የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w96 2/15 ገጽ 30-31
  • ከትምክህተኝነት ተጠበቁ!

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ከትምክህተኝነት ተጠበቁ!
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1996
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • ትምክህተኛ አሳዳጆች
  • ማስጠንቀቂያ የሚሆኑ ታሪኮች
  • ቅዱስ ጽሑፋዊ ምክሮችን ስሙ
  • ኩራት ወደ ትምክህተኝነት ይመራል
  • እብሪት ለውርደት ይዳርጋል
    ክርስቲያናዊ ሕይወታችንና አገልግሎታችን​—የስብሰባው አስተዋጽኦ—2022
  • ትዕቢት ውርደትን ያስከትላል
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2000
  • ‘መታዘዝ ከመሥዋዕት ይበልጣል’
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2011
  • ልክን ማወቅ ዛሬም አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2017
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1996
w96 2/15 ገጽ 30-31

ከትምክህተኝነት ተጠበቁ!

ስሕተት መሥራት የሚፈልግ ማን አለ? ስሕተት መሥራት የሚያሳፍር፣ ብዙውን ጊዜ ደግሞ ከፍተኛ ወጪ የሚጠይቅና በጣም የሚያሳዝን ሊሆን ይችላል! አሳዛኝ የሆኑ ስሕተቶችን ከመፈጸም ለመራቅ እንፈልጋለንን? የምንፈልግ ከሆነ በቀላሉ ወደ ስሕተት ሊመራን ከሚችል አንድ ባሕርይ መጠበቅ አለብን። ከትምክህተኝነት መጠበቅ አለብን!

ትምክህተኝነት ምንድን ነው? “አንድን ልዩ ኃላፊነት ወይም መብት በራስ ሥልጣን መውሰድ፣” “ከገደብ ማለፍ፣” “በተግባርም ሆነ በሐሳብ ያለቦታ ጥልቅ ማለት” ነው። በእርግጥም ትምክህተኝነት አንድ ሰው በራሱ ሐሳብ እንዲመራና ምክርን ወይም እርማትን እንዳይቀበል ያደርገዋል።

ነገር ግን ትምክህተኞች እነማን ናቸው? ክፉ መሆናቸው ገሃድ የወጣ ሰዎች ብቻ ናቸውን? ከትምክህተኝነት መጠበቅ የሚያስፈልጋቸው እነማን ናቸው?

ትምክህተኛ አሳዳጆች

ከሰው ልጆች መካከል ከሁሉ የባሱ ትምክህተኞች የአምላክን ሕዝቦች የሚያሳድዱ ሰዎች ናቸው። ሰዎች ከይሖዋ ይልቅ እነርሱን እንዲታዘዙ ያስገድዳሉ። ከዚህ የሚበልጥ ትምክህተኝነት ሊኖር ይችላልን?

የጥንቱ የባቢሎን ኃያል መንግሥት እንዲህ ያለ ትምክህት አሳይቶ ነበር። በዚህ የተነሳ አምላክ በነቢዩ አማካኝነት ባቢሎን እንደምትጠፋ አስታወቀ። አምላክ “የትዕቢተኞችንም [“የትምክህተኞችንም፣” አዓት] ኩራት እሽራለሁ፣ የጨካኞቹንም ኩራት አዋርዳለሁ” በማለት ገልጾ ነበር። በተጨማሪም “ትዕቢተኛው [“ትምክህተኛው፣” አዓት] ሆይ፣ የመጎብኘትህ ጊዜ፣ ቀንህ ደርሶአልና እነሆ፣ በአንተ ላይ ነኝ” የሚል እናነባለን።—ኢሳይያስ 13:11፤ ኤርምያስ 50:31

በተመሳሳይ በዛሬው ጊዜ አያሌ ትምክህተኛ ሰዎች የይሖዋ ምሥክሮችን አሳደዋል። ሆኖም እነዚህ እብሪተኛ አሳዳጆች አልተሳካላቸውም። እንደ ናዚው አዶልፍ ሂትለርና እንደ ታዋቂው የካናዳው ዱፕሌሲስ ያሉ ትምክህተኞች ዛሬ የት አሉ?

