ቤዛ—ደብዛው የጠፋው የሕዝበ ክርስትና መሠረተ ትምህርት
ኢየሱስ ለኃጢአተኞች የሰው ልጆች ልዋጭ በመሆን ሞቶአል የሚለው የቤዛ እምነት የእውነተኛው ክርስትና መሠረት ነው። ነገር ግን የሕዝበ ክርስትና ሃይማኖታዊ ሊቃውንት ይህን መሠረተ ትምህርት ለብዙ ዘመናት ሲተቹትና ሲዘብቱበት ቆይተዋል።
ይህ የሆነው ለምንድን ነው? ኢየሱስ ራሱ በማርቆስ 10:45 ላይ “የሰው ልጅ ሊያገለግልና ነፍሱን ለብዙዎች ቤዛ ሊሰጥ እንጂ እንዲያገለግሉት አልመጣም” ብሎ የለምን?
አንዳንዶች እነዚህ ቃላት ኢየሱስ ከሞተ በኋላ በሐዋርያው ጳውሎስ ግፊት የተጨመሩ ናቸው እንጂ ኢየሱስ ራሱ የተናገራቸው አይደሉም ይላሉ። ሌሎች ደግሞ እዚህ ላይ ቤዛ የተጠቀሰው የአነጋገር ዘይቤ እንዲሆን ብቻ ነው ወይም ከግሪካውያን አፈታሪክ የተወሰደ መሠረተ ትምህርት ነው ብለው ይከራከራሉ። ስለዚህ ቤዛ ከቤተክርስቲያናት ትምህርት ፈጽሞ ጠፍቶአል።
ይሁን እንጂ ታዲያ የጥንት ክርስቲያኖች የኢየሱስን ሞት እንዴት ይረዱት ነበር? ብለህ ትጠይቅ ይሆናል። ጳውሎስ በ2 ቆሮንቶስ 5:14, 15 ላይ እንዲህ በማለት ይነግረናል፦ “የክርስቶስ ፍቅር ግድ ይለናልና፤ አንዱ ስለ ሁሉ ሞተ . . . በሕይወትም ያሉት ስለ እነርሱ ለሞተውና ለተነሣው እንጂ ወደፊት ለራሳቸው እንዳይኖሩ ስለ ሁሉ ሞተ።” ይህ አነጋገር የቤተክርስቲያን ሊቃውንት በኋላ ዘመን ካመጡአቸው የተወሳሰቡ ጭማሪዎች ሁሉ ነጻ የሆነ ግልጽና ቀላል መሠረተ ትምህርት ነው።
ይህን መሠረተ ትምህርት የፈለሰፈው ጳውሎስ ሊሆን ይችላልን? አይችልም፤ ምክንያቱም በ1 ቆሮንቶስ 15:3 ላይ “እኔ ደግሞ የተቀበልሁትን ከሁሉ በፊት አሳልፌ ሰጠኋችሁ። . . . መጽሐፍ እንደሚል ክርስቶስ ስለ ኃጢአታችን ሞተ” በማለት ይገልጻል። ጳውሎስ መልእክቶቹን ከመጻፉ ከብዙ ዓመታት በፊት ጀምሮ ክርስቲያኖች የኢየሱስ ሞት መሥዋዕታዊ እንደሆነ፣ ኃጢአተኞቹን የሰው ልጆች ለመቤዠት የተከፈለ ዋጋ እንደሆነና ቤዛ እንደሆነ ያምኑ እንደነበረ ግልጽ ነው። ከዚህም በላይ ጳውሎስ እንዳመለከተው የክርስቶስ ሞት እንደ መዝሙር 22 እና ኢሳይያስ 53 ያሉትን “የብሉይ ኪዳን” ወይም የዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች “መጻሕፍት” ትንቢት እንደሚፈጽም ያውቁ ነበር።
መልስ ያላገኙ ጥያቄዎች
