የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • be ጥናት 17 ገጽ 139-ገጽ 142 አን. 1
  • የማይክሮፎን አጠቃቀም

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • የማይክሮፎን አጠቃቀም
  • በቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ከሚሰጠው ሥልጠና ተጠቀም
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • ድምፅን ማሻሻልና የድምፅ ማጉያ አጠቃቀም
    ቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት መመሪያ መጽሐፍ
  • ተስማሚ የድምፅ መጠን
    በቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ከሚሰጠው ሥልጠና ተጠቀም
  • “ሁልጊዜ ደስ ይበላችሁ”! የተባለው የ2020 የክልል ስብሰባ ትርጉም
    የምታደርጉት መዋጮ ጥቅም ላይ እየዋለ ያለው እንዴት ነው?
  • የአገልግሎት ስብሰባ ለበጎ ሥራ ሁሉ የተሟላ ብቃትና ዝግጅት እንዲኖረን ያስችለናል
    የመንግሥት አገልግሎታችን—1994
ለተጨማሪ መረጃ
በቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ከሚሰጠው ሥልጠና ተጠቀም
be ጥናት 17 ገጽ 139-ገጽ 142 አን. 1

ጥናት 17

የማይክሮፎን አጠቃቀም

ምን ማድረግ ይኖርብሃል?

ጉባኤያችሁ ማይክሮፎን ካለው በትክክል ተጠቀምበት።

አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

የምትናገረው ነገር ሌሎችን ሊጠቅም የሚችለው ጥርት ብሎ ከተሰማ ብቻ ነው።

ክርስቲያን ወንድሞቻችንና እህቶቻችን በስብሰባዎች ላይ ለመገኘት ብዙ መሥዋዕትነት ይከፍላሉ። በዚያ ከሚቀርበው ትምህርት እንዲጠቀሙ ካስፈለገ የሚነገረውን ያለችግር መስማት መቻል አለባቸው።

በጥንቷ እስራኤል ዘመን በኤሌክትሪክ የሚሠራ የድምፅ ማጉያ መሣሪያ አልነበረም። እስራኤላውያን ተስፋይቱ ምድር ከመግባታቸው በፊት ሙሴ በሞዓብ ሜዳ ሰብስቦ ንግግር ሲያደርግላቸው በሚልዮን የሚቆጠሩት ተሰብሳቢዎች ድምፁን ሊሰሙ የቻሉት እንዴት ነው? ሙሴ በሰፈሩ ውስጥ በየተወሰነ ርቀት የቆሙ ወንዶች የእርሱን ድምፅ እየተቀበሉ በትክክል እንዲያስተጋቡ አድርጎ መሆን አለበት። (ዘዳ. 1:​1፤ 31:​1) እስራኤላውያን ከዮርዳኖስ በስተ ምዕራብ ያለውን አካባቢ ድል እያደረጉ መቆጣጠር ከጀመሩ በኋላ ብዙም ሳይቆይ ኢያሱ ብሔሩን በገሪዛንና በጌባል ተራሮች ፊት ለፊት ሰብስቧል። በዚህ ጊዜ ሌዋውያኑን በመሃል ባለው ሸለቆ ውስጥ እንዲቆሙ ሳያደርግ አልቀረም። በወቅቱ ሰዉ ሁሉ የተነገረውን መለኮታዊ በረከትና መርገም ሰምቶ ምላሽ ሰጥቷል። (ኢያሱ 8:​33-35) በዚህ ጊዜም ቢሆን የሚነገረውን ቃል ተቀብለው የሚያስተጋቡ ሰዎች ኖረው ሊሆን ይችላል። ይሁንና ድምፅ የማስተጋባት ባሕርይ ያለው የአካባቢው ግሩም መልከዓ ምድራዊ አቀማመጥም አስተዋጽኦ እንደነበረው ግልጽ ነው።

ከ1,500 ዓመት በኋላ ኢየሱስን ለመስማት በገሊላ ባሕር አቅራቢያ “ብዙ ሰዎች” ተሰብስበው ነበር። በዚህ ጊዜ ኢየሱስ በታንኳ ላይ ተቀምጦ ከባሕሩ ዳርቻ ትንሽ ፈቀቅ እንድትል ካደረገ በኋላ ለሕዝቡ መናገር ጀመረ። (ማር. 4:​1, 2) ኢየሱስ ጀልባ ላይ ሆኖ መናገር የመረጠው ለምንድን ነው? ፀጥ ያለ ባሕር የሰዎች ድምፅ ጥርት ብሎ እንዲሰማ ስለሚያደርግ ሊሆን ይችላል።

