አጋጥሞህ ያውቃል? መጽሐፍ ቅዱስ ዛሬ ያሉ ሰዎች “ጨካኞች፣ መልካም የሆነውን የማይወዱ፣” እንደሚሆኑ ተንብዮአል። (2 ጢሞቴዎስ 3:3) የቱንም ያህል ‘ከቍጡና ከወፈፍተኛ ሰው’ ጋር ከመወዳጀት ለመራቅ ብትጥር አንዳንድ ጊዜ ንዴተኛ ሰዎች ሊያጋጥሙህ ይችላሉ። (ምሳሌ 22:24) እንደዚህ ዓይነት ሁኔታ ሲያጋጥምህ ምን ማድረግ ይኖርብሃል?
ለቁጣ የምትሰጠው ምላሽ
ዛሬ ያሉ ብዙ ወጣቶች ቁጣን በቁጣ ይመልሱ ይሆናል። ይህ ግን ትርፉ ችግሩን ማባባስ ነው። ከዚህም በላይ ራስህን መቆጣጠር ካቃተህ ከቁጠኛው ሰው አልተለየህም ማለት ነው። ምሳሌ 26:4 እንዲህ ይላል:- “አንተ ደግሞ እርሱን እንዳትመስል ለሰነፍ አንደ ስንፍናው አትመልስለት።” ወጣቱ ጀረሚ የዚህን አባባል እውነተኝነት የተማረው ከመከራ ነው። በትምህርት ቤት የመመገቢያ ጠረጴዛ ዙሪያ ተቀምጠው ሳለ የሆነውን በማስታወስ እንዲህ ይላል:- “እርስ በርሳቸው የሚተራረቡ ወጣቶች ነበሩ። እነዚህ ልጆች ሌሎችንም ይተርባሉ። ብዙ ጊዜ ስለ እኔ ሲያወሩ ችላ ብዬ የማልፋቸው ቢሆንም ከመካከላቸው አንዱ ስለ እናቴ መናገር ሲጀምር ራሴን መቆጣጠር ስላቃተኝ ዘልዬ አነቅኹት።” ውጤቱ ምን ሆነ? “ደህና አድርጎ አቀመሰኝ” ይላል ጀረሚ።
መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ሲል ጥበብ የተሞላበት ምክር ይሰጣል:- “የለዘበች መልስ ቁጣን ትመልሳለች፤ ሸካራ ቃል ግን ቁጣን ታስነሣለች።” (ምሳሌ 15:1) አዎን፣ ለቁጣ “ሸካራ ቃል” መመለስ ትርፉ ሁኔታውን ማባባስ ነው። የለዘበ መልስ ግን ብዙውን ጊዜ ነገሩ ቀዝቀዝ እንዲል ከማድረጉም በላይ ውጥረቱን ለማርገብ ያስችላል።
በመግቢያው ላይ የተጠቀሰውን ዳዊትን አስታውስ። ጉልበተኛውን ልጅ አግባብቶ የተናደደበትን ምክንያት እንዲነግረው አደረገ። ለካስ ልጁ ምሳው ስለተሰረቀበት መጀመሪያ ባገኘው ሰው ላይ ንዴቱን መወጣቱ ነበር። ዳዊት “እኔን ስለደበደብከኝ ምሳህ አይመለስልህም” ሲል አስረዳው። ከዚያም አብረው ወደ መመገቢያ አዳራሹ እንዲሄዱ ሐሳብ አቀረበ። እንዲህ ሲል ያስታውሳል:- “አስተናጋጅዋን አውቃት ስለነበር ምሳውን ተካሁለት። ተጨባብጠን ተለያየን፣ ከዚያ ጊዜ ወዲህ ለኔ ያለው አመለካከት ተቀይሯል።” የለዘቡ ቃላት ምን ያህል ኃይል እንዳላቸው አስተዋልክ? በምሳሌ መጽሐፍ ላይ እንደተገለጸው “ለስላሳ አንደበት ዐጥንትን ይሰብራል።”—ምሳሌ 25:15 አ.መ.ት
የዋህነት ድክመት ነው ወይስ ጥንካሬ?
እርግጥ ነው፣ ‘አንደበታችን ለስላሳ መሆን አለበት’ የሚለው ሐሳብ ለሰዎች አይዋጥላቸው ይሆናል። የጥንካሬ ምልክት ወይም ወንድነት የሚመስለው ቁጣን በቁጣ መመለስ ሊሆን ይችላል። እንዲያውም የዋህ ከሆንኩ ሌሎች ደካማ እንደሆንኩ ያስባሉ ብለህ ትፈራ ይሆናል። ሆኖም የዋህ መሆን ማለት ምን ማለት ነው? አንድ የማመሳከሪያ ጽሑፍ እንዳሰፈረው የዋህ መሆን ማለት ገራም መሆን ማለት ነው። ይሁን እንጂ ይኸው የማመሳከሪያ ጽሑፍ “ከገራምነቱ በስተጀርባ የብረትን ያህል ጥንካሬ አለ” ሲል ጨምሮ ገልጿል። ስለዚህ የዋህነት ከድክመት ይልቅ የጥንካሬ ምልክት ሊሆን ይችላል ማለት ነው። እንዴት?