እውነቱን ራስህ መርምረህ ለማወቅ ከፈለግህ የክህደት ትምህርት ወደ ክርስትና ሰርጎ የገባው ከሐዋርያት ዘመን ጀምሮ እንደሆነ ትገነዘባለህ። (ሥራ 20:29, 30፤ 2 ጢሞቴዎስ 4:3, 4) ነገር ግን የጥንት ቤተክርስቲያን ጽሑፎች እንደሚያመለክቱት በክርስቶስ ቤዛዊ መሥዋዕት ማመን ለብዙ ዘመናት ጸንቶ ቆይቶ ነበር። ይሁን እንጂ በኋለኞቹ ዘመናት የተነሱ የሃይማኖት ሊቃውንት የቤዛን መሰረተ ትምህርት ጠለቅ ብለው መመርመር ሲጀምሩ ቤዛው የተከፈለው ለማን ነው? እንዲህ ያለውስ ክፍያ ያስፈለገው ለምንድን ነው? የሚሉትን የመሰሉ ከባድ ጥያቄዎች አጋጠሙአቸው።
በአራተኛው መቶ ዘመን እዘአ ላይ የኒሳው ግሪጎሪና ሌሎች ሰዎች ቤዛው የተከፈለው ለሰይጣን ዲያብሎስ ነው ብለው ማስተማር ጀመሩ። የሰው ልጆችን የሚቆጣጠረው ሰይጣን ስለሆነ የሰው ልጆችን ነጻ የሚያወጣው ቤዛ የተከፈለው ለሰይጣን ነው ብለው ተከራከሩ። ይሁን እንጂ በዚሁ ዘመን ይኖር የነበረ የናዚያንዙስ ግሪጎሪ የተባለ ሰው ይህ ዓይነት ትምህርት አንድ ትልቅ ክፍተት እንዳለው ተመለከተ። አምላክ ለሰይጣን ዕዳ እንዳለበት የሚያስመስል እምነት ሆኖ ታየው። እውነትም በፍጹም ሊሆን የማይችል ትምህርት ነበር። ቢሆንም ቤዛው የተከፈለው ለሰይጣን ነው የሚለው ትምህርት ኃይል እያገኘ መጥቶ ለብዙ መቶ ዓመታት እየተንገዳገደ ቆየ።
ቤዛው የተከፈለው ለአምላክ ይሆንን? የናዚያንዙሱ ግሪጎሪ ይህም አስተሳሰብ ችግር እንዳለበት ተሰምቶት ነበር። ‘የአምላክ ምርኮኞች ባለመሆናችን’ ለአምላክ ቤዛ መክፈል ለምን ያስፈልጋል? ብሎአል። በተጨማሪም አብ ቤዛ ይከፈለኝ ብሎ ልጁ እንዲሞት በማድረግ ደስታ ያገኛልን? እነዚህ በቤዛው ላይ ጥርጣሬ የሚጥሉ አስቸጋሪ የሚመስሉ ጥያቄዎች ናቸው።
የቤዛው እምነት መሞት
ስለዚህ ይህን ጉዳይ ለመመርመር ወደ 12ኛው መቶ ዘመን መመለስ ሊያስፈልግ ይችላል። አንሰልም የተባሉት የካንተርበሪ ሊቀጳጳስ አምላክ ለምን ሰው እንደሆነ? በተባለው መጽሐፋቸው እነዚህን ጥያቄዎች ለመመለስ ሞክረዋል። መጽሐፉ የክርስቶስ ሞት ቤዛ ባይሆንም መለኮታዊ ፍትሕ የሚጠይቀውን ለማሟላት አገልግሎአል በማለት አስተምሮአል። ፍትሕ የሚጠይቀው ብቃት ሳይሟላ በቤዛው አማካኝነት ኃጢአትን ይቅር ማለት ኃጢአት ሳይታረም እንዲቀር ከመፍቀድ ተለይቶ ሊታይ አይችልም በማለት አንሰልም ተናገሩ። “አምላክ ግን በመንግሥቱ ውስጥ ያልታረመና ያልተስተካከለ ነገር እንዲኖር አይፈቅድም” ብለዋል አንሰልም። ታዲያ አምላክ ነገሮችን ያስተካከለው እንዴት ነው?