ማስጠንቀቂያ የሚሆኑ ታሪኮች

ሆኖም የአምላክ ሕዝቦች አሳዳጅ ያልሆኑ ሌሎች ሰዎችም በትምክህተኝነት ወጥመድ ውስጥ ወድቀዋል። ይህም አሥራ ሁለት ነገድ ባላት በጥንቷ እስራኤል ላይ የመጀመሪያ ንጉሥ በነበረው በሳኦል ላይ ታይቷል! መጀመሪያ ሲመረጥ ልኩን የሚያውቅ ሰው ነበር። እንዲያውም ለንጉሥነት ሲታጭ ተደብቆ ነበር። (1 ሳሙኤል 10:17-24) ቢሆንም ሳኦል ያገኘው ከፍተኛ ክብር ከጊዜ በኋላ ራሱን በጣም ከፍ አድርጎ እንዲመለከት አደረገው። ውጤቱ ምን ሆነ? የተለያዩ የትምክህተኝነት ተግባራት ፈጸመ።

በመጀመሪያ ደረጃ ከፍልስጤማውያን ጋር በሚዋጋበት ጊዜ ትምክህተኝነት አሳይቷል። ነቢዩ ሳሙኤል ከሳኦል ጋር ተገናኝቶ ለይሖዋ መሥዋዕት ለማቅረብ ቀጠሮ ይዞ ነበር። ነገር ግን ሁኔታው አሳሳቢ ሲሆንና ሳሙኤል ሲቀር መሥዋዕቱን በማንአለብኝነት ራሱ አቀረበ። ውጤቱ ምን ነበር? በትምክህት የፈጸመው ተግባር ንግሥናውን አሳጣው!—1 ሳሙኤል 13:5-14

ከጊዜ በኋላ ይሖዋ እስራኤላውያን በምድረ በዳ ሲጓዙ አማሌቃውያን አድርሰውባቸው የነበረውን ጭካኔ የተሞላበት ጥቃት እንዲበቀል ሳኦልን አዘዘው። ሳኦል አማሌቅን ጠራርጎ ማጥፋት ቢኖርበትም በስስት ተነሳስቶ ከአማሌቃውያን መንጋ ምርጡን አስቀረና እነዚህን እንሰሳት ያስቀረው መሥዋዕት አድርጎ ለማቅረብ እንደሆነ ተናገረ። የአማሌቃውያን ንጉሥ የሆነውን አጋግንም አልገደለውም ነበር። በዚህ የትምክህተኝነት ተግባር ምክንያት ሳሙኤል “የእግዚአብሔርን ቃል [በትምክህተኝነት] ንቀሃልና እግዚአብሔር ንጉሥ እንዳትሆን ናቀህ” በማለት ለሳኦል ነገረው። (1 ሳሙኤል 15:1-23) ትምክህተኝነት እንዴት ያለ አሳዛኝ ውጤት አስከተለበት!

ሌላኛው የማስጠንቀቂያ ምሳሌ ትምክህተኛ ንጉሥ የነበረው የዖዝያን ወይም የዓዛርያስ ሁኔታ ነው። ዖዝያን ያለ ቦታው በይሖዋ ቤተ መቅደስ ዕጣን ለማጠን ሞክሮ ነበር። ውጤቱ ምን ሆነ? ዖዝያን በትምክህት በፈጸመው ነገር የተነሳ ከባድ በሆነ ለምጽ ተመታ! አዎን፣ “እግዚአብሔርም ንጉሡን ቀሠፈው፣ እስከሚሞትበትም ቀን ድረስ ለምጻም ሆነ።” (2 ነገሥት 15:5፤ 2 ዜና መዋዕል 26:16-23) ከትምክህተኝነት እንድንጠበቅ የሚያደርግ እንዴት ያለ ማስጠንቀቂያ ነው!

