የአገልግሎት ስብሰባ ለበጎ ሥራ ሁሉ የተሟላ ብቃትና ዝግጅት እንዲኖረን ያስችለናል
1 የአገልግሎት ስብሰባ ዓላማ በስብከቱና ደቀ መዛሙርት በማድረጉ ሥራ ሙሉ በሙሉ እንድንካፈል ለማበረታታትና የተሟላ ብቃትና ዝግጅት እንዲኖረን ማድረግ ነው። (2 ጢሞ. 3:17 የ1980 ትርጉም) ይሁን እንጂ ለስብሰባው በደንብ ተዘጋጅተን ካልሄድን ወይም የተማርነውን ካልሠራንበት የምናገኘው ጥቅም እጅግ በጣም አነስተኛ ይሆናል።
2 ስብሰባው ከመደረጉ አስቀድሞ መዘጋጀታችሁ ትምህርቱ በይበልጥ ወደ አእምሮአችሁ እንዲገባ ይረዳችኋል። በስብሰባው ወቅት ውይይት የሚደረግባቸውን ጽሑፎች አስቀድማችሁ ተመልከቷቸው። በተጨማሪም ትዕይንት በሚቀርብበት ወይም ትምህርቱ በሚሰጥበት ጊዜ ለመከታተልና ለመሳተፍ እንድትችሉ ወደ ስብሰባ ይዛችኋቸው ሂዱ። በጥሞና የምታዳምጡ ሁኑ፤ በኋላ ልትጠቀሙባቸው የምትችሏቸውን ነጥቦችም በማስታወሻ ላይ ጻፉ።
3 መሪ የበላይ ተመልካቹ በመንግሥት አገልግሎታችን ላይ የወጣውን ፕሮግራም በጥንቃቄ ይመረምራል። ብቃትና ችሎታ ላላቸው ሽማግሌዎችና ዲያቆናት ክፍሎቹን ይደለድላል። (አገልግሎታችን፤ ገጽ 70 ወይም በአማርኛው ገጽ 37) ጥቂት ሽማግሌዎችና ዲያቆናት ያሏቸው ጉባኤዎች ክፍሉን እንዲያቀርቡ ጥሩ ችሎታ ያላቸውን ሌሎች ወንድሞች ሊመድቡ ይችላሉ። (የመንግሥት አገልግሎታችን፤ ኅዳር 1976 የጥያቄ ሣጥን) እያንዳንዱ ተናጋሪ በደንብ የተዘጋጀና የተሰጠውን መመሪያ አጥብቆ የሚከተል መሆን ይኖርበታል። በተጨማሪም ከተመደበው ሰዓት በላይ ማሳለፍ የለበትም።
4 አብዛኛውን ጊዜ ስብሰባው የሚጀምረው በማስታወቂያዎች ነው። የማስታወቂያውን ክፍል እንዲያቀርብ የተመደበው ወንድም ምን ነገሮች መነገር እንዳለባቸው ለማወቅ አስቀድሞ ከመሪ የበላይ ተመልካቹ ጋር መገናኘት ይኖርበታል። በማስታወቂያ የሚነገሩት ነገሮች ከማኅበሩ የተላኩ ደብዳቤዎችን ወይም የአገልግሎት ቅንጅቶችን ወይም ወርኃዊ የአገልግሎት ሪፖርትን የሚመለከቱ ሊሆኑ ይችላሉ። መጠየቅ ስለሚያስፈልጋቸው የታመሙ ወንድሞችና እኅቶች ወይም ወደፊት በጉባኤው ውስጥ ሊሠሩ ስለታቀዱት እንቅስቃሴዎች ዝርዝር ማብራሪያዎች ይቀርቡልን ይሆናል። አዲስ ነገሮችን ማወቅና የበኩላችሁን ድርሻ ማበርከት ትችሉ ዘንድ የሚነገሩትን ማስታወቂያዎች በጥሞና አዳምጡ።
5 የስብሰባው ከፍል የአድማጮችን ተሳትፎ የሚጠይቅ ከሆነ አንቀጾቹን በማንበብ በደንብ ተዘጋጁ፤ እንዲሁም ጥቅሶቹን አውጥታችሁ ተመልከቱ። የቀረቡትን ነጥቦች ከሌሎች ነገሮች ጋር አገናዝባችሁ ምን ማብራሪያ እንደምትሰጡና ሌሎችን ለማበረታት ምን ዓይነት ሐሳቦችን ልታቀረቡ እንደምትችሉ አስቡ። አጠር ያለ ተሞክሮ በመናገር የትምህርቱን ተግባራዊ ጥቅም በምሳሌ ልታስረዱ ትችላላችሁ።
6 ትዕይንት በሚቀርብበት ጊዜ ራሳችሁን በተመሳሳይ ሁኔታዎች ለማስቀመጥ ሞክሩና ምን ብላችሁ ትናገሩ እንደነበር አስቡ። የቀረቡትን የማሳመኛ ነጥቦችና ምክንያቶች ልብ ብላችሁ አስተውሉ። እንዲህ ዓይነት ሁኔታ አጋጥሟችሁ በነበረበት ጊዜ ምን ብላችሁ ተናግራችሁ እንደነበረ ለማስታወስ ሞክሩ። በተጨማሪም በትዕይንቱ የቀረቡት ነጥቦች ለወደፊቱ የተሻሉ ውጤቶችን እንዴት ሊያስገኙላችሁ እንደሚችሉ አሰላስሉ።
7 በትዕይንቶችና በቃለ ምልልሶች የሚካፈሉ ሁሉ አስቀድመው በደንብ ልምምድ ያደረጉ መሆን ይኖርባቸዋል። እያንዳንዱ መድረክ ላይ ሲወጣ ምን መናገርና ማድረግ እንዳለበት ማወቅ ይኖርበታል። በደንብ ልምምድ ያልተደረገባቸው ክፍሎች አድማጮችን እምብዛም አያበረታቱም ወይም አያነቃቁም። አንዳንዶች ክፍላቸውን ተዘጋጅተው ይመጡና ከመጠበቂያ ግንብ ጥናት በኋላ በመድረክ ላይ ወጥተው ይለማመዳሉ። በዚህ ጊዜ የድምፅ ማጉያውን የሚያስተካክሉ ወንድሞች ምን እንዲያደርጉላቸው እንደሚፈልጉ ያሳውቋቸዋል።
8 አንዳንድ ጊዜ የአገልግሎት ስብሰባው ፕሮግራም ለጉባኤው በሚያስፈልግ በአንድ የተወሰነ ነገር ወይም ወቅታዊ በሆነ የመጠበቂያ ግንብ ርዕስ ላይ የሚሰጥ ንግግርን ሊጨምር ይችላል። በደንብ አዳምጡ፣ የሚሰጠውን ምክር ከልብ ተቀብላችሁ በሥራ ላይ ለማዋል ጣሩ።
9 ‘ለበጎ ሥራ ሁሉ የተዘጋጀን’ ለመሆን እንፈልጋለን። (2 ጢሞ. 2:21) ይሖዋ በዚህ ረገድ እኛን ለመርዳት ካደረጋቸው ዝግጅቶች አንዱ የአገልግሎት ስብሰባ ነው። በስብሰባው ሳናቋርጥ መገኘታችንና የተማርነውን በሥራ ላይ ለማዋል ከልብ ጥረት ማድረጋችን ‘አገልግሎታችንን ሙሉ በሙሉ እንድናከናውን’ እንደሚረዳን የተረጋገጠ ነው። — 2 ጢሞ. 4:5