አንሰልም ‘ኃጢአት ለአምላክ ክብር የማይሰጥ ነው’ ካሉ በኋላ የአዳም ኃጢአት “ያሳጣውን መልሶ መስጠት“ በቂ አይሆንም ብለዋል። አምላክ ስለተሰደበ ፍጹም የሆነ ሰው ተሰውቶ ቤዛ መከፈሉ እንኳን በቂ አይሆንም። እኚሁ ሃይማኖታዊ ባለሥልጣን “ከታጣው የበለጠ ነገር መከፈል ይኖርበታል” ብለዋል። ይህ በመሆኑ “አምላክም ሰውም የሆነ እንዲሞት የሚያስገድድ ሆነ” በማለት አንሰልም ይከራከራሉ።
ለአንሰልም ትምህርት ምንም ዓይነት አመለካከት ቢኖርህ በዘመኑ የነበሩትን ሰዎች አሳምኖአቸው ነበር። በዘመናችንም ቢሆን ይህ ትምህርት ኃይሉን አላጣም። አንሰልም በአንድ ምት የሥላሴን ትምህርት አጠናክሮ ቢያንስ በሕዝበ ክርስትና ውስጥ የቤዛን ትምህርት ፈጽሞ ገድሎታል። “ቤዛ” የሚለው ቃል ቀስ በቀስ እየተረሳ ሄዶ ሃይማኖታውያን ሊቃውንት በአብዛኛው የሚጠቀሙበት ቃል “ረክተናል” የሚል ሆነ። ይሁን እንጂ የአንሰልም ንድፈ ሐሳብ በአብዛኛው የተመሰረተው በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ሳይሆን በግል ግምታዊ አስተሳሰብ ላይ ብቻ ነው። ጊዜው እያለፈ በሄደ መጠን እንደ ቶማስ አኪናስ የመሰሉት ምሑራን የየራሳቸውን ምክንያታዊ አስተሳሰብ በመጨመር የአንሰልምን “የእርካታ” ንድፈ ሐሳብ መቆነጻጸል ጀመሩ። የግምት አስተሳሰብ እየተስፋፋ ሄደ። የመቤዠት ንድፈ ሐሳቦች እየበዙ ሄዱ። ክርክሩም ከቅዱሳን ጽሑፎች እየራቀ ወደ ሰብዓዊ አስተሳሰቦች፣ ፍልስፍናዎችና ምሥጢሮች ጠልቆ መግባት ጀመረ።
የተሐድሶ እንቅስቃሴና ቤዛው
አሁን ደግሞ ወደ ዘመናችን ትንሽ ቀረብ እንበል። የፕሮቴስታንቶች የተሐድሶ እንቅስቃሴ ማዕበል ባጥለቀለቀበት በ16ኛው መቶ ዓመት ሶስናውያን የሚባል ሃይማኖታዊ ቡድን ተወለደ።a ይህ ቡድን የኢየሱስ ሞት በምንም መንገድ “ደህንነት እንዳስገኘልን” ክዶ ይህ እምነት “ሐሰተኛ፣ የተሳሳተ፣ ግልጽ ያልሆነ . . . ከቅዱሳን ጽሑፎችም ሆነ ከምክንያታዊ አስተሳሰብ የሚቃረን” እንደሆነ ገልጾአል። (ዘ ራኮቪያን ካቴኪዝም) አምላክ ይቅር የሚለው በነጻ ስለሆነ ምንም ዓይነት መሟላት የሚገባው የፍትሕ ጉዳይ የለም አሉ። የክርስቶስ ሞት ሰዎችን የተቤዠው ሰዎች የኢየሱስን ፍጹም ምሳሌ እንዲከተሉ ስለቀሰቀሳቸው ነው ብለው ተናገሩ።
የካቶሊክ ቤተክርስቲያን የደረሱባትን እነዚህና እነዚህን የመሰሉ ሌሎች የመናፍቅነት ጥቃቶች ለመቋቋም የትራንትን ጉባኤ (ከ1545 እስከ 1563 እዘአ) ጠራች። በዚህ ጉባኤ ላይ በብዙ መሠረተ ትምህርታዊ ጥያቄዎች ላይ አንድ አቋም ላይ ለመድረስ ቢቻልም በቤዛ ጉዳይ ላይ ቁርጥ ያለና የጠራ አቋም መያዝ አልተቻለም። የኢየሱስ ክርስቶስ ሞት ስላስገኘው ጥቅም ቢናገርና “እርካታ” የሚለውን ቃል ቢጠቀምም “ቤዛ” የሚለውን ቃል ሆን ብሎ አጥፍቶታል። ይህንንም በማድረግ ቤተክርስቲያን ቁርጥ ያለ ቅዱስ ጽሑፋዊ አቋም ሳትይዝ ቀረች። ለግምታዊ አስተሳሰቦች ሰፊ በር ተከፈተ።
ሃይማኖታዊ መሪዎች ያልተሳካላቸው ለምንድን ነው?