እስከ 20ኛው መቶ ዘመን መጀመሪያ ድረስ የአንድ ተናጋሪ የድምፅ መጠንና ጥራት የሚለካው የሚናገረውን ነገር በደንብ በሰሙት አድማጮች ብዛት ነበር። ይሁን እንጂ ከ1920ዎቹ ዓመታት አንስቶ የይሖዋ አገልጋዮች በአውራጃ ስብሰባዎቻቸው ላይ በኤሌክትሪክ የሚሠሩ የድምፅ ማጉያ መሣሪያዎችን መጠቀም ጀምረዋል።

የድምፅ መሣሪያዎች። እንዲህ ያሉት መሣሪያዎች የድምፁን ጥራትና ቃና ሳይለውጡ የተናጋሪውን የድምፅ መጠን በብዙ ጊዜ እጥፍ ማጉላት ይችላሉ። ተናጋሪው ድምፁ እንዲሰማ ለማድረግ ጉሮሮው እስኪነቃ መጮህ አያስፈልገውም። አድማጮችም ምን እየተባለ እንዳለ ለመስማት ራሳቸውን ማስጨነቅ አያስፈልጋቸውም። ከዚህ ይልቅ ዘና ብለው ትምህርቱን መከታተል ይችላሉ።

የይሖዋ ምሥክሮች በሚያደርጓቸው የአውራጃና ሌሎች ትልልቅ ስብሰባዎች ላይ ጥሩ የድምፅ መሣሪያዎች እንዲኖሩ የተቻለውን ያህል ጥረት ይደረጋል። ከዚህም በተጨማሪ በብዙ የመንግሥት አዳራሾች ንግግር የሚሰጡትን፣ ስብሰባ የሚመሩትን ወይም ከመድረክ ሆነው የሚያነብቡትን ወንድሞች ድምፅ ለማጉላት የሚያገለግሉ የድምፅ መሣሪያዎች አሉ። አንዳንድ ጉባኤዎች ደግሞ አድማጮች በስብሰባዎች ላይ መልስ ሲሰጡ በማይክሮፎን እንዲጠቀሙ ያደርጋሉ። ጉባኤያችሁ እንደዚህ ዓይነት መሣሪያ ካለው በሚገባ መጠቀም የምትችለው እንዴት እንደሆነ ተማር።

አንዳንድ መሠረታዊ መመሪያዎች። መሣሪያዎቹን በሚገባ ለመጠቀም የሚከተሉትን ነጥቦች አስታውስ:- (1) ማይክሮፎኑ በአብዛኛው ከአፍህ ሊኖረው የሚገባው ርቀት ከ10 እስከ 15 ሴንቲ ሜትር ነው። በጣም ከቀረበ ድምፅህ ሊነፋነፍ ይችላል። በጣም ከራቀ ደግሞ የምትናገረውን መስማት ያስቸግራል። (2) ማይክሮፎኑ ከጎን ሳይሆን ፊት ለፊት ሊሆን ይገባል። ወደ ቀኝ ወይም ወደ ግራ ዞር ካልክ አፍህ በማይክሮፎኑ ትክክል ሲሆን ብቻ መናገር እንዳለብህ አስታውስ። (3) በጣም መጮህ ባያስፈልግህም ከሰዎች ጋር ስታወራ ከምትጠቀምበት የበለጠና ትንሽ ጠንከር ያለ የድምፅ መጠን ሊኖርህ ይገባል። የድምፅ መሣሪያው ሩቅ ላሉት አድማጮችህ ሳይቀር ድምፅህን በቀላሉ ማድረስ ይችላል። (4) ጉሮሮህን መጥረግ ካስፈለገህ ወይም ካሳለህ ወይም ካስነጠሰህ ከማይክሮፎኑ ዘወር በል።

