የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w99 2/15 ገጽ 30-31
  • ሁልጊዜ ነጥቡን ለማስተዋል ትሞክራለህ?

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ሁልጊዜ ነጥቡን ለማስተዋል ትሞክራለህ?
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1999
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • ትሕትና ይረዳል
  • ‘ለመስማት የፈጠኑ መሆን’
  • በተዘዋዋሪ መንገድ የሚሰጥን ምክር ማስተዋል
  • ምክርን ሰምቶ መከተል በረከቶችን ያስገኛል
  • ‘የጥበበኞችን ቃል አዳምጥ’
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2022
  • ምክርን ስማ፤ ተግሣጽን ተቀበል
    እውነተኛውን አንድ አምላክ አምልክ
  • የምትሰጡት ምክር ‘ልብን ደስ ያሰኛል’?
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2022
  • ሰዎች የምትሰጠውን ምክር ይቀበሉታል?
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1999
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1999
w99 2/15 ገጽ 30-31

ሁልጊዜ ነጥቡን ለማስተዋል ትሞክራለህ?

ታላቅየው ወንድም በጣም ተናድዷል። የተናደደውም በታናሽ ወንድሙ ላይ ነው። ያናደደው ምንድን ነው? ወንድሙ እርሱ ያላገኘውን እውቅና በማግኘቱ ነው። ንዴቱ እየጨመረ ሲሄድ ጎጂ ስሜቱን እንዲቆጣጠር አንድ የቅርብ ወዳጁ መከረው። አለዚያ አንድ መጥፎ ነገር ሊከሰት ነው። ይሁን እንጂ ይህ ሰው የተሰጠውን ጥሩ ምክር ቸል አለ። ምክሩን በመቀበል ፈንታ ታናሽ ወንድሙን በአሠቃቂ ሁኔታ ገደለው።

ይህ ሰው የመጀመሪያዎቹ ወላጆቻችን ማለትም የአዳምና የሔዋን የመጀመሪያ ልጅ የነበረው ቃየል ነው። ይሖዋ፣ አቤል ያቀረበውን መሥዋዕት ተቀብሎ ቃየል ያቀረበውን መሥዋዕት ሳይቀበል በመቅረቱ ቃየል ታናሽ ወንድሙን አቤልን ገደለው። ቃየል በቸልታ ሳይቀበለው የቀረውን ፍቅራዊ ምክር የለገሰው ጠቢብ የሆነው ወዳጅ ከይሖዋ ሌላ ማንም ሊሆን አይችልም። በዚህ መንገድ ገና ባልጠናው ሰብዓዊ ቤተሰብ ውስጥ ግድያ ጀመረ፤ እንዲሁም ቃየል ረዥሙን ቀሪ የሕይወት ዘመኑን ከሰዎች ተገልሎ እንዲኖር ተፈረደበት። ምክር ሲሰጥ የምክሩን ነጥብ አለማስተዋል የሚያስከትለው ውድቀት ምንኛ አሳዛኝ ነው!—ዘፍጥረት 4:3-16

ቃየን ከሞተ ከብዙ መቶ ዘመን በኋላ የእስራኤል ንጉሥ የነበረው ዳዊት ከኬጢያዊው ከኦሪዮን ሚስት ከቤርሳቤህ ጋር ምንዝር ፈጸመ፤ እርሷም ጸነሰች። ኦሪዮን ከሚስቱ ጋር እንዲተኛ ዳዊት ደጋግሞ በመወትወት የተፈጠረውን ችግር ለማዳፈን ሙከራ አድርጎ ነበር። ኦርዮን ግን ከሚስቱ ጋር ለመተኛት እምቢ ባለ ጊዜ ዳዊት ሁኔታዎችን በማቀነባበር በጦር ሜዳ እንዲሞት ካደረገ በኋላ እንደ አመንዝራ ተቆጥራ እንዳትገደል ሲል ቤርሳቤህን አገባ። ይሁን እንጂ አንድ የአምላክ ነቢይ ወደ ዳዊት ሄደና የፈጸመው ድርጊት ምን ያክል ከባድ እንደሆነ ለዳዊት አስገነዘበው። ዳዊት የምክሩን ቁም ነገር ወዲያው አስተዋለ። ዳዊት የፈጸመው ጥፋት በቀሪ የሕይወት ዘመኑ ሥቃይ ያስከተለበት ቢሆንም እንኳ ከልብ የገባውን ንስሐ ይሖዋ ተቀብሎለታል።—2 ሳሙኤል 11:1–12:14