ከትራንት ጉባኤ ወዲህ የካቶሊክም ሆነ የፕሮቴስታንት ሃይማኖታዊ ሊቃውንት ለቁጥር የሚያታክቱ የመቤዠት ንድፈ ሐሳቦችን አቅርበዋል። (በገጽ 7 ላይ የሚገኘውን ሣጥን ተመልከት።) ይሁን እንጂ በክርስቶስ ሞት ትርጉም ላይ አንድ ሐሳብ ላይ መድረስ የሚችሉ አይመስሉም። ሃይማኖታዊ ሊቃውንት የሚስማሙበት ነገር ቢኖር “ቤዛ” የተባለውን ቃል ችላ በማለት ወይም በማቃለል ወይም አድበስብሶ በማለት ብቻ ነው። የክርስቶስ ሞት ትርጉም የሚብራራው እንደ “ሞራላዊ ተጽእኖ” “የውክልና አካላዊ እርካታ” ባሉት የተጠማዘዙና ግራ የሚያጋቡ ቴክኒካዊ ሐረጎች ነው። የሕዝበ ክርስትና ቀሳውስት ሰዎች በክርስቶስ ሞት ላይ ያላቸውን እምነት ከመገንባት ይልቅ የክርስቶስን የመከራ እንጨት ግራ የሚያጋባ የማሰናከያ ድንጋይ አድርገውታል።
ይህን ታላቅ ውድቀት ያመጣው መሰረታዊ ምክንያት ምንድን ነው? የካቶሊክ ሃይማኖታዊ ምሑር የሆኑት ቦኒፈስ ኤ ቪሌምስ ምክንያቱን ሲገልጽ ሃይማኖታዊ ሊቃውንት “የሚሰለጥኑት ከሰው ሁሉ ተገልለው ስለሆነ ነው” ብለዋል። ከሰዎች እውነተኛ ፍላጎት ፈጽመው የራቁ ናቸው።b ከዚህ ግምገማ ጋር አትስማማምን? ይሁን እንጂ ኤርምያስ 8:9 ጠለቅ ብሎ የችግሩን መሰረታዊ መንስዔ ሲገልጽ “እነሆ [የይሖዋን (አዓት)] ቃል ጥለዋል፣ ምን ዓይነት ጥበብ አላቸው?” ብሎአል።
የቤዛ መሰረተ ትምህርት አስቸጋሪ የሆኑ ጥያቄዎችን እንደሚያስነሳ አይካድም። (2 ጴጥሮስ 3:16) ይሁን እንጂ የሃይማኖት ሊቃውንት መልሱን ከቅዱሳን ጽሑፎች ከመፈለግ ይልቅ በሰብዓዊ ጥበብና አስተሳሰብ ተጠቅመዋል። (1 ቆሮንቶስ 1:19, 20፤ 2:13) የራሳቸውን የቅዠት አስተሳሰብ ወይም ንድፈ ሐሳብ የማይደግፉትን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ለመካድ ተዳፍረዋል። (2 ጢሞቴዎስ 3:16) እንደ ሥላሴ የመሰሉትን ቅዱስ ጽሑፋዊ ያልሆኑ መሰረተ ትምህርቶች አስፋፍተዋል። (ዮሐንስ 14:28) ትልቁ ስህተታቸው ከሁሉ የበለጠ ክብደት ያላቸውን የአምላክን ስምና መንግሥት የሚመለከቱ ጉዳዮች ወደ ጎን ገሸሽ አድርገው ለሰው ልጅ መዳን ከፍተኛውን ቦታ መስጠታቸው ነው።—ማቴዎስ 6:9, 10
አንድ የቤዛው ጠበቃ
አሁን ምርመራህን ወደ 1800ዎቹ ዓመታት መጨረሻ መለስ አድርግ። ቻርልስ ቴዝ ራስል የተባለ ፈሪሐ አምላክ ያደረበት ሰው ከዋነኞቹ ሃይማኖቶች ተለይቶ ይህንኑ መጠበቂያ ግንብ የተባለው መጽሔት ማተም ጀመረ። ይህ መጽሔት “ከመጀመሪያው አንስቶ የቤዛው ልዩ ጠበቃ ሆኖ ቆሞአል” በማለት ራስል ተናግሮአል።
መጠበቂያ ግንብ እስከዚህ ዘመን ድረስ በዚህ ዓይነት ሲያገለግል ቆይቶአል። ከመቶ ዓመት በላይ ስለ ቤዛ የሚያሳምኑ ጠንካራ ቅዱስ ጽሑፋዊ ምክንያቶች አቅርቦአል። ተቺዎች ለሚያቀርቧቸው ክርክሮችም ምክንያታዊና ቅዱስ ጽሑፋዊ መልሶችን ሰጥቶአል። ስለዚህ አሁን መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ክርስቶስ ሞትና የክርስቶስ ሞት ምን ትርጉም እንዳለው የሚናገረውን ጠለቅ ብለህ እንድትመረምር እንጋብዝሃለን።
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
