የኑሮ ውድነትን መቋቋም
እውነታውን ተቀበል
የሸቀጦች ዋጋ የሚጨምረው ቀስ በቀስ ከሆነ ለውጡን ያን ያህል ላናስተውለው እንችላለን፤ በተለይ ገቢያችንም እኩል የሚሄድ ከሆነ። ይሁን እንጂ የዋጋ ንረቱ ድንገተኛ ሲሆን እንዲሁም ገቢያችን እምብዛም ካልተለወጠ ልንጨነቅ እንችላለን፤ በተለይ የምናስተዳድረው ቤተሰብ ካለን ሁኔታው ያሳስበናል።
የሸቀጦች ዋጋ በእኛ ቁጥጥር ሥር አይደለም። እውነታውን መቀበላችን ግን ይጠቅመናል።
አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
የኑሮ ውድነት ሲከሰት እውነታውን አምነው የሚቀበሉ ሰዎች በአብዛኛው . . .
መረጋጋት አይከብዳቸውም። ስንረጋጋ ደግሞ በደንብ ማሰብና ጥሩ ውሳኔዎች መወሰን እንችላለን።
ተገቢ ካልሆኑ ልማዶች ይቆጠባሉ። ለምሳሌ ክፍያዎችን ችላ አይሉም ወይም አባካኝ አይሆኑም።
ከቤተሰባቸው አባላት ጋር በገንዘብ ዙሪያ አይጨቃጨቁም።
ሁኔታውን ለመቋቋም መንገድ ይፈልጋሉ፤ ለምሳሌ ቅድሚያ የሚሰጧቸውን ነገሮችና የገንዘብ አወጣጣቸውን ያስተካክላሉ።
ምን ማድረግ ትችላለህ?
ማስተካከያ ለማድረግ ፈቃደኛ ሁን። የዋጋ ንረት በሚከሰትበት ወቅት፣ የሚቻል ከሆነ ወጪዎቻችንን መቀነሳችን ጥበብ ነው። አንዳንድ ሰዎች ከገቢያቸው በላይ ቢሆንም የቀድሞ ሕይወታቸውን ላለመተው ብዙ ይፍጨረጨራሉ፤ ሁኔታው በፍጥነት ከሚፈስ ወንዝ በተቃራኒ አቅጣጫ ለመዋኘት እንደመሞከር ነው! ትርፉ ድካም ብቻ ነው። እርግጥ ነው፣ ቤተሰብ ካለህ ለእነሱ የሚያስፈልጋቸውን ነገር ማሟላት መቻልህ ያሳስብህ ይሆናል፤ ደግሞም ይህ ትክክል ነው! ይሁንና ቤተሰብህ ከምንም በላይ የሚፈልገው የአንተን ፍቅር፣ ጊዜ እንዲሁም ትኩረት መሆኑን አትርሳ።
ቀድሞ የነበረንን የምቾት ሕይወት ላለመተው መፍጨርጨር በፍጥነት ከሚፈስ ወንዝ በተቃራኒ አቅጣጫ ለመዋኘት እንደመሞከር ነው