እነዚህ ሁለት ታሪካዊ ምሳሌዎች ምክር የመስማትን አስፈላጊነት ያሳያሉ። ምክርን የመስማት አስፈላጊነት የስኬትና የውድቀት፣ የደስታና የሐዘን ሌላው ቀርቶ የሕይወትና የሞት ጉዳይ ሊሆን ይችላል። መጽሐፍ ቅዱስ “የሰነፍ መንገድ በዓይኑ የቀናች ናት፤ ጠቢብ ግን ምክርን ይሰማል” ብሎ መናገሩ አያስገርምም። (ምሳሌ 12:15) ሆኖም ምክር መስማት ቀላል አይደለም። ቀላል ያልሆነው ለምንድን ነው? በዚህ ረገድ የንጉሥ ዳዊትን ጥሩ ዝንባሌ መኮረጅና የቃየልን መጥፎ ምሳሌ ከመከተል መራቅ የምንችለው እንዴት ነው?

ትሕትና ይረዳል

ሰዎች እርዳታ የሚያስፈልጋቸው መሆኑን አምነው ስለማይቀበሉ ብዙውን ጊዜ የሚሰጣቸውን ምክር መስማት ይቸገራሉ። እርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው ቢያምኑም እንኳ እሱ ማነውና በሚል ዝንባሌ ምክሩን መቀበል እንደሌለባቸው ይሰማቸዋል። ይህ ዓይነቱ አመለካከት ኩራት ነው፤ በመጠኑም ቢሆን ነገሮችን ለማመዛዘን መሞከር እንዲህ ያለውን ኩራት ለማሸነፍ ሊረዳ ይችላል። ለምሳሌ ያህል ጳውሎስ “ሁሉ ኃጢአትን ሠርተዋልና የእግዚአብሔርም ክብር ጎድሎአቸዋል” በማለት ተናግሯል። (ሮሜ 3:23) ይህ ጥቅስ ሁሉም ሰው በየጊዜው ምክር እንደሚያስፈልገው ይነግረናል። በተጨማሪም ምክር የሚሰጡን ሰዎችም ቢሆኑ ጉድለቶች እንዳሉባቸው ይገልጽልናል። ከዚህ ነፃ የሆነ ማንም ሰው የለም። ስለዚህ አንድ ሰው ጉድለቶች ያሉበት መሆኑ ምክር ለመስጠት በሚያስችለው ቦታ ላይ ሆኖ የሚሰጥህን ማንኛውንም ዓይነት እርዳታ እንዳትቀበል እንቅፋት እንዲሆንብህ አትፍቀድ።

ኢየሱስ ለተከታዮቹ “ካልተመለሳችሁ እንደ ሕፃናትም ካልሆናችሁ፣ ወደ መንግሥተ ሰማያት ከቶ አትገቡም” ብሎ በተናገረ ጊዜ ኩራትን የመዋጋትን አስፈላጊነት ጠበቅ አድርጎ ገልጿል። (ማቴዎስ 18:3) ወላጆች ልጆቻቸውን ሲመክሩና መመሪያ ሲሰጧቸው ልጆች የደህንነት ስሜት ይሰማቸዋል። አንድ ሰው ሲመክርህ እንዲህ ያለው ምክር ሰውየው የሚወድህና የሚያስብልህ መሆኑን የሚያረጋግጥ እንደሆነ አድርገህ በመገንዘብ አንተም ተመሳሳይ የሆነ የደህንነት ስሜት ይሰማሃልን? (ዕብራውያን 12:6) ንጉሥ ዳዊት ምክር ለመቀበል ፈቃደኛ መሆኑ የገባውን ንስሐ ይሖዋ እንዲቀበልለት በር ከፍቶለታል። ከዚህም የተነሳ “ጻድቅ በምሕረት ይገሥጸኝ፣ ይዝለፈኝም፣ የኃጢአተኛ ዘይት ግን ራሴን አይቅባ” ብሎ ለመጻፍ ተገፋፍቷል።—መዝሙር 141:5