a የዚህ መጽሔት ተባባሪ የሆነውን የንቁ መጽሔት የህዳር 22, 1988 እትም “ሶስንያውያን፣ ለምን የሥላሴን ትምህርት አንቀበልም አሉ?” የሚለውን ርዕሰ ትምህርት ተመልከት።
b ይሁን እንጂ ቪለም ራሳቸውን ያቀረቡትን ንድፈ ሐሳብ ከላይ ባለው ሣጥን ውስጥ ተመልከት።
[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
ለዓይነት የቀረቡ የመቤዠት ንድፈ ሐሳቦች
◻ የመሪነት ወይም የመንግሥት ንድፈ ሐሳብ፦ የሆላንድ ሃይማኖታዊ ሊቅ የነበረው ሂውጎ ገሮሽየስ የሶሲንያውንን ንድፈ ሐሳብ ለማስተባበል ሲል በአሥራ ሰባተኛው መቶ ዓመት የቀመረው ንድፈ ሐሳብ ነው? ግሮሽየስ የክርስቶስ ሞት “አምላክ የመሪነት ወይም የገዥነት ሰው ደግሞ የበደለኛነት ሚና የተጫወቱበት የፍርድ ቤት ጉዳይ” እንደሆነ አድርጎ ገልጾ ነበር።—የሄስቲንግ የሃይማኖትና ሥነምግባር ኢንሳይክሎፒዲያ
◻ የዋነኛ ሥርየት ንድፈ ሐሳብ፦ ይህ ንድፈ ሐሳብ የቀረበው በ1946 ከፕሮቴስታንቱ ሃይማኖታዊ ሊቅ ከክላሬንስ ኤች ሄዊት ነበር። እርሱም ክርስቶስ የፈጸመው ሥራ ለሕጋዊ ቅጣት ክፍያ የሚያስገኝ ሳይሆን ‘ከኃጢአትና ከሞት ሕግ ነጻ የሚያወጣን፣ ንሥሐ እንድንገባና አምላካዊ ጸጸት እንዲሰማን በመገፋፋት በአምላክ ፊት ይቅርታ የሚያስገኝ አቋም እንድናገኝ የሚያስችለን’ እንደሆነ ገልጾአል።
◻ በክርስቲያን ኅብረት መቤዠት፦ የሮማ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን ሃይማኖታዊ ሊቅ የሆኑት ቦኒፈስ ኤ ቪሌምስ (1970) “መቤዠት” “ከራስ ወዳድነት ባሕርይ መመለስና አንዱ ለሌላው ልቡን መክፈት” ማለት ነው ብለዋል። ቀጥለው ሲያብራሩ “ክርስቲያናዊው የውክልና ወይም ምትክ የመሆን ሥቃይ የመቀበል አስተሳሰብ አንድ ሰው ኃጢአት ካፈራረሰው ዓለም ጋር አንድነትና ጥምረት እንዳለው ማወቅ ነው። . . . ስለዚህ ቤተክርስቲያን ለሌሎች ሰዎች ልዩ አገልግሎት ለመስጠት ዝግጁ የሆኑ ሰዎች ኅብረት ነው” ብለዋል።
◻ የራስን ኃጢአት በሌላው ላይ የመጫን ንድፈ ሐሳብ፦ ይህን ሐሣብ በ1978 ያቀረቡት የካቶሊክ ሃይማኖታዊ ሊቅ የሆኑት ሬይሙንድ እሽቫገር ናቸው። እርሳቸውም አምላክ “ዐይን ስለ ዐይን” ይጠይቃል የሚለውን ሐሳብ አልቀበልም ብለዋል። የክርስቶስ መሥዋዕት ሰብዓዊው ቤተሰብ በውስጡ የሚገኘውን የአመጸኝነት ባሕርይ የሚያስወጣበት ወይም የሚያስተነፍስበት የማንጻት ውጤት ያለው ነገር እንደሆነ ገልጸዋል።
◻ ማህበረ ሰብዓዊና ፖለቲካዊ ቤዛ፦ የባፕቲስት ሃይማኖታዊ ሊቅ የሆኑት ቶርዋልድ ሎረንዘን በ1985 እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል፦ “አምላክ የሚፈልገው ኃጢአተኛው ሃይማኖታዊ ይቅርታ እንዲያገኝ ብቻ ሳይሆን ድሃውና ጭቁኑ የፖለቲካ ነጻነት እንዲያገኝ ጭምር ነው። . . . ስለዚህ የኢየሱስ ሞት ሁሉም የሰው ልጅ ሕይወት ገጽታዎች ፈውስ እንዲያገኙ የሚፈልገውን አምላክ ይገልጽልናል።”
[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የፕሮቴስታንትና የካቶሊክ መንፈሣዊ ሊቃውንት ከኃጢአት ስለ መቤዠትና ስለ ቤዛ በርካታ ንድፈ ሐሳቦችን ፈጥረዋል። መጽሐፍ ቅዱስ ስለዚህ ጉዳይ ምን ያስተምራል?