አንደኛ ነገር የዋህ የሆነ ሰው ራሱን ስለሚቆጣጠር በቀላሉ ሚዛኑን አይስትም። በሌላ በኩል ደግሞ የዋህነት የሚጎድለው ሰው ያልተረጋጋ፣ ብስጩ አልፎ ተርፎም ተስፋ ቢስ ሊሆን ይችላል። ራሱን መግዛትም አይችልም። ስሜቶቹን መቆጣጠር ባለመቻሉ ደግሞ በተደጋጋሚ ከሌሎች ጋር መጋጨቱ አይቀርም። አዎን፣ “ቅጥር እንደሌላት እንደ ፈረሰች ከተማ፣ መንፈሱን የማይከለክል ሰው እንዲሁ ነው።” (ምሳሌ 25:28) እንግዲያው ጠንካራ የሚባለው የዋህ የሆነ ሰው ነው ማለት ነው!
በየዋህነት የተመላለሱ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌዎች
የኢየሱስ ክርስቶስን ምሳሌ ተመልከት። ስለ ራሱ ሲናገር “እኔ የዋህ በልቤም ትሑት ነኝ” ብሏል። (ማቴዎስ 11:29) በክፉ ፈንታ ክፉን የሚመልስ ጨካኝ ወይም ግትር አልነበረም። እንዲያውም የኢየሱስ የቅርብ ወዳጅ የነበረው ሐዋርያው ጴጥሮስ “[ኢየሱስ] ሲሰድቡት መልሶ አልተሳደበም መከራንም ሲቀበል አልዛተም፣ ነገር ግን በጽድቅ ለሚፈርደው ራሱን አሳልፎ ሰጠ” ሲል ዘግቧል። (1 ጴጥሮስ 2:23) ሆኖም ኢየሱስ ራሱ ‘ወደ መቅደስ ገብቶ በመቅደስ የሚሸጡትንና የሚገዙትን ሁሉ እንዳወጣ’ አስታውስ። (ማቴዎስ 21:12) መለኮታዊ ድጋፍ ቢፈልግ ኖሮ ደግሞ “ከአሥራ ሁለት ጭፍሮች የሚበዙ መላእክት” እንዲረዱት መጠየቅ ይችል ነበር! (ማቴዎስ 26:53) ኢየሱስ በፍጹም ደካማ አልነበረም።
መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በመሳፍንት 8:1-3 ላይ ተመዝግቦ የሚገኘውን መስፍኑ ጌዴዎን የተወውን ምሳሌ ደግሞ ተመልከት። ታላቅ ወታደራዊ ድል አግኝቶ ሲመለስ የውጊያው ክብር ተካፋይ የመሆን መብት እንደተነፈጋቸው የተሰማቸው ከኤፍሬም ነገድ የመጡ አንዳንድ ወታደሮች ተቆጥተው ጠበቁት። “ይህ ያደረግህብን ምንድር ነው? ምድያምን ለመዋጋት በወጣህ ጊዜ ለምን አልጠራኸንም?” ሲሉ አፋጠጡት። “ጽኑ ጥልም ተጣሉት።” በመሠረቱ ጌዴዎን “ጽኑዕ ኃያል ሰው” ነበር። (መሳፍንት 6:12) ለዚህ የጠብ አጫሪነት ድርጊታቸው ምላሽ የኃይል እርምጃ መውሰድ ይችል ነበር። ከዚያ ይልቅ ግን የዋህነት የተሞላበት ምላሽ በመስጠት በደም ፍላት የመጡትን ሰዎች አብርዷቸዋል። “እኔ ካደረግሁት እናንተ ያደረጋችሁት አይበልጥምን?” ሲል ጌዴዎን ጠየቀ። ይህ በትህትና የቀረበ ምላሽ ምን ውጤት አስገኘ? “ይህን በተናገረ ጊዜ ቁጣቸው በረደ።”
በመጨረሻም አቢግያ ስለተባለች ሴት የሚናገረውን የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ ተመልከት። ዳዊት ከጠላቱ ከእስራኤል ንጉሥ ከሳኦል ተሸሽጎ በስደት እየኖረ ነው። ከእርሱ ጋር የነበሩት ሰዎች በስደት ላይ ቢሆኑም እስራኤላውያን ወገኖቻቸውን ይጠብቋቸውና ከጥቃት ይከላከሉላቸው ነበር። ከረዷቸው ሰዎች መካከል አንዱ የአቢግያ ባል ናባል ሲሆን በጣም ሀብታም ሰው ነበር። ሆኖም ናባል “ባለጌ . . . ግብሩም ክፉ ነበረ።” ከዳዊት ጋር የነበሩት ሰዎች አንዳንድ ነገር ባስፈለጋቸው ጊዜ ጥቂት ምግብ እንዲሰጣቸው ናባልን ጠየቁት። እሱ ግን ዳዊትና ጭፍሮቹ ውለታ ሳይጠብቁ ላደረጉለት እንክብካቤ አመስጋኝ ከመሆን ይልቅ የዳዊትን መልእክተኞች ‘ሰድቦ’ ባዶ እጃቸውን ሰደዳቸው።—1 ሳሙኤል 25:2-11, 14