እንዲህ ያለው የትሕትና ባሕርይ ግልጽ የሆነ ሕግ ያልወጣላቸውን ጉዳዮች በሚመለከት ምክር በሚሰጠን ጊዜ ምክሩን እንድንቀበል ሊረዳን ይችላል። ለምሳሌ ያህል አጋጌጣችንና አለባበሳችን በጉባኤ ያሉ አንዳንድ ሰዎችን የሚያሰናክል እንደሆነ ምክር ቢሰጠን ምክሩን ለማስተዋል ልባዊ ትሕትና ይጠይቃል። ያም ሆነ ይህ እንዲህ ማድረጉ ሐዋርያው ጳውሎስ “እያንዳንዱ የባልንጀራውን ጥቅም እንጂ አንድ ስንኳ የራሱን ጥቅም አይፈልግ” ብሎ የተናገረውን ምክር እየተከተልን እንዳለን ያሳያል።—1 ቆሮንቶስ 10:24

ይሖዋ ከሁሉ የተሻለ ምክር የያዘውን መጽሐፍ ቅዱስን ስለ ሰጠን ደስ ይለናል። እንዲያውም “ምክር” የሚለው ቃል በተለያዩ መንገዶች ከ170 ጊዜ በላይ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ሰፍሮ እናገኘዋለን። በተጨማሪም ይህን ምክር በሕይወታችን ላይ መተግበር እንድንችል የሚረዱን አፍቃሪ እረኞችን ሰጥቶናል። የቤተሰብ ዝግጅትም ቢሆን ኃላፊነቶቻቸውን ጠንቅቀው የሚያውቁ ወላጆች በሚሰጡን ምክር አማካኝነት ፍቅራዊ እርዳታ የምናገኝበት ሌላው የይሖዋ ስጦታ ነው። ከእነዚህ የሚመጡትን ምክሮች ሁልጊዜ በትሕትና የምንቀበል እንሁን።

‘ለመስማት የፈጠኑ መሆን’

ያዕቆብ 1:19 “ሰው ሁሉ ለመስማት የፈጠነ ለመናገርም የዘገየ ለቁጣም የዘገየ ይሁን” በማለት ይመክረናል። በተለይ ምክር ሲሰጠን ለመስማት የፈጠንን መሆን ያስፈልገናል። ለምን? ብዙውን ጊዜ ድክመቶቻችን ለእኛ የተሰወሩ ባለመሆናቸው የሚያስብልን አንድ ወዳጃችን ቀርቦ እነዚህን ድክመቶቻችንን በማንሣት ሲመክረን ለጉዳዩ እንግዳ አለመሆናችን እውነት አይደለምን? ሊናገር የፈለገውን ነገር ወዲያው ተገንዝበን ፍቅራዊ እርዳታውን በትሕትና ብንቀበል ለመካሪውም ለተመካሪው ቀላል ይሆንለታል።

አንድ ወዳጃችን እኛን ለመምከር በሚመጣበት ጊዜ እርሱ ወይም እርሷ ትንሽ የመረበሽ ስሜት ሊኖራቸው እንደሚችል ማስታወስ ይኖርብናል። ምክር መስጠት ቀላል አይደለም። ጥሩ መካሪ ነኝ የሚል ሰውም እንኳ ቢሆን ምን መናገርና እንዴት ብሎ መቅረብ እንዳለበት አስቀድሞ ማሰቡ አይቀርም። አንድ ሽማግሌ በክርስቲያናዊ አገልግሎት ጥሩ እንቅስቃሴ ያደረግንባቸውን ጥሩ ጥሩ ጎኖች እያነሳ በመናገር ንግግሩን ሊጀምር ይችላል። ይሁን እንጂ ምክር መስጠት ሲጀምር ምክሩን ለመስጠት የተነሳሳበትን ምክንያት ጥርጣሬ ውስጥ አንከተውም። ምክር ሰጪው ብልሃት በጎደለው ሁኔታ ጉዳዩን ፊት ለፊት አንስቶ ላለመናገር ሲል መጀመሪያ ላይ በተዘዋዋሪ መንገድ መናገር ይጀምር ይሆናል። ሊናገር የፈለገውን ነጥብ ቶሎ ማስተዋላችን ምክር ሰጪው በቀላሉ ኃላፊነቱን እንዲወጣ ከማስቻሉም በላይ እኛም ስሜታችን እንዳይጎዳ ሊጠብቀን ይችላል።