ንግግር ስትሰጥ። መድረክ ላይ ስትወጣ ማይክሮፎኑን የሚያስተካክልልህ ወንድም ይኖራል። በዚህ ጊዜ ከአንገትህ ቀና ብለህ ቁም። ማስታወሻህን አትራኖሱ ላይ አስቀምጥና ማይክሮፎኑ እንደማይከልልህ አረጋግጥ።

መናገር ስትጀምር ከድምፅ ማጉያው የሚወጣውን የራስህን ድምፅ ለመስማት ሞክር። በጣም ይጮሃል? ወይም ደግሞ አንዳንዶቹ ቃላት ይነዝራሉ? ከሆነ ከሁለት እስከ አምስት ሴንቲ ሜትር ራቅ ማለት ያስፈልግህ ይሆናል። ማስታወሻህን በምታይበት ጊዜ፣ መናገርም ሆነ ማንበብ ያለብህ ፊትህ ወደ ማይክሮፎኑ ሆኖ ወይም ትንሽ ከእርሱ ከፍ ብሎ እንጂ ከማይክሮፎኑ በታች መሆን እንደሌለበት አስታውስ።

ከመድረክ ስታነብብ። ፊትህ ወደ አድማጮችህ እንዲሆን መጽሐፍ ቅዱስህንም ሆነ ሌላውን ጽሑፍ ከፍ አድርገህ መያዝህ ጥሩ ይሆናል። በአብዛኛው ማይክሮፎኑ ፊት ለፊት ስለሚሆን የምታነብበውን ጽሑፍ ወደ አንድ ወገን አድርገህ መያዝ ያስፈልግህ ይሆናል። ይህም ጭንቅላትህን በመጠኑ ወደ ሌላኛው ወገን ዘንበል ማድረግ ይጠይቅብሃል። እንደዚያ ከሆነ በምታነብበት ጊዜ ድምፅህ በቀጥታ ወደ ማይክሮፎኑ ይገባል።

በጉባኤ መጠበቂያ ግንብ ሲጠና የሚያነብቡ ወንድሞች ብዙውን ጊዜ የሚጠቀሙት በቁም ማይክሮፎን ነው። ይህም እንደ ልብ እንዲተነፍሱና የመልእክቱን ስሜት ጥሩ አድርጎ በሚገልጽ መንገድ እንዲያነቡ ያስችላቸዋል። በጥናቱ ወቅት ትልቅ ድርሻ ያለው ንባቡ እንደሆነ አትዘንጋ። አድማጮች ከትምህርቱ ይበልጥ የሚጠቀሙት አንቀጾቹ በደንብ ሲነበቡ ነው።

በስብሰባዎች ላይ ሐሳብ ስትሰጥ። በጉባኤያችሁ አድማጮች ሐሳብ በሚሰጡበት ጊዜ ማይክሮፎን የሚጠቀሙ ከሆነ ድምፅህ ጥርት ብሎ እንዲሰማ አጠቃቀሙን ማወቅ ያስፈልግሃል። ሐሳብ በምትሰጥበት ጊዜ ጽሑፉን ወይም መጽሐፍ ቅዱስህን በእጅህ ለመያዝ ሞክር። ይህም በቀላሉ ጽሑፉን እያየህ በማይክሮፎኑ ለመናገር ያስችልሃል።

በአንዳንድ ጉባኤዎች ማይክሮፎን የሚያዞሩ ወንድሞች ይመደባሉ። መልስ ለመስጠት አጋጣሚ ስታገኝ ማይክሮፎኑን የሚያዞረው ወንድም የት እንደተቀመጥህ ዓይቶ እስኪያመጣልህ ድረስ እጅህን አታውርድ። ማይክሮፎኑ በእጅ የሚያዝ ከሆነ ቀልጠፍ ብለህ መቀበል ይኖርብሃል። ማይክሮፎኑ በአፍህ ትክክል ሳይሆን መናገር አትጀምር። እንደጨረስህ ደግሞ ወዲያውኑ መልሰህ ስጥ።