ዳዊት ይህንን ሲሰማ በጣም ተቆጥቶ አብረውት የነበሩትን ሰዎች “ሁላችሁ ሰይፋችሁን ታጠቁ” አላቸው። አቢግያ በጉዳዩ እጁዋን ጣልቃ ባስገባችበት ወቅት ዳዊትና ሰዎቹ ናባልንና በቤቱ ያሉትን ንጹሐን ወንዶች በሙሉ ለመግደል እየሄዱ ነበር። ዳዊትን ስታገኘው በጣም ብዙ የምግብና የመጠጥ እጅ መንሻ ይዛ ነበር። ባሏ ላሳየው ይቅርታ የማይደረግለት ምግባር ይቅርታ ከጠየቀች በኋላ ዳዊት ንጹሐን ሰዎችን እንዲምር ለመነችው።—1 ሳሙኤል 25:13, 18-31
አቢግያ በትህትና ያቀረበችው ልመና የዳዊትን ቁጣ አበረደው። ዳዊት ቁጣው ምን ያህል አደገኛ እንደነበር በመገንዘቡ እንዲህ አለ:- “ዛሬ እኔን ለመገናኘት አንቺን የሰደደ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ይመስገን። ወደ ደም እንዳልሄድ፣ በእጄም በቀል እንዳላደርግ ዛሬ የከለከለኝ አእምሮሽ የተመሰገነ ይሁን፣ አንቺም የተመሰገንሽ ሁኚ።” (1 ሳሙኤል 25:32-35) አዎን፣ በብዙ አጋጣሚዎች ‘የለዘበ መልስ’ የሌሎችን ቁጣ ያበርዳል። ይሁን እንጂ በየዋህነት የሰጠኸው ምላሽ የዚህ ዓይነት ውጤት ባያስገኝስ?
“አንተ ራቅ”
ከአካባቢው በመራቅ ነገሮች እንዳይባባሱ ማድረግ ትችላለህ። መጽሐፍ ቅዱስ “እንጨት ባለቀ ጊዜ እሳት ይጠፋል” ይላል። እንዲሁም “ጠብ ሳይበረታ አንተ ራቅ” ሲል ይመክራል። (ምሳሌ 17:14 NW ፤ 26:20) “በትምህርት ቤት ታዋቂ የሆነ ልጅ ወደ እኔ መጥቶ ሊያዋራኝ ፈለገ” ትላለች የ17 ዓመቷ መሪሰ። “ቆንጆ እንደሆንኩ ነገረኝ። ብዙም ሳይቆይ የሴት ጓደኛው እየተንጨረጨረች መጥታ ጓደኛዬን አሽኮረመምሽብኝ በማለት ልትመታኝ ተጋበዘች! ምን እንደተፈጠረ ላስረዳት ሞከርኩ፤ እሷ ግን አላዳመጠችኝም። ከትምህርት ቤት ስንወጣ ከሌሎች ልጃገረዶች ጋር ሆና ልትደበድበኝ መጣች! ቶሎ ብዬ የጥበቃ ሠራተኛውን ጠራሁና መደባደብ እንደማልፈልግ ከነገርኳት በኋላ እኔ እንዳላሽኮረመምኩትና የመጣው ራሱ እንደሆነ አስረዳኋት። ከዚያ ጥያት ሄድኩ።” መሪሰ ለስሜቶቿ አልተሸነፈችም። ከጥል ከመራቋም በላይ ራሷን ለመከላከል እርምጃዎች ወስዳለች። ምሳሌ 17:27 እንደሚለው “ጥቂት ቃልን የሚናገር አዋቂ ነው፣ መንፈሱም ቀዝቃዛ የሆነ አስተዋይ ነው።”
ይሁን እንጂ ምናልባትም ሳታስበው አንድን ሰው አበሳጭተህ ከሆነስ? ቶሎ ብለህ ይቅርታ ጠይቅ! የሌላውን ሰው ቁጣ ለማብረድ የሚያስፈልግህ እንዲህ ማድረግ ብቻ ሊሆን ይችላል። ያለንበት ጊዜ ውጥረት የበዛበት በመሆኑ ብዙ ሰዎች ቶሎ ቁጣ ይቀናቸዋል። ሆኖም ከሌሎች ጋር ባለህ ግንኙነት የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች በተግባር ካዋልክ የተቆጣ ሰው የንዴት መወጫ ከመሆን ልትድን ትችላለህ።
[በገጽ 14 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
“የለዘበች መልስ ቁጣን ትመልሳለች”
[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
አንዳንድ ጊዜ ከአካባቢው ከመራቅ የተሻለ አማራጭ የለም