አንዳንድ ጊዜ ምክር ሰጪው ነጥቡን በቀላሉ እንድናስተውል ሲል አንድ ምሳሌ ሊጠቀም ይችላል። አንድ ወጣት ከባድ ኃጢአት አልፈጸመም፤ ሆኖም ወደዚያው በማምራት ላይ ነበር። አንድ በዕድሜ የገፋ ክርስቲያን ይህን ወጣት ምክንያታዊ በሆነ መንገድ ለማስረዳት ጠረጴዛው ላይ የነበረውን አንድ ማስመሪያ አነሳ። ማስመሪያውን በእጁ አጉብጦ ከያዘ በኋላ “ይህን ማስመሪያ እንዲህ አጉብጬ ይዤ አንድ ቀጥ ያለ መስመር መለካት እችላለሁን?” ሲል ጠየቀው። ወጣቱ ወዲያው ነጥቡን አስተዋለ። ከራሱ ፍላጎት ጋር ለማስማማት ሲል ሕጎችን ለማጉበጥ ሲሞክር ቆይቷል። የቀረበለት ይህ ምሳሌ “ምክርን ስማ፣ ተግሣጽንም ተቀበል በፍጻሜህ ጠቢብ ትሆን ዘንድ” የሚለውን በምሳሌ 19:20 ላይ የሰፈረውን ጥበብ ያዘለ ምክር እንዲከተል አስችሎታል።

በተዘዋዋሪ መንገድ የሚሰጥን ምክር ማስተዋል

እንዲህ ያለውን ማስተዋል ማግኘታችን የሌላ የማንም ሰው ጣልቃ ገብነት ሳይኖር በተዘዋዋሪ መንገድ ከሚሰጥ ምክርም ጥቅም እንድናገኝ ያስችለናል። ይህ ሁኔታ ፖርቱጋል በሚኖር በአንድ ወጣት ላይ ሠርቷል። መጽሐፍ ቅዱስን በማጥናት ላይ የነበረ ሲሆን ወጣትነትህን ከሁሉ በተሻለ መንገድ ተጠቀምበት የተባለውን መጽሐፍም አንድ ቅጂ አገኘ። ገና ጥቂት ቀናት ከማለፋቸው መጽሐፉን ሦስት ጊዜ አንብቦ እንደጨረሰና ከፍተኛ ጥቅምም እንዳገኘ ተናገረ። በምን መንገድ? ወጣቱ እንዲህ በማለት ተናግሯል:-

“ለወደፊቱ ጊዜ ምንም ዓይነት ብሩህ አመለካከት አልነበረኝም። ይሁን እንጂ ምዕራፍ 2 [“የወደፊቱን ጊዜ በልበ ሙሉነት ለማየት የምትችለው ለምንድን ነው?”] ሕይወቴ ትርጉም እንዲኖረው አደረገልኝ። እንዲሁም ከተወሰኑ ዓመታት ጀምሬ ማስተርቤሽን እፈጽም ነበር። ይህ ድርጊት አምላክን የሚያሳዝን እንደሆነና በእኔ ላይም ጉዳት ሊያስከትል እንደሚችል የነገረኝ ማንም ሰው አልነበረም። ምዕራፍ 5ን [“ማስተርቤሽንና ግብረ ሰዶም”] ካነበብኩ በኋላ ይህን ልማድ ለማቆም ወሰንኩ። ምዕራፍ 7 [“አለባበሳችሁና የሰውነታችሁ አቋም ስለ እናንተ ይናገራል”] ቁመናዬን መለስ ብዬ እንድመለከት ረዳኝ፤ አሁን እንደምታዩኝ ፀጉሬን ተቆርጫለሁ።”ከዚህ በታች ባለው ዝርዝር ለእያንዳንዱ ረድፍ ተራ ቁጥር የተሰጠው ከፊት ወደ ኋላ ሲሆን ስሞቹ የሰፈሩት ከግራ ወደ ቀኝ ነው።

እንዲህ በማለት ይቀጥላል:- “ለብዙ ዓመታት አጨስ ነበር። ምዕራፍ 15 [“ለጥሩ ሕይወት ቁልፉ አደንዛዥ መድኃኒቶች ናቸውን?”] በዚህ ረገድ የነበረኝን አመለካከት ለውጦልኛል። ወደ ይሖዋ ጸለይኩ፤ ይኸው ከእሁድ ጀምሮ አንድም ሲጋራ አላጨስኩም። ባለፉት ጊዜያት ከሴት ጓደኛዬ ጋር የፆታ ግንኙነት ስፈጽም ቆይቻለሁ። ይሁን እንጂ ምዕራፍ 18 [“የፆታ ስነ ምግባር ምክንያታዊ መስሎ ይታይሃልን?”] አምላክ በዚህ ረገድ ያለውን አመለካከት እንድገነዘብ ረዳኝ። ይህን ጉዳይ በተመለከተ አነጋግሬያታለሁ። እርሷም ግንኙነታችንን ለማቆም ተስማምታለች።”

