3. ጥሩ ሰዎች መከራ የሚደርስባቸው ለምንድን ነው?
ይህን ማወቅ ለምን አስፈለገ?
የፍትሕ ስሜት ስላለን ጥሩ ሰዎች መከራ ሲደርስባቸው እናዝናለን። በተጨማሪም እንዲህ ያለው ሁኔታ አንዳንድ ሰዎች ጥሩ ሰው መሆን ምንም ጥቅም እንደሌለው እንዲሰማቸው ያደርጋል።
ሊታሰብባቸው የሚገቡ ነጥቦች
አንዳንዶች መከራ የሚደርስብን በዕድላችን ወይም በዕጣ ፈንታችን ምክንያት እንደሆነ ያምናሉ። በተጨማሪም ክፉ ሰዎች መከራ የሚደርስባቸው አምላክ ስለሚቀጣቸው እንደሆነ ይናገራሉ። ከዚህም ሌላ አምላክ በጥሩ ሰዎች ላይ መከራ የሚያመጣው እምነታቸውን ለመፈተን እንደሆነ ያምናሉ። እንዲያውም ‘ዓለም የፈተና ቦታ እንደሆነች’ ሲናገሩ ይሰማል። ይሁንና ይህ ሐሳብ ያስኬዳል? እስቲ አስበው፦
በሕይወታችን ውስጥ የሚያጋጥሙን ነገሮች የሚወሰኑት በዕድላችን ወይም በዕጣ ፈንታችን ከሆነ ጤናማ ለመሆንና ኃጢአት ላለመሥራት ጥረት ማድረጋችን ምን ጥቅም አለው?
አምላክ ሰዎችን ለመፈተን ሲል መከራ የሚያመጣባቸው ከሆነ በእርግጥ ደግና መሐሪ ነው ሊባል ይችላል?
ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት
jw.org ላይ የሚገኘውን አምላክ መከራ እንዲኖር የፈቀደው ለምንድን ነው? የሚለውን ቪዲዮ ተመልከት።
መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?
መከራ የሚደርስብን አምላክ ስለቀጣን አይደለም።
አብዛኛውን ጊዜ መከራ የሚደርስብን በአጋጣሚ ነው፤ በሌላ አባባል በአጉል ሰዓት አጉል ቦታ ላይ በመገኘታችን መከራ ሊደርስብን ይችላል።
“ፈጣኖች በውድድር ሁልጊዜ አያሸንፉም፤ ኃያላን በውጊያ ሁልጊዜ ድል አይቀናቸውም፤ ጥበበኞች ሁልጊዜ ምግብ አያገኙም፤ አስተዋዮች ሁልጊዜ ሀብት አያገኙም፤ እውቀት ያላቸው ሰዎችም ሁልጊዜ ስኬታማ አይሆኑም፤ ምክንያቱም ሁሉም መጥፎ ጊዜና ያልተጠበቁ ክስተቶች ያጋጥሟቸዋል።”—መክብብ 9:11
ለሚደርስብን መከራ አንዱ መንስኤ ኃጢአተኛ መሆናችን ነው።
አብዛኛውን ጊዜ ሰዎች “ኃጢአት” የሚለውን ቃል የሚጠቀሙበት አንድ ሰው መጥፎ ነገር ሲፈጽም ነው። ሆኖም መጽሐፍ ቅዱስ ይህን ቃል ጥሩ ሰዎችም ሆኑ መጥፎ ሰዎች በዘር የወረሱትን ኃጢአት ለመግለጽም ይጠቀምበታል።
“እነሆ፣ በደለኛ ሆኜ ተወለድኩ፤ እናቴ ከፀነሰችኝ ጊዜ አንስቶ ኃጢአተኛ ነኝ።”—መዝሙር 51:5 የግርጌ ማስታወሻ
ኃጢአት በሰው ልጆች ላይ ብዙ ጉዳት አስከትሏል።
ኃጢአት ከፈጣሪያችን ጋር ያለንን ዝምድና ከማበላሸት ባለፈ ከሌሎች የአምላክ ፍጥረታት ጋር ሰላማዊ ግንኙነት እንዳይኖረን አድርጓል። ይህ ደግሞ በግለሰቦችም ሆነ በመላው የሰው ዘር ላይ ከባድ መከራ እንዲደርስ ምክንያት ሆኗል።
“ትክክል የሆነውን ነገር ማድረግ ስፈልግ ከእኔ ጋር ያለው ግን መጥፎ ነገር ነው።”—ሮም 7:21
“ፍጥረት ሁሉ እስካሁን ድረስ አብሮ በመቃተትና በመሠቃየት ላይ [ይገኛል]።”—ሮም 8:22