ቅዱስ ጽሑፋዊ ምክሮችን ስሙ

በጥንት ዘመን ይኖሩ የነበሩ የይሖዋን ሕዝቦች የሚያሳድዱ ሰዎችና ሌላው ቀርቶ ራሳቸውን ለአምላክ የወሰኑ ሰዎች እንኳ በትምክህተኝነት ወጥመድ ተይዘው ነበር። ሆኖም በአሁኑ ጊዜ የምንኖረውስ? ትምክህተኛ የመሆን አደጋ በጊዜያችንም አለ። የወረስናቸው የኃጢአት ዝንባሌዎች፣ የዚህ ክፉ ዓለም ፈተናዎችና የሰይጣን ዲያብሎስ ‘የተንኮል ሥራዎች’ ስላሉብን ትምክህተኛ እንዳንሆን መጠበቅ ያስፈልገናል።—2 ቆሮንቶስ 2:11 የ1980 ትርጉም፤ መዝሙር 51:5፤ 1 ዮሐንስ 2:15-17

ይሖዋ አምላክ በቃሉ አማካኝነት ትምክህተኛ እንዳንሆን በፍቅር ያስጠነቅቀናል። ለምሳሌ “ትዕቢት [“ትምክህት፣” አዓት] ከመጣች ውርደት ትመጣለች፤ በትሑታን [“አቅምና ቦታቸውን በሚያውቁ፣” አዓት] ዘንድ ግን ጥበብ ትገኛለች” በማለት ይናገራል። (ምሳሌ 11:2) ንጉሥ ዳዊት ትምክህት ምን ያህል መጥፎ እንደሆነ በመገንዘብ እንዲህ በማለት ጥበብ የተሞላበት ጸሎት አቅርቧል፦ “የድፍረት ኃጢአት [“ትምክህት” አዓት] እንዳይገዛኝ ባሪያህን ጠብቅ፤ የዚያን ጊዜ . . . ከታላቁም ኃጢአት እነጻለሁ።”—መዝሙር 19:13

ኩራት ወደ ትምክህተኝነት ይመራል

ትምክህተኝነትን ማስወገድ ከፈለግን ከኩራት መሸሽ አለብን። ሳኦል የእስራኤል ንጉሥ ሆኖ በተመረጠበት ጊዜ ልኩን የሚያውቅ እንደነበረ ታስታውሳለህ። ቢሆንም እስከ መጨረሻው በዚህ አልገፋም። በተለያዩ ጊዜያት ትምክህት አሳይቷል። ቢሆንም ትምክህተኛ እንዲሆንና መጥፎ ተግባር እንዲፈጽም የገፋፋው አንዱ ምክንያት ኩራት ነበር።

ሳኦል አንድ ጊዜ የእስራኤል ሴቶች “ሳኦል ሺህ፣ ዳዊትም እልፍ ገደለ” ብለው ሲዘፍኑ ሰማ። ይህም ኩሩ የነበረውን ሳኦልን በጣም አስቆጥቶት ስለነበር ዳዊትን በጥርጣሬና በምቀኝነት ይመለከተው ጀመር። እንዲያውም ሳኦል ዳዊትን ለመግደል በማሰብ ያሳድደው ጀመር። ሳኦል በኩራትና በቁጣ ተነሳስቶ አንዱ አባላቸው ከዳዊት ጋር በመወዳጀቱ ምክንያት 85 ካህናትንና በኖብ ከተማ የሚኖሩ ወንዶችን፣ ሴቶችንና ልጆችን በጠቅላላ ጠራርጎ አጠፋቸው።—1 ሳሙኤል 18:6-9፤ 21:1-10፤ 22:16-19

ሳኦል በኩራቱና በትምክህተኝነቱ በመግፋት በመጨረሻ ራሱን ገደለ። (1 ሳሙኤል 31:4) ከጊዜ በፊት ልኩን ያውቅ የነበረው ሰው ፍጻሜው ምንኛ አሳዛኝ ሆነ!

ሳኦልና ዖዝያን ከተከተሉት የትምክህት መንገድ እንራቅ። በምትኩ ቅዱስ ጽሑፋዊ ምክሮችን እንከተል፤ እንዲሁም በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኙትን የማስጠንቀቂያ ምሳሌዎች እንጠቀምባቸው። (ሮሜ 15:4) በተጨማሪም አቅምንና ቦታን የማወቅ ባሕርይ እናዳብር። ይህ አምላካዊ ባሕርይ ኩራትንና ኃጢአት የሆነውን ትምክህተኝነትን ለማስወገድ ይረዳናል።

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