ሠርቶ ማሳያ ስታቀርብ። በሠርቶ ማሳያ ወቅት ማይክሮፎን መጠቀም ቅድመ ዝግጅት የሚጠይቅ ጉዳይ ነው። ማይክሮፎኑ በእጅ የማይያዝ ከሆነ መጽሐፍ ቅዱስህንና ማስታወሻህን ለመያዝ ሁለቱንም እጆችህን እንደልብ መጠቀም ትችላለህ። በእጅህ የሚያዝ ከሆነ ደግሞ ወዲያ ወዲህ ለመንቀሳቀስ ያመችሃል። ሆኖም በዚህ ጊዜ አብሮህ ያለው ሰው እንዲይዝልህ ማድረግ ያስፈልግህ ይሆናል። እንዲህ ካደረግህ መጽሐፍ ቅዱስህን ያለ ችግር መግለጥ ትችላለህ። ስለዚህ አንተም ሆንህ ረዳትህ ማይክሮፎኑን እንዴት በትክክል መያዝ እንደሚቻል አስቀድማችሁ መለማመድ ይኖርባችኋል። ሌላው ደግሞ መድረክ ላይ ስትሆን በተለይ እየተናገርክ ከሆነ ለአድማጮች ጀርባህን መስጠት እንደሌለብህ አስታውስ።

በአገልግሎት ስብሰባ ላይ በርከት ያሉ ተሳታፊዎች ያሉበትና መድረክ ላይ መንቀሳቀስን የሚጠይቅ ሠርቶ ማሳያ ሊኖር ይችላል። በዚህ ጊዜ ከአንድ በላይ ማይክሮፎን ያስፈልግ ይሆናል። እነዚህ ማይክሮፎኖች አስቀድመው ሊዘጋጁ ወይም ደግሞ ሠርቶ ማሳያውን የሚያቀርቡት ወንድሞች ወደ መድረክ ሲወጡ ሊሰጧቸው ይገባል። በተቀናጀ መንገድ ለመሥራት ግን አስቀድሞ ዝግጅት ማድረግ ያስፈልጋል። ሠርቶ ማሳያዎቹ ከመቅረባቸው በፊት የሚደረገው ልምምድ ማይክሮፎኑን በተገቢው መንገድ እንዲጠቀሙበት መመሪያ ለመስጠት ያስችላል። ልምምዱን መድረክ ላይ ማድረግ ካልተቻለ ተሳታፊዎቹ ከማይክሮፎን ጋር የሚመሳሰል መጠን ያለው ነገር በመጠቀም ስለ አያያዛቸው እንዲለማመዱ ማድረጉ የተሻለ ሊሆን ይችላል። ከሠርቶ ማሳያው በኋላ ተሳታፊዎቹ ከመድረክ ሲወርዱ የሌላ ማይክሮፎን ገመድ እንዳይጠልፋቸው ተጠንቅቀው በእጃቸው ይዘውት የነበረውን ማይክሮፎን በቦታው መመለስ ይኖርባቸዋል።

የስብሰባዎቻችን ዋነኛ ዓላማ በአምላክ ቃል ላይ በምናደርገው ውይይት እርስ በርስ መተናነጽ ነው። ማይክሮፎኖችን በሚገባ መጠቀም መቻላችን ደግሞ በዚህ ረገድ ትልቅ ድርሻ አለው። (ዕብ. 10:​24, 25) ስብሰባዎቻችን የሚያንጹ እንዲሆኑ ማይክሮፎኖችን በትክክል መጠቀምን በመማር እኛም የበኩላችንን አስተዋጽዖ ማበርከት እንችላለን።

ይህንን ማድረግ የሚቻልበት መንገድ

  • ማይክሮፎኑ ከአፍህ ከ10 እስከ 15 ሴንቲ ሜትር ይራቅ።

  • መናገር የሚኖርብህ አፍህ በማይክሮፎኑ ትክክል ሲሆን ብቻ እንደሆነ አትዘንጋ።

  • ከሰዎች ጋር ስታወራ ከምትጠቀምበት ከፍ ያለና ትንሽ ጠንከር ያለ የድምፅ መጠን ይኑርህ።

  • ጉሮሮህን መጥረግ ካስፈለገህ ከማይክሮፎኑ ዘወር በል።

መልመጃ፦ በመንግሥት አዳራሻችሁ ውስጥ ማይክሮፎን የምትጠቀሙ ከሆነ ተሞክሮ ያላቸው ተናጋሪዎች በእጅ የሚያዘውንም ሆነ የማይያዘውን ማይክሮፎን እንዴት እንደሚጠቀሙበት ልብ ብለህ ተመልከት። ምን ማድረግ እንዳለብህና እንደሌለብህ ከነምክንያቱ አስብ።

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