ፌበን
[ንጹሕ፣ ብሩሕ፣ አንጸባራቂ]።
በመጀመሪያው መቶ ዘመን የክንክራኦስ ጉባኤ አባል የነበረች ክርስቲያን እህት ናት። ጳውሎስ ለሮም ክርስቲያኖች በጻፈው ደብዳቤ ላይ ይህችን እህት ‘ሲያስተውቃቸው’ “እኔን ጨምሮ ለብዙ ወንድሞች ድጋፍ ሆናለች” ብሎ የጻፈ ሲሆን የምትፈልገውን እርዳታ ሁሉ እንዲያደርጉላት ጠይቋቸዋል። (ሮም 16:1, 2) ፌበን፣ ጳውሎስ ለሮም ክርስቲያኖች የላከውን ደብዳቤ አድርሳ አሊያም ደብዳቤውን ካደረሰው ሰው ጋር አብራ ሄዳ ሊሆን ይችላል።
ጳውሎስ ፌበንን “በክንክራኦስ ጉባኤ የምታገለግለው” በማለት ጠቅሷታል። ይህም እዚህ ላይ የገባው ዲያኮኖስ (አገልጋይ) የሚለው ቃል የተሠራበት ከምን አንጻር እንደሆነ ጥያቄ ያስነሳል። አንዳንድ ተርጓሚዎች ቃሉ ሹመትን እንደሚያመለክት በማሰብ “ሴት ዲያቆን” (RS, JB) ብለው ተርጉመውታል። ይሁን እንጂ ቅዱሳን መጻሕፍት ሴቶች የጉባኤ አገልጋይ መሆን እንደሚችሉ አይገልጹም። የጉድስፒድ ትርጉም የቃሉን መሠረታዊ ፍቺ ግምት ውስጥ በማስገባት “ረዳት” ብሎ ተርጉሞታል። ይሁን እንጂ ጳውሎስ ፌበን አገልጋይ እንደሆነች ሲናገር ምሥራቹን እንደምታስፋፋ ማለትም በክርስቲያናዊ አገልግሎት እንደምትካፈል መግለጹ ነበር፤ ፌበን የክንክራኦስ ጉባኤ አባል የሆነች ሴት አገልጋይ ወይም ሰባኪ ነበረች።—ከሥራ 2:17, 18 ጋር አወዳድር።
ፌበን “ለብዙ ወንድሞች ድጋፍ” ሆና አገልግላለች። “ድጋፍ” (ፕሮስታቲስ) ተብሎ የተተረጎመው ቃል መሠረታዊ ትርጉም “ጠባቂ” ወይም “እርዳታ ሰጪ” የሚል ሲሆን እንዲሁ ወዳጃዊ መሆንን ብቻ ሳይሆን ችግር ላይ ለወደቁ ሰዎች መድረስን ያመለክታል። በተጨማሪም “በጎ አድራጊ” ተብሎ ሊተረጎም ይችላል። ፌበን ወደተለያዩ ቦታዎች ለመጓዝና በጉባኤ ውስጥ በግልጽ የሚታይ አገልግሎት ለመስጠት መቻሏ መበለት እንደነበረች እንዲሁም ቁሳዊ ሀብት እንደነበራት ሊያመለክት ይችላል። በመሆኑም በማኅበረሰቡ ውስጥ ተደማጭነት ከነበራት፣ በሐሰት ለሚከሰሱ ክርስቲያኖች ጥብቅና ቆማላቸው ይሆናል፤ ወይም በአደጋ ጊዜ ከለላ በመሆን ጠባቂያቸው ሆና አገልግላ ሊሆን ይችላል። ዘገባው ስለዚህ ጉዳይ በዝርዝር አይናገርም።