አንድ ወጣት እንዲህ በአጭር ጊዜ ውስጥ ይህን የመሰሉ ለውጦች ሲያደርግ መመልከት ምንኛ የሚያስደስት ነገር ነው! እንዲህ ሊሳካለት የቻለው ለምንድን ነው? ያነበባቸው ነገሮች እርሱን በግል የሚመለከቱት እንደሆኑ በመገንዘቡና ምክሮቹን ለማስተዋል በመቻሉ ነው።

ምክርን ሰምቶ መከተል በረከቶችን ያስገኛል

በተዘዋዋሪ መንገድ ከመጽሐፍ ቅዱስ ወይም በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ከተመሠረቱ ጽሑፎች የምናገኘውም ይሁን በቀጥታ በአንድ ወዳጃችን የሚነግረን ምክር ጠቃሚያችን ሊሆን ይችላል። የሚሰጠውን ተግሣጽ አልሰማ ያለ አንድ የ18 ዓመት ልጅ ያለው በጉባኤው ያሉ ሽማግሌዎችን እርዳታ የጠየቀ አንድ አባት ያጋጠመው ሁኔታ ይህ ነገር እውነት መሆኑን ያሳያል። ክርስቲያን ሽማግሌዎች አምላክን ለማገልገል ቀናተኛ ከሆነውና ከቤተሰቡ ጋር ባለው ግንኙነት ግን ይበልጥ ሚዛናዊ መሆን ከሚያስፈልገው ከዚህ አባት ጋር በፍቅር ላይ የተመሠረተ ጥሩ ውይይት አደረጉ።

“እናንተም አባቶች ሆይ፣ ልጆቻችሁን በጌታ ምክርና በተግሣጽ አሳድጉአቸው እንጂ አታስቆጡአቸው” የሚለውን የጳውሎስን ቃላት አነበቡለት። (ኤፌሶን 6:4) አባትየው በሚከተሉት ነጥቦች ላይ እንዲያስብባቸው ነገሩት:- ምንም እንኳ በአሳቢነት የሚያደርገው ቢሆንም ልጁን ለማበረታታት የሚጠቀምበት መንገድ ልጁን የሚያስቆጣው ይሆን? በቅድሚያ ልጁ ለክርስቲያናዊ ስብሰባዎችና ለአገልግሎት በውስጡ ፍቅር እንዲቀረጽበት ሳያደርግ በእነዚህ ነገሮች ረገድ ልጁ የእሱ ዓይነት ቅንዓት እንዲያሳይ ጠብቆበት ይሆንን? ልጁ ‘ይሖዋ አምላኩን መፍራት እንዲማር ’ ረድቶታልን?—ዘዳግም 31:12, 13

አባትየው የተሰጠውን ምክር ተቀበለና ሠራበት። ታዲያ ውጤቱ ምን ሆነ? የ18 ዓመት ልጁ አሁን በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ ይገኛል እንዲሁም አባትየው በየሳምንቱ መጽሐፍ ቅዱስ ያስጠናዋል። አባትየው “አሁን ጥሩ የሆነ የአባትነትና የልጅነት ዝምድና አዳብረናል” በማለት ይናገራል። አዎን፣ አባትየውም ሆነ ልጁ የተሰጣቸውን ምክር ለማስተዋል ችለዋል።

ሁላችንም ስህተት እንደምንሠራና በየጊዜው ምክር እንደሚያስፈልገን ምንም ጥርጥር የለውም። (ምሳሌ 24:6) ነጥቡን የምናስተውልና የተሰጠንን ጥበብ የተሞላበት ምክር በጥንቃቄ የምንከተል ከሆነ ብዙ በረከቶችን እናጭዳለን። ከእነዚህ መካከል የሚከተለው ተወዳዳሪ የማይገኝለት በረከት ይገኝበታል:- አፍቃሪ ከሆነው ከሰማዩ አባታችን ከይሖዋ ጋር ትርጉም ያለው የግል ዝምድና ለመመሥረትና ይህንንም ዝምድና ጠብቀን ለማቆየት ያስችለናል። እኛም “የመከረኝን እግዚአብሔርን እባርካለሁ” ብሎ የተናገረውን የንጉሥ ዳዊትን ቃላት የምናስተጋባ እንሆናለን።—መዝሙር 16